Friday 10 January 2014

የፓርቲያችንን ህጋዊ እንቅስቃሴ ለፖለቲካ ፍጆታ ማዋል የገዥውን ፓርቲ የፕሮፓጋንዳ ውድቀት እና ኢ-ህገመንግሥታዊነት የሚያሳይ ነው!!!

ከአንድነት ለዴሞክራሲ እና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) የተሰጠ መግለጫ!!!
ፓርቲያችን አንድነት የተቋቋመለትን ሕዝባዊ ዓላማ መሰረት በማድረግ በኢትዮጵያ ውስጥ ከ50 ዓመት በላይ ትግል ተደርጎበት እውን መሆን ያልቻለውን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ሳይሸራረፍ ለማስፈን፤ አምባገነኑን ስርዓት በሰላማዊ ትግል ለመለወጥ እንዲሁም የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ ለማድረግ ህግን መሰረት አድርጎ እየሰራ ይገኛል፡፡ በዚህ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የማስፈን ትግልም ፓርቲያችን፣ አመራሩና ቁርጠኛ አባላቱ ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍለዋል፤ እየከፈሉም ይገኛሉ፡፡ ዋጋ በከፈሉና ዋጋ እየከፈሉ ባሉ አመራሮቻችንና አባሎቻችን መራራ ትግል ምስጋና ይሁንና በመላ ኢትዮጵያ ሕዝባዊ መሰረት በመጣል ከኢትዮጵያ ህዝብ ጎን መሆናችንንም አረጋግጠናል፡፡ ይህ የፓርቲያችን ጥንካሬ የራስ ምታት የሆነበት ገዥው ፓርቲ ግን ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ህዝባዊ መሰረታችንን ለመናድ በስም ማጥፋት፣ በፍረጃና ባልዋልንበት እንደዋልን የማስመሰል ስራውን አጠናክሮ በመቀጠል በህዝቡ ዘንድ ያለንን መልካም ስማችንን ለማጉደፍ ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ እየሰራ ይገኛል፡፡
አንድነትም የገዥውን ፓርቲ ኢ-ህገ መንግስታዊ የሆነ እኩይ ተግባር ተገቢ እንዳልሆነ፣ ለሀገርና ለህዝብ እንደማይጠቅም፣ የህዝብን ጥያቄ በዶክመንተሪ ጋጋታ መመለስ እንደማይቻል፣ ከፍረጃና ከሴራ ተላቅቆ በሰከነ መንገድ ወደ ውይይት እንዲመጣ በተደጋጋሚ መክረናል፤ ሀገራዊ ጥሪም አቅርበናል፡፡ ነገር ግን አምባገነኑ ስርዓት የሚቆጣጠራቸውን የመንግስት ተቋማት በመጠቀም አሁንም በዶክመንተሪ ስም ከማጥፋት፣ ከመፈረጅና ከማስፈራራት መላቀቅ አልቻለም፡፡
ሰሞኑን በተከታታይ 3 ክፍል ተላልፎ ይቀጥላል በተባለውና የፀረ-ሽብር ግብረ ሃይል ከኢቲቪ ጋር በመሆን አዘጋጅቶታል በተባለው ተከታታይ የዶክመንተሪ ፕሮግራም ላይ መሰረት የተደረገው ፓርቲያችን በመላ ኢትዮጵያ ህዝባዊ ንቅናቄ በመፍጠር እንዲሰረዝ እንቅስቃሴ ያደረገበት የፀረ ሽብር ህጉ ላይ ነው፡፡ አንድነት የፀረ-ሽብር ህጉ ይሰረዝ ሲል አሳማኝ መከራከሪያዎችን በማንሳትና በሰላማዊ መንገድ ቢሆንም ገዥው አካል ግን እንደተለመደው ማስተላለፍ ከፈለጉት አላማ ጋር የፓርቲያችንን ስም በማይገባ ቦታ በማንሳትና ለሚመለከተው አካል በህጉ መሰረት አሳውቀን ባካሄድናቸው ሰላማዊ ሰልፎች እና ህዝባዊ ስብሰባዎች ላይ ያስተላለፍናቸውን  አቋሞች  የሃሰት ትርጉም እየሰጠ የተለመደ የዶክመንተሪ ድራማው ማድመቂያ ሲያደርገን ተስተውሏል፡፡  የፓርቲ አመራሮች በህጋዊ ሰላማዊ ሰልፎች ላይ ያደረጉትን ንግግር ቆርጦ በመጠቀም በህዝብ ዘንድ ያለን ተቀባይነት ላይ ተፅዕኖ ለማሳረፍ የታቀደ መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ሁሌም ምርጫ ሲቃረብ እንደሚያደርጉት ሁሉ በ2007 ዓ.ም ለሚካሄደው ሀገራቀፍ ምርጫ የተቃውሞ ጎራውን በፀረ-ሰላምነት ለመፈረጅ እየተደረገ ያለ የኢህአዴግ የምርጫ እንቅስቃሴ ክፍልም ነው፡፡
