Monday 14 March 2016

የፈጠራ ዉንጀላ ማካሄድና ሠላማዊ ዜጎችን ማፈንና መግደል ይቁም” – ከኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ የተሰጠ መግለጫ

ምንም እንኳን የአዲስ አበባ ማስተር ፕላንም ሆነ የኦሮሚያ ከተሞች አዲሱ አወቃቀር በገጠመዉ ሕዝባዊ ተቃዉሞ ምክንያት ሳይተገበር እንዲቆይ በኦህዴድ/ኢህአዴግ የተወሰነ ቢሆንም፤ ከዚህ ጋር ተያይዞ የተቀጣጠለዉ ሕዝባዊ ንቅናቄ የመጠንና የዓይነት ለዉጥ እያስከተለ ቀጥሏል፡፡ ገዥዉ ፓርቲም የችግሩ መንስኤ የኦሮሚያ ክልል አካሉ ኦህዴድ መሆኑን በሕዝብ ዜና ማሰራጫዎች ቢገልጽም፤ ነገር ግን ለጥፋቱ ይቅርታ እንደመጠየቅ ፋንታ ባለፉት አራት ወራት ዉስጥ ዉስጥ ብቻ ከ270 በላይ የኦሮሞ ዜጎች ተገድለዋል፤ የፓርቲያችን አባላትና ደጋፊዎችን ጨምሮ ንፁሐን ዜጎች ታስረዋል፤ ከመኖሪያ ቀዬያቸዉ እንዲሰደዱ ተደርገዋል፡፡ ይባስ ብሎም፣ ጅራፍ እራሱ ገርፎ ለራሱ ይጮሃል እንዲሉ መንግስት ሠላማዊ የመብት ጥያቄ በአቀረቡ ዜጎች ላይ ያላንዳች ርህራሄ የጭካኔ እርምጃ መዉሰዱን እንዲያቆም ደጋግመን በመጠየቃችንና የሕዝብን ሠላማዊ የመብት ጥያቄ ደግፈን በመቆማችን የአህአዴግ መንግስት ባለሥልጣናት ድርጅታችንና አባሎቻችንን መክሰስ ገፍተዉበታል፡፡
ኦፌኮ በሠላማዊ አግባብ ታግሎ ዲሞክራሲያዊ የሕዝብ መንግስትን ለመመስረት የሚታገል ፓርቲ እንጂ በሽብር ፈጠራ ሥልጣን ለመያዝ ዓላማና ዕቅድ የለዉም፡፡ ከዚህ መሠረታዊ ዓላማችን የተነሳም በአጠቃላይ በኢትዮጵያዊያን ዘንድ፣ በተለይ ደግሞ በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ ሰፊ ተቀባይነት በማግኘታችን ሁሉንም ዜጎች ፍትሐዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ የመንግስት ሥርአትን ዕዉን ለማድረግ የሄድንበት ርቀት የድሉ ጊዜ ሩቅ እንዳልሆነ አመላካች ነዉ፡፡ ዲሞክራሲያዊ የመንግስት አስተዳደር ዕዉን ከሆነ ደግሞ ሙሰኛነት፣ ኪራይ ሰብሳቢነት፣ የመልካም አስተዳደር ዕጦት እና ከሕገ መንግስታዊ አግባብ ዉጭ ሥልጣን መያዝ ብቻ ሳይሆን ከሕገ መንግስታዊ አግባብ ዉጭ ሥልጣን ላይ መቆየትም የማይታለም ይሆናል፡፡ በፖለቲካ ልዩነት የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትን መወንጀልም በበኢህአዴግ አገዛዝ ላይ ያበቃል፡፡
የኦሮሞ ሕዝብም ሆነ ሌሎች የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መብታቸዉን ለማስከበር የሚያደርጉትን መነሳሳት ከሕገ መንግስታዊ አግባብ ዉጭ ሥልጣን የያዙም ሆነ ሥልጣን ላይ የቆዩት ኃይሎች ግን፤ ኦፌኮን የመሳሰሉ ሐቀኛ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሕዝብን ዓላማ ደግፈዉ ሲሰለፉ የገዥዉ መንግስት አባላት የአሸባሪነት ታፔላ ይለጥፉባቸዋል፡፡ ከፖለቲካ ጨዋታ ዉጭም ለማድረግ የማይሰጡት መግለጫ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም፡፡
