Saturday 10 January 2015

የአንድነት የምስራቅ ቀጠና አደራጅ የሆነው ምርቱ ጉታ በደህንነት ሐይሎች ታፈነ!

ምርቱ ጉታ የአዳማ ከተማ አንድነት ሰብሳቢ ሆኖ በ2006ዓ/ም ሲያገለግል ጀምሮ ክትትል ሲደረግበትና ዛቻ ሲፈጸምበት ቆይቶ በዛሬው ዕለት ወደአዲስ አበባ ለመሄድ ከቤቱ በማላዳ ሲወጣ በተከታተሉት የደህንነት ሰዎች አማካኝነት ታፍኖ መወሰዱን ከአይን ምስክሮች ለማወቅ ተችሏል፡፡በመልካም ስነምግባሩና ለትውልዱ ካለው ተቆርቋሪነት የተነሳ በሚኖርበት ቀበሌ የህዝብ ቤተመጽሀፍት በማቋቋም ምስጋና የተቸረው ይኸው ወጣት በህዝቡ ላይ ያለውን ጫና ለመቀነስ ከሚያደርገው ጥረት በተጨማሪ በ1997 ዓ/ም በአንድ ሲቪል ድርጅት አማካኝነት ስለምርጫ አፈጻጸም በሚያስተምርበት ወቅት ነበር ስለፖለቲካ ግንዛቤውን ማስፋት የጀመረው፡፤በዚያም ወቅት በሲቪል ድርጅቱ የተሰጠውን ስራ በመስራት ላ ሳለ ወከባና ክትትል ሲደረግበት ወደ አዲስ አበባ በመሄድ የሆቴል ሙያን በማጥናት በሸራተንናበኢትዮጵያ አየር መንገድ ሲሰራ ቆይቷል፡፡አንድነት ፓርቲ ሲመሰረትም ከወጣቶቹ የፓርቲው አባላት ጋር በመሆን ፓርቲውን መስርቷል፡፡
‹‹ልጅህን ብታሳድግ ይሻልኃል፡፡››እየተባለ ማስፈራረሪያ ሲደርስበት የከረመው ምርቱ በዛው ዕለት በማለዳ ለስብሰባ ወደ አዲስአባባ ሊጓዝ ከቤቱ ሲወጣ ጀምሮ በመኪና ሲከታተሉት የነበሩት ሰዎች ማንነታቸው ተገልጦ ከኋላዋ ክፍት በሆነች መኪና ላይ በአንድ ደህንነትና በሶስት ፖሊሶች ታጅቦ መወሰዱን የአይን ዕማኞች ገልጸዋል፡፡
የአዳማ አንድነት ጽ/ቤት በደርጅታችን የወጣቶች ጉዳይ ሐላፊና በቀጠናው አደራጅ ላይ የደረሰውን አፈና ለማጣራት በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡እስካሁን በሁለት የከተማው ፖሊስ ጣቢያዎች ባደረግነው ጥያቄ ለም የሚል ምላሽ ተሰጥቶናል፡፡በሰላማዊ ትግላችን ኢህአዴግን ከስልጣን ለማውረድ የምናደርገውን ትግል እንቀጥላለን፡፤
ድል የሕዝብ ነው!
የአዳማ አንድነት ጽ/ቤት10930100_1513059112292103_1900285716832279613_n

የሕዝባችን አንድነት እና የአገራችን ታሪካዊ መልካአ-ምድር ለመጠበቅ ታሪካዊ ሃላፊነት ለሚሰማችሁ ኢትዮጵያውያን በሙሉ፦

እንደሚታወቀው የጎንደር ክ/ሀገር፤ የጋራ መመኪያችን ለሆነችው ኢትዮጵያችን የአንድነት መሰረት የታሪክ እምብርት በመሆን ትታወቃለች። በመሆኑም፤ ለሁላችንም ኩራት እና መመኪያ የሆነችውን ኢትዮጵያ አገራችን ለማጥፋት መሰሪ አላማን ይዘው የተነሱ አገር አጥፊዎች ሁሉ የመጀመሪያ የጥፋት ክንዳቸውን የሚሰነዝሩት፤ ጦራቸውን የሚወረውሩት አላማቸው በቀላሉ ይሳካ ዘንድ በቅድሚያ በጎንደር ላይ ነው። እንደምሳሌ የውጭ ወራሪዎችን ብንጠቅሥ፤ በእጅ አዙር ቱርኮች ከግብፃዊያን ጋር በመተባበር የሀገር ውስጡን ግራኝ መሃመድን በመሳርያነት በመጠቀም ከ1519-1535 ዓ. ም፤ እንዲሁም ድርቡሾች በ1880-81 ዓ. ም. በቀጥታ፤ በማዝመት፤ ስፍር ቁጥር የሌለው ወገኖቻችን ጨፍጭፈዋል፤ የታሪክ ቅርሶችን መዝብረው፤ ቀሪውን ለማሥረጃ እንዳይተርፍ ለቃቅመው አቃጥለዋል። —

አሁንም ምርጫ ቦርድ ሃላፊነት ከጎደለው አፍራሽ ተግባሩ እንዲቆጠብ እንጠይቃለን!!! – አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት)

ከአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) የተሰጠ መግለጫ
አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ትግሉን በቁርጠንነት በመምራት የሚያደርገውን ጠንካራ እንቅስቃሴ ተከትሎ ፓርቲውን ከፖለቲካው ምህዳር የማጥፋት ዘመቻው ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ ፓርቲያችንን ወደ ኋላ ለመመለስ ከህግ አግባብ ውጭ የተሰጠውን ስልጣን ካላግባብ በመጠቀምና ለገዥው ፓርቲ በመወገን እየሰራ ያለው ምርጫ ቦርድ መሆኑ ደግሞ እንደ ፓርቲ ብቻ ሳይሆን እንደዜጋ እንድንሸማቀቅ አድርጎናል፡፡
በ2007 ዓ.ም የሚካሄደውን ሀገር አቀፍ ምርጫ ተከትሎ ጠንካራ ፓርቲዎችን ከውድድር የማስወጣት ሃላፊነት ወስዶ እየተንቀሳቀሰ ያለው ይሄው የምርጫ ቦርድ አሁንም በታሪክና በህዝብ ዘንድ የሚያስጠይቀውን ተግባር አይኑን ጨፍኖ እየተገበረ ይገኛል፡፡ በተለይም በፓርቲያችን ላይ የያዘው የማፍረስ አቋም የቦርዱን ለህወሃት/ኢህአዴግ አሸርጋጅነትና አንጋሽነት ያጋለጠ ሆኖ አግንተነዋል፡፡
ቦርዱን እንደተቋም ቆጥረን ባደረግናቸው የደብዳቤ ልውውጦች አማካኝነት የጉባኤ ኮረም ቁጥር እንዲሟላ በመጠየቁ ታህሳስ ሦስትና አራት ቀን 2007 ዓ.ም የቦርዱ ተወካይ በተገኘበት የደመቀና ህጉን የጠበቀ ጉባኤ ማድረጋችን ይታወቃል፡፡ ሆኖም ግን አንድነት ወደ ምርጫ እንዳይገባ የፖለቲካ ውሳኔ በመወሰኑና ቦርዱም እጁ የተጠመዘዘ ተቋም በመሆኑ ጉባኤውን ውድቅ የሚያደርግበት ሰበብ ፈልጎ ታህሳስ 28 ቀን 2007 ዓ.ም በፃፈው ደብዳቤ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ እንዲጠራ ጠየቀ፡፡ የሚገርመው መጠየቅ ብቻ ሳይሆን በ4 ቀን ውስጥ እንዲካሄድ ማለቱ ነው፡፡
የአንድነት አባላት በቦርዱ አድሎአዊ አሰራር በመቆጣታቸው ለዳግም ጉባኤው እንደሚገኙ በማረጋገጣቸው ለእሁድ ጥር 3 ቀን 2007 ዓ.ም ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል፡፡ ነገር ግን ቦርዱ የፈለገው አንድነት በሚስጥር ድምፅ አሰጣጥ ፕሬዘዳንት መምረጡን አይደለም፡፡ ቦርዱ የፈለገው አሳፋሪ በሆነ መንገድ ፕሬዘዳንት የመምረጥ መብት የአንድነት የጠቅላላ ጉባኤ አባላት ሆኖ እያለ ቦርዱ እኔ ፕሬዘዳንት ካልመረጥኩላችሁ እያለ ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር በጎንዮሽ አሻንጉሊት የሆነ አንድነት በመፍጠር ገዥው ፓርቲ ለብቻው የሚሮጥበት ሜዳ ማበጀት ነው፡፡
ይሄው ቦርድ አስቸኳይ ጉባዔ እንድንጠራ አዝዞ እያለ በጎን ከተለጠፊና አንድነት ከማያውቃቸው ግለሰቦች ጋር በመሞዳሞድ ተወካይ አልክም የሚል ድፍረት ላይ መድረሱ አሁንም የውንብድና ስራ እየሰራ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው፡፡ በተጨማሪም የቦርዱ ም/ሰብሳቢ የሆነው አቶ አዲሱ ገ/እግዚአብሄር የተባለው ግለሰብ በሬድዮ ፋና በመቅረብ ታዛቢ እንዲልኩ በደብዳቤ ጠይቀናቸውና ፈርመው ተቀብለው እያለ ይህንን በመካድ ምንም አይነት ጥያቄ አልደረሰንም የሚለው ቅጥፈታቸው በታሪክም በህግም ተጠያቂ ያደርጋቸዋል፡፡
አሁንም ፓርቲያችን የተጠመዘዘው የምርጫ ቦርድ ሃላፊነቱን ይወጣል የሚል እምነት ባይኖረውም ቢያንስ ከአፍራሽነት ሚናው እንዲታቀብ እንመክራለን፡፡ ፓርቲያችንን ከሰላማዊ ትግል መንገድ ለማስወጣት እያደረገ ያለውን ሃላፊነት የማይሰማው አሳፋሪ ተግባር አቁሞ ሃላፊነቱን ለመወጣት ትንሽ እንዲሞክር እንጠይቃለን፡፡ ፓርቲያችን ህገወጥነትን ከህዝቡ ጋር በመሆን አምርሮ እንደሚታገለውና አሸናፊም እንደሚሆን ለህዝባችን ቃል እንገባለን፡፡
አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት)
ድል የሕዝብ ነው
ጥር 2 ቀን 2ዐዐ7 ዓም
አዲስ አበባ10153833_587630041337455_4078181881316786241_n

Friday 9 January 2015

በመላው ሀገሪቱ ለምትገኙ ለአንድነት ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች በሙሉ! ወሳኝ የትግል ምእራፍና ወሳኝ ሰዓት ላይ እንገኛለን !!!

