Sunday 12 January 2014

ኢትዮጵያ ለምን ኋላ ቀረች? ……….……. ግርማ ሞገስ

ኢትዮጵያ ከውጭ ወረራ ረጅም የነፃነት ዘመን እንዳላት የአገር ተወላጅ እና የውጭ አገር የታሪክ ተመራማሪዎች
ያረጋግጣሉ። ይሁን እንጂ በስልጣኔ ግን ብዙም እንዳልገፋች ይኸው ዛሬ የእኛም ትውልድ ሳይቀር የሚያየው ሃቅ
ነው። ይኽ እንዴት ሊሆን ቻለ? ረጅሙን የነፃነት ዘመን በስልጣኔ ወደፊት ለመራመድ ለምን አልተጠቀመችበትም
ኢትዮጵያ? ምን ስትሰራ ነበር? የሚሉት የቁጭት ጥያቄዎች የሁላችንም አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ጥያቄዎች
ናቸው። በ19ኛው ክፍለ ዘመን በራሳቸው አነሳሽነት አውሮፓውያን ጎብኚዎችን እና ሚሲዮናውያንን እየተከተሉ
ከአገራቸው ወጥተው የፖለቲካ ሳይንስ፣ የህክምና፣ የምህንድስና፣ የኢኮኖሚ፣ የመንገድ ስራ የመሳሰሉ ዘመናዊ
(Secular) ትምህርት ቀስመው አገራቸውን ለመርዳት ወደ አገራቸው የተመለሱት የመጀመሪያዎቹ የኢትዮጵያ
ምሁራን የእነ ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ (1886-1919) ሁሉ የቁጭት ጥያቄ ነበር። በጣት የሚቆጠረው
የነገብረ ሕይወት ትውልድ የውጭ ትምህርት ቀስሞ ወደ ኢትዮጵያ የተመለሰው ባፄ ምኒልክ ዘመን ነበር። ይሁን
እንጂ ለዘመናዊነት በር የተከፈተው ባፄ ኃይለ ስላሴ ዘመን እንደነበር፣ በኃይለ ስላሴ ዘመነ መንግስት በ1942
ዓመተ ምህረት (እ.ኤ.አ. 1950) የአዲስ አበባ የተፈጥሮና የሶሻል ሳይንስ ኮሌጅ መከፈቱን፣ ኮሌጁ የተደራጀው
በኢትዮጵያ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን በመክፈት በንቃት ይሰሩ በነበሩ ካናዳውያን እየሱሳውያን
(Jesuits) ሲሆን የተማሪዎቹ ቁጥር ከ100 በታች እንደነበር ክፍሉ ታደሰ (The Generation, p. 15-16)
ያመለክታል። እሱም ቢሆን እጅግ ዘግይቶ የመጣ በውቅያኖስ ላይ ያረፈ ትንሽ ጠብታ ያህል ነበር።

ይኽን የቁጭት ጥያቄ ተክለ ፃዲቅ መኩሪያም በተለይ የቅኝ አገዛዝን አፍላ እሳት ስለተሸከሙት ዐፄ ዮሐንስ 4ኛ
(1872-1889) በጻፈበት “ዐፄ ዮሐንስ እና የኢትዮጵያ አንድነት” በሚለው መጽሐፉ ደጋግሞ ያነሳዋል። ባፄ ዮሐንስ
ዘመን ኢትዮጵያ እንግሊዘኛ ቋንቋ አጥርቶ የሚናገር እና በአውሮፓ እየተዘዋወረ የኢትዮጵያን ጥቅም የሚያስከብር
የተማረ ሰው አልነበራትም። የዘመኑን የአለም ፖለቲካ አውቆ የአውሮፓውያን ቅኝ ገዢዎችን ድብቅ የፖለቲካ
ፍላጎት ለነገስታቱ የሚመክር አንድም ሰው ኢትዮጵያ እንዳልነበራትም። በዚህ ምክንያት ለምሳሌ ያህል ካፄ ሠርፀ
