Saturday 16 November 2013

የፌደራል ፖሊሶች በሳውድ አረቢያ የሚፈጸመውን ግፍ ለመቃወም አደባባይ በወጡ ኢትዮጵያውያን ላይ ጥቃት ሰነዘሩ

በሳውድ አረቢያ በኢትዮጵያውያን ላይ እየተፈጸመ ያለው ግፍ ተባብሶ በቀጠለበት በዚህ ወቅት፣ የሳውዲን መንግስት ለመቃወም በሳውድ አረቢያ ኢምባሲ ፊት ለፊት ተቃውሞዋቸውን ለመግለጽ የወጡ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በፌደራል ፖሊሶች ተደብድበዋል።
ከ100 በላይ ሰዎች ታስረው የነበረ ሲሆን እስከ ምሽት ድረስ 40 የሚሆኑት ተለቀዋል። ሰልፉን ያዘጋጀው የሰማያዊ ፓርቲ 15 የአመራር አካላትም በእስር ላይ እንደሚገኙና ይህን ዜና እስካጠናከርንበት ጊዜ ድረስ አለመፈታታቸው ታውቋል።
የሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ የሆነው ወጣት ብርሀኑ ተክለያሬድ እስር ቤት ውስጥ ሆኖ በድብቅ በስልክ እንደተናገረው የድርጅቱን ሊቀመንበር ኢንጂነር ይልቃል ጌትነትንና ምክትላቸው አቶ ስለሺ ፈይሳን ጨምሮ 15 አመራሮች ጃንሜዳ በሚገኝ እስር ቤት ውስጥ ይገኛሉ። ወጣት ጥላየ ታረቀኝ ታስሮና ድብደባ ተፈጽሞበት ከተለቀቁት መካከል አንዱ ሲሆን ፣ የኢትዮጵያን መንግስት ድርጊት ለመግለጽ እንደሚቸገር ገልጿል።
ሌሎች አስተያየት ሰጪዎችም በመንግስት ድርጊት አገር አልባነት እንደተሰማቸው  ይናገራሉ
ሰማያዊ ፓርቲ ከጥቃቱ በሁዋላ ባወጣው መግለጫ ” የኢትዮጵያ መንግስት ከሳውዲ አረቢያ መንግስት ጎን በመቆም ዋና ተባባሪ መሆኑን በዛሬው እለት አስመስክሯል ብሎአል።
የመንግስት ፖሊሶች የራሳቸውን ዜጋ በመደብደብና በማሰቃየት ብሎም በማሰር በሳውዲ በሚገኙ ኢትዮጵያዊ ወገኖች ላይ የተፈጸመውን በደል ሀገር ውስጥ በሚገኙ ንጹሀን ወገኖቻቸው ላይ ደግመውታል ብሎአል።
በውሸት ዲሞክራሲ ስም የተደበቀው አምባገን መንግስት ህዝብን ለማሸማቀቅ የወሰደውን እርምጃ በመቋቋም የኢትዮጵያ ህዝብ አያት ቅድመ አያቶቻችን የሰጡንን አደራ በመቀበል ያስረከቡትን ክብርና ማንነት ለማስመለስ ወደ ሁዋላ እንደማንል እርገኛ መሆናችንን እንገልጻለን ብሎአል።
የመንግስት ቃል አቀባይ የሆኑት ሽመልስ ከማል ለአልጀዚራ  ሰልፈኞቹ የተከለከሉት ባልተፈቀደ ሰልፍ ላይ በመገኘታቸውና ኢትዮጵያን ህዝብ በጸረ-አረብ ስሜት በማነሳሳታቸው ነው ብለዋል።

ዋና ጠላታችን የትግሬ ነፃ አውጪ ወያኔ ነው!

ከቴዎደሮስ ሐይሌ
‘’ ወዴት ነው የምንሄደው ለማን ነው
የምንነግረው መንግስት ረስቶናል ኤንባሲው
አላቃችሁም …ብሏል ነገ እኔ እህትህን ወይ ተደፍሬ
ወይ ሞቼ ወይ አብጄ ነው የምታገኘኝ’’ አንዲት
በሳውዲ ተደብቃ ያለች እህታችን ያስተላለፈችው
መልዕክት
አቦይ ስብሃት ከጉልምስና እስክ ሽምግልና የታገልክለት ኢትዮጽያና ኢትዮጽያዊነት የማዋረድ
አላማህ ከሃገር አልፎ በአለም ሁሉ ሆኖዓልና እንኳን ደስ ያለህ አዜብ መስፍን የባልሽ እረፍት የለሹ እስከ
መቃብር ያለመታከት የቆመለት አላማ ትቶት ያለፈው ራዕይ የአገዛዝ ውጤቱ ይህው ኢትዮጽያውያንን
አንገት የማስደፋት ተሳክቶ እዚህ በመድረሱ የሃዘንሽ መጽናኛ ከሆነልኝ እንኳን ደስ አለሽ፤ በረከት ስምዖን
የውሸት ጋጋታህ የክፋት ፕሮፓጋንዳህ ኢትዮጽያዊነት የማወረዱ አላማህ ግቡን መቷልና ከነሳውዲው
ቱጃር ወዳጅህ እንኳን ደስ አለህ፤ ደብረጽዮን ገብረሚካዔልና ጌታቸው አሰፋ የገደላው መሃንዲሶች
የአፈናው ሊቃውንቶች እንኳን ደስ አላችሁ ስታሳድዱት ያመለጣችሁን ሁን ብላችሁ ከፍታችሁ
ባደላችሁት የባርነት ማረጋገጫ ፓስፖርት ሃገሩን እንዲለቅ ያደረጋችሁት ትኩስ ትውልድ ይህው ደሙ
ደመከልብ ሆኖ ከውሻ አንሶ በዚህ ዘመን የሰውልጅ
ሊቀበለው የማይችለውን ግፍ እየተቀበለ በመሆኑ
የጥላቻ የበቀልና የዘር ማጥፋት ዘመቻችሁ ስኬት
በመሆኑ እንኳን ደስ አላችሁ። በአጠቃላይ መላው
የትግሬው ነጻ አውጪ አባላትና ደጋፊዎች
የዘበታችሁበት ኢትዮጽያዊነት የቀለዳችሁበት
ኢትዮጽያዊ ዜጋ የመንግስታችሁ ደብል ድጂት
የልማት በረከት ይህ የሃገርና የወገን ውርደት ስቃይ
በመሆኑ እንኳን ደስ አላችሁ።
ኢትዮጽያና ኢትዮጽያዊነት ክብርና ኩራት ጀግንነትና
አትንኩኝ ባይነት እንግዳ ተቀባይነት ደግነት የመሆኑ ታሪክ
ተለውጦ አዋርደው ለውርደት ገለው ለገዳይ ሰድበው ለሰዳቢ
አሳልፈው የሰጡን የሃገራችን አንጡራ ሃብት እየዘረፉ
በቅንጦት ህይወት አለማቸውን ከመቅጨት በቢሊዮን ዶላር
የሚቆጠር ገንዘብ ከሃገር አሽሸተው ሰርቶ የመኖር ነግዶ
የመክበር አርሶና ቆፍሮ ኑሮን የማሸነፉን እድል ያሰጡት
ትውልድ ህይወት ቢከብደው ተስፋው ቢጨልም ስደትን
አማራጭ አድርጎ በላብ በወዙ ጥሮ ግሮ ህይወቱን ሊለውጥ ቤተሰቡን ሊረዳ የሄደበት የመከራ መንገድ