በዚሁ ዶክመንተሪ ላይ መቀመጫውን በውጭ በማድረግ የተለያዩ ዜናዎችንና ፕሮግራሞችን በማሰራጨት የሚታወቀውን ኢሳት (ESAT) ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ ፓርቲያችን ለአባላቱ እና ለደጋፊዎቹ መልዕክት ማስተላለፉን እንዲሁም እንደፓርቲ ለማንኛውም ሚዲያ የፓርቲያችንን ሰላማዊ እንቅስቃሴ በተመለከተ ስንጠየቅ የመመለስ መብታችንን በሚጋፋ መልኩ የፓርቲያችንን አቋም አዛብቶ ለማቅረብ ሞክሯል፡፡
ይህም የኢህአዴግን  የፖለቲካ ባህሪ እና አቋም በግልፅ ያሳየ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በፓርቲያችን ዕምነት ኢህአዴግ በሚጠላቸው እና በሚያጥላላቸው ሚዲያዎች ሃሳብን መግለፅ በየትኛውም መመዘኛ አሸባሪነት ሊሆን አይችልም፡፡ የኢህአዴግ መንግስት ሲያስነጥሰው ከሚያለቅሱለት የፕሮፓጋንዳው ፍጆታዎች ከሆኑት ሚዲያዎች ውጪ የኔ ያልሆኑ የሌላ ናቸው ብሎ የሚያምን በመሆኑም ፍረጃው ህጋዊ አግባብነትም ሆነ መረጃ የሌለው ባዶ ፍረጃ መሆኑ ከማንም የተሰወረ አይደለም፡፡
ከሁሉም በላይ ህገ መንግስታዊ መሰረት የሌለው ቢሆንም እንኳ ቢያንስ ራሳቸው ላወጡት ህግ  ታምነው ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በማቅረብ ሳያስወስኑ አንድን የሚዲያ ተቋም ያውም ለአንድ አላማ የተቋቋመ የፀረ-ሽብር ግብረሃይል ‹‹የአሸባሪ ድርጅት ልሳን ነው›› ወይም ‹‹አሸባሪ ነው›› በማለት ሲፈርጅ ስናይ አሁንም የሀገራችን ፖለቲካ ፓርቲና መንግስት የተደበላለቁበት፣ አንድ ድርጅት እንደፈለገው የሚፈርጅበት ስርዓት እንዳለ የሚጠቁም ነው፡፡
ፓርቲያችንም ይህንን ህገ ወጥ ፍረጃ በቀላሉ የማይመለከተው መሆኑን እየገለፅን ገዥው ፓርቲ ከድርጊቱ እንዲቆጠብ፤ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንም ለተፈፀመብን የስም ማጥፋት ከተጠያቂነት የማያመልጥ መሆኑን እያሳወቅን አሁንም ህገ-መንግስት የሚጥሰውንና ተቀናቃኝ ሃይሎችን ለማሸማቀቅ እያገለገለ ያለው የፀረ-ሽብር አዋጅ እንዲሰረዝ ሰላማዊ ህዝባዊ ትግላችንን በማጠናከር እንደምንቀጥል እንገልፃለን፡፡ የህዝብ ልዕልና እና የህግ የበላይነት እንዲከበር ትግሉ የሚጠይቀንን መስዋዕትነት እንደምንከፍል ለመላው የኢትዮጵየ ህዝብ በድጋሚ እናረጋግጣለን፡፡
                               አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ
                 ታህሳስ 29 ቀን 2006 .
   አዲስ አባባ
UDJ

ሰበር ዜና) እነ ሌንጮ ለታ ኢትዮጵያ ሊገቡ ነው

ሐበሻ) “ከእንግዲህ የቀድሞው መንገድ አይሰራም” በሚል የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባርን የመሰረቱት የቀድሞ የኦነግ አመራሮች እነኦቦ ሌንጮ ለታ ኢትዮጵያ ሊገቡ መሆኑ ተሰማ፡፡
የዘ-ሐበሻ የሚኒያፖሊስ ምንጮች እንዳስታወቁት ከዚህ ቀደም ኦሮሚያ ክልልን ለማስገንጠል ይንቀሳቀሱ ከነበሩ ሃይሎች ጋር የነበሩት እነ ኦቦ ሌንጮ ለታ የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባርን በሚኒሶታ ከመሰረቱ በኋላ በሃገር ቤት ገብተው ለመታገል መወሰናቸውን አስታውቀዋል።