ድንግል (1556-1590) ወዲህ ጀምሮ በቱርኮች/ግብጾች እጅ የነበረችውን የምጽዋን ባህር በር ታሪካዊ ባለቤት ወደ
ሆነችው ኢትዮጵያ ለማስመለስ የታሪካዊ እና የህጋዊ ባለቤትነት ጥያቄ ያነሱትን ዐፄ ዮሐንስ እንግሊዝ የቅርብ
ወዳጃቸው እና የቤት ውስጥ መካሪያቸው መስላ ከቀረበቻቸው በኋላ ከጀርባቸው ግን ከኢጣሊያ ጋር ተመሳጥራ
ምጽዋን ከቱርኮች/ግብጾች ወደ ኢትዮጵያ ሳይሆን ወደ ኢጣሊያ እንድትሸጋገር ማድረግ የቻለችው የዘመኑን አለም
አቀፍ ፖለቲካ ከጋዜጣዎች እየተከታተለ ከአለም አቀፍ ህግ ጋር እያጣቀሰ ኢትዮጵያን የሚመክር አንድም ምሁር
ስላልነበራት እንደነበር በማስታወስ ተክለ ፃዲቅ መኩሪያ በቁጭት ደጋግሞ ይተርካል “ዐፄ ዮሐንስ እና የኢትዮጵያ
አንድነት” በሚለው መጽሐፍ።

በዚያን ዘመን ስለነበረው ጥቅጥቅ ኋላቀርነት እናውራ እንጂ ዛሬም ለማዕድን ምርምሩም ሆነ ለሐዲድ ቅየሳው
የውጭ ሰው እንደምንፈልግ መዘንጋት የለበንም። ዘመናዊ (Secular) ትምህርት ዘመናዊ ባህል ያስከትላል።
የህዝብን አስተሳሰብ፣ ግንኙነት እና ባህል ይቀይራል። ስለዚህ ቀደም ብሎ ዘመናዊ ባህል በኢትዮጵያ ማደግ
ባለመጀመሩ ዛሬም ከፍተኛ ትምህርት አላቸው በሚባሉት ገዢዎቻችን እና በእኛም ተማርን በምንለው
ተቃዋሚዎች ዘንድ ኋላቀርነት በህይወት እየኖረ ስለመሆኑ ጥርጥር ሊገባን አይገባም። ያ ባይሆን ኖሮ በእርስ በርስ
ጦርነት የሚካሄደውን ኋላቀር የመንግስት ሽግግር ባህላችንን ዛሬ በ21ኛው ክፍለ ዘመን አንስተን ሰላማዊ ትግል
ይሻላል የሚል ውይይታ ባልከፈትን ነበር። ያ ባይሆን ኖሮ አምባገነን ገዢዎቻችን ለምርጫ እና ዴሞክራሲ ባህል
ማደግ እንቅፋት ባልሆኑ ነበር። ዛሬም ኢትዮጵያ በመሐይምነት፣ በድህነት እና በኋላቀርነት እየተሰቃየች ነው።

የሆነው ሆኖ “ኢትዮጵያ ረጅም የነፃነት ዘመን ሲኖራት በስልጣኔ ያልተራመደቸው ለምንድን ነው? ለሚለው ጥያቄ
ይህ ጥናት አውራ (አብይ) ምክንያቶች ናቸው የሚላቸውን ያቀርባል፥ (1ኛ) ዘመናዊ ትምህርት (Secular
Education) ቀደም ብሎ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ በመደረጉ እና (2ኛ) በእርስ በርስ ጦርነት የሚፈጸመው
የመንግስት ሽግግር ባህላችን ናቸው። እነዚህን ሁለት አውራ ምክንያቶች ለጥቀን በአጭር ባጭሩ እንመለከታለን።

(1ኛ) ዘመናዊ ትምህርት (Secular Education) ለረጅም ዘመን ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ በመደረጉ
ስመ ጥሩዋ አክሱም የኢትዮጵያ መንግስት መቀመጫ ከተማ በነበረችበት ዘመን በንግድ ላይ የበቀለ ስልጣኔ
ነበራት። የራስዋ ፊደል ነበራት። የራሱዋን ገንዘብ ከወርቅ እና ከብር አቅልጣ በመስራት በዚያን ዘመን በአለም ገበያ