እሱም በዝቶ ሬሳው በየመንገዱ ሲጎተት እየታየ ሴቶች በማንም ደደብ አራዊት ጀማላ በግፍ ሲደፈሩ ሃገር
እመራለሁ የሚለው የትግሬ ወያኔዎች ጥርቃሞ ትንሽ ለማስመሰል ያህል እንኳ ግፉን ለማቆም ከመሞከር
ይልቅ የሚባለው ተጋኗል ያን ያህል ችግር የለም የሚል መግለጫ ሲሰጡ አድምጠናል ጎበዝ ከአስር ሰው
በላይ በተገደለበት በመቶዎች የአካል ጉዳተኛ በሆኑበት በአስር ሺዎች በግፍ ሃብትና ንብረታቸው
እየተቀማ በየእስር ቤቱ ሲታጎሩ ጉዳቱን አቅሎ ማየት ፖለቲካ ነው ዲፕሎማሲ ወይስ ዘረኝነት የዛሬ
ስምንት አመት ትግሬ ወደ መቀሌ እቃ ወደ ቀበሌ የሚል የባልቴቶች ተረት ይዞ ሁለት መቶ ሰዎች
ለመግደል የበቃው ይህ ጠባብ ቡድን ጉዳዩን ማሰነሱ የጥላቻው ልኬታና ለኢትዮጽያውያን እንግልት
ያለውን ፍላጎት ከማሳየት የዘለለ አለመሆኑን ዳግም ያረጋገጠበት አጋጣሚ ነው።
በሃገራችን የትግሬ ነጻ አውጪ ወያኔዎች ገበሬውን
ከእርሻው ነዋሪውን ከቅዬው በግፍ እያፈናቀሉ መድረሻ
በማሳጣት በዶላር ሄክታር ለምና ድንግል መሬታችንን ለሳውዲ
አራሾች እያከራየ መጤ አረቦችን ብረት ለበስ በታጠቀ ሰራዊት
በማስጠበቅ ተቃውሞ ሊያቀርብ የሞከረውን በፊታቸው
እየገደለ እያሰረ ያቃለለውን ኢትዮጽያዊ ወገን እንዲህ
በሃገራቸው ቢያዋርዱት የሚደንቅ አይደለም። የሃገሩ መንግስት
እንደሰው ሲያከብረው ያላዩትን (በጋንቤላ የተፈጸመውን ጅምላ
ፍጅት በኦጋዴ የተደረሰው ዘር ማጥፋት በአፋር ወገኖች ላይ የተቃጣው ጥቃት በጉራፈርዳና በቤኒሻንጉል
በአማራ ተወላጆቸ ላይ የተካሄደውን ያለ አንዳች ህጋዊ መሰረትና ማስጠንቀቂያ የተካሄደውን ሽብር ያዩት
የሳውዲ ራቢጣዎች ይህንን በሃገራቸው ቢደግሙት ጥፋተኛው ማን ነው። በአጼውና በደርጉ ዘመን
እንዲህ ያለ ብሄራዊ ውርደት በወገን ላይ ተቃጥቶ አያውቅም።
 ‘’ባለቤቱን ካልናቁ አጥሩን አይነቀንቁ’’
ይላል የሃገሬ ሰው ልጁ የሚያወርደው አባት
ከማህበረሰቡ አክበሮት የሚሰጠው እንደሌለ ሁሉ
የትውልድ ሃገሩ መንግስት ዜጋዬ ያላለውን ዘብ
ያልቆመለትን የኔ ያላላለውን ከቶስ ሌላው እንዴት
እንዲያከብረው እንጠብቃለን እንኳን ሳውዲ
የነዳጅ ሃብት ዲታ ያደረጋቸውን ቀርቶ ዛሬ ወገኖቼ
ኢትዮጽያዊ ሱዳንና ኬንያ እንኳ ሳይቀር
እንደሰውያማይታይበት ደረጃ ደርሷል። ለዚህ ደግሞ ሃገራችንን የተቆጣጠረው የዘረኛ አገዛዙ እድሜ
ከማራዘም ውጪ ቅንጣት ሃገራዊ ራዕይ የሌለው የትግሬ ወያኔዎች ቡድን ለጎረቤት ሃገራት የኬላና የፀጥታ
ሃይሎች ጉቦ በመስጠት ኢትዮጽያዊው ዜጋ የለውጥ እንቅስቃሴ ያደርግብኛል ከሚል ፍርሃት ድንበር
አልፎ በስደተኛው ላይ ሳይቀር ግድያ ፈጽሞ እየወጣ ሲገልና ሲያዋርደው እያዩ እንዴት ይራሩልን። ወያኔ
ድንበር አልፎ በጎረቤት ሃገራት ውስጥ ይህን የመሰለ ግፍ መፈጸም ብቻ ሳይሆን በነዚሁ ድንበረተኞቻችን
በኩል የለውጥ ትግል እንዳይካሄድ በሺህ ኪሎ ሜትር የሚቆጠር ለም መሬታችንን አሳልፎ እጅ መንሻ
እስከመስጠት የደረሰ ሃገር ሻጭ ብሄራዊ ክህደት የሚፈጽም በፖለቲካ ግልሙትና የዘቀጠ አገዛዝ
ኢትዮጽያ ውስጥ መኖሩን የሚያውቀው ዓለም ተሸክመን ያለንውን ወራዳ አገዛዝ ከላያችን ለማውረድ
ያልቻልን ደካሞች መሆናችንን እያየ እንዴት ያክብረን የመዋረዳችን ምክንያቱ የዛች ሃገር ዜጋ ነን የምንል
ሁላችንም ነን። የአባቶቻችን ልጆች መሆን ያቃተን ፈሪና ደካማ ስለሆን ነው። በአሁኑ ወቅት ስደትና መከራ በመጋራት በአለም ፊት ግንባር ቀደም የሆኑት የኢትዮጽያና የኤርትራ
ህዝብ ሆኖ እያለ በጎረቤትም ሆነ በመካከለኛው ምስራቅ ያሉ ኤርትራውያን ላይ እንዲህ ያላ ጥቃት
እንዳይኖር የሃገራቸው መንግስት አቅሙ የፈቀደውን እንደሚያደርግ ይደመጣል።ዜጎቹም ላይ እንዲህ
እንደኛ ያለ ግፍነና በደል ብዙም አይስተዋልም። ይህ የሚያሳየው ሻብያ ምንም ይሁን ምን ለዜጎቹ ደህንነት
ዘብ የመቆሙን ሁኔታ የሚያሰረዳ ሁኔታ ነው። የትግሬ ነጻ አውጪ ወያኔዎች በመላው ዓለም ባሉት
ኤንባሲዎች ውስጥ ያሉት ዲፕሎማት ተብዬዎቹ እንደሚባለው ሻንጣ ተሸካሚ ፤ በድርጅትና ፖለቲካና
በግል ቢዝነሳቸው ላይ ስለሚያተኩሩ የዲፕሎማሲና የተመደቡበትን ሃገር ቋንቋና የፖለቲካ አካሄድ በቅጡ
ያልተረዱት እውቀት አጠሮች ስለሆኑ ብቻ አይደለም ለኢትዮጽያውያን ሰቆቃ ምላሽ የማይሰጡት ዋናው
ቁልፉ ችግራቸው ከራሳቸው ጎጥ ውጪ ያለውን እንደ ተቃወሚና እንደ ጠላት የሚቆጥሩ ዘረኞች ስለሆኑ
ነው። እዚህ ላይ አንድ የመን የነበረ ወገን ሲያጫውተኝ ለይስሙላ ከላይ ለይምሰል ከሚቀመጡት የሌሎች
ብሄር አባላት ስር በየኤንባሲው የሚቀመጡት የትግራይ ተወላጆች ከራሳቸው አካባቢ ሰው በስተቀር
ሌላውን ኢትዮጽያዊ በክፉ የሚመለከቱ በመሆናቸው እንኳን ሊረዱን ይቅርና ለየመን የደህንነት መስሪያ
ቤት አሳልፈው እስከመስጠት በደል ሲፈጽሙብን ነበር ሲል በሃዘን የነገረኝ ነው ከላይ በጥቅስ ውስጥ
ያለውን ከዛው ከሳውዲ ሰቆቃ ውስጥ ያለች እህታችን ለኢሳት የገለጸችው።
 እንኳን የነጻነት ጭለማ በዋጠው የአረብ ሃገራት
ይቅርና በሰሜን አሜሪካ ያለው ኤንባሲ ከነስሙም (የወያኔ
ኤንባሲ) በሚል መታወቅ የደረሰ የትግራይ ልማት ማህበር፤
የትግራይ ሴቶች፥ ወጣቶች፤ወዘተ በሚል የአንድ አካባቢ
ሰዎች የሚሰበሰቡበት ዳንኪራ የሚረግጡበት የኢትዮጽያ
ህዝብን ለመከፋፈልና አንገት ለማስደፋት የሚወጠንበት
ከግማሽ ሚሊዮን የማያንስ ኢትዮጽያዊ ባለበት አካባቢ
የአንድ ጎጥ ሰዎች ቁጥጥር ስር የመዋሉ እውነታ ለሚያውቅ
ሃብታችንን እንዲፈነጩበት መሬታችንን በልግስና
በሠጣቸው የመካከለኛው ምስራቅ ሃገሮች ያለው የወያኔ ዲፕሎማሲ የመዋቅር መዘውር በጎጠኝነት
የተተበተበ በጥቅምና በጥላቻ የተጠነጠነ በመሆኑ በሃገር ውስጥ በትውልድ ማንነቱ በኦሮሞነቱ፤
በአማራነቱ፤በአፋርና ፤ጋንቤላነቱ እየለዩ እንደሚያስሩት እንደሚገሉትና እንደሚያሰቃዩት ሁሉ በስደትም
ስቃዩ የሚበዛው እንግልቱ የነገሰው በሃገሩ የመኖር ነጻነት የገፈፉት ህብረተሰብ እሱው በመሆኑ በሌሎች
ቢንገላታ ቢዋረድ ቢሞት ሬሳው ቢጎተት ግዳቸውም ምንድን ነው እነሱው የሚያደርጉት አይደለም እንዴ
ስለዚህ ቀደሚና ዋና ጠላታችን የትግራይ ነጻ አውጪ ወያኔ ለመሆኑ ከዚህ በላይ ምን ማስረጃ ማቅረብ
ያስፈልጋል።
ባለፉት 22 አመታት ብዙ ተወርቷል አያሌ መስዋዕትነት ተከፍሏል ውጤቱ መታሰር መጋዝ
መሞት መዋረድን አልገታም እስከ መቼ ታሪክ አውሪ ከመሆን አልፈን ታሪከ ሠሪ የምንሆነው መቼ ነው።
እስከመቼስ ነው በላያችን የተንሰራፋውን ሌባ ዘራፊና ዘረኛ ወያኔን የምንሸከመው ፤ ስደቱ መፍትሄ
አልሆነም ዝምታው አልሰራም ሞት እስራትና እንግልት አልተለየንም፤ ስደታችን ውርደት በሃገር መኖራችን
ረሃብ ቸነፈር ተስፋ መቁረጥ ይህ ሁሉእስከመቼ ማብቂያው የት ላይ ነው እርሻችንን እየነጠቀ ለውጭ
ባለሃብት የሚሸጥ ፤ንብረታችንን እየቀማ ክልልህ አይደለም ውጣ ተብለን ያፈራንውን ሃብት ተቀምተን
ለጎዳና ፤ገዳማችንን እያፈረሰ ሸንበቆ የሚተክል መስኪዳችንን የካድሬ መናሃሪያ ያደረገ ከዚህ ሁሉ አልፎ
ጸጥታ አስከባሪ የተባሉት የወያኔ አፋኞች በዜጎች ላይ ግብረሰዶም ወደመፈጸም ክብራችንን ያወረደውና
አሳልፎ ለአዋራጅ የሰጠህ ወገኔ ሆይ የትግሬ ነጻ አውጪ ወያኔ ነው።የእነሱ ልጆች ከኛ በተቀማ ሃብት

