Tuesday, 29 March 2016

የሄነከን ቢራ ዘረፋ ምስጢር በኢትዮጵያ ሲጋለጥ (ክንፉ አሰፋ)

ክንፉ አሰፋ
የሆላንድ ዜምብላ[1] ጋዜጠኞች የኦሮሞ ጸሃፊው የሆነውን ያሶ ካባባን ይዘው ወደ ጊንጪ ያመራሉ። እግረመንገድ ላይ  የሚያገኟቸው ገበሬዎችም ሲጠይቋቸው በምስሉ ይታያል።  እነዚያ በቀያቸው ማረፍያ እንኳን የሌላቸው ገበሬዎች የጋዜጠኞቹን መኪና ከብበው እንዲህ ሲሉ ይደመጣሉ።  “መሬታችንን ቀምተው ለነጮች ሰጡብን። እኛንም በታተኑን…”Heineken Ethiopia
በገዛ ቀያቸው ስደተኛ የሆኑ እነዚህ ወገኖቻቸን ሰቆቃቸው የከፋ ነበር። በመጨረሻ ተሰባሰቡና መከሩ።  ሰባት ሺህ የሚሆኑ የጊንጪ ተወላጆች ሆ! ብለው ወጥተው ይህንን የሁለት ሚሊዮን ዩሮ (ሃምሳ ሚልዮን ብር) ንብረት በሰኮንዶች ውስጥ አወደሙት። ምስላቸውን ለካሜራ ሳይደብቁ፣ ስሜታቸውን እና የወደፊት እቅዳቸውን ይናገራሉ። “ከአንባገነን መንግስት ጋር አብሮ ከመስራት ይልቅ የአካባቢው ነዋሪዎች ሊጠቀሙ በሚችሉበት መንገድ መስራት እንደሚችሉም።” ለፈረንጆቹ ይመክራሉ። “ይህ ካልሆነ ግን ማውደሙን እንቀጥልበታለን!” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።  ይህ ማስጠንቀቅያ  ግዙፉ አለም አቀፍ ኩባንያ የሆነው ሄነከን ቢራንም ይመለከታል።
ባለፈው ሳምንት በሆላንድ ብሄራዊ ቴለቭዥን የተላለፈው ዜምብላ ፕሮግራም የሚሊዮኖችን ቀልብ ስቧል። ለዚህም ምክንያቶች አሉት። አንደኛው ምክንያት፤ የዜምብላ ፕሮግራም በምርመራ ጋዜጠኞች የሚሰራ በመሆኑ እጅግ የሚፈራ እና በሃገሪቱ ፖለቲካ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ማሳደሩ ሲሆን፣ በሁለተኛ ደረጃ በኢትዮጵያ እየወደመ ያለው ይህ ንብረት የተቋቋመው በሆላንድ መንግስት ድጎማ ሲሆን፣  ይህ ደግሞ የእያንዳንዱ ሆላንዳዊ ግብር ከፋይ ገንዘብ በመሆኑ ነው።
የሆላንድ የልማትና ትብብር ሚንስተር ለድሃ ሀገሮች እርዳታ ከመለገስ ይልቅ ወደ ንግድ ድጎማ ፊቱን ባዞረ ግዜ፣ 130 አትራፊ የንግድ ድርጅቶች ድጎማ እየተቀበሉ ወደ ኢትዮጵያ ገብተዋል።  ከነዚህ ውስጥ ትልቁን የድጎማ ድርሻ የወሰደው ሄነከን ቢራ ነው። ሄነከን ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ  የሆላንድ መንግስት አንድ ቢሊየን ዩሮ ድጎማ አድርጓል። እንደ ሆላንድ መንግስት እሳቤ፣  ይህንን የልማት ትብብር ገንዘብ በእርዳታ መልክ ከመስጠት ይልቅ ይህንን አትራፊ ተቋም አበራትቶ ስራ በመፍጠር እና በንግድና በስራ ታክስ ሃገሪቱ ተጠቃሚ እንድትሆን ማድረግ ነበር።  የሆነው ግን በተቃራኒ ነው።
የዜምብላ ቴሌቭዥን ዘገባ ያጋለጠው ጉዳይ በእጅጉ ያስደምማል። እንዲህ ነው የሆነው። እ.ኤ.አ. በ 2011 ሄነከን ወደ ኢትዮጵያ እንደገባ የቢራ ስራ አዋጭ መሆኑን ስለተገነዘበ ስመ ጥሮቹን በደሌ እና ሃረር ቢራን ገዛቸው።  ስራውንም በእጅጉ አስፋፋ። በአኢትዮጵያ የቢራ ተጠቃሚዎች ቁጥር በእጥፍ እንዳደገም ዘገባው አስምሮበታል። ትርፉም እንደዚያው አደገ።
በደሌ ቢራ ከመሸጡ በፊት አንድ ነጥብ አምስት ሚሊየን ዩሮ ግብር ይከፍል ነበር።  ሄነከን ከገዛው በኋላ ግን የከፈለው ዘጠኝ መቶ ሺህ ዩሮ ብቻ ነው። አንድ ሚሊየን ዩሮ ግብር ይከፍል የነበረው ሃረር ቢራም አሁን ሁለት መቶ ሃምሳ ሺህ ዩሮ ብቻ ነው ያስገባው። ትርፉ ከእጥፍ በላይ እያደገ፣ ግብሩ ከእጥፍ በላይ የመቀነሱ ምስጢር ምን ይሆን?
