Saturday 5 April 2014

ህወሓት በአፅቢ (እንዳስላሴ) ረብሻ ለመቀስቀስ እየሞከረ ነው፤ ነገ እሁድ አረና ለጠራው የተቃውሞ ሰልፍ ቅስቀሳውን ቀጥሏል

አብርሃ ደስታ ከመቀሌ
የዓረና አባላት ለነገ እሁድ መጋቢት 28 በአፅቢ (እንዳስላሴ) ከተማ ለሚደረግ ህዝባዊ ስብሰባ ቅስቀሳ እያደረጉ ይገኛሉ። በዓድዋ ቅስቀሳ ስናደርግ “እንዳትነኳቸው፣ በሰላም ይቀስቅሱ!” ብሎ መመርያ የሰጠ በመቐለ ከተማ የሚገኝ የህወሓት ከፍተኛ አመራር ዛሬ በአፅቢ ከተማ በምናደርገው ቅስቀሳ ረብሻ እንዲነሳ መመርያ መስጠቱ ከአንድ ሰዓት በፊት ሰማሁ። አላመንኩም ነበረ። ለማረጋገጥ ወደ አፅቢ ደወልኩ።
የዓረና አባላት ቅስቀሳ ሲያደርጉ ገብረማርያም የተባለ የወረዳው የሚልሻ አዛዥ ወጣቶችን አሰባስቦ የሚታደለውን ወረቀት መቅደድና መሳደብ መጀመራቸው ተነገረኝ። በራሪ ወረቀቱ መቅደድና መሳደብ የጀመረው የወረዳው ዋና አስተዳድሪ ሲሆን እሱን ተከትለው የሚረብሹ የተደረጁ ወጣቶችም ነበሩ። አሁን ህዝቡ ጣልቃ ገብቶ የሚረብሹ ወጣቶችን አስፈራርቷል። ዋና አስተዳዳሪውን በህዝብ ተሰድቧል። አሁን ሁኔታው ተረጋግተዋል። አቅጣጫው ግን በተደራጀ መልኩ የሚከናወን የዓዲግራትን ዓይነት ይመስላል። በአፅቢ ወንበርታ በጣም ብዙ የዓረና አባላትና ደጋፊዎች አሉ። ከወራት በፊት ህወሓትን ተቃውመው ዓመፅ አስነስተው እንደነበር ይታወሳል። አሁን ወደ አፅቢ እየሄድኩ ነው።
የተጋላቢጦሽ! ተቃዋሚ ፓርቲ ሰላምና ፀጥታ እንዲከበር ጥረት ሲያደርግ ገዥው ፓርቲ (መንግስት) ደግሞ ረብሻ ለመቀስቀስ ጥረት ያደርጋል፤ ስልጣኑ ተጠቅሞ የህዝብን ሰላም የሚበጠብጡ ወጣቶች በክፍያ ያደራጃል፣ ሰለማዊ ሰው እንዲደበድቡ ያበረታታል። ዓመፅ መቀስቀስ ለምዷቸው ይሆን?! ዓረና ግን ሰለማዊ ፓርቲ ነው። ለህዝብ ነፃነት ስንል እንደበደባለን፤ ለሰላም ስንል መስዋእት እንሆናለን። ምክንያቱም የሰላም መንገድ ሰለማዊ መሆን መሆኑ እንረዳለን። ትግሉ ስንጀምር ብዙ መስዋእትነት እንደሚያስከፍለን እናውቃለን። የአፅቢ ህዝብ እንደሚተባበረንም እርግጠኞች ነን።

ረዳት ፓይለት ሃይለመድህን አበራን ለማስመለስ የኢህአዴግ ልኡካን በጄኔቫ

ረዳት ፓይለት ሃይለመድህን አበራን ወደ ኢትዮጵያ ለማስመለስ በአቶ አስመላሽ ወልደ-ስላሴ የተመራ
ከፍተኛ የኢህአዴግ ልኡካን ቡድን ጄኔቭ፣ ስዊዘርላንድ ከርሞ ባለፈው ሳምንት ተመልሷል።
 በፓርላማው የህግ እና የአስተዳደር ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ሊቀ-መንበር የሆኑት አቶ አስመላሽ ወልደ-ስላሴ የተመራው
ይህ ቡድን ከሜይ 13፣ 2014 ጀምሮ የስዊዘርላንድ መንግስት አካላት ጋር በሃይለመድህን ጉዳይ ላይ ለቀናት ተወያይቷል።
ስዊዘርላንድ ረዳት ፓይለቱን አሳልፋ እንድትሰጥም ቡድኑ ብዙ ሙከራ አድርጎ እንደነበርና ሙካራው ሁሉ ሳይሳካ
መቅረቱንም ለማወቅ ችለናል።
 ቡድኑ የስዊስ ፌዴሬሽን የህግ አካላትን ለማሳመን ካቀረበው ምክንያት ዋነኛው፣ ረዳት ፓይለት ሃይለመድህን
አበራ የአእምሮ በሽተኛ መሆኑን እና ይህንንም ከራሱ ቤተሰብ አባላት እንዳረጋገጡላቸው ገልጸዋል። የስዊዝ መንግስት ግን
ጥያቄውን ውድቅ አድርጎታል። ለዚህም የሰጠው ዋነኛ ምክንያት፤ የሞት ፍርድን ተግባራዊ ለሚያደርግ መንግስት ማንንም
አሳልፌ አልሰጥም የሚል ሲሆን ይህ ባይሆንም፣ በስዊዘርላንድ እና በኢትዮጵያ መሃል ተጠርጣሪ እስረኛን የማስመለስ ውል
የለም ብለዋል።
 በተያያዘ ዜና ወንድሙ ዶ/ር እንዳላማው አበራ እና በጀርመን የምትኖር እህቱ ሃይማኖት አበራ ጄኔቭ ድረስ
በመምጣት የረዳት ፓይለት ሃይለመድህን አበራን ከሚገኝበት እስር ቤት ጎብኝተውታል። የስዊስ ጠበቆችም የፓይለቱ
መብት እንዲከበር አጥብቀው እየሰሩ ይገኛሉ። መገናኛ ብዙሃን ላይ ሲደሰኩሩ የነበሩ አንዳንድ የኢትዮጵያ የህግ ባለሞያዎች
እዚህ ጉዳይ ላይ እንዲተባበሩ ሲጠየቁ አሳፋሪ ምላሽ መስጠታቸውንም ጉዳዩን በቅርብ ከሚከታተሉት ኢትዮጵያውያን
ለመረዳት ችለናል።
 ረዳት ፓይለት ሃይለመድህን አበራ ባለፈው የካቲት 10፣ 2006 ዓ.ም. የኢትዮጵያ አየር መንገድ ንብረት የሆነውን
ቦይንግ 767 አግቶ ጄኔቭ ስዊዘርላንድ ላይ በማሳረፍ እዚያው የፖለቲካ ጥገኝነት መጠየቁ ይታወሳል። የአለም ዜና ርዕስ
ሁሉ ትኩረት ስቦ የነበረው ይህ ልዩ ክስተት የኢትዮጵያን የሰብአዊ መብት ሁኔታና የአስተዳደር በደል አደባባይ በማውጣቱ
የገዢው ፓርቲ አባላትን እጅግ እንዳበሳጨ ይነገራል።
 አንዳንድ መገናኘ ብዙሃን እንደገለጹት የአጎቱ ድንገተና ህልፈት ርዳት ፓይለቱን አስቆጥቶት ነበር። የሃይለመድህን
አበራ አጎት፤ ዶ/ር እምሩ ሥዩም ህይወት በድንገት ማለፍ ለብዙዎች ያልተፈታ እንቆቅልሽ ነው። ዶ/ር እምሩ ሥዩም የአዲስ
አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር ነበሩ።
 በአለም ዙሪያ ያሉ ኢትዮጵያውያን ወጣቱ ፓይለት ሃይለመድህን አበራን መደገፋቸውን እንደቀጠሉ ሲሆን በረዳት
ፓይለቱ ስም የተከፈቱ ድረ-ገጾች እና የፌስቡክ መድረኮች ላይ ሰፊ ዘመቻ በማድረግ ላይ ይገኛል።
 የስዊዝ ቴሌቭዥን በረዳት ፓይለት ሃይለመድህን አበራ ዙርያ አንድ ዘጋቢ ፊልም የሰራ ሲሆን ይህ ዘገባ ለትንሽ
ግዜ እንዲዘገይ ተደርጓል። ዘጋቢ ፊልሙ አየር ላይ ያልዋለበት ምክንያት የረዳት ፓይለት ሃይለመድህን አበራ ጠበቆች
እንዲዘገይ በመጠየቃቸው ነው ሲሉ ጉዳዩን የሚከታተሉት ኢትዮጵያውያን ገልጸዋል። 

ያልዘሩትን ማጨድ ከቶ አይቻልም! (ግንቦት7)

April 5, 2014
Ginbot 7 weekly editorialየወያኔ መንግስት የኢትዮጵያን ብሄር ብሄረሰቦች አጋጭቶ በመካከላቸው ጥርጣሬና መፈራራት አንግሶና የታሪክ ጠባሳዎችን እንደ አዲስ በመጓጐጥ እያደማ ከፋፍሎ ለመግዛት ካለመታከት ያደረጋቸው ሙከራዎች ገና ፍሬ ባያፈሩም ቁጥቋጦዎቹ መብቀል ጀምረዋል። እዚህም እዚያም በካድሬዎች የውስጥ ለውስጥ ተልእኮ የሚለኮሱ እሳቶች መብለጭለጭ ጀምረዋል። ሌላው ቀርቶ በአንድ ብሄረሰብ መሃል ሳይቀር በከባቢ ልዩነቶች ብቻ መናቆሮችና መጋደሎች እያስተዋልን ነው። ሰሞኑን በጉጂና በቦረና ኦሮሞዎች መካከል የወያኔ ሎሌዎች በሚያበረታቱት አተካሮ የብዙ ወገኖቻችን ህይወት ጠፍቷል። ሰዎች ከኑሮአቸው ተፈናቅለዋል። ወያኔ እንደኳስ ጨዋታ ተመልካች ዳር ሆኖ ይመለከታል፣ ያጨብጭባል።
ሰሞኑን ባህርዳር ከተማ ውስጥ በተካሄደ የስፖርት ውድድር ላይ አሳፋሪ ክስተት ነበር። ለሰሚው የሚቀፍ ብልግና የተቀላቀለበት ስድብና ቁርቋሶ አይተናል። ከበስተጀርባ ሆነው ይህንን ለፍቅር ብቻ ሊውል የሚገባ የስፖርት ዝግጅት መርዝ ረጭተውበታል። ከዚህ ላቅ ያሉ የተንኮል ድግሶችም ተደግሰው ህዝብ ውስጥ በወያኔ ከተነዙ የመርዝ ቢልቃቶች ውስጥ ስራ ላይ ሳይውሉ ቀርተዋል።
ይህ በታሪካችን ታይቶ የማይታወቅ ዘር የሚዘራው ወያኔ ያልተከፋፈለ ህዝብ አይገዛልኝም በሚል ፍልስፍና እንደሆነ በተደጋጋሚ እያየን ነው። ሶማሌ ክልል ውስጥ በተቋቋሙ ልዩ ፖሊስ በሚል ስያሜ በሚጠሩ የመንግስት ሃይሎች ጥቃት ቁጥሩ እጅግ በርካታ የሆነ የኦሮሞ ማህበረሰብ ከኖረበት መሬት ተጠራርጎ እንዲወጣ ተደርጓል። ብዙዎቹ ተገድለዋል። ብዙ ደም መቃበት ተፈጥሯል። በየክልሉ ምስኪን የአማራ ገበሬዎችን መሬት ንብረት በመንጠቅ አከባቢውን ለቀው እንዲሄዱ አድርገዋል። መሄጃ የለንም ያሉትንም ቀጥቅጠው እንደገደሏቸው ሰሞኑን ከጅባትና ሜጫ አካባቢ ያሉ መረጃዎችን አይተናል።
እነዚህ በየቦታው የሚብለጨለጩ እሳቶች በዚህ ከቀጠሉ ሁላችንም ወደ ሚያቃጥልና የሚለበልብ የሰደድ እሳት ማደጉ አይቀርም። የወያኔ ባለሟሎች ካለምንም ይሉኝታና ማሰላሰል ይህንን እሳት እያራገቡ ይገኛሉ።
ይህንን አደገኛ አዝማሚያ በንጭጩ ማስወገድ የሚችለው ራሱ ህዝቡና የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ የነጻነት ሃይሎች ድምጽና ህብረት እንጂ የወያኔ መንግስት አይደለም። ስለዚህ ህዝቡ በተለይም ወጣቶች ከዚህ ወጥመድ ሰብረው እንዲወጡ ግንቦት 7 የነጻነት፣ የፍትህና የዲሞክራሲ ንቅናቄ አጥብቆ ያሳስባል። ተመሳሳይ ተንኮሎችንም ማጋለጡን ይቀጥላል። የብሄርሰብ ልሂቃንም ይህንን መርዝ እንዲቋቋሙ፣ ይልቁንም ወያኔ እንዳይመቸው ይበልጥ መቀራረብና ፈተናውን በጋራ እንድንቋቋም ጥሪያችን በድጋሜ እናቀርባለን።
ያልተዘራ አይታጨድም። ወያኔ የዘራልን መርዝ የሚያፈራው መርዝን እንጂ ሌላ አይደለም። ልዩነቶቻችን እንደዘመኑ በሰለጠነ ዲሞክራሲያዊ መንገድ እንጂ በተያዘው መንገድ ማስወገድ አይቻልም።
ዞሮ ዞሮ በዚህ ሳይጣናዊ የወያኔ መሰሪ ሴራ ለምትፈስ ለእያንዳንዶ የደም ጠብታ ተጠያቂው የወያኔ ጉጅሌ መሆኑን አጥብቀን እናሳስባለን። በመሆኑም ለመከፋፈል ከመመቻቸት ይልቅ አንድነታችን በማጥበቅ የነጻነት ሃይሎችን በመቀላቀል ራሳችን እና የሀገራችንን ህልውና ከዚህ ከወያኔ የመከፋፈል መርዝ እንታደግ።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!

