Monday, 29 February 2016

“ባልተማሩ የህውሓት ታጋዮች አንመራም…” የፌደራል ፖሊስ አባላት

አርበኞች ግንቦት 7 ድምፅ ሬድዮ
አዲስ አበባ ላይ ያልተሳካላቸው የህወሓት አገዛዝ ፌደራል ፖሊስ አዛዦች ባህር ዳር ላይ በድጋሚ ስብሰባ አካሂደው የባሰውን ተበጣበጡ፡፡
የፌደራል ፖሊስ አመራሮቹ ከእሁድ የካቲት 13 እስከ 16 2008 ዓ.ም ድረስ ነው በባህር ዳር ከተማ ምንም አይነት አዎንታዊ ውጤት ያላመጣ ውይይት ለማድረግ የሞከሩት፡፡ በስብሰባው ላይ “ባልተማሩ የህውሓት ታጋዮች አንመራም… ” የሚል ተቃውሞ ተነስቷል፡፡
በልዩ ልዩ የአገሪቱ ክፍሎች የተነሳውን የህዝብ ተቃውሞ የጠብመንጃ ጉልበት ተጠቅሞ ፀጥ የማስኘትን የአገዛዙን የፀና አቋም በሚመለከት ደግሞ በአዛዦች መካከል እስከ አምባጓሮ የዘለቀ አለመግባባት ተከስቶ ነበር፡፡ “ወደ ህዝባችን እንዲተኮስ ትእዛዝ አንሰጥም…“ በማለት በግልፅ ተቃውሟቸውን ያሰሙ በርካታ የፈዴራል ፖሊስ አመራሮች ነበሩ፡፡
በመጨረሻም ስብሰባው እንደተለመደው ያለምንም ውጤት ተበትኗል፡፡ ከስብሰባው በኋላ 4 የፌደራል ፖሊስ አመራሮች ስርአቱን ከድተዋል፡፡ ከአራቱ መካከል አንዱ ኢንስፔክተር ፀጉ ይሰኛል፡፡ አራቱም መኮንኖች እስካሁን የት እንደደረሱ የታወቀ ነገር የለም፡፡
Ethiopian Federal Police

