Thursday, 17 December 2015

ትግላችንን ተጠናክሮ በአንድነት ይቀጥል! (አርበኞች ግንቦት7)

የኢትዮጵያ ህዝብ ለመብቱ በያቅጣጫው መነሳቱ የሚያኮራ ነው። ባለፉት 3 ዓመታት ብቻ ሙስሊም ኢትዮጵያውያን ያደረጉትን የመብት ትግል ጨምሮ በደቡብ፣ አማራ፣ አፋር፣ ጋምቤላና በሌሎችም አካባቢዎች በርካታ የነጻነት ትግሎች ተካሂደዋል። አሁን በኦሮምያ እና በአማራ በተለይም በሰሜን ጎንደር አካባቢዎች እየተካሄዱ ያሉት የነጻነት ትግሎች የአጠቃላዩ የነጻነት ትግል አካሎች ናቸው። በእነዚህ የነጻነት ትግሎች ገዢው ፓርቲ ከህዝብ ጋር ለምንጊዜውም መለያየቱን ለማየት ችለናል። ስልጣኑን ለማስጠበቅ ሲልም፣ አቅሙ ቢፈቅድለትና ማግኘት ቢችል በምድር ላይ ያሉትን ጅምላ ጨራሽ መሳሪያዎችን ሁሉ በገዛ ህዝቡ ላይ ለመጠቀም ወደ ሁዋላ የማይል የአረመኔዎች ስብስብ መሆኑን አረጋግጠናል። በጭካኔውና በፍርሃቱ ብዛት የተነሳ በርካታ ሙስሊሞች፣ ክርስቲያኖች፣ መብታቸውን በሰላም ለመጠየቅ ወደ አደባባይ የወጡ ወጣቶች ተገድለዋል፤ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎችና ጋዜጠኞች በእስር ተንገላተዋል፤ በእስር ቤትም ማንነታቸውን ከማዋረድ ጀምሮ የተለያዩ አካላዊ ጥቃቶች ተፈጽሞባቸዋል።
የኦሮሞ ህዝብ መብቴ ይከበርልኝ ብሎ መነሳቱን ተከትሎ ኢትዮጵያውያን ከያቅጣጫው ድጋፋቸውን እየገለጹ ነው። ይህ ለነጻነት ሃይሎች ብስራት ሲሆን ዘርን ከዘር በማጋጨት የስልጣን እድሜውን ለማራዘም ለሚፈልገው የሽፍታ አገዛዝ ደግሞ ትልቅ መርዶ ነው። ባለፉት 25 ዓመታት ወያኔ አንዱን ዘር ከሌላው ዘር እያጋጨ፣ በወንድማማቾችና እህትማማቾች መካከል መተማመን እንዳይፈጥር መርዙን ሲረጭ ቆይቷል፤ ያሰበው አልሰምርለት ሲል ደግሞ በአገሪቱ አንጡራ ሃብት በሸመተው ጠመንጃ ለመብቱ የተነሳውን ህዝብ ደረት ደረቱን እየመታ ፈጅቶታል። በተለይም የአማራው ህዝብ ከሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር በአንድነት ተሰልፎ በህወሃት አገዛዝ ላይ የነጻነት ክንዱን ለማሳረፍ እንዳይችል ሌት ተቀን የጥላቻ መርዙን በመርጨት ከሌላው ህዝብ ጋር እንዲጋጭ ለማድረግ በእጅጉ ደክሟል። ወያኔ የረጨውን የጥላቻ መርዝ የኦሮሞ እና የአማራ ልጆች በጋራ እያረከሱት መገኘታቸው፣ የሌሎች ብሄሮችና ብሄረሰቦች ህዝቦችም እንዲሁ ” አንለያይም” በማለት በጋራ ለመሰለፍና ትግሉን ለማቀጣጠል ዝግጁነታቸውን መግለጻቸውና በተግባር እያሳዩ መምጣታቸው የ25 አመታት የወያኔ የአፈናና የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲ እያከተመ መምጣቱን የሚያመላክት ነው። ወያኔ የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲው በመላው ኢትዮጵያውያን ትብብር እንደረከሰበት ሲያውቅ ደግሞ የግድያ አዋጅ አውጥቶ በ-ኢትዮጵያውያኑ ላይ ጥይት አርከፍክፎ ጸጥ ሊያሰኛው መዘጋጀቱን በአዋጅ አስነግሯል። ከታሪክ መማር የማይችለው ጠባቡ ወያኔ፣ ህዝባቸውን አዋጅ አስነግረው የገደሉ ጨቋኝ መንግስታት መጨረሻቸው ምን እንደነበረ እንኳን ቆም ብሎ ማሰብ አልቻለም። ዛሬ የእሳት ላንቃ በሚተፋ ጠመንጃቸው ሊጨፈልቀው የሚያስበው ህዝብ ነገ መልሶ ራሱን እንደሚጨፈልቀው ለአፍታም ቢሆን ለማሰላሰል አልቻለም። የዘረፈው ሃብትና የታጠቀው መሳሪያ አእምሮውን ደፍኖት፣ እየመጣ ያለውን ህዝባዊ ሱናሚ ለማየት ተስኖታል። በጦር መሳሪያ ጋጋታና ድንፋታ ቢሆን ኖሮ ወራሪዋ ጣሊያን እስከዛሬ ድረስ ከአገራችን ለቃ ባልወጣች ነበር፣ በጦር መሳሪያ ጋጋታ ቢሆን ኖሮ እነ ጋዳፊን ዛሬ ቤተመንግስት እንጅ መቃብር ውስጥ አናገኛቸውም ነበር።