Wednesday 2 April 2014

የአዲስ አበባ ህዝብ እሪታውን እንዲቀላቀል በድጋሚ ተጠየቀ!! ህግን ተላልፈን ከህገወጦች ጋር አንተባበርም! ከአንድነት የአዲስ አበባ ም/ቤት የተሰጠ መግለጫ

የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ የአዲስ አበባ ስራ አስፈጻሚ በዛሬው ዕለት በፓርቲው ዋና ጽ/ቤት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ‹‹በህገ ወጥ መንገድ የሚቀለበስ ሰላማዊ የትግል ስልት ባለመኖሩ የአዲስ አበባ ህዝብ ለቀረበለት የሰላማዊ ሰልፍ ጥሪ ምላሹን እንዲሰጥ በአክብሮት እንጠይቃለን››ብሏል፡፡
የሰላማዊ ሰልፍ ማሳወቂያ ክፍል ህገ ወጥ ደብዳቤ በመጻፍ ሰልፉን ማከናወን አትችሉም ማለቱ ከህግ በላይ ነኝ የሚል መንፈስ እንዳለው እንደሚያሳይ የገለጸው ፓርቲው በአገሪቱ ህገ መንግስቱንና ሌሎች አዋጆችን የማስከበር ስራ የሚሰሩ ተቋማትም ለህግ መከበር ያላቸውን ቁርጠኝነት እንዲያሳዩ ጠይቋል፡፡
‹‹የእሪታ ቀን›› በሚል መሪ ቃል መጋቢት 28 ቀን 2006 ዓ.ም በአዲስ አበባ እንዲደረግ ቀጠሮ የተያዘለት ሰላማዊ ሰልፍ በተያዘለት ቀጠሮ መሰረት እንደሚደረግም ፓርቲው በመግለጫው አስታውቋል፡፡
ህግን ተላልፈን ከህገወጦች ጋር አንተባበርም!
ከአንድነት የአዲስ አበባ ም/ቤት የተሰጠ መግለጫ
የእሪታ ቀን በሚል መሪቃል በመዲናችን አዲስ አበባ ያሉ ማህበራዊና ኢኮ ኖሚያዉ ቀውሶችን አስመልክቶ በተለይም ከተማዋን ወደ ማህበራዊ ቀውስ እየመሯት የሆኑትን የውሃ፣ መብራት፣ ስልክ፣ የትራንስፖርት ችግር እንዲቀረፍ ህዝቡ የተቃውሞ ድምፁን እንዲያሰማ መጋቢት 28 ቀን 2ዐዐ6 ዓም ለማካሄድ ያቀደውን ሕዝባዊ ሠላማዊ ሠልፍ አስመልክቶ በህዝብ መገናኛ ብዙሃን ይፋ ካደረግንበት ቀን ጀምሮ የሚጠበቅብንን ህጋዊ የማሣወቅ ሥራዎችን ስንሠራ የቆየን መሆኑና መድረስ ለሚገባው አካል ሁሉ አካል ሁሉ በተገቢው ሁኔታ ማሳወቃችን ይታወቃል፡፡ ነገር ግን ጥሪው ለሕዝብ ይፋ ከተደረገበት ጊዜ ጀምሮ የሚመለከተው የሠላማዊ ሠልፍና ስብሰባ ማሳወቂያ ክፍል በህግ የተቋቋመበትን ኃላፊነት በመዘንጋት ለጠየቅነው ጥያቄ ቀጥተኛ መልስ ከመስጠት ይልቅ ህግ በመተላለፍ ክልከላ አዘል ደብዳበ ልኳል፡፡ ሆኖም የአንድነት የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት በትላንትናው እለት ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ ለሠላማዊ ሠልፍ ማሳወቂያ ክፍል የላከው ደብዳቤ በአዋጅ ከተደነገገ ህግ ጋር የሚጣረስና የዜጎችን መብት የሚያፍን መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ የአንድነት ምክር ቤት ግንዛቤ በመያዝ ከዚህ የሚከተለውን የአቋም መግለጫ በማውጣት ለመገናኛ ብዙሃን እንዲተላለፍ ወስኗል፡፡
የአቋም መግለጫው የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር የሠላማዊ ሠልፍና የፖለቲካ ስብሰባ ማሳወቂያ ክፍል ፓርቲያችን መጋቢት 15 ቀን 2ዐዐ6 ዓም ላስገባለት የሠላማዊ ሠልፍ እውቅና መጠየቂያ ደብዳቤ መጋቢት 17 ቀን 2ዐዐ6 ዓም በሠጠው ምላሽ የሠላማዊ ሠልፍ ጥያቄውን አለመቀበሉን ማሳታወቁንና ለዚህ ደብዳቤ የላክንለትን መልስ አልቀበልም በማለት የወጣ ነው፡፡
1. የሠላማዊ ሠልፍ ማሳወቂያ ክፍሉ ለሚቀርብለት የሠላማዊ ሠልፍ የእውቅና ጥያቄ ህገ መንገሥቱንና አዋጅን በሚቃረን መልኩ ምላሽ መስጠት የማይችል ቢሆንም በማን አለብኝነት አዋጁን በጣሰ መልኩ ምላሽ መስጠቱን አልተቀበልነውም፡፡
2. ህዝብን በተለይም ህገ መንግሥታዊ ድንጋጌዎች እንዲያገለግል ኃላፊነት የተሰጠው አካል ህጋዊ እውቅና ካገኘ ተፎካካሪ ፓርቲ የሚቀርብለትን ደብዳቤ አልቀበልም ማለቱም ህገ ወጥ ተግባር በመሆኑ ግለሰቡ በመደበኛ ፍርድ ቤት ክስ እንዲመሰረትባቸው ወስነናል፡፡
3. ለህግና ህገ መንግሥታዊነት ጥብቅና ለመቆም ቃል የገቡት የፌዴራልና የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊሶች ህግን አክብሮ እየተንቀሳቀሰ ከሚገኘው ፓርቲያችን ጎን እንዲቆሙ እንጠይቃለን፡፡
4. አዋጁን ያፀደቀው ፖርላማ ለሠላማዊ ሠልፍ ጥያቄያችን የተሰጠን ምላሽ ህገ ወጥ መሆኑን እንዲመለከት አባሪ በማድረግ ለላክንለት ደበዳቤ አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጠን እንጠይቃለን፡፡
5. ለመጋቢት 28 ቀን 2ዐዐ6 ዓም የጠራነው ‹‹የእሪታ ቀን›› ሠላማዊ ሠልፍ ህጋዊ መስመሩን ተከትሎ የቀረበ በመሆኑና በህገ ወጥ አሰራር ሊታጠፍ ስለማይችል ምክር ቤታችን ሙሉ እውቅና ሰጥቶታል፡፡
6. በሠላማዊ ሠልፍ ለሚደርስ ማናቸውም አይነት ኪሳራዎች፣ ጉዳቶችና መጉላላቶች ተጠያቂው ህጋዊ ቢሮ ይዞ ህገ ወጥ አሰራር የሚከተለው አካል መሆኑን ለማሳወቅ እንወዳለን፡፡
7. አሁን የገጠመን የመሠረታዊ አገልግሎቶች ችግር የውሃ፣ የመብራት፣ የስልክ ችግር የመኖርና ያለመኖር ጥያቄ ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ህዝብ የገጠመውን ስቃይ እሪ በማለት እንዲያሰማ አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) መድረኩን ያዘጋጀ ስለሆነ ጥያቄያችሁን ለመንግሥት እንድታስተላልፉ የአዲስ አበባ አንድነት ም/ቤት ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡
ስለሆነም በአዲስ አበባ ከተማ የሚደረገው የቅስቀሳ ስራ ከዛሬ መጋቢት 24 ቀን 2ዐዐ6 ዓም ጀምሮ በይፋ የሚጀመር መሆኑን እየገለጽን፤ በዚህ የዘመቻ ስራ ላይ መንግሥት አስፈላጊውን ትብብር እንዱያደርግ ከወዲሁ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡ ከዚህ ውጭ በቅስቀሳው ስራላይ ለሚገጥመን ህገወጥ ችግር መንግሥት እንደሚወስድ እንገልፃለን፡፡
ድል የህዝብ ነው!
መጋቢት 24 ቀን 2ዐዐ6 ዓም
አዲስ አበባ10157340_613396448745293_925372809_n