እርቅ፤ የሚነገር – የማይተገበር (ይገረም አለሙ

ይገረም አለሙ
በአቶ ኦባንግ ሜቶ በሚመራው ድርጅት አዘጋጅነት በተጠራ ጉባኤ ላይ የተገኙ ኢትዮጵያዉያን ስብሰባቸውን ያጠናቀቁት በሀገራችን እርቅ አስፈላጊ መሆኑ ላይ በመተማመንና  ለዚህም ተግባራዊነት እርቅን ከራስ መጀመር እንደሚገባ አጽንኦት በመሰጠት  መሆኑን ሰምተናል፡፡ የእስከዛረሬው ተሞክሮአችን ተግባራዊነቱን አንድንጠራጠር ቢያደርገንም የአሰባሳቢዎቹ ተግባርም ሆነ ተሰብሳቢዎቹ የደረሱበት ድምዳሜ የሚደነቅ ብቻ ሳይሆን ለተግባራዊነቱ ድጋፍ ሊቸረው የሚገባ ነው፡፡
የእርቅ ተቃራኒ ጸብ ነው፡፡ ከሁለቱ ደግሞ የትኛው ቀላል እንደሆነ ለማንም ግልጽ ነው፡፡ እርቅ ብዙ መንገድ መሄድ፣ ብዙ ተግባር መከወንን ያሻል ብዙ መስዋዕትነትም ይጠይቃል፡፡ ለዚህም ነው ሲነገር እንጂ ሲተገበር የማንሰማው፣ ሲወጠን አንጂ ከግብ ሲደርስ የማናየው፡፡ ጸብ ግን  ማሰብና መጨነቅ፣ ማመዛዘንና ረጋ ብሎ መወሰን የማይጠይቅ በደቂቃ ውስጥ  ሊከውኑት የሚችል ነው፡፡Ethiopian Council for Reconciliation and the Restoration of Justice
ቢያንስ ባለፉት ሀያ ዓመታት የእርቅን አጀንዳ  በየግዜው ቢነሳም ከንግግር ማድሚቂያነት አልፎ  ተግባራዊነቱ ሊታይ አልቻለም፡፡ የሚናገሩትን መተግበር  ያልቻሉቱ የፖለቲካው  ተዋናዮች የሚያቀርቡት ምክንያት ደግሞ  አንድና የተለመደ  ከቁም ነገር ሊገባ የማይችል ነው፡፡ ኮ/ል መንግሥቱ ስለ እርቅ ሲጠየቁ የሀገር ጉዳይ ነው የባልና ሚስት ጸብ አይደለም ማለታቸውን የሰሙና መጨረሻ የሆኑትን ያዩ ወያኔዎች ከዚህ ባለመማር እነርሱ ደግሞ በተራቸው እርቅ ሲባሉ ማን ከማ ጋር ተጣላና ነው በማለት ይሳለቃሉ፡፡በአንጻሩ አንዴ ብሔራዊ እርቅ ሌላ ግዜ ሀገራዊ መግባባት ወይንም ብሔራዊ መግባባት ያስፈልጋል እያለ የሚጮኸው ተቃዋሚ ለነገሩ ተግባራዊ አለመሆን የወያኔን እምቢተኝነት በምክንያት እያቀረበ ለአመታት ዘልቋል፡፡
እርቅን የማይፈልጉ ከጸብ የሚያተርፉ መሆናቸው እሙን ነው፡፡ ወያኔ አጣልቶ እንጂ አስማምቶና ተስማምቶ፤ አለያይቶ አንጂ አንድነትን አጠናክሮ  በስልጣኑ ሊቆይ አንደማይችል ስጋት ስላለው እርቅን ቢጠላ መግባባትን በሩቁ ቢል ከዓላማው የመነጨ ነው፡፡ ተቀዋሚዎቹ ግን ሀያ አራት አመታት ስለ እርቅ ሲጠይቁ አንጂ የሚችሉትን ሲያደርጉ አለመታየታቸው ለምን ይሆን  የሚል ጥያቄ ያነሳል፡፡  ለዚህ መልሱ የወያኔ አምቢተኝነት ነው  የሚባል ከሆነ ራስን ማታለል ይሆናል፡፡