በኦሮሚያ ክልላዊ መስተዳድር ዉስጥም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች የሚነሳሱ የሕዝብ ጥያቄዎች ሠላማዊ በመሆናቸዉ መንግስት ሕጋዊና ተገቢ መልስ መስጠት ኃላፊነቱና ግዴታዉ እንደሆነ ኦፌኮ ዛሬም ያምናል፡፡ ሠላማዊ ሰልፍ በወጡና የመብት ጥያቄ በሚያቀርቡ ዜጎች ላይ የሚተኩስ መንግስት ለሕዝብ መብት መከበር ደንታ እንደሌለዉ ከዚህ የበለጠ ተጨማሪ ማስረጃ የማያስፈልግና ፓርቲያችንና አባላቱ የሕዝብን ጥያቄ ደግፈዉ የተሰለፉ እንጂ የአሸባሪነት ታፔላ ሊለጠፍባቸዉ እንደማይገባ ሚሊዮኖች የሚመሰክሩት ጉዳይ ነዉ፡፡ የሕዝብን ሠላማዊ ጥያቄ ደግፌንና ዜጎች መገደላቸዉ፣ መታሰራቸዉ፣ መሰደዳቸዉ፣ መቁሰላቸዉ፣ መደፈራቸዉ፣ መንገላታታቸዉ፣ ወዘተ እንደማይገባ መቃወማችን በምንም ዓይነት መስፈርት አሸባሪ የሚያስብል አይደለም፡፡
አሸባሪነት በፓርቲያችንም ላይ ሆነ በአባሎቻችንን ላይ መለጠፍን አጥብቀን እንቃወማለን፡፡ በሠላማዊ አግባብ ዲሞክራሲያዊ መንግስት እንዲቋቋም የመፈለጋችን ያህል የዜጎች ሕይወት በመንግስት ሠራዊት መቀጠፉን እናወግዛለን፡፡ በተለይ እስካሁን ከሁለት መቶ ሰባ በላይ ለተገደሉ ዜጎች የኢህአዴግ መንግስት ሙሉ ኃላፊነት መዉሰድ አለበት ብለን እናምናለን፡፡
ስለሆነም፤ የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ አባላትና ደጋፊዎች ሕዝባዊ ዓላማን አንግቤን የሕዝባችንን ሠላማዊ ጥያቄ እየደገፍን፤ አንደኛ ሠላማዊ የመብት ጥያቄ ባቀረቡ ሕዝቦች፣ ሴቶች፣ ወጣቶች፣ ሕፃናትና አዛዉንቶች ላይ በጦር መሳሪያ የታገዘ እርምጃ መዉሰድን እናወግዛለን፡፡ ሁለተኛ በኢህአዴግ ባለሥልጣናት ክስ ሳንሸማቀቅ ትግላችንን እንደምንቀጥል ቃል እንገባለን፡፡ በዚህ አጋጣሚ ለምናራምደዉ የተቀደሰ ዓላማ መላዉ የኢትዮጵያ ሕዝቦችና ዓለም አቀፍ ሕብረተሰብ ከጎናችን እንዲቆሙ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡
ለኦሮሞ ሕዝብ የመብት ትግል መልሱ የጠመንጃ አፌሙዝ መሆን የለበትም!
የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ
መጋቢት 2 ቀን 2008
ፊንፊኔ

ነገሮች አዲስ የሚሆኑት፣ በእኛ ትናንትን መርሳት ነው (ይገረም አለሙ)

ይገረም አለሙ
ሰሞኑን  በደቡብ ኢትዮጵያ በሚኖሩ ዜጎች ላይ የተፈጸመን የባሪያ ፍንገላን ዘመን የሚያስታውስ  ኢሰብአዊ ድርጊት  የሚያሳይ ፎቶ  በማህበራዊ ድረ-ገጽ ተሰራጭቶ አጀኢብ ጉድ ብለናል፡፡ ነገሩ ትናንትን እየረሳን ዛሬ ለሚያጋጥመን ነገር አዲስ እየሆንን ጉድ ጉድ ለምንለው  ለእኛ ነው እንጂ አዲስነቱ ለወያኔ ከበርሀ ጀምሮ አብሮት የኖረ ተግባሩ ነው፡፡ This is 2016 Ethiopia where the government chains and forcefully removes indigenous peoples
አይደለም ሥልጣኑን ሊነጥቁት በተቃውሞ የተሰለፉ፣  እኩይ ድርጊቱን እያጋለጡ ማንነቱን ጸሀይ የሚያሞቁ ፣ ሀሳብ እቅዱን እየተቃወሙ ጉዞውን የሚያደናቅፉ ቀርቶ የህውሀት አባል ሆነው ስህተት የጠቆሙ የዓላማቸውን መስመር መሳት የገለጹ የመሪዎቹን እኩይ ተግባር የነቀፉ ወዘተ ምን እንደተፈጸመባቸው የአይን ምስክር የሆኑ ሰዎች ሲናገሩ ሰምተናል ጽፈው አንብበናል፡፡ ባዶ ምንትስ ይባሉ በነበሩት እስር ቤቶች በውልደታቸው ትግሬ በድርጅታቸው ህውኃት የነበሩ ዜጎች ሳይቀሩ ምን አይነት ኢሰብአዊ ድርጊት አንደተፈጸመባቸው እነ ገብረ መድህን አርአያ ደጋግመው የነገሩን ነው፡፡ ዛሬም በተለያየ የሥልጣን ስም ተቀምጠው አረመኔያዊውን ድርጊት የሚፈጽሙ የሚያስፈጽሙት እነዛ የበርሀው ሲኦል እስር ቤቶች ሀላፊዎች የነበሩቱ ናቸው፡፡