[በአባይ ግድብ ዙሪያ የተጻፈ አጭር ሀተታ]ትንሹዋ ወያኔና ትልቁ ወያኔ አላኖሩኝም

ለለውጥ ያህል ከራሴ ችግር ብጀምር ምን አለበት? ግለሰብ ካልኖረ ማኅበረስብ አይኖርም፡፡ ደሞም የኔ ችግር የሁሉም ፣ የሁሉም ችግር የኔ መሆኑን የማያምን አንባቢ ቢኖር ችግር አለበት ማለት ነውና በጊዜ ራሱን ፈትሾ መድሓኒት ቢጤ ቢያፈላልግ ሳይሻለው አይቀርም፡፡
ትንሹዋ ወያኔ ጠምሳኛለች፡፡ እኔን ብቻም አይደለም የጠመሰችው፡፡ ብዙዎች ኢትዮጵያውያንንም እንጂ ነው፡፡ ከወያኔ ባልተናነሰ ሁኔታ ኑሯችንን እያቃወሰችው ትገኛለች – ትልቁ ወያኔ በደጅና በቤት ውስጥ እርሷ ደግሞ በቤት ውስጥ ብቻ በተናጠልና በቡድን እየተጋገዙ ወዲያ ወዲህ ውልፊት ልንል በማይቻለን ሁኔታ ወጥረውናል፡፡ ምን እንደምናደርግም ጨንቆናአለ፡፡ ይቺ የቤት ውስጥ ወያኔ ዐይጥ ናት፡፡
ዘመኑ ለይቶለት የዐይጦችና  የወያኔዎች ሆኗል ወንድሞቼና እህቶቼ ማለትም ኢትዮጵያውያን፡፡ በኔ ቤት የተረፋት ነገር የለም፤ ለወትሮው ካልሲና ጨርቃ ጨርቅ እየለቃቀመች ነበር ወደጎሬዋ እምትወስድ፡፡ ዛሬ ግን ዘመን ተቀይሮ ባዶ ሞሰብ ሣይቀር መቆርጠም፣ አልሙኒየም የምጣድ አከንባሎ መጎርደም፣ ቁም ሣጥን መቀርጠፍ ይዛለች፤ ወያኔነት ከዚህ በላይ አለ? መጽሐፎችን አንብባ ላታነብ ነገር በጥርሶቿ መከታተፍ፣ ምግቦችን ከጉሮሮዋችን እየነጠቀች ማንከት፣ በሌሊትና አንዳንዴ ደግሞ በማንአለብኝነትና ወደር በሌለው ዕብሪት በቀንም ቤትን ተቆጣጥራ ሰላምን ማወክ የዘመናችን ትንሹዋ ወያኔ ገደቡን ያለፈ የድፍረት ተግባር ሊሆን በቅቷል – ወያኔን ተማምና መሆን አለበት መቼም፡፡ ድፍረቷ እኮ ድፍረት እንዳይመስላችሁ፡፡ ኧረረረረረ…. እንዳቃጠልሽኝ የሚያቃጥል ይዘዝብሽ፡፡ ብዙ ሰዎች በርሷ እንደተቸገሩና ዘመኑ ለርሷና ለወያኔ ዓይነቶቹ ምሥጥ መሠሪዎች የሰጠ መሆኑን ይህን ችግር የማወያያቸው ሰዎች ሁሉ ይነግሩኛል፡፡
ዛሬና አሁን በኢትዮጵያ የሰዓት አቆጣጠር ከሌሊቱ 6፡30 ገደማ ሲሆን ቀን የገዛሁትን እንትን በስምንት የጦር ግምባር አጥምጄ ወደብሶት አደባባይ መውጣቴ ነው – እንዳትሰማኝና እንዳታውቅብኝ ነው የገዛሁትን ነገር በእንትን የገለጸኩላችሁ ታዲያን – እንጂ “እዚያው በላች እዚያው ቀረች” የሚል አደገኛ መርዝ መግዛቴን ለመናገር አፍሬ እንዳይመስላችሁ፡፡ ለነገሩ ወያኔና ዐይጥ ከጠላታቸው የሚከላከሉበት ብዙ ተለዋዋጭ ዘዴ ስላላቸው በበሶ ዱዔት ያዘጋጀሁትን ግብዣ እንደሚቀበሉትና እንደማይቀበሉት አላውቅም – ውጤቱን ነገ አያለሁ፤ ዲዲቲና ወባ እንኳን ተለማምደው ጓደኛሞች መሆናቸውን ቀደም ሲል ሰምተን የለም? የሆነው ሆኖ ችግሩ ቀላል እንዳይመስላችሁ፤ ከአራት ኪሎ ቤተ መንግሥት የተለቀቁ ነው የሚመስሉት – እንደደፋርነታቸውና እንደሆዳምነታቸው፡፡ የሚምሩት ነገር እኮ የላቸውም፡፡ የሚሆንልኝ መስሎኝ “ዕቃ አትንኩብኝ፤ ቤቱ እንደሆነ ይበቃናል፡፡ ካለኝ አልፎ አልፎ ቀለብ እቆርጥላችኋለሁ – ከሌለኝ ግን ምን አደርጋለሁ? ብቻ አትተናኮሉኝ እንጂ እኔ መርዝ አላጠምድባችሁም፤ የዛሬን ኑሮ መቼም እናንተም ታውቁታላችሁ፡፡ ከመጠለቁ እግርን የሚፋጀው እሳተ መለኮቱ የቻይና ካልሲ እንኳን ባቅሙ ሠላሣና ዐርባ ብር በገባበት ወቅት እባካችሁን ተከባብረን እንኑር፡፡…” ብዬ ቃል ገብቼ በቤቴ ውስጥ የሚያደርሱትን ጉዳት ሰምቼ እንዳልሰማሁና ዐይቼም እንዳላየሁ ለብዙ ጊዜ ትቻቸው ነበር፡፡ እነሱ ግን የእንጀራ ሞሰብ አልጋችን ላይ አስቀምጠን ከባለቤቴ ጋር በየተራ እየጠበቅን እስክናድር ድረስ አሰቃዩን – የቤት ውስጥ ወያኔዎች! አሁን ባሰብኝና ቃሌን አፈረስኩ፡፡ እናም … የነሱስ አብነቱ ቀላል ነው፡፡ አለ እንጂ ወያኔ ለያዥ ለገራዥ ያስቸገረ! የወያኔስ ሰማያዊ መርዝ ካልተጨመረበት በምድራዊ መርዝ ብቻ አይጠራም፡፡ እናም ጎበዝ ግዴላችሁም ለላይኛውም በርትተን እንጩህ፡፡ የቃመ ብቻ ሣይሆን የጮኸም ተጠቀመ ሲባል ሰምቻለሁ፡፡

ወያኔና ዐይጥ አንድ ናቸው፡፡ ይሉኝታ አያውቁ፤ ፍቅር አያውቁ፤ ሀፍረትና ኅሊና እሚባል የላቸው፤ የተረገሙ ፀረ-ሕዝቦች፡፡

የሰሞኑ የወያኔ ኢቲቪ ወሬ የአባይ የህዳሴ ግድብ ብቻ ሆኗል፡፡ ነገሩ “አንድ ያላት እንቅልፍ የላት” ዓይነት ነው፡፡ በሌሎች ሀገራት በየአሥር ኪሎ ሜትሩ የሚገኝ ግድብ ኢትዮጵያ ውስጥ ብርቅ ሆኖ ጆሯችን እስኪደነቁርና እጅ እጅ እስኪለን ድረስ አባይን እየተጋትን ነው፡፡ ይህ ግድብ ከኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው ይልቅ ፖለቲካዊ ፋይዳው እንደሚያመዝን ቀድሞውንም የታወቀ ነው፡፡ ፈረንጆቹ አንድን ነገር “politicized” ሆኗል ሲሉ ያ እንዲያ ሆነ የሚሉት ነገር በፊት ለፊት ከቆመለትና ከሚወራለት ዓላማ ውጪ ለሌላ ጉዳይ ውሏል ማለታቸው ነው፡፡ የወያኔ የህዳሴ ግድብም ወያኔ እንደሚለው ለሀገሪቱ የሚሰጠው የተለዬ ጥቅም ኖሮ ሣይሆን ሕዝብን ለማዘናጊያነትና ሊጠቀስም ሣይጠቀስ ሊዘለልም ለሚችል የተለዬ ፖለቲካዊ ፍጆታ መሆኑን እናውቃለን፡፡ አለበለዚያ የስድስት ሺህ ሜጋ ዋት ኮረንቲ ከቁም ነገር ተጥፎ እስከዚህን ድረስ 24 ሰዓት ከበሮ የሚያስደልቅና ይቀምሰውና ይልሰው ያጣን ድሃ ሕዝብ ያለ ርህራሄ የሚያዘርፍ ሆኖ አይደለም፡፡ “አንቺ ቁም ነገርሽ የጎመን ወጥሽ” እንደምንል ወያኔም በዚህች ድልድይ ማነው ግድብ ዕንቅልፍ አጥቶ እኛንም እንደሱ አትተኙብኝ እያለን ነው፡፡
በማለፊያ ክርስቶሳዊ አባባል አንድ የአደባባይ ምሥጢር እንድናገር መልካም ፈቃዳችሁ ይሁንልኝ፤ “እውነት እውነት እላችኋለሁ” አባይ ተገድቦ ቢያልቅ በኔም ሆነ በሌሎች ወገኖቼ ሕይወት ላይ አንዳችም ቁሣዊም ሆነ መንፈሣዊ ለውጥ አያመጣም፡፡ በምንም ዓይነት መንገድ፡፡ እርግጥ ነው – የተሟላ የቴክኒክ ዕውቀት ያለው የሰው ኃይል ካለና እንዳሁኑ በተጭበረበረ የግዢ ሂደት አማካይነት ፎርጅድና የአገልግሎት ዘመኑን ጨርሶ የተጣለ የማቴሪያል አቅርቦት ከተወገደ እንዲሁም የሕዝብ ብዛት በቁጥጥር ሥር ከዋለ ምናልባት ልክ እንዳሁኑ በመብራት ዕጦት ዳፍንት ውስጥ ላንገባ እንችል ይሆናል፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን አሁንም ልክ እንዳሁኑ ሁሉ ለማይጠረቃው የመንግሥት ባለሥልጣናት ኪስ ማደለቢያና ለአነስተኛ የሀገር ገቢ ሲባል ቤት ያለው ሰው ሳይጠግብ ለዬጎረቤት ሀገር ኮረንቲ መቸብቸቡ ከቀጠለ የዚያኔም ቢሆን – አባይም ተገድቦ ማለት ነው – የመብራት ፈረቃው ላይቀርልን ይችላል፡፡ እናም በአባይ ግድብ ሳቢያ ከወያኔ ጋ ድብን ያለ ፍቅር የገባችሁ ወገኖች እውነቱን ከወዲሁ እንድትረዱት ላሳስብ እወዳለሁ፡፡ ወጥመድ ውስጥ ዘው ብላችሁ አትግቡ፡፡ ሀገር ካላችሁ ሁሉም አለና፡፡
ኢትዮጵያዊ መንግሥት ቢኖረን አንድ አይደለም አሥርና ከዚያም በላይ ትላልቅ ግድቦች ሊኖሩን የመቻላቸው ዕድል ሰፊ ነው፡፡ “ልማታዊ መንግሥታችን፤ ባለራዕዩና አባይን የደፈረ ጠቅላይ ሰይጣናችን ማነው ሚኒስትራችን” እያላችሁ ሟቹን ወያኔ የምታንቆለጳጵሱ ጥቅመኞች ሁሉ ዐይናችሁን ወደጭቁኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ አዙሩና እውነቱን ለመረዳት ሞክሩ፡፡ ወያኔ ከኢትዮጵያ ታሪክ አንጻር ዕድሜው የጤዛ ያህል ነው፡፡ በማታለልና በማጭበርበር 23 ዓመታትን መኖሩም የሚገርም ነው፡፡ ለዚህ ቆይታው ግን ተጠያቂው ወያኔ ብቻ ሣይሆን በተንሸዋረረ ልማት ስም አንጀታቸው ለወያኔ የሚንቦጫቦጭ አድር ባዮችና እበላ ባይ ሆዳሞች የሚያደርጉለት ሁለገብ እገዛም ጭምር ነው፡፡ የኛም አንድ አለመሆንና በሃሳብ መለያየት ለወያኔ ዕድሜ መርዘም የድርሻውን አበርክቷል፡፡ ሌላ ሌላውን ምክንያት እናንተም ታውቃላችሁ፡፡