እርቅ የሚጠይቁት ፖለቲከኞች ርስ በርሳቸው አይደለም መጀመሪያ ከራሳቸው መች ታረቁ፤ብሄራዊ መግባባት ሲሉ የሚደመጡት እነርሱ በተቃዋሚነት ደረጃ ፓርቲ ከፓርቲ አይደለም በአንድ ፓርቲ ውስጥ ግለሰቦች አንኳን መች መግባባት አላቸው፡፡ ብዙ ተባዙ የተባሉ ይመስል የተግባር ሳይሆን የቁጥር ፓርቲ በውጪም በውስጥም የሞላው በዚሁ ምክንያት አይደለምን፡ ከወያኔ ጋር ውይይት እንሻለን የሚሉት እነርሱ መች ለውይይት አንድ ላይ መቀመጥ የሚችሉ ናቸው፡፡ በአንድ ብሄር ስም አራት አምስት ድርጅት የመሰረቱ ስለ አንድነት እያወሩ መለያየየትን የሚተገብሩ፣ ሀገራዊ መግባባት እየጠየቁ ድርጅታዊ መናቆር የሚያካሂዱ አይደሉምን፡፡
ወያኔ ተቀዋሚዎቹ እርቅ ብለው የሚጮሆት በምርጫ ያጡትን ሥልጣን በአቋራጭ እናገኛለን ብለው በማለም ነው ብሎ እያሰጋ የሥልጣን ነገር ደግሞ ለርሱ የነበር ጅራ ሆኖበት ማስተዋል ነስቶት እንጂ እኔ ከዚህ ሁሉ ድርጅት ተብየ ጋር ውይይት መቀመጥ አልችልም መጀመሪያ ራሳችሁ ታረቁና፣ አለያም  በመካከላችሁ መግባባት ፍጠሩና ከዛ በኋላ ጠበብ ባለ ቁጥርና በተወሰነ አጀንዳ መነጋገር አንችላለን ቢል ተቀዋሚዎቹ ይህን ፈተና ማለፍ ይችላሉ ብሎ  በርግጠኝነትመናገር አይቻልም፡፡
መጀመሪያ ከራሳችን አንታረቅ የሚለው የእነ አቶ ኦባንግ ስብሰባ ውጤት ተግባራዊ ቢሆን ይህን ችግር ይቀርፍ ነበር፤ መጀመሪያ ግለሰቦች ከራሳቸው ጋር፣ ቀጥሎ በአንድ ፓርቲ ወስጥ ያሉት ርስ በርሳቸው  ከዛም በመቀጠል  ፓርቲ ከፓርቲ እየተባለ እርቁም ይን መግባባቱ ቢፈጠር ፓርቲዎቹ ቁጥራቸው የተወሰነ ከወያኔ ጋር አንነጋገርበታለን የሚሉት አጀንዳ የተመጠነ ሀይላቸው የጠነከረ ይሆናል፡ ያኔ ወያኔ በእምቢተኝነቱ ቢጸና የማስገደድ አቅም ይኖራቸዋል፡፡አሁን ባሉበት ደረጃ ሆኖ ስለ እርቅ አስፈላጊነትና ስለ ወያኔ አምቢተኝት ማውራት  ከምር እርቅ ፈላጊነትን አያሳይም፡፡ የዓለም አቀፉ ማህበረስብ አካላትና የሀያላኑ መንግሥታት ተወካዮች በአንዲት ሀገር ኢትዮጵያ ጉዳይ ከስንቱ ጋር እንደሚነጋገሩ እየቸገራቸው እባካችሁ አንድ ሆናችሁ ኑ ማለታቸውን በተደጋጋሚ ራሳቸው ፖለቲከኞቹ አንደነገሩን አንዘነጋውም፡፡
የእርቅ አስፈላጊነትንና ጠቀሜታን የማይረዳ ሰው ይኖራል ተብሎ አይታሰብም፡፡ ችግሩ ሁሉም የሚያሰበው እርቅ ለሀገሪቱ ስለሚያስገኘው ጠቀሜታና ለትውልድ ስለሚያቆየው በረከት ሳይሆን እሱ ስለሚያጣውና ስለሚያገኘው ግለሰባዊ ጥቅም ( ፕ/ር መስፍን በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ጭንቅላት ላይ አለ የሚሉት ዘውድ ሊሆን ይችላል) በመሆኑ  እርቅ የሚናገሩት አንጂ የማይተገብሩት አጀንዳ  ሆኖ አመታት ያስቆጠረው፡፡
ዛሬ የተነሳው እርቅን ከራስ የመጀመር ጉዳይ በተለያየ ግዜ በግለሰቦችም በድርጅቶችም የተባለና ከመባል ያላለፈ ነው፡፡ ከፖለቲካው መድረክ ውጪም ያሉ በጽሁፍም በንግግርም ሀሳብ የሰጡበት ነው፡፡ ምንግዜም በኢትጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ በቀዳሚነት የሚወሳው  ቅንጅት በምርጫ 97 ማንፌስቶው ውስጥ  “በሐገሪቱ ታሪክ ውስጥ እንደ መጥፎ ገጽታ የሚታዩ የእርስ በእርስ ግጭቶችም ደም ያፋሰሱ ጦርነቶችና እልቂቶችም በተለያዩ ምክንያቶች ተከስተዋል፡፡በሀገራችን የሚመሰረተው ዴሞክራሲያዊ ሥርዐት በማይናወጥ ዴሞክራሲያዊ መሰረት ላይ መገንባት  ካለበት የእስካሁኑ የጥላቻ የበቀልና ያለመተማመን ምዕራፍ ተዘግቶ ለተከታይ ትውልድ የሚዘልቅ አዲስ ምዕራፍ መከፈት ይኖርበታል፡፡ በመሆኑም እያንዳንዳችን ከራሳችን ፤ሕዝብ ከሕዝብ መንግሥት ከሕዝብ የፖለቲካ ፓርቲ ከፖለቲካ ፓርቲ ለመግባባት የሚችሉበት ብሔራዊ ዕርቀ ሰላም ከሁሉ በፊት መቅድም አለበት ብሎ ቅንጅት ይምናል፡ በማት ነበር የገለጸው፡፡
ይህን የጻፉት ሰዎች ግን ራሳቸውም አብረው መዝለቅ ሳይችሉ ቀርተው የማይሆን ሆነ፡፡  እርቅ አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን በወያኔ አባባል ለመጠቀም የህልውና ጉዳይ ነው፡፡ ስለሆነም ሀያ አራት አመት የተነገረው ይብቃና አሁን ከምር ወደ ተግባር ይገባ፡፡ ለዚህ ደግሞ ሁሉም ከራሱ ከቤቱ ከጎረቤቱ የሚጀምርበት ሁኔታ ይፈጠር፡፡ በተመሳሳይ ስም ( በአንድ ብሄር)  እየተጠሩ አንድ አይነት አላማ እየተናገሩ አራት አምስት ሆነው የቆሙ ውደ አንድ ይምጡ፤የሚችሉ የታረቁ፣የማይችሉ የአንድ ሀገር ልጅነት መግባባት ይፍጠሩ፤ ይህም የማይሆንላቸው ወያኔ ከኢትዮጵያ ህዝብ ላይ መነሳት ያለበት በመሆኑና በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ይግባቡ፡፡ ይህን ማድረግ ከተቻለ የወያኔ ምርጫ  ተገዶ ወደ እርቅ መምጣት አለያም በተባበረ ሀይል ተገፍቶ ሥልጣኑን ማጣት ይሆናል፡፡ ከወያኔ በኋላ ስልጣን በሚይዝ ሀይል ፖለቲካዊ የበቀል ርምጃ የማይጠበቅ ቢሆንም ተገዶ ከስልጣን መውረድ ብዙ ነገር ስለሚያከትል ሁለተኛውን መንገድ  ወያኔዎች ባይመርጡት ይመከራል፡፡
እኔም ለማለት ያህል አልኩት አንጂ  ተቀዋሚው ወገን ካለፈው ተምሮ ፣በወያኔ እብሪትና እኩይ ድርጊት ተማሮ ስለ እርቅ ከማውራት አለፍ ብሎ  እርቅን ከየራሱ በመጀመር  በተቀዋሞው ጎራ ሀገራዊ መግባባት ሊፈጠር ይችላል ብሎ ማሰቡ ራሱ ይከብዳል፡፡ በተቃውሞው ጎራ ይህ አንደ ተአምር የሚፈጠር ነገር ተግባራዊ ሆኖ ጠንካራ የተባበረ ሀይል መፍጠር ቢቻል ወያኔን ለእርቅ ማስገደድ ካላሆነም ከሥልጣን ለማስወገድ የሚገድ አይሆን ነበር፡፡
ወያኔ ንቀቱ የበረታው ጥፋቱ የከፋውና የሚፎክር የሚደነፋው የተቃውሞው ጎራ ምንነትና ማንነት አንደማያሰጋው ስላረጋገጠ ነው፡፡ አንባገነን ያሉትን ሀይል ያስገድዱታል አንጂ እንታረቅ እያሉ አይለምኑትም፡፡ ወያኔ ልመና አይሰማ ተቀዋሚው ለማስገደድ አይበቃ፣በዚህ መሀል ህዝብ አሻፈረኝ ብሎ ተነስቶ በየቀኑ የጥይት ሰለባ እየሆነ ነው፡፡የሚያሳዝነው ይህ የዜጎች እልቂት ለወያኔ ከቁብ ያልተቆጠረ ለተቀዋሚው ያላስመረረ መሆኑ ነው፡፡