ኢህአዲግና ምርጫ ቦርድ በስውር ከተደራጁ ህገ-ወጥ የማፊያ ቡድኖች ጋር በመሆን አይበገሬና በቆራጥ ሰላማዊ የነፃነት አርበኞች የተገነባውን አንድነት ፓርቲን ላለፉት ጊዜያት ፓርቲያችንን ለመበታተንና የህዝብ አለኝታነቱን በማሳጣት ከምርጫ ለማስወጣትና ሰላማዊ የትግል ሂደቱን ለማኮላሸት ያልፈነቀሉት ድንጋይ እንዳልነበረ፤..መላው ለውጥ ፈላጊ ኢትዮጵያውያንና የአንድነት አባላት ሲከታተሉት የነበረ ሀቅ ነው፡፡ ……በኢህአዲግ የበላይነት የሚመራው ምርጫ ቦርድ፤….. በህወሀት ካድሬዎች ተቀባብሎ የሚሰጠውን አንድነትን ኢላማ ያደረገ ጥይት ለመተኮስ ወደኋላ አልተመለሰም፡፡ ….ከጥቂት የስርአቱ ተላላኪ በአንድነት ውስጥ የተሰገሰጉ ሰርጎ ገቦችና በገንዘብ የተገዙ የሀገርም ሆነ የወገን ፍቅር የሌላቸው ባንዳዎች ጋር በመደራጀት አንድነትን የመፈረካከስ ውጥናቸውን ለማሳካት በሚሊየን የሚቆጠር ገንዘብ በጅተው ሲንቀሳቀሱ ሰንብተዋል፡፡ ….ለነዚህ ህገ-ወጥ የማፊያ ቡድኖች፤…የህጋዊ ነን ጥያቄ የሽፋን ምላሽ የሰጠው ምርጫ ቦርድ፤….የአንድነት አመራሮች ላይ ለህጋዊና ሀገራዊ ፋይዳ ላለው ጉዳይ የማያዥጎደጉድትን ደብዳቤ ህፀፅ እየፈለጉ የተልእኮ ምእራፋቸውን ጀመሩ፡፡ ነግር ግን ጉዳዩን በታላቅ ፖለቲካዊ ብስለትና ህጋዊ አካሄድ ሲመረምሩትና ሲከታተሉት የነበሩት በሳል የአንድነት አመራሮች፤…የውሀ ቀጠነ አይነት የምርጫ ቦርድ ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ በመስጠት የፓርውን ህጋዊነት ያረጋገጡ ቢሆንም፤….አላማው ‹‹የኢህአዲግንና የባንዳ ሰርጎ ገቦቹን ተልእኮ ማስፈፀም የሆነው ምርጫ ቦርድ ግን በሰላማዊ ትግል ውስጥ ታሪክ ሊሽረው የማይችል ጥቁር ነጥብ አሳርፎ፤……አንድነትን የመበታተን ተልእኮውን በማገዝ ላይ ይገኛል፡፡ …በዚሁም መሰረት ይኸን ጠንካራ ህዝባዊ ፓርቲ መርህን እናስከብራለን የሚሉት የህወሀት የማደጎ ልጆች የሆኑት የምርጫ ቦርድ ሀላፊ ተብዬዎች መርህን ባልተከተለ መልኩ አንድነትና መኢአድ በምርጫው አይሳተፉም ሲሉ በድፍረት በሚዲያዎች ሲዘባርቁ ተሰሙ፡፡ …… ይህ ግን ምን ያህል ዋጋ እንደሚያስከፍላቸው ጠንቅቀው አለመረዳታቸውና አንድነት እነርሱ በሚያደርጉት ስውር ደባ ሰላማዊ ትግሉን በማጠናከር፤መከፈል ያለበትን መስዋትነት በመክፈል እንደሚገፋበት ባለመገንዘባቸው ይኸን ታሪካዊ ቅሌት ሊሰሩ ተገዷል፡፡
ውድ የአንድነት ደጋፊና አባላት፤……ይሄ ‹‹አንድነትን ከምርጫ አትሳተፍም›› የሚል ውሳኔ ሁላችንም የምንመለከተው ‹‹ባቄላ አለቀ ቢሉት፤…..›› እንደተባለው የሀገራችን ብሂል ነው፡፡ ….አንድነት በህዝብ ያለውን ሰፊ መሰረት በመጠቀም የተዘጋውን በር አስከፍታለሁ ብሎ ያለቅድመ ሁኔታ በምርጫው ለመሳተፍ ሲወስን ምርጫውን ያለማንም አለማቀፍም ሆነ ሀገራዊ ታዛቢዎች እራሱ አዘጋጅቶ ሊበላው ያቀደው ዋንጫ መሆኑን ሳንረዳ ቀርተን አይደለም፡፡ …… አንድነት ፓርቲ በገዢው የኢህአዲግ መንግስትም ሆነ በአጃካሪዎቹ ምርጫ ቦርድና ሌሎች ተላላኪዎች ሴራ ጥቂት እንኳ አይደነብርም እንደውም ትግሉን አጠናክሮ ይገፋበታል እንጂ፤…….ወደደም ጠላም አንድነት በ2007 ዓ.ም ለለውጥ የሚያደርገውን ግስጋሴ አንዳችም አካል ሊገታው እንደማይችል ሊረዱት ይገባል፡፡ ……እናም የአንድነት አባላትና ደጋፊዎች ፓርቲያችን የሚሻለውን አማራጭ ሁሉ ተጠቅሞ፤….አልሆን ሲለው ለሚወስደው ቆራጥ ፖለቲካዊ ውሳኔ ከወዲሁ ቀበቷችንን ጠበቅ በማድረግ፤…… በዚህ ወሳኝ የትግል ምእራፍ ላይ ኢህአዲግንም ሆነ የማደጎ ልጆቹን አንገት ማስደፋት ይጠበቅብናል፡፡ ድል የሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ ነው!!! …….. ለለውጥ እንነሳ!!!10153833_587630041337455_4078181881316786241_n

ምርጫ ቦርድና ከመኢአድና ከአንድነት ፓርቲዎች ጋር የገባው ውዝግብ ይበልጥ እየ ተካረረ ነው።

ጥር ፩(አንድ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-መኢአድ መስዋትነት ለመክፈል ዝግጁ ነን፤ ሲል አንድነት ፦” ኢህአዴግን በምንም መልኩ አንፋታውም እያለ ነው።
ባሳለፍነው ሳምንት መግቢያ የምርጫ ቦርድ  ምክትል ሰብሳቢ  <<አንድነትና-መኢአድ በውስጠ ድንባቸው መሰረት ያልፈቷቸው ችግሮች አሉ፤ችግሮቻቸውን ካልፈቱ በምርጫው ላይሳተፉ ይችላሉ>> ማለታቸው ነው  የውዝግቡ መነሻ።
በወቅቱ በውስጠ-ደንቡ መሰረት ምንም ያልፈታው ችግር እንደሌለ የገለጸው አንድነት ፓርቲ፤ ምርጫ ቦርድ  በምርጫው እንዳይሳተፍ ካገደው ውሳኔው ፖለቲካዊ ስለሚሆን ፤ፓርቲውም ተመጣጣኝ የሆነ ፖለቲካዊ ውሳኔ ለመወሰን እንደሚገደድ ማስጠንቀቁ ይታወቃል።
ፓርቲዎቹ  ይህን ቢሉም ምርጫ ቦርድ  በምክትል  ሰብሳቢው በኩል ካንጸባረቀው አቛም ለውጥ ሊያደርግ ባለመቻሉ በ የ እለቱ ውጥረቱ እየተካረረ መጥቷል። ስለጉዳዩ ኢሳት ያነጋገራቸው  የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት የህዝብ  ግንኙነት ሀላፊ አቶ ተስፋሁን ኣለምነህ   ምርጫ ቦርድ ከ2005 ጀምሮ በመ ኢ አድ የውስጥ ጉዳይ እየገባ ሴራ ሲጎነጉንና ሲበጠብጣቸው  መቆየቱን በመጥቀስ እና የዛሬ ሁለት ኣመት ጠቅላላ ጉባ ዔ ከማካሄዽ ጀምሮ አማሉ የተባሏቸውን ነገሮች ሁሉ ቢያሟሉም  ቦርዱ ምክንያት እየፈጠረ ሊቀበላቸው እንዳልቻለ በማውሳት፤<< ችግር አለ ከተባለ ላለው ችግር ሁሉ ተጤያቂው ራሱ ቦርዱ ነው።>>ብለዋል።
የችግሩ ምክንያት ምርጫ ቦርድ ገለልተኛ ያልሆነና  የገዥው ፓርቲ አንድ ቅርንጫፍ የሆነ ተቋም በመሆኑ ነው ሲሉም የህዝብ ግንኙነት ሀላፊው ይናገራሉ ህልውናችን በምንከፍለው መስዋ እትነት ላይ እንጂ በምርጫ ቦርድ ይሁንታ ላይ የተንጠለጠለ አይደለም”ያሉት አቶ ተስፋሁን ዓለምነህ<<ምርጫ ቦርድ ፈቀደም አልፈቀደም መኢአድ ለዚች ሀገር ዲሞክራሲያዊ ስር ኣት ግንባታ አስፈላጊ ነው ያለውን ነገር ከማድረግ ወደ ሁዋላ እንደማይል አስታውቀዋል።
በተመሳሳይ<<ኢህአዴግ-አንድነትን ከምርጫ ውጪ ለማድረግ ደፋ ቀና እያለ ነው፤ ይሁን እንጂ ዘንድሮ ኢህአዴግን በምንም መልኩ አንፋታውም!>>ሲሉ የአንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ ገልጸዋል።
ሀላፊው አቶ አስራት እንደጠቆሙት፤ አንድነት በገዥው ፓርቲ በተሸረበበት ሴራ ዙሪያ ለመነጋገርና ምን ማድረግ እንዳለበት ለመምከር ለፊታችን እሁድ ጠቅላላ ጉባዔ ጠርቷል።
ፓርቲያቸውን ከምርጫ ጨዋታ ውጪ ለማድረግ በገዥው ፓርቲ በኩል  የተያዘው አቋም ያስቆጣቸው የሚመስሉት አቶ አስራት<< ኢህአዴግ የእግዴ ልጁ በሆነው ምርጫ ቦርድ በኩል ከአንድነትና ከመኢአድ ጋር የመረረ ትግል ውስጥ ገብቷል ።>>ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል።
<< አንድነት እጅግ በጣም አስደማሚና አስገራሚ የሆነ ጠቅላላ ጉባኤ አካሄዶ ሁሉም ማሳፈሩ የሚታወቅ ነው>>ያሉት የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ፤ <<ይህን አይቶ ማመን ያልቻለው ኢህአዴግ ግን እስኪ  ድገሙት ልየው እያለ ነው!>>ብለዋል።
ዥው ፓርቲ ከዚህም በተጨማሪ አንድነትን ከምርጫ ውጪ ለማድረግ ጭፍሮቹን ይዞ ደፋ ቀና እያለ ቢሆንም አንድነቶች  እጅ መስጠት የለም እያሉ እንደሆነ አቶ አስራት ገልጸዋል።
<<አንድነትን ከዘንድሮ ምርጫ ውጭ ለማድረግ የተሸረበውን ሴራ ለማምከን፤ በታሪክም አንድነት ያለምንም ምክንያት ከምርጫው እንደታገደ ለማሳየት አሁንም በድጋሚ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ ለእሁድ ጥር ሶስት መጠራቱን የጠቀሱት የህዝብ ግንኙነት ሀላፊው፤ <<ከዚያ በኋላ አምባገነኑ የኢህአዴግ መንግስት ዓይኑን በጨው አጥቦ አንድነትን ይዘጋው እንደሆን እናየዋለን። ዘንድሮ ኢህአዴግን በምንም መልኩ አንፋታውም!!>>ብለዋል።
የምርጫ ቦርድ  ምክትል ሰብሳቢ <<አንድነትና-መ ኢአድ በውስጠ ድንባቸው መሰረት ያልፈቷቸው ችግሮች አሉ፤ችግሮቻቸውን ካልፈቱ በምርጫው ላይሳተፉ ይችላሉ>> ማለታቸው ይታወሳል።
በውስጠ-ደንቡ መሰረት ምንም ያልፈታው ችግር እንደሌለ የገለጸው አንድነት ፓርቲ በበኩሉ፤ ምርጫ ቦርድ  በምርጫው እንዳይሳተፍ ካገደው ውሳኔው ፖለቲካዊ ስለሚሆን ፤ፓርቲውም ተመጣጣኝ የሆነ ፖለቲካዊ ውሳኔ ለመወሰን እንደሚገደድ ማስጠንቀቁ ይታወቃል።
በተያያዘ ዜና ምርጫ ቦርድ ሰማያዊ ፓርቲ ስብሰባ ረግጦ በመውጣቱ ይቅርታ ይጠይቅ ማለቱን  ፓርቲው እንደማይቀበለው አስታወቀ። የፓርቲው የየድርጅት  ጉዳይ ሀላፊ አቶ ብርሀኑ ተክለያሬድ፦” ጓዶች እኛ ሰማያዊዎች ነን፤ ማስፈራራት እኛ ላይ አይሰራም፡፡ ማንም ሊያንበረክከን ቢሞክር አንንበረከክም፡፡ ከተንበረከክንም ለፍቅር ብቻ ነው፤ አልያም የትእቢተኛውን ጉልበት ጎትተን ለመጣል!!!!!” በማለት ነው ለቦርዱ   ይቅርታ ጠይቁኝ  መግለጫ  ምላሽ የሰጡት።