አውሮፓና አሜሪካ በውድ ኮሌጆች ይማራሉ፤ ከኛ በተቀማ ገንዘብ የገላቸውን ጭቅቅት የጎፈሬያቸውን
ተባይ የእግራቸውን ንቃቃት አራግፈው እኛ ጥሬ መቆርጠም ዳገት ሆኖብን እነሱ ቁርሳቸው ሻኛ
ትራሳቸው ጮማ ሆኖ በላያችን ላይ የሚዘባነኑት ከደደቢት የወርቅ ጭብጦ ይዘው መጥተው አይደለም ።
ወገናችን ሆዱን ምግብ እያማራው ገላው በእጦት ተራቁቶ የጣር ህይወት እንዲገፋ የፈረደበት ይህ የወያኔ
ድኩማን ቡድን ነው። እንዲህ በላያችን የነገሰው ከሰማይ ተቀብቶ ወይም የተለየ ችሎታ ኖሮት ሳይሆን
በእኛ ፍርሃት አለመተባበር ደካማነት ብቻ ነው። ስለሆነም የፍርሃት ቀንበርን የግለኝነት አባዜን ወደጎን
ጥለን በቀዳሚውና በዋናው ጠላታችን የወያኔ ቡድን ላይ እናንሳ ያኔ የመጨረሻው መጀመሪያ ይሆናል።
የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት የድህረገጽ ዝግጅት ክፍሎች በአርቲ ቡርቲ አጀንዳ የተጠመዳችሁ
የመንደር ሬድዮ ጣቢያዎች ርዕስ አጥታችሁ የስድብ ወጀብ ለምታዘንቡ የፓልቶክ ክፍሎች የወገን ውርደት
ይበቃ ዘንድ የትውልዱ መከራ መፍትሔ እንዳያገኝ ጠፍሮ የያዘንን አሮጌና ኋላ ቀር ኢዲሞክራሲያዊ
የፖለቲካ ባህል ወደ ጎን በማድረግ በአንድነትና በጋራ ለተደራራቢና ተደጋጋሚ ችግር እየዳረገን ያለውን
ሰውበላ ትውልድ አምካኙን የወያኔን አገዛዝ በማስወገድ ላይ ሃይላችሁንና እውቀታችሁን በማስተባበር
ለአንዴና ለመጨረሻ ግዜ ስር ነቀል ሕዝባዊ ንቅናቄ የሚካሄድበት ሁኔታ ለማመቻቸት በጋራ እንድትቆሙ
ተገቢውን የቅስቀሳና የማንቃት ሚና ለመጫወት እንድትነሱ የወገን መከራ የሃገር ህልውና ግድ ይላችኋል።
ኢትዮጽያዊ ነኝ የምትል ኳስ ጨዋታ አለ ስትባል ባንዲራ ለብሰህ እምቢልታ የምትነፋው ቦታ አልበቃ
የሚልህ የሃገርህን ቡድን ለመደገፍ በነቂስ የምትወጣው ወጣት ይህን ማድረግህ መልካም ነው ተገቢም
የሚደገፍም ነው። የወንድሞችህ አናት በጥይት ሲነደል ወገባቸው በቆመጥ ሲጎብጥ ለቅሪላው ግዜ
የምታነግባትን ባንዲራ ለብሰህ ወገንህን ላይ ግፍ የፈጸሙትን የአረመኔው የሳውዲ መንግስት ኤንባሲዎችና
በወገን መከራ በሚነግደው የወያኔ አገዛዝ ላይ በያለህበት በነቂስ በመውጣት ተቃውሞህን በማሰማት
ወገናዊ ድርሻህን ተወጣ።
አዲሱ ትውልድ ወጣቱ ሆይ ስደት ይብቃህ ለለውጥ ተነስ ወይ በተገቢው ለመኖር አለያም
ለክብር ሞት ራስህን አዘጋጅ የአህዛብ መቀለጃ የደደቦች መጫዎቻ የመሆን ታሪክህን አድስ፤ ሃገርህ እንኳን
ላንተ ለነዚህ ደንቆሮ ጀማላዎች የተረፈ ወርቅ ተፈጥሮ አላት፤ ከበረታህ አንተ ሳትሆን እነሱ ወዳንተ
ይመጣሉ። ትላንትም በአባቶችህ ዘመን ክፉ ቀን በክብር ያሳለፉት ባንተ ሃገር ነበር፤ እንዲህ ሊያወርዱህ
እድል ያገኙት ሃገርህን የወረረው የትግሬ ነፃ አውጪ ሌባ ቀማኛና ሰዶማዊ አገዛዝ ታፍሮና ተከብሮ የኖረ
ሃገራዊና ታሪካዊ ክብርህን በዓለም ፊት ያቀለለ በመሆኑ ክንድህን ማንሳት ያለብህ በዚህ ሃገር በቀል
የአረቦች የጭን ገረድ በሆነ የወያኔ አገዛዝ ላይ ነው ። ስለዚህም በሚቻለውና በማንኛውም መንገድ
በሰላም ይሁን በአመጽ በጓንዴ ይሁን በጎራዴ በቀለም ይሁን በፍራፍሬ አብዮት ስደት በቃኝ ብለህ
አገርህን ሳትለቅ ለውርደትና ለስቃይ አሳልፎ የሠጠህን መሪር ጠላትህ የሆነውን የወያኔ ቡድን አፈርድሜ
ለማስጋጥ ተነስ፤ ታጠቅ፤ ዝመት፤ የውርደት ማርከሻ መድሃኒቱ እንደአባቶችህ እንቢኝ በማለት ባንዳና
ቅጥረኛውን ማስወገድ ብቻ ነው። ይቻላል! ተችሏልም!! የግድ መቻልም አለበት!!
 ከዘላለም ባርነት የአንድ ቀን ነጻነት!!!