የግብር ማጭበርበር ጥቆማ የደረሳቸው እነዚህ ጋዜጠኞች ጉዳዩን ለማጣራት ወደ ንግድ ሚንስትር ሄዱ። ምኒስትሩ በዚህ የማጣራት ጉዳይ ላይ ሊተባባራቸው ፈቃደኛ አልነበረም። ከዚያም ወደ ጉምሩክ እና ቀረጥ ቢሮ አመሩ። እዚያም ምንም መረጃ እንሰጥም ይሏቸዋል። ምስጢሩን ለማውጣት የጓጉት እነዚህ ጋዜጠኖች ተስፋ አልቆረጡም። በመጨረሻ ወደ ንግድ ምክር ቤት አመሩ።  የዚያ ባለስልጣን የሰጧቸው ምላሽ የሚያስቅ ነው። “የንግድና ትርፍ ዘገባ አይደርሰንም።” አሉ። ታዲያ ንግድ ምክር ቤት ይህንን ካልመዘገበ ምን ይሆን የሚሰራው?
የንግድና የስራ ግብር መቀነሱ ብቻ አይደለም። ቀድሞ በሃረር እና በበደሌ ቢራ ቋሚ ሰራተኛ የነበሩ 699 (44%) ሰራተኞችም ከሄነከን ቢራ ተቀንሰዋል።  የሆላንድ መንግስት ስራ ፍጠሩ ብሎ ድጎማ ሲያደርግ፣ ይልቁንም ነባሩን ሰራተኛ ከስራው አፈናቀሉት።
በኢትዮጵያ የሄነከን ተወካይ ሆላንዳዊ ነው። የዜምብላ ጋዜጠኖች የዚህን እንቆቅልሽ ለመፍታት እሱን ማፋጠጥ ይችላሉ። ስለዚህም ወደሱ አመሩ።  የገቢና ወጪ ዘገባውን እንዲሰጣቸው ጠየቁት።  እንቢ እንዳይል ቸገረው። ምክንያቱም በዚያ ዘገባ የሆላንድ መንግስት የድጎማ ገንዘብ ሰላለበት። እሺ ብሎ ይፋ እንዳያደርገው ደግሞ ምስጢሩ ለህዝብ ሊወጣ ነው። እሱም አለ። “የፋይናንስ ሪፖርቱን እሰጣችኋለሁ። እናንተ ግን ለህዝብ ይፋ እንደማታደርጉት ቃል ግቡልኝ።”
ዘገባውን በእጃቸው ያስገቡት እነዚህ ጋዜጠኖች፣ ዶክመንቱን አለም አቀፉ የገንዘብ ተቁዋም አማካሪዎች ጋ ይዘውት ሄዱ። የ አይ. ኤም. ኤፍ. ባለሙያው ወረቀቱን እንዳየ ምስጢሩን ለማወቅ ሰከንዶች አልፈጁበትም። የኢትዮጵያ ህዝብ በታክስ ተዘርፏል። ሰራተኛውም ወገን ከስራው እንዲፈናቀል ተደርጓል።
የመንግስት ባለስልጣን ሃገር ሲዘረፍ እና ወገን ከስራ ሲፈናቀል፣ ጉዳዩን ማፈን መርጠዋል። ምክንያት ቢኖራቸው እንጂ ይህን መረጃ መስጠት ሀገርን የሚጠቅም ነበር።  በእርግጥ ይህ የግብር ማጭበርበር ተግባር እነሱ ሳያውቁት ሊሆን አይችልም። “የአባትህ ቤት ሲዘረፍ አብረህ ዝረፍ!”  ነው ነገሩ። እንዲህ እየተዘረፈ ኢኮኖሚው እንዴት ነው በ 11 በመቶ የሚያድገው?