ለሥልጣናቸው የሚያሰጋ፣ ያሰቡ ያቀዱትን ተፈጻሚ እንዳያደርጉ አንቅፋት የሚሆን፣ ማንም ሆነ ከየትም  ከማጥፋት የማይመለሱት ወያኔዎች (በተለይም አቶ መለስ) ዘር ሀይማኖት ሳይለዩ አስሮ ማሰቃየቱን አፍኖ መሰወሩን ገድሎ መጣሉን ብሎም ርስ በርስ ማገዳደሉን አብይ ተግባራቸው አድርገው የኖሩ ለመሆናቸው  ብዙ እጅግ ብዙ ማረጃዎችን መዘርዘር ይቻላል፡፡
የህውኃት ቀኝ እጅ የነበረው የደህንነቱ ሹም ክንፈየአግልግሎት ግዜው ሲያበቃ እንዴት እንዳስገደሉትና የግድያ ትዕዛዙን በፈጸመው የዋህ ታዛዥ ላይ ያደረጉትን የምናውቅ  በሌላው ኢትዮጵያዊ ላይ የሚፈጽሙት አረመኔያዊ ተግባር ለምን አዲስ አንደሚሆንብንና እንደሚገርመን  ራሱ የሚገርም ነው፡፡ ለህይወታቸው መድህን ለሥልጣናቸው ዘብ ሆነው የኖሩ ሰዎቻቸውን ለማጥፋት የማይመለሱ ሰዎች አንገዛም ባሉ ኢትዮጵያውያን ላይ የሚፈጽሙት ኢሰብአዊ ድርጊት ሁሌም አዲስ የሚሆንብን እኛ ትናንትን በመርሳት በሽታ በመለከፋችን  አለያም ሞኝ የሰማ/ያየ እለት እንደሚባለው እየሆነብን እንጂ ድርጊቱ ለወያኔ አዲሰ  አይደለም፡፡ እንደውም  ትናትን የመርሳት ችግራችን ከእባብ አንቁላል ርግብ አይጠበቅም የሚለውን አባባል  አስረስቶን የተቃውሞአችን እንዴትነትና  የጩኸታችን ምንነት  ከወያኔ የባህሪው ያልሆነ ነገር የምንጠብቅ ያስመስለናል፡፡
መቅረጸ ድምጽም ሆነ ምስል ያልደረሰባቸው የአይን ምስክርም ተገኝቶ ይፋ ያላደረጋቸው ብዙ አጅግ ብዙ ዘግናኝ አረመኔያዊ ድርጊቶች በወያኔ ለመፈጸማቸው በመረጃ ከተረጋገጡት ድርጊቶቹ ተነስቶ መገመት ይቻላል፡፡እነዚህ ሰዎች ለሥልጣን የበቁት የመረጃ ማስተላለፊያው ጥበብ እንዲህ ባለልተስፋፋበትና ባልተራቀቀበት ዘመን ቢሆን ምን ያደርጉ ነበር ብላችሁ አስባችሁ ታውቃላችሁ፡፡የሚሰሩት ብቻ ሳይሆን በር ዘግተው በምስጢር የሚነጋገሩት ድምጽ ከምስል እየሾለከ ለአለም ህዝብ አይንና ጆሮ ሲበቃ የማያስደነግጣቸው፣ የማያሳፍራቸውና የማያስፈራቸው (ለነገሩ ማን ሰው ብለው) ወያኔዎች በድብቅ የሚሰሩት ሁሉ ተደብቆ የሚቀር ቢሆን የአረመኔነታቸው መጠን የክፋታቸው ደረጃ  የአገዛዛቸው ግዞት እስከምን ይደርስ አንደነበር መገመት አይገድም፡፡
ጎምቱ ጋዜጠኞች ውሻ ሰው ነከሰ ዜና አይሆንም ሰው ውሻ ቢነክስ ግን ትልቅ ዜና ነው ይላሉ፡፡ የአባባሉ ምንነት ግልጽ ነው፡፡ ውሻ ሰው መንከሱ የተፈጥሮው፣ የባህሪው፣ የሚጠበቅበት ተግባሩም ስለሆነ  ነው ዜና የማይሆነው፡፡ ሰው ግን ውሻ ቢነክስ  ያልተለመደ ብቻ ሳይሆን የማይጠበቅና የማይገመት አዲስ አስገራሚ ክስተት  በመሆኑ ነው ትልቅ ዜና የሚሆነው፡፡
ወያኔም ማሰሩ፣ መግደሉ፣ ማሰቃየቱ፣ መዋሸቱ ፣ማታለሉ ሰው በሀሰት መወንጀሉ ወዘተ  ለሥልጣን የበቃበትና ሀያ አራት ዓመታትም ለመግዛት የቻለበት የተፈጥሮ ባህሪይው እና ተግባሩ  በመሆኑ በዚህ መልክ የሚፈጽማቸው ድርጊቶች ለጋዜጠኞች ዜና ሊሆኑ ቢችሉ አንኳን ለእኛ ለኢትዮጵያውያን  አዲስ ክስተት የሆኑ ያህል ሊያስገርሙን ሊያስደንቁንም ሆነ ሊያስደደነግጡን  አይገባም ነበር፡፡ ምነው ቢሉ እየረሳናቸው ካልሆነ በቀር አብረውን ያሉ ናቸውና፡፡
ይልቁንስ ከወያኔ አንጻር ለመገናኝ ብዙኃን ትልቅ ዜና ሊሆን ከኢትዮጵያውያን አልፎ የኢትዮጵያን ጉዳይ (ለራሳቸውም ዓላማም ሆነ ለህዝቡ ጥቅም ሲሉ) በቅርብ ለሚከታተሉ አለም አቀፍ ግለሰቦች ቡድኖችና መንግሥትታ አስገራሚ ክስተት ሊሆን የሚችለው፡፡
  • ሀያ አራት አመት የተጓዝንበት መንገድ ወደ ትክክለኛው አቅጣጫ እየወሰደን እንዳልሆነ ስለተገነዘብን  መሰረታዊ ለውጥ ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ አግኝተነዋል ቢባል፤
  • ለዘመናት አብረውን የዘለቁ ሀገራዊ ችግሮችን እየቆፈሩ  አዳዲስ ልዩነቶችን መፍጠር የዛሬ መንገዳችንንም ሆነ  የነገ ግባችንን ከማሰናከሉም በላይ ኢትዮጵያን አንደ ሀገር ለማቆየት አስጋቸሪ የሚያደርጉ በመሆናቸው በእርቅ እልባት ሰጥቶ ሀገራዊ መግባባት መፍጠር አስፈላጊ መሆኑን ተገንዝበናል ቢባል፤
  • የገደለ ያስገደለ፣ የሰረቀ የተባበረ፣ በህዝብ ሀብት የከበረ፣ ከህግ በላይ ያደረ፣ወዘተ ለፍትህ ቀርቦ የህግ የበላይነትን በተግባር ለማረጋገጥ የሚያስችሉ  ርምጃዎች መታየት ቢጀመሩ፣
  • የመገናኛ ብዙሀን ሰራተኞች አፋሽ አጎንባሽ መሆናቸው ቀርቶ እውነትን አነፍናፊ፣ የባለሥልጣናትን ፊት እያዩና ትንፋሽ እያዳመጡ የሚሰሩ ሳይሆን የሙያቸውን ነጻነት አክብረው ለህሊናቸው ታማኝ ሆነው መስራት የሚችሉበትን አሰራር ተግባራዊ  የማድረግ ጅምር ቢታይ፤
  • ክልሎች በህገ መንግሥቱ የሰፈረው ሙሉ ነጻነታቸው ተጠብቆ ከህውኃት የሞግዚት አስተዳደር ተላቀው ራስን በራስ የማስተዳደር መብታቸውን በተግባር የሚያረጋግጥ ጅማሮ ቢታይ ፤
  • አባልም ሆነ አጋር የሚባሉት በህውኃት ተፈጥረው በህውኃት የሚዘወሩት ድርጅቶች የአገልጋይነት ዘመናቸውን ፈጽመዋል ተብሎ  በራሳቸው መቆም የሚያስችላቸው እንቅስቃሴ ቢጀመር፡፡
  • በድርጅት ታጥሮ በታማኝነት ተወስኖ ሀገር መምራት አንዳማይቻል የሀያ አራት አመት ልምዳችን አስተምሮናል፣ ስለሆነም ከዚህ በኋላ ሀገር መምራት በእውቀትና ሁሉን አሳታፊ በማድረግ  መሆን እንለበት ተገንዝበናል  ተብሎ ይህንኑ ገቢራዊ ማድረግ የሚያስችል ተግባራዊ ርምጃ  ቢታይ፡፡ ሌላም ሌላም ተመሳሳይ ነገር ከወያኔ ሰፈር ቢታይ ቢሰማ ትልቅ አስገራሚና ማራኪ ድንቅ ዜና ይሆናል፡፡ከዚህ ውጪ መልካም አስተዳደር የፍትህ መጓደል እያሉ ማላዘንም ሆነ  ይቅርታ እንጠይቃለን ማለት ሸብረክ ያሉ መስሎ ግዜ መግዣ የወያኔ የባህሪው  ተግባር ነውና ሊደንቀን አይገባም፡፡
ነገር ግን ወያኔ ያልፈጠረበትን በምክርም በመከራም ሊቀበለው ያልቻለውን ይህን ቅዱስ ተግባር በምን ተአምር ፈጽሞት ይህ  እውነት ሆኖ ለመስማት እንበቃለን! አይታሰብም፡፡ ወያኔዎች ይህን ለማድረግ አንደገና መፈጠር ይኖርባቸዋል፡፡ እኛስ ትናንትን እየረሳን በየግዜው የሚገጥሙንን የወያኔን የባህርይ ድርጊቶች  እንደ አዲስ  ከማየት ለመላቀቅ እና ትግሉን በምሬትና በወኔ ለማጥበቅ  እንደገና መፈጠር ይጠይቀን ይሆን?