የአገራችን ህዝብ ከመቼውም ጊዜ በላይ ለነጻነቱ የሚያደርገውን ትግል በጥንቃቄ የሚመራበት ጊዜ ላይ ነን ። የገጠመን ጠላት በታሪካችን አይተነው የማናውቅ፣ የገዛ ህዝቡን በጠላትነት ፈርጆ ሊያጠፋው የተነሳ በመሆኑ፣ አገዛዙ እስከዛሬ ካደረሰው ጥፋት ሌላ ተጨማሪ ጥፋት ሳያጠፋ፣ ከአገራችን መሬት ለመንቀል እንድንችል እርምጃችን ሁሉ ጥንቃቄ የተሞላበት ሊሆን ይገባል። ጠላታችን ህዝብን ከህዝብ ለማፋጀት ያለ የሌለ ሃይሉን የሚጠቀም መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ አቅሙ በፈቀደለት መጠን ሁሉ ህዝቡን በጅምላ ለመፍጀት ወደ ሁዋላ የማይል ነው። ህዝቡ የጠላቱን አውሬነት ተገንዝቦ እሱ በሚከፍተው ቀዳዳ ዘው ብሎ ላለመግባት መጠንቀቅ አለበት። ሊገድሉን ሲመጡ ዘወር ብሎ በማሳለፍ፣ እንደገና ደግሞ ወደ አደባባይ በመውጣት፣ እንዲሁም የተቃውሞውን አድማስ በማስፋትና የሃይል መከፋፈል እንዲፈጠር በማድረግ ወያኔን አዳክሞና ተስፋ አስቆርጦ ካለሙት ግብ መድረስ ይቻላል። አሁን እየታየ ያለው አንድነት ይበልጥ እየተጠናከረ፣ ከኦሮሞው ጎን አማራው፣ ከአማራው ጎን ጉራጌው፣ ከጉራጌው ጎን ትግሬው፣ ከትግሬው ጎን አፋሩ፣ ከአፋሩ ጎን ጋምቤላው፣ ከጋምቤላው ጎን ሀረሪው፣ ከሃረሪው ጎን ጉሙዙ፣ ከጉሙዙ ጎን አዲስ አበቤው፣ ከአዲስ አበቤው ጎን ጋሞው በአጠቃላይ መላው ህዝብ እጅ ለእጅ እየተያያዘ የነጻነት ባበሩ ወደፊት እንዲሮጥ ማድረግ አለበት። ወጣቱ ራሱን ባለበት ቦታ እያደራጀና አመራር እየሰጠ በያቅጣጫው የጀመረውን የነጻነት ትግል አጠናክሮ ይቀጥል።
አርበኞች ግንቦት7 ትግሉን በተለያዩ አቅጣጫዎች አጠናክሮ ቀጥሎአል፤ የአርበኛው ሰራዊት የወያኔን ጀሌዎች በቀኝና በግራ መውጫና መግቢያ እያሳጣቸው ነው። የንቅናቄው አባላት በዳር አገር በአፈሙዝ፣ በመሃል አገር ደግሞ ወጣቱን እያደራጁ ለትግል እንዲሰልፍ እያደረጉት ነው። የንቅናቄያችን መሪ ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ፣ “ከነጻነት ትግሎች ጎን አለን” እንዳሉት የአርበኛው ልጆች ፊት ለፊት ተሰልፈው አመራር በመስጠት የነጻነት ትግሉን ለማቀጣጠል እና መከፈል ያለበትን የህይወት መስዋትነት ለመክፈል ተዘጋጅተው በያቅጣጫው እየተንቀሳቀሱ ነው።
ተደጋግሞ እንደተነገረው የአርበኞች ግንቦት7 አላማ በአገራችን የዲሞክራሲያዊ የሽግግር ስርዓት ማስጀመር ነው። ሁሉም ኢትዮጵያዊ በዚህ አላማ ዙሪያ ተሰልፎ ትግሉን ይቀጥል። ይህን አላማ የሚደግፉ የፖለቲካ ድርጅቶችም ዛሬውኑ ከጎናችን ተሰልፈው ወያኔን ለማስወገድ በሚደረገው የሞት ሽረት ትግል ይሰለፉ!
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!
አገራችን በልጆቿ ነጻ ትወጣለች!
አርበኞች ግንቦት7

No comments:

Post a Comment