ምርጫ ቦርድ ወደ ፈንጂ ወረዳ እየተጠጋ እንደሆነ የገለጹት አቶ ብርሀኑ፤<<መስመሩን ያለፍክ ቀን ቀፎው የተነካበት ንብ- ንብ መሳይ ዝንቦችን ለመውረር እየተንደረደረ ይመጣል፡፡>>ብለዋል። የዘንድሮው ብሔራዊ ምርጫ ሊካሄድ ጥቂት ወራት በቀሩበት በአሁኑ ወቅት  በገዥው ፓርቲና በተቃዋሚዎች መካከል ውዝግቡ እያየለ፣ውጥረቱ እየተካረረ  መጥቷል። መንግስት ከዛሬ ነገ ከፓርቲዎቹ ጋር የገባውን ውዝግብ ያጠብ ይሆናል ተብሎ በሚጠበቅበት በ አሁኑ ወቅት የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት  በሰጠው መግለጫ፦”በሠላማዊ መንገድ መንቀሳቀስ ለሚፈልግ ኃይል ሰፊ የፖለቲካ ምህዳር በመኖሩ ብጥብጥ የሚያስነሳ ምንም አይነት ሰበብ የለም ፡፡”የሚል መግለጫ ሰጥቷል።
ይህም መንግስት በፓርቲዎቹ ላይ ከያዘው አቋም እንደማይመለስ  የሚያመላክት በመሆኑ-ውጥረቱ እያደር ወደ ከፋ ደረጃ ላይ መድረሱ አይቀርም የሚል ስጋት አሳድሯል።

ለጥምቀት ሰማያዊ ቲሸርት እንዳይለበስ ተከለከለ • ህዝብን ያነቃቃሉ የተባሉ መንፈሳዊ ጥቅሶች መጠቀም አይቻልም ተብሏል

ነገረ ኢትዮጵያ) የክርስትና እምነት ተከታይ ወጣቶች ጥምቀት በዓል ላይ ሰማያዊ ቲሸርቶችን እንዳይለብሱ መከልከላቸውን ለነገረ ኢትዮጵያ ገለጹ፡፡ ፈረንሳይ ሌጋሲዮን ጀምሮ እስከ ጃንሜዳ አካባቢ የሚኖሩ ወጣቶች በተለያዩ ማህበራት ስር ለጥምቀት በዓል ዝግጅት እያደረጉ እንደሚገኙ የገለጹት ምንጮቹ ከዝግጅታቸው መካከል ቲሸርት አሳትሞ መልበስ አንዱ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ሆኖም ወጣቶቹ ለጥምቀት በዓል የተለያዩ የመጽሀፍ ቅዱስ ጥቅሶች የታተሙበት ሰማያዊ ቲሸርት ማሳተማቸውም ተከትሎም ደህንነትና ሲቪል የለበሱ ፖሊሶች በየ ቤታቸው እየዞሩ ‹‹ጥምቅት በዓል ላይ ሰማያዊ ቲሸርት መልበስ አይቻልም፡፡›› እያሉ እያስጠነቀቁ መሆኑን ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ በነገው ዕለትም ካድሬዎች ከፈረንሳይ ሌጋሲዮን እስከ ጃን ሜዳ አካባቢ የሚገኙ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን በጉዳዩ ላይ ለማነጋገር ስብሰባ መጥራታቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
በተመሳሳይ ህዝብን ያነቃቃሉ ከሚል ስጋት አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን በቲሸርት ላይም ሆነ ሌላ ለጥምቀት በዓል ላይ በማድመቂያነት በሚውል ነገር ላይ ማተም እንደማይቻል ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው ወጣቶቹ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ ለጥምቀት በዓል ማድመቂያነት እንዳይውሉ ከተከለከሉት ጥቅሶች መካከል ‹‹የጌታ ፈቃድ ይሁን ብለን ዝም አልን፣ ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚያብሄር ትዘረጋለች፣ የአባቶቻችን ርስት አንሰጥም….›› የመሳሰሉት ይገኙበታል ተብሏል፡፡ እነዚህን መንፈሳዊ ጥቅሶች መጠቀም እንደሚያስቀጣም ደህንነትና ፖሊሶች የበዓሉ አዘጋጅ ወጣቶችን አስጠንቅቀዋል፡፡
ወጣቶቹ ሰማያዊ ቲሸርትም ሆነ የተከለከሉትን መንፈሳዊ ጥቅሶችን በሐይማኖታዊ ፋይዳቸው ምክንያት ባለፉት የጥምቀት በዓላት ላይ ሲጠቀሙባቸው እንደቆዩ፣ አሁን ደህንነቶች እነሱ ካላሰቡት ፖለቲካ ጋር ማገናኘታቸው እንዳሳዘናቸውና ከሐይማኖታዊ ፋይዳቸው ውጭ ምንም አይነት ትርጉም እንዲኖራቸው ታስበው የተሰሩ ባለመሆናቸው በበዓሉ ላይ እንደሚጠቀሙባቸው ገልጸዋል፡፡

Thursday 8 January 2015

ኢትዮጵያዊያን አንዳርጋቸውን ሲያዩ የሚታያቸው ጽናት፣ አርበኝነትና አልበገር ባይነት ነው። ሲል ግንቦት 7 ለፍትህ፣ ለዲሞክራሲና ለነፃነት ንቅናቄ ገለጸ።









g7-logoግንቦት 7 <<ሁላችንም አንዳርጋቸው ጽጌን እንሁን!!!>> በሚል ርእስ ዛሬ ታህሳስ 29 ቀን ባስነበበው ርእሰ-አንቀጽ፤በህወሓት ሙሉ ቁጥጥር ስር የሚገኘው የፌደራል ፖሊስ እሁድ እለት በቴሌቪዥን ፕሮግራሙ በግፍ እስር ላይ የሚገኘውን የግንቦት 7 ዋና ፀሐፊን አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን ለ 10 ደቂቃ አቅርቦት እንደነበር በማውሳት፤ይህ የ10 ደቂቃዎች ምስል ለቁጥር በሚያታክት ሁኔታ ተቆራርጦ የተቀጣጠለ በመሆኑና አቶ አንዳርጋቸው በትክክል ምን እንዳለ የሚያስረዳ ባለመሆኑ፤ በይዘቱ ላይ አስተያዬት መስጠት አስፈላጊ እንዳልሆነ ገልጿል።
ከዚያ ይልቅ ህወሀት አንዳርጋቸውን ለምን አሁን ሊያቀርበው ፈለገ?የሚለውን ነጠብ ማዬት እንደሚያስፈልግ የጠቆመው ግንቦት 7፤ ህወሀት በውስጥም፣በውጪም በከፍተኛ ውጥረት ውስጥ የገባበት ወቅት በመሆኑ በተለይ ውስጣዊ ውጥረቱን ለማስተንፈስና አቅጣጫ ለማስቀየር አንዳርጋቸውን በተቆተራረጠ ምስልና ድምጽ አጅቦ ማቅረቡን ጠቅሷል። <<የህወሓት ሌላው መተማመኛው የጦር ሠራዊቱ ነበር።>>ያለው ግንቦት 7፤ ህወሓት፣ የኢትዮጵያን መከላከያ ጦር ሠራዊት ዘረኛ በሆነ መንገድ አደራጅና ከፍተኛ አመራሩን በታማኝ አባላቱ ሞልቶ ተደላድሎ የተቀመጠ መስሎ ቢቆይም አሁን ግን የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላት የኢትዮጵያ ጠላት የሆነውን ህወሓትን የማገልገል ፍላጎት እንደሌላቸውና ይልቁንም ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጎን በመቆም የህወሓትን ውድቀት ለማፋጠን ያላቸውን ጉጉት በግልጽ እያሳዩ መሆናቸውን መረጃዎችን ዋቢ አድርጎ አብራርቷል።
እንደ አየር ኃይል ተቃውሞ ገሀድ የወጣ ዜና አይሁን እንጂ በሌሎችም የሠራዊቱ ክንፎች ያለው አመጽ ተመሳሳይ የጡዘት ደረጃ ላይ መድረሱን የገለጸው ግንቦት 7፤ብአዴን እና ኦህዴድ ውስጥም ለአገራቸው ለኢትዮጵያ እና እንወክለዋለን ለሚሉት ሕዝብ እና ለራሳቸው ክብር ያላቸው አባላት ብቅ ብቅ እያሉ ነው ብሏል። እነኚህንና ሌሎችንም በመላ ሀገሪቱ የተቀጣጠሉትን የመብት ጥያቄዎችና አመጾች የተነተነው ግንቦት 7፤ <<ተቃውሞዎችና አመጾች ተቀናጅተው የመጡ ዕለት መድረሻ እንደሚያጣ የተገነዘበው ህወሓት ትኩረት ለማስቀየስ ሲል አቶ አንዳርጋቸውን እንዳቀረበው ገልጿል።
የፊልሙ ማጀቢያዎች የነበሩት የሂውማን ራይትስ ዎች ሪፓርት፣ ስለእንግሊዝ ጋዜጣ የተነገረው፣ አሜሪካ ስለምትፈጽመው የሰብዓዊ መብት ጥሰት የተዘከረው ሁሉ የሚያመላክቱት አንድ አቢይ ሀቅ አለ።>>ያለው ንቅናቄው፤ ይህም ኢትዮጵያዊያን ፀሐይና ብርድ ሳይበግራቸው “እኔ አንዳርጋቸው ጽጌ ነኝ” እያሉ በእንግሊዝ መንግሥት የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት፣ በእንግሊዝ ኤምባሲዎች እና በአውሮፓ ኅብረት ሲያደርጓቸው የቆዩ ተቃውሞዎች ውጤታማ መሆናቸውን ነው ብሏል። <<ኢትዮጵያዊያን አንዳርጋቸውን ሲያዩ የሚታያቸው ጽናት፣ አርበኝነትና አልበገር ባይነት ነው። የአንዳርጋቸው ምስል በታየ ቁጥር ኢትዮጵያዊያን ፀጉራቸው ይቆማል፤ ደማቸው ይፈላል።>> ያለው ግንቦት 7፤ ወያኔዎች አንዳርጋቸውን ወደፊትም እንዲሁ ሊናገር ያልፈለገውን ቢያናግሩት የሚፈጠር ምንም ለውጥ እንደሌለ አስምሮበታል።
<< እንኳንስ እነሱ አሳሪዎቹ እሱም ራሱ በማይገባው መንገድ አንዳርጋቸው ኢትዮጵያዊያን ልብ ውስጥ ገብቷል።>> ያለው ግንቦት 7፤<< አንዳርጋቸውን ስናይ በህወሓት ፋሽስታዊ መዳፍ ውስጥ የወደቁብንን በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ጀግኖቻችንን ሁሉ ያስታውሰናል። ያነቃናል፣ ያነሳሳናል!!!”ብሏል። ንቅናቄው በመጨረሻም _<<አንዳርጋቸው ጽጌን፣ በርካታ ጀግኖቻችንን፣እራሳችንንና አገራችንን ከወያኔ እስር ነፃ ለማውጣት ክንዳችንን እናበርታ፤ ሁላችንም “እኔም አንዳርጋቸው ጽጌ ነን” እንበል፤ ሁላችንም አንዳርጋቸው ጽጌን እንሁን >>ሲል ለ ኢት ጰያ ህዝብ ጥሪ አቅርቧል።