ክብር አግኝታለች። በቀይ ባህር እና ህንድ ውቅያኖስ ላይ የምትነግድ ኃያል አገር ነበረች። በዚያን ዘመን በአለም
ውስጥ ከነበሩት አራት ኃያላን አገሮች አንዷ ኢትዮጵያ ነበረች። የነ ኢዛና እና የነ ካሌብ ዘመን የአክሱም ስልጣኔ
ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰበት ዘመን እንደነበር ተጽፎ እናያለን። የነብዩ መሐመድን ስብከት ተከትሎ አዲስ ስልጣኔ ከተነሳበት ጊዜ ወዲህ ጀምሮ ስልጣኔዋ ማቆልቆል ይጀምራል። ተከትሎም በመንግስት ሽግግር እርስ በርስ ጦርነት
ውስጥ ለረጅም አመቶች ትዘፈቃለች። እስከ ንግስት ዮዲት ዘመነ መንግስት ፍጻሜ ድረስ ኢትዮጵያ ለረጅም ጊዜ
ጦርነት ውስጥ እንደነበረች ከእስክንድሪያ ግብጽ ይመጡ የነበሩት አቡኖች ታሪክ ይጠቁማል። ጦርነቱ ያበቃው
መራ ተክለ ሃይማኖት በጦርነቱ ቀንቶት የኢትዮጵያን የመንግስት መቀመጫ ከአክሱም ነቅሎ ደጋፊዎቹ ወደ
ተበራከቱበት ላስታ ከተማ ሲተክል ነበር። ይኽ የዛጉዌ ስረወ መንግስት ጅማሬ ነበር።
የሆነው ሆኖ አክሱም ገናና ሳለች ክርስቶስ ከተወለደ 200 አመቶች ግድም ወዲህ በአክሱም የነበሩት የኢትዮጵያ
መሪዎች ስለ አዲሱ ክርስትና ሃይማኖት ከክርስቲያን ነጋዴዎች፣ ከውሮፓውያን ጎብኚዎች እና ከመንገደኞች ወሬው
ነበራቸው። ሃይማኖቱ ኢትዮጵያ ሊደርስ የቻለው ፍሬምናጦስ እና አዲየስ በተባሉ ሁለት የአረብ ተወላጆች
(ምናልባት ሶሪያ) ነበር ተብሎ ይታመናል። በ320 ዓ.ም. ግድም ኢዛና ያባቱን ዙፋን ሲወርስ ፍሬምናጦስ ወደ
እስክንድሪያ ግብጽ ተጉዞ በእስክንድሪያ ግብጽ የተቀመጡትን የአካባቢው የበላይ መንፈሳዊ አባት`(ፓትሪያክ)
በኢትዮጵያ አዲሱን ሃይማኖት (ክርስትናን) በበላይነት የሚመራ መንፈሳዊ አባት (አቡን) ወደ ኢትዮጵያ እንዲልኩ
እንደጠየቀ እና ፓትሪያኩ ፍሬምናጦስን የኢትዮጵያ የመጀመሪያው አቡን አድርገው እንደሾሙት ሃሮልድ
ማርኩይስ ይተርካል። አቡን ፍሬምናጦስ ወደ ኢትዮጵያ እንደተመለሰ ኢዛናን የኢትዮጵያ የመጀመሪያው
ክርስቲያን ንጉስ አደረገ። የዐፄ ኢዛና ክርስቲያን መሆን በአገሪቱ ታሪክ አዲስ ምዕራፍ ከፈተ። የክርስትና ሃይማኖት
በኢትዮጵያ ፈጥኖ በመሰራጨት ለአብዛኛው ደጋማ ሰሜናዊ የኢትዮጵያ ህዝብ የማንነት መገለጫ ሆነ። በ4ኛው
መቶ አመት ውስጥ መነኩሴዎች የወንጌልን ቃል ሊያስተምሩ በኢትዮጵያ ተሰማሩ። በዚያው ዘመን በአክሱም
ጽዮን ማሪያም የኢትዮጵያ የሃይማኖት ማዕከል ሆነች። ከአዲግራት በስተ መዕራብ ተራራማ አምባ ላይ የሚገኘው
ደብረ ዳሞ ገዳም በ5ኛው መቶ አመት ውስጥ ተመሰረተ።