Friday 15 November 2013

የማለዳ ወግ … ጭንቁን ቀን እንዴት እንለፍ ! ? * የመረጃው ክፍተት የለያየን ግፉአን ዜጎችና ዲፕሎማቶች ነቢዩ ሲራክ

ጥላቻው እያደገ ሔዷል ፣ ሳውዲ አሰሪዎች ኢትዮጵያውያን የቤት ሰራተኞቻቸውን ድሮ ድሮ በአረቦች ዘንድ የተከበርን ፣ የታፈርን የእኛን የሃበሻ ልጆች “ጨካኞች ፣ የማይታመኑ !” እያሉ ጥላቻቸውን መገልጽ ጀምረዋል። November 14,2013 የወጣው አረብ ኑውስ Recent clashes make Saudis wary of Ethiopian maids በሚል ርዕስ ስር ሳውዲ አሰሪዎች ኢትዮጵያን ሰራተኞችን ለማባረር እየዛቱ ነው ! ይህ የአረብ ኒውስ ዘገባ በሹክሹክታ የምንሰማው ቁልጭ አድርጎ ያሳያል።
የሪያድ መንፉሃን ግጭት ተከትሎ ደም እድገብሮም ለኢትዮጵያን ተሰጠው ወደ ሃገር ቤት የመግባትን እድል ለመጠቀም ከሃያ ሽህ በላይ ኢትዮጵያውያን የሪያድ መጠለያወችን አጨናንቀዋል። እንዳውም በሪያድ የኢትዮጵያ አንባሳደር ቁጥሩን ወደ ሃያ ሶስት ሽህ እንደሆነ ረቡዕ November 14,2013 ለወጣው አረብ ኒውስ አስታውቀዋል። አሁንም በሽዎች የሚቆጠሩ ወደ መጠለያ ለመግባት እየጎረፉ ነው ። በመጠለያው የምግብና የሚጠጣ ውሃ እጥረቱ ደግሞ ኢትዮጰያውያኑ አጥር ሰብረው እንዲወጡ እያስገደደ ነው ተብሏል።
በጅዳ እና በተለያዩ የሳውዲ ከተሞች ያሉ ህጋዊ መኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው ኢትዮጵያውያንም የሚይዙት የሚጨብጡት አጥተው በቋፍ ላይ ናቸው ። በሪያድ እና በተለያዩ ከተሞቸ ባሳለፍነው ቅዳሜ በመንፉሃው ሁከት ጭካኔ የተቀላቀለበት በሃገሩ ነዋሪዎች ተወሰደ በተባለው እርምጃ ገና በመሰራጨት ላይ ያለው መረጃ ምስል ህጋዊ ሆነ ህገ ወጥ የሆነውን ሁሉንም እያስጨነቀ ነው ። እኔም እዚያው መንፉሃ ሆነውን የአይን እማኝ ከሰማሁ ወዲህ ከ16 አመታት በላይ የማውቃቸው ሳውዲዎች ይህን ፈጸሙ ለማለት ብቻ ሳይሆን በዚህች ሃገር ይህ መሰል ግፍ በሰው ልጅ ይፈጸማል ለማለት ተቸግሬያለሁ። እውነት መሆኑን ደጋግሜ ሳሰላስለው ደግሞ የሳውዲ ኑሮ እየጎረበጠኝና ተስፋየን እየሟጠጠው ሄዷል። ብዙዎች በዚህና በመሳሰለው የማሳደድ ችግር ምክንያት ወደ ሃገር መግባት ይፈልጋሉ ፣ በሪያድ ከመንፉሃ በተጨማሪ በኮንትራት ስራ የመጡና ለበርካታ አመታት በሳውዲ ነዋሪ የሆኑት ሳይቀሩ እንደ መንፉሃ ግፉአን በውድ የገዙትን እቃ በርካሽ እየሸጡና መኖሪያ ፍቃዳቸውን አሽቀንጥረው በመጣል ወደ መጠለያው እየገቡ ነው ።
“በመንፉሃ ቁጥራቸው የማይታወቅ ኢትዮጵያውያን ሞተዋል … ” በሚል ነዋሪው በሚሞግተውና መንግስት ” ሶስት ብቻ ነው የሞተው! ” ያላቸው ኢትዮጵያውያን ደም ፈስሶ በድርድርም ቢሆን ሳውዲዎች የጣሉትን ቅጣት አንስተው ህገ ወጥ ነዋሪዎች በፍላጎት እንዲገቡ ተፈቅዷል። ይህ ለሪያድ ነዋሪዎች የተሰጠው እድል በሁሉም ከተማ ላሉት ዜጎች ስለመስራቱ ማወቅ ባለመቻሉ ነዋሪው ተጨናንቋል። በመካ ያለው ከበድ እያለ መጥቷል። በጅዳ ከንደራ የሚፈራውን ያህልም ባይሆን በእለተ ሃሙስ November 14,2013 እኩለ ቀን ለግማሽ ሰአት የዘለቀ ፍጥጫ እንደ ነበር እለታዊው አረብ ኒውስ ጋዜጣ ከቀትር በኋላ ዘግቦታል። በጣይፍ ፣ በጀዛንና በአቅራቢያ የተለያዩ አካባቢዎችም ጉዳይ አሳሳቢ ነው ። ቢያንስ የመንግስት ሀላፊዎች መረጀ በመስጠት ሰውን ማረጋጋት ካልቻሉ ያየን የሰማነው የመንፉሃ አደጋ በከፋ መልኩ እንዳይጫር ስጋት አለኝ።
በጅዳ ቆንስል ምን እየተሰራ እንዳለ የሚታወቅ ነገር የለም ። እርግጥ ነው ስራ እየተሰራ ነው ። ፖስፖርት ይታደሳል ፣አዲስ ይሰጣል፣ ከአስር ሽህ በላይ ይሆናሉ ለሚባሉ በእስር ቤት ላሉት ሊሴ ፖሴ ይሰጣል፣ ሌላም ሌላ ስራ ይሰራል። ከዚህ አልፎ ከግቢው በመታመስ ላይ ላሉ ወደ አስር የሚጠጉ ያበዱትን ፣ ከሰላሳ በላይ የነሆለሉና የታመሙትን ጨምሮ ሁለት መቶ የሚጠጉ ዜጎች ጉዳይ መቋጫ አልተገኘለትም። ለወራት ሲንከባለል የቆየ ወደ ሃገር የማሳፈር ክትትል ምን ምን ላይ እንደ ደረሰ የሚታወቅ ነገር የለም። የቻለው ምግብ እና ውሃ ብሎም አንዳንድ አስፈላጊ ቁሳቁስ እያቀረበላቸው ይገኛል ። ከዚህ ባለፈ ሁኔታውን አይቶ እንባውን እየረጨ ከመሄድ ባለፈ ምንም መስራት አልቻለም ፣ አቅሙም የለውም! በርካታ ወገኖች እየሆነ ያለውን ለማወቅ ጉጉት አላቸው ። ያም ሆኖ የጅዳ ቆንስል የበላይ መረጃ መስጠትም ሆነ መቀበል አልፈለጉም። ወጌን በማስረጃ በአንዲት ማስረጃ ብቻ ላስረግጥ … !
ኢትዮጵያውያን እንደጨው ተበትነናል። ከቀናት በፊት ባሳለፍነው እሁድ ሰባት ኢትዮጵያውያን ታሳሪዎች ይዞ ከጀዛን ክልል ወደ ሽሜሲ አዲሱ እስር ቤት ሲጓዝ የነበረ አንድ የፖሊስ መኪና እኩለቀን ሊዝ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በደረሰበት አደጋ አራት ኢትዮጵያውያን መሞታቸውና ሶስት ያህሉ መቁሰላቸውን በሰማሁ ማግስት መረጃውን በትኩሱ ለማድረስ ተወካዮቻችን በስልክ ደውየ ሳጣቸው ከጭንቀቱ ጋር ውስጤ የተሰማውን ለመግለጽ እቸገራለሁ ። ነገሩ እንዲህ ነው …እሁድ ለሰኞ አጥቢያ በጅዳ መኮሮና አካባቢ እኩለ ሌሊት ላይ አንድ መረጃ ደረሰኝ “ኢትዮጵያውያንና እዚህ አገር ተወልደው ባደጉ የውጭ ዜጎች መካከል ሁከት ተቀስቅሷል! “የሚል ነበር። መረጃ ለማቀበል ለብቸኛ ተጠሪዎቻችን ስልክ ደወልኩ ። አይመልሱም። መረጃ አቀባዮቸን መልሸ ስደውል አካባቢው በጩኸትና ረብሻ ሲታመስ ሰማሁ። ደግሜ ወደ ለሃላፊዎች ደወልኩ ። ዋና ሃላፊው አቶ ዘነበ ከበደም ሆነ ምክትላቸው አቶ ሸሪፍ ኸይሩ ተንቀሳቃሽ ስልካቸውን አያነሱም ። ፖሊስ ደርሶ ረብሻው ተበተነ። አካባቢው መረጋጋት ያዘ ። መንፉሃን እያስታወስኩ በደረቁ ሌሊት በአይኔ እንቅልፍ ሳይዞር ነጋ … !
አይነጋ የለም ነግቶ ፣ ኢትዮጵያውያኑ የተያዙት ተይዘው የቀሩት ቤታቸው ተዘርፎ ድልድይ ስር ማደራቸውን በቦታው ሔጀ ተመልክቻለሁ። በግጭቱ የቅርብ ርቀት ተሸብረው ያገኘኋቸው የግጭቱ ተጎጅዎች ህክምና ያገኙ እንደሁ እና ጉዳዩንም ስልክ የማያነሱት የቆንሰሉ ሃላፊዎች ጉዳታቸውን እንዲያውቁላቸው አሁንም ወደ ሃላፊዎች ደወልኩ። አያነሱም ። ተጎጅዎችም ሌሊት ለእኔ እንደ ደወሉ ወደ ቆንስሉ ከሃያ ጊዜ በላይ ደውለው ስልኩን የሚያነሳ ስላጡ ወደ እኔ መደወላቸውን አጫወቱኝ ። ግራ ብጋባም ቢያንስ የሆነውን ሁሉ ለማስረዳት ተጎጅዎችን ወደ ቆንስሉ ለመውሰድ ወስኘ ሳማክራቸው ” አድርገህው ነው! ” አሉኝ ከነፍሰ ጡሯ እህት ተጎጅና ሁለት በግጭቱ የቆሰሉ የተደበደቡትን እና ወደ ስምንት የሚደርሱ እማኞችን ይዠ ወደ ጅዳ ቆንስል መስሪያ ቤት አመራሁ። በሙግት ወደ ግቢው ብንገባም ሃላፊውን እኔን ለማነጋገር እንደማይችሉ እና ስብሰባ ላይ መሆናቸው እንደ ምክንያት ተሰጠኝ። ሰውነቴ ተቆጣ ፣ “የእነሱን ስራ ስሰራ ለምን አይተባበሩኝም!” ራሴን ጠየቅኩ ፣ መልስ ግን የለኝም! ከማይጋነን መጉላላቱ በኋላ ዋና ሃላፊው አቶ ዘነበ ከበደ አማካኝነት በወረደ ትዕዛዝ የዲያስፖራዋ ሃላፊ ቆንስል ሙንትሃ እንዲያነጋግሩኝ ተደርጎ ቆንስሏን አግኝቸ አነጋገርኳቸው ። ለመኮረና ግጭት መረጃ አዲስ እንደሆኑ ገልጸው ለመረጃው አመስግናውኝ ቁስለኛና ተጎጅዎችን አስተዋውቄያቸው ወደ ስራየ ከመውጣቴ በፊት ማለት የፈለግኩትን በስጨት እንዳለኩ ተናገርኳቸው ! ቆንስል ሙንትሃ ባዩትና በሰሙት ተደናግጠው እዚያው እያለሁ በውስጥ መስመር ደውለው ለአቶ ዘነበ የጉዳዩን አሳሳቢነት አሰረዷቸው። ወደ ቆንስሉና ወደ ሃላፊዎች ስልክ ስደውል የማይነሳበትን እንቆቅልሽ ከማስረዳት ባለፈ በዚህ ሰአት በአንድ የስልክ ጥሪ በሚታጣ መረጃ ብዙ ጥሩም መጥፎም ሁኔታ ስለሚያስከትል የዜጎችን መብት ለማስከበር የተቀመጠ የመንግስት አካል ለመረጃ የራቀ መሆኑን አደገኛ አካሔድ ገለጽኩላቸው ። ብዙም ሳልቆይ ባለጉዳዮችን እዚያው ትቸ ወደ ስራየ አቀናሁ …
ከቀትር በኋላ የቆንስሉ ሃላፊ አቶ ዘነበን ጨምሮ ሶስቱም ዲፕሎማቶች የመኮረናው ግጭት ወደ ሚመለከታቸው የሽማልያ ፖሊስ ጣቢያ ማቅናታቸውን ሰምቻለሁ። በመኮረና ሆነ ተብሎ በወሰድኳቸው ተጎጅወች የሰማነውን በዜጎች ላይ የመቁሰልና የሞት አደጋ መከሰቱን ጠይቀው ከጀኔራል አዛዡ መልስ እንደተሰጣቸው ቆንስል ሙንትሃ ስልክ ደውለው ገልጸውልኛል። የፖሊስ አዛዡም ረብሻው በኢትዮጵያውያንና በቻድ ዜጎች መካከል ከሶስት ቀብ በፊት በተጀመረ መጠነኛ ጸብ ምክንያት እንደነበር መረጃ እንደነበራቸው ፣እሁድ ለሰኞ አጥቢያ ደግሞ ሁከቱ መከሰቱን እና ፖሊስ እንዳበረደው ማስረዳታቸውን ፣ በእለቱ ግጭት ተኩስ እንደ ነበር ነገር ግን በተኩሱ የቆሰለ እንደ ሌለ እንዳሰረዷቸው ፣ አምስት ያህል በድብድቡ የቆሰሉ እንጅ የሞተ ሰው እንደ ሌለ አስረግጠው ሲነግሯቸው በግርግሩ የታሰሩትን ኢትዮጵያውያን እንዳስጎበኟቸው ቆንስል ሙንትሃ ገልጸውልኛል። ሳውዲ ጋዜት በቀጣዩ ቀን Tuesday 12 November 2013 የመኮሮናውን ግጭት እንዲህ ብሎ አሽሞንሙኖ አቀረበው 57 held after Chadian-Ethiopian clash http://www.arabnews.com/news/475786 . እንግዲህ ከላይ ለማሳየት የሞከርኳቸው የመረጃ ግብአቶች በዲፕሎማቶች ዙሪያና በጭንቀት ላይ ስላለው ነዋሪ መጠነኛ መረጃ በመስጠት እየሆነ እና እየተሰራ ያለውን በትክክል ካሳየ መልካም ነው ።