ዶ/ር ማይገነት ሽፈራው ታላቅ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ

ኢትዮጵያ ሀገራችን የሰብአዊ መብት ተሟጋች ልጇን አጣች።
በሰብአዊ መብት ተሟጋችነታቸው፣ ለሰላምና ለዲሞክራሲ መስፈን ታጋይነታቸው የሚታወቁት ዶር ማይገነት ሽፈራው ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።
Dr. Maigenet shiferaw passed away
ዶር ማይገነት ሽፈራው ስለ ሰላም የሰበኩ ያስተማሩና የጻፉ ቀንዲል ኢትዮጵያዊ ነበሩ። ድህነትና በሽታ፣ ርሐብና ስደት፣ አምባገነንትና ጦርነት እያለ የኢትዮጵያ ሴቶች መብት መከበር፣ የሰብአዊ መብት መረጋገጥ፣ ዲሞክራሲና ሰላምን ማስፈን አይቻልም በሚል እምነታቸው በጽናት ታግለው ያታገሉ የዘመናችን ጣይቱ ነበሩ። የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ፣ የመናገር የመጻፍ የመሰብሰብ የመደራጀትና በሰላማዊ መንገድ ተቃውሞን የማሰማት መሠረታዊ መብቶች እውን እንዲሆኑ እንዲሁም ለኢትዮጵያ ሕዝብ ሰብአዊ መብት መከበር፣ ለሃገራችን ሰላም፣የሃገራችን የፖለቲካ ችግር በዲሞክራሲ፣ በመቻቻልና በሰከነ ውይይት እንዲፈታ፣ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ እድሜያቸውን ሙሉ ታግለው ያታገሉ እናት፣ እህትና ወገን ነበሩ።
ዶር ማይገነት ሽፈራው (Ethiopian Women for peace and development (EWPD) ) እ.ኤ.አ. በ 1991 ዓም ከመሥራቾቹ አንዷ በመሆን ለ21 ዓመታት ያገለገሉ ሲሆን በ2012 ዓለምአቀፍ የኢትዮጵያ ሴቶች ጉባኤ ባደረገውም ተከታታይ ስብሰባ የኢትዮጵያ ሴቶች የመብት ማዕከልን (Center for Rights of Ethiopian Women (CREW) ) ሲመሠረት ሀሳቡን ከመጠንሰስ ጀምሮ በምሥረታው ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ካደረጉትና ከመሥራቾቹ አንዷ ናቸው። ከተመሠረተም በኋላ በተደጋጋሚ በመመረጥ ድርጅቱን በብቃት የመሩ የመሪነት ችሎታቸውን በተግባር ያስመሰከሩ ናቸው።
ይህ አዲስ የተወለደው የሴቶች ማዕከል የተነሳበት ዓላማና የሚታገልላቸው ጥያቄዎች የኢትዮጵያ ሴቶች የሰላምና የልማት ድርጅት (EWPD) ለ21 ዓመታት ሲታገሉላቸው ከነበሩት ዓላማዎች ጋር አንድ በመሆናቸው ተመሳሳይ ድርጅት ለየብቻ ሆኖ ኃይልና ጉልበትን ከመከፋፈል በአንድ ላይ ሆኖ ያለውን ጉልበትን አሰባስቦ ጠንክሮ ለውጤት በመሥራት የተሻለና ጠንካራ የሴቶች ድርጅት በመሆን ለኢትዮጵያ ሴቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማህበራዊ ፍትህ፣ ለሰብአዊ መብት መከበር፣ ለዲሞክራሲ መብት መስፈን እየታገሉ የሴቶችን በራስ የመተማመን አቅም ለማጎልበት እጅ ለእጅ ተያይዞ መሥራት የወቅቱ ቁልፍ መፍትሔ መሆኑን በማመን ለ21 ዓመት በጽናት የቆዬውን የኢትዮጵያ ሴቶች የሰላምና የልማት ድርጅት የሠራቸውን ሕዝባዊ ሥራዎችንና ያካበተውን የትግል ልምድ ይዞ ኢትዮጵያ ሀገራችን የሰብአዊ መብት የሚከበርባት፣ የሕግ የበላይነት የሚያብባት፣ ሰላም የሰፈነባትና የሴቶች ስብእናቸው የሚከበርባት አገር እንድትሆን በጋራ ቆሞ ለመሥራት ከኢትዮጵያ ሴቶች የመብት ማዕከል ጋር አንድ በመሆን ሲዋሃድ ዶር ማይገነት ሽፈራው ውህደቱን እውን እንዲሆን ወሳኝ ሚና ተጫውታዋል::
ዶር ማይገነት ሽፈራው የኢትዮጵያ ሴቶች ጠንካራ ተቋም እንዲኖራቸውና በሃገራቸው የፖለቲካ፣የኤኮኖሚና የማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ እንዲኖራቸው በነበራቸው ከፍተኛ አላማና ምኞት ንቃተ ህሊናቸውን ለማሳደግ የመጀመሪያው እርምጃ ሴቶች ወደ ትምህርት ቤት እንዲሄዱ እንዲማሩ የሚያበረታቱና የሚያስተምሩ ኃላፊነት የሚሰማቸው አብነታቸው ብዙዎችን የሚያነሳሳ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ሴቶችን ለመሪነት ማብቃት ለነገ የማይባል ግዴታችንና ኃላፊነታችን ነው ብለው የሚያምኑ ለዚህም ሳያሰልሱ ያስተማሩ ምርጥ መምህር ነበሩ።
የኢትዮጵያ ሴቶች የመብት ማእዕከል (CREW) መሪውን በማጣቱ የተሰማውን ከፍተኛ ኃዘን እየገለጸ ዶር ማይገነት በተውሉንን መልካም ሥራዎቻቸውንና በጎ ሀሳባቸው እየተጽናናን  የደከሙበትንና የታገሉለትን አላማና አርማ ቀጣዩ ትውልድ በማንሳት የነገይቱ ኢትዮጵያ  የሃገራችን የፖለቲካ ችግር በዲሞክራሲና በሰከን ውይይት ተፈትቶ የሴቶች መብት የሚሰፍንባት፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰብአዊ መብት የሚከበርበት፣ የመልካም አስተዳደር መሠረት የሚጥልበት እንደሚሆን ጥርጥር  አይኖረንም።
“ዞሮ ዞሮ ከቤት ኖሮ ኖሮ ከመሬት” የማይቀርበት የህይወት ጉዞ ነውና ለዶር ማይገነት የሰላም እረፍትን እንዲሆንላቸው እየጸለይን፤ እንዲሁም ለባለቤታቸው፣ ለልጆቻቸው፣ ለቤተሰቦቻቸውና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ብርታትና መጽናናትን እንመኛለን።
የኢትዮጵያ ሴቶች የመብት ማእዕከል (CREW)
የዶ/ር ማይገነት ሽፈራው  የቀብር ስነስርአት ፕሮግራም የሚካሄደው ሰኞ ፌብሩዋሪ 29 2016 ነው፡፡
የቤተክርስትያን ስነስርአት የሚፈዐመው ፡ ከ 10፡00 ኤ.ም -1፡00 ፒ.ኤም
ቦታው፡ ቅዱስ ገብርኤል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን
አድራሻ፡ 2601 Evarts St. N.E Washington DC 20018
የቀብር አገልግሎት የሚከናወነው፡ 2፡00ፒ.ኤም
የቀብር ቦታ አድራሻ፡ 9500 Riggs RD Adelphi, MD, 20783

