Thursday 26 December 2013

አንድነትና የሚሊየንም ድምጽ ለነጻነት ንቅናቄ – አማኑኤል ዘሰላም

ታህሳስ 15 ቀን 2006 ዓ.ም
 
የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር፣ አቶ ይልቃል ጌትነት፣ በዉጭ አገር የሥራ ጉብኘት እያደረጉ እንደሆነ በስፋት እየተዘገበ ነዉ። ታዲያ «ስለ ሰማያዊ ብዙ እየሰማን፣ የአንድነት ፓርቲ ድምጽ ግን ምነዉ ጠፋ። የሚሊየነሞች ድምጽ ለነጻነትስ ወዴት ገባ ?» ብለን የምንጠይቅ ልንኖር እንደምንችል አስባለሁ። በዚህም ረገድ በአንድነት ፓርቲ ዙሪያ አንዳንድ ሃሳቦች ለአንባቢያን ለማካፈል እሞክራለሁ።
በቅድሚያ አንድ መረዳት ያለብን ነገር አለ። የአንድነት ፓርቲና እና ሰማያዊ ፓርቲ፣ ሁለቱም ተመሳሳይ የፖለቲካ ፕሮግራም ቢኖራቸውም ፣ ሁለቱም ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለዉጥ ለማምጣት ቢታገሉም፣ የአሰራር ልዩነቶች አሏቸው። የአንድነት ፓርቲ፣ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ የትግሉ አካል እንደሆነ ቢያውቅም፣ መሰለፍ ብቻ በራሱ ምንም ሊያደርግ እንደማይችል ጠንቅቆ የተረዳ ደርጅት ነዉ። በዚህም ምክንያት ግብታዊ የሆኑ እንቅስቃሴዎችን ከማድረግ ብዙ ይቆጠባል። ሰልፎችም ሆነ ማናቸዉም አይነት ሰላማዊ እንቅስቅሴዎች ተጠንተዉ፣ በጥንቃቄና ዉጤት በሚያመጣ መልኩ መደረግ አለባቸው ብሎ ያማናል። ካለፈው የቅንጀት ስህተቶች ብዙ የተማረ ነው።
በመሆኑም ሰልፍ አልተደረገም ማለት እንቅስቃሴ የለም ማለት አይደለም። የአንድነት ፓርቲ በአሁኑ ወቅት እያደረጋቸው ያላቸዉን አራት በጣም አስፈላጊና መሰረታዊ ጉዳዮች እንዳካፍል ይፈቀድልኝ፡
1. አንድነት፣ ከሰኔ እስከ መስክረም የተደረገዉን የሚሊየኖችም ድምጽ ለነጻነት እንቅስቃሴዎች፣ እንዲሁም የፓርቲዉ ጠቅላላ ስራዎች፣ ወደ ኋላ ተመልሶ ግምገማ እያደረገ ነዉ። «የቱ መስተካከል አለበት ? የቱ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ? ..»እየተባለ ፣ ጠቃሚ ትምህርቶችን ለማሰባሰብ እየተሞከረ ነዉ። ዝም ብሎ መሮጥ አይደለም። ቆም ብሎም ማሰብና እራስን መመርመር፣ ካለፉትን ተግባራት መማር ያስፈልጋል።