መሬት ላይ በአይናችን የምናየውን እንዲህ ሆኖ እያለ እውነት የሚጣረስ ፕሮፖጋንዳ መሰል መረጃ ደግሞ ከመንግስት ቴሌቪዥንና ራዲዮ ሲነገር እየሰማን ነው። መንፉሃ ላይ ፍጅቱ ሊጀመር ሲዳዳው ፍጥጫውን ማርገብ ያልቻሉት ዲፕሎማቶች መንፉሃ በደም ከተበከለች በኋላ ዜጎች ያለ መቀጮና እስራት ወደ ሃገራቸው እንዲገቡ ስምምነት ማድረጋቸው እውነት ነው። ያም ሆኖ የመንግስት መገናኛ ብዙሃን እንደሚነግሩን ስራውን በቅንጅትና በማቀላጠፍ እየሰሩ አይደለም የሚል መረጃ ከተጨባጭ ምንጮች ይደርሰኛል።
ከቀናት በፊት አንድ ጽነፈኛ የምለው የፊስ ቡክ አፍቃሬ ኢህአዲግ ወዳጀ Ramatohara Dertogada ችግሩ ሲከሰት የሰጣቸው ለወገን ተቆርቋሪነት የታየበት አስተያየት ተቀይሮ ተመለከትኩት ። “… ሳውዲን ጨምሮ በሁሉም ዓረብ ሀገራት በዜጎቻችን የሚያደርሱት በደልና ግድያ ሆን ተብሎ የተቀነባበረ የጥላቻ ሴራ ነው። … መንግስት በዜጎቹ የሚደርሰው በደል እንዲቆም ህጋዊ የሆነ አቋም ለዓለም ማህበረሰብ ያቀርባል። በአሁኑ ስዓት ለዜጎቹ ግዝያዊ የሆኑ የነብስ አድን ስራዎችና የዲፕሎማሲ ማግባባቶች እየሰራ ነው። ” ይላል! ይህን ሃሳብ ወዳጀ አለመጻፉን ብረዳም በሃሳቡ መስማማት መደገፉን ጠረጠርኩና የተዛባ መረጃ እየሰጠ ያየሁትን የኢትዮጵያ ቲቪን ረገምኩ! እንደተባለው ስራው እየተሰራ መሆኑ እውነት ቢሆን ምንኛ ደስ ይል ነበር! ግን በመንግስተ መገናኛ ብዙሃን ” በሳውዲ የሚገኙ ዲፕሎማቶች 24 ሰአት እየሰሩ ነው! ” የተባለው መረጃን ተሰራ ከተባለው ስራ ጋር ስናነጻጽረው እውነት አይደለም! ባሳለፍናቸው ቀናት መረጃን ለማግኘት በየቀኑ ወደ ሪያድ እደውላለሁ። በርካታ መረጃዎችን ለመስብሰብ ሞክሬያለሁ ፣ በመጠለያ ያሉት በርሃብና በውሃ ጥም እየተቸገሩ ነው። ማረጋገጥ አልተቻለም እንጅ አዲስ የሞት ዜናም አለ!
አሁን አሁን በመላ ሃገሪቱ በተለይም በሪያድ የሚሰማው ደስ አይልም። ረቡዕ ከቀትር በኋላ ሪያድ መንፉሃ የከፋ ችግር ተከስቶ ነበር ። ለጊዜው በረድ ቢልም የተጎዳ ሰው አለ ….መካ ውስጥ ወደ ሃገራችን ስደዱን ባሉ ዜጎቻችን መካከል ሁከት ሊቀሰቀስ እንደ ነበር ተጨባጭ መረጃዎች ደርሰውኛል። የሳውዲ ጋዜጦችም ይህንን አረጋግጠዋል። የሪያድ ዲፕሎማቶች ነዋሪውን በማቀናጀት ማስተባበሩ ላይ ዳተኛ መሆናቸው ሲያስተዛዝብ ፣ በጅዳ ዲፕሎማቶች ሌላው ቢቀር ነዋሪውን ሰብሰበው መረጃ ሊሰጡት አልፈቀዱም። በቆንስሉ መጠለያው እየተርመሰመሱ አንጀት ስለሚበሉት ተፈናቃይ ሰራተኞችም ሆነ “ከሃገር ይውጣ !” በተባለው ህጋዊነመኖሪያ ፈቃዱን ማስተካከል ባልቻለው ዜጋ ዙሪያ እንዲመክር እንዲዘክር የሚሰሩት ስራ የለም! ይህን ለማጣራት ከቀናት በፊት ወደ ጅዳ ቆንስል ጎራ ብየ ነበር ። ጠባቂው ወንደሜ የቀድሞው የህዝባዊ ሃርነት ግንባር መድፍ አገላባጭ ታጋይ “ገሬ! ” አትገባም አለኝ ። ምክንያቱን ስጠይቀው ” አቶ ዘነበ እኔ ሳልፈቅድ አታስገባው ብለውኛል !” ሲል መለሰልኝ ። ከብዙ ሙግት በኋለ በአማላጅ ገባሁ ። በጅዳና አካባቢው ያለ ነዋሪ መረጃ ተጠምቷል ፣ ሃላፊዎች መረጃ መስጠት ቀርቶ መረጃ ለነዋሪው ለመስጠት የምንሞክረውን ክብራችን እየነኩ እያሳዘኑን ነው! እውነቱ ይህ ነው! ብዙ አልልም ! ብቻ በሳውዲ አረቢያ ሪያድና ጅዳ የሚገኙት የኢትዮጵያ መንግስት ኢንባሲና ቆንስል መስሪያ ቤቶች እያደረጉት ያለውን እንቅስቃሴ መረጃ በመስጠት እንኳ ለህዝብ ማስረዳት ፣ማረጋጋት እንዳይቻል በራቸው በብረት ሰረገላ ተከርችሟል። በሩን ለማስከፈት ተደጋጋሚ ሙከራ ቢደረግም አልተቻለም!
የሳውዲ በርካታ ክልሎች የተለያዩ መረጃዎችን አገኛለሁ። መረጃዎችን በተገቢ መንገድ ለመጠቀም እሞክራለሁ። ከሪያድ መንፉሃ ከተሰደው እርምጃ ውጭ በቀሩት የሃገሪቱ ክፍሎች በኢትዮጵያውያን ላይ ማንኛውም ህገ ወጥ እንደሚያዘው ይያዛሉ እንጅ የተለየ ተጽዕኖ ወይም ማሳደድ ተፈጠረ ሲባል አልሰማሁም። ከምህረት አዋጁ ማለቂያ ከፍተሻው የመጀመሪያ ቀን ጀምሮ በሪያድ መንፉሃ እየሆነ ስላለው የአይን እማኞችን በአካል ከማግኘት ጀምሮ በስልክ እና በተንቀሳቃሽ ምስል ሳይቀር መረጃዎች ይደርሱኛል። አሁን አሁን ቁጥራቸው ወደ ሃምሳ ሽህ ይዘልቃሉ የሚባሉት ዜጎች ኢትዮጵያውያን በመላ ሳውዲ ይገኛሉ ተብሎ እየተገመተ ነው ። ይህ ቁጥር ቀላል አይደለም ። ጉዳዩ የሃገር የህዝብ ጉዳይ በመሆኑ ዜጎችና የመንግስት ተወካዮች ዘር ፣ ሃይማኖት እና ፖለቲካ ሳይለያየን በጋራ መረጃን ከመለዋወጥ ባለፈ ብዙ መንገድ ሂደን በአደጋ፣ በስጋትና በጭንቀት ላይ ያሉ ወገኖቻችን ብንታደጋቸው መልካም ነበር ። ባሳለፍነው ሳምንት በዘር በሃይማኖትና በፖለቲካ ለየቅል የሚያነጉደው በመላ ሳውዲ አረቢያ ብቻ ሳይሆን በመላ አለም በሚገኙ ወገኖች መሆናቸውን እንደኔ የታዘበ ካለ አላውቅም። ያም ሆኖ መንግስት በአዋጁ ማብቂያ የመጨረሻ ቀን በሰጠው መግለጫ “የቤት ለቤት ሰበራ አይኖርም!” ብሎ ነበር ። ይህ የወጣው መመሪያ ግን በእኛ ላይ አልሰራም። መመሪያው በመንግስት ፈታሾች ለመጣሱ እና በመንፉሃ ለተወሰደው እርምጃ በመንፉሃ በዜጎቻችን ከዚህ ቀደም የተሰሩ ወንጀሎች እንደ ምክንያት ቢቀርቡም ተንቀን ለተወሰደብን ከሰብዕና የወጣ ነውረኛ ወንጀል ግን ብዙዎች አብረን በህብረት ደወርጊቱን በማውገዝ የተሳካ ድምጽ መሰማቱን ተመልክቻለሁ !
በመንፉሃ ዳግም ሁከት ተቀስቅሶ ከበረደ ወዲህ በሪያድ መጠለያ አና በአካባቢው የመረጃ ክፍተት የፈጠረው ከባድ ጭንቀት ነግሷል። ይህ ጭንቀት በሪያድ ከሴቶች እና ከወንዶች ጊዜያዊ መጠለያ ቤት ጀምሮ ከውስጥም ከውጭም አገር ቤትን ባካለለ መልኩ እየተስፋፋ መሆኑን ከሚደርሱኝ መረጃዎች ለመረዳትና ለማወቅ ችያለሁ። በተለይም ከመጠለያ ፣ ከእስር ቤት እና ከነዋሪው ከሚበተኑትና ከሚደርሱት መረጃዎች አንጻር ነዋሪው ችግሩን እየለጠጠው ፣ ችግሮች በራሳቸው እያደጉ የሚያዝ የሚጨበጥ እንዳይጠፋ ስጋቴ ከብዷል ! የከበደውን አደጋ በመረጃ ልውውጥ የተደፋብንን የጭንቀት ደመና ለመግፈፍ መጠቀም ከቻልን እድሉ አላለቀም! በአሁኑ ሰአትም የመረጃው ክፍተት የሚታይበት የመንግስት ዲፕሎማቶችና የነዋሪው ግንኙነት መጠገን የማይቻል አይደለም ። ይቻላል! እናም የመፍትሄ ሃሳብ ልጠቁም …
እኔም እንደ መፍትሔ ሃሳብ በጅዳና ሪያድ የምትገኙ መንግስት ተወካዮች እንደ ከዚህ ቀደሙ በድርጅታዊ አወቃቀር ሳይሆን ሁሉም አትዮጵያዊ እንደ ዜጋ የሚሳተፍና የሚመክርበት ስብሰባ በአስቸኳይ መጥራት ! ሌላው በዙሪያው የምንገኝ ወገኖች በማህበራዊ ገጾች አምድ ላይ የመጻፍ መብታችን የተጠበቀ ቢሆንም በየስርቻው እየተነዛ የስነ ልቦና ጭንቀት እየለቀቀ ያለው ያልተጨበጠና ያልተረጋገጠ መረጃ ከማሰራጨት መቆጠብ ይኖርብናል ! ጠቃሚ መረጃዎች ካሉ ከላይ ይቋቋም ዘንድ ሃሳብ ላቀረብኩት ኮሚቴ በመላክ የመረጃ ክምችት ከመፍጠር ባለፈ ትክክለኛውን መረጃ ለህዝብ አንዲደርስና በጥንቃቄ እና በተረጋጋ ሁኔታ እንድንመራ ይረዳናል።
ሌላውና ዋንኛው ስራ መሰራት አለበት ብየ የማምነው ወደ ሃገር ለማሳፈር የሚደረገው መንገድ እስኪስተካከል ድረስ ማንኛውም ስደተኛ ሰልፍ ማድረግና ወደ ንብረት ሰበራ አመጽ እንዳይሸጋገር ነዋሪውን የማረጋጋት ስራ መስራቱ ግድ ይላል !
መላ ካልተባለ አጠቃላይ ሁኔታው ጥሩ አይደለም ፣ ልዩንትን አስወግደን በህብረት የማንሔድ ከሆነና አሁንም በተቃራኒ ጥላቻ የምንሔደው አካሔድ ፍጹም አዋጣም! ይህ አደጋም ከዜጎች አልፎ በሳውዲና በኢትዮጵያ የቆየ ግንኙነት ታሪክ ትልቁን ስህተት ወደ መስራቱ እንዳያስኬደን ስጋት አለኝ ! ችግሩ ሳያንሰን በግፉአን ዜጎችና በዲፕሎማቶች የሰመረ ግንኙንት እጦት ከሚኮላሸው የነፍስ አድን ህብረት ክፍተት ጣጣ አንድየ ይሰውረን !
የግርጌ ማስታዎሻ :
በመላ አሜሪካና አውሮፖ ብሎም በተለያዩ አለማት የምትገኙ ኢትዮጵያውያን በሳውዲ አረቢያ ላለው ወገን ድጋፍ ስታደርጉ ማየት ለወገን ያላችሁን ፍቅር ያሳያልና ደስታየ ወሰን አጥቷል። የሳውዲ አረቢያን ባንዴራ ነገር ግን አደራ ! ይህ በአረንጓዴ መደብ ላይ በነጭ ቀለም የቁርአን ቃል የሰፈረበት ባንዴራ በመሆኑ በክብር ልንይዘው ይገባል! በስህተት አለያም በጥላቻ ስሜት ተገፋፍተን ለማቃጠልና ለመቅደድ ብንሞክር መላ የአለምን ሙስሊም አስከፍቶ ወገኖቻችን ወደ ሃገራቸው እንዳይሄዱ ከሚፈጥረው ጫና በተጨማሪ በዜጎቻችን መብት ይከበርልን ጥያቄ ዙሪያ ልናጣ የምንቸለው ድጋፍ ማስተዋል ግድ ይለናል! ይህን አልፈን ከሔድን ተጠቃሚ ካለመሆናችን በተጨማሪ ጸብ ቅያሞታችን ከሳውዲ ጋር ብቻ ሳይሆን ከመላ የሙሰሊም እምነት ተከታዮች ጋር ስለሚሆን ጥንቃቄ ያስፈልጋል! በፍጹም ጨዋነት የሚካሔደው ሰላማዊ ሰልፍ ለማየት ጓጉቻለሁ!
ከምንም በላይ ደግሞ ከመጣብንን መከራ አንድ አምላክ ይጠብቀን!