ከጥቂት አመታት ወዲህ ፕሮፌሰር ኤፍሬም ኢስሃቅ እነ ሌንጮ ለታን ለማስማማት ወደሚኒያፖሊስ ከ2008 ጀምሮ በተደጋጋሚ ሲመላለሱ እንደነበር የዘ-ሐበሻ ምንጮች በፎቶ ግራፍ ጭምር የተደገፈ መረጃ ያቀረቡ ሲሆን “ከ እንግዲህ የቀድሞው መንገድ አይሰራም” የሚል አቋም የያዘው ይኸው የሌንጮ ለታ ግሩፕ የፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሃቅን ምልጃ ተቀብሎ ወደ ኢትዮጵያ በመግባት በቀጣዩ ምርጫ ለመወዳደር እንደሚዘጋጅ የዘ-ሐበሻ ምንጮች ገልጸዋል።
የሌንጮ ለታ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ወደ ኢትዮጵያ በቅርብ ቀን እንደሚገባ ያስታወቁት እነዚሁ ምንጮች፤ በተለይ በአሁኑ ወቅት በርካታ የኦሮሞ ምሁራን፣ የሰብ አዊ መብት ተከራካሪዎች የመብት ጥያቄ አንስተው በአሸባሪነት በታሰሩበት ወቅት በዴሞክራሲያዊ መንገድ ኢሕ አዴግን እንታገላለን ብለው መወሰናቸው በሚኒሶታ የሚገኙ በርካታ ኦሮሞ ኢትዮጵያውያንን እያነጋገረ እንደሚገኝ በተደጋጋሚ መዘገቡ ይታወሳል።

አዲስ ዓመት ለጋራ ራዕይ – በአበራ ሽፈራው /ጀርመን/

በአበራ ሽፈራው /ጀርመን/
በፈረንጆቹ ወይም እንደ ጎርጎርያን አቆጣጠር 2013 ዓ.ም  በኢትዮጵያና በኢትዮጵያውያን ላይ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭው አለም ታላላቅ አሳዛኝና አስቸጋሪ ሁኔታዎች ግጥመውን አልፏል፡: አንዳንዴም ይህ ዓመት ባልነበረ የሚያስብል ነበር :: እንኳን አለፈ ::
ኢትዮጵያውያን በአገር ውስጥ ብዙዎች ለእስር የተዳረጉበት፣ ፍርደገምድል ፍርዶች በፍርድ ቤቶች የታዩበት፣ የፖለቲካ እስረኞች በከፍተኛ ሁኔታ የተበራከቱበት፣ እስር ቤቶች በፖለቲካ አቋማቸውና አስተሳሰባቸው ብቻ በህወሓት ሰዎች አይን ውስጥ በገቡ የተሞሉበት ፣ የነጻው ፕሬስ ከመቼውም ጊዜ በላይ በህወሓቶች ጥቃት የደረሰበት ፣ የአማራ ተወላጆች በዘረኞችና ግልጽ በወጣ የዘር ጥቃት በሚፈጽሙ በህወሃቶች ባለሟሎች እቅድ ማፈናቀል የተደረገበት በዚህም ምክንያት ብዙዎች ለመከራና ለችግር የተዳረጉበት፣ አጥፊው የህወሓት ማኔፌስቶም አሁንም ትግበራውን ይቀጥላል ማኔፌስቶው ሳይሆን ምስጊን የቤንሻንጉልና ጉምዝ ሰዎች በትግበራ ዙሪያ እንደደቡቡ በተጠና መልኩ ማፈናቀሉን ባለማድረጋቸውና ህወሓቶችን በአደባባይ ያጋለጠ ድርጊት በመሆኑ ለቅጣት ተዳረጉ፣ አዛዡ አሳሪ ታዛዡ ታሳሪ ሆነና ድራማው ተጠናቀቀ በዚሁ ክፉ ዓመት : : በተለይም የሙስሊም ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የሃይማኖት ነጻነት ትግልን በሃይል ለመጨፍለቅ ታስቦ ብዙዎች በአደባባይ የተገደሉበት፣ የታሰሩበትና እጅግ አስከፊ ግፍ የተፈጸመበት ዓመት ነበር በአገራችን ኢትዮጵያ::
ይኸው 2013 የህወሓት ዘረኛ ቡድን የአገሪቷን ወታደራዊ ኃይል ለመቀራመት በድርጊቱ ጠንሳሽና መሃንዲስ በነበረው መለስ ዜናዊ እቅድና ራዕይ መሰረት ሁሉንም ወታደራዊ ሃይል በህወሓቶች ለማስያዝና የአፈናውን ሥርዓት ለማጠናከር ሲባል በየትኛውም የአገሪቷ ዘመናት ባልታየ መልኩ ከፍተኛ የጀነራልነት ማዕረጎችና ሌሎች ወታደራዊ ሥልጣኖችን 99% በሚባል መልኩ የህወሓትን የበላይነት ለማረጋገጥና ስርዓት የለቀቀውን አገርን የመምራት አቅም ማጣት ለማስጠበቅ ሲባል ምንም ወታደራዊ አቅምና ትምህርት ለሌላቸው ሰዎች ብዛት ያለው የጀነራልነት ማዕረጎችን በመስጠት በአለምና በአገሪቷ  ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ የሹመት ድግስ የተደገሰበት ዓመት በመሆን ተመዝግቧል ::