አቡን ፍሬምናጦስ ሲሞት እስክንድሪያ ግብጽ አዲስ አቡን ላከች። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስከ ኃይለ ስላሴ ዘመነ
መንግስት ፍጻሜ ድረስ ለ1600 አመቶች ያህል ጊዜ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ሃይማኖት የሚመራው ከእስክንድሪያ
ግብጽ በሚላኩ አረብ አቡኖች ነበር። በኢትዮጵያ በዘመናዊ መልክ የተደራጀው ዳግማዊ ምንሊክ አንደኛ ደረጃ
ትምህርት ቤት የተከፈተው በ1900 ዓ.ም. እንደሆነ እና እሱም እንዲመራ የተደረገው ከእስክንድሪያ ግብጽ
በሚመጡት በእነዚሁ አረብ አቡኖች እንደነበር ባህሩ ዘውዴ ይተርካል። ና በሚከተሉዋቸው ቄሶች ስለነበር
በኢትዮጵያ የመፈጠሩት ምሁራን በሙሉ መንፈሳውያን ነበሩ። የኢትዮጵያ ነገስታትም በልጅነታቸው የሚማሩት
ይኼንኑ መንፈሳዊ ትምህርት ብቻ ነበር። በኢትዮጵያ የሚሰጠውም ትምህርት በእስክንድሪያ ግብጽ በአረበኛ
ተጽፎ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጣ ብሉይ ኪዳንን፣ አዲስ ኪዳንን፣ መጽሐፈ ሊቃውንትን ምነናን፣ ምንኩስናንና
ብህትናን የሚያወድስ እንዲሁም የጻድቃን፣ የሰማዕታትና የመልአክት ገድል (ስራዎች) እና ድርሳን (ታሪክ) ያካትት
እንደነበር “የግራኝ ወረራ” በሚለው መጽሐፉ ተክለ ፃዲቅ መኩሪያ ዘርዘር አድርጎ ያመለክታል። ከዚያ ይህ
ትምህርት ከአረብኛ ቋንቋ ወደ ግዕዝ እየተተረጎመ በየገዳሙ እና ደብሩ እየተሰራጨ ወጣቱ (ወደፊት ንጉስ
የሚሆኑትን ጨምሮ) እንዲማሩት ይደረጋል። ስለዚህ በዚያን ዘመን ኢትዮጵያ የምታመርታቸው ምሁራን የውጭ
አገር ቋንቋ ችሎታም አረበኛ ብቻ ነበር።
የክርስትና እምነት በአክሱም ኢትዮጵያ ካለምንም እክል ቢሰራጭም በውጭው የክርስቲያን አለም ውስጥ ግን
የእየሱስ ክርስቶስን ባህሪ በሚመለከት የእምነት ልዩነት ተፈጥሮ ውስጥ ውስጡን ያነጋግር ነበር። አብዛኛው
የምዕራብ አውሮፓ (ስፔይን፣ ፖርቱጋል፣ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ወ.ዘ.ተ.) ክርስትና እምነት መንፈሳዊ
አባቶች እየሱስ ክርስቶስ በአንድ በኩል ከአምላክ በሌላ በኩል ደግሞ ሰው ከሆነችው ከማሪያም በመወለዱ
“ሁለት-ባህሪ” አለው የሚል እምነት ሲይዙ በተለይ የኦርቶዶክስ እምነት ፈጣሪዋ የእስክንድሪያ ግብጽ እና
እየሩሳሌም መንፈሳዊ አባቶች ግን ሁለቱ ባህሪዎች ተዋህደው “አንድ-ባህሪ” ሆነዋል የሚል አቋም ነበራቸው።
በተፈጠረው የእምነት ልዩነት ላይ ለመወያየት ከተደረጉት ጉባኤዎች ውስጥ በ451 ዓ.ም. በጥንታዊቷ ኬልቄዶን
(Chalcedon) ከተማ (ዛሬ የኢስታንቡል/ቱርክ አካል ነች) በተደረገው ጉባኤ የክርስቲያኑ አለም በጸብ ከሁለት