ሰበር ዜና – ወያኔ የሰማያዊ ፓርቲ መሪዎችን አሰረ፤ ሰልፉም እንዳይደረግ ከለከለ፤ በሰልፉ ላይ የነበሩ የአንድነት ፓርቲ አባላትም መታሰራቸው ታውቋል

የሰማያዊ ፓርቲ ዛሬ በጠራው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ለመሳተፍ የወጡ የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮችና አባላት ታሰሩ፡፡ ከጽ/ቤታቸው ተነስተው ወደ ሰላማዊ ሰልፉ ቦታ ሲሄዱ 4 ኪሎ የኦሮሚያ ሲቪል ሰርቪስ ቢሮ ጎን በሚገኘው ወታደራዊ ገራዥ መታሰራቸውን ዘጋቢያችን ከቦታው አድርሶናል፡፡ ከመታሰራው ቀደም ብሎ ከፖሊስ ጋር እንሂድ አትሄዱም በሚል ጭቅጭቅ ላይ እንደነበሩ ሰምተናል፡፡ ሌሎች የፓርቲው አባላትና አመራሮች ተበታትነው ወደ ሳውዲ አረቢያ ኤምባሲ እየሄዱ እንደሆነ ለማወቅ ችለናል፡፡
ዘግየቶ በደረሰን ዜና ደግሞ በኤምባሲው በተገኙ ሰዎች ላይ ፌዴራል ፖሊስ ከፍተኛ ድብደባ ማድረሱ ታውቋል፡፡ በተጨማሪም በሰልፉ ላይ የነበሩ የአንድነት ፓርቲ አባላትም መታሰራቸው ታውቋል፡፡
በተለይ አንዲ ሴት ክፉኛ በመመታቷ ለህይወቷ እንዲያሰጋ ለማወቅ ችለኛል፡፡ አንድ አስተያየት ሰጪ በበኩላቸው “በሰው አገር ወገኖቻችን ላይ የደረሰውን ለመቃወም ወጥተን ተመሳሳይ ስቃይ አስተናገድን” ብለዋል፡፡

Thursday 14 November 2013

ታላቅ ሀገራዊ የተቃውሞ ጥሪ!! ሰማያዊ ፓርቲ ሰላማዊ ሰልፍ ጠራ!!!

ሰሞኑን የሳውዲ አረቢያ መንግሥት በኢትዮጵያዊያን ላይ እየፈፀመ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት በመቃወም ሰማያዊ ፓርቲ ታላቅ የተቃውሞ ጥሪ አስተላልፏል፡፡በመሆኑም በዜጎቻችን ላይ እየደረሰ ያለውን ኢሰብዓዊ ድርጊት ለማስቆምና የዜጐችን ህይወት ለመታደግ እንዲሁም ዜጐቻችን በአፋጣኝ ወደ ሀገራቸው የሚመለሱበትን ሁኔታ መንግሥት እንዲያመቻች እና በተጨማሪም በዜጐቻችን ላይ ለደረሰው የአካል መጉደል፣ እንግልት፣ ድብደባ፣ አስገድዶ መድፈርና የህይወት መጥፋት ኃላፊነቱን የሚወስዱ አካላት ተጠያቂ እንዲሆኑ፤ ለተጐዱ ወገኖቻችንና ቤተሰቦቻቸውም አስፈላጊው ካሳ እንዲደረግላቸው ፓርቲያችን አበክሮ እያሳሰበ፤ የብሄራዊ ክብርና የወገኖች ስቃይ የሚያሳስባቸው አካላት በሙሉ በዚህ ታላቅ የተቃውሞ እንቅስቃሴ ላይ እንዲሳተፉ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡Ethiopia's Semayawi party (blue party)
የተቃውሞ እንቅስቃሴ አፈፃፀም፡-
1. በዜጐቻችን ላይ የአካል መጉደል፣ እንግልት፣ ድብደባ፣ አስገድዶ መድፈርና የህይወት መጥፋት ያደረሰው የሳውዲ አረቢያ መንግሥት ኢምባሲ በሚገኝበት ቦታ አርብ ከረፋዱ 5፡30 ሰዓት ጀምሮ የሚደረግ የተቃውሞ ሰልፍ፣
2. ከአርብ ጠዋት ጀምሮ እስከ እሁድ ማታ ድረስ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሀዘን ልብስ (ጥቁር ልብስ) በመልበስ በግፍ ለሞቱና ለተንገላቱ ወገኖቻችን ሀዘናችንን መግለፅ፣
3. የእምነት ተቋማት አርብ በመስጊድ በጁምአ ሥነ ሥርዓት ላይ እና ቅዳሜና እሁድ በአብያተ ክርስቲያናት የፀሎት ሥነ ሥርዓቶች ላይ ወገኖቻችንን በፀሎት እንዲታሰቡ፣
4. ቅዳሜ በሚደረገው የኢትዮጵያና የናይጄሪያ የእግር ኳስ ጨዋታ ላይ ተጫዋቾቻችን ጥቁር ሪቫን በክንዶቻቸው ላይ አጥልቀው እንዲጫወቱ፣ እንዲሁም መላው ደጋፊ ጥቁር ጨርቆችን በመያዝ ወይም ልብስ በመልበስ ሀዘኑንና ቁጭቱን እንዲገልፅ፣
በፓርቲው የተወሰነ በመሆኑ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች፣ ሲቪክ ተቋማት፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፣ ፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ዓለም አቅፍ ማኅበረሰቡ በአጠቃላይ መላው ኢትዮጵያዊና የኢትዮጵያ ወዳጆች በጠራነው የተቃውሞ ሰልፍና እንቅስቃሴዎች ላይ በመገኘት ከግፉአን ወገኖቻችን ጐን መቆሙን እንዲያረጋግጥ በአፅንኦት እንጠይቃለን፡፡
♦♦♦♦♦♦♦♦♦♦♦♦♦♦♦♦♦♦♦♦♦♦♦♦♦♦♦♦♦♦♦♦♦♦♦♦♦♦♦♦
የወገኖቻችን ሰቆቃ እስኪያበቃ በፅናት እንታገላለን!!!

ብሄራዊ ውርደት፤ የምንመጻደቅበት ‘ሌጋሲ’