በዚሁ በ2013 የሰላማዊ ትግል አራማጅ ፓርቲዎች በአገር ውስጥ በተለይም የአንድነት ፓርቲ፣ የሰማያዊ ፓርቲና የመድረክ አመራሮችና አባሎቻቸው ለከፍተኛ ጥቃት የተጋለጡበት፣ በየምክንያቱ አባሎቻቸው ለእስር፣ ለድብደባና ለእስራት የተዳረጉበት ጊዜ በመሆን የሥርዓቱ አስቸጋሪነትን የተመለከትንበት ዓመት በመሆን አልፏል :: የተቃዋሚው ሃይል ከገዢው የማፍያ ቡድንም ጋር  ግልጽ የሆነ ትንቅንቅ ውስጥ የገባበትና የህወሓት ገዢ ቡድንም በከፍተኛ ትዝብት ላይ የወደቀበት ጊዜ በመሆን የተሰናበተን ዓመት ሲሆን በተቃዋሚው ላይ የደረሰው መከራ ግን ከመቼውም ጊዜ በላይ የሆነበት  ዓመት ለመሆን በቅቷል ::
አገራችንና ህዝቦቿ በእነዚህ ሙሰኞችና በዝባዦች እጅ ከወደቀችበት ጊዜ ጀምሮ ፍጹም ባልታየ መልኩ ጥቂቶች እየበሉና እየጠጡ የሚኖሩባት ሌሎች ወይም አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ለፍጹም የኑሮ ውድነት የተጋለጠበት ዓመት ከመሆኑም በላይ በኑሮው ውድነት ምክንያትም ህዝቡ ለከፍተኛ የኑሮ ምስቅልቅሎሽ ተዳርጎና ለከፍተኛ ስደትም በመዳረግ በልዩ ልዩ ቦታዎች የሚደርስበት የስደት መከራና ሞት ቀላል አልነበረምና አብዛኛው ህዝቡ ችግሩን ተጋፍጦ መፍትሄ የሚያመጣለት አጥቶ አምላክን በመማጸን ያሳለፈበት አመት በመሆን አልፏል :: ይሁንና ህወሓቶችና ባለሟሎቻቸው ግን በየምክንያቱ ጮማ እየቆረጡና ውስኪ እየተራጩ ዓመቱን ሲያሳልፉ መክረማቸውንና በተለያዩ አገራት ያሸሿቸው የገንዘብም መጠን ቀላል እንዳልሆነና ከሟቹ መሪያቸው ጀምሮ እስከ ትልልቅ ሹማምንቶቻቸው ድረስ የአገሪቷን ገንዘብ ለመበዝበዛቸው የውጭ ሚዲያዎችና እራሱ ኢቲቪ ሳይቀር ተገዶ “ሙሰኞች ነን” ለማለት የሞከሩበት አመት ሆኖ ተመዝግቧል :: ይሁንና ከዚሁ ከሙስና ጋር ተያይዞ ሙሰኛ ጋኖችን ሳይሆን ሙሰኛ ገንቦዎችን በመስበር ሲቀልዱ የታዩበት ዓመት ነበር :: ከዚህም የተረዳነው የጠገቡ ሙሰኞች ያልጠገቡ ሙሰኞችን ሲያጠቁ ተመለከትን ::
በዚሁ ባሳለፍነው የፈረንጆች ዓመት ህወሓት በታሪክ አጋጣሚ ከሱዳን ጋር ባለው የጥፋት ቁርኝት አገርን ለባእዳን አሳልፎ በመስጠት የሚታወቀው ሥርዓት ከኢትዮጵያ ድንበር ሰፊውን ግዛትና ለም የሆነውን የአገሪቷን መሬት ለሱዳን ለመስጠት ውሎችን ለመፈራረምና ለዘመናት ደም እየተከፈለበት የኖረን የአገሪቷን መሬት አሳልፎ ለመስጠት የተዘጋጀበትና ህወሓት ምን አልባትም ኢትዮጵያዊ ነኝ ብሎ የሚያስብ ቡድን እንኳን ሆኖ ቢገኝ በአገሪቷ ታሪክ በክህደት የሚጠየቅበትን ሁኔታ ያስመዘገበበት አመት ሆኖ ከመመዝገቡም በላይ ኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ በላይ ከአሰብና ከሌሎች በህወሓት ምክንያት ደም ካፋሰሱ የኢትዮጵያ ድንበሮች በተጨማሪ አሁን ደግሞ በዚህ ዘመን ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ አገርን ለመሸጥ ሲደራደሩ የከረሙበት ዓመት በመሆን ተመዝግቧል ::
የብዙዎች የኢትዮጵያ ሱማሌዎችና የአፋር ህዝቦች ደምም በህወሓት ወታደሮች የፈሰሰበትና ህወሓቶች በሌሎች ዓለም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ግፍ የፈጸሙበትን ማስረጃ የቀረበበት፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መፈጸማቸውንና ማስፈጸማቸውን የሚያሳዩ ማስረጃዎች የተገኙበትና ያንንም ለማጠናከር ትልቅ ግልጽ ዘመቻ የተከፈተበት ዓመት በመሆን በአውሮፓዊቷ አገር በሲውዲን አገር እንቅስቃሴ የተጀመረበት ዓመት በመሆንና ከዚሁ ጋር ተያያዥ የሆኑ ጉዳዮችን ለማጠናከር እንቅስቃሴ የተጀመረበት ዓመት በመሆንም ይታወሳል 2013 ::