2. ፓርቲው በቅርቡ የአመራር አባላትን ይመርጣል። አብዛኞቹ አገር ዉስጥም ሆነ በዉጭ ያሉ ድርጅቶች አንድ መሪ ነው ለዝንተ አለም የሚመራቸው። የአንድነት ፓርቲን መጀመሪያ ብርቱካን ሚደቅሳ፣ ከዚያም ኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራዉ፣ ከዚያም ዶር ነጋሶ ጊዳዳ መርተዋል። አሁን ደግሞ ዶር ነጋሶን ለመተካት ሶስት እጩዎች የምረጡኝ ዘመቻ ላይ ናቸው። እነርሱም የፓርላማ አባል የተከበሩ አቶ ግርማ ሰይፉ፣ ቀድሞ ፓርቲዉን ሲመሩ የነበሩትና በበርካታ አባላት እንደገና እንዲወዳደሩ ግፊት እንደተደረገባቸው የሚነገረዉ፣ አንጋፋው ኢንጂነር ግዛቸው እንዲሁም ኮንሴንሰን ቢልድ በማድረግና በአስተዋይነታቸው የሚታወቁት፣ በአሁኑ ወቅት ፓርቲዉን በፋይናንስ ሃላፊነት የሚመሩት፣ አቶ ተክሌ በቀለ ናቸው።ይህ በአንድነት ዉስጥ እየተደረገ ያለው ፉክክር ፣ በማንም የአገራችን ድርጅቶች ያልታየ ዴሞክራሲያዊ  ፉክክር ነዉ።
3. እርግጥ ነዉ ከአሁን ለአሁን ሕብረት ያስፈልጋል ተብሎ፣ ወደ ኋላ ከሚጎትትና ስራን ከማያሰራ ድርጅት ጋር ሕብረት አይፈጠርም። ሕብረት ሲፈጠር ለዉጤት መሆን አለበት። በዚህም ረገድ አንድነት ከዚህ በፊት አካል ከሆናቸው እንደነ መድረክ ካሉ ስብስቦች ጋር ያለዉን ግንኙነት እየፈተሸ ነዉ። በአንጻሩም ደግሞ ፓርቲውን ሆነ ትግሉ ወደፊት እንዲሄድ ሊረዱ የሚችሉ ፣ ከሌሎች ድርጅቶች ጋር ፣ የላይ ላይ ትብብር ሳይሆን የዉህደት እንቅስቃሴ እያደረገ ነዉ። ከዚህ በፊት እንደ ብርሃን ፓርቲ ያሉ ድርጅቶች ከአንድነት ጋር መዋሃዳቸው ይታወቃል። አሁን ደግሞ አንድነት ፓርቲ ከአንጋፋዉ መኢአድና በአሁኑ ወቅት አስደሳች እንቅስቅሴ በሜዳ ላይ አያደረገ ካለው ከአረና ጋር ለመዋሃድ ትልቅ ሥራ እየሰራ ነዉ።
4. ሰላማዊ ሰልፍ ሆነ ሌላም ሌላም እንቅስቅሴዎች እንዲሁ በግብታዊነት አይሰሩም። ጥናት፣ ጥንቃቄ፣ ዝግጅት ያስፈልጋል። የስሜት ትግል የትም አያደርሰም። ትግሉ የሰከነ፣ የበሰለና ዉጤት የሚያመጣ መሆን አለበት። የአንድነት ፓርቲ የሚሊየነም ድምጽ ለነጻነት በሚል ስም የጀመረው እንቅስቃሴ ክፍል ሁለት፣ ከአመራር አባላት ምርጫ በኋላ፣ ይታወጃል። ይህ እንቅስቃሴ አዲስ አበባ ዉስጥ ብቻ ያተኮረ ሳይሆን፣ በመላ አገሩቷ ያተኮረ፣ ትግሉን አንድ እርምጃ ወደፊት የሚወስድ እንቅስቃሴ ይሆናል። ለዚህም እንዲረዳ አባላት በሰላማዊ ትግል ዙሪያ የተለያዩ ስልጠናዎች እየወሰዱ ናቸው።
እንግዲህ አገር ዉስጥና ከአገር ውጭ ለምትኖሩ ኢትዮጵያዊያን እንዲህ እላለሁ። በአገራችን ሙስና የመስፋፋቱ፣ ዘረኝነት የመብዛቱ፣ የሕግ ስርዓት ያለመኖሩ፣ የኑሮ ዉድነቱ፣ የሰባአዊ መብት ረገጣዉ ፣ ኢትዮጵያ ለብዙሃኑ ሲኦል፣ ከገዢው ፓርቲ ጋር ግንኙነት ስላላቸው ብቻ በአጭር ጊዜ ዉስጥ ሚሊየንር ለሆኑት ለጥቂቶች ገነት ለመሆኗ ምክንያቱ የፖለቲካዉ ችግር ነው። የፖለቲካ ችግርን ለማስተካከል ደግሞ የፖለቲክ ትግል ይጠይቃል። የአንድነት ፓርቲ ይህ ለሰላምና ለፍትህ የሚደረገዉን የፖለቲክ ትግል ለመምራት እየሰራ ነዉ።
