Friday 26 December 2014

የባህርዳሩን ተቃውሞ ጋር በተያያዘ በአንድነት ፓርቲ አደራጅ ላይ ደህንነቶች ድብደባ ፈፀሙ! – ፍኖተ ነፃነት

የአንድነት ፓርቲ የሰሜን ቀጠና አደራጅ አቶ አዕምሮ አወቀ በመንግስት የደህንነት ሀይሎች ታፍነው ዝርፊያና ድብደባ እንደተፈፀመባቸው የፓርቲው ድርጅት ጉዳይ ለፍኖተ ነፃነት አስታወቀ፡፡
አቶ አዕምሮ ዝርፊያና ድብደባው የተፈፀመባቸው በትላንትናው ዕለት በግምት ከምሽቱ 12 ሰዓት ተኩል የፓርቲያቸውን ሰነድ እንደያዙ ከአንድ ኢንተርኔት ካፌ ሲወጡ አምስት የመንግስት የደህንነት አባላት ታርጋ በሌለው ሚኒባስ ውስጥ አስገድደው በማስጋት ከባህርዳር ከተማ በግምት የ35 ደቂቃ በመንዳት ለጊዜው ስፍራው ባልታወቀ ጫካ በማስገባት ድብደባና ዝርፊያ ፈፅመውባቸዋል፡፡ አቶ አዕምሮ ታፍነው ሲወሰዱ አይናቸው በጨርቅ ተሸፍኖና አፋቸው ውስጥም ጨርቅ ተጠቅጥቆ በሰደፍና በዱላ ከፍተኛ ድብደባ የተፈፀመባቸው ሲሆን፣ በእጃቸው የሚገኝ የፓርቲው ሰነድ፣ የባህርዳር ከተማ የአንድነት ጽ/ቤት ቁልፍ፣ ፓስፖርት ፣ሁለት የሞባይል ስልክ ፣ከ800 ብር በላይ የሚሆን ገንዘብ፣ ለብሰውት የነበረ የቆዳጃ ኬትና ሸሚዝ በደህንነት ሀይሎቹ ተዘርፎ እራቁታቸውን ከምሽቱ 5 ሰዓት ከአርባ አምስት ላይ ጫካ ውስጥ ተጥለዋል፡፡ ዝርፊያና ድብደባ የፈፀሙት የመንግስት የደህንነት ሀይሎች አቶ አዕምሮን “የፓርቲውን የገንዘብ ምንጭ ተናገር፣ አርብ እለት ባህርዳር የተደረገውን ተቃውሞ ያስታበረው አንድነት ፓርቲ ነው” እያሉ ሲደበድቧበው እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡10418149_749229755161961_2576733285857530569_n

ኢትዮጵያዊውን የገደለው ቻይናዊ ‹‹ለሁለቱ አገራት መልካም ግንኙነት›› ሲባል ክሱ መቋረጡ ተጋለጠ

December 26, 2014
በነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር
በምዕራብ ጎጃም ዞን ሰሜን አቸፈር ወረዳ ውስጥ ኢትዮጵያዊውን የገደለው ዠንግ ቢንዥንግ የተባለ ቻይናዊ ‹‹በቸልተኝነት ሰው በመግደል›› ወንጀል ክስ ተመስርቶበት የነበር ቢሆንም ‹‹ለሁለቱ አገራት መልካም ግንኙነት›› በሚል ትዕዛዝ ክሱ መቋረጡን ከክልሉ ፍትህ ቢሮ የተገኘው ሰነድ አጋለጠ፡፡
የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ለአቸፈር ወረዳ ፖሊስ ጽ/ቤት ተከሳሹ ካሳ ከፍሎ መውጣቱ ለሁለቱ አገራት መልካም ግንኙነት እንደሚበጅ በጻፈው ደብዳቤ ክሱ እንዲቋረጥ መደረጉን ‹‹በአማራ ፍትህ ቢሮ የምዕራብ ጎጃም ዞን የፍትሕ መምሪያ የወንጀል መዛግብት መርምሮ መወሰንና ተከራክሮ ማስወሰን የስራ ሂደት›› ለሰሜን አቸፈር ፖሊስ ጽ/ቤት በጻፈው ደብዳቤ ተመልክቷል፡፡ በትዕዛዙ መሰረትም ክሱ ቀሪ ሆኖ የምርመራ መዝገቡ ተመላሽ መደረጉን በደብዳቤው ላይ ተገልጾአል፡፡
Negere Ethiopia news, Chines man killed Ethiopian freed

በ15 ከተሞች በተመሳሳይ ሰዓት ሰልፎች ይደረጋሉ፣ የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር ሁለተኛ ዙር መርሃ ግብሩን ይፋ አደረገ