“አልጠግብ ባይ ሲተፋ ያድራል ” እንዲሉ ዘረኛውና አንባገነኑ የህወሓት መሪ ለ21 ዓመታት ለብቻው ይዞት የነበረው የጭቆና ቀንበር ለዘለዓለም ወደዚች ምድር ላይመለስ በሞት በመሰናበቱ ምክንያት አገሪቷን ለከፍተኛ ችግርና አዳጋች ሁኔታ አጋልጧት እንደሄደና ህወሓትንም እርቃኑን አስቀርቶት ባዶ ቡድን መስርቶ የነበረ ለመሆኑ ማስረጃ መሆኑ እስኪታይ ድረስ ተተኪን ለመፍጠር እንኳን እንዳይቻል እያስፈራራ የፈጠረውና የገነባው ሥርዓት ለመሆኑ በግልጽ እስከሚታይ ድረስ በህወሃቶች መካከል ብቻ ሳይሆን በተለጣፊዎቹ የህወሃት ኢህአዴግ ፓርቲዎች ጭምር የዕርስ በርስ ትርምስ የተፈጠረበትና አገሪቷን የሚመሩ ግማሽ ደርዘን ሊጠጋ ትንሽ ቁጥር የቀረው የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሮችን በመያዝ የተመዘገበችም አገር በመሆንና ኢትዮጵያውያንን በማስገረም ያለፈ ዓመት ሆኖ አልፏል ይኸው 2013 ጉደኛ ዓመት ::
ይኸው 2013 በአባይ ግድብ ሰበብ ከመላው ኢትዮጵያና ከመላው ዓለም ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን ኪስ የህወሓት ቀማኞች ገንዘብ የሰበሰቡበት፣ በግዳጅ የነጠቁበትና ገንዘባቸውን ለቀማኛ ቡድን ለመስጠት ያልፈለጉ በውጭው አለም የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ደግሞ የአባይን ግድብ እንዲገደብ ቢደግፉም በብዝበዛ፣ በሙስናና በመስረቅና የሃገርን ሃብት በውጭው ዓለም በሚገኙ ባንኮች በማስቀመጥ የሚታወቁትን የህወሓት የማፍያ ቡድንን ከአባይ በፊት ሰብዓዊ መብት እንዲያከብሩ በመጠየቅ፣ መለስና ሌሎች የህወሓት ሰዎች በውጭ ያከማቿቸው ገንዘቦች አንድ አባይን አይደለም ብዙ አባይን ይገነባሉና አውጡና በአገራችሁ አውሉት እያሉና ሌሎች ተመሳሳይነት ያላቸውን ሃሳቦች በማንሳትና በመቃወም በመላው ዓለም ህወሓት የቀለለበት ዓመት ነበር 2013 በእርግጥም ሕወሓት ቀድሞውንም ቢሆን በኢትዮጵያ ህዝብ ፊት የቀለለ ለመሆኑ እራሱ ህወሓትም ያውቀዋል ::
በዚሁ በ2013 በአገራችን በተለይም በጋምቤላ ክልል ሰፊ የመሬት መቀራመት የተፈጸመበትና ከፍተኛ ተቃውሞም በዚሁ ዙሪያ የተደረገበት ዓመት ከመሆኑም በላይ የጋምቤላ ነዋሪ ወገኖቻችንም በተወለዱበት፣ በአደጉበትና ተፈጥሮና ትውልድ ያስረከባቸውን መሬት በህወሓት ቀማኞች በአደባባይ በሃይል የተነጠቁበት ዓመት ነበር :: በሌሎች ክልሎች የገጠር ቦታዎች ብቻ ሳይሆን በከተማ ቦታዎችም ዙሪያ ግልጽ ቅሚያ የተፈጸመበትና ህወሓትን ተው የሚለው ጠፍቶ ያሻውን ያደረገበት ዓመት ነበር ::
የህወሓት አንዱ የመበዝበዣ ተቋም የሆነው የመከላከያ ሚንስቴር መስሪያ ቤትና ተያያዥ መምሪያዎችና የወታደራዊ መዋቅሮች በአገሪቷ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በአንድ ዘር ስር መውደቁ የታወቀ ቢሆንም የአገሪቷ ሃብት በዚሁ ተቋም በነዚሁ በህወሓት ጀነራሎችና ከፍተኛ መኮንኖች እንደሚበዘበዝ ግልጽ እየሆነ ባለበትና ወቅትና ይህንንም ችግር ለማስቆም የተለያዩ አካላት ጥያቄ ማንሳት በጀመሩበት ወቅት ማንም ምንም አያመጣም ያሉ እስኪመስል ድረስ መከላከያ ኦዲት አይደረግም የሚል ሃሳብ መነሳቱና ጉዳዩ የህግ ከለላ እንዲያገኝ ለማድረግ ጥረት ማድረጋቸው የታየበትና ጉዳዩ በግልጽ እንደሚያሳየው ብዝበዛው በህግ እንዲደገፍ አዋጅ ያስነገሩበት ዓመትም ነበር በእርግጥም አይን ያወጣ ዝርፊያ ለመቀጠል ከፍተኛ መሰረት የተጣለበት ነበር ይህ ክፉ ዓመት:: አይ 2013 ጉደኛ ዓመት ::