ወገናችንን በጥይት ሲደፉት በራሱ ላይ አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ባንድራችንን ጠምጥመውበታል[1]። ጭካኔ በተሞለበት መንገድ የተገደለው ይህ ኢትዮጵያዊ አስከሬኑም በሰላም አላረፈም። በአካሉ ላይ ያረፈውን ጨርቅ በሴንጢ እየቆራረጡ በሰብአዊ ፍጡር ላይ ሊደረግ የማይገባውን ሁሉ አደረጉበት። ድርጊቱ ናዚዎች በኦሽዌትስ ይፈጽሙት የነበረውን አሰቃቂ ግፍ ያስታውሰናል። በ21ኛው ዘመን እንዲህ አይነቱ ክስተት ይደገማል ብሎ የሚያስብ የለም። እነሆ ሳውዲ አረቢያ በኢትዮጵያውያን ላይ እየፈጸመችው ነው። በስውር ሳይሆን በግልጽ። እንደ ኦሽዊትስ በታጠረ የማጎርያ ካምፕ ሳይሆን በአደባባይ።
ሰው ከሞተ በኋላ ለምን ሙት አካሉን ማሰቃየት አስፈለገ? ምን አይነት ጭካኔ ነው? ምን አይነትስ ጥላቻ ነው? ለሳውዲዎች ግማሽ ፈረንሳይን የሚያህል መሬት ሰጥተናቸው የለም እንዴ? ሀጥያታችን ምኑ ላይ ነው ታዲያ? አስከሬኑን ውሻ፣ ውሻ ሲሉ ሲሳለቁበት ከማየት በላይ የሚያም ነገር የለም።  በአደባባይ እንደዋዛ የተጣለው አስከሬን በእርግጥ የዉሻ አስከሬን ቢሆን ኖሮ የእንስሳ ተከራካሪዎች  አለምን ቀውጢ ባደረጓት ነበር።
መገናኛ ብዙሃን እና ማህበራዊ ድረ-ገጾች ይህንን ጉዳይ በስፋት ቢዘግቡትም፤ አለም አቀፉ ህብረተሰብ ግን ዝምታን መርጧል። በዚህ በሰለጠነ ዘመን፤ እንደ እንስሳ እየታደኑ ከሚያዙትና ከሚገደሉት ወገኖች ውስጥ አንድ አሜሪካዊ ዜጋ ቢገኝበት ኖሮ ትርምሱ ምን ደረጃ ላይ እንደሚደርስ እናይ ነበር። የኛስ ነብስ የሰብአዊ ፍጡር ነብስ አይደለችም እንዴ? ስንቀጠቀጥ፣ ስንታረድና ስንገደል የሚፈሰን ደም ከሌላው ዜጋ የተለየ ደም ነው? ግፉ ለምን በኛ ላይ ብቻ በረታ? ሌላ ዜጋ ሲገደል አላየን። እየተሳደዱ የሚታጎሩት ሁሉ ኢትዮጵያዊ ናቸው። ይህ ሁሉ ግፍ እና መከራ ለምን በኢትዮጵያዊያን ላይ ብቻ? ድህነታች የዜግነት ክብራችንን አስነጥቆን ይሆን? እርግጥ ነው። የገንዘብ ድሆች ልንሆን እንችላለን። የአስተሳሰብና የስነ-ምግባር ድሆች ግን አይደለንም።
ችግሩ ያለው ሌላ ቦታ ነው። ብሄራውነት የሚሰማው መንግስት፤ ብሄራዊ ክብራችንንና ማንነታች የሚያስመልስ። በአለም አቀፍ መድረክ የሚያስከብረን ጠንካራ አካል ማጣታችን ነው የውርደታችን ምክንያቱ።
እንግዲህ ይህ ነው አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ የተረከቡት ቅርስ እና ውርስ። ይኸው ነው ገዢው ፓርቲ የሚመጻደቅበት ‘ሌጋሲ’። በምእራብ አፍሪካ ኮሌጆች የኢትዮጵያ ታሪክ እንደኮርስ ይሰጣል። የአድዋ ገድል፣ የጸረ-ቅኝ ግዛት ተምሳሌት፣ የነ ማርክስ ጋርቤይ፣ የነ ክዋሜ ንክሩማ፣ የነ ጆሞ ኬንያታ ለነጻነት ትግል መነሳሳት ከኢትዮጵያ ታሪክ ጋር ተቆራኝቶ በታሪክ ይዘከራል። ላለፉት 20 አመታት የተፈጠረው ክስተት ግን ይህንን ሁሉ መልካም ስም ድራሹን እያጠፋው ይገኛል። የተስፋይቱ ምድር እያሉ የሚጠሩዋት ራስ ተፈሪያን  የዛሬዩቱን ኢትዮጵያ የውርደት ታሪክ  እንዴት እንደሚያዩት እንጃ። ለአፍሪካ ነጻነት ተምሳሌት የሆንን ሰዎች ዛሬ ስደትን እንደመፍትሄ ለመውሰድ ተገደድን። በስደቱ ብቻ ሳያበቃ ሰብአዊነት በማይሰማቸው አካላት እነሆ ብሄራዊ ውርደትን እየተከናነብነው እንገኛለን።
እ.ኤ.አ. በ2004 የደች ንግስት ቢያትሪክስ ታይላንድ ተጉዛ ነበር። ቢያትሪክስ ወደ ታይላንድ የተጓዘችበት ዋነኛው ምክንያት በአደንዛዥ እጽ ዝውውር ታስረው የነበሩ ሁለት ሆላንዳውያንን ለማስፈታት ነው። አርባ እና ሃምሳ አመት ተፈርሮባቸው የነበረው እነዚህ ዜጎች በንግስቲቱ ጉብኝት ወቅት እንዲፈቱ ተደረገ።  የታይላንድና የሆላንድ የኢኮኖሚ ግንኙነት በኢትዮጵያ እና በሳውዲ አረቢያ ካለው የንግድ ትስስር በልጦ አይደለም። ንግስቲቱ በባዶ እጅዋ ወንጀለኛ ዜጎችዋን ማስፈታት ቻለች። ለዜጎችዋ ክብር ስለነበራት። በርግጥ ወንጀል ሰርተዋል። ቅጣቱን እኛው እንስጣቸው ብላ ዜጎችዋን ይዛ ተመለሰች ንግስት ቢያትሪክስ። ሳውዲ አረቢያ የኔዘርላንድን ቆዳ ስፋት በእጥፍ የሚበልጥ መሬት ከኢትዮጵያ ተችራለች። በወንጀል ሳይሆን ይልቁንም በጉልበት ስራ የተሰማሩ ዜጎቻችን የሚፈጸምባቸውን ግፍ ለማስቆም አንድ ሄክታር መሬት ብቻ በቂ ነበር። ሳውዲ በኢትዮጵያ ከ200,000 በላይ ሄክታር ለም መሬት ይዛለች።  ለብሄራው ውድቀታችን እና ውርደታችን ዋነኛው ምክንያት የዜጎቹን ክብር የሚያስቀድም ብሄራዊ  መንግስት ስላጣን እንጂ በዚህ ብቻ ሳውዲን ማስፈራራት ይቻል ነበር።
በሳውዲ ያለው ኢትዮጵያዊ ከ30 ሺህ በላይ ይገመታል። በጉልበቱ ጥሮ እያደረ ያለን ዜጋ ህገወጥ እያሉ ያሳድዱታል። እነሱ ግን በሃገራችን ላይ  እንደአንደኛ ዜጋ በነጻነት የመኖር መብት ተሰጥቷቸዋል። ለሳውዲ ባለሃብቶች የተሰጠው ለም መሬት ለነዚህ ዜጎች ቢሰጥ ኖሮ፤ ወገኖቻችን ባልተሰደዱና ባልተዋረዱ ነበር። 
የኛ ትውልድ፤ ሀገር አልባ፣ ዜግነት አልባ ትውልድ። ከዚህ በላይ የሆነ ብሄራዊ ውርደት የለም።
ጋዜጠኛ ነብዩ ሲራክ ከሳውዲ በላከው ማስታወሻ እንዲህ ይላል፤…
…የእኛን መያዝ የተመለከቱ የሳውዲ ወጣቶች (ሸባቦች) ሚስት እህቶቻችን ይደፍራሉ፣ ንብረታችን ይዘርፋሉ!  ይህ ለሶስት ቀናት ሲቀጥል የደረሰልን የለም! ኢንባሲ ደወልን ምንም ማድረግ አንችልም ይሉናል፣ አንተም ድምጻችንን ታሰማናለህ ብለን ብንደውልልህ ፈራህ መሰል አታነሳልንም! የት እንድረስ? ምን እናድርግ?  ንብረታችን እየተዘረፍን ሴቶቻችን  እየተደፈሩ ዝም ብለን ማየት ነበረብን?  ይህን በመቃወም ሻንጣና ቤተሰቦቻችንን  ይዘን ወደ ሃገራችን ስደዱን ነው ያልናቸው“  የሚል እየተቆጣና ድምጹን ከፍ እያደረገ መልስ የሰጠኝን አንድ ወንድም መጨረሻችሁ ምን ሊሆን ይችላል ? አልኩት “… ወደ ሃገራችን ከነሚስት እህቶቻችን ይውሰዱን ነው የምንለው! ያለበለዚያ መንፉሃን እና ሚስት እህቶቻችን አንለቅም! ገድለው ያስለቅቁን” ሲል ክችም ያለ መልሱን ሰጥቶ ስልኩን ጀሮየ ላይ ዘጋው…
በርግጥ ድርጊቱ አዲስ አይደለም። በአረብ ሃገር ያሉ ኢትዮጵያውያን ሁሌም ይታደናሉ፣ ይደበደባሉ፤  ይገደላሉ፤  እህቶቻችን በግፍ ይደፈራሉ። በባርነት ዘመን እንደሰማነው ሁሉ፤ አሳዳሪዎቻቸው እንደ እቃ ይዋዋሱዋቸዋል። ሲከፋቸ ደግሞ የፈላ ውሃ በቁማቸው ይደፉባቸዋል። ይህ ሁሉ ሲሆን አቤት የሚልላቸው፤ መብታቸውን የሚያስከብርላቸው መንግስት የለም። ሸዋዬ ሞላን የጋዳፊ ቤተሰቦች በቁምዋ ሲይቃጥሏት ይጮህ የነበረው ዲያስፖራው ነበር። ጋዳፊን የነቀለው የሊቢያ አብዮት ሲፋፋም፤ በሊቢያ ነዋሪ የነበሩ የውጭ ዜጎች በየኤምባሲያቸው ሲጠለሉ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን መግቢያ አጥተው ነበር። የኋላ ኋላ በሱዳንና በናይጄርያ ኤምባሲዎች እንዲጠለሉ ተደረገ። በግብጽና በሶሪያም ተመሳሳይ ክስተቶች ተፈጽሟል። በዱባይና በሊባነን በቤት ሰራተኝነት ተቀጥረው ይሰሩ የነበሩ ሴት እህቶቻችን ላይ ያላግባብ የሞት ፍርድ ሲፈረድ፤ ይከራከሩ የነበሩት ኢትዮጵያውያን የሲቪክ ማህበራት ናቸው። የዜጋውን መብት የሚያስቀድም ብሄራዊ መንግስት ቢኖረን ኖሮ እንዲህ ባልተደፈርን ነበር።
አንድ የዚህ ሰለባ የሆነ ወገናችን በፌስቡክ ገጽ ላይ እንዲህ ብሎ ጽፏል።
መንግስታችን‘ ኢትዮዽያውያን አርሶአደሮችና ነባር ነዋሪዎችን ከቀያቸው እየነቀለና እያፈናቀለ ለም መሬታችንለሳዑዲ ባለሃብቶች በመናኛ ዋጋ ይቸበችባል። መሬታቸውን በወያኔ የተነጠቁ ወጣቶቻችን ስራ ፍለጋ ወደ ሳዑዲይሰደዳሉ። በአፀፋው ዐረቦች የተሰደዱ ኢትዮዽያውያን ይገድላሉ። የሳዑዲ ባለሃብቶች ግን መሬታችን ይዘውበገዛ ሀገራችን እንደፈለጉ ይፈነጫሉ። የኢትዮዽያ ‘መንግስት በችግር ላይ ካሉ የኛ ዜጎች ይልቅ ለሳዑዲባለሃብቶች ደህንነት የሚጨነቅ ይመስላል። በእውነት እንደው መቼ ነው ለኛ ደህንነት የሚቆረቆር መንግስትየሚኖረን?
እርግጥ ነው። መንግስታችን ለዜጋው ግድ አይሰጠውም። ሲጀመር ዜጋው ከሀገሩ እንዲሰደድ ያደረገው ብልሹ የሆነ ስርአቱ ነው። እርግማን ይመስል ወገናችን በገዛ ሀገሩ የሚደርስበት በደል በስደት ከሚደርስበት ግፍ አይተናነስም። እዚህም ስቃይ እዚያም ስቃይ። የዘመኑ ወጣት በሁለት ጎን በተሳለ ሰይፍ ገፈት ቀማሽ…።
The suffering of Ethiopians in Saudi Arabia
የሃይሌ ገሪማን  ’ጤዛ’ ፊልም ያስተውሏል? አንበርበር ከጀርመን ሃገር ክብሩን እና አንድ እግሩን ይዞ እትብቱ ወደተቀበረባት ቀዬ ተመለሰ።  አንድ እግሩን በኒዮ-ናዚዎች አጣ። ክብሬ ባላት ሀገሩ የገጠመው መከራ ደግሞ ሊሸከመው የማይችለው ነበር። በትውልድ መንደሩ ወገን ወገኑን እያሳደደ ሲደፋው ሲያይ፣ አንድ እግር ያሳጣው የኒዮ ናዚ ጉዳይ አላሳሰበውም። ወገን ሲጨንቀው ይሰደዳል። ታዲያ የትኛውን እንኮንን? የሳውዲውን? አ’ይ እሱ በራሱ ስራ ይጨነቅበት። የኛው ግን ሊያሳስበን ይገባል። ለም መሬታቸውን እየተቀራመቱ ማፈናቀላቸው ሳየንስ፤ ወጣቱ እንዳለው  ‘ከውጭ የገቡ እንግዶች መልሰው እኛኑ ባይተዋር እያደረጉን ነው።’
እ.ኤ.አ በ1980ዎቹ በርካታ የኩባ ዜጎች የፊደል ካስትሮ መንግስትን በመቃውም ወደ አሜሪካ ገብተዋል።  አሜሪካ የገቡት ኩባውያን የካስትሮን መንግስት ከማውገዝ አርፈው አየውቁም ነበር። ካስትሮ ከ 20 አመታት በኋላ አሜሪካን ለመጀመሪያ ጊዜ ሲጎበኙ፡ “የአሜሪካ መንግስት የኩባ ስደተኞችን መብት እየገፈፈ ነው።”  የሚል ወቀሳ ነበር ያቀረቡት። እናም በስደት ያሉ ኩባውያን መብት እንዲጠበቅ ከአሜሪካ መንግስት ጋር ድርድር ያዙ።  ካስትሮ እዚህ ላይ እንደግለሰብ ሳይሆን እንደመንግስት ነው የሚያስቡት።
የኛዎቹ ግን እንደመንግስት ሳይሆን አሁንም እንደግለሰብ ነው የሚያስቡት። በጅምላ የሚጠሉት ዲያስፖራ ላይ በቀላቸውን እየተወጡ ያሉ ይመስላል። ዛሬ በውጭ ያሉ ወገኖች የሚጮሁትን ያህል እንኳን በስልጣን ላይ ያሉት ድምጻቸውን ቢያሰሙ ኖሮ በወገኖቻችን ላይ የሚደርሰው በደል እዚህ ደረጃ ላይ አይደርስም ነበር።
እንደ ሉአላዊ አካል የሚያስብ ብሄራዊ መንግስት እስኪኖረን ድረስ አሁንም የታማኝ በየነን ፈለግ ተከትለን ለወገኖቻችን መጮህ ግድ ይለናል።

Tuesday 12 November 2013

በሳዑዲ አረብያ የመከራ ማጥ ውስጥ ላሉት ወገኖቻችን ሲባል ፈጥነን እንነሳ!