December 26, 2014
በነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር
የ9ኙ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ትብብር ‹‹ነጻነት ለፍትሃዊ ምርጫ›› በሚል ያወጣውን ሁለተኛ ዙር መርሃ ግብሩን ዛሬ ታህሳስ 17 ቀን 2007 ዓ.ም ይፋ አድርጓል፡፡ ትብብሩ የመጀመሪያ ዙር መርሃ ግብሩን በህዳር ወር በተለያዩ እንቅስቃሴዎች ማከናወኑ የሚታወስ ሲሆን፣ ሁለተኛ ዙር መርሃ ግብሩ ደግሞ ለ2 ወራት የሚቆይ እንደሚሆን ተገልጹዋል፡፡Statement from 9 Ethiopian coalition parties
የትብብሩ አመራሮች በሰማያዊ ጽ/ቤት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቁት በሁለተኛ ዙር የትብብሩ መርሃ ግብር መሰረት የካቲት 15 ቀን 2007 ዓ.ም በተመሳሳይ ሰዓት በ15 የሀገሪቱ ትላልቅ ከተሞች ላይ ህዝባዊ የተቃውሞ ሰልፎች ይደረጋሉ፤ በአዲስ አበባ፣ በሀዋሳ፣ በባህር ዳርና በአዳማ ደግሞ ህዝባዊ ስብሰባዎች እንደሚደረጉ የትብብሩና የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ይልቃል ጌትነት (ኢ/ር) በመግለጫው ወቅት ተናግረዋል፡፡
‹‹የመግባቢያ ሰነዳችንና የጥናት ሪፖርታችንን እንዲሁም ከመጀመሪያው ዙር ያገኘውን ተሞክሮ በሠረት በማድረግ ይህን የሁለተኛ ዙር የሁለት ወር ዕቅድ (ከታህሳስ 16 እስከ የካቲት 15 /2007) አውጥቶ በቀዳሚነት ለዋነኛ ባለቤቶቹና ፈጻሚዎቹ ኢትዮጵያዊያን ሲያቀርብ እንደመጀመሪያው ዙር ከጎኑ እንደሚቆሙ ሙሉ እምነት በማሳደር ነው›› ያለው መግለጫው፣ በትብብሩ በኩል በአመራር ከፊት ቆመው ትግሉን ለመምራት ዝግጁነትና ቁርጠኝነት መኖሩን አስረድተዋል፡፡
‹‹የያዝነው የትግል መንገድ ሠላማዊና ህገ-መንግሥታዊ ብቻና ብቻ፣ መጓጓዣችን ዴሞክራሲያዊ ምርጫ፣ መድረሻችን መድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት፣ እንዲሁም በጉዞኣችን ላይ የቱንም ያህል አረመኔያዊ የኃይል እርምጃ ይወሰድብን፣ ትግሉ የቱንም ዓይነት ዋጋና መስዋዕትነት ይጠይቅ ከጅምሩ ያለመስዋዕትነት ድል የለም ብለን ተነስተናልና ከያዝነው ዓላማ ኢንች የማናፈገፍግና ለቃላችን በጽናት የምንቆም መሆኑን ዳግም እናረጋግጣለን›› ብሏል ትብብሩ በመግለጫው፡፡
እቅዱ የመጀመሪያው ዙር ቀጣይ መሆኑን ያተተው የትብብሩ መግለጫ፣ ‹‹ዓላማችን የምርጫ ሁኔታዎች ባልተሟሉበትና የመራጩ ህዝብ ነጻነት በሌለበት ስለምርጫ መናገር አስቸጋሪ ነው፣ እነዚህ በሌሉበት አማራጭ የምርጫ ኃሳቦች በህዝብ ውስጥ ሊንሸራሸሩም ሆነ አማራጭ ኃሳባችንን ከህዝብ ማድረስ አይቻልም፣ ሚናችንም የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታው አማራጭ ሆኖ መቅረብ ሣይሆን የህወኃት/ኢህአዴግ አጃቢነትና የሀገር ሃብት በአላስፈላጊ መንገድ የማባከን ሥራ ተባባሪነት የዘለለ አይሆንም ከሚል የመነጨ ነው›› ሲል አቋሙን አሳውቋል፡፡ ነጻነት በሌለበት ተጨባጭ ሁኔታ ምርጫ ቧልት ነው ሲልም አክሏል መግለጫው፡፡
ሁለተኛ ዙር ፕሮግራም ዕቅዱ እንደባለፈው ተደጋጋፊ፣ ተመጋጋቢና ተከታታይ ሦስት ዋና ዋና ተግባራትና በሥራቸው አስራ አራት ዝርዝር ተግባራት ማካተቱም ተመልክቷል፡፡ እነዚህ በትብብሩ አስተባባሪ ኮሚቴ ጥልቅና ዝርዝር ውይይት ተደርጎባቸው የጸደቁ ዋና ዋና ተግባራትም፡-
1. የአባላትና የትብብሩ አቅም ግንባታ፡- የትብብሩን አባላት አብሮነት ማጠናከርና የጋራ ዓላማውን የማስፈጸም አቅም ማጎልበት፤
2. የህዝብ ግንኙነት ተግባራት፡- የህዝብ ተደራሽነት ማስፋትና ዓላማ ማስተዋወቅ፣
3. የህዝብ ንቅናቄ መድረኮች ማመቻቸት፡- በአዲስ አበባና የተመረጡ ከተሞች አራት የአዳራሽ/አደባባይ የህዝብ ውይይት፤ በአዲስ አበባና በተመረጡ አስራ አምስት የክልል ከተሞች በተመሳሳይ ቀንና ሰዓት ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግን፤ የሚያጠቃልሉ ናቸው፡፡
የትብብሩ አስተባባሪ ኮሚቴ ተግባራቱን በጊዜ ሠሌዳ በማስቀመጥ ለነዚህ ተግባራት ማስፈጸሚያ የብር 1,215, 000.00 (አንድ ሚሊየን ሁለት መቶ አስራ አምስት ሺህ ) በጀት ማጽደቁንም ለማወቅ ተችሏል፡፡ ትብብሩ ለያዘው ሠላማዊና ህገ-መንግሥታዊ የመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ትግል በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከጎኑ እንዲቆሙ ጥሪውን አስተላልፏል፡፡ ሌሎች ትብብሩን ያልተቀላቀሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ትብብሩን እንዲቀላቀሉ ጥሪ አቅርቧል፡፡