እንግዲህ ይህ በኢትዮጵያ ከዘመቱት 130 የሆላድ የንግድ ድርጅቶች አንዱ ታሪክ ነው። ገቢውና ወጭው በግልጽ የሚታይ፣  ግዙፍ እና አለም አቀፍ ድርጅት። ሄነከን ከገዥው ፓርቲ ባለስልጣናት ጋር በመመሳጠር ይህንን ያህል ከዘረፈ የሌሎቹ – የማይታወቁት ምን ያህ ይሆን?
የቀድሞው የሆላንድ ልማትና ትብብር ሚንስቴር የነበሩት ጃን ፕሮንክ፣ በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። ከልማት እና እደገት ጋር ምንም አይነት ግንኙነት ለሌላቸው የንግድ ድርጅቶች የገንዘብ ድጋፍ ማድረግን ክፉኛ ይወቅሳሉ። በተለይ መንግስታቸው በልማትና ትብብር ስም፣ በብሄራው ጥቅም ስም የስብአዊ መብት ረገጣን ችላ ማለቱን ያወግዛሉ።
በልማት ስም በሚሊዮኖች እየፈሰሰ ያለው የሆላንድ ግብር ከፋዮች ገንዘብ በኢትዮጵያ ስራ አልፈጠረም። እንደውም ሰራተኞችን አፈናቀለ። ሀገሪቱን በበለጠ የስራና የንግድ ግብር ተጠቃሚ ያደርጋል ይባል እንጂ ግብሩ በ 70 እጅ ያነሰ ሆኗል። ከሁሉም በላይ ደግሞ የገበሬው መሬት እየተነጠቀ ለነዚህ ዘራፊዎች መሰጠቱ የህዝብ ቁጣን አስነስቷል።
በኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት  እየተካሄደ ያለው ህዝባዊ አመጽ የገዥው ፓርቲ ችግር ብቻ ሳይሆን የሆላንድም ችግር መሆኑን በመግለጽ ዜምብላ ዘገባውን ይደመድማል።

የጋራ ፊልሚያ በዘረኛው ወያኔ ላይ! (ታደለ መኩሪያ)

ታደለ መኩሪያ
ወያኔ    የአጋዚን ጦር ፣ የስለላ መረቡን፣ በሕብረተሰቡ የተጠሉ ግለሰቦችን ፣  የዘር ወርዴ  ሰለባዎችን፣ የገንዘብና የሥልጣን ጥመኞችን ይዞ ለሃያ አምሰት ዓመታት በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ሲ ፏሏል ቆይቷል፤ በጋራ ፊሊሚያ በቃህ ሊባል ይገባዋል። የሀገራችን ክፍለ ሃገር የሆነችው  የትግራይን  ሕዝብ ስም ይዞ  በወቅቱ ደርግ  በሕዝብ ላይ ከሚያደርሰው በደል  ለመላቀቅ መቀሳቀሱ የታወቀ ነበር፤ ይሁን  እንጂ ሀገርን ለመበታተን የቆመ መሆኑ ቢታወቅ  በምንም ዓይነት  የተከዜን ወንዝ  አይሻገርም ነበር፤ እንደማይሻገሯት የወያኔ መሪዎች  ጠንቅቀው ያውቁታል። ዛሬ እንደጌኛ ሊጭኑት የተነሱት  የወልቃይት ጠገዴ፣የከፍታ ሑመራ፣ የጥልመት ሕዝብ  ባለውለታቸው ነበር፤ባጎረስኩ  እጄን ተነከስኩ ሆኖበት ፤ ዛሬ  ንብረቱን ተቀምቶ፤ እርሱነቱ ተገፎ፤  በስውር በጥይት እየተቆላ ነው፤  ልጆቹ  ከትምህርት ቤት ይልቅ  በእስር ቤቶች ታጉረው ይገኛሉ።
ወደ መሐል ሀገር ሰንመጣ፡ በየፈርጁ  ወያኔዎች   የሚያሳዩን  ትዕይንቶች እንደተመልካቹ  ይለያያሉ፤ ሆኖም ግን  ግባቸው አንድ ነው፤ ሕዝብ በጋራ  ሰለሀገሩ እንዳይመክር ማድረግ ነው።  የሚከተለውን ሃይማኖት፣  የመጣበትን የሕብረተሰብ ክፍል፣  በመጠቀም  ሕዝቡን  ለመከፋፈል  አጥብቆ ሠርተዋል፤
