አቶ በቀለ ነጋ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ዋና ጸሀፊ ሁኔታውን እንዲህ በማለት ገልጸውታል፣
———————–
ወዳጆቼ
ዛሬ ማለዳ ወደ ስራ እያመራሁ ሲቪል የለበሱ 4 ሰዎች ስሜን ጠርተው ሰላምታ ካቀረቡልኝ በኋላ ፖሊሶች መሆናቸውን ነግረውኝ እኔን ካስቆሙበት ቦታ አጠገብ ወደሚገኘው መኪናቸው እንድገባ ጠየቁኝ።ፈቃደኛ አለመሆኔን ስነግራቸውም እጆቼን ይዘው እየጎተቱኝ በመኪናቸው የኋላ መቀመጫ ላይ እንድቀመጥ አድርገውኝ መንዳት ጀመሩ።
መኪናው መንቀሳቀስ እንደጀመረም መማታት ጀመሩ፣ በቀኝና በግራዬ የተቀመጡት ሁለት ሰዎች ሲደበድቡኝ ጋቢና የተቀመጠው ወደኋላ ዞሮ በመሳሪያው ፊቴን ይነካ ነበር።
እየደበደቡኝ ይህንን የሚያደርጉት ማስጠንቀቂያቸውን ችላ ብዬ ለሚዲያ መረጃ በመስጠቴ እንደሆነ ይነግሩኝ ነበር ።ድብደባቸውን እንዳቆሙም መሳሪቸውን እንደደገኑ ስልኬን ወሰዱብኝ ።የሚሉኝን ካላደረግኩም ለእኔና ለቤተሰቦቼ እንደሚመጡ አስፈራርተውኛል።
“ከዛሬ ጀምሮ ከቤትህ ብትወጣ ወይ ሚዲያ ብታናግር በአንተም ሆነ በቤተሰቦችህ ላይ ለሚሆነው ነገር ሃላፊነቱ ያንተ ነው” ብለውኛል።
የእኔ ብቻ ሳይሆን የቤተሰቦቼ ህይወት አደጋ ውስጥ እንደሆነ በመንገርም ከመልቀቃቸው በፊት የሚሉኝን ካላደረኩ እንደሚገሉኝ ዝተውብኛል።
“ከእንግዲህ ወዲህ እናንተን የምናስርበት ቦታ የለንም:: ወይ እንገድልሃለን ወይ በመኪና ገጭተን ፓራላይዝ እናደርግሃለን ”ብለውኛል።
የኢትዮጵያ መንግስት በኦሮሚያ ክልል ብዙዎች እያቀረቡለት ለሚገኘው አቤቱታ ጆሮውን ደፍኖ ሰላማዊውን ጥያቄ በኃይል ለማፈን እየሰራ በመሆኑ ያለምንም ኃላፊነት ዜጎችን እያሰረ፣እያዋረደና እየገደለ ይገኛል።
በቀለ ገርባ፣ ደጀን ጣፋ፣ አዲሱ ቡላላና ደስታ ዲንቃን ጨምሮ 4.000 የሚደርሱ የፓርቲያችን አባላት በግፍ ታስረዋል።
መንግስትና ሁኔታውን በፀጥታ እየተመለከቱ የሚገኙ አካላት ንፁሃንን ማሰርና መግደል የሚልዮኖችን ህጋዊ ጥያቄ ለማፈን መፍትሔ እንደማይሆንና ኦሮሞውንም ይህ ድርጊት እንደማያስቆመው ይገነባሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።
እስከዛው ግን እንደግለሰብና እንደ ኦፌኮ አባልነቴ በሰላማዊ አግባብ የኦሮሞ ህዝብ አንደበት መሆኔን እቀጥላለሁ ።ምክንያቱም ለነፃነትና ለህዝባችን ክብር ስንል በምንከተለው ሰላማዊ ትግል እኔና ሚልዮን ኦሮሞዎች ህይወታችንን ጭምር ለመክፈል ተዘጋጅተናል።
ከአክብሮት ጋር
በቀለ ነጋ
የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ዋና ጸሀፊ
No comments:
Post a Comment