ሁለት የኢሳት ጋዜጠኞች በድንበር አካባቢ ያሉ እንቅስቃሴዎችን ለመዘገብ ወደ ኤርትራ መሄዳቸው የበርካታ ኢትዮጵያንን እያነጋገረ ነው።

ታኀሳስ ፴(ሠላሳ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ኢሳት በትናንት በዘገባው እንዳስታወቀው ጋዜጠኛ መሳይ መኮንን እና ጋዜጠኛ ፋሲል የኔዓለም  ወደ ኤርትራ ያቀኑት  በኤርትራ ድንበር አካባቢ የሚንቀሳቀሱ የ ኢት ጰያ ተቃዋሚዎች እያደረጉት ያለውን እንቅስቃሴ በዓይን
አይቶ ለመዘገብ፤እንዲሁም  ከተሳካላቸው በወደፊቱ የኢትዮጰያና የኤርትራ ግንኙነት ዙሪያ  የኤርትራ ባለስልጣናትን ቃለ ምልልስ ለማድረግ ነው። ይህን ተከትሎ  እጅግ በርካታ ኢትዮጰያውያን ለጋዜጠኞቹ ያላቸውን አክብሮትና አድንቆት  በመግለጽ ላይ ይገኛሉ።
እነኚህ ወገኖች ፤ጋዜጠኞቹ-  እንደ ጋዜጠኛ በተግባር መሬት ላይ ያለውን ነገር አይተው ለህዝብ ለማሳወቅ  ወደ ድንበር ማምራታቸው ፤ ለሙያቸው የተሰጡ መሆናቸውን የሚያመላክት ከመሆኑም ባሻገር – ውሳኔያቸው በሁለቱ ሀገራት ህዝቦች መካከል መልካም መቀራረብና ወንድማችነት እንዲኖር  የሚያበረክተው አስተዋጻኦ ከፍተኛ  ነው ብለዋል።
አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በየመን መንግስት ለኢህአዴግ ተላልፎ መሰጠቱ  ያስቆጣቸው  ኢትዮጰያውያን ደግሞ፤ በማህበራዊ ሚዲያዎችም ሆነ ወደ ኢሳት ስልክ በመደወል  በሰጡዋቸው አስተያየቶች  ፤ጋዜጠኞቹ የወሰዱትን ድፍረት በማድነቅ በሰላም እንዲመለሱ ምኞታቸውን ገልጸዋል። እነኚህኞቹ  ጋዜጠኞቹ በሰላም  እንዲመለሱ ምኞታቸውን እየገለጹ ያሉት ፤ በሀገር ቤት ያሉ ጋዜጠኞችን  ለእስርና ስደት የዳረገውና በኢሳት ክፉኛ የሚበሳጨው የኢህአዴግ መንግስት እንደ አቶ አንዳርጋችው ጽጌ ጋዜጠኞቹን በመንገዳቸው ላይ  በገንዘብ እንዳያስጠልፋቸው በመስጋት ነው።
በሌላ በኩል የገዥው ፓርቲ አባላት የሆኑ ካድሬዎች ደግሞ፤ የጋዜጠኞቹ ለዘገባ ወደ ኤርትራ ማቅናት  ከተሰማ በሁዋላ ቁጣና ንዴታቸውን ያለመቋረጥ በመግለጽ ላይ ናቸው። በአሁኑ ወቅት ጋዜጠኛ መሳይ መኮንን እና ፋሲል የኔዓለም  በሰላም ኤርትራ ከመግባታቸውም በላይ በነጻነት በመንቀሳቀስ የሄዱበትን ስራ እየከወኑ ይገኛሉ።
ጋዜጠኛ መሳይ በፌስ ቡክ ገጹ አስመራ ከተማን ከሁዋላው አድርጎ በተነሳው ፎቶ ስር ባሰፈረው ጽሁፍ፦<<አስመራ፡ ተራራ ላይ የከተመች፡ ጥንታዊ ገጽታዋን ያለቀቀች ውብ ከተማ። ኢሳት አስመራ ገብቷል፡፡ ሰላማዊውን ትግል በሰፊው እየዘገብን ነው። ዱር ቤታቸው አድርገው በሃይል ህወሀትን ለማስወገድ የተዘጋጁትን ሃይሎች ደግሞ በአካል ተገኝተን ልናያቸው ነው፡፡ባልደረባዬ ፋሲል የኔዓልምም ከአምስተርዳም አስመራ ከቷል። ታሪካዊ ጉዞ ነው፡፡>>ብሏል።
በሚቀጥሉት ቀናት ወይም ሳምንታት ፋሲልና መሳይ በኤርትራ ቆይታቸው ከስፍራው  የሚያጠናቅሯቸውን ዘገባዎች  በቀጥታ የምናቀርብ መሆኑን ከወዲሁ እናሳውቃለን።