ከአራት ዓመት በፊት ጀምሩ ‘ድምፃችን ይሰማ’ በማለታቸው በ እስር የሚማቅቁት  የእስልምና ተከታይ ወገኖቻችን  ለፍትህ፣ ለነፃነት፣ ለዲሞክራሲ በጽናት በቆራጥነት ቆሙ እንጂ ሕልውናቸውን አሳልፈው አልሰጡም።  በእኛ ላይ እየተፈጸመ ያለው፣ ‘ቤሔራዊ በደል ነው’ በማለት የመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የፍትህ እጦት ሰለባ መሆኑን በዚህ አገላለፃቸው ግለጽ አድርገውታል፤
እውነትን  ለሕዝብ በማቅረባቸው የታሰሩ ጋዜጠኞች፣ ለሰበዐዊ መብት የቆሙ፣ ግለሰቦች፣ በሰላም  ለውጥ ጠያቂዎች ሁሉ  ጭህታቸው አንድ ነው። እንደሙሰሊም ወንድሞቻችን የፍትህ ነው፤ የፍትህ ጥያቄው የእስር ቤት ብቻ ሣይሆን የመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥያቄ ሆኗል።
ዛሬ በኦሮመኛ ተናጋሪው ሕዝባችን  የተነሣው የ መሬት አንቀጥቅት አመጽ የወያኔን መሪዎች የተነፈሰ ጎማ አስመስሏቸዋል። የኦሮሞ እናቶች ባዶ እጃቸውን   ሞትን ሳይፈሩ በቆራጥነት ታንክና መትረየሰ ካሰለፈው፤ ቦንብና ክላሽ ከታጠቀው፣ የአጋዚ ጦር ፊት ለፊት ተጋፍ ጠው፣ ታሪክ ሠርተዋል። የኦሮሞን ሕዝብ በአድር ባዩ  ኦፒዲዎ መነጽር ይመለከቱት የነበሩት፤ የወያኔ መሪዎች የውርደት ማቃቸውን ለብሰዋል፤ ‘ልክ እናገባችሃለን’ ባዩ  አባይ ፀሐዬ ድንፋታው  ባዶና  ግልብ የቁራ ጭሆት ሆኖ ቀርቷል።
ወያኔ  በኮንሶ፣ በደቡብ ኦሞ ሕዝብ ላይ  አጋዚ ጦሩን አሰልፎ   የዘር ማጥፋቱን  ተልኮውን  ቢያጧጥፍም  ሕዝብ አልተበረከከም። ለፍትህ ለነፃነት ለዲሞክራሲ ለአንድነት ፊሊሚያው ከወያኔ ጋር በተባበረ ሃይሉ ቀጥሏል።
የቤገምድር ባጠቃላይ የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ በተናጥል፣ ከወገኔ ከትግራይ ሕዝብ ጋር አታጣሉኝን ብሎ የወያኔ መሪዎችን ቢማጠን  ጆሮ ዳባ ልበስ አሉ፣  ልመናው እንደፍረሃት ተቆጠረበት፣ ሃያ አምስት ዓመት  ዘንባባ አንጥፎ መለመኑ እንደጅል አስቆጠረው፣  በደሉና ወርደቱ  ሳይበቃው ርዕስቱን ተቀምቶ  ‘ማደሪያ  እንደጣች  ወፍ ‘ተከራተተ፣አሁን  ግን  ወርደት በቃኝ  ብሎ እራሱን  ከወያኔዎች ጥቃት ለመከላከል ‘ጓንዴ  አነሣ!  ጥያቄው የፍትህ ጥያቄ ነው።
ወያኔዎች ሀገር ለማሰተዳደር   ሕዝብን  በጎሣ  አለያይቶ በክልል ከልሎ የቀኝ ገዥዎችን መንገድ መከተላችውን  ሊገባን ይገባል፤  በሕብረተሰባችን  አነጋገር ክልል ለግጦሽ ሣር፣ ዘርም  ለገበሬ ነው ይባላል።  በዚህ  በከፋፍለህ ግዛው መመሪያችው ዜጎችን  እርስ በእርስ ማጫረሱ  አልሳካ ሲላችው፤  መጪው ትውልድ  እንደሕዝብና ሀገር ሊኖርባቸው የሚገባውን የተፈጥሮ ሐብቶቹ  ላይ  ዘምተዋል፤  የአፈር መመረዝ  ፣ የወንዞች  መበከል፣ ሆን ብሎ   ተወላጁን  ከመሬቱ አፈናቅሎ ለባአዳን መሰጠት  ትውልድን ከማጥፍት  ሀገርን   ከመሸጥ ተለይቶ የሚታይ አይደለም፤  ፈጥነን ይህንን  የወያኔ  እብደት  በጋራ   ካላስቆምነው   ከአስር ዓመት በኋላ  ሀገር አለን ብለን  ማውራት  አንችልም። የሀገራችንን ሁኔታ በጥልቀት ካየነው፣ በመግለጫ፣ በዲስኮር፣ በ ጉንጭ አልፋ  ይሰጥ  አገባ  የምንወጣው አይደልም። በእግር  ኳስ  ሕግ ‘ኳሷን ለማን እንድምታቀብላት ከመጨነቅህ  በፊት አስቀድመህ ወደ ኳሷ ተጠጋና  በቁጥጥርህ ሥር አውላት ’ ይላል ። ዛሬ ኳሷ  በኢትዮጵያ  ሕዝብ ሜዳ ላይ  ትገኛለች  ፤  በሀገር ጉዳይ  ላይ  ገለልተኛም  ቆሞ  ተመልካችም   መሆንን  ከዜጋ የሚጠበቅ  አይደለም።  