እንደ ሰው አንድ የሚያደርገን ባሕርይ፣ እንደ ኢትዮጵያዊነትም ሁላችንንም የሚመለከተንና የፖለቲካም ሆነ የሃይማኖት ልዩነት የማይነጣጥለው በደል በሳዑዲ አረብያ ግዛት እየተፈጸመ ነው። የጥቃት ዒላማዎቹ ኢትዮጵያውያን ናቸው። የጥቃቱ ልክ የለሽነትና አሰቃቂነት ደግሞ ይበልጥ የጎላው በሴት እህቶቻችን ላይ ነው። ይህ ዛሬ በሳዑዲ አረብያ የሚደረገው ጥቃትን ማስቆምና ቁጣችን መቆምያ እንደማይኖረው ማሳየት ለነርሱ ብቻ ሳይሆን ለራሳችን ደህንነትም ጭምር የምናደርገው ነው። ምክንያቱም ነገ ተመሳሳይ ጥቃትና በደል በመላው አለም ይስፋፋል። በአፍሪካ ሀገሮች የተበተኑ ኢትዮጵያን ከሶማሌና ኤርትራ ከሚሰደዱት በተለየ ይዘረፋሉ፣ ይደፈራሉ ይዋረዳሉ። እንደ አገር ልጅ አብረው እንዳይቆሙ በዘር በሀይማኖትና በፖለቲካ አቋም ምክንየት የተበተኑ ናቸው። ለሰላሳና አርባ አመት አምባገነኖች ያደረጉት ጭፈጨፋና በደል ፍርሃትን ሰማይ ጥግ አውጥቶታል። እናም ኢትዮጵያዊ በየተበተነበት ሁሉ ተኛ ሲሉት የሚተኛ አውልቅ ሲሉት እርቃኑን የሚቆም ፈሪ እንዲሆን ተደርጓል። ሲቸግረው የሚጮኸውን ያህል ሲመቸው ለወገን የሚደርሰው ጥቂቱ ነው። ይህ ሊቀጥል አይገባም!Protest at Saudi Arabia Mission to United Nations!
ቀደም ባለው ጊዜ አንድ ኢትዮጵያዊ ጥቃት ቢደርስበት ባገኘው መሳርያ ዘነጣጥሎም ቢሆን ይገድል ስለነበር ማንም አይደፍረውም ነበር። በዘመነ ኮሎኒያሊዝም ኢትዮጵያውያን በሄዱበት ሁሉ አንገት የማይደፉና ክብራቸውን የማያስነኩ ነበሩ። ዛሬ ጠቁመው የሚያስይዙ፣ ወገናቸውን የሚያሻሽጡና የሚሰልሉት ሁሉ ኢትዮጵያውያን ናቸው። የዚህ ጽሁፍ መነሻም ሆነ መድረሻው የድሮውን አሁን እየሆነ ካለው ጋር ማወዳደር አይደለም። ለዚህ የሚሆን የቅንጦት ጊዜም የለንም። ዓላማው አሁን እየደረሰብን ያለውን በደል በቁርጠኛነት አንታገለው ነው። ይህ ኢትዮጵያውያንን በሙሉ ከዳር እስከዳር ማስነሳት ካልቻለና ቁጣቸውንም ለመላው አለም ማሳየት ካልቻለ እውነትም አገራችን እያበቃላት ነው ማለት ይቻላል።
የዱር አውሬ እንኳን ከዚህ የተሻለ ክብር አለው። እነዚህ አጅግ ሁዋላ ቀር የሆኑ አረመኔዎች ከእንስሳ እንኳን አንሰው አንዲት በፍርሃት ነብሷን የሳተችን ሴት አስር ሆነው የሚደፍሩትን እያየን የተደፈሩት ህጋዊ ናቸው ህገወጥ የሚል የሕግ አንቀጽ መረጣ ውስጥ ልንገባስ እንዴት ይቻለናል? በመላው አለም ያለ የሳዑዲ ኤምባሲ ፊት ለፊት ሰልፍ ሊደረግና የሳዑዲ ወሮበሎች በወጣት ሴቶች ላይ እያደረሱ ያለው ግፍ በመረጃም ተደገፎ በበራሪ ወረቀትም ተዘጋጅቶ ለአለም ሕዝብ ሊበተን ይገባዋል። ተፈጥሮ ዘይትን ስትቸራቸው አእምሮ ግን እንደነፈገቻቸው ከዚህ በላይ መረጃስ ከየት ይመጣል?
እንደ ትውስታ ከወሰድነው በኬንያ ያሉ ስደተኞች ላይ በደል ይደርስ በነበረበት ወቅት ያ በጨካኝነቱ የሚታወቀው መንግሥሰቱ ሀይለማርያም አንኳን “ኢትዮጵያውያኑ የተሰደዱት የምናራምደውን ፖለቲካ እንጂ ሀገራቸውን ጠልተው አይደለም…” በሚል ኬንያን ማስጠንቀቁን መስማቴ ትዝ ይለኛል። በየወሩ 40 ሺህ ሴቶችን እንልካለን እያለ እንደ እንቁላል በየአረብ ቤቱ ሲያከፋፍል የነበረው መንግስት ዛሬ ዜጎቹ እንዳይሆን መጫወቻ ሲሆኑ ዝም ብሎ መመልከቱ እጅግ የሚያሳዝን ነው። ኢትዮጵያውያኑ ምናልባትም ኤምባሲውን ራሱን መቆጣጠር የሚገባቸው እስኪመስል ያስቆጣል።
በኢትዮጵያዊነት ላይ የተነጣጠረን ክፋት እንደ ሀገርና እንደ ሕዝብ ካላስቆምነው በሳዑዲ የተጀመረው መረን የጥላቻ ሰደድ ሊቀጣጥል የሚችልና የየሀገሩ የፖለቲካ ኪሳራ ማስተንፈሻ የሚሆነው አገር አጥቶ የተሰደደው ኢትዮጵያዊው ላይ ሁሉ ይሆናል። ይህንን በአስቸኳይ ለመቃወም ያሉ የትግል መንገዶች ሁሉ ክፍት ሊሆኑ ይገባል። እኔ አዘጋጀሁ እኔ ጠራሁ የሚል ደካማ የፖለቲካ ትርፍ ፍለጋ መንቀሳቀስ ሳይሆን ለሰብዓዊ ክብርና የመከራ ማጥ ውስጥ ሆነው የወገን ያለህ ለሚሉት እህት ወንድሞቻችን የድረሱልን ጥሪ ምላሽ እንስጥ። በጣም የሚያሳዝነው አብዛኞቹ ለስራ የሚሄዱት ወጣቶች የትምህርት ደረጃቸው አነስተኛ የሆነና በድህነት ውስጥ ያሉ ቤተሰቦቻቸውን ለመርዳት የሆነው ይሁን ብለው ከቤታቸው የወጡ ናቸው። አንዳንዶቹም ግሩም እድል አንደሚገጥማቸው በደላላዎች እየተነገራቸው ከቤት ወጥተው የቀሩ ናቸው። ለኒህ አጋር መሆን ለሀገር እንኳን ደንታ ባይኖረን ለነብስ የሚበጅ ስራ ነው። የኢትዮጵያ ኮሙኒቲዎች፣ በኢትዮጵያ ስም የተቋቋሙ የሀይማኖት ማዕከላት፣ ሲቪክ የፖለቲካ ድርጅቶች በሙሉ ለዚህ ዓላማ ቢቻል አደራጆች ካልተቻለም ዋንኛ ተሳታፊዎች ሊሆኑ ይገባል። ይህ በደል እጅ ለእጅ ሊያስተሳስረንና አንድ ላይ እንድንቆም ሊያደርገን የሚችል የጋራ ጉዳይ ነው። ዛሬ ነገ ሳንል በተደራጀና አለም አቀፍ ትኩረት ሊኖረው በሚያስችል አቅሙ እንነሳ ለወገንም አንድረስ።የመከራ ቀናችንን ለማሳጠር እንደ ሕዝብም ከአንገታችን ቀና እንድንል በያለንበት እንትጋ!

ሳውዲ አረቢያ በዜጎቻችን ላይ እየደረሰ ስላለው ህልፈተ ህይወት መንግስት የሚጠበቅበት እንዲወጣ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ አሳሰቡ

የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ሊቀመንበር ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ እየታካሄደ በሚገኘው የአዲስ አበባ ዞን ምክር ቤት 2ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ በመገኘት በሀገራችን ኢትዮጵያ ባለው የፖለቲካ፤ የዲሞክራሲ እና የፍትህ እጦት እንዲሁም ሁሉንም ኢትዮጵውያንን የሚያሣትፍ የኢኮኖሚ እድገት ባለመኖሩ ምክንያት ብዙ ዜጎች ወደ ደቡብ አፍሪካ ሃገራትና ወደ አረብ ሀገራት በእግር ሳይቀር ለመሰደድ ከመገደዳቸው በተጨማሪ በጉዞ ወቅት በአውሬ መበላት በበሽታ መሞትና ለአስገድዶ መደፈር መዳረጋቸውን አውስተዋል በተላይ ከቅርብ ግዜ ወዲህ የሳውዲ አረቢያ መንግስት በኛ ዜጎች ላይ እያደረሰ ያለው ስቃይና እንግልት ሳያንስ እስከመግደል የሚያድርስ እርምጃ በመወሰዱ የበርካታ ኢትዮጵውያን ህይወት እየተቀጠፈ እንደሚገኝ ለማወቅ ችለናል በመሆኑም በሀረብ ሀገራት ለስራ ተሰደው በሚገኙ ዜጎቻችን ላይ እየደረሰ ያለው ህልፈተ ህይወትና ጉዳት ፓርቲውን በእጅጉ እንደሚያሳስበውና ለዚህም በስልጣን ላይ ያለው መንግስት በአፋጣኝ የሚጠበቅበትን እንዲወጣ በማለት አሳስበዋል:: በመጨረሻም ለተጠቂ ቤተሰቦች የተሰማቸውን ሀዘን በመግለፅ ይሔ ግፍና ጭቆና እንዲቀር ፍትህና ዲሞክረሲ እንዲረጋገጥ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ጥሪዬን አቀርባለሁ ብለዋል፡፡1426366_605593059499529_213620200_n