የአንድነት ፓርቲ ከሁለት ወራት በፊት ባደረጋቸው አገረ ሰፊ፣ የሚሊየም ድምጽ ለነጻነት እንቅስቃሴዎች፣ በአዲስ አበባ፣ በመቀሌ፣ በጎንደር፣ በባህር ዳር፣ በደሴ፣ በጂንካ፣ በአርባ ምንጭ፣ በወላይታ ሶዳ፣ በባሌ/ሮቢ ፣ በፍቼና በአዳማ ሰላማዊ ሰልፎች አድርጓል። በመቀሌ ሰልፉ ሊደረግ አንድ ቀን ሲቀረዉ የሕወሃት ባለስልጣናት «እንኳን አንድነት፣ ቅንጅትም መቀሌን አልደፈረም»በሚል የቅስቀሳ መኪናዎችን እና ማይክሮፎኖችን በማገታቸውና የአመራር አባላትን በማሰራቸው፣ ከአሥር አምስት ቀናት ቅስቀሳ በኋላ ሰልፉ ሊሰረዝ ችሏል። በባሌ/ሮቢ፣ ኦሕድዶች ሰልፉ ከመደረጉ አንድ ቀን በፊት፣ «ሰልፉን ካደረጋቸው ከፍተኛ ደም መፋሰስ ይሆናል» የሚል ዛቻ በመሰንዘራቸው ፣ ሕዝብን አደጋ ላይ ላለመጣል ሲባል፣ ሰልፉ ሳይደረግ ቀርቷል።
የአንድነት ፓርቲ በአዋሳ፣ በጋምቤላ፣ በወሊሶ፣ በድርደዋና በአሳሳም ሰልፎች ለማድረግ እቅድ ነበረዉ። ነገር ግን በገንዘብ ማነስ ምክንያት እነዚህ ከተሞች ሰልፍ ማድረግ እንዳልተቻለ ነው።
አሁንም ፓርቲዉ የተቻለዉን ለማድረግ የወሰነነ የቆረጠ ቢሆንም፣ ፓርቲዉ የሕዝብ ድጋፍ ከሌለዉ ሊያደርግ የሚችለው የተወሰነ ነዉ። በተለይም የገንዘብ አቅም ላይ ትልቅ ትኩረት መስጠት እፈልጋለሁ። እንዲሁ ለዉጥ ስለተመኘን ለዉጥ አይመጣም። አገር ቤት ያሉ ኢትዮጵያዉያን በጓዳና በሹክሹክታ ብሳታችንን መግለጽ ማቆም ይኖርብናል። ትግሉ የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊን ተሳትፎ ይጠይቃል። ጠንካራ ፓርቲ ሲመጣ መቀላቀሉ ሳይሆን፣ አሁን ያሉትን፣  እንድ አንድነት ፓርቲ አይነቶችን ጠንካራ እንዲሆኑ ማድረጉ ይበጃል።
ዉጭ አገር ያለነው ፣ ምን እንኳን የመገደል፣ የመታሰር፣ የመዋከብ አደጋ ባያገኝንም፣ ቢያንስ ስራችን እና አፋችን መገናኘት ያለባቸው ይመስለኛል። «አገር ቤት ካሉት ድርጅቶች ለዉጥ ለምን አያመጡም» ብለን መናገርና መጠየቅ ሳይሆን፣ ለዉጥ እንዲያመጡ የነርሱ አካል ሆን ድጋፋችንን መስጠት ይጠበቅበናል። ሕዝቡ ካልተነሳና ካልተነቃነቀ በምን ሁኔታ ለዉጥ ሊመጣ አይችልም። ህዝቡ እንዲነሳ ሕዝቡ መሃከል ሆኖ ትልቅ ድርጅታዊ ሥራ መስራት ያሰልጋል። ይህን አይነት ድርጅታዊ ሥራ ለመስራት፣ ሕይወታቸው ለዚህ ሥራ አላልፈው ከሰጡ አገር ቤት ካሉ ጀግኖች ጎን መቆም ይኖርብናል።
እንግዲህ ለሚሊዮኖች ድምጽ ለነጻነት እንቅስቃሴ ክፍል ሁለት ከወዲሁ ሁላችንም እንዘጋጅ። ፓርቲዉን በገንዘባችን እንደግፍ። በገንዘብ ለመርዳትና ከሚሊዮኖች አንዱ ለመሆን የሚፈልጉ ከሆነ የሚከተለዉን ድህረ ገጽ ይጎብኙ !
http://www.andinet.org/

No comments:

Post a Comment