መታረም የሚገባዉ ማነዉ? ርዕዮት አለሙ ከቃሊቲ እስር ቤት

በግል የህትመት ዉጤቶች አማካኝነት በሀገሬ ዉስጥ የምመለከታቸዉን ችግሮች ለህዝብ ማቅረብና እንደዜጋም መፍትሔ ይሆናሉ ብዬ የማስባቸዉን ሀሳቦች መጠቆም ከጀመርኩ አምስት አመታት አለፉ፡፡ የመጀመሪያ ፅሑፌን ያዘጋጀሁት ” “ስህተቶችን” ለማረም የተፈፀሙ ስህተቶችና የስህተት ማረሚያ እርምጃዎች” በሚል ርዕስ እንደነበረ አስታዉሳለሁ፡፡ በዚህም ፅሑፍ የፕሬስ፣የፖለቲካፓርቲዎች ምዝገባና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን የተመለከቱ አዋጆች የወጡበት ምክንያትና እንደሀገር የሚያሳድሩትን ተፅእኖ ለመዳሰስ ብሎም ኢህአዴግ ከስህተቶቹ እንዲታረም ለመምከር ሞክሬያለሁ፡፡
የኢህአዴግ ሰዎች በአንድ የገዢዉ ፓርቲ ልሳን በሆነ ድረገፅ አማካኝነት የማስጠንቀቂያ ይዘት ያለዉ ምላሽ መስጠት የጀመሩት ከላይ ከጠቀስኩት የመጀመሪያ ፅሁፌ ጀምሮ የነበረ ቢሆንም በአዲስፕሬስ ጋዜጣ ላይ በአዘጋጅነት ተቀጥሬ መስራት ስጀምር ግን ሁኔታዉ እየባሰ መጣ፡፡ በተለይ የኢትዮጵያ እንባ ጠባቂ ተቋም አዳማ ላይ ከተለያዩ ሚዲያዎች ለተዉጣጣን ጋዜጠኞች የሰጠዉን ስልጠና ከተካፈልኩ በኋል ከስልጠናዉ ጋር በተያያዘ ለህትመት ያበቃሁት ፅሁፍ ኢህአዴጎችን በእጅጉ አስቆጣቸዉ፡፡ በመሆኑም ወደቢሮአችን ተደዉሎ ከኢህአዴግ ፅህፈት ቤት የተደወለ መሆኑ ከተገለፀ በኋላ ለጽሑፌ ምላሽ የላኩ በመሆኑ በፍጥነነት እንድናወጣዉ ቀጭን ትዕዛዝ ተሰጠን፡፡ ምላሻቸዉን ለማዉጣት የእነሱ መደወልም ሆነ ትዕዛዝ አስፈላጊ አልነበረም፡፡ የዝግጅት ክፍላችን አንድ ጽሑፍ የቀረበበት አካል ምላሹን በዚያዉ በተፃፈበት የህትመት ዉጤት ላይ ማስነበብ እንደሚችል በህግ የተደነገገ መሆኑን ከማወቁም በላይ የትኛዉንም አይነት ሀሳብ ለማስተናገድ ክፍት ነበርና ምላሻቸዉን በጋዜጣችን ላይ ታተመ፡፡ በዚህ ብቻ ግን አልተገቱም፤ በወቅቱ የገዢዉ ፓርቲን ሀሳብ በማቀንቀን ይታወቁ የነበሩት እንደ ዳጉ ኢትዮጵያና ሰነድ ያሉ ጋዜጦች ሀሳቦቼን በሃሳብ መምታት ባለመቻላቸዉ ይሁን ባለመፈለጋቸዉ ተራ ዘለፋዎችን ያወርዱብኝ ጀመር፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ የገዢዉ ፓርቲ ደህንነቶች ስልክ በመደወል፣ በዝግጅት ክፍላችን አድራሻ በስሜ ደብዳቤ በመላክና በአካልም በማግኘት ጭምር መንግስትን የሚተቹ ፅሑፎችን እንዳልፅፍ ሊያስፈራሩኝ ሞከሩ፡፡ “ማስፈራራት የሚቻለዉ የሚፈራ ሲኖር ነዉ” እንዲሉ ሙከራቸዉ ዋጋ አልነበረዉም፡፡ ምክንያቱም የመጀመሪያ ፅሑፌን ለህትመት ከማብቃቴ በፊት ልከፍለዉ ስለምችለዉ መስዋዕትነት በሚገባ አስቤበታለሁ፡፡ የሀገሬን ጉዳይ በንቃት የምከታተል ዜጋ እንደመሆኔም ከገዢዉ ፓርቲ የተለየ ሀሳብ ያቀነቀኑ ሰዎች የደረሰባቸዉን በሚገባ አዉቃለሁ፡፡ በመሆኑም ከሁለት መጥፎ ምርጫዎች አንዱን ማለትም እነሱ የደረሰባቸዉን ግፍ እንዳይደርስብኝ የሀገሬን ጉዳይ በተመለከተ ፍዝ ተመልካች መሆንን ወይም በሙያዬ የምችለዉን አስተዋፅኦ አበርክቼ የሚመጣዉን መቀበል መምረጥ ነበረብኝ፡፡ ሁለተኛዉን የተሻለ መጥፎ ምርጫ ከመረጥኩ የሰነበትኩ በመሆኑም እየበረከቱ የመጡትን ማስፈራሪያዎች ከቁብ ሳልቆጥር የጋዜጠኝነት ስራዬን መቀጠል ቻልኩ፡፡ በዚሁ መሰረት ስራ ለመያዝ፣ የደረጃ እድገት ለማግኘትም ሆነ በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ዉስጥ ከደህንነት ስጋት የፀዳ ኑሮ ለመኖር የኢህአዴግ አባል ካልሆነም ደጋፊ መሆን ከጊዜ ጊዜ ግድ እየሆነ መምጣቱን የሚያሳዩ፣ ገዢዉ ፓርቲ እንዳጎናፀፈን የሚገልፅልን ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት በተጨባጭ አለመኖሩን የሚሞግቱ፣ የኢህአዴግን እንደሀገር የማሰብ ችሎታ ወይም ፍቃደኝነት አናሳ መሆን የሚተቹና ሌሎችም መንግስት ቀናነት ቢኖረዉ ኖሮ ሊታረምበት የሚያስችሉትን በርካታ ፅሑፎች አቀረብኩ፡፡ አንድ ቀን ጧት ግን አምባገነኑ መንግስታችን ከጀመርኩት ጉዞ ገታኝ፡፡ ሰኔ10/2003 በወቅቱ እሰራባት በነበረችዉ ተወዳጇ ፍትህ ጋዜጣ ላይ የቀድሞዉን ጠቅላይ ሚኒስትር በተመለከተ ፅሑፍ ለህዝብ ማቅረቤን ተከትሎ ሰኔ14/2003 ዓ.ም ለእስር ተዳረግሁ፡፡
ማዕከላዊና ቃሊቲ ምንና ምን ናቸዉ?ዉድ አንባብያን፤ ፊዘኛዉ መንግስታችን በሽብርተኝነት እንደሚጠረጥረኝ ገልፆ በእጆቼ ካቴና በማጥለቅ በቁጥጥር ስር አዋለኝ ካዋለኝ ከዚያ ቀን ጀምሮ እስካሁን ድረስ ለቁጥር የሚያታክቱ የመብት ጥሰቶችን እየፈፀመብኝ ይገኛል፡፡ ለአብነት ያህል እጅግ በጣም ጥቂቶቹን እነሆ!
ከህጎች ሁሉ የበላይ ህግ ነዉ የሚባልለት ህገመንግስት በጥበቃ ስር ያሉ ሰዎች በጠበቆቻቸዉ የመጎብኘት መብት እንዳላቸዉ ቢገልፅም እኔና ሌሎች የፖለቲካ እስረኞች ግን ይሄ መብታችን በማዕከላዊ አለቆች ተጥሷል፡፡ ጠበቃዬን ለማግኘት የተፈቀደልኝ ምርመራዉ ከተጠናቀቀና ቃል ከሰጠሁ በኋላ ወደቃሊቲ ለመዉረድ የአስርቀናት ዕድሜ ያህል ሲቀረኝ ነበር፡፡ በቤተሰብና በጓደኞቼ ለመጎብኘት የተፈቀደልኝም ሁለት ወር ከ3 ሳምንታት ክልከላ በኋላ ነበር፡፡ ከጠበቃዬ ጋር እንዳልገናኝ ተደርጎ የሚካሄደዉ ምርመራ የፃፍኳቸዉን ፅሑፎች ለምን እንደፃፍኩ፣ ከበስተኋላዬ ሆኖ የሚገፋኝ አካል ስለመኖር አለመኖሩና የመሳሰሉት ጥያቄዎች ላይ ያተኮረ ቢሆንም አልፎ አልፎ ደግሞ መልኩን ይቀይራል፡፡ አንዳንድ ቀን መርማሪዎቹ በማስተምርበት ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት በተካሄዱ ስብሰባዎች ላይ ያቀረብኳቸዉን ሀሳቦች እያነሱ ከመንግስት የደህንነት ሀይሎች የሚያመልጥ ምንም ነገር እንደሌለ በመግለፅ ቢጤ ያሰሙኝ እንደነበር ሳልጠቅስ ማለፍ አልፈልግም፡፡፡ እንዲህ አይነቱ ንግግራቸዉ አሰልቺዉን ምርመራ ዘና እልበት ዘንድ የሚረዳኝ የእፎይታ ጊዜ ሰጥቶኛል፡፡ በአደባባይ ስብሰባዎች ላይ የተናገርኩትንና ደህንነት ሊሰልለዉ የማያስፈልገዉን ግልፅ ነገር እንደ ትልቅ የደህንነቶች የስራ ዉጤት ተደርጎ ሲገለፅ ከመስማት በላይ ምን የሚያዝናና ነገር ይገኛል? የት/ቤት ርዕሰ መምህራኖች በሙሉ የኢህአዴግ አባል እንዲሆኑ የተደረገበት ምክንያት መንግስት እንደሚለዉ የትምህርት ፖሊሲዉን ለማስፈፀም ሳይሆን የመምህራንንና የተማሪዎችን የፖለቲካ አቋም ለማወቅና ይህንኑ ሪፖርት ለማድረግ መሆኑን የማይረዳ መምህር ይኖራል? ይህንን ለማድረግ ፍቃደኛ ያልሆኑ ርዕሰ መምህራኖች ሰበብ እየተፈለገላቸዉ ከቦታቸዉ እንዲነሱ ሲደረግስ ስንታዘብ አልኖርንም? “ሁሉን ቢናገሩት ሆድ ባዶ ይቀራል” አለ ያገሬ ሰዉ! ሆዴ ባዶ እንዳይቀር ሁሉን መተንፈሴን ትቼ የጀመርኩትን የማዕከላዊ ምርመራ ጉዳይ ልቀጥል፡፡
የምርመራዉ ይዘት ከጥቂት ሳምንታት በኋላ መልኩን እየቀየረ መጣ፡፡ በሪፖርተርነት እሰራበት የነበረዉ የኢትዮጵያ ሪቪዉ ድረገፅ አዘጋጅ ኤልያስ ክፍሌ የሽብር ተልዕኮ እንደሰጠኝ በሀሰት እንድናገርና ተከሳሽነቴ ቀርቶ ምስክር ሆኜ እንድፈታ ለማድረግ የተለያዩ ጫናዎቸው ይደርሱብኝ ጀመር፡፡ ለአምስት ደቂቃ ያህል ጧትና ማታ ወደመፀዳጃ ቤት ለመሄድ ከሚከፍቱልኝ በስተቀር ለአስራሶስት ቀናት ያህል ብቻዬን አንድ መጥፎ ሽታ ያለዉ ክፍል ዉስጥ ተዘግቶብኝ ከረምኩ፡፡ በዚህ ወቅት ጉዳዬን የያዘዉ ዐቃቤህግ ማዕከላዊ በመምጣት እያስጠራኝ ሀሳቤን የማልለዉጥ ከሆነ እድሜ ልክ ወይም ሞት እንደሚያስፈርድብኝ ይዝትብኝ ነበር፡፡ ሀሰን ሽፋ በበኩሉ በሀሳባቸዉ የማልስማማ ከሆነ የያዘኝን የወጣት ጀብደኝነት ማስተንፈስ ለነሱ ከባድ ስራ አለመሆኑን ነግሮኛል፡፡ በኔ በኩል ደግሞ ከተጠረጠርኩበት ወንጀል ንፁህ መሆኔ እንጂ ኤልያስ ላይ በሀሰት መመስከሬ ሊያስፈታኝ እንደማይገባ ስለማምን ይህንኑ በተደጋጋሚ አስታዉቄ ተከሳሽ መሆንን መረጥኩ፡፡ ኢህአዴግ እስካለ ድረስ የተሻለዉን መጥፎ እየመረጡ መኖር ዕጣፋንታችን ከሆነ ቆየ አይደል?
ማዕከላዊ እያለሁ ከተፈፀሙብኝ የመብት ረገጣዎች ዉስጥ አንዱ የሆነዉ በአንድ ፖሊስ የተሰጠኝ ጥፊና ከግድግዳ ጋር ማጋጨት በተለይ ወንድ የፖለቲካ እስረኞች ከሚፈፀምባቸዉ ለዘላቂ የአካል ጉዳት የሚዳርግ ከባድ ድብደባ አንፃር ሳስተያየዉ የማዕከላዊ መርማሪዎች እንደሚሉት “ቁንጥጫ” ተብሎ ከመግለፅ የሚያልፍ ባለመሆኑ ብዙ ልልበት አልፈልግም፡፡ በወቅቱ የነበርነዉ ሴት እስረኞች ላይ ያን ያህል የከፋ አካላዊ ድብደባ አልተፈፀመም ማለት ግን የማዕከላዊ መርማሪዎች ለሴቶች ይሳሳሉ ማለት አይደለም፡፡ ለማሳያነት እስካሁን ድረስ ማዕከላዊ በተፈፀመባት ከባድ ድብደባ የተነሳ በህመም የምትሰቃየዋን የፖለቲካ እስረኛ እማዋይሽ አለሙን መጥቀስ ይቻላል፡፡ አይ ማዕከላዊ! ማዕከላዊ ዘና ብለዉ የሚራመዱ ኩሩ የኢትዮጵያ ልጆች በገቡ ሳምንት በማይሞላ ጊዜ ዉስጥ በቃሬዛና በሰዎች ድጋፍ በሸክም ሲያሳልፉና የድረሱልኝ ዋይታ ሲያቀርቡ የሰማሁበት አሰቃቂ ቦታ ነዉ፡፡ ምስላቸዉ ከአይኔ ላይ፣ ጩኸታቸዉ ከጆሮዬ ተጣብቆ የሚኖረዉ እነዚህ ወገኖቼን እያሰብኩ መናደድ መቆጨት የዕለት ተዕለት የኑሮዬ አካል ሆኗል፡፡
የማዕከላዊዉን የመብት ረገጣ እዚህጋ ገታ ላድርገዉና በተለይ የፖለቲካ እስረኞችን ሰብአዊ መብት ከመጨፍለቅ አንፃር አምሳያዉ ወደ ሆነዉ የቃሊቲ እስር ቤት ልለፍ፡፡ ጳጉሜ3/2003 ዓ.ም ቃሊቲ እንደገባሁ በኋላ ላይ የጥበቃ ክፍል ሀላፊ እንደሆነች በተገነዘብኩት ሀላፊ አማካኝነት ጋዜጠኝነቴ ከታሰርኩ በኋላ የቀረ በመሆኑ ግቢዉ ዉስጥ በሚኖረኝ ቆይታ አርፌ መቀመጥ እንደሚኖርብኝ ተነገረኝ፡፡ አልጋ እስከሚለቀቅ ተብሎም እኔና በአንድ መዝገብ የተከሰስነዉ ወ/ሮ ሂሩት ክፍሌ ምንም እንኳን ሁለታችንም የሳይነስ በሽታ ያለብን ቢሆንም ሽንት ቤት አጠገብ መሬት ላይ ፍራሽ አንጥፈን እንድንተኛ ተደረገ፡፡ ዉድ አንባቢያን ስለቃሊቲ ስታስቡ ወደ አዕምሮአችሁ የሚመጡት ያማሩ ግንብ ቤቶችና የተዋቡ አልጋዎች ከሆኑ ኢቲቪ እንደሸወዳችሁ ልነግራችሁ እወዳለሁ፡፡ የፓስተር ዳንኤል ገ/ስላሴ ፕሪዝን ፌሎሽፕ የተባለ ድርጅት እንዳሰራቸዉ የሚናገሩት እነዚህ ያማሩ ግንብ ቤቶች ሁለት ክፍሎችና መፀዳጃ ቤት ብቻ ያሏቸዉ ሲሆኑ የተቀሩት በሴቶች ዞን ዉስጥ ያሉ ክፍሎች ከሁለት ያረጁ ግንብ ቤቶች በስተቀር በቆርቆሮ የተሰሩና እስረኞች በተጨናነቀ ሁኔታ የሚኖሩባቸዉ ናቸዉ፡፡ የቃሊቲ ምቾት አልባነት የሚሰማዉ አካልን ብቻ አይደለም፡፡ ቃሊቲ ከአካል በከፋ ሁኔታ ለነፍስና ለመንፈስ ይጎረብጣል፡፡ እንዴት ቢሉ እንዲህ እልዎታለሁ፡፡ የቃሊቲ የሴቶች ዞን ቤተመፃሕፍት ከጥቂት ወራት ጀምሮ በመፅሐፍቱ አይነትም ሆነ ቁጥር መሻሻልን ቢያሳይም እኔ ቃሊቲ ከገባሁ ጀምሮ እስከቅርብ ጊዜያት ድረስ ግን ከመኖር በማይቆጠር ደረጃ የሚገኝ ነበር፡፡ ይህንን ክፍተት ቤተሰብና ጓደኞቼ በሚያስገቡልኝ መፀሐፍት ለመሙላት ባስብም ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የሚመጡልኝ መፅሐፍት የቃሊቲን ሳንሱር እንደወደቁ ተገልፆ እኔጋ ሳይደርሱ ይመለሳሉ፡፡ ከነዚህ መፅሐፍት ዉስጥ አዲስአበባ ዩኒቨርስቲ የሚሳትማቸዉ የታሪክ መፅሐፍት ሳይቀር ይገኙበታል፡፡ ቃሊቲ ለመንፈስም አይመችም ያልኳችሁ በዚህ ብቻ አይደለም፡፡ በራሴ ወጪ ኢንድራ ጋኒዲ ናሽናል ኦፕን ዩኒቨርስቲ በርቀት ፖለቲካል ሳይንስ ለማጥናት ከብዙ ዉጣዉረድ በኋላ ተፈቅዶልኝ የተበዘገብኩ ቢሆንም የመማሪያ ሞጁሎቹን ለማስገባት ግን የቃሊቲ አለቆች ፍቃደኛ አልነበሩም፡፡ ከብዙ ደጅጥናት በኋላ ሞጁሎቹ ሲገቡ ደግሞ በትምህርቱ ዙሪያ ላነባቸዉ የሚገቡኝ አጋዥ መፅሐፍት ስለፖለቲካ የሚያወሩ በመሆናቸዉ በፍጹም ሊገቡ እንደማይችሉ የመፅሐፍት ገምጋሚዎቹ አረዱኝ፡፡ ይባስ ብሎ በዚያን ወቅት ከሌላዉ ጊዜ በተለየ ሁኔታ ምንም አይነት መፅሐፍት እንዳይገቡልኝ በመደረጉ ለጠቅላላ ዕዉቀት ያህል ሞጁሎቹን ማንበቤን ብቀጥልም ትምህርቱ ግን በዚህና በሌሎች ምክንያት ለማቋረጥ ተገደድኩ፡፡