ትናትን እየረሱ የእለት የእለቱን አዲስ እያደረጉ መጮኹ በትግሉ ላይ ትልቅ አሉታዊ ተጽእኖ ያለው ለመሆኑ አጠያያቂ አይደለም፡፡ የበደል ሸክሙ የሚከብደን፣ የጥቃቱ ምሬት የሚመረን፣አንባገነናዊ አገዛዙ የሚያንገሸግሸን ከ እስከ አሁን ያለውን ስናስታውስ ነው፡፡ የዛሬው ሲያስለቅሰን ሲያስቆጣን ብቻ ሳይሆን የትናቱም ሲቆጠቆጠን ነው፡፡  የትናንቱን እየረሳን ለዛሬው አንድ ሳምንት እየጮኸን ከዛም ሌላ አዲስ ነገር እስኪመጣ ይህን እየረሳን  እኩል መብሰል ባለመቻላችን (ጥሬ  ብስልና የአረረ) ነው ሀያ አራት አመት ሙሉ ትግል እንጂ ለውጥ ማስመዝገብ ቀርቶ አዳዲስ ጥቃቶችን ማስቀረት፤ ተጨማሪ ጥፋት እንዳይፈጸም ማስቆም ወያኔን ከደደቢት ህልሙ ስንዝር መግታት  ያልቻልነው፡፡  እውቁ የጽሁፍ ሰው አቶ ከበደ ሚካኤል ልጆች ሆነን ባነበብነው አንድ ጽሁፋቸው ፤
ያለፈው ሲረሳኝ መጪውን ሳላውቀው
እኔ መቼ ይሆን የምጠነቀቀው፤  ብለው የነበረው  ከላይ ለተገለጸው  ለእኛ እኛነት  በቂ ገላጭ አይሆንም ትላላችሁ?

ይድረስ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ጉልበት ላላችሁ ሁሉ (ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም)

ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም
ልጆች ሆነን ታላላቆቻችን ጉልበት አለን ብለው በደል ሲፈጽሙ ‹እግዚአብሔር በቀዳዳ ይየው!› እንል ነበር፤ ለመርገምም እየፈራን አንዲያው ድርጊቱ እንዲመዘገብልን ማሳሰባችን ይመስለኛል፤ አሁንም እንደዚያ ለማለት ይቃጣኛል፤ ግን አግዚአብሔር በሰማይ ላይ መኖሩን፣ በእያንዳንዳችን ውስጥ መኖሩን የቤተ ሃይማኖት ሰዎች እንኳን ማመናቸው በሚያጠራጥርበት ዘመን ለዓለማዊ ባለሥልጣኖች የእግዚአብሔርን ስም ማንሣት ፋይዳ ይኖረዋል ብዬ አልገምትም፤ ሆኖም እኔ ስለማምንበት የራሴን አሳውቃለሁ፤ ኢትዮጵያ የእግዚአብሔር አገር ነች፤ ኢትዮጵያን ጎድቶ የተጎዳ እንጂ የተጠቀመ የለም፤ ኢትዮጵያን አዳክሞ የደከመ እንጂ የበረታ የለም፤ ኢትዮጵያን አደህይቶ የደኸየ እንጂ የበለጸገ የለም፤ ኢትዮጵያን አዋርዶ የተዋረደ እንጂ የተከበረ የለም፤ ይህ የታሪክ ሐቅ ነው፡፡Prof. Mesfin Woldemariam
የኢትዮጵ ባለሥልጣኖች ዓላማችሁ ምንድን ነው? እስከዛሬ ድረስ በየትም አገር በሰማይ ጠቀስ መቃብር ውስጥ የተጋደመ ባለሥልጣን የለም፤ ደግሞስ ሰማይ ጠቀስ መቃብር ካስፈለገ ለአንድ ባለሥልጣን ከነቤተሰቡ ስንት ሰማይ ጠቀስ ፎቆች፣ ስንት ሺህ ካሬ ሜትር መሬት ያስፈልጉታል? ከዚህ በፊት ምጽዓት በሚል ግጥም የሚከተለውን አመልክቼ ነበር፡፡
ከራስ በላይ ነፋስ ትልቁ ሃይማኖት፤
ዘረፋን ሲያውጀው ቂም ሲያስረግዝ ጥቃት፤
ዓይን አያይም አሉ፤ ጆሮም አያዳምጥ፤
ተለጉሞ አንደበት ሁሉም ይዞታል ምጥ!
