Thursday, 14 November 2013

ብሄራዊ ውርደት፤ የምንመጻደቅበት ‘ሌጋሲ’

ወገናችንን በጥይት ሲደፉት በራሱ ላይ አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ባንድራችንን ጠምጥመውበታል[1]። ጭካኔ በተሞለበት መንገድ የተገደለው ይህ ኢትዮጵያዊ አስከሬኑም በሰላም አላረፈም። በአካሉ ላይ ያረፈውን ጨርቅ በሴንጢ እየቆራረጡ በሰብአዊ ፍጡር ላይ ሊደረግ የማይገባውን ሁሉ አደረጉበት። ድርጊቱ ናዚዎች በኦሽዌትስ ይፈጽሙት የነበረውን አሰቃቂ ግፍ ያስታውሰናል። በ21ኛው ዘመን እንዲህ አይነቱ ክስተት ይደገማል ብሎ የሚያስብ የለም። እነሆ ሳውዲ አረቢያ በኢትዮጵያውያን ላይ እየፈጸመችው ነው። በስውር ሳይሆን በግልጽ። እንደ ኦሽዊትስ በታጠረ የማጎርያ ካምፕ ሳይሆን በአደባባይ።
ሰው ከሞተ በኋላ ለምን ሙት አካሉን ማሰቃየት አስፈለገ? ምን አይነት ጭካኔ ነው? ምን አይነትስ ጥላቻ ነው? ለሳውዲዎች ግማሽ ፈረንሳይን የሚያህል መሬት ሰጥተናቸው የለም እንዴ? ሀጥያታችን ምኑ ላይ ነው ታዲያ? አስከሬኑን ውሻ፣ ውሻ ሲሉ ሲሳለቁበት ከማየት በላይ የሚያም ነገር የለም።  በአደባባይ እንደዋዛ የተጣለው አስከሬን በእርግጥ የዉሻ አስከሬን ቢሆን ኖሮ የእንስሳ ተከራካሪዎች  አለምን ቀውጢ ባደረጓት ነበር።
መገናኛ ብዙሃን እና ማህበራዊ ድረ-ገጾች ይህንን ጉዳይ በስፋት ቢዘግቡትም፤ አለም አቀፉ ህብረተሰብ ግን ዝምታን መርጧል። በዚህ በሰለጠነ ዘመን፤ እንደ እንስሳ እየታደኑ ከሚያዙትና ከሚገደሉት ወገኖች ውስጥ አንድ አሜሪካዊ ዜጋ ቢገኝበት ኖሮ ትርምሱ ምን ደረጃ ላይ እንደሚደርስ እናይ ነበር። የኛስ ነብስ የሰብአዊ ፍጡር ነብስ አይደለችም እንዴ? ስንቀጠቀጥ፣ ስንታረድና ስንገደል የሚፈሰን ደም ከሌላው ዜጋ የተለየ ደም ነው? ግፉ ለምን በኛ ላይ ብቻ በረታ? ሌላ ዜጋ ሲገደል አላየን። እየተሳደዱ የሚታጎሩት ሁሉ ኢትዮጵያዊ ናቸው። ይህ ሁሉ ግፍ እና መከራ ለምን በኢትዮጵያዊያን ላይ ብቻ? ድህነታች የዜግነት ክብራችንን አስነጥቆን ይሆን? እርግጥ ነው። የገንዘብ ድሆች ልንሆን እንችላለን። የአስተሳሰብና የስነ-ምግባር ድሆች ግን አይደለንም።
ችግሩ ያለው ሌላ ቦታ ነው። ብሄራውነት የሚሰማው መንግስት፤ ብሄራዊ ክብራችንንና ማንነታች የሚያስመልስ። በአለም አቀፍ መድረክ የሚያስከብረን ጠንካራ አካል ማጣታችን ነው የውርደታችን ምክንያቱ።