ወያኔ የአባይን ግድብ ብቻ ሣይሆን ሌሎች በሃያና ሠላሣ የሚቆጠሩ ታላላቅ ግድቦችን መሥራት ይችላል፡፡ እንዴት? በየተራ እንይ፡፡

  1. ለአንድ ጡረተኛ ፕሬዚደንት መኖሪያ ቤት የተከራዩት በወር ስንት ብር ነው? (ልብ አድርግ – ከ400 ሺ ብር በላይ ነው!) በየወሩ የተመደበው ሌላ ሌላ ጥቅማ ጥቅምስ ስንት ነው ? ይህ በራሱ ቢደማመር በዓመትና በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ – የሙስና መርዝ ካልተጠናወተው በቀር- አንድ መለስተኛ ግድብ ይሠራል፡፡ ለአንዲት ድሃ ሀገር ተጧሪ “ፕሬዚደንት” – ለዚያውም ፈርም የሚባልን ወያኔያዊ ደብዳቤ ለሚፈርም ከዘበኛ ያነሰ ሥልጣን ለነበረው ሰው – ይህን ሁሉ ወጪ መመደብ በስተጀርባው ሌላ ቤተኛን በእግረ መንገድ ለመጥቀም የተሸረበ ሤራ አለ ማለት ነው እንጂ አሳማኝነቱና ምክንያታዊነቱ በፍጹም አይተየኝም – “ራቁቱን ለተወለደ … “ ምን አነሰው ነበር እንዴ የሚባል? ይህ ነገር ራስን ያለማወቅ ችግር ወይም ስለሀገር ያለማሰብና በእልህ የሀገርን ሀብት የማባከን አዝማሚያ ይመስለኛል፡፡ እንደኢቲቪ የቁጭ በሉ አገላለጽ ሣይሆን እንደተጨባጩ እውነታ ከአጠቃላዩ ሕዝብ ከ85 በመቶ በላይ በባዶ እግሩ በሚሄድባት የድሃ ገበሬዎች ሀገር ውስጥ አንድን ተጧሪ ባለሥልጣን እንዲህ አንቀባርሮ የሚይዝ መንግሥት ደግሞ አንድ ግድብ ለመገንባት በሚል ሰበብ ከኔ ቢጤው ተራ ዜጋ – የወር ደመወዙ ከልመና ካላወጣው፣ እየሠራ ከሚደኸይና የኗሪ አኗኗሪ ከሆነ ምንዱብ ሠራተኛ መዋጮ መጠየቅ አልነበረበትም – አሣፋሪ ነው፡፡ እኔ እንዴት እንደምኖር አውቃለሁ፡፡ እንኳንስ ከደመወዜ ተቆርጦ ይቅርና አሁን የሚከፈለኝ ደመወዝ ተብዬ ዕጥፍ ድርብ ቢከፈለኝ እንኳን የኑሮውን ክብደት ሊያቃልልኝ አይችልም፤ የኔ ቢጤዎች የምንኖረው አንዷን ኪሎ ቅቤ በ“አጠቃቀስኩሽ” ሥልት ለዓመት እንደተጠቀመችባት ብልህ ሴት ዓይነት የኑሮን ጨውና ቅመም በብልሃት ‹አጠቃቀስኩሽ› እያልን ነው፡፡ ይህን የአባይ መዋጮ በተመለከተ የወያኔ መንግሥት ደደብነትና አስተዋይነትን ማጣት በእጅጉ ይገርመኛል – ለነገሩ ደደብነትና ወያኔ ለካንስ ሞክሼዎች ናቸውና፡፡ ስንቶችን እያዘባነነ የሚያኖር መንግሥት ጦሙን ከሚያድር ዜጋ በግድ የወር ደመወዙን ሲቆርጥ በዚህ መንግሥት ባለሥልጣናት ጭንቅላት ውስጥ የሚገኘው ነጭ ጭቃ ምን እንደሆነ ወይም የምን እንደሆነ ለማወቅ በከንቱ የምንዳክር አንጠፋም – በበኩሌ በራስ ቅላቸው ውስጥ ምን ተሸክመው እንደሚዞሩ ለመረዳት ሞክሬ ሲሰለቸኝ ደክሞኝ ትቸዋለሁ – እንዲያው ግን አምባርጭቃ ይሆን እንዴ? ሲገርሙ!!
  2. ወያኔዎች ኢንሳ በሚሉት የስለላ ድርጅታቸው ኢሳትን በዋናነት ጨምሮ የተቃዋሚ ሚዲያዎችን ሲቻላቸው ከዓለም ለማጥፋት ያ ባይቻል ደግሞ ወደ ሀገር ገብተው ሕዝብን በማንቃት የወያኔ ቅሌትና ውርደት እንዲሁም ከብረት የጠነከረ ፈርዖናዊና ናቡከደነፆራዊ የግፍ አገዛዛቸው ሕዝብ ላይ በዬጊዜው የሚፈጥረው ጭቆናና ግፍና በደል እንዳይገለጥባቸው በማሰብ በየወሩ የሚከሰክሱት የሀገር ሀብት አንድ አባይን ብቻ ሳይሆን አሥር ባሮና አሥር አዋሽን ያስገድባል፡፡ በዚያ ረገድ እኛን ብቻ ሣይሆን ሌላውን ዓለምም በሚያስደምም ሁኔታ እንደጉድ ነው ገንዘባችንን ለኛው መጨቆኛ የሚመዠርጡት፡፡ ይህን የማናውቅ እየመሰላቸው ከሆነ ተሞኝተዋል፡፡ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር ለትርኪ ምርኪ የሚዲያ ማፈኛ ቁሣቁስና የውጪ ኤክስፐርቶች እንዲሁም የስለላ ቫይረስ ለመግዛት ሜዳ ላይ ከሚበትኑት ለሀገር ዕድገት ቢያውሉት ከጉራማይሌያዊ የልመና ባህላቸው በወጡ ነበር፡፡ እንደነሱ የገንዘብ አወጣጥ እኮ ኢትዮጵያ እጅግ ሀብታም ናት፡፡ እነሱ ገንዘብን በሚሊዮንና በቢሊዮን መዝረጥ የሚያደርጉት የነሱን ሥልጣን ለማስጠበቅ መሆኑ ከፋ እንጂ እንዳመነዛዘራቸው ለጭቁኑ ሕዝብ ቢሆን ኖሮ ረሀብና እርዛት ከሀገራችን ጠቅልለው ከወጡ በትንሹ 23 ዓመታትን ባስቆጠሩ ነበር፡፡ ለደኅንነት የተቃዋሚ ክትትልና የፀረ-ስለላ ስለላ አባላት በገፍ የሚወጣው መዝገብ የማያውቀው ወጪ፣ በወያኔ አገዛዝ የፊጥኝ ከታሰረው ምሥኪን ሕዝብ ተቀምቶ የወያኔን ወንበር ለመጠበቅ ለተሠማራው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ተብዬ የሚገፈገፈው ገንዘብ፤ ለመሣሪያ ግዢና በግዢው ሰበብ በሙስና ወደግል ካዝና የሚዶለው ቁጥር የማይገልጸው እጅግ ብዙ ገንዘብ፣ በመከላከያና በደኅንነት እንዲሁም በመሰል የፀጥታ ተቋማት ለሚርመሰመሰው ጆሮ ጠቢና አፋዳሽ ሁላ ካለበቂ ሥራ እንደ ቅጠል የሚረግፈው የሀገር ገንዘብ፣ ካበቂ ጥናትና ካለተጨባጭ ሀገራዊ ፋይዳ በዬጊዜው ለሚቋቋሙ አዳዲስ መሥሪያ ቤቶችና አደረጃጀቶች የሚወጣው ገንዘብ፣ ውጤቱ አስቀድሞ ለሚታወቅ የማይረባ ምርጫ የሚከሰከሰው ብዙ ሚሊዮን ገንዘብ፣ ለአብዮታቸው ጥበቃ ሲባል ለዬግልገል ካድሬው የሚዘራው ብር፣ሕወሓትን በዋናነት ይዞ ለዬአጋር ድርጅት ተብዎች ዓመታዊ የምሥረታ በዓላት ለፈንጠዝያና ለቸበርቻቻ የሚወጣው ገንዘብ፣ በሀገር ውስጥም ከሀገር ውጪም በባለሥልጣናት የሚመዘበረው የሀገር ሀብትና ንብረት … ሁሉ ቢደማመር ሀገራዊ ልመና ሱስ ላልሆነበት የመንግሥት መዋቅር ያለ አንዳች ምፅዋትና ቡገታ  አንድ አይደለም ከመቶ በላይ ግድብና ሌላም የልማት ዕቅድ ያሠራል፡፡ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ አንድ ብሔራዊ እስቴዲየም ለማሠራት ወገቤን የሚል መንግሥት ያላት ኢትዮጵያ 200 ታንኮችንና በአሥራዎች የሚቆጠሩ የጦር አውሮፕላኖችን በአንዴ ሲገዛ በሰበቡም ከፍ ሲል ለመግለጽ እንደተሞከረው በመቶ ሚሊዮን የሚገመት ገንዘብ በየማይማን የጦር “ጄኔራሎች” የግል ካዝና ሲገባ ስናይ “የነዚህ ሰዎች ዜግነት ምን ይሆን? በውነቱ ኢትዮጵያዊነቱ ይቅርና ጤናማነታቸው የማያጠራጥር ሰዎችስ ናቸው ወይ?” ብለን መጨነቃችን አይቀርም፡፡ ሰው እኮ አንድ ዓመት ይዘርፋል፤ አንድ ዓመት ይዋሻል፤ አንድ ዓመት ይሰርቃል፤ አንድ ዓመት ይሞስናል፤ አንድ ዓመት ይዘሙታል፣ አንድ ዓመት ያጭበረብራል፣ አንድ ዓመት … አዎ፣ በወረት ለተወሰነ ጊዜ ከመስመር መሠወር/መጥፋት ያለ ነው፡ አንድ ሰው የሀብት ፍቅር ካራዠው  መቼስ ምን ይደረጋል በሚፈልገው ነገር እስኪጠረቃ ድረስ ወይም በቃኝን እስያውቅ ድረስ ለተወሰነ ጊዜ መጥፎ ነገርን እያደረገ ይቆያል፤ ሰው ከሆነ ግና በሕይወት ውጣ ውረድ መማር አለበት፡፡ የተሸከመው አንጎል ጭቃ ሣይሆን ዛሬን ከነገና ትናንትን ከትናንት በስቲያ እያመዛዘነ ገምቢ ግንዛቤን ሊያስጨብጠው የሚችል ትልቅ መለኮታዊ ስጦታ ስለሆነ በሕይወት ፈተና ተሸንፎ ከተዘፈቀበት ሰውነትን ከሚያሳንስና ኅሊናን ከሚያጎድፍ ወደእንስሳነት ደረጃም ከሚያወርድ አዘቅት ለመውጣት መሞከር አለበት – ከወያኔ እንዲያውም ብዙ እንስሳት የተሻሉ “ሞራላዊ” ፍጡራን ናቸው፡፡ ዕድሜ ልኩን በክፋትና በመጥፎ ድርጊቶች ተበክሎና በዚያው ቆርቦ መኖር ለታዛቢም ይሰቀጥጣል፡፡ ወያኔዎች ከጧት እስከማታ ቢያጋፍሩ በቃኝን የማያውቁና በቂምና በበቀል የታጀሉ ትንግርተኛ ፍጡራን ናቸው – “የሞኝ ዘፈን ሁልጊዜ አበባዬ” እንዳትሉኝ እንጂ ለምሳሌ በዐሥራዎቹ ዕድሜ ሳሉ የጀመራቸው ፀረ-ኢትዮጵያና ፀረ-አማራ ጥላቻ አሁን ድረስ በስተርጅናም አብሮ ዘልቆ እነስብሃትንና ሣሞራን ምን ያህል እያሰቃያቸው እንደሆነ የምናውቀው ነው፡፡ ይሄ ታዲያ መረገም አይደለም ትላላችሁ? ብቻ ይህንን የምለውን ሁሉ የማናውቅና ሁኔታዎች ሲያመቹና ጊዜው ሲደርስ የማንጠይቅ ከመሰላቸው አሁንም ተሞኝተዋል፡፡
  3. ካሉት ጥቂት መጻሕፍት ውጪ ምንም ምድራዊ ሀብትና ንብረት እንዳልነበረው ካላንዳች ሀፍረት በራሱ አንደበት ሲናገር የነበረውና የባሕርይ አምሳያው ወላጅ አባቱም “ [በድህነቱ ምክንያት] የአምስት ብርና የአሥር ብር ኖቶችን እንኳን መለየት አይችልም” በማለት የወፍ ምሥክሯ ድምቢጥ ዓይነት የዋቢነት ቃሉን የሰጠለት መለስ ዜናዊ 3.7 ቢሊዮን ዶላር በስሙ ተመዝግቦ መገኘቱን አንድ ዓለም አቀፍ ተቋም በቅርቡ አጋልጧል፡፡ ከዚያም ቀደም ብሎ በዚሁ ብዔል ዘቡል የበኩር ልጅ በሰምሃል መለስ ስም ከአምስት ቢሊዮን ዶላር (ሚሊዮን አይደለም!) – ልድገመው ከአምስት ቢሊዮን ዶላር በላይ ተቀማጭ ገንዘብ እንደተገኘ ተዘግቧል፡፡ በአባትና ልጅ ስም የተገኘው ገንዘብ ብቻውን ከሁለት በላይ የአባይን መሰል ግድቦችን ያስገነባል፡፡ ታዲያ የምን ቧጋችነትና ማራሪነት ነው? የምንስ ማስመሰል ነው? የቆሎ ተማሪ የሀብታምም ልጅ ቢሆን ቧግቶ መብላቱ፣ ለምኖ ካልበላ ትምህርቱ ስለማይገባው ነው የሚል አፈ ታሪክ ስላለ ነው፡፡ ኢትዮጵያስ ካልቧገተችና ድሃ ልጆቿን ራቁታቸውን ካላስቀረች ልትለማ አትችልም ማለት ነው? ምን ዓይነት ዕንቆቅልሽ ነው? ኢትዮጵያየን ከ30 ዓመታት በላይ በሙያዬ ያገለገልኳት ሰውዬ የእኔ ልጅ በወያኔ ወለድ የኑሮ ውድነት ሳቢያ በቀን አንዴም መመገብ እያቃተው ከኔ ከአባቱ መናኛ የወር ደሞዝ ለአባይ አዋጣ ስባል ሰምሃል መለስ ደግሞ የኢትዮጵያን አንጡራ ሀብት በሎንዶን ታላላቅ ሆቴሎች እየተዘዋወረች ከሎንዶናውያንና ወያኔያውያን ወሮበሎች ጋር በዬምሽት ክበባቱ ጢምቢራዋ እስኪዞር እየጠጣች ስታስታውክበትና አለመላው ስትዘባነንበት ሲታይ ምን ዓይነት ሀገራዊ ስዕል ነው የምናስተውለው? የዚህን አስገራሚ እውነት ተፈጥሯዊ ፍትህስ መቼ ነው የምናየው? የሆነ የሚያበሳጭ ሀገራዊ ምስል በአእምሯችሁ ብልጭ አላለባችሁም? ስንቱ ባለሥልጣንና የጦር አበጋዝ ነው ከነየልጁ በዚህ መልክ በሀገር ሀብት እየተጫወተ የሚገኘው? ታዲያ ይሄ ሁሉ አላግባብ በሙስናና በዝርፊያ የሚባክን ሀብት ስንት ግድብ፣ ስንት የባቡር መንገድ፣ ስንት አውራ ጎዳና፣ ስንት ሆስፒታል፣ ስንት ትምህርት ቤት፣ ስንት ኮሌጅና ዩኒቨርስቲ (ያልተማሩ መምህራን የታጨቁበት ባዶና ከርክክብ ሥነ ሥርዓቱ ቀድሞ የሚሰነጣጠቅ – ጥቂት ቆይቶም የሚፈራርስ ሕንፃ ሣይሆን በሁሉም ረገድ ደረጃውን የጠበቀ ማለቴ እንደሆነ ተረዱልኝ)፣ ስንት የበጎ አድራት ተቋም፣ ስንት ክሊኒክና የጤና ኬላ፣ ስንትና ስንት የመኖሪያ ቤቶችና ሕንፃዎች አይሠራም ነበርን? ይህ ሁሉ ገንዘብ ቅን ተገዢ ያደረገንን ማይምነት ከኢትዮጵያ ምድር ጠራርጎ አያወጣውም ነበርን? ይህንንም ሕዝቡ አያውቅብንም ዘመኑ ሲደርስም አይጠይቀንም ብለው ከሆነ በርግጥም ተጃጅለዋል፡፡ ለነገሩ ሆድ አለልክ ሲጠግብ እኮ ጭንቅላት ፉዞ ይሆናል አሉ፡፡
    1. በቀዳማዊ ኃ/ሥ ጊዜ ስንት ብድርና ዕርዳታ ወደ ሀገር ገባ? በደርጉስ? በአሁኑ የወያኔ ጉጅሌስ? በዕርዳታና በብድር መልክ ከሚገባው ገንዘብ ምን ያህሉ ነው በትክክል በታለመበት ሥራ ላይ የሚውለው? አሁን የሚባለውን እንስማ ካልን ወደ ሀገር ከሚገባው የብድርም ሆነ የዕርዳታ ገንዘብ ውስጥ ሩብ ያህሉ እንኳን የሀገር ጥቅም ላይ አይውልም፡፡ ይመዘበራል፤ የግለሰቦችን ኪስ ያሞቃል፡፡ ለሀገር የሚቆረቆር ባለሥልጣንም ሆነ ተቆጣጣሪ ለጋሽና አበዳሪ ሀገር ባለመኖሩ በኢትዮጵያ ስም የተቃፈፈው የዕርዳታም ይሁን የብድር ገንዘብ እሳት ውስጥ የገባ ቅቤ ሆኖ ይቀራል፡፡ በመሠረቱ ሙሰኝነት ዱሮም ነበር – ግን እንደዛሬው ዐይኑን ያፈጠጠና ግዘፍ ነስቶ በአደባባይ ሲራመድ የሚታይ አልነበረም፤ ይሉኝታ የሚባል የኅሊና ዳኛ በመጠኑም ቢሆን  ነበር፡፡ ዛሬ ግን ደመወዙን የምናውቀው አነስተኛ ባለሥልጣንና የሥራ ኃላፊ ሁሉ የወር ገቢው ለሦስት ቀንም እንደማይበቃው እየተረዳን ወር ከወር ጮማ ሲቆርጥና ዊስኪ ሲጨልጥ ነው የሚገኘው – የሚመነዝረው ረብጣ ብርማ አይነሣ፡፡ ከየት አመጣው? ባለፈው ከአንድ መጽሔት እንዳነበብኩት እርሱና ሚስቱ ተኝተው ባደረጉት ነገር ምክንያት ፈጣሪ የሰጣቸውን ሦስተኛ ልጅ ሚስቱ ብቻ እንደሰጠችው በመቁጠር ትልቅ የፌሽታ ድግስ በቤቱ ውስጥ አድርጎ የ2.5 ሚሊዮን ብር መኪና ቁልፍ ለምሽቱ የሸለመው ወያኔ ሀብታም ያን የሚጫወትበትን ገንዘብ ከየት አባቱ እንዳመጣው ብንጠይቅ መልስ የሚሰጠን የለም፡፡ እነዚህን መሰል የወያኔ ንፋስ ወለድ ሀብታሞች በከንቱ የሚቀዳድዱትን ብር ለቁም ነገር ቢያውሉት አንድ ቀርቶ አምስት ስድስት ግድብ አይሠሩም ነበር ወይ? የኔ ቢጤን የሥጋን ምግብ ተውትና በቅጡ የተሠራች ኩርጥ ያለች የአተር ወጥ እንኳን ካዬ ወራት ያስቆጠረ መንዳካ ድሃ ያለችውን መናኛ ሣንቲም በግድ ከሚቀሙ እነዚህንና አላሙዲንን የመሳሰሉ ደደብ ሀብታሞችንና ቱጃር የባለሥልጣን ነቀዞችን  ቢያስተባብሩ አባይን የሚያስንቅ ስንትና ስንት ግንባታ ሊሠሩ አይችሉም ነበር ወይ? እነሱ እንደልባቸው ለሚምነሸነሹባት ሀገር እኔ ምን ቤት ነኝና የሌለኝን ልስጥ? ይህኛው ግፍ ከሁሉም ግፎች አይበልጥምን? አሁን ኢትዮጵያ በርግጥ የማን ናት? ከትንሽ ጣት ምን ተቆርጦ ይወሰዳል? እነዚህ የመንግሥት ሰዎች ግፍ ማለት ምን ማለት እንደሆነ አያውቁም ማለት ነው? ጤፍ በኩንታል ከብር 1600 በላይ በሆነበትና የአንድ ወዛደር ወርሃዊ ደሞዝ ከ400 ባልበለጠበት ሁኔታ ምኑን ነው ከምኑ የሚቆርጡት? ምነው እስከዚህን አቅል አሳጣቸው? …
    2. አባይን ተገድቦ ማየት ማንም አይጠላም፡፡ “አሻራውን አባይ ላይ የማያስቀምጥ ኢትዮጵያዊ አይደለም” የሚሉት ፈሊጥ ደግሞ የእውነት መሠረት የሌለውና ጠርዝ የለቀቀ የግድብ ‹ፖሊቲሳይዜሽን› ነው፡፡ ከእውነቱ ፍጹም የራቀ የማጨናበሪያ ፕሮፓጋንዳ ነው፡፡ መቼም ቢሆን አባይ ቢገድብ የሚጠላ ኢትዮጵያዊ ሊኖር አይችልም – መንግሥት ቀርቶ የመንግሥት ጳጳስ ቢያወግዘንም የአባይን መገደብ ሣይሆን የምንቃወመው ጠንጋራ አካሄዱንና የወያኔን ገደብ የለሽ ቱልቱላ ነው፡፡ ለምሳሌ ከፍ ሲል እንደተገለጸው ግድቡ ለሆነ ችግር ማስተንፈሻ ድንገት ጣልቃ ገባ እንጂ ሕዝብ አልመከረበትም፤ የሥራው ኮንትራት አሰጣጥም ብዙ ችግር እንዳለበት፣ ዕቃ አቀራረብና ሌላ ሌላ ሂደት ላይም ወያኔያውያን ባለጠጎችና ሞሰቦን የመሳሰሉ የወያኔው መርዝአቀባይ  ደንገጡር ድርጅቶች ይበልጥ እንዲከብሩበት ተደርጎ እየተካሄደ መሆኑ ከታማኝ የዜና ምንጮች ሰምተናል፤ ታዲያስ? ለምን እንታለላለን? እንጂ በመሠረቱማ ወያኔን መጥላትና የአባይ መገደብ የግድ የሆነ ግንኙነት ሊኖራቸው አይችልም፡፡ ችግሩ ተደጋግሞ እንደተነገረው ዘረኝነትን በዋነኛነት ጨምሮ ከአባይ በፊት መገደብ ያለባቸው ብዙ ወያኔያዊ የመጥፎ አገዛዝ ጎርፎች መኖራቸው ነው፡፡ እኔ ለምሳሌ ለአባይ ድምቡሎ አላዋጣም፤ ፍላጎቴ ራሱ ዜሮ ነው፡፡ የኔ ሰዎች የያዙት ስለማይመስለኝና ስላልሆኑም እንዲያውም ስለአባይ ወሬው ራሱ ባይነሳብኝ እመርጣለሁ – ወያኔን ብሎ ለኢትዮጵያ አሳቢ ይታያችሁ! አንድስ አንድስ እሚያህል መሬት እየገነደሰ ለባዕድ የሚሸጥ ወያኔ እንዴት ለሀገር ተቆርቁሮ ይህን ታላቅ ፕሮጀክት ሊጀምር ይችላል? እደግመዋለሁ – ግድቡን ግን ጠልቼ አይደለም፡፡ በሌላም በኩል ካየነው እኔን እየራበኝ፣ ኑሮየ የጎሪጥ እያየኝ ነጋ ጠባ እያላገጠብኝ ከኔ ተርፎ ለአባይ ማለት ከጅብ ተርፎ ለውሻ እንደማለት ስለሆነ ላዋጣ ብዬ ልግደርደር ብል እንኳን እንደስድብ ተቆጥሮ “ተው አንተ፣ አቅምህን ዕወቅ፣ ዕረፍ እንጂ፣ አንተን አይመለከትም፤ ምን አለህና! “ ነው ልባል እሚገባ፡፡ ዐይን አይቶ ልብ ይፈርዳል ይባላል፡፡ በቀን አንዴ መቅመስ ያቃተው ሰው፣ የነተበ ሸሚዝና አቧራ የቃመ የሸራ ይሁን የላስቲክ ጫማ ማድረጉ የማይታወቅ ሰው፣ ወር በገባ በአምስተኛውና ስድሰተኛው ቀን ሁሉም የቤት አስቤዛው ተመካክሮ በአንዴ የሚያልቅበትና ኑሮውን በብድርና እልፍ ሲልም በውጭ ሀገራት በሚኖሩ ዘመዶቹ መጠነኛ የበጀት ድጋፍ ተሰናባቹን ወር ከአዲሱ ወር ለማገጣጠም የሚፍጨረጨር ሰው፣ ልብሱ እላዩ ላይ አልቆ – ከአንሶላ ጋር ተቆራርጦ – ከሶፋና አዳዲስ የቤት ዕቃዎች ግዢና ጥገና ጋር እስከወዲያኛው ተፋትቶ፣ … በደመ ነፍስ ብቻ (ጌታ) ናስቲለው የሚኖር ሰው የግድብ ወሬ አይገባውም – እንዲገባው መጠበቅ ራሱ ቂልነትና ለተቀማጭ ሰማይ ቅርቡን የሚያስተርት ፌዝና ቀልድ ነገር ይመስለኛል፡፡ ይህ ግድብና የግድብ ቱሪናፋ የቅንጦት ወሬና እውነትም ለቡትለካ እንዲያመች ለወያኔ ዕድሜ ማራዘሚያነት ተለክቶ የተሰፋ መለስ ዜናዊያዊ የማጭበርበሪያ ካባ ነው – ካባ አሰፋፍ እንደሱ እንደመለስ የሚሆን ደግሞ በዓለም የለም፤ ማገብት፣ ተሓት፣ ተሓህት፣ ሕወሓት፣ማሌሊት፣ ኢማሌኃ፣ ኢዴመአን፣ ኢሕዲን፣ ብኣዴን፣ ደኢሕዴግ፣ ኦሕዴድ፣ ብዙ ንቅናቄዎች፣ ብዙ ዴዶች … ስልቻ ቀልቀሎ፣ ቀልቀሎ ስልቻ …ይህ ሁሉ ካባ ወያኔ ላይ የሚጠለቅና በአብዛኛው በኢንጂኔር መለስ ዜናዊ የተሰፋ ነውና ነበርም – አማርኛውም ጠፋኝ ልጄ፡፡ በዚህ በአባይ ግድብ የውሸት ካባ ደግሞ ኢትዮጵያዊነት አይለካም – መለካት ካለበት እንግዲያውስ ይህን ወያኔያዊ ቅራቅንቦና የነፃነት ትግልን የማደናቀፊያ ሥልት ተከትሎ ራሱ በመወናበድ ሌሎችን የሚያወናብድ ቀፎ ዜጋ ነው – በቃ ቀፎ፡፡ አናቱን በመዶሻ እየወቀጡት እግሩን ሲያኩት መታለሉ የማይገባው ዝንጉ ካለ ቀፎ ብቻ ሣይሆን ድንጋይ ራስም ሆዳምም ደንቆሮም ነው፡፡ ለእኔ ሀገርና መሪ ሲኖረኝ ሁሉም ይደርሳል፡፡ ዝንጀሮ “ቀድሞ የመቀመጫየን” እንዳለችው  ሀገራዊ ነፃነት ሣይኖረኝ አንድ ሺህ ግድብና አንድ ሌላ ሺህ ባቡር ከነሃዲዱ ቢኖረኝ ምንም አይፈይድልኝም፡፡ ጣሊያን በአምስት ዓመት የሠራቸው የልማት አውታሮች ጥቅማቸው እንዳለ ሆኖ ቅኝ ገዢውን ግን ወደ መልአክነት አልለወጡትም፤ በአፓርታይድ ዘመን ደቡብ አፍሪካ ውስጥ የታዩና ሀገሪቷን ከበለጸጉ የዓለም ሀገሮች ተርታ ያስሰለፉ የዕድገትና ልማት እመርታዎች የአፓርታይድን ሥርዓት ከመገርሰስ ካለማዳናቸውም በላይ ሥርዓቱን ከዓለም አቀፍ ውግዘትና መነጠል አውጥተው ለጽድቅና ለበረከት አላበቁትም፡፡ ኦ!ኦ! አሁንስ በቃኝ እባክህን፡፡ ዕንቅልፌ እያዳፋኝ ነው፡፡ እነዚያ እርጉም ትናንሽ ወያኔዎችም ግብዣየን መቀበል አለመቀበላቸውን ላረጋግጥና ጋደም ልበል፡፡ ከቅብዥር ነፃ የሆነ እውነተኛ ዕንቅልፍ ባይኖርም ዐረፍ ማለቱ አይከፋም፡፡ እነዚህ ነቀዝ ወያኔዎች እያሉ በቅጡ መተኛትም እኮ ቀረ፡፡ 11፡30 ሌሊት (ንጋት?)፡፡ 24/7/2006ዓ.ም