ከቀብር ስነስርአቱ ፍፃሜ በኋላ የምሳ ፕሮግራም በቅዱስ ገብርኤል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን ተዘጋጅቷል፡፡

በሚኒሶታ እና አካባቢው ለምትኖሩ ኢትዮጵያውያን የቀረበ 



በሚኒሶታና አካባቢው የምትገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ; የፕሮቴስታንት እና በኦሮሚኛ ቋንቋ አገልግሎት የሚሰጡ አብያተ ክርስቲያናት በአንድነት እንዲካፈሉበት የተጠራ የ3 ቀናት የጸሎትና የሻማ ማብራት ጥሪ:: ሁሉም ኢትዮጵያዊና ኢትዮጵያን ወዳጆች እንዲሳተፉበት ጥሪ ቀርቧል::
global-vigil_web_ed

የፌደራል ፖሊስ ኢንስፔክተር ተስፉ በርካታ አባላቱን ይዞ ስርዓቱን ከዳ



inspecter
(ዘ-ሐበሻ) የኢሕ አዴግ አስተዳደር ኢንስፔክተር ተስፉ የተሰኘ የፌደራል ፖሊስ ጦር መሪ በርካታ አባላትን ከነሙሉ ትጥቃቸው ይዞ ከሁመራ ስርዓቱን መክዳቱን የአርበኞች ግንቦት 7 ራድዮ ዘገበ::
እንደራድዮው ዘገባ ኢንስፔክተር ተስፉ ሁመራ እና አካባቢው የሚንቀሳቀሰው ፌደራል ፖሊስ መሪ፣ ለህወሓት ታማኝ እና ጠንካራ ከሚባሉት ቀዳሚው የነበረ ሲሆን በትናንትናው ዕለት የካቲት 19 2008 ዓ.ም የሚመራቸውን በርካታ አባላት ከነሙሉ ትጠቃቸው ይዞ ሁመራ ከሚገኝ ጦር ግንባር ጠፍቷል፡፡
በራድዮው ዘገባ መሠረት የኢንስፔክተር ተስፉን እና በርካታ ተከታዮቹ የሆኑ የፌደራል ፖሊስ አባላትን መጥፋት ተከትሎ ህወሓት ጎዳናዎችን በጦር ዘግቶ ወጥሯል፤ ከፍተኛ አሰሳም እየተካሄደ ይገኛል፡፡ ነገር ግን ኢንስፔክተር ተስፉና ተከታዮቹ እስካሁን የገቡበት አልታወቀም፡፡ አገዛዙ እነ ኢንስፔክተር ተስፉ ወደ ኤርትራ ተሻግረው ብረት ያነሱ የነፃነት ድርጅቶችን እንደተቀላቀሉ ያምናል፡፡
የአርበኞች ግንቦት 7 ራድዮ ከኢንስፔክተሩ ጋር የከዱት ወታደሮች ቁጥር ምን ያህል እንደሆኑ ባይገልጽም በርካታ ሲል ይጠራቸዋል::

