በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተለያዩ ዞንና ወረዳዎች አማራ ናችሁ ተብለው በተባረሩ በሺዎች በሚቆጠሩ ዜጎች ላይ የሰብአዊ መብት ጥሰት እና አካላዊ ጉዳት እንደተፈፀመ የሰብአዊ መብቶች ጉባኤ ባካሄደው ጥናት አረጋግጧል ፡፡
በክልል በተለያዩ ዞንና ወረዳዎች ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ቁጥራቸው ከ10 ሺህ በላይ የሚገመቱ ዜጐች ለረዥም አመታት ይኖሩበት ከነበረው አካባቢያቸው የዚህ ክልል “ተወላጆች አይደላችሁም” በማለት በሀይልና በግዳጅ ቤት ንብረታቸውን ጥለው ከመጋቢት 15/2005 ዓ.ም ጀምሮ እንዲሰደዱ መደረጋቸውን ተቋሙ አውስቷል፡፡
በዚህም ምክንያት ህፃናትና ሴቶች እንዲሁም አቅመ ደካማዎች በቂ ምግብና ህክምና ባለማግኘታቸው በከፍተኛ ችግር ላይ ወድቀው እንደነበር ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ዞን ቡለን ወረዳ ከአካባቢያቸው የተፈናቀሉ ሰዎች ተወካዮቻቸው አቤቱታና የምስክርነት ቃል ማረጋገጡን የሰብአዊ መብቶች ጉባኤ ያካሄደው ጥናት አመልክቷል፡፡
ጉባኤው በአካባቢው በመገኘት የጉዳዩን ስፋትና ተፈናቃዩች በዚህ ጊዜ የሚገኙበትን አጠቃላይ ሁኔታ ለማጣራት መቻሉንም ገልጿል።
ተፈናቃዮቹ አሁን የሚገኙበት ሁኔታ አስቸጋሪ ነው ያለው ሪፖርቱ፤ በአንዳድ አካባቢዎች ለምሳሌ በካማሼ ዞን ተፈናቃዮቹ ወደ ቦታቸው እንዲመለሱ የተደረገ ቢሆንም ከተመለሱ በኃላ ንብረታቸው በመወሰዱና በመጥፋቱ ለመቋቋምና ወደ ነበሩበት የኑሮ ሁኔታ ለመመለስ አልቻሉም ። ለእርሻ ግብዓት የሚሆኑ እንደ ዘር ፣ማዳበሪያ የመሳሰሉትን ለመግዛት አለመቻላቸውን፤ ብድርም ለመውሰድ ሲጠይቁ ብሔረሰባቸው እየተጠቀሰ አድልዎ እየተፈፀሙባቸው እንደሚገኝ የሰመጉ ባለሙያዎች በአካባቢዉ ተገኝተው ባጣሩበት ወቅት ከተጐጂዎቹ አንደበት ለመረዳት ችለዋል፡፡ በመተከል ዞን ቡለን ወረዳ በባሩዳ ቀበሌና በአካባቢው ካሉት ቀበሌዎች የተፈናቀሉት ሰዎች
ብዛት 5 ሺ እንደሆነ የተፈናቃዮዎቹ ተወካዩች የገለፁ ሲሆን እነዚህ ተፈናቃዮች በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ውስጥ በሚገኙት ጓንጓና ቻግኒ ከተሞች ውስጥ በብዛት ይገኛሉ፡፡ ይሁንና በሌሎች አካባቢዎችም በዘመድ ወዳጅ ቤት ውስጥ ተጠግተው እንደሚገኙ የተወሰኑ ተፈናቃዮችና ተወካዮቻቸው ቻግኒ ከተማ ውስጥ ለሰመጉ ባለሙያዎች ለማጣራት በሄዱበት ወቅት አረጋግጠውላቸዋል፡፡ በተለይም ይህንን የማጣራት ስራ በሚሰሩበት ወቅት በቻግኒ ከተማ ውስጥ ብቻ በተለያዩ ቦታዎች ተበታትነው የሚገኙ ተፈናቃዮች ብዛት 500 እንደሚደርስ በአካል ተገኝተው ለመረዳት ችለዋል፡፡