ኢህአዴግ የአፍሪካ ቀንድ ስጋት?

አሜሪካ መለስ ከቆፈሩት ጉድጓድ ለመውጣት ወስናለች
eprdf and the usa
ለአፍሪካ ቀንድ ሰላም ብቸኛ ተዋናይና ፊት አውራሪ አድርጎ ራሱን የሾመው ኢህአዴግ ለቀጠናው ስጋት እንደሚሆን ተጠቆመ። አልሸባብንና አልቃይዳን ከምንጩ እናጠፋለን በሚል ስትራቴጂ መለስ ከቆፈሩት ጉድጓድ ውስጥ ሰምጣ የነበረችው አሜሪካ ከጉድጓዱ ለመውጣት ወስናለች። ኢትዮጵያዊያን የሚያምኑትና የሚቀበሉትን መሪ በድፍረት አደባባይ የማውጣት ሃላፊነቱ “አገር ወዳድ” በሚሉ ዜጎችና የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ጫንቃ ላይ ነው።
ህወሃት ያቋቋማቸው ጥቃቅን መንግስታት ከህዝብ ይልቅ ለህወሃት የወደፊት እቅድ ታማኝ በመሆን መጓዛቸው ከቀን ወደቅን የፈጠረው ስሜት ኢህአዴግን እየበላው እንደሆነ የጠቆሙ የዜናው ምንጮች፣ ኢህአዴግ የምስራቅ አፍሪቃ የሰላም አባት ሊሆን ቀርቶ የራሱንም ችግር መፍታት ወደማይችልበት የቁርሾ ማሳ ውስጥ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
ህወሃት “በነጻ አውጪነት” ያሰላውና፣ ይህንኑ ዓላማውን በፈለገበት ቀን ተግባራዊ ለማድረግ ያመቸው ዘንድ በየክልሉ ለጣጥፎ ያቋቋማቸውን ፓርቲዎች ሲመሩ የነበሩት አቶ መለስ በድንገት ካለፉ በኋላ ኢህአዴግ ውስጣዊ ሰላሙ መናጋቱ በተደጋጋሚ እየተገለጸ ነው። ኢህአዴግ በበኩሉ “የጓድ መለስን ውርስና ራዕይ ያለማዛነፍ እናስቀጥላለን” እያለ አገሪቱን በደቦ እንድተመራ ማድረጉ የሚታወስ ነው።
አቶ መለስ በጓዶቻቸው ቋንቋ “ተሰው” ከተባለበት ጊዜ ጀምሮ ምክትል ጠ/ሚኒስትር የነበሩትን አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝን ለመተካት ተቸግሮ ነበር። ደህንነቱን፣ መከላከያውን፣ ፖሊስና ዋንኛ የአገሪቱን ተቋማት ጠቅልሎ የያዘው ህወሃት በቀጥታ አሜሪካ ባደረገችው ጫና ሳይወድ በግዱ አቶ ሃይለማርያምን በጠ/ሚኒስትርነት ለመሰየም ተገደደ። የስልጣን ክፍተቱን በተመለከተ አቻ ድርጅቶችና ህወሃት ውስጥ አለመግባባት ተፈጥሮ ስለነበር “ምደባ” በሚል ኢትዮጵያ በደቦ የሚመሯት አራት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሮች ተሰየሙላት።
ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አንድ የአሜሪካ ዲፕሎማት እንዳሉት አሜሪካ ስጋት የገባት ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ነበር። መለስ እንዳለፉ ልዩ ልዑክ ወደ አዲስ አበባ በመላክ ሁኔታውን በመገምገም ስራ የጀመረችው አሜሪካ አሁን አሁን በህወሃት ስትራቴጂ የተሰራው ኢህአዴግ የምስራቅ አፍሪካ ቀንድ ዋንኛ የችግር ምንጭ ስለመሆኑ ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል። በዚህም የተነሳ የአሜሪካ ፖሊሲ አውጪዎች ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት በመስጠት እየመከሩበትና የመፍትሔ ስትራቴጂ እየነደፉ ነው።
“We cannot afford to lose Ethiopia” አሜሪካ ኢትዮጵያን ልታጣት አይገባም በማለት ለጎልጉል የዋሽንግቶን ዘጋቢ የተናገሩት የዲፕሎማት ምንጭ “የአሜሪካን ባለስልጣናት ኢህአዴግን በተመለከተ የሚጠቀሙት ቃልና የድምጻቸው ቃና ተቀይሯል” ሲሉ የጉዳዩን ክብደት አመላክተዋል።
በዋሽንግቶን የአሜሪካ ፖሊሲ አውጪዎች፣ የምክር ቤት አባላት እንዲሁም ሌሎች የሚመለከታቸው ኢህአዴግን አስመልክቶ ተደጋጋሚ ስብሰባ መቀመጣቸው ታውቋል። አዲስ አበባም ተወካይ በመላክ ከሚመለከታቸው ባለስልጣናት ጋር በግል እየተነጋገሩ ነው። በያዝነው ሳምንትም ለተመሳሳይ ስራ አዲስ አበባ የተጓዙ አሉ። እንደ ዲፕሎማቱ ገለጻ የህወሃት ሰዎች ውስጣዊ ችግር እንዳለ አይቀበሉም። በግል ያነጋገሯቸው የሌሎች ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ግን ኢህአዴግ ውስጡ አለመረጋጋትና ስጋት የተሞላው ስለመሆኑ ማረጋገጫ ሰጥተዋል።
በኢትዮጵያ አንድ ችግር ቢፈጠር ለማረጋጋት አስቸጋሪ እንደሚሆን፣ ህዝቡ በተለይ በህወሃቶች ላይ የሚያሳየው ጥላቻ እየተካረረ መምጣቱ፣ በአገሪቱ የሚፈጸመው ያልተመጣጠነ የሃብት ስርጭት፣ አፈናውና ሌሎች የህወሃት/ኢህአዴግ ተግባራት ተዳምረው ህዝቡን ክፉኛ ማስቀየሙ ያልታሰበ ችግር ሊቀሰቅስ እንደሚችል አሜሪካ መገንዘቧን ያወሱት ዲፕሎማት፣ “ህወሀቶች የቀጠናው የሰላም ምንጮች ስለመሆናቸው ለራሳቸው ምስክርነት ለመስጠት ቢሞክሩም በተግባር የሚታየው ግልባጩ ነው” ብለዋል።
ኢትዮጵያ ላይ የተተከለው የጎሳ አገዛዝ እንደሆነ ያመለከቱት እኚሁ ዲፕሎማት “በጎሳ አስተሳሰብ የተዋቀረው ኢህአዴግ ችግሩ ከገነፈለ ሊቆጣጠረው የሚችል ባለስልጣንና መሪ የለውም። አስተዳዳራዊ ማዕከላዊነት አይታይበትም። በግል የሚወስን ባለስልጣንና ርምጃ የሚወስድ አካል የለውም” ሲሉ የስጋቱን ግዝፈት ያሳያሉ። በዚህ ሂደት ውስጥ ችግሩ ቢከሰት ምን ሊፈጠር እንደሚችል ማሰቡ አዳጋች እንደማይሆን ይጠቁማሉ። አያይዘውም “አሜሪካ ቸል ብላ ስትመለከተው የነበረውን ጉዳይ አጽንኦት ብትሰጠው አይገርምም” ብለዋል። አሜሪካ ይህንን የምታደርገው ለራሷ ስትል እንደሆነ ያልሸሸጉት ዲፕሎማት አንድ ጥያቄም ጠይቀዋል። “እናንተስ ለራሳችሁ ስትሉ ምን እየሰራችሁ ነው?” ከረጅም ፈገግታ ጋር።
አልቃይዳን ከምንጩ ማድረቅ በሚለው የመለስ ስትራቴጂ ለኢህአዴግ ግብር ስታስገባ የነበረችው አሜሪካ ግብሯን ስትገብር የኖረችው በፔንታጎን ወታደራዊ ውሳኔ መሰረት ነበር። ኢህአዴግም ግብሩ እንዳይቆምበት በአዲስ አበባ ታክሲ ላይና ህዝብ በሚያዘወትርባቸው ቦታዎች ፈንጂ በማፈንዳት ሲጫወተው የነበረውን ድራማ ዊኪሊክስ (ሹልክ ዓምድ) አምባሳደር ያማማቶን ጠቅሶ ማጋለጡ አይዘነጋም። በዚሁ መነሻ ይመስላል ኢህአዴግ የቀድሞውን ጨዋታ የመጫወት እድሉ እንዳከተመ እንደራሴ ክሪስ ስሚዝ ባደባባይ የመለስን ስብዕና በመዝለፍ ባልተለመደ መልኩ ተናግረው ነበር።
ለጎልጉል መረጃ የሰጡት ዲፕሎማት “እናንተስ” በሚል ለሰነዘሩት ጥያቄ ማብራሪያ ተጠይቀው “እኔ ኢትዮጵያዊ ብሆን አገሬን አስቀድማለሁ” የሚል አጭር ምላሽ ሰጥተዋል። አሜሪካ አማራጭ ማጣቷንም እንደ አንድ ችግር አንስተዋል።
በዲፕሎማቱ አስተያየት ላይ ገለልተኛ ወገኖችን አነጋግረናል። ያሰባሰባንቸው አስተያየቶች “አሜሪካ እዚህ ደረጃ ከደረሰች፣ ኢህአዴግም በዚህ ደረጃ ከተመደበ ተቃዋሚዎች የግል ጉዳያቸውንና ፕሮግራማቸውን ለህዝብ ውሳኔ በመተው ለመጪው ትውልድና ለአገር ሲሉ ከመቧደን በሽታ ሊፈወሱ ይገባል” የሚል ይገኝበታል።
የተቃዋሚ ፓርቲዎች ተቀናጅቶ መበተን፣ ተደራጅቶ መፍረክረክ፣ ተደላድለው መስለል በተለያዩ ወቅቶች ህዝብ ተስፋ እንዲቆርጥ አድርገዋል። የሚፎካከሩትን ፓርቲ ትተው እርስ በርሳቸው ለተራ ጉዳይ ሲሻኮቱ ዓመታት አሳልፈዋል። በዚህም የተነሳ “አማራጭ የለም” በሚል ኢህአዴግን ማንገስ ግድ እንደሆነ የጠቆሙት አስተያየት ሰጪዎች “የተቃዋሚ ፓርቲዎች ይህንን አስተሳሰብ ሰብረው አገር መምራት እንደሚችሉ የሚያረጋግጥ ህብረት መፍጠር ይገባቸዋል። ይህም ካልሆነ የርስ በርስ ውዝግባቸውን ማቆምና የራሳቸውን የቤት ስራ መስራት ላይ ማተኮር ግዳጃቸው ይሆናል” ብለዋል።
ምሁራን ከተደበቁበት ሊወጡ እንደሚገቡም ያሳሰቡ አሉ። አገር የመምራት፣ በህዝብ የመታመን፣ የህዝብን ይሁንታ ማግኘት እንችላለን የሚሉ ከፊት ለፊት፣ አሁን ከፊት ያለውን ችግር በመጥረግ የወደፊቷን ኢትዮጵያ በመገንባትና መጪውን ትውልድ በማዳኑ ስራ አጋዥ ሃይል ለመሆን መወሰን እንደሚገባቸው በመግለጽ ጥሪ አቅርበዋል። ከሁሉም በላይ ግን “አሁን ካለው ህዝብን ካገለለ ዘመናዊ የመሳፍንት ስርዓት ኢትዮጵያንና ህዝቧን ማሻገር የሚችል ሞገሰ ሙሉ፣ ቅን፣ ከጥላቻ የጸዳ፣ ከሥልጣን ይልቅ የወደፊቷን ኢትዮጵያ አሻግሮ መመልከት የሚችል መሪ ወደ ፊት ወጥቶ በግልጽ ለህዝብ የሚተዋወቅበትን መንገድ የማህበራዊ ሚዲያዎች፣ ድረገጾች፣ ሬዲዮኖች አገር ወዳድ የመገናኛ አውታሮች አጀንዳ አድርገው ሊወያዩበት ይገባል” የሚለው አስተያየት ሚዛኑን የደፋ ሆኗል።

ኢህአዲግ/ወያኔ ሕዝብ ለማፋጀት የገነባውን “የመርዝ ብልቃጥ”