በጋራ  በሀገር ሰም ተቧድኖ  ወደ መስኩ ገብቶ  ኳሷን   ከግብ  ማግባትን  ይጥይቃል።   በሀገር ጉዳይ ካታንጋና   ትሪቢዮን  ላይ   ተቀምጦ በቲፎዞነት   ማጨብጨቡ  ዋጋ አይኖርውም።
በመስኩ ላይ  ለነፃነት ለፍትህ  ለዴሞክራሲና ለአንድነት  እየሠራን  ሕብረት ፈጥረን    የወያኔን የዘረኛ አካሄድ እንፋለም!

በኢትዮጵያ የወደፊት አቅጣጫ ላይ የመከረው ስብሰባ ተጠናቀቀ

(ኢሳት ዜና) — በቪዥን ኢትዮጵያና ኢሳት በዋሽንግተን ዲሲ ጆርጅ ታውን መሪየት ሆቴል ከማርች 26-27 2016 የተዘጋጀውና በኢትዮጵያ የወደፊት ሁኔታ በለውጥ፥ ዲሞክራሲና፣ የብሄራዊ አንድነት ላይ የሚመክር ስብሰባ በስኬት መጠናቀቁን የስብሰባው አዘጋጆች ገለጹ። በስብሰባው የኢትዮጵያ የወደፊት አቅጣጫ የሚመለከቱ ጉዳዮች የተዳሰሱበት ሲሆን በርካታ የአገር ውስጥና የውጭ አገር ምሁራን፣ የሲቢክ ድርጅቶች እና የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ጥናታዊ ጽሁፎቻቸውን ያቀረቡበትና የተሳተፉበት እንደነበር ለማወቅ ተችሏል።
ፕሮፌሰር ጌታቸው በጋሻው የመግቢያ ንግግር ያደረጉ ሲሆን፣ በኮንፈረንሱ አንኳር አንኳር አገራዊ ጉዳዮች እንደሚነሱ ሃሳባቸውን አንስተዋል። በኢሳትና በቪዥን ኢትዮጵያ ትብብር ተዘጋጅቶ በነበረው በዚሁ ኮንፈረንስ ከተለያዩ አለም አቀፍ ተቋማት የተወከሉ ምሁራን በኢትዮጵያ ወቅታዊና የወደፊት አቅጣጫ ዙሪያም ሰፊ ውይይትን አካሄደዋል።
ከተለያዩ የሲቪክና የሰብዓዊ መብቶች እንዲሁም የእምነት ተቋማት የተወከሉ ተጋባዥ እንግዶች በኢትዮጵያ ዴሞክራሲና የተረጋጋ ሰላምን ማምጣት በሚቻልበት ዙሪያ የመከሩ ሲሆን፣ ዴሞክራሲያዊ ኢትዮጵያን ለመፍጠርም ብሄራዊ እርቅና ብሄራዊ ትብብር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
የአፍሪካ ሃገራትን ተሞክሮ በዋቢነት በማንሳት ለታዳሚ ገለጻን ያደረጉት ፕሮፌሰር አቻምየለህ ደበላ፣ በአህጉሪቱ በኢትዮጵያ በስልጣን ላይ ያለው የኢህአዴግ መንግስት አይነት ምርጫ አድርጎ መቶ በመቶ አሸንፌያለሁ ብሎ ያወጀ መንግስት እንደሌለ አውስተዋል።
በጋና በናይጀሪያና በሌሎች ሃገራት በትምህርት ቆይታቸው የታዘቧቸውን ፖለቲካዊ ጉዳዮች ለኮንፈርነሱ ያካፈሉት ፕሮፌሰር አቻምየለህ፣ በሌሎች የአህጉሪቱ ሃገራት ፖለቲካዊ ለውጦች መታየት ቢጀምሩም በኢትዮጵያ ያለውን አካሄድ ግን ገና ብዙ የሚቀረው እንደሆነም አስረድተዋል።
በኒው ዮርክ ሲቲ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር የሆኑት ፕሮፌሰር ጆን ሀርብሰን በበኩላቸው, በኢትዮጵያ ከ1960 የአብዮት ፍንዳታ ጀምሮ ሃገሪቱን ዴሞክራሲያዊ ሊያደርጉ የሚችሉ አራት እድሎች ሳይሳኩ መቅረታቸውን ገልጸዋል።