በቁንጣን፣ በስካር ጥቂቶች ሲንሩ፣
ብዙዎቹ ደግሞ በረሀብ መንምነው በቁንጫ ሲያርሩ፣
የደሀ እንባ ሲጎርፍ መሬቱ ሲሸበር፣
ዝብርቅርቁ ወጣ፤
ሕይወት ትርጉም አጣ፤
ኧረ የት ነው ጉዞው ዓላማው ምንድን ነው?
ቀድመው የሄዱትን ምነው አናያቸው?
የት ገቡ? የት ጠፉ? ፋና እንኳን አይታይ፤
ብልጭ የሚል የለ ከመሬት ከሰማይ!
መንገዱ ጠበበ፤ ትርምስምሱ በዛ፤
እሪታው ኡኡታው ቀለጠ እንደዋዛ!
መሬቱም ዓየሩም በክፋት ጠነዛ!
ጥላቻና ቂሙ በሰፊው ተነዛ፡፡
እምቢልታው ሲጣራ ነጋሪት ሲያገሳ፣
የአለው ሁሉ ሞቶ የሞተው ሲነሣ፣
ምጽዓት መድረሱ ነው ሊስተካከል ነው ፍርድ፤
በግና ፍየሉ ሊለዩ በገሃድ!
እንደሚመስለኝ በአሁኑ ጊዜ ይህንን አቅጣጫ ማየት የሚያዳግተው ሰው በራሱ ላይ ብቻ ሳይሆን፣ በቤተሰቡና በአገሩ ሕዝብ ላይ መቅሠፍትን የሚጠራ ነው፤ እየተማረርን ነው፤ የርኅራኄ ወዛችን እየደረቀብን ነው፤ መጨካከን እንደጀግንነት እየተቆጠረ ነው፡፡
በሌላ ሞት ማለት በሚል ግጥም፡–
ሞት ማለት፡-
አለመናገር ነው፤ ጭው ያለ ዝምታ፣
የመቃብር ሰላም የሬሳ ጸጥታ፤
ደሀ በሰሌኑ ሣጥን ገብቶ ጌታ፤
የውሸት ልዩነት ተጋድሞ በተርታ!
እኔ እንደምገምተው ጉልበተኞች የሆናችሁ ሁሉ ዓላማችሁ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ዓላማ የተለየና በቅራኔ ላይ ያለ አይመስለኝም፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ብልጽግና፣ እድገትና ክብር የናንተም ነው፤ በየትም አገር ስትሄዱ የሚነጠፍላችሁና የሚጨበጨብላችሁ የኢትዮጵያን ሕዝብ በመወከላችሁ ነው፤ ዛሬ በአውሮፓና በአሜሪካ የኢትዮጵያ ሕዝብ ያለው ክብርና በአጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመን የኢትዮጵያ ሕዝብ የነበረው ክብር በጣም የተለየ ነው፤ አጼ ኃይለ ሥላሴ ያገኙትን ክብር ከሳቸው በኋላ የመጡት አላገኙትም፤ ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያን ሕዝብ አዋርዶ ከየትም ክብርን ማግኘት አይቻልም፤ የራስን ሕዝብ ንቆ መከበር አይቻልም፤ የራስን ሕዝብ አንገቱን አስደፍቶ ቀና ብሎ መሄድ አይቻልም፡፡
እስር ቤቶችን ሁሉ ዝጉ፤ የዘጋችሁትን አንደበት ሁሉ ልቀቁ፤ ያፈናችሁትን አእምሮ ሁሉ ለነጻነት አብቁት፤ ጭካኔን በርኅራኄ፣ ጉልበትን በእውቀት፣ ዱላን በክርክር፣ ቁጣን በፍትሐዊነት እየለወጣችሁና እያበረዳችሁ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ታረቁ፤ በተለይ ከኢትዮጵያ ወጣት ጋር ልብ ለልብ ተገናኙ፤ ነገ የወጣቱ ነው፡፡
አይተናል፤ አንበሶች ነን የሚሉ ቀሚስ ለብሰው ሲሸሹ! አይተናል፤ አለኛ ማን? እያሉ ሲወጠሩ የነበሩ እንዳይጥ በጓሮ ተደብቀው የሙጢኝ ሲሉ! አይተናል፤ ጀግኖች ነን ብለው ሲያቅራሩ የነበሩ በየፈረንጅ አገሩ አንገታቸውን አቀርቅረው ትሕትና ሲማሩ! አይተናል፤ የዘረፉትን ሁሉ ሳይበሉ፣ ሳያጌጡበት ሲቸገሩ! አይተናል! ሰምተናል አይደለም አይተናል!