ምርቃቱ የሩዋንዳው የዘር ማጥፋት ግጭት ከተጀመረበት 20ኛ ዓመት ጋር ገጥሟል
በአርሲ ዞን በሂቶሳ ወረዳ ከሃያ ሚልዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ያሰራውን  ''አኖሌ ሐውልት'' እና ሙዝዬም
ኢትዮጵያን እየመራ የሚገኘው ኢህአዲግ/ወያኔ የኢትዮጵያን ሕዝብ ከቀን ወደ ቀን እርስ በርሱ እንዳይተማመን፣ እንዲነቃቀፍ፣ እንዲጠራጠር ከእዚህ ባለፈ ደግሞ ግጭት እንዲፈጠር እያደረገ 22 ዓመታትን ዘለቀ። ህዝቡ እለት ከእለት በገዢው መንግስት የሚወጠኑለትን የእርስ በርስ ማጋጫ ተንኮሎች እየተመለከተ ልቦናው በእጅጉ እየደማ ነው።
አንድ ወራሪ የውጭ ጠላት ሊሰራ የሚችለውን ያህል ህዝብን ከሕዝብ ጋር የማጋጨት ሥራ ኢህአዲግ/ወያኔ በትክክል ሰርቶበታል። የሃገሪቱን ፌድራል አስተዳደር በየትኛውም ዓለም ያልታየ ቋንቋን መሰረት ያደረገ አስተዳደር ለኢትዮጵያ ደገሰላት። ፌድራላዊ አስተዳደር በዘመናዊው ዓለም አንዱ እና አማራጭ የአስተዳደር ዘይቤ ይሁን እንጂ በየትኛውም ሀገር መሰረት የሚያደርገው የመልክዓ ምድርን አቀማመጥ እና ታሪካዊ አሰፋፈርን ነው። እርግጥ ነው ጣልያን ሀገራችንን በወረረ ዘመን አሁን ወያኔ የሚጠቀምበትን የክልል አስተዳደር የመሰለ ቋንቋን መሰረት ያደረገ የአስተዳደር መዋቅር ዘርግቶ ነበር።
አንዳንዶች የአሁኑ ቋንቋን መሰረት ያደረገ አስተዳደር የብሔር ብሄረሰቦችን መብት ከማስከበር አንፃር የሚመስላቸው የዋሃን አይጠፉም። ግን ፈፅሞ አላማው ይህ ላለመሆኑ ብዙ ማስረጃ መጥቀስ ይቻላል።እርግጥ ነው የህዝብ ባህል ማለትም ቋንቋው፣ አለባበሱ፣ ታሪኩ ወዘተ ሊጠበቅለት እና ከለላ ማግኘት አለበት። ይህ ከለላ በማግኘት መብት  ስም ወንጀል ሲሰራ፣ ቁርሾ በባትሪ እየተፈለገ ሲራገብ እና ሕዝብን ከሕዝብ ለማጋጨት ሲውል ነው ወንጀሉ።
ኢህአዲግ/ወያኔ ሕዝብ እርስ በርሱ በጎሳ ሲጋጭ መፍትሄ ለመፈለግ ከመነሳት ይልቅ ጉዳዩን ሲያባብስ እና ቤንዚን ስያርከፈክፍ ማየት ለኢትዮጵያ ሕዝብ ዕለት ከዕለት የሚመለከተው ድራማ ሆኗል። ለእዚህም ብዙ አብነቶችን መጥቀስ ይቻላል። ለእዚህ ፅሁፍ ግን ሁለት ምሳሌዎችን እንጥቀስ -
  1. በዩንቨርስቲዎች ውስጥ ወጣቶች ‘አንተ የእገሌ ነህ አንተ የእንቶኔ ነህ’ ተባብለው ፀብ ሲነሳ ጉዳዩ የመጪው ትውልድ እና የአሁኑ ትውልድ አደገኛ አቅጣጫ ነው ብሎ የችግሩን ስር ለመፍታት ከመጣር እና የጉዳዩን አስከፊነት  በመገናኛ ብዙሃን ከመግለፅ እና ከማስተማር ይልቅ ፖሊስ ይልቁን ከአንድኛው ወገን ቆሞ ሌላውን ሲያስር እና ሲቀጣ መመልከት ዘግናኝ ተግባር ነው።
  2. ሕዝብ ለዘመናት ከኖረበት የእርሻ ቦታ ”የእገሌ ዘር ነህ” ተብሎ በክልል መስተዳድሮች ጭምር ሲባረር ለጉዳዩ እንደ መንግስትነት ለመዳኘት ሳይሆን የሚሞከረው እንደ ቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ አባባል ”ቀድመው ባልተወለዱበት ሀገር መስፈር የለባቸውም” እንደ አቶ አለምነህ የብአዴን ቢሮ ምክትል ኃላፊ ደግሞ ”የትዕቢት ልጋግ” ነው የሚሉ መልሶችን መስማት እራስ ያማል። መሪዎቻችን እንዲህ እያሉ ከጉርዳፈርዳ እስከ አሶሳ፣ ከአሶሳ እስከ ሐረር፣ ከሐረር እስከ ጅጅጋ፣ ከጅጅጋ እስከ ቦረና ጉጂ፣ ድረስ በብዙ አስር ሺህ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን በኢህአዲግ/ወያኔ የጎሳ ፖለቲካ ተሰደዱ፣ ተገደሉ። ይህ ሁሉ ሲሆን ግን መንግስት ጉዳዩን እንደ ትልቅ ችግር ሳይሆን እንደ አንድ የማስተዳደርያ ዘዴ እንደቆጠረው በ እርግጠኝነት መረዳት ይቻላል።
በያዝነው ሳምንት  በሃያ ሚልዮን ብር ወጪ የሚመረቀው የመርዝ ብልቃጥ 
በአርሲ ዞን በሂቶሳ ወረዳ ከሃያ ሚልዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ያሰራውን  ''አኖሌ ሐውልት'' እና ሙዝዬም
ኢህአዴግ በአርሲ ዞን በሂቶሳ ወረዳ ከሃያ ሚልዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ያሰራውን ”አኖሌ ሐውልት” እና ሙዝዬም
የእርስ በርስ ግጭቶች ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲሻገሩ የሚጥረው ኢህአዲግ/ ወያኔ ለእርስ በርስ ጦርነቶች እየመረጠ ሃውልት ሲሰራ ከርሞ በእዚህ ሳምንት ደግሞ ለየት ያለ የጥፋት ድግስ የሚሆን ከመቶ አመታት በፊት ለመፈፀሙ ምንም አይነት የታሪክ ማስረጃ የሌለው በዳግማዊ ምኒልክ ዘመን በአርሲ ዞን በሂቶሳ ወረዳ ተፈፅሟል ያለውን የታሪክ ምሁራን ያላረጋገጡትን የፈጠራ ታሪክ ከሃያ ሚልዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ያሰራውን  ”አኖሌ ሐውልት” እና ሙዝዬም  በእዚህ በያዝነው ሳምንት እንደሚመረቅ ኢቲቪ ዛሬ መጋቢት 22/2006 ዓም የዜና እወጃው ላይ አስታወቀ። የፈጠራው ታሪክ ከመቶ ዓመታት በፊት የአፄ ምኒልክ ሰራዊት የኦሮሞ ሴቶችን ጡት ቆርጦ ነበር እና ማስታወሻነቱ ለተቆረጡት ጡት እና እጅ ይሁን” ይላል የሃውልቱ የመሰራት ምክንያትን ኦህዴድ /ኢህአዲግ/ወያኔ ሲናገር። አሳዛኝ የደረስንበት የዝቅጠት ዘመን። በየትኛውም ሀገር ውስጥ በቀደሙ መሪዎች ያውም ከመቶ አመታት በላይ ለሆነው ታሪክ ቀርቶ የቅርቦቹም ቢሆን ለተሰሩ ተገቢ ያልሆኑ ድርጊቶች ለመጪው ትውልድ የሚያቆይ የእልቂት ድግስ ከፋች ሃውልት አይሰራም። የሚጠጣ ውሃ፣ የምበላው ምግብ ለሌለው ሕዝብከ 20 ሚልዮን ብር በላይ አውጥቶ መበተን ምን የሚሉት ፈልጥ ነው?
አንድ መንግስት ሕዝብ ከህዝብ ጋር አብሮ የሚኖርበትን ዘዴ ሲቀይስ ልዩነትን እያጎላ ሳይሆን አንድነትን እያሳየ እና እያጎላ ሕዝብ በፍቅር እና በስምምነት እንዲኖር ይጥራል እንጂ እንዴት ከአሁኑ ትውልድ አልፎ ለመጪው ትውልድ ቂም ለማውረስ ተግቶ ይሰራል? ይህ ተግባር ማንን ይጠቅማል? ለመሆኑ ያለፉ ነገስታት በወቅቱ በነበረው የቅጣት መንገዳቸው ሁሉ የቀጡትን የቅጣት አይነት እየዘረዘርን ሃውልት ብንሰራ የቱን ከየቱ እንመርጣለን?
የሃውልቱ ምርቃት እንደ ትልቅ የሀገር ልማት ዛሬ ኢቲቪ ቀድሞ ዛሬ ይናገረው እንጂ ወቅቱ የሩዋንዳው እልቂት የተጀመረበት 20ኛ አመት ጋር ገጥሟል። በሚያዝያ 7/1994 ዓም  እስከ ሐምሌ/1994 ዓም እ ኤ አቆጣጠር የቆየው በቱትሲዎች እና በሁቶዎች መካከል የተደረገው እልቂት ከአምስት መቶ ሺህ በላይ ሕዝብ ሕይወት ቀጥፏል። የሩዋንዳው እልቂት በአንድ ሌሊት ድንገት የደረሰ ጉዳይ አይደለም። በሂደት አልፎ አልፎ በተነሱ ቁርሾዎች ጥርቅም ሳብያ መሆኑን መዘንጋት አይገባም። የዛሬ የባለ ሃያ ሚልዮን ሃውልት ገንቢዎችም ሆኑ አስገንቢዎች መዘንጋት የሌለባቸው  በሰሩት ሥራ ሁሉ የሚጠየቁበት ቀን እንደሚመጣ መጠራጠር አይገባም። የመርዝ ብልቃጡም ይሰበራል የፍርድ ቀኑም ይቆረጣል።
(ምንጭ: ጌታቸው በቀለ ጉዳያችን)

የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት በ‹‹አኬልዳማ›› ፕሮግራሙ ላይ በቀረበበት ክስ ተረታ! -በፕሮግራሙ ያስተላለፈውን ስም አጥፊ ዘገባ እንዲያርም ታዟል ! – ታምሩ ጽጌ