የህዝቡን የፍትህና የነጻነትን ጥማት ይልቁንም ለመቀልበስና የህወሓትን ብዝበዛና ጭቆናን ለመቀጠል በታሰበ መልኩ “1 ለ 5″ የሚልን የአፈና መዋቅር ለመተግበር ከፍተኛ ርብርብ የተደረገበትም ዓመትም ነበር::
በሌላ በኩል  በዚሁ አስከፊ ሥርዓት ምክንያት በዓረቡ ዓለም ተበትነው የሚኖሩና በተለይም በሳውዲ አረቢያ በልዩ ልዩ መንገድ ወጥተው ተቀጥረው የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ላይ በደረሰው ችግርና ሰቆቃ ምክንያት ብዙው ኢትዮጵያዊ በዓለም ህዝብ ፊት በዕንባ የተራጨበትና አምላክንም የተማጸነበት ዓመት ሆኖ ነበር :: በዚህ ምክንያት ብዙ ኢትዮጵያውያን ውስጣቸው ያዘነበት ዓመት ነበር::

ይህም ሆኖ ግን የኢትዮጵያ ህዝብ ከመቼውም ጊዜ በላይ ህወሓትን ለመጋፈጥና በግልጽ መስዋዕትነት ለመክፈል የቆረጠበት፣ የሠላማዊ ትግል አራማጆችም ትግሉን በተለያዩ አቅጣጫዎች ያደረጉበትና የህወሓትን ማንነት በማሳወቅ ዕርቃኑን እንዲቀር ያደረጉበት ፣ የትጥቅ ትግል አራማጆችም ትግሉን በተለያየ አቅጣጫ በማድረግ ህወሓት ድንጋጤ ውስጥ እንዲገባና የሚይዘውና የሚጨብጠው እንዲያጣ በማድረግ ያደረጉት ትግልም ቀላል አልነበረም:: በዚህ ዙሪያ አርበኞች ግንባር፣ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር፣ የኦጋዴን ነጻነት ግንባርና ሌሎችም ያደረጉት የትጥቅ ትግልና ድል ቀላል አልነበረም:: ከዚህ በተጨማሪ የግንቦት 7 ህዝባዊ ሃይልም ትግሉን ወደፊት ለመውሰድ የጣለው መሰረት በህወሓት መንደር ትልቅ ድንጋጤን ከመፍጠሩም በላይ በህወሓት ላይ ከፈጠረው ጫና የተነሳ ህወሓት ሳይወድ በግዱ የንደራደር ጥያቄንም እንዲያቀርብ ያስገደደው ሁኔታ ገጥሞታል ::

እነዚህ ከላይ ያየናቸው ሁኔታዎችና ሌሎች አሁን ያልጠቀስናቸው ሰፊ የአገራችን ችግሮች በዚሁ በ2013 በመፈጠራቸው ዓመቱ እጅግ አሳዛኝና መራራ አመት ነበር ለማለት ያስችላል :: ለዚህ ሁሉ ችግር ትልቁ ተጠያቂም ህወሓት እራሱ ለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለኝም  :: 2014 አዲሱ ዓመት ግን ለዓመታት በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነት ላይ ከሁሉም በላይ ደግሞ በሰብዓዊ ፍጥረት ላይ ይህ ዘረኛ ቡድን የሚፈጽመውን ግፍ ለማስቆም በጋራ የምንቆምበትና በአገራችን ሁላችንንም በእኩልነት፣ በፍትህ፣ በነጻነት፣ በህግ የበላይነት ሥር ሁላችንም በህግ ፊት እኩል ሆነን የምንኖርባትን አገር ለመመስረትና ለዚህም የህዝብና የአገር ራዕይ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለራሱ ሲል አቅሙ በቻለ ሁሉ ትግሉን እንዲቀላቀልና ህወሓትን በመደምሰስ በጋራ ሁላችንንም የምትወድ አገር  ልንመሰርትበት የምንችልበትን መሠረት የምንጥልበት ዓመት ሊሆን  ይገባናል  እላለሁ :: ቸር ይግጠመን ::
comment pic
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን  ይባርክ !