እንግዲህ ይህ ነው አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ የተረከቡት ቅርስ እና ውርስ። ይኸው ነው ገዢው ፓርቲ የሚመጻደቅበት ‘ሌጋሲ’። በምእራብ አፍሪካ ኮሌጆች የኢትዮጵያ ታሪክ እንደኮርስ ይሰጣል። የአድዋ ገድል፣ የጸረ-ቅኝ ግዛት ተምሳሌት፣ የነ ማርክስ ጋርቤይ፣ የነ ክዋሜ ንክሩማ፣ የነ ጆሞ ኬንያታ ለነጻነት ትግል መነሳሳት ከኢትዮጵያ ታሪክ ጋር ተቆራኝቶ በታሪክ ይዘከራል። ላለፉት 20 አመታት የተፈጠረው ክስተት ግን ይህንን ሁሉ መልካም ስም ድራሹን እያጠፋው ይገኛል። የተስፋይቱ ምድር እያሉ የሚጠሩዋት ራስ ተፈሪያን  የዛሬዩቱን ኢትዮጵያ የውርደት ታሪክ  እንዴት እንደሚያዩት እንጃ። ለአፍሪካ ነጻነት ተምሳሌት የሆንን ሰዎች ዛሬ ስደትን እንደመፍትሄ ለመውሰድ ተገደድን። በስደቱ ብቻ ሳያበቃ ሰብአዊነት በማይሰማቸው አካላት እነሆ ብሄራዊ ውርደትን እየተከናነብነው እንገኛለን።
እ.ኤ.አ. በ2004 የደች ንግስት ቢያትሪክስ ታይላንድ ተጉዛ ነበር። ቢያትሪክስ ወደ ታይላንድ የተጓዘችበት ዋነኛው ምክንያት በአደንዛዥ እጽ ዝውውር ታስረው የነበሩ ሁለት ሆላንዳውያንን ለማስፈታት ነው። አርባ እና ሃምሳ አመት ተፈርሮባቸው የነበረው እነዚህ ዜጎች በንግስቲቱ ጉብኝት ወቅት እንዲፈቱ ተደረገ።  የታይላንድና የሆላንድ የኢኮኖሚ ግንኙነት በኢትዮጵያ እና በሳውዲ አረቢያ ካለው የንግድ ትስስር በልጦ አይደለም። ንግስቲቱ በባዶ እጅዋ ወንጀለኛ ዜጎችዋን ማስፈታት ቻለች። ለዜጎችዋ ክብር ስለነበራት። በርግጥ ወንጀል ሰርተዋል። ቅጣቱን እኛው እንስጣቸው ብላ ዜጎችዋን ይዛ ተመለሰች ንግስት ቢያትሪክስ። ሳውዲ አረቢያ የኔዘርላንድን ቆዳ ስፋት በእጥፍ የሚበልጥ መሬት ከኢትዮጵያ ተችራለች። በወንጀል ሳይሆን ይልቁንም በጉልበት ስራ የተሰማሩ ዜጎቻችን የሚፈጸምባቸውን ግፍ ለማስቆም አንድ ሄክታር መሬት ብቻ በቂ ነበር። ሳውዲ በኢትዮጵያ ከ200,000 በላይ ሄክታር ለም መሬት ይዛለች።  ለብሄራው ውድቀታችን እና ውርደታችን ዋነኛው ምክንያት የዜጎቹን ክብር የሚያስቀድም ብሄራዊ  መንግስት ስላጣን እንጂ በዚህ ብቻ ሳውዲን ማስፈራራት ይቻል ነበር።
በሳውዲ ያለው ኢትዮጵያዊ ከ30 ሺህ በላይ ይገመታል። በጉልበቱ ጥሮ እያደረ ያለን ዜጋ ህገወጥ እያሉ ያሳድዱታል። እነሱ ግን በሃገራችን ላይ  እንደአንደኛ ዜጋ በነጻነት የመኖር መብት ተሰጥቷቸዋል። ለሳውዲ ባለሃብቶች የተሰጠው ለም መሬት ለነዚህ ዜጎች ቢሰጥ ኖሮ፤ ወገኖቻችን ባልተሰደዱና ባልተዋረዱ ነበር። 
የኛ ትውልድ፤ ሀገር አልባ፣ ዜግነት አልባ ትውልድ። ከዚህ በላይ የሆነ ብሄራዊ ውርደት የለም።
ጋዜጠኛ ነብዩ ሲራክ ከሳውዲ በላከው ማስታወሻ እንዲህ ይላል፤…
…የእኛን መያዝ የተመለከቱ የሳውዲ ወጣቶች (ሸባቦች) ሚስት እህቶቻችን ይደፍራሉ፣ ንብረታችን ይዘርፋሉ!  ይህ ለሶስት ቀናት ሲቀጥል የደረሰልን የለም! ኢንባሲ ደወልን ምንም ማድረግ አንችልም ይሉናል፣ አንተም ድምጻችንን ታሰማናለህ ብለን ብንደውልልህ ፈራህ መሰል አታነሳልንም! የት እንድረስ? ምን እናድርግ?  ንብረታችን እየተዘረፍን ሴቶቻችን  እየተደፈሩ ዝም ብለን ማየት ነበረብን?  ይህን በመቃወም ሻንጣና ቤተሰቦቻችንን  ይዘን ወደ ሃገራችን ስደዱን ነው ያልናቸው“  የሚል እየተቆጣና ድምጹን ከፍ እያደረገ መልስ የሰጠኝን አንድ ወንድም መጨረሻችሁ ምን ሊሆን ይችላል ? አልኩት “… ወደ ሃገራችን ከነሚስት እህቶቻችን ይውሰዱን ነው የምንለው! ያለበለዚያ መንፉሃን እና ሚስት እህቶቻችን አንለቅም! ገድለው ያስለቅቁን” ሲል ክችም ያለ መልሱን ሰጥቶ ስልኩን ጀሮየ ላይ ዘጋው…
በርግጥ ድርጊቱ አዲስ አይደለም። በአረብ ሃገር ያሉ ኢትዮጵያውያን ሁሌም ይታደናሉ፣ ይደበደባሉ፤  ይገደላሉ፤  እህቶቻችን በግፍ ይደፈራሉ። በባርነት ዘመን እንደሰማነው ሁሉ፤ አሳዳሪዎቻቸው እንደ እቃ ይዋዋሱዋቸዋል። ሲከፋቸ ደግሞ የፈላ ውሃ በቁማቸው ይደፉባቸዋል። ይህ ሁሉ ሲሆን አቤት የሚልላቸው፤ መብታቸውን የሚያስከብርላቸው መንግስት የለም። ሸዋዬ ሞላን የጋዳፊ ቤተሰቦች በቁምዋ ሲይቃጥሏት ይጮህ የነበረው ዲያስፖራው ነበር። ጋዳፊን የነቀለው የሊቢያ አብዮት ሲፋፋም፤ በሊቢያ ነዋሪ የነበሩ የውጭ ዜጎች በየኤምባሲያቸው ሲጠለሉ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን መግቢያ አጥተው ነበር። የኋላ ኋላ በሱዳንና በናይጄርያ ኤምባሲዎች እንዲጠለሉ ተደረገ። በግብጽና በሶሪያም ተመሳሳይ ክስተቶች ተፈጽሟል። በዱባይና በሊባነን በቤት ሰራተኝነት ተቀጥረው ይሰሩ የነበሩ ሴት እህቶቻችን ላይ ያላግባብ የሞት ፍርድ ሲፈረድ፤ ይከራከሩ የነበሩት ኢትዮጵያውያን የሲቪክ ማህበራት ናቸው። የዜጋውን መብት የሚያስቀድም ብሄራዊ መንግስት ቢኖረን ኖሮ እንዲህ ባልተደፈርን ነበር።
አንድ የዚህ ሰለባ የሆነ ወገናችን በፌስቡክ ገጽ ላይ እንዲህ ብሎ ጽፏል።
መንግስታችን‘ ኢትዮዽያውያን አርሶአደሮችና ነባር ነዋሪዎችን ከቀያቸው እየነቀለና እያፈናቀለ ለም መሬታችንለሳዑዲ ባለሃብቶች በመናኛ ዋጋ ይቸበችባል። መሬታቸውን በወያኔ የተነጠቁ ወጣቶቻችን ስራ ፍለጋ ወደ ሳዑዲይሰደዳሉ። በአፀፋው ዐረቦች የተሰደዱ ኢትዮዽያውያን ይገድላሉ። የሳዑዲ ባለሃብቶች ግን መሬታችን ይዘውበገዛ ሀገራችን እንደፈለጉ ይፈነጫሉ። የኢትዮዽያ ‘መንግስት በችግር ላይ ካሉ የኛ ዜጎች ይልቅ ለሳዑዲባለሃብቶች ደህንነት የሚጨነቅ ይመስላል። በእውነት እንደው መቼ ነው ለኛ ደህንነት የሚቆረቆር መንግስትየሚኖረን?