የኢትዮጵያ ሬዲየና ቴሌቪዥን ድርጅት ከኅዳር 16 እስከ 18 ቀን 2004 ዓ.ም. በተከታታይ ሦስት ክፍሎች ‹‹አኬልዳማ›› በሚል ባቀረበው ዘጋቢ ፕሮግራም፣ክብርና ዝናን የሚያጠፋ በድምፅ፣ በምስልና በጽሑፍ በተቀነባበረ መንገድ ስሙን እንዳጠፋው በመግለጽ፣ አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) በመሠረተበት የፍትሐ ብሔር ክስ ተረታ፡፡
የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ዘጠነኛ የፍትሐ ብሔር ችሎት መጋቢት 23 ቀን 2006 ዓ.ም. በሰጠው ውሳኔ፣ አንድነት ፓርቲ መጋቢት 24 ቀን 2004 ዓ.ም. ባቀረበው ክስ የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅትንና ፕሮግራሙን አቅርቧል በተባለው አቶ አብዲ ከማል ላይ ክስ መመሥረቱን አስታውሷል፡፡
አንድነት በክሱ እንዳብራራው፣ በዲስፕሊን ግድፈት ከፓርቲው የተባረሩትን፣ በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ መሠረት በራሳቸው ፈቃድ የለቀቁትንና በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው በሕግ ቁጥጥር ሥር የሚገኙትን ግለሰቦችና ተከሳሾች፣ የፓርቲው አባል እንደሆኑ አድርጐ በፕሮግራሙ ማሳየቱ አግባብ አለመሆኑን በክሱ አቅርቧል፡፡ ፓርቲውንና ሕጋዊ አባላቱን ሁከትና ብጥብጥ ፈጣሪዎች እንደሆኑ አድርገው ስም ማጥፋታቸውን አክሏል፡፡ ፓርቲውና ሕጋዊ አባሎቹ አሸባሪ ተብሎ በሕግ የተፈረጀው ግንቦት 7 የተባለው ድርጅት፣ በህቡዕ በፓርቲው ውስጥ ሰርጐ እንደገባና እንደተደራጀ እያወቁ ሽፋን እንደሰጡ አድርገው ማቅረባቸውን አንድነት በክሱ አካቶ አቅርቧል፡፡ ፓርቲውን ግንቦት 7 የተባለው ድርጅት ለህቡዕ አደረጃጀት እየተጠቀመበት መሆኑንና የፓርቲው አባል ያልሆኑትን ወይም አባል ለመሆናቸው ምርጫ ቦርድ ያላረጋገጠለትን የሰዎች ስም በመጥቀስ አባል እንደሆኑ አድርገው በማቅረብ ተከሳሾቹ የፓርቲውን ስም ማጥፋታቸውን በመዘርዘር ለችሎቱ ክሱን ማቅረቡን ውሳኔው ያስረዳል፡፡
ተከሳሾቹ ስም የሚያጠፋውን ፕሮግራም የሠሩት ሆን ብለው፣ አቅደውና አስበው፣ ፓርቲው በሌሎች ወገኖች እንዲጠላ፣ እንዲዋረድ፣ እንዲሳቅበት፣ ያለው ተወዳጅነት፣ እምነት፣ መልካም ዝና ወይም የወደፊት ዕድሉ እንዲበላሽ በማድረግ፣ በቀጣዩ ምርጫ ሕዝቡ ጥርጣሬና ውዥንብር ውስጥ ገብቶ ድምፅ እንዲያጣ ከኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያገኘውን የሞራልና የገንዘብ ድጋፍ ለማዳከም በማሰብ የተፈጸመ መሆኑን አንድነት በክሱ ዘርዝሮ ማቅረቡን ክሱ ያብራራል፡፡
ድርጅቱና አቅራቢው የስም ማጥፋት ዘገባውን የሠሩት በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 24(1) የመልካም ስም መከበር መብትን፣ የብሮድካስት አገልግሎት አዋጅ ቁጥር 533/1999 አንቀጽ 30(1) እና አንቀጽ 16(1)ሠን አንቀጽ 30(2)ን በመተላለፍ መሆኑንም የውሳኔው መዝገብ ይገልጻል፡፡ ሌላው ዘገባውን ከሠሩ በኋላ የመገናኛ ብዙኃንና የመረጃ ነፃነት አዋጅ ቁጥር 590/2000 አንቀጽ 40(1)ለንም ለመቀበል ፈቃደኛ አለመሆናቸውን አንድነት በክሱ መጥቀሱንና የምስክሮችንም ስም ለፍርድ ቤቱ ማቅረቡን ውሳኔው ያብራራል፡፡
ተከሳሹ ድርጅት በሰጠው ምላሽ ስም የማጥፋት ወይም የሐሰት ዘገባ አለመሥራቱን፣ በፕሮግራሙ የዘገበው እውነት መሆኑን፣ የማንንም ስም ለማጥፋት አቅዶ የሚንቀሳቀስ ተቋም አለመሆኑን፣ የፌዴራል መንግሥትና የሕዝብ መገናኛ ብዙኃን ድርጅት በመሆኑ በሕግ የተጣለበትን እውነትን የመዘገብና ለሕዝብ መረጃ የማቅረብ ግዴታውን በአግባቡ የሚወጣ ተቋም መሆኑንም አስረድቷል፡፡
በፕሮግራሙ ያቀረበው ዘገባ እውነትና ትክክለኛ መሆኑን፣ ሁሉንም የሚመለከቱትን አዋጆች ባከበረና መሠረት ባደረገ መንገድ መሆኑን፣ ሕዝብ መረጃ የማግኘትን መብት መሠረት ባደረገ የሕግ አስከባሪ አካላት የወሰዷቸውን ዕርምጃዎች ምንነት ማሳወቅ ግዴታ ስላለበት፣ በተጨባጭ መረጃ ተደግፎ የቀረበ እንጂ የማንንም ስም ለማጥፋት ተብሎ የተላለፈ ፕሮግራም አለመሆኑን በምላሹ አካቷል፡፡ የከሳሽ መልካም ስምና ክብሩ የተጐዳበት ዘገባ አለማስተላለፉንም አክሏል፡፡
በአዋጅ ቁጥር 590/2000 አንቀጽ 40(1) መሠረት አንድነት ፓርቲ ስሜና ክብሬ ተጐድቷል የሚል ከሆነ፣ በቅድሚያ ጉዳቱን ማረጋገጥ እንዳለበት ገልጾ፣ ፓርቲው ስሙና ክብሩ ባለመጐዳቱ የላከውን ማስተባበያ እንዳልተቀበለው በመልሱ አስታውቋል፡፡
የአባላቱ መልካም ስም መጥፋቱን ገልጾ ፓርቲው የመሠረተውን ክስ በሚመለከት ተከሳሹ እንዳስረዳው፣ አባሎቹ እነማን እንደሆኑ ባለመግለጹና በዘገባው መሠረት የተፈጸመውን በደል አለማረጋገጡን በመጥቀስ ክሱ ውድቀ እንዲደረግለት ፍርድ ቤቱን ጠይቋል፡፡ ድርጅቱ ዘርዘር ያለ መከራከሪያ ነጥቦችን በማቅረብ የተመሠረተበትን ክስ ተቃውሟል፡፡
በሁለተኛነት የተከሰሰው አቶ አብዲ ከማል በበኩሉ ባቀረበው የመከራከሪያ ሐሳብ የፕሮግራሙ አዘጋጅ አለመሆኑን በመግለጽ፣ አቅራቢ መሆኑንና በአዋጅ 590/2000 መሠረት ፕሮግራም አቅራቢ የሚከሰስበት ኃላፊነት እንደሌለ በማስረዳት፣ የቀረበበትን ክስ በመቃወሙ ፍርድ ቤቱም ተቀብሎ ክሱን በመሰረዝ በነፃ አሰናብቶታል፡፡
ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር መርምሮ የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት በሦስት ክፍሎች ባቀረበው ‹‹አኬልዳማ›› ፕሮግራም የአንድነትን ስም አጥፍቷል ወይስ አላጠፋም? አጥፍቷል የሚባል ከሆነ በአዋጅ ቁጥር 590/2000 አንቀጽ 40(1) መሠረት ማስተባበል አለበት የለበትም? የሚሉ ጭብጦችን ይዞ መመርመሩን ውሳኔው ይገልጻል፡፡
‹‹አኬልዳማ›› ፕሮግራም ከኅዳር 16 እስከ 18 ቀን 2004 ዓ.ም. ድረስ መቅረቡ አለማከራከሩን ፍርድ ቤቱ በውሳኔው ገልጿል፡፡ አንድነት ከፓርቲው በሥነ ምግባር ጉድለት የተባረሩትን፣ በራሳቸው ፈቃድ የለቀቁትንና አባል ያልሆኑትን ወይም አባል መሆናቸው በምርጫ ቦርድ ያልተረጋገጠውን የድርጅቱ አባል እንደሆኑ በማስመሰል ‹‹አኬልዳማ›› ፕሮግራም ላይ ዘግቧል የሚለውን ፍርድ ቤቱ በጥልቀት መመርመሩን በውሳኔው ገልጿል፡፡
ፓርቲው በቴሌቪዥን ዘገባው የፓርቲው አባል እንደሆኑ ተደርጐ ተዘግቧል ያላቸውን ሰዎች ስም ዝርዝር ገልጾ በክሱ ባለማቅረቡ፣ ጥያቄው ለፍርድ ቤቱም ሆነ ለተከሳሽ ድርጅት አስቸጋሪ መሆኑንና በደፈናው መቅረቡ ተከራካሪ ወገን የመከራከር መብትንም የሚያጣብብ ሆኖ በማግኘቱ፣ የአንድነትን ክርክር ውድቅ ማድረጉን ውሳኔው ያሳያል፡፡ በፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 33 እና 231 ድንጋጌዎች መሠረት የቀረበ አለመሆኑንም ጠቁሟል፡፡
ፓርቲውንና ሕጋዊ አባላቱን በሕግ ከተፈረጀው ግንቦት 7 ጋር በህቡዕ ግንኙነት እንዳላቸው በማስመሰል፣ አመራሮቹ ግንቦት 7 በህቡዕ በፓርቲው ውስጥ ሰርጐ እንደገባና እንደተደራጀ እያወቁ ሽፋን ሰጥተዋልና ግንቦት 7 አንድነትን ለህቡዕ አደረጃጀት እየተጠቀመበት መሆኑን በመግለጽ፣ ፓርቲው የመሠረተውን ክስና ተከሳሽ ድርጅት ያቀረበው ምላሽ ፍርድ ቤቱ ትኩረት ሰጥቶ መመርመሩን ውሳኔው ያብራራል፡፡ ፍርድ ቤቱ ለትክክለኛ ፍትሕ አሰጣጥ ይረዳ ዘንድ ‹‹አኬልዳማ›› በሚል ርዕስ በሦስት ተከታታይ ክፍሎች የቀረበውን የቴሌቪዥን ዘገባ አስቀርቦ መመልከቱን በውሳኔው ገልጿል፡፡
በተላለፉት ዘገባዎች ውስጥ የአንድነት ፓርቲን ስም ተከትለው የሚነሱ ስምንት ነጥቦችን ለማግኘት መቻሉን በውሳኔው ዘርዝሮ አቅርቧቸዋል፡፡ በመሆኑም የአንድነት ፓርቲም ሆነ አመራርና አባላቱ በክሱ እንደዘረዘረው በሕግ ከተፈረጀው ግንቦት 7 ጋር ግንኙነት እንዳላቸው በዘገባው መተላለፉ የሚያከራክር አለመሆኑን ፍርድ ቤቱ በሰጠው የውሳኔ ዝርዝር ውስጥ አካቶታል፡፡
በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 24(1) መሠረት ማንኛውም ሰው ሰብዓዊ ክብሩና መልካም ስሙ የመከበር መብት እንዳለው መደንገጉን የጠቀሰው ፍርድ ቤቱ፣ አንድነት ፓርቲ መልካም ስሙ ሊከበርለት እንደሚገባ በውሳኔው አስፍሯል፡፡
አንድ ሰው በንግግሮቹ፣ በጽሑፎቹ፣ በሌላ ዓይነት አድራጐቶቹ በሕይወት ያለውን የአንደኛውን ሰው ስም በማጥፋት፣ ሰው እንዲጠላው፣ እንዲያዋርደው፣ እንዲሳቅበትና በእሱ ላይ ያለው እምነትና መልካም ዝናውና የወደፊት ዕድሉ እንዲበላሽ ያደረገ ሰው፣ በፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 2044 መሠረት ጥፋተኛ እንደሚባል ፍርድ ቤቱ በውሳኔው ጠቁሟል፡፡ ጥፋተኛ መሆኑ በፍርድ ቤት ውሳኔ ያልተረጋገጠበትን ሰው ተጠርጣሪም ቢሆን እንኳ፣ በሕግ የሚያስቀጣ ወንጀል ሠርቷል ማለት ስም ማጥፋት እንደሆነ በፍትሐ ብሔር ሕግ 2109(ሀ) መደንገጉን ፍርድ ቤቱ ጠቅሶ፣ አንድነትን የሽብር ሁከትና ብጥብጥ ፈጣሪ፣ እንዲሁም በሕግ አሸባሪ ከተባሉ ድርጅቶች ጋር ግንኙነት ያለው ከመሆን አልፎ የሽብር ተልዕኳቸውን እንዲያሳኩ አመቻች የሆነ መሆኑን የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድረጅት መግለጹን በውሳኔው አስፍሯል፡፡
ተከሳሽ ድርጅት በጠቀሳቸው የሽብር፣ የሁከትና የብጥብጥ ፈጣሪ መሆንና በሕግ አሸባሪ በመባል ከተፈረጁ ድርጅቶች ጋር ሆኖ መገኘት፣ በፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 5፣ 6 እና 7 መሠረት በወንጀል ሊያስቀጣ እንደሚችል የጠቆመው ፍርድ ቤቱ፣ ድርጊቱ ባልተረጋገጠበት ሁኔታ በአንድነት ፓርቲ ላይ ዘገባ ማስተላለፍ የፍትሐ ብሔር ሕግ 2044 እንዲፈጸምበት ከማድረግም በተጨማሪ፣ በፍትሐ ብሔር ሕግ 2109(ሀ) መሠረት ተከሳሽ ስም ማጥፋቱን የሚያረጋግጥ መሆኑን በውሳኔው አረጋግጧል፡፡
ተከሳሹ ያስተላለፈው ዘገባ እውነትና በመረጃ የተደገፈ መሆኑን ገልጾ ያቀረበው መከራከሪያን ፍርድ ቤቱ ውድቅ ማድረጉን፣ የከሳሹ የክስ አቤቱታ ውድቅ እንዲደረግ ተከሳሽ መጠየቁ የሕግ ድጋፍ እንደሌለው፣ ተከሳች በአጠቃላይ የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 24(1)ን፣ የብሮድካስት አገልግሎት አዋጅ 533/1999 አንቀጽ 30(1)ንና አንቀጽ 30(2)ንና የመገናኛ ብዙኃንና የመረጃ ነፃነት አዋጅ 590/2000ን የተላለፈ መሆኑን ፍርድ ቤቱ በውሳኔው አብራርቷል፡፡
በመሆኑም በአዋጅ 590/2000 መሠረት ከሳሽ በ‹‹አኬልዳማ›› የቴሌቪዥን ፕሮግራም ዘገባ ስሙ የጠፋበትን ማስተባበያ ዘገባ የሚያርም መልስ በቴሌቪዥን ጣቢያው እንዲያስተባብል ፍርድ ቤቱ መፍረዱን መጋቢት 23 ቀን 2006 ዓ.ም. በሰጠው ዝርዝር ውሳኔ አስታውቋል፡፡