Thursday 9 January 2014

ሰማያዊ ፓርቲ ሀሳቡን በኢሳት ላይ ለመግለጽ የማንንም ይሁንታ እንደማይጠይቅ አስታወቀ

ፓርቲው ” የምንናገርበትን የመገናኛ ብዙሃን ማንም እንዲመርጥልን ወይም እንዲወስንልን አንፈቅድም” በሚል ርእስ ባወጣው የአቋም መግለጫ፣ ” ሰማያዊ ፓርቲ መልዕክቱን የሚያስተላልፍበትን መገናኛ ብዙሃን ማንም አካል እንዲመርጥለት ወይም እንዲወስንለት የማይፈልግ መሆኑን ግልፅ ” አድርጓል።
“በሕገ መንግስቱ የተረጋገጠውን ማንም ሰው በመረጠው መንገድ ሃሳቡን የማስተላለፍ መብቱን በመጠቀም በኢሳትም ሆነ እድሉን ካገኘ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን አቋሙንና እምነቱን ማስተላለፍ የሚቀጥል መሆኑን ማረጋገጥ ይወዳል” በማለት ፓርቲው በኢሳት ላይ ቀርቦ አቋሙን ከመግለጽ እንደማይገታ ግልጽ አድርጓል።
ሰማያዊ ፓርቲ ታህሳስ 25 ቀን 2006 ዓም በኢቲቪ የተላላፈውን ዶክመንታሪ ፊልም “የእብሪት መልዕክት” ያዘለና እና “ከተራ ርካሽ ፕሮፓጋንዳነት የማያልፍ የሕግና የዲሞክራሲያዊ መብት ገደብን ካለማወቅ የሚመነጭ አስተሳሰብ ነው” ሲል አጣጥሎታል።
“የብሔራዊ ደህንነት መረጃ እና የፀረ ሽብር ግብረ ኃይል  በተደጋጋሚ ጊዜ በሽብር ወንጀል ጠርጥሬአቸዋለሁ የሚላቸውን ሁሉ በመክሰስ ወደ እስር ቤት እንዲወርዱ እያደረገ ጉዳያቸው የፍርድ ቤት ውሳኔ ሳያገኝ እንደፈለገ በሚቆጣጠረው ወይም በሚያዘው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና ሬዲዮ ድርጅት አማካኝነት የፈለገውን ዓይነት ፍረጃና ሥም ማጥፋት ሲያካሒድባቸው” መቆየቱን ያስታወሰው ሰማያዊ ፓርቲ፣ ይህ ራሱን ከሕግ በላይ የሰቀለ አካል ያለምንም ገደብ ከሚሰራቸው ተግባራት እንዲታቀብ በሕግ የሚያስቆመው በመጥፋቱ እስካሁን የፈፀማቸውን የማንአለብኝነት ተግባራት እንደጥፋት ሳይሆን እንደ መልካም ሥራ ቆጥሯቸው በተመሳሳይ የሥም ማጥፋትና የፍረጃ ተግባሩ እንዲገፋበት አድርጎታል” ብሎአል።
“ኢሳት” የተባለ የመገናኛ ብዙሃን በኢትዮጵያ መንግስት በሽብርተኝነት ከተፈረጀ ድርጅት የገንዘብ ድጋፍ እንደተደረገለትና በሰላማዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች በተለይም ሰማያዊ ፓርቲ በዚህ የመገናኛ ብዙሃን እንዳይጠቀም የማስጠንቀቂያ ዛቻ ተላልፎለታል” ሲል ያስታወሰው ሰማያዊ ፓርቲ፣  ይህ አስፈራሪ አካል ራሱን ሕግ አውጭና ሕግ ተርጓሚ በማድረግ የዚህች ሐገር ዜጎች ሃሳባቸውን የሚገልጹበትንና የማይገልጹበትን የመገናኛ ብዙሃን እየወሰነላቸውና እየመረጠላቸው ይገኛል፣ ብሎአል ።
የገዥው ቡድን ሰዎች ሀሳብን በሃሳብ ማሸነፍ እንደማይችሉ ስለሚያውቁት የቀራቸው አማራጭ ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች ሃሳባቸውን የሚያሰራጩባቸውን መንገዶች መዝጋት ብቻ መሆኑን ፓርቲያችን ይገነዘባል ያለው ሰማያዊ ፓርቲ፣  ማንም አካል በሕግም ሆነ በሞራል ተጠያቂ የሚሆነው የሚያስተላልፈው መልዕክት ይዘት የሌሎችን ዲሞክራሲያዊና ሞራላዊ መብት የሚጋፋ መሆን አለመሆኑ እንጂ ገዥው ቡድን በጠላው ወይም በወደደው የመገናኛ ብዙሃን መልዕክቱን ማስተላለፉ አይደለም” ሲል አቋሙን ግልጽ አድርጓል፡፡ መልዕክትን የገዥው ቡድን ሰዎች በጠሉት የመገናኛ ብዙሃን ማስተላለፍ በራሱ ወንጀለኛ ወይም ሽብርተኛ ለማድረግ የሚያበቃ ምንም ዓይነት የሕግ መሰረት እንደሌለውም ገልጿል፡፡