ተከፍሎ እንደተለያየ ተክለ ፃዲቅ መኩርያ “የግራኝ ወረራ” በሚለው መጽሐፉ በሰፊው ይተርካል። ከዚህ ጉባኤ
ወዲህ ሁለቱ ወገኖች በጸበኛነት ስሜት መተያየት ይጀምራሉ። በመካከላቸው አለመተማመን እና መናናቅ ተተከለ።
ጠቃሚ የቴክኒክ፣ የህክምና፣ የምህንድስና እውቀት ከሁለት-መንፈሶች (ምዕራብ አውሮፓ አገሮች) ሲመጣም
አንድ-መንፈሶች የከሃዲዎች ንብረት አድርገው በመቁጠር ያናንቁ ጀመር፡፡ ኢትዮጵያ ተወካይ የመላክ መብት
ስላልነበራት የእስክንድሪያ ግብጽ አቡኖችን የነገሯትን ነበር የተከተለችው።
ያም ሆነ ይኽ ጥያቄው መነሳቱ እና ውይይት መደረጉ የስልጣኔ ምልክት ነው። አንድ-መንፈስ ወይንም ሁለት-
መንፈስ የሚለውን እምነት መከተልም ችግር አይደለም። ችግሩ የእስክንድሪያ ግብጽ አቡኖች በድፍን ጥላቻ
መዋጣቸው ነበር። ኢትዮጵያን በጥላቻ መርዝ መበከላቸው እና ከምዕራብ አውሮፓ የሚመጣን ማንኛውን ዘመናዊ ስልጣኔ የእየሱስ ክርስቶስ ከሃዲዎች ንብረት አድርጋ በመቁጠር የስልጣኔው ተጠቃሚ እንዳትሆን ማድረጋቸው
ትልቅ ስህተት ነበር። የኢትዮጵያም ጭፍን ተከታይነት ስህተት ነበር። የቀድሞ አባቶቻችን በመንፈሳዊ እና
በምድራዊ (Secular) ስልጣኔ መካከል ያለውን ልዩነት ለይተው አለማየታቸው ስህተት ነበር። ጥላቻ ያሳውራል
የሚለው አባባል ሃቅ እንደሆነ እናያለን። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያ ለዘመናዊ ትምህርት (Secular Education)
ማለትም ለስልጣኔ እና ለዘመናዊነት በሯን ዘጋች።
እንደሚታወቀው ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ8ኛው መዕተ ዓለም ጀምሮ እስከ ከክርስቶስ ልደት ወዲህ 6ኛው
ምዕተ ዓመት ድረስ ለ1300 አመቶች ያህል በሜድትራኒያን ባህር አካባቢ የጥንታዊ ግሪክና ሮማ (Greco-Roman
World) ስልጣኔ አብቦ ነበር። የጥንታዊ ግሪክና ሮማ ፈላስፋዎችና ምሁራን በሳይንስ፣ በሂሳብ፣ በምህንድስና፣
በህክምና፣ በአስተዳደር፣ በፖለቲካ ሳይንስ፣ በስዕልና በቅርጽ ስነ-ጥበብ፣ በባሩድ የሚተኮስ መሳሪያ በመስራት፣
በህንጻና በመንገድ ስራ መስኮች ብዙ ጽፈው ትተውት ሄደዋል። በዚኽ ዘመነ ከነበሩት ሰዎች ውስጥ አርስቶትል
(348-322 ዓ.ዓ.)፣ ሶቅራጥስ (469-399 ዓ.ዓ.)፣ ፕሌቶ (427-347 ዓ.ዓ.)፣ ፓይታጎርስ (570-495 ዓ.ዓ.) ጥቂቶቹ
እንደሆኑ በስልጠና ክፍል አንድ ጠቅሰናል። (ፓይታጎርስ - Pythagoras Theorem ታስታውሳላችሁ? )
ከ11ኛው መቶ ዓ.ም. ጀምሮ ደግሞ በኬልቄዶን ጉባኤ ሁለት-መንፈስ የሚል አቅዋም በወሰዱት አገሮች (ስፔይን፣
