Wednesday 11 June 2014

የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ (ሸንጎ) Ethiopian People's Congress for United Struggle (Shengo)

የአንድነትና መኢአድ ስምምነት፣ ሊበረታታ የሚገባው መልካም ተግባር!
ሰኔ 2፣ 2006 (June 9, 2014)
የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ(ሸንጎ)፣ የመላ ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት(መኢአድ)ና አንድነት ለዴሚክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) በትላንትናው ዕለት ለውህደት  የሚያበቃ የመጀመሪያ ስምምነት በመፈራረማቸው የተሰማውን ታላቅ ደስታና አድናቆት ይገልጣል።  
ዘላቂና አስተማማኝ ሰላም የሰፈነባት፣ የህግ የበላይነት የተረጋገጠባትና የሰብዓዊ መብቶች ሳይሸራረፉ እውን የሚሆንባት፣ በዜጎች እኩልነት ላይ የጸና መሰረት ያላት ዴሞክራሲያዊት ሀገር በጋራ ለመገንባት እንድንችል የስርዓት ለውጥን የሚሹ የተቃዋሚ ድርጅቶች  ሁሉ ጥቃቅን ልዩነቶችን ትተው በመተባበርና አንድ ላይ በመምጣት ህዝባዊ ኃይሉ በአንድነት በመቆም አምባገነናዊነትን በጽናት እንዲታገል ማብቃት ይጠበቅባቸዋል። 
ከዚህም አንጻር፣ ውስብስብ ችግሮችን አልፈውና የብቸኛነት ድንበርን ሰብረው በአንድነትና በጋራ ዓላማ መሰለፍን መምረጥ ትልቅ አስተዋይነትና ለወደፊት ጉዞም አስተማማኝ መሰረትን የሚጥል  በመሆኑ በሁለቱ ድርጅቶች በኩል የደረሱበት ቅድመ ውህደት ስምምነት ትልቅ ተስፋ ሰጭና  በሁሉም የአንድነትና የዴሞርራሲ ኃይላት ሊበረታታ የሚገባ ነው።  ሌሎቹም በተናጠል እየታገሉ የሚገኙ በኢትዮጵያዊነታቸውና በኢትዮጵያ አንድነት የሚያምኑ ኃይሎች ይህን የመኢአድንና የአንድነትን ፈለግ እንደምሳሌ ወስደው የመተባበርንና የአንድ የመሆንን ጎዳና እንዲመርጡና   አስፈላጊውን እርምጃም ሳይዘገዩ እንዲወስዱ  በአንክሮ ለማሳሰብ እንወዳለን። 
እንደዚህ ያሉ ሂደቶች እንዳይሳኩ በጸረ አንድነት ሃይሎች መሰናክሎች መዘርጋታቸው አይቀሬ ነው። ህወሓት/ኢሕአዴግ   ለሚሸርበው ተንኮልና ለሚያደርሰው ጉዳት ፣ ሳይበገሩ  ያሰቡትን ዓላማ ከግብ ማድረስ ግን  የጀግንነት ሙያ ነው።
የአንድነትና የመኢአድ አባላትና መሪዎች ለገጠማቸው ችግርና የገዥው ቡድን ተጽዕኖ ሳይንበረከኩ ወዳቀዱት የውህደት መጀመሪያ ደረጃ ላይ መድረሳቸው ሊያኮራቸው የሚገባና የሚመሰገኑበት ሲሆን ወደ ዘላቂ ግብ ለመድረስም በሚያደርጉት ጉዞ የበለጠ  መሰናክልና ዕይን ያወጣ አፍራሽ ፈተና ሊገጥማቸው እንደሚችል አውቀው እስካሁን እንዳደረጉት ሁሉ  በድፍረትና በብልሀት የጀመሩትን ጉዞ በስኬት እንደሚያጠናቅቁ ታላቅ ተስፋችን ነው።
የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ (ሸንጎ) ቀደም ሲልም ሆነ አሁንና ወደፊት በተናጠል የቆመው የአንድነትና የዴሞክራሲ ጎራ ተባብሮ በአንድ የጋራ አመራር ስር ተሰልፎ ትግሉን አቀናጅቶ እንዲቀጥል ማድረግ ከተመሰረተባቸውና እውን ለማድረግ  ከፍተኛ ጥረት ከሚያደርግባቸው ዋና ዋና ራዕዮቹ ውስጥ አንዱ ነው። ስለሆነም፣ በመኢአድና በአንድነት መካከል የተጀመረው የውህደት ሂደት ያስደሰተው ሲሆን ከፍጻሜ ደርሶ ለማየት ከፍተኛ ጉጉት አለው። ጅምሩ የተሳካ እንዲሆን ምኞቱን እየገለጸ ለቀጣዩ የትግል ጉዞ አብሮ ለመቆም ያለውን ፍላጎትና አጋርነቱን ከወዲሁ ሊገልጽ ይወዳል።
አንድነታችን  ለድላችን  ዋስትናችን ነው።
የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ(ሸንጎ)  

No comments:

Post a Comment