ሌላ ዙር ግፍ ቂምን እየወለደ፣ ቂም በቀልን እየወለደ፣ በቀል አዲስ ግፍን የሚወልድበት ሁኔታ ሲፈጠር ለማየት አንፈልግም፤ በቃን ግፍ! በቃን ቂምና በቀል! በቃን እየተዋረደ የሚያዋርደንን ማየት! በቃን መንፈሳዊ ወኔ በሌላቸው ጉልበተኞች መነዳት! በቃን ጠመንጃቸውን ሲነጠቁ አይጥ የሚሆኑ አሻንጉሊቶች! በቃን በደሀ ጉልበት ጉልበተኞች፣ በደሀ ሀብት ሀብታሞች መስለው የሚታዩ ኅሊና-ቢሶችን መሸከም! እስቲ እኛ ደካማዎቹ ሰዎች እንሁን! አስቲ እናንተም ጉልበተኞች ሰዎች ሁኑልን! እንደሰዎች በሰላም እንድንነጋገር ድፍረቱን፣ መንፈሳዊ ወኔውን ከቅን መንፈስ ጋር እንዲሰጠን እግዚአብሔርን እንለምነው! ክፋትን እንሻረው! ነቢዩ ኢሳይያስ እንዳለው ‹‹ለክፉዎች ሰላም የላቸውም፤ ይላል እግዚአብሔር፤›› እንዳይሆንብን!

ዜና መረጃ — ህወሃት አሉኝ የሚላቸዉ ጄኔራሎቹን አጣጣለ

በልኡል አለም
በ11/03/2016 በመከላከያ ሚኒስቴር ቅጥር ግቢ ዉስጥ በተደረገ ድንገተኛ ስብሰባ ላይ የተገኙ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ጄኔራሎች እራሳቸዉን ከኤርትራ ጄኔራሎች ብቃት ጋር በማወዳደር መናቆራቸዉን ምንጮች እየገለጹ ይገኛሉ።general samora yenus
በሚኒስቴር ጀኔራል ሲራጅ ፈጀታ የዉስጥ ደንብና ምክክር የተጠራዉ ይህ ድንገተኛ ስብሰባ አሉ የሚባሉ የወያኔ ጄኔራሎችን ያካተተ ሲሆን የምክክር መድረኩ ባስገራሚ መልኩ ይዘቱን ቀይሯል። ይህዉም የኤርትራ ጄኔራሎችን ብቃት በተመለከተ ጠቅለል ያለ መረጃ ያቀረቡት ጠ/ሚኒስቴር ጄኔራል ሲራጅ ፈጀታ ለሻቢያ ስራዊት የመጀመሪያዉን ጥይት ከተኮሱ ከነ ሃሚድ ኢድሪስ አዉት ጀምሮ እስከ አሁኑ የጸጥታ ሐላፊ የበላይ ጠባቂ ከሜጄር ጄኔራል ፊሊፖስ ወልደዮሓንስ እንዲሁም እስከ እታች ለመዉረድ የሞከረ ሲሆን በንግግሩ መደምደሚያ ላይ ኤርትራን ለመዉጋት ብንነሳ እነዚህ የሻቢያ መኮንኖች ምን ያህል ይከላከላሉ የሚል እሳቤ ነበርዉ።
ከዚህ ወዲህ የቀረቡት አስተያየቶች እጅግ አስደንጋጭ የንበሩ ሲሆን… በሰሜኑ እዝ የጠ/ላይ መምሪያ አዛዥ እንዳስቀመጡት
“እስካሁን የተጠቀሱት የሻቢያ ጄኔራሎች በዉጊያዉ ላይ ጉልህ አስተዋጾ አያደርጉም ባይባልም ጠላት ግን አይናቅም ! ! በመሆኑም ዋነኞቹ እና ቀንደኞቹ ግን አልተጠቀሱም ለምሳሌ በባድሜ ጦርነት ወቅት የአሰብን እራስ ገዝ ሲጠብቅና ሲያጠቃ የነበረዉ በቡሬ ግንባር መሬት ወርዶ ሲያርመሰምሰን የኖረዉ ግንባር 71 የሚባለዉን የኢትዮ-ኤርትራን ድንበር ቆርሶ አስገራሚዉን ምሽግ የገነባዉ በ70ዎቹ የእድሜ ክልል ዉስጥ የሚገኘዉ ሜጀር ጄኔራል ዳንኤል አብረሃ በምን መልኩ ነዉ የታየዉ!!! የኛ ጄኔራሎች በተንጣለለ መኖሪያ ቤት ዉስጥ በከተማ ይኖራሉ የኤርትራ ሰራዊት ጄነራሎች አስቸጋሪዉን የሬንጀር ኮርስ የበረሃ ጉዞ 50 ኪ/ሜ ከወታደሮቻቸዉ ጋር ያሳልፋሉ መመሪያ ይሰጣሉ በኮምፒተር ከመታገዝ አልፈዉ መሬት እየሰነጠቁ የጦር ምህንድስናዉን ይጠልፋሉ! የትኛዉ የኛ ሰራዊት አዛዥ ነዉ ኤርትራን ለመዉጋት የሚዘልቀዉን ጦራችንን ከጎኑ ሆኖ አይዞህ የሚለዉ ሳሞራ የኑስ ነዉ! ወይስ እርሶ ክቡር ሚኒስቴር አቶ ሲራጅ!”