ፖርቱጋል፣ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ወ.ዘ.ተ.) ዋና ከተማዎች ጥንታዊ የግሪክና የሮማ ፈላስፋዎችና ምሁራን
በእጅ ጽፈው በየቦታው ትተውት የሄዱት የሳይንስ፣ የሂሳብ፣ የምህንድስና፣ የንግድ፣ የስነጥበብ፣ የመንገድ ስራ፣
የህክምና፣ የአስተዳደር፣ የፖለቲካ ሳይንስ እና የመሳሰለው እውቀት ዳግማዊ ትንሳኤውን (Renaissance) አገኘ።
ይህ እውቀት ከተቀበረበት እየተፈለገ በተለያዩ ቋንቋዎች እየተተረጎመ ተባዝቶ በአውሮፓ ተሰራጨ። አውሮፓ
እነዚህን እውቀቶች ከ11ኛው እስከ 16ኛው መቶ አመት ሳታቋረጥ በህዝቧ ውስጥ በማሰራጨቷ ትልቅ የባህል
ለውጥ አደረገች። ስለዚህ ምዕራብ አውሮፓ በእንዱስትሪ፣ በቴክኒክ፣ በንግድና በእርሻ፣ በምህንድስና፣ በህክምና፣
በቤትና በመርከብ ግንባታ፣ በአስተዳደር፣ በድንጋይ ቀረፃ፣ በብረታ ብረት፣ በባሩድ ስራና በባሩድ የሚተኮሱ
መድፍና ነፍጥ ስራዎች ወደፊት ተራመደች። መርከቦችና ዘመናዊ መሳሪያ በብዛት ማምረት ጀመረች። በኢንግሊዝ
አገር የተካሄደው የኢንዱስትሪ አብዮትም ይህን የባል ለውጥ ተከትሎ የመጣ ነበር።
ከ11ኛው እስከ 13ኛው ምዕተ ዓመት በምዕራብ አውሮፓ ዳግማዊ ትንሳኤውን (Renaissance) ያገኘው ዘመናዊ
እውቀት በየአገሩ ከተሰራጨ በኋላ የህዝቡን አስተሳሰብና ባህል መለወጥ የተቻለው ትምህርት ቤቶች በተለይም
ኮሌጆችና ዩንቨርስቲዎች ተከፍተው የህብረተሰቡን ወጣት በማስተማር ነበር። በምዕራብ አውሮፓ፣ በአረብ
ሙስሊም አገሮች እና በኢትዮጵያ ዩንቨርስቲዎች የተከፈቱበት ጊዚያት በንፅፅር እንመልከት፥
(1) በምዕራብ አውሮፓ፥ የቦሎኛ ዩንቨርስቲ (University of Bologna) የመጀመሪያው ዩንቨርስቲ ሆኖ በ1080
ዓመተ ምህረት ተከፈተ። የቦሎኛ ዩንቨርስቲ በህግና በመድፍ ስራ ትምህርቶች የታዋቂነት ታሪክ አለው።
ኦክስፎርድ ዩንቨርስቲ በ1088 ስራ ጀመረ። የፓሪስ ዩንቨርስቲ ደግሞ በ1100 ዓመተ ምህረት ተከፈተ። ርስተ
ጉልተኛው (ፊውዳሊዝም) ስርአትና ሃይማኖት ተባብረው ዘመናዊ አስተሳሰብን ክፉኛ በመታገላቸው ለጊዜው
በ1221 ዓመተ ምህረት ተቋርጦ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ እንደገና ጀመረ። ኦክስፎርድ ዩንቨርስቲ ትምህርት መስጠት
የጀመረው በ817 ዓመተ ምህረት ነው የሚሉም አሉ። እስከ አሁን የተገኙ ሰነዶች እንደሚያመለክቱት ከሆነ ግን
የጀመረው በ1088 ዓመተ ምህረት ነው። ካምብሪጅ ዩንቨርስቲ ደግሞ በ1201 ዓመተ ምህረት ግድም ተከፈተ
(ይኽ ዘመን ኢትዮጵያ በመራ ተክለ ሃይማኖት መሪነት ወደ ዛጉዌ ዘመነ መንግስት የገባችበት ጊዜ ነበር)።
በዘመነ ፊውዳሊዝም ቤተ ክህነት የነበራትን የፖለቲካ የበላይነት እየተጠቀመች ሳይንስ (Secular) ትምህርት