ፓርቲው በመጨረሻም ” ሰማያዊ ፓርቲ መልዕክቱን የሚያስተላልፍበትን መገናኛ ብዙሃን ማንም አካል እንዲመርጥለት ወይም በዚሁ አጋጣሚም የፓርቲያችንን መልካም ስም በሃሰት ለማጉደፍ የተሰነዘሩ ቃላትን በቀላሉ የማንመለከታቸው መሆኑን ሕግ ባለበት ሐገር ራስን ከሕግ በላይ በማስቀመጥ ማንንም አካል መፈረጅና ስም ማጉደፍ በሕግ የሚያስጠይቅ መሆኑን የዘጋቢ ፊልሙ ባለቤቶች እንዲያውቁትና ወደፊትም ተመሳሳይ ድርጊት ከመፈፀም እንዲቆጠቡ እናሳስባለን፡፡” ብሎአል።
በአገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱት ሰማያዊ ፓርቲ እና አንድነት ፓርቲ በኢሳት ላይ ቀርበው አቋማቸውን እንዳይገልጹ መንግስት ሰሞኑን ምክር አዘል ማስጠንቀቂያና ማስፈራሪያ በኢቲቪ አማካኝነት መስጠቱ ይታወሳል።
ከመጪው ምርጫ ጋር ተያይዞ ኢሳት ገዢውን ፓርቲ ጨምሮ በአገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ፕሮግራሞቻቸውንና መልእክቶቻቸውን በነጻ እና ያለገደብ የሚያስተላልፉበትን አሰራር በመቀየስ ላይ ነው።

ከ100 ሺ በላይ የሚሆኑ የቴክኒክ እና ሙያ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የብቃት ምዘና ፈተናውን ማለፍ ሳይችሉ ቀሩ

10ኛ ክፍልን እንዳጠናቀቁ ወደ ዩኒቨርስቲ መግባት ያልቻሉ ታዳጊ ወጣቶች  መሰረተ ልማት ባልተሟላበት ፤ የኮምፒዩተር አቅርቦት በሌለበት ፤ የተሰናዳ የትምህርት ክፍል፣ ወንበር እና የማሰተማሪያ መርጃ መሳሪያዎች ሳይሟሉ እና ከተግባር መሳሪያዎች ጋር በደንብ ሳይተዋወቁ ተምረው ለምረቃ ይበቃሉ፡፡
በየአመቱ ከመቶ ሺህ በላይ የሚሆኑ ተማሪዎች የሚመክኑበት ይህ የትምህርት ዘርፍ አላማው ብቁ ባለሙያዎችን ማፍራት ቢሆንም ውጤታማ ሊሆን አለመቻሉን ጥናቶች ያሳያሉ።
ተማሪዎች “በቂ እውቀት እና ትምህርት ማግኙት አልቻልንም ” በማለት አቤቱታ ቢያቀርቡም ከመንግስት ተገቢ መልስ አለማግኘታቸውን ይገልጻሉ፡፡
በአሁኑ ስዓት ከቴክኒክና ሙያ ተመርቀው በስራ ፈጠራ ወይም በስራ መስክ የተሰማሩት 10 በመቶ እንኳን መሙላት እንደማይችሉ ጥናቶችን ያሳያሉ።
መንግስት በገጠመው የበጀት እጥረት ለቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ከሚጠይቁት በጀት ግማሽ ያህሉን እንኳን ማሟላት ባለመቻሉ አንዳንድ ኮሌጆች የግቢያቸውን ሳር በመሸጥ እና  በብድር ለመምህራን ደሞዝ ለመክፈል  ተገደዋል፡፡
በአሁኑ ስዓት በሃገሪቱ ካሉ 173 የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች እና ተቋማት ሙሉ አገልግሎት መስጠት የሚችሉት አስራ ሶስት ብቻ ናቸው፡፡ 119 ትምህርት ቤቶች ገና በጅምር ያሉ ሲሆን መንግስት ግንባታቸው በህዝብ መጠናቀቅ አለበት የሚል አቋም ይዟል።
በ2005 ዓ.ም በደረጃ አንድ ፣ በደረጃ ሁለት እና ሶስት በሰርተፍኬት ተመርቀው ለሙያ ብቃት ምዘና ፈተና ከወሰዱ 126 ሺ 642 ተማሪዎች ፈተናውን ማለፍ የቻሉት 26 በመቶዎች ብቻ ናቸው፡፡
“መንግስት ባላሰተማረን ትምህርት ፣ በአይናችን ያላየነውን መሳሪያ ለመፈተኛ በማቅረብ ያልሰጠንን ሊቀበለን በመፈለግ በአግባቡ መምራት ባልቻለው ሴክተር ውድቀታችንን አርድቶናል” ሲሉ ተማሪዎች ለዘጋቢያችን ገልጸዋል፡፡
አስረኛ ክፍል አጠናቀው በቴክኒክና ሙያ ትምህርት ቤት የተመረቁ ተማሪዎች በመንግስት ዩኒቨርስቲ የዲፕሎማ መርሃ ግብር መማር የሚችሉት የብቃት ፈተና ማለፍ ሲችሉ ብቻ ነው፡፡