Wednesday, 5 November 2014

ሚሊዮኖች ድምጽ – የአንድነት የአዲስ አበባ ምክር ቤትን ይተዋወቁ

የአንድነት ፓርቲ በተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች መዋቅሩን የዘረጋ ድርጅት ነው። ወደ አምስት ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ በሚኖርባት አዲስ አበባ ፣ ፓርቲው እስከታች በመዝለቅ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ድርጅታዊ መዋቅሩን ዘርግቶ የሚንቀሳቀስ ነው።
- የአዲስ አበባ ምክር ቤት የተቋቋመው በአዲስ አበባ ከሚገኙ 23 የምርጫ ወረዳዎች በተወከሉ ስድስት ስድስት አባላት ነው። በአጠቃላይ 138 አባላት አሉት።
- በ23ቱም የምርጫ ወረዳዎች ፣ ዘጠኝ የወረዳው የስራ አስፈፃሚ አባላት ያሉት ሲሆን፣ በ116 መንግስታዊ መዋቅር ወረዳዎች 5 የመሰረታዊ ድርጅት አመራር አባላት አሉት
- ከወረዳ መዋቅር በተጨማሪ፣ ከአሥሩም ክፍለ ከተማ ተመርጠው የመጡ፣ በአጠቃላይ 70 የክፍለ ከተማ አስተባባሪዎች አሉት።
በአጠቃላይ በአዲስ አበባ አንድነት ዉስጥ ያሉ አመራሮች፣ በድምሩ 895 ሲሆኑ፣ አንድነት በሺዎች የሚቆጠሩ አባላትና ደጋፊዎች በአዲስ አበባ ያሉት፣ በትልቅ ህዝባዊ መሰረት ላይ የታነጸ ድርጅት ነው።
አንድ ድርጅት ለዉጥ ሊያመጣ የሚችለው ሕዝቡን ከላይ እስከ ታች ማደራጀት ሲችል ነው። አገዛዙ ኢሕአዴግ ስማቸው በምርጫ ቦርድ ሰነድ ላይ ብቻ የሚታወቁ፣ ወደ ሕዝብ የማይሄዱና ሕዝቡን የማያደራጁ፣ ገለባ ድርጅቶችን ብቻ ነው ማየት የሚፈልገው። በየወረዳው ህዝቡ ለመብቱና ለመጻነቱ እንዲነሳ ድርጅታዊ ሥራ የሚሰራን ፣ እንደ አንድነት ፓርቲ ያለ ድርጅት፣ ለገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ አይመቸዉም። ስለዚህም ነው አንድነት ፓርቲ በየጊዜው፣ ሕገ-ውጥ በሆነ መንገድ የአገዛዙ ዱላ እያረፈበት ያለው።
ሆኖም አንድነት፣ የሕዝብ ድጋፍ ያለው እንደመሆኑ፣ የሚነሳበትን ዱላ ተቋቁሞ ትግሉን እየመራ ነው። የአዲስ አበባ አንድነት አሁን ከተደረገው በላይ የአባላትን ቁጥር ለማስደግ፣ ለሕዝቡ የጠራና የተሻለ አማራጭ ሆኖ ለመቅረብ፣ በአዲስ አበባ ሃያ ሶስቱም ወረዳዎች ጠንካራ ተወዳዳሪ ለማሰለፍ፣ የቀረቡ ተወዳዳሪዎች በሕዝቡ እንዲመረጡ ከፍተኛ ቅስቀሳ በማድረግና ህዝቡ የሰጠዉም ድምጽ እንዳይሰረቅ ነቅቶ ለመቆጣጣር የሚቻልበትን ሁኔት ከወዲሁ ለማመቻቸት በመንቀሳቀስ ላይ ያለ፣ ከኢሕአዴግ ቀጠሎ መረቡን በስፋት የዘረጋ ብቸኛ ድርጅት ነው።
የአዲስ አበባ ምክር ቤት ይህን ሲመስል፣ የአንድነት ፓርቲ በተመሳሳይ ሁኔታ በአዳማ፣ በባህር ዳር፣ በጂንካ፣ በአርባ ምንጭ፣ በሶዶ፣ በአሰላ ፣ በመቀሌ ..እንዲሁም በርካታ ከተሞችና ዞኖች ሰፊ መዋቅር ያለው ድርጅት እንደሆነም ይታወቃል።
ለዉጥ ስለተመኘነው አይመጣም። ለዉጥ ሥራ ይጠይቃል። ነጻነት ዋጋ ያስከፍላል። ህዝቡን ለመብቱና ለነፃነቱ እንዲነሳ፣ ሕዝቡን እስከታች ድረስ ማደራጀት ያስፈልጋል። የአንድነት ፓርቲ በአዲስ አበባ በ23 ወረዳዎች እያደረገ ያለውም ይሄንኑ ነው።
እንግዲህ በዚህ ወሳኝ ወቅት፣ በአገር ዉስጥም ሆነ ከአገር ዉጭ የምንኖር ኢትዮጵያዉያን ትግሉን በመቀላቀል የአንድነት አባል እንሁን። በአገራችን ያለው መጠነ ሰፊ ችግሮችን የኑሮ ዉድነቱን፣ የፍትህ መጓደሉን፣ ዘረኝነቱን እየተነጋገርን ከምናወራ ብሶትና ምሬት ጎን ለጎን፣ መፍትሄ ልናመጣ እንደምንችል በማሰብ “እስከ መቼ ? ብለን በመጠየቅ በግልና በቡድን ምን ማድረግ እንዳለብን እንደ ዜጋ መነጋገር መጀመር አለብን። በግላችን “ የለውጥ አካል እሆናለሁ” ብለን ልንነሳ ያስፈልጋል። ሁሉም በግሉ ዉሳኔ ከወሰነ፣ አንድ ተብሎ አሥር ሚሊዮኖች እንሆናለን።UDJ-SEAL

No comments:

Post a Comment