በግንቦት 1977 የተካሄደው ብሄራዊ ምርጫ ጨምሮ ሌሎች የፖለቲካ ትግሎችን ያወሱት ፕሮፌሰር ሀርብሰን፣ ከኢትዮጵያ ጋር በሽብርተኛ ዙሪያ ትብብር ያላት አሜሪካ በሃገሪቱ ዴሞክራሲ እንዲያብብ ትብብር ማድረግ እንዳለባት ባቀረቡት ገለጻ አመልክተዋል።
የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ግንባት የስራ አስፈጻሚ አባል የሆኑት ሌንጮ ባቲ፣ በመንግስት የሚፈጸሙ የኢሰብዓዊ ድርጊቶች በዝርዝር ካስረዱ በኋላ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በአንድነት በመሆን በስልጣን ላይ ያለውን ኢህአዴግ መስወገድ እንዳለበት ተናግረዋል።
በሃገሪቱ እየተፈጸሙ ስላሉ ኢሰብዓዊ ድርጊቶች ሰፊ ሪፖርትን ያቀረቡት አቶ ነዓምን የኢህአዴግ መንግስት ፌዴራላዊ፣ ዴሞራሲያዊ ወይም ሪፐብሊክ ተብሎ ሊፈረጅ እንደማይችል አክለው ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የወደፊት ጉዳይ የሚመክረው ስብሰባ እሁድ እለትም በዚሁ በማሪየት ሆቴል ቀጥሎ የዋለ ሲሆን፣ በትግሉና በግጭት አፈታት እና ለዲሞክራሲ፣ አንድነት ዙሪያ ሴቶች የሚጫወቱት ሚና በሚል መድረክ ውይይት ተካሄዶበታል።
በሃዋርድ ዩንቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስ ተማሪ የሆነችው ወ/ሪት ኤልሳቤጥ ላቀው ወደአሜርካ የፈለሱ አፍሪካውያን ሴቶችን ጉዳይ ከኢትዮጵያውያን ትግል አንጻር ትንተና ሰጥታለች። በመቀጠልም በኖርዌይ ሃገር የሚኖሩት ወ/ሮ ሰዋሰስ ጆሃንሰን ሁሉም ኢትዮጵያውያን ዲሞክራሲንና ነጻነትን በኢትዮጵያ ለማምጣት በአንድነት መታገል እንዳለባቸውና ካወሱ በኋላ፣ አዲሲቷን ኢትዮጵያ እውን ለማድረግ በመጀመሪያ እርቅ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አስምረውበታል። በመቀጠል የተናገሩት በፍራንክፈርት የሚኖሩት የሰብዓዊ መብት አቀንቃኝ ወ/ሮ አሳየሽ ታምሩ ሲሆኑ፣ በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በአገር ውስጥ ለሚሰቃዩ ኢትዮጵያውያን ሴቶች አጋርነታቸውን ማሳየት እንዳለባቸው ተናግረዋል። ወ/ሮ አሳየሽ፣ “ለልጆቻችን ማውረስ ያለብን ነጻነትን ነው” ሲሉ ተደምጠዋል። በዚህ ፓነል መጨረሻ ላይ የተናገሩት በዋሽንግተን ዲሲ የኢትዮጵያ ሴቶች የሰብዓዊ መብት አቀንቃኝ ወ/ሮ ወሰን ደበላ ሲሆኑ፣ 51% የሚሆነውን የኢትዮጵያን የሚሸፍኑት ሴቶች ቢሆኑም፣ በአገራዊ ጉዳይ ተሳትፏቸው ግን እጅግ ዝቅተኛ ነው ብለዋል። ወ/ሮ ወሰን የኢትዮጵያ ሴቶች በአገራዊ ጉዳዮች ላይ እንዲሳተፉም ጥሪ አቅርበዋል። ፓነሊስቶቹ የኢትዮጵያ ሴቶች ድምጽ እንዲሰማ ቪዥን ኢትዮጵያና መድረኩን በማመቻቸታቸው አመስግነዋቸዋል።