በማለት ያንጓጠጠ ሲሆን ከእርሱ በመቀጠል ተቀማጭነቱ አዲስ አበባ ቤተ መንግስት የሆነ የቤተ መንግስቱ የክፍለ ጦር መምሪያና የብርጌድ ሃላፊ በበኩሉ፣
“እኔም በዚህ ሐሳብ እስማማለዉ በተለይም ወታደራዊ ፖለቲካ ሳይንስ አወራረዳችን ዜሮ በመቶ ነዉ ቢባል አያሳፍርም ለምሳሌ የኤርትራዉን ወታደራዊ ፖለቲካ ብንመለከት ጄኔራል ስብሓት ኤፍሬምን መዉሰድ በቂ ነዉ እርሱ የረገጠበት ቦታ ላይ እኛ ምን ያህል ዘልቀን ገብተናል በእርሱ አንጻር የሚገኙ የእኛ ጀኔራሎች የፖለቲካዉ አመራሮች እነማን ናቸዉ! ዉጊያ ተጀመር ይባል ከጀመርን ደግሞ እንድንገባ የተነደፈዉ በአሰብ በኩል ያለዉ አንዱ መንገድ ነዉ! ከዚያ ዉጪ በአማሐጅር ጀርባ አድርገን በባረንቱ ቆርጠን እስከ ተሰኔ ሊሆን ይችላል ነዉ የሚባለዉ!! ሁለቱም መንገድ ያዋጣናል የሚል እምነት የለኝም ” በማለት አስተያየታቸዉን ከሰጡ ወዲያ ሌላኛዉ ተናጋሪ በተመሳሳይ መልኩ፣
“በአሰብ በኩል ሻቢያን ለመዉጋት የታሰበዉ እቅድ ዋና ፍሬ ነገሩ ተቃዋሚዎቻችን ናቸዉ ዛሬ እነርሱ እኛ ከመጣንበት አይነት ስፍራ በረሃዉን ተሸክመዉ ይገኛሉ ከዚህ ቀደም ባደረግነዉ ዉጊያ በአሰብ በኩል ግንባር 71 ላይ የሰፈርዉን የሻቢያ ሰራዊት ምሽግ ለመምታት የአየር ሐይላችን ያደረገው ሙከራ ትዝብት ዉስጥ ጥሎናል እንኳን ያንን ምሽግ መምታቱ ይቅርና ሶጃ የተባለ የመንገድ ስራ ድርጅት የሰራዉን በኢትዮ-ኤርትራ መንገድ ላይ የተገነቡ ድልድዮችን ማፍረስ እንክዋን ተስኖን ነበር። ዛሬ አሰብ በነ ሳኡዲ አረቢያ መዳፍ ዉስጥ ነች ወደ አሰብ የምናደርገዉ ግስጋሴ ከጅምሩ አደጋ ይገጥመዋል ከሳዉዲ አሰብ የሚወረወሩት አሜሪካን ሰራሽ የጦር መርከቦች ከበዛ 60 ደቂቃ ካነሰ 42 ደቂቃ ዉስጥ አሰብ ይደርሳሉ የጦር ጀቶቹ ከ15 እስከ 20 ደቂቃ አሰብን ይጎበኛሉ ወደድንም ጠላንም በአሰብ በኩል ያሉትን እነ አርበኞች ግንቦት 7ን ለማጥቃት ስንነሳ በአሰብ ወደብ ላይ የሚገኙት የጸረ ሽብር ጥምር ሐይሎች ከሸባሪዎቹ እንደ አንዱ ነዉ የሚቆጥሩን! በተለይም አሁን ባሉን ጄነራሎች የመዋጋት ብቃት የለንም!”
በማለት እጅግ አንገት የሚያስደፋ ትችቶችን በማቅረብ ስብሰባዉ በከንቱ በኤርትራ ጄኔራሎች ብቃት የበላይነት የተካሄደ እና ለ3 ሰአታት የዘለቀ ሲሆን በመጨረሻም ዉጊያዉ የማይቀር ነገር ግን አለም አቀፍ ትኩረትን ወደኛ እንዲያዘነብል በማድረግ በኩል ስራ እንዲሰራ ተወስኖ አስቸኳይ እርምጃ እንዲወሰድ መመሪያ ተላልፏል።