8ኛውን የብሄር ብሄረሰቦች ቀን ለማክበር በሚል የጅጅጋ ከተማ በፌደራል ፖሊስ አባላት መወረሯን ነዋሪዎች ገልጸዋል። የፌደራል ፖሊስ አባላት ከተማውን ከተቆጣጠሩት በሁዋላ ልዩ ፖሊስ እየተባሉ የሚጠሩት ሀይሎችን ወደ ዳር የገፉዋቸው ሲሆን፣ ፖሊሶቹ በየተወሰኑ ሜትሮች ቁጥጥር እያደረጉ ነው። የጸጥታ ጥበቃው በሄሊኮፕተር ላይ በሚደረግ ቅኝት የታጀበ ሲሆን፣ በየ አቅጣጫውም በዙ 23 እና በሌሎች ከባድ መሳሪያዎች ጥበቃ እየተደረገ ነው። ጄኔራል ሳሞራ የኑስ ከሶስት ቀናት በፊት የአካባቢው የጸጥታ አጠባበቅ ምን እንደሚመስል ጎብኝተው መመሪያ ሰጥተው መሄዳቸው ታውቋል።
የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት በቅርቡ በእጅ ስልካቸው ላይ ከአልሸባብ መልክት እንደደረሳቸው መዘገባችን የሚታወስ ሲሆን፣ በትናንትናው እለት ደግሞ እንግዶች ከሚያርፉበት የክልሉ መስተዳድር ግቢ ውስጥ 4 የተቀበሩ ፈንጆች በአነፍናፊ ውሾች መገኘታቸውን ጅጅጋ የሚገኙ የውስጥ ምንጮች ለኢሳት ገልጸዋል። ፈንጂዎቹ እንደተገኙም እንግዶቹ ” ተረፍን” ሲባባሉ ተሰምቷል። ሁኔታው በበአሉ ላይ ለመገኘት በሄዱ የክልል ባለስልጣኖች ላይ ከፍተኛ ድንጋጤ መፍጠሩንም የቅርብ ምንጮች ገልጸዋል።
ለበአሉ ከክልሎች የመጡ ዋና ዋና እንግዶች የመስተዳድሩ መስሪያ ቤቶች ተዘግተው፣ በመስተዳድሩ ግቢ ውስጥ አልጋ ተዘርግቶላቸው እንዳረፉ መዘገባችን ይታወሳል።
ይህ ከ250 ሚሊዮን ብር በላይ የወጣበት ዝግጅት በወጪ ደረጃ አምና በባህርዳር የተካሄደውን ዝግጅት በ50 ሚሊዮን ብር እንደሚበልጥ ለማወቅ ተችሎአል። ከፍተኛ ሙስና ተፈጽሞበታል በተባለው በዚህ ዝግጅት ላይ አርቲስቶች በተለይም የህወሀት ሰዎች ከፍተኛ ተጠቃሚዎች መሆናቸውን የደረሰን መረጃ ያሳያል። አርቲስት ኪሮስ ወልደስላሴ የማስታወቂያውን ስራ ለመስራት 8 ሚሊዮን ብር ውል የተፈራረመ ሲሆን፣ የባዛር ዝግጅቱን እና በባዛሩ ላይ ለሽያጭ የቀረቡት᎐ አብዛኞቹ የህወሀት ኩባንያዎች ምርቶች መሆናቸው ታውቋል።
ውድ ተመልካቾቻችን በክልሉ ውስጥ የህወሀት ጄኔራሎች ስለገነቡት የሀብት ኢምፓየርና ለበአሉ እንዲደርስ ተሰርቶ በዛሬው እለት እንደፈረሰ በተነገረለት የመለስ ሀውልት ዙሪያ ላይ በነገው እለት ተጨማሪ ዘገባ ይዘን እንቀርባለን።
No comments:
Post a Comment