በሰሜን ጎንደር ዳባት ሕዝባዊ እምቢተኝነት ተቀሰቀሰ | ወደ መቀሌና ሽሬ የሚወስዱ መንገዶች ተዘጋግተዋል

(ዘ-ሐበሻ) በሰሜን ጎንደር ዳባት ሕዝባዊ እምቢተኝነት መቀስቀሱን ከአካባቢው የሚመጡ መረጃዎች አስታወቁ:: ምንጮች ለዘ-ሐበሻ እንደሚገልጹት ወደ መቀሌና ሽሬ የሚወስዱ ወይም ከዚያ ወደ ዳባት የሚያመጡ መንገዶች ተቃውሞውን ባነሳው ሕዝብ በድንጋይ እና በ እንጨት መዘጋጋቱ ተሰምቷል::
በዳባት ከተማ ሕዝቡ ሕዝባዊ እምቢተኝነቱን ያነሳው ከወልቃይት መሬት እና ከመልካም አስተዳደር ጋር በተያያዘ እንደሆነ ከስፍራው የሚመጡ መረጃዎች ጠቁመው ሕዝባዊ ቁጣው እስከ እኩለሊት ድረስ እንደቀጠለ የዘ-ሐበሻ ምንጮች አስታውቀዋል::
ይህን ጉዳይ ተከታትለን እንዘግባለን::
በኦሮሚያ የተለያዩ ከተሞች አሁንም ሕዝባዊ እምቢተኝነቱ መቀጠሉ የሚታወስ ነው:

በአዲስ አበባ የታክሲዎችን የስራ ማቆም አድማ ተከትሎ የትራንስፖርት ችግር ተከሰቷል

በአዲስ አበባ የሚገኙ የታክሲ ሹፌሮች የወያኔ አገዛዝ ያወጣውን የትራንስፖርት እና መንጃ ፍቃድ ሕግ በመቃወም የጠሩት የስራ ማቆም አድማ በዛሬው እለት የአዲስ አበባን መንገዶች ከትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ውጪ በማድረጋቸው ተገልጋዩ በትራትስፖርት ችግር ሲገጥመው ተስተውሏል::
የአዲስ አበባን የታክሲ ሹፌሮች ከስራ ውጪ ለማድረግ እና ስራ ፈት ዜጎችን ለመፍጠር ታስቦ በወያኔ የወጣው አዲስ ሕግ ማንኛውም ሹፌር 21 ጊዜ ጥፋት ካለበት መንጃ ፈቃዱ ተነጥቆ ከሹፌርነት ለመጨረሻ ጊዜ የሚያግድ ሲሆን የታክሲ ሹፌሮችን ሆን ብሎ በማጥቃት ከስራ ውጪ በማድረግ የደህንነት አካላት የሆኑ አዳዲስ እየሰለጠኑ የሚገኙ የሕወሓት አባላትን የታክሲ ባለቤቶች ላይ ጫና በመፍጠር በሹፌርነት ለማሰማራት የታቀደ እንደሆነ ውስጥ አዋቂዎች ይናገራሉ::
የወያኔው አገዛዝ በተለያዩ በዝባዥ እና ሕዝብን በሚበድሉ ሕጎች ኢትዮጵያውያንን እያሰቃየ ሲሆን ይህም ከፍተኛ የሆነ ብሶት አደባባይ ላይ መሰማቱ ሲቀጥል የስራ ማቆም አድማውም የዚሁ ብሶት አካል መሆኑ ታውቋል::በአዲስ አበባ የትራንስፖርት ተገልጋዮች በተለያዩ መንገዶች ትራንስፖርት ለማግኘት ቢሞክሩም እንዳልቻሉ ታይተዋል::የወያኔ አገዛዝ ለሶስት ወር አራዘምኩት ይሕጉን ተግባራዊነት የሚል መግለጫ ቢሰጥም ተቀባይነት አጥቶ የስራ ማቆም አድማው ተደርጓል::ሕዝቡ ብሶቱን በተለያየ መንገድ በመግለጽ ስርኣቱ እንዲወገድ ትግሉን ቀጥሏል::‪#‎ምንሊክሳልሳዊ