እርግጥ ነው። መንግስታችን ለዜጋው ግድ አይሰጠውም። ሲጀመር ዜጋው ከሀገሩ እንዲሰደድ ያደረገው ብልሹ የሆነ ስርአቱ ነው። እርግማን ይመስል ወገናችን በገዛ ሀገሩ የሚደርስበት በደል በስደት ከሚደርስበት ግፍ አይተናነስም። እዚህም ስቃይ እዚያም ስቃይ። የዘመኑ ወጣት በሁለት ጎን በተሳለ ሰይፍ ገፈት ቀማሽ…።
The suffering of Ethiopians in Saudi Arabia
የሃይሌ ገሪማን  ’ጤዛ’ ፊልም ያስተውሏል? አንበርበር ከጀርመን ሃገር ክብሩን እና አንድ እግሩን ይዞ እትብቱ ወደተቀበረባት ቀዬ ተመለሰ።  አንድ እግሩን በኒዮ-ናዚዎች አጣ። ክብሬ ባላት ሀገሩ የገጠመው መከራ ደግሞ ሊሸከመው የማይችለው ነበር። በትውልድ መንደሩ ወገን ወገኑን እያሳደደ ሲደፋው ሲያይ፣ አንድ እግር ያሳጣው የኒዮ ናዚ ጉዳይ አላሳሰበውም። ወገን ሲጨንቀው ይሰደዳል። ታዲያ የትኛውን እንኮንን? የሳውዲውን? አ’ይ እሱ በራሱ ስራ ይጨነቅበት። የኛው ግን ሊያሳስበን ይገባል። ለም መሬታቸውን እየተቀራመቱ ማፈናቀላቸው ሳየንስ፤ ወጣቱ እንዳለው  ‘ከውጭ የገቡ እንግዶች መልሰው እኛኑ ባይተዋር እያደረጉን ነው።’
እ.ኤ.አ በ1980ዎቹ በርካታ የኩባ ዜጎች የፊደል ካስትሮ መንግስትን በመቃውም ወደ አሜሪካ ገብተዋል።  አሜሪካ የገቡት ኩባውያን የካስትሮን መንግስት ከማውገዝ አርፈው አየውቁም ነበር። ካስትሮ ከ 20 አመታት በኋላ አሜሪካን ለመጀመሪያ ጊዜ ሲጎበኙ፡ “የአሜሪካ መንግስት የኩባ ስደተኞችን መብት እየገፈፈ ነው።”  የሚል ወቀሳ ነበር ያቀረቡት። እናም በስደት ያሉ ኩባውያን መብት እንዲጠበቅ ከአሜሪካ መንግስት ጋር ድርድር ያዙ።  ካስትሮ እዚህ ላይ እንደግለሰብ ሳይሆን እንደመንግስት ነው የሚያስቡት።
የኛዎቹ ግን እንደመንግስት ሳይሆን አሁንም እንደግለሰብ ነው የሚያስቡት። በጅምላ የሚጠሉት ዲያስፖራ ላይ በቀላቸውን እየተወጡ ያሉ ይመስላል። ዛሬ በውጭ ያሉ ወገኖች የሚጮሁትን ያህል እንኳን በስልጣን ላይ ያሉት ድምጻቸውን ቢያሰሙ ኖሮ በወገኖቻችን ላይ የሚደርሰው በደል እዚህ ደረጃ ላይ አይደርስም ነበር።
እንደ ሉአላዊ አካል የሚያስብ ብሄራዊ መንግስት እስኪኖረን ድረስ አሁንም የታማኝ በየነን ፈለግ ተከትለን ለወገኖቻችን መጮህ ግድ ይለናል።

No comments:

Post a Comment