በቃሊቲ የኔ ብቻ ሳይሆን ከእኔ ጋር የተቀራረቡ ወይም ደግሞ ሰላምታ ያቀረቡልኝ ሰዎች ሳይቀር መብታቸዉ ተጥሷል፡፡ ከሁለት አመታት በላይ የሚሆነዉን ጊዜ በርካታ እስረኞች በነበሩበት ክፍል ያሳለፍኩ ቢሆንም እኔን እንደሌላዉ እስረኛ ለመቅረብ የሞከሩ በሙሉ ስሜትን የሚጎዳ ወከባ፣ዘለፋና ለየት ያሉ ፍተሻዎችን አስተናግደዋል፡፡
በህክምና ጉዳይ የነበሩብኝን ችግሮች በተመለከተ ቤተሰቦቼ ደጋግመዉ የገለፁት መሠረታዊ ችግር በመሆኑ በዚህ ፅሑፍ ነካ አድርጌዉ ብቻ አልፋለሁ፡፡ ጡቴ ዉስጥ በበቀለዉ እጢ ምክንያት ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የህክምና ክትትል በማደርግበት ወቅት በቀጠሮዬ ቀን ወደ ሆስፒታሉ ከምወሰድባቸዉ ይልቅ የማልወሰድባቸዉ ጊዜያት ይበዙ ነበር፡፡ የግራ ጡቴ ቀዶጥገና ከተደረገለት በኋላ በወቅቱ ክትትል ታደርግልኝ የነበረችዉ ዶክተር በሶስተኛ ቀን የቁስሉ ፕላስትር መቀየር እንዳለበትና በሳምንቱ ደግሞ ክሩ መዉጣት እንዳለበት ገለፀችልኝ፡፡ አብረዉኝ የሚሄዱት አጃቢ ፖሊሶች ከዶክተሬም ጋር ስነጋገር እዛዉ ነዉና የሚቆሙት እንዲህ አይነቱን ነገር ለማድረግ የሚችል ጤናጣቢያ ማረሚያቤቱ እንዳለዉ ተናገሩ፡፡ እኔም ቀጠሮ ቢሰጠኝ እንኳ በዚህ በአጭር ጊዜ ዉስጥ ወደሆስፒታሉ ተመልሼ መሄድ አዳጋች መሆኑን ስለማዉቅ የተባሉት ነገሮች ቃሊቲ መፈፀማቸዉን አልጠላሁትም፡፡ በመሆኑም ለህክምና ክትትል የሶስት ወራት ቀጠሮ ተሰጠኝ፡፡ ክሩ መዉጣት ባለበት ቀን ስለጉዳዩ ለጥበቃ ክፍሉ አስታወቅኩ፡፡ እነሱም አሁን ደቡብ ሱዳን ከሚገኝዉ ጦር ጋር አብራ ከተጓዘች አንዲት የህወሐት ታጋይ የነበረች ነርስ ጋር አገናኙኝ፡፡ እሷም እዛዉ ጨርሼ መምጣት እንደነበረብኝና እዚህ ክሩን ማዉጣት እንደማይችሉ ነገረችኝ፡፡ የምታሳየኝ ጥላቻ በሷ እጅ የህክምና አገልግሎት ከማግኘት ቢቀር የሚሻል መሆኑን የሚጠቁም በመሆኑ ብዙም ልከራከራት አልፈለኩም፡፡ ጉዳዩ ይመለከታቸዋል የተባሉ ሌሎች ሀላፊዎች ወደጥቁር አንበሳ ሆስፒታል እንዲወስዱኝ ብጠይቅም “ቀጠሮ የለሽም” በሚል ሰበብ ሳይወስዱብኝ ቀሩ፡፡ በአሁኑ ወቅት የቀኝ ጡቴም ተመሳሳይ እጢ ያለበት በመሆኑ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ወደ ምኒሊክ ሆስፒታል ቀዶጥገና አደርግ ዘንድ የላከኝ ቢሆንም (ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በእድሳት ላይ በመሆኑ)እጅግ የከፋ ህመም ካልታመምኩ በቀር ቃሊቲ ሆኜ ቀዶጥገና ማድረጉን አልፈለኩም፡፡ በመሆኑም አልፎ አልፎ የሚሰማኝን ህመም በህመም ማስታገሻ መድሀኒቶች በማቃለል የቃሊቲን አስቀያሚ ቀኖች በመግፋት ላይ እገኛለሁ፡፡
ሌላዉ የቃሊቲ ቆይታዬን በተመለከተ ልጠቅሰዉ የምፈልገዉ ጉዳይ ከመንግስት አካላትና ከተለጣፊዎቻቸዉ ጋር ካለፍላጎቴ እንድንገናኝ እየተደረገ የሚፈፀምብኝ የሰብአዊ መብት ረገጣ ነዉ፡፡ ለምሳሌ ያህልአንዱን ብቻ ልጥቀስ፡፡ አምና መጋቢት ወር ዉስጥ አምባሳደር ጥሩነህ ዜናን ጨምሮ ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን መምጣታቸዉን የገለፁ ሌሎች አስር ሰዎች ከአመት በፊት ወደገባሁበትና ከሌሎች ከአራት ሰዎች ጋር ብቻ ወደምኖርበት ክፍል መጡ፡፡ እኔም ኮሚሽኑ በተለይም ደግሞ አምባሳደሩ የሰብአዊ መብት አከባበርን አስመልክቶ የሚሰጧቸዉ ከእዉነት የራቁ መግለጫዎች የሚያሳዝኑኝ በመሆኑ ለመነጋገር ፍቃደኛ አለመሆኔን በማስታወቅ ከክፍሉ ወጥቼ በሩ ላይ ቆምኩ፡፡ ከሰዎች አንዱ የምኖርበትን ክፍልና አልጋዎቻችንን ፎቶ ሲያነሳ ተመለከትኩ፡፡ ገረመኝ፤ መሬት አንጥፌ ስተኛ፣በተደራራቢ አልጋ የላኛዉ ክፍል ላይ ከጡት ህመም ጋር እየታገልኩ ስተኛና በተፋፈገ ክፍል ዉስጥ ስኖር ለምን የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ፎቶ አላነሳም? ማረሚያ ቤቱ በጥሩ ሁኔታ እስረኞቹን የያዘ መሆኑን ማሳያ ለማድረግ እንደተፈለገ ገመትኩ፡፡ እዉነታዉ ግን ይቺ ያለሁባት በቆርቆሮ የተሰራች ክፍልና ጠባቧ ግቢ አምና መስከረም ላይ በጠያቂዎች የመጎብኘት መብቴ መጣሱን ተከትሎ በጥድፊያ የተዘጋጀች ማግለያ ቦታ መሆኗ ነዉ፡፡ ክፍሉን ብቻ ፎቶ አንስተዉ መሄዳቸዉ ያላረካቸዉ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ሰዎች በማግስቱ አራት ሆነዉ መጡ፡፡ ሁለቱ ወደግቢዉ ዉስጥ ሲገቡ ሌሎቹ ሁለቱ ደግሞ በሩጋ ቆሙ፡፡ ግቢዉ ዉስጥ ከገቡት አንዱ ትላንት ለምን ላናግራቸዉ እንዳልፈለኩ ጠይቆኝ በድጋሚ ከነሱ ጋር መነጋገር ያልፈለኩበትን ምክንያት እያስረዳኋቸዉ እያለ የግቢዉ በር ክፍት ስለነበር ግቢዉ በርጋ ከቆሙት አንዱ ፎቶ ሊያነሳኝ ሲሞክር ለመመልከት ቻልኩ፡፡ ምስሌን አንስቶ ቢሆንና ስለኔ አንዳች አይነት ዉሽት ሲናገሩ ብሰማ ጉዳዩን በዝምታ እነደማላልፈዉ ነገርኩትና ወደቤት ዉስጥ ገብቼ በሩን ዘጋሁት፡፡ ከተወሰኑ ደቂቃዎች በኋላ ከክፍሉ ወጥቼ ኢህአዴግ ማሰሩ ሳይበቃዉ ሰብአዊ መብትን ለማስከበር እንዳቋቋማቸዉ በሚናገረዉ ተለጣፊ ድርጅቶቹ ሳይቀር ሰብአዊ መብቴን ለምን እንደሚጥስ ከሀላፊዎቹ አንዷን በማስጠራት ጥያቄ አቀረብኩላት እሷም ሰዎቹ ካሜራ መያዛቸዉን እንደማታዉቅ ነገረችኝ፡፡ በ2005ዓ.ም ከፌዴራል ማረሚያ ቤቶች የህዝብ ግኑኝነት ክፍል እኔን ለማናገር እንደመጣ የገለፀልኝ ሰዉ ኮቱ ዉስጥ ደብቆ በያዘዉ ሪከርደር ድምፄን ለመቅረፅ ሲሞክር ደርሼበት ይህንን ማድረግ የሚችለዉ የግል ፕሬስም ተገኝቶ ንግግራችንን የሚቀርፅ ከሆነ ብቻ መሆኑን ነግሬዉ ነበር፡፡ ይሄንን ያልኩበት ምክንያት የግል ፕሬሱ ባልተገኘበት ለመንግስት ሚዲያዎች ብቻ አስተያየታቸዉን የሰጡ ግለሰቦች ሀሳባቸዉ ተቆርጦና ተቀጥሎ ለማለት ያልፈለጉት ይዘት ይዞ እንደሚቀርብ አዉቅ ስለነበር ነዉ፡፡ የተናገርኩትን ሙሉዉን ነገር ቀርፀዉ ሊያወጡልኝ የሚችሉ አካላት በሌሉበት ለሰዉዬዉ አስተያየቴን መስጠት ያለፈለኩትም ይኸዉ እንዳይደርስብኝ በመስጋት ነበር፡፡ አስገራሚዉ ነገር ይቺ የኮሚሽኑ ሰዎች ካሜራ መያዛቸዉን እንደማይታወቅ የገለፀችልኝ ሀላፊ ያኔም የሰዉየዉን የድምፅ ሪከርደር መያዝ በተመለከተ ላቀረብኩላት ጥያቄ የሰጠችኝ ተመሳሳይ መልስ ነበር፡፡
የቃሊቲ ጉድ ማብቂያ ስለሌለዉ አንድ የመጨረሻ ጉዳይ ላንሳና የፅሁፌ መነሻ ወደሆነዉ የአመክሮ ጉዳይ አልፋለሁ፡፡ ዉድ አንባቢያን በሀገሪቱ ዉስጥ ያሉ የትኞቹንም እስረኞች አያያዝ የተመለከቱ ህጎችን፣ አዋጆችን፣ ደንቦችንም ሆኑ መመሪያዎችን በጣሰ ሁኔታ ከወላጆቼ በቀር ጠበቃን ጨምሮ በሌላ በማንም ሰዉ የመጎብኘት መብቴን ከተነጠቅኩ አመት ከኣራት ወራት አልፎኛል፡፡ አዛዉንት እናትና አባቴም ከእርጅና፣ ህመምና ድካም ጋር እየታገሉ የቃሊቲን ፈታኝ መንገድ መዉጣትና መዉረዳቸዉን ቀጥለዋል፡፡
ነገረ አመክሮ ያለፈዉ አመት ነሐሴ ስምንት ቀን ከሰአት በኋላ ወደ ጠበቃ ክፍል ሃላፊዋ ቢሮ በአንዲት ፖሊስ ተጠርቼ ተወሰድኩ፡፡ እዚያም ከፌደራል ማረሚያ ቤቶች ዋናዉ መስሪያ ቤት የይቅርታና የአመክሮ ጉዳይ ክፍል እንደመጣና ኮማንደር አስቻላዉ እንደሚባል ከነገረኝ ሰዉ ጋር ተገናኘሁ፡፡ ኮማንደሩ ሰላምታ ከተለዋወጥን በኋላ ያቀረበልኝ የመጀመሪያዉ ጥቃቄ “ይቅርታ ለምን አልጠየቅሽም? ይቅርታ በመጠየቅ ላይ ያለሽ ሀሳብስ አልተቀየረም ወይ?” የሚል ነበር፡፡ ይቅርታ ያልጠየኩት ስላላጠፋሁና የተፀፀትኩበት ጉዳይ ስለሌለ በመሆኑና አሁንም ምንም የተቀየረ አቋም እንደሌለኝ አስረዳሁተ፡፡ “ይሄ የፍርድቤት ጉዳይ ነዉ፡፡ ፍርድ ቤቱ ጥፋተኛ እስካለሽ ድረስ ወደዚያ መመለስ አይኖርብንም” አለኝ፡፡ እኔም አምባገነኑ የኢህአዴግ መንግስት እንዳሻዉ የሚያሽከረክረዉ ፍርድቤት በንፁሃን ላይ የጥፋተኝነት ዉሳኔና ፍርድ ማስተላለፉን አሜን ብዬ ይቅርታ የምጠይቅበት ምንም አይነት ምክንያት እንደሌለ ገለፅኩለት፡፡ ጥቂት ደቂቃዎች ያህል ስለጤንነቴና በጊቢዉ ዉስጥ ስለሚያጋጥሙኝ ችግሮች በተመለከተ ጥያዎችን ስያቀርብልኝ ቆየና ወደ መጣበት ሌላዉ ዋና ጉዳይ ተመለሰ፡፡
“ቅድም ይቅርታ የማልጠይቀዉ ስላልተፀፀትኩ ነዉ ብለሻል፡፡ አመክሮ እኮ የሚሰጠዉ ለተፀፀተ ሰዉ ነዉና እንዴት ልታደርጊ ነዉ?” በማለት ስለ በአመክሮ የመፈታት አካሄድ አንዳንድ የሚኒስተሮች ምክር ቤት ደንቦችን ጭምር በመጥቀስ ሊያብራራልኝ ሞከረ፡፡ “ታዲያ እንዲህ ከሆነ በይቅርታና በአመክሮ መሀል ምንም አይነት መሰረታዊ ልዩነት የለም ማለት ነዋ?” ለሚለዉ ጥያቄ ቀጥታ መልስ ሊሰጠኝ አልፈለገም ይልቁኑ ሁሉም ታራሚ 2/3ኛዉን የእስር ቅጣቱን ለመፈፀም ሁለት ወራት ገደማ ሲቀሩት እንደታረመና እንደተፀፀተ የሚገልፅ ፎርም መሙላት ስለሚኖርበት እኔም ለመፈታት ከፈለኩ ይህንኑ ማድረግ እንደሚጠበቅብኝ አስረግጦ ነገረኝ፡፡ የፃፍኩት የማምንበትንና መቼም ልቆምለት የምችለዉ እዉነት መሆኑን፣ በዚህ የተነሳ አሸባሪ መባሌ ደግሞ የበለጠ ኢህአዴግን እንድታገለዉ የሚየደርገኝ እንጂ የሚያፀፅተኝ ባለመሆኑ እንዲህ አይነቱን ከማንነቴ ጋር የሚቃረን ፎርም እንደማልሞላ አስረግጬ ነገርኩት፡፡ ኮማንደሩም ላልታረመና ለልተፀፀተ ሰዉ አመክሮ መስጠት ለእነሱም እንደሚከብዳቸዉ ከገለጸልኝ በኋላ “እኛ ፎርሙን ብንሞላልሽስ?” የሚል አስገራሚ ጥያቄ አቀረበልኝ፡፡ እኔ “ታርሜያለሁ” እንዳልኩ ተደርጎ ምንም አይነት ነገር ቢደረግ ሀሰት መሆኑን ከማጋለጥ ወደኋላ እንደማልል አስታወቅኩት፡፡ በዚህ አይነት ተመሳሳይ ሀሳቦች ላይ እየተሸከረከርን ጥቂት ጊዜ ከፈጀን በኋላ እንዳሰብበት አሳስቦኝ ተለያየን፡፡
ይህ ከሆነ ሀሁለት ወራት በኋላ የመፈቻዬ ቀን የነበረዉ ጥቅምት 14/2007 ማለፊን ተከትሎ “የአመክሮ ፎርሙን ለምን አትሞይም?” የሚል ጥያቄ ከተለያዩ ሀላፊዎች ይቀርብልኝ ጀመረ፡፡ ከህዳር አጋማሽ ጀምሮ ደግሞ ጥያቄዉ እየጨመረ መጣ፡፡ በተለይ በመጨረሻዎቹ የህዳር ወር ቀናት በአንዱ አራት ሆነዉ ክፍሌ ድረስ በመምጣት አነጋገሩኝ፡፡ ለኮማንደሩ የሰጠሁትን ምላሽ ሰጠኋቸዉ፡፡ የሃለፊዎቹ ሁኔታ ከሁለት አመት በፊት የሆነዉን አስታወሰኝ፡፡ ያኔም የይቅርታ ፎርም ለመሙላት ፍቃደኛ ሳልሆን በመቅረቴ እንዳሁኑ ሰላማዊ በሆነ መልኩ ፎርሙን እሞላ ዘንድ ይጠይቁኝ ነበር፡፡ በእንቢታዬ ስፀና ግን የተለያዩና አብዛኛዎቹም እስከዛሬ የዘለቁ የመብት ጥሰቶችን ይፈፅመብኝ ጀመር፡፡ ያሁኑስ እምቢታዬ ምን ያስከትል ይሆን? አላዉቅም፡፡ አንድ ነገር ግን አዉቃለሁ፡፡ መታረምና መፀፀት ያለብን ኢህአዴግ በሀገር ላይ የሚያደርሰዉን ጥፋት በመቃወማችን ምክንያት የታሰርን እኛ ሳንሆን አምባገነኑ መንግስት መሆኑን!
ዉድ አንባቢያን በመጨረሻ ሰብአዊ መብቶች የተከበሩባት ኢትዮጰያን ለማየት እንዲያበቃን እየተመኘሁ፣ ለተግባራዊነቱም የምችለዉን ሁሉ እንደማደርግና እንደምከፍል ቃል እየገባሁ እሰናበታችኋለሁ፡፡ “ምን ልታደርጊ ትችያለሽ?” የምትሉኝ ካላችሁ መልሴ የሚሆነዉ ማን እንደተናገረዉ ባላስታዉስም “የፍቅር አብዮት” የተሰኘ መጸሀፍ ሳነብ ያገኘሁት አንድ አባባል ነዉ ፡፡
” ሁሉን ማድረግ አልችልም ሁሉን ማድረግ አለመቻሌ ግን የምችለዉን ከማድረግ ወደ ኋላ አያስቀረኝም”
ርዕዮት አለሙ
ከቃሊቲ እስር ቤትreyot_468

