Monday, 23 December 2013

ገዢው ፓርቲ የአንድ ለአምስት አደረጃጀትን ወደ ቤተሰብ አወረደ

 ገዢው ፓርቲ በመንግስት መስሪያ ቤቶች ፣ በትምህርት ቤቶች ፣ በአርሶ አደሩና በከተማው ነዋሪዎች ላይ  ሲዘረጋ የቆየውን የአንድ ለአምስት አደረጃጀት በቤተሰብ ደረጃ ለማዋቀር የተለያዩ ደብደባዎችን እየበተነ ነው።
የቦሌ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ ለወረዳ 02 የቤተሰብ አባላት ባዘጋጀው የቤተሰብ ማቋቋሚያ ቅጽ ላይ የቤተሰብ ፖሊስ መመስረት ያስፈለገበት ዋና ምክንያት ” በቤተሰብዎ መካከል ለሚፈጠሩ የጸጥታ ችግሮች ማለትም ያለመግባባቶች፣ የተለያዩ ማህበራዊ ግችቶች ወዘተ የመሳሰሉት ችግሮች ሲፈጠሩ እርስዎ ወይም የቤተሰብዎ  ወኪል እንደ ፖሊስ ሆኖ በቅርበት ከፖሊስ ጋር እየተወያየ የማስታረቅ፣ የማስማማት ስራ እንዲሰራ እና ችግሩን እየተከታተለ እዛው መፍትሄ እንዲሰጥና መፍታት ያልተቻለ በአካባቢው ከተመደቡት የፖሊስ አባላት ጋር ለመፍታት ታስቦ የተዘጋጀ ነው” ይላል።
በቤተሰብ ፖሊስ ማቋቋሚያ ቅጹ ላይ ” የመራች የቤተሰብ ፖሊስ ወይም ተወካይ ስም፣ የቤተሰብ ብዛት፣ ስልክ ቁጥር፣ የተወካይ ፊርማ፣ መንደር ወይም ልዩ ቦታ፣ የብሎክ ቁጥር፣ ብሄርና መግለቻ የሚሉ  ጥያቄዎች ተካተዋል።
በተመሳሳይ ዜናም የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ በከተማው ውስጥ በሚገኙ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የመማር ማስተማሩን ሒደት በጥራት ለማከናወን ይረዳል በማለት ‹‹ኮማንድ ፖስት›› የተሰኘና ሌሎች ተጨማሪ አደረጃጀቶች በማስተዋወቅ ላይ መሆኑን ሪፖርተር ዘግቧል።
የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ በዳግማዊ ምኒሊክ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በከተማው ከሚገኙ ሁሉም ትምህርት ቤቶች ለተጠሩ ርዕሳነ መምህራን፣ ሱፐርቫይዘሮችና ከሁሉም ክፍላት ከተሞችና ወረዳ ጽሕፈት ቤቶች ለተወከሉ ኃላፊዎች በአዲሶቹ አደረጃጀቶች ዙሪያ ገለጻ አድርጓል።
በቅርቡ ወደ ሁሉም ትምህርት ቤቶች ይወርዳል ከተባለው የኮማንድ ፖስት አደረጃጀት በተጨማሪ፣ ‹‹ትራንስፎርሜሽን ፎረም›› እና ‹‹የልማት ቡድን›› የሚሰኙ አደረጃጀቶችም እንደሚተዋወቁ ጋዜጣው ዘግቧል።
‹‹ኮማንድ ፖስት›› አደረጃጀት ዋና ተግባሩ ትምህርት ቤቶችን ከሕዝባዊና ከመንግሥት ክንፎች ጋር ማስተባበር እንደሆነ የዘገበው ጋዜጣው ፣ የ‹‹ትራንስፎርሜሸን ፎረም›› እና ‹‹የልማት ቡድን›› የተባሉት አደረጃጀቶችም በየትምህርት ቤቱ በሚገኙ የትምህርት ክፍሎች ውስጥ ተግባራዊ የሚደረጉ ሲሆን፣ ‹‹አንድ ለአምስት›› በሚል ስያሜ የተጀመረውን አደረጃጀት ለማጠናከርና ለማስቀጠል ጠቃሚ መሆናቸው ተመልክቷል።
ላለፉት ጥቂት ዓመታት በ‹‹ግንባር ቀደም›› አደረጃጀት በኋላም በ‹‹ተጓዳኝ›› አማካይነት የተከናወነው ሥራ የታሰበውን ውጤት ማምጣት አለመቻሉ ግልጽ መሆኑ በመታወቁ ‹‹ኮማንድ ፖስት›› የተባለውን አደረጃጃት ለማስተዋወቅ አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱ ተገልጿል።
መንግስት የትምህርት ጥራት ለማሻሻል ‹‹ተጓዳኝ›› የሚባለውን አደረጃጀት ማምጣቱን ቢገልጽም፣ አንዳንድ መምህራን ግን መንግሥት መምህራኑን ‹‹ለመጠርነፍ›› ሲል ያመጣቸውና ‹‹ከጥቅሙ ጉዳቱ የሚያመዝን አላስፈላጊ መሣሪያ›› ነው ሲሉ ውድቅ ያደርጉታል።
ጋዜጣው አያይዞም ፣ ‹‹አደረጃጀት በዛ፣ እኛም ለማስፈጸም እየተቸገርን ነው፤›› በማለት ርዕሰ መምህራን ለትምህርት ቢሮ ኃላፊው መግለጻቸውን ዘግቧል፡፡ ባለስልጣኑ ግን መምህራን የማሳመን ስራ መስራት ይኖርባቸዋል በማለት የርእሰ መምህራኑን ቅሬታ ሳይቀበሉት ቀርተዋል።
ጋዜጣው ያነጋገራቸው መምህር ስለአደረጃጀት መብዛት ተጠይቀው  ‹‹አደረጃጀት በማለት መንግሥት በየትምህርት ቤቶቻችን የሚያመጣብን አሠራሮች ብዙ ጊዜ መምህራንን ከማባሳጨት አልፎ የትምህርት ጥራትን የባሰ እየገደለ ነው፤›› በማለት መልሰዋል።
መንግስት የአገሪቱን ህዝብ በመላ በአንድ ለ አምስት አደረጃጀት ለመቆጣጠር ያስባል በሚል ወቀሳ እቀረበበት ቢሆንም፣ ኢህአዴግ በ9ኛው መደበኛ ጉባኤ በአደረጃጀቱ እንደሚገፋበት ውሳኔ አሳልፎአል።

No comments:

Post a Comment