ተፈናቃዮቹ ለሰመጉ እንደሚያስረዱት የደረሰባቸውን ከፍተኛ በደልና እንግልት እንዲሁም የሚገኙበትን አስቸጋሪ ሁኔታ በተለያዩ የሀገር ውስጥ ጋዜጦችና የውጭ ሚዲያ በመናገራቸው ምክንያት እስራት ዛቻና ክትትል እየተፈፀመባቸው እንደሆነና በከፍተኛ ስጋት ላይ እንደሚገኙ በምሬትና የተስፋ መቁረጥ ስሜት በዶቢ፣ ያሶ፣ ባሩዳ ከተማ የተፈናቃይና ተወካዮቻቸው ለሰመጉ ያቀረቡት አቤቱታና የምስክርነት ቃል አስረድቷል፡፡
ለረዥም አመታት ያፈሯቸውን ንብረቶችና የእርሻ መሬታቸውን በአካባቢው ባለስልጣናትና በሌሎች ብሔረሰብ አባላት መነጠቃቸው፣ በባሩዳ ከተማ ህጋዊ በሆነ መንገድ ያፈሯቸው የሚንቀሳቀስና የማይንቀሳቀሱ ንብረቶቻቸውን እንዳያዙበት መደረጋቸው፣ መታወቂያ እንዳያወጡ መከልከላቸው፣ ልጆቻችው በትምህርት ቤቶች ውስጥ ገብተው እንዳይማሩ የተለያዩ አድልኦና ጫና እንዲደርስባቸው መደረጉ፣ በእርሻ ስራ የሚተዳደሩትን አርሶ አደሮችንም የምርጥ ዘርና ማዳበሪያ “የዚህ ክልል ተወላጅ አይደላችሁም” በሚል አድልኦ እንደሚደረግባቸውና እንደሚከለከሉ፣ በጥቅሉም ”እናንተ የዚህ ክልል ባለቤት አይደላችሁም ስለዚህ ለቃችሁ ውጡ” መባላቸውንና ይህንንም በተቃወሙት ላይ ዛቻ፣ ድብደባ፣ ንብረት ነጠቃና ለእሰራት ጭምር እንደተጋለጡ የተፈናቃይ ተወካዮች ለሰመጉ በፃፉት ከ140 በላይ ተፈናቃዮች ፊርማ ያረፈበት ማመልከቻና የተለያዩ ሰነዶች አመልክተዋል፡፡
የባሩዳ ቀበሌ ተፈናቃዮች “ በአካባቢው አስተዳደር አካላትና በሌሎች የክልሉ ብሄረሰብ አባላት የተነጠቁትን የተለያዩ ንብረቶች ተመላሽ አለመደረጉን ፣በአሁኑ ወቅት ከሌሎች ብሄረሰቦች እየተለዩ ማስፈራሪያና ድብደባ እየተፈፀመባቸው መሆኑ፣ ምንም አይነት እገዛና ማቋቋሚያ አለመደረጉ፣ የእርሻ ግብዓትን እንደ ዘር ማዳበሪያ ያሉ ግብዓቶችን “እናንነተ የዚህ (ብሄር) አባላት ናችሁ” በማለት እየተከለከሉ ነገር ግን ለሌሎች እየተሰጠ እንደሚገኝና በፌዴራል መንግስት አማካኝነት ቢመለሱም የዞንና የቀበሌ አስተዳደር አካላት “እናንተ ከዚህ ክልል ውጪ ናችሁ” በማለት ልዩ ልዩ አድልዎና መገለል እየተፈፀመባቸው እንደሚገኝ ለሰመጉ አመልክተዋል፡፡
ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚገኙ የአማራ ተወላጆች ለረዥም አመታት ይኖሩበት ከነበረው ቦታ “ የዚህ አካባቢ ሰዎች አይደላችሁም” በማለት ከተፈናቀሉ በኋላ ወደ ነበሩበት ቦታ ይመለሱ እንጂ ምንም አይነት እገዛ ከመንግስት እንዳልተደረገላቸውና ይባስ ብሎም እንግልትና የተለያዩ አስተዳደራዊ በደሎች እየተፈፀመባቸው እንዳለ ዘጋቢያችን ሪፖርቱን ተከትሎ ባደረገው ማጣራት ለማረጋገጥ መቻሉን ገልጿል።
No comments:
Post a Comment