Tuesday 6 January 2015

ወሎ ውስጥ በኦሮሞዎች ላይ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየተፈጸመ ነው ተባለ

ታኀሳስ ፳፰(ሃያ ስምንት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የአፍሪካ ቀንድ የሰብዓዊ መብቶች ሊግ፤ ከአማራ ክልል ኦሮሚያ ዞን ያለ ፍርድ ቤት ማዘዣ  ታስረው ከስምንት ወራት በላይ ፍርድ ቤት ያልቀረቡ ታሳሪዎችን ስም ዝርዝር ይፋ አደረገ።
ሊጉ  የ 26  እስረኞችን ስም ዝርዝር በማያያዝ ባወጣው መግለጫ፤ ከወራት በፊት የአዲስ አበባን አዲስ ማስተር ፕላን በመቃወም ተነስቶ ከነበረው ሰላማዊ ተቃውሞ ጋር በተያያዘ  የወሎ ኦሮሞዎችን ጨምሮ በመላ ሀገሪቱ በሚገኙ የኦሮሞ ተወላጆች ላይ እየተፈፀመ ያለው ማዋከብና እስር ሊቆም አለመቻሉን አስታውቋል።
በዚህም የተነሳ አንዳንዶች የት እንደደረሱ ባልታወቀ ሁኔታ መሰወራቸውንና በርካቶች “አጋዚ”ተብሎ በሚጠራው የኮማንዶ አባላት ጥቃት እንደፈፀመባቸው የገለጸው ሊጉ፤ እነዚህ  ታጣቂ ሀይሎች በማስተር ፕላኑ ምክንያት ከተነሳው ተቃውሞ ጋር በተያያዘ እስካሁን ድረስ ዜጎችን ከየቦታው ማሰራቸውን አላቆሙም ብሏል።
የሚጠብቃቸውን እስር በመፍራት በመቶዎች የሚቆጠሩ የዩኒቨርሲቲ፣የኮሌጅና የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ  ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው አለመመለሳቸውን በመግለጫው ያወሳው ሊጉ፤ አብዛኞቹ  ለህይወታቸው አስጊ ወደሆኑ ወደ ሶማሊዩ ላንድና ወደ ፑንት ላንድ ለመሰደድ መገደዳቸውን ገልጿል።
የጥቃቱ ሰላባ ከሆኑት መካከል በአማራ ክልል የኦሮሚያ ልዩ ዞን ነዋሪ የሆኑ የወሎ ኦሮሞዎች እንደሚገኙበት የጠቆመው የሰብዓዊ መብት ሊጉ፤ ከተቃሞው ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች “የኦሮሞ ነጻነት ግንባር አባል ናችሁ” ተብለው ያለፍርድ ቤት ማዘዣ መታሰራቸው እና ላለፉት ስምንት ወራት  ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ በወህኒ እየተሰቃዩ እንደሚገኙ አመልክቷል።
እስረኞቹ በአሁኑ ወቅት በደሴ ወህኒ ቤት እንደሚገኙ ያመለከተው የሰብዓዊ መብት ሊጉ፣ ሰብዓዊ መብታቸው እንዲጠበቅላቸውና በሚታሰሩበት ጊዜ የተወሰደባቸው የእጅ ስልካቸውና ገንዘባቸው እንዲመለስላቸው እና ያለምንም ቅድመ-ሁኔታ እንዲፈቱ  ፤ ለጋሸ ሀገሮች፣ ዓለማቀፍ የሰብዓዊ መብት ተቋማትና አክቲቪስቶች በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ጫና ያሳድሩ ዘንድ ተማጽኗል።