እሁድ ከሰዓት በኋላ የወደፊቷን ኢትዮጵያ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ለመዳሰስ ስብሰባ ተካሄዷል። ስብሰባውን የመሩት አቶ ግዛው ለገሰ ናቸው። በመጀመሪያ ጥናታዊ ጽሁፋቸውን ያቀረቡት አቶ ኤርሚያስ ለገሰ ሲሆኑ፣ በፓርቲዎችና በማህበረሰብ (ኮሚኒቲ) አባላት መካከል መተባበር አለመኖር ለለውጥ ከፍተኛ እንቅፋት እንደሆነ ተናግረዋል። ለአጭር ይሁንም ለረጅም ጊዜ የጋራ ግብ በእነዚህ የማህበረሰብ አባላትና ፓርቲዎች መካከል በመተማመን ላይ የተመሰረተ ትብብር እንደሚያስፈልጋቸው ተናግረዋል። ዶ/ር መስፍን አብዲ በመሬት ጉዳይ ዙሪያ ትንተና ሰጥተዋል። በህወሃት አገዛዝ መሬት የገበሬዎች ሆኖ እንደማያውቅና ከመሬት ይዞታ ጋር የተያያዙ አያሌ ያልተመለሱ ጥያቄዎች እንዳሉ ተናግረዋል።
አሁን ያለችዋን ኢትዮጵያ በማስመልከትም ያለፈው ታሪክ ሆኖ ያለፈ በመሆኑ የወደፊቷን ኢትዮጵያ ሁሉም በእኩል አይን የሚታይባት አገር መሆን ይኖርባታል ብለዋል። ከዚህ ጋር በማያያዝም ኦሮምኛ የኢትዮጵያ የስራ ቋንቋ እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል። የኦሮሞና የአማራ ልሂቃንም በሁለቱ ህዝቦች መካከል መተማመን እንዲኖር እንዲሰሩ እንዲሰሩ ጠይቀዋል።
በመሬይ ስቴት ዩንቨርስቲ የኢኮኖሚክስ መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር ሰይድ ሃሰን በመሬት ነጠቃና ሙስና ላይ ጥናታዊ ጽሁፍ አቅርበዋል። ፕ/ር ሰይድ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሙስና በአለም ላይ ከታዩት ሙስናዎች ለየት ያለ ነው ብለዋል። መሬት የስልጣን ምንጭ በመሆኑ የህወሃት/ኢህአዴግ መንግስት መሬት ነጠቃውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተንብየዋል። ሁሉም የኢትዮጵያ ተደራሽ አካላት ይህ ዘርፈ-ብዙ ውስብስብ ችግር ለመፍታት ተቀራርበው መነጋገር እንዳለባቸው ተናግረዋል።
በኬተሪንግ ዩኒቨርስቲ የታሪክ ምሁር የሆኑት ፕሮፌሰር እዝቅኤል ገቢሳ፣ የዲሞክራሲ፣ የእድገት፣ የሰብዓዊ መብት፣ የሰላም ማስፈን እሴቶችን ከውስጣችን መመልከት እንዳለብን የሚተነትን ጥናታዊ ጽሁፍ አቅርበዋል። ኢትዮጵያ ወደ ዲሞክራሲ የምትሻገርበትን ብዙ እድሎችን ያጣችበትን አጋጣሚ የተነተኑት ፕሮፌሰር እዝቅኤል፣ ኢትዮጵያውያን ህወሃት ኢህአዴግን ከማስወገድ ባለፈ የወደፊት እቅድ ሊኖራቸው እንደሚገባ አስረድተዋል። ፕሮፌሰር እዝቅኤል በገዳ ስርዓትና በኦሮሞ እሴቶች ላይ ትንተና ሰጥተዋል።
“ከዚህ በኋላ ወዴት? ያልተመለሱ ጥያቄዎች!” የሚለው የመጨረሻው ስብሰባ የተመራው በኮሎራዶ ሜትሮፖሊታን ስቴት ዩንቨርስቲ መምህር በሆኑት በፕሮፌሰር ሚንጋ ነጋሽ ነው። ለዲሞክራሲ፣ ለለውጥና ለአንድነት ምን መደረገ እንዳለበት የመከረው ይኸው ስብሰባ፣ ኢትዮጵያ በአስቸኳይ ለውጥ የሚያስፈልጋት አገር እንደሆነች ተናግረዋል። የኢትዮጵያውያንን ህይወት የዳሰሰ በምስል ያሳዩት ፕሮፌሰር ሚንጋ፣ ኢትዮጵያ የሰላም፣ የዲሞራሲና የብልጽግና አቅጣጫ (Roadmap) ያስፈልጋታል ብለዋል። በመሆኑንም ከኤርትራ ጋር ያንዣበባት የጦርነት አደጋ፣ በኦሮሚያ፣ ኮንሶ፣ አማራ፣ ሶማሌ እና ጋምቤላ አካባቢዎች የሚታየው ግጭት ኢትዮጵያን ከፍተኛ አደጋ ውስጥ እንደከተታት ተናግረዋል። ከህወሃት/ ኢህአዴግ መወገድ በኋላ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚተገበር አቅጣጫ መቀመጥም እንዳለበት ፕሮፌሰር ሚንጋ ተናግረዋል።
ፕሮፌሰር ተሾመ ከበደ በኢትዮጵያ እየተከሰተ ያለው ብጥብጥ የመንግስት የስልጣን ምንጭ እንደሆነ ለተሰብሳቢው ተናግረዋል። ፕሮፌሰር ተሾመ ኢትዮጵያ የዲሞክራሲ እሴቶችን የምታከብር፣ በሉዓላዊነቷ የማትደራደር አገር እንድትሆን ማድረግ ሃላፊነት እንዳለብን ለታዳሚው ተናግረዋል። ሕወሃት/ኢህአዴግን በተመለከተ ሙሉ በሙሉ እንዲደመሰስ ማድረግ ሳይሆን ዲሞራሲያዊ እሴቶችን እንዲቀበል ማስገደድ እንዳለብን ተናግረዋል። “አገራችን ችግር ላይ ናት፣ የእኛን እርዳታ ትሻለች” ሲሉ ለተሰብሳቢው ተናግረዋል።
ከዚህ ቀጥሎ የተናግሩት  የህግ ባለሙያና የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባት አባል የሆኑት ዶ/ር በያን አሶባ ሲሆኑ፣ ያለፉትና የአሁኑ አምባገነን መንግስታት በህዝቦቻችን ላይ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መፈጸማቸውን ተናግረዋል። ሌሎች ኢትዮጵያውያን በኦሮምያ እየተከሰተ ያለውን ህዝባዊ እንቅስቃሴ በጥርጣሬ መመከታቸውን ትተው እንዲደግፉት ጥሪ አቅርበዋል።
በካሊፎርኒያ ግዛት ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማሪያም የአምባገነን መንግስታት ባህሪ ነገሮችን መደበቅ ነው ብለዋል። በመሆኑም ህወሃት ኢህአዴግ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዳይታወቅበት ኢሳትን በብዙ ሚሊዮን ብር በመክፈል በተደጋጋሚ በሞገድ ለማገድ መሞከሩን ለተሰብሳቢው ተናግረዋል። ሆኖም ህወሃቶች ለሰሩት ጥፋት ሁሉ ተጠያቂ የሚሆኑበት ጊዜ ሩቅ እንዳልሆነ ለተሰብሳቢው ገልጸዋል። ለዲሞክራሲና ለእኩልነት የሚደረገው ትግልም ህወሃት/ወያኔ ኖረም አልኖርም መቀጠሉ አይቀሬ መሆኑን አስረድተዋል። አዲስ አቅጣጫ የሚያመላክት ህገ-መንገስትም መዘጋጀት እንዳለበት ተሰብሳቢውን መክረዋል።
በመጨረሻ የቀረቡት በዳይተን ዩኒቨርስቲ የፍልስፍና መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር መሳይ ከበደ ናቸው። የተሻለው አቅጣጫ አሁን ያለውን በዘውግ የተከለለውን አስተዳደር መከተል መሆኑን አስመረው፣ ኢህአዴግ ቢወገድም የዘውግ ጥያቄ በቀላሉ የሚጠፋ አለመሆኑን ገምተዋል።
ከቀረቡት ጥናታዊ ጽሁፎች በሁላ በርካታ ጥያቄዎች ለተሰብሳቢዎች የቀረቡ ሲሆን፣ አብዛኞቹ ከመድረክ መልስ ተሰጥቶባቸዋል። አንዳንድ ያልተመለሱ ጥያቄዎች ወደ ፊት በሚካሄዱ ስብሰባዎች እንደሚነሱ ለማወቅ ተችሏል።