አንድነት ፓርቲን ለማፍረስ 2 ሚሊዮን መመደብ ለምን አስፈለገ! እንግዲህ እኔም ላጠፋሁት ጥፋት መላውን የአንድነት አባልና ደጋፊን እንዲሁም የኢትዮጽያን ህዝብ ከልቤ ይቅርታ እጠይቃለሁ! – ከመሳይ ተኩ

እንደምታውቁት እሁድ እለት መርህ ይከበር ከሚሉት የወያኔ አፍራሽ ቡድን እኔንም ጠርቶኝ ባለማወቄ በቦታው ተገኝቼ ነበር፤ እኔም በቦታው የተገኘሁት ሲጠሩኝ የሆነ የእርቅ ኮሚቴ አቋቁመናልና የቡድኑ የኮሚቴ አባል እንድትሆን ነው ብለውኝ ነበር። መቼም እርቅን የሚጠላ የለምና ደስብሎኝ ነበ፤ ነገሩ ግን የእርቅ ኮሚቴ ሳይሆን አንድነት ፓርቲን ለማፍረስ እንደሆነ ነው የገባኝ፤ ሰዎቹ እኛ የምንፍልገው ፓርቲው ፈርሶ ሌላ ፓርቲ ለማቁዋቁዋም ነው፤ ለዚህም አስፈላጊውን ውጭ የሚመድብልን ሰው አለ እሱም እንጂነር ዘለቀ ነው አለ በይፋ ይሄን ያለው ወዲ የማነ ነው በመቀጠል አንድነት አሁን ባለው አመራር አንድነትን በተመለከተ ምንም አይነት ስራ እንዳይስራ የሚል ፊርማ ማስፍረም ጀመሩ፤ ሁሉም ፈረመ፤ እኔንም ፈርም ሲሉኝ እኔ አልፈርምም የማልፈርመውም አንደኛ ፓርቲ የማፍረስ ተልእኮ የለኝም ፓርቲውንም እየመራ ያለው ህጋዊ ቡድን ነው፤ የመረጠውም ጠቅላላ ጉባኤ ነው፤ እናንተ የምትሉት አልገባኝ፤ ብዬ በዚሁ አቆምኩኝ የሚገርመው አንጃው ትእዛዝ የሚሰጠው ቀጥታ ከምርጫ ቦርድ ነው፤ እንደውም የማነ በመሀል ስልክ ሲደወልለት ከምርጫ ቦርድ ሰዎች ነው ብሎናል። እንግዲህ እነዚህ ሰዎች ከምርጫ ቦርድ ትእዛዝ እየተቀበሉ ነው ፓርቲውን ለማፍርስ የሚሯሯጡት፤ ይህ ቡድን ከመንግስት ጋርም በቅርበት እንደሚስራ አንድ አንድ አባላትም ነግረውናል። በሚገርም ሁኔታ እኛን መንግስት ይፍልገናል ለምን ከመንግስት ጋር አንሰራም? ሲል ዳንኤል ሙላት ብዙ ሰዎችን ጠይቆአል፤ ይህ ቡድን ነው እንግዲህ መርህ ይከበር! የሚለን ጎበዝ ይህ ፓርቲ እኮ ብዙ ህይወት የተከፈለለት ፓርቲ ነው፤ ብዙ ጀግኖች መሰዋትነትን እየከፈሉለት ያለ ፓርቲ ነ፤ እንዴትስ በመንደር ወሮበሎች ይፈርሳል? እኔ የሚገርመኝ ከወረዳ 6 ተመርጠው ለስላሳ ጠጥተው አንድነትን ለማፍረስ የመጡት አባል ያልሆኑት የሰፍር ወጥምሾች ነው፤ ያለ ጫት የማያውቁትን ሰዎች ይዞ መምጣት እራሱ ስብስቡ እራሱ የቦዘኔ ስብስብ መሆኑን በዚው ያስታውቃል።
የኢትዮጽያ ህዝብ አንድነትን ይጠብቃል!! የኢትዮጽይል ህዝብ ከአንድነት ትልቅ ተሰፋም አለው፤ ይህን የህዝብ ፓርቲ ነው እንግዲ የስፍር ዱርዬ ከወያኔ ጋር ከምርጫ ቦርድ ጋር ተባብረው ከጫወታ ውጭ ለማድርግ ተግተው እየሰሩ ያሉት አንዳንዱ ለምን አልተቀጠርኩም ነው አንጃ ያደረገው፤ አንዱ ደሞ ባጠፋው ጥፋት ለምን በዲሲፕሊን ኮሚቴ ተገመገምኩኝ ብሎ ነው ፓርቲውን ካላፈረስኩኝ የሚለው እንግዲህ እኔም ላጠፋሁት ጥፋት መላውን የአንድነት አባልና ደጋፊን እንዲሁም የኢትዮጽያን ህዝብ ከልቤ ይቅርታ እጠይቃለሁ!!
ድል ለኢትዮጺያ ህዝብ!
ሞት ለናት ጡት ነካሽ!!
ሞት ለመርጋ በቃናና ለግብረ አበሮቹ!!
አንድነት ህያው ነው!!
እናቸንፋለን!!10153833_587630041337455_4078181881316786241_n

ሕወሃት/ምርጫ ቦርድ በአንድነት ፓርቲ መደናገጡን እያሳየ ነው – ግርማ ካሳ

የሕወሃቱ ምርጫ ቦርድ፣ አንድነት ፓርቲ እንደገና ጠቅላላ ጉባኤ እንዲጠራ ማዘዙን የሚጠቁሙ ፍንጮች ደርሰዉኛል። የምርጫ ቦርድ ሃላፊ ባላበት፣ ጠቅላላ ጉባኤ ተጠርቶ፣ ምርጫ ቦርድ በወቅቱ እንዲሻሻል የጠየቀው ደንብ ተሻሽሎ የኮረም ቁጥር ማስገባቱ ማለት ነው) ፣ ብሄራዊ ምክር ቤቱ መርጦት የነበረዉን አዲስ አመራር እንደገና አጽድቆ ተለያይቶ ነበር። ሆኖም ምርጫ ቦርድ ፣ አይ ምርጫ እንደገና በሚስጠር መካሄድ አለበት በሚል አንድነት ሌላ ጠቅላላ ጉባኤ ካልጠራ የምርጫ ምልክት እንደማይሰጥ አሳውቋል። ኢንጂነር ግዛቸው በፍቃዳቸው ሲለቁ፣ በደንቡ መሰረት ብሄራዊ ምክር ቤቱ ሶስት ተወዳዳሪዎችን አሳልፎ ምርጫ አደረገ። አዲስ አመራር መጣ።
ምርጫ ቦርድ ለአዲሱ አመራር እውቅና ሰጥቶ ነገር ግን ደንብ ማሻሻል አለባችሁ በሚል ደብዳቤ ላከ (የጠቅላላ ጉባኤ ኮረም ቁጥር አስገቡ የሚል) ። ደንብ ለማሻሻል ጠቅላላ ጉባኤ መጠራት ስለላበት ጠቅላላ ጉባኤ ተጠራ። የደንብ መሻሽል ተደረገ። አዲሱን አመራርን ጠቅላላ ጉባኤው እንደገና ኣጸደቀ።
ሆኖም ምርጫ ቦርድ አሁንም እንደገና ጠቅላላ ጉባኤ እንዲጠራ አዘዘ። ከዚህ በፊት የገለጸዉን ቀልብሶ፣ አመራሩ በጠቅላላ ጉባኤ እንደገና በሚስጠር ድምጽ አሰጣጥ እንዲመረጥ የሚል።
ጠቅላላ ጉባኤ እንደገና ለመጥራት ትልቅ ወጭ አለው። ሆኖም ሰላማዊ ትግል ማለት አንዱን መሰናክል እያለፉ ወደፊት መሄድ በመሆኑ አንድነት እርግጠኛ ነኝ ምርጫ ቦርድ እንደገና የደቀነበት መሰናክል በቀላሉ አልፎ እንደሚሻገር። እንኳን ለሁለትኛ ጊዜ ጠቅላላ ጉባኤ ጥሩ ማለት፣ የአንድነት አመራሮችና አባላት ለመታሰር፣ ለመሞት የተዘጋጁ ናቸዉና።
ምርጫ ቦርድ ለይቶ አንድነት ላይ እንደዚህ መዝመቱ አሳዛኝ ቢሆንም እንደ አንድነት ደጋፊ የኮራሁበትም ነገር ነው። አንድነት ጥሩ ሥራ እየሰራ እንዳለ፣ በአገዛዞችም ላይ ፍርሃትን እና ድንጋጤን መፍጠሩን እንዳወቅ አድርጎኛል። ወደ ስድሳ ምናንም የሚሆኑ ኮልቶሌ ድርጅቶችን አንዲት ነገር ያላለ ምርጫ ቦርድ፣ ይሄን ያህል በአንድነት ፓርቲ ላይ ጡንቻውን ማንሳቱ፣ በርግጥ የኢትዮጵያ ህዝብን የሚመራ፣ ሊያታግል የሚችል ጠንካራ ድርጅት መኖሩን አመላካች ነው። በርግጥም የፊታችን 2007 ምርጫ አገዛዙን ማሸነፍ ብቻ ሳይሆን ህዝቡን አስተባበሮ ድምጹን እንዲያስከብር የማድረግ አቅም እንዳለም ተረድቻለሁ። ለዚህም ነው ህውሀአት ርጫ ቦርድ ተጠቅሞ ደባ እየፈጸመ ያለው። ሆኖም ይሄን የአገዛዙን ደባ ህዝቡ ያጠዋል ወይም ታጋዮች በዚህ ይወናበዳሉ ብዬ አላስብም።
አንድነት ወደ ምርጫ እገባለው ብሎ ሰፊ ንቅናቄ የማድረጉም አንዱ ሌላ ድልም፣ ይሄው የምርጫ ቦርድን የገጠጡ ጥርሶች እንዲታዩ ማድረጉ ነው። ይህ ምርጫ ቦርድ መመሪያ ከሕወሃት ማእከላዊ ኮሚቴ የሚቀበሉ መሆናቸዉን በግልጽ ለማየት ችለናል።
በመሆኑም ህዝቡ ይሄን አወቆ፣ ነጻነቱን እና መብቱን ለማስከበር መዘጋጀት አለበት። ነጻነት የሕወሃት ወይም የምርጫ ቦርድ ስጦታ አይደለም። ነጻነት ከእግዜር በነጻነት የተሰጠን ማንም ሊወስድብን የማይገባ የከበረ ነገር ነው። አንደናገጥ፣ ተስፋ አንቁረጥ። አንድ መሰናክል ሲስያስቀመጡ እያለፍን፣ ሌላ ሲያመጡ እያለፍን ፣ ነጻነታችንን እናወጃለን።10153833_587630041337455_4078181881316786241_n