እንዳይስፋፋ ታደርግ ነበር። እግዚአብሔርን ተፈታተኑ እየተባሉ ከየዩንቨርስቲው የሚከሰሱ አልፎም የሚታሰሩ
መምራን ነበሩ። የፈረንሳይ እና ኦክስፎርድ ዩንቨርስቲዎች እንዲዘጉ ለማድረግ ቤተ ክህነት ብዙ ጥራለች።
ስለዚህ ከ11ኛው ክፍለ ዘመን ግድም ጀምሮ በአውሮፓ የቤተ ክህነት መንፈሳዊ ትምህርት እና ዘመናዊ
(Secular) ትምህርት እርስ በርስ እየታገሉ ጎን ለጎን አብረው ሲጓዙ ቆይተዋል። ወደፊት ከቦታው ስንደርስ
እንደምናየው በኢትዮጵያ ግን ዘመናዊ (Secular) የኮሌጅ ትምህርት የተጀመረው በ1942 ዓ.ም. ግድም ነበር።
(2) በአረብ አገሮች፥ በግብጽ በአረበኛ ቋንቋ ድግሪ የሚሰጥ ዩንቨርስቲ የጀመረው በሳላዲን ዘመነ መንግስት
(1166-1185) እንደነበር ተጽፎ እናያለን። ዩንቨርስቲው የመንፈሳዊ፣ የህግ፣ የአስትሮኖሚ፣ የፍልስፍና፣
የስነጽሑፍ፣ የግራመር፣ የህክምና ትምህርቶች ይሰጥ ነበር። የባግዳድ (ኢራቅ) ዩንቨርስቲ ደግሞ በ1225 ዓመተ
ምህረት ፍልስፍና፣ ሂሳብ፣ የተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርት በአረበኛ ቋንቋ በመስጠት ስራውን መጀመሩ ተጽፏል። (3) በኢትዮጵያ፥ በቅድመ አድዋ ጦርነት ዘመን ዘመናዊ እውቀት የነበራቸው ኢትዮጵያውያን ወጣቶች
የኢትዮጵያ የመጀመሪያዎቹ ምሁራን ሲሆኑ ቁጥራቸው በጣት የሚቆጠር ነበር። እነዚህ ወጣቶች
ትምህርታቸውን ያገኙት ከሚስዮናውያን እንዲሁም ከአንዳንድ አገር ጎብኚዎች ጋር በግላቸው በፈጠሩት
መወዳጀት እንጂ የኢትዮጵያ የቤተ መንግስት እና የቤተ ክህነት ባለስልጣኖች ወደ ውጭ ልከው
ያስተማሩዋቸው አይደሉም። የእነዚህን የመጀመሪያ የኢትዮጵያ ምሁራን ትምህርት እና ወደ አገራቸው
ከተመለሱ በኋላ ያደረጉትን ባህሩ ዘውዴ (ታሪክ ገጽ 103-107) ዘርዘር አድርጎ ይተርካል። (የአድዋ ጦርነት
የተደረገው እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር በ1888 ዓመተ ምህረት ነበር)።
ከአድዋ ድል ወዲህ ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ጋር የነበራት ግንኙነት እያደገ በመሄዱ እጅግ ብዙ የውጭ አገር
ቋንቋ የሚተረጉሙ ሰዎች አስፈለጋት። በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ዘመናዊ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት
ዳግማዊ ምኒልክ ት/ቤት በ1900 ዓመተ ምህረት ተከፈተ። ቢሆንም ግን በዘመናዊና በነባሩ መንፈሳዊ
ትምህርት መካከል ሚዛን መፍጠር ያስልጋል በሚል ከእስክንድሪያ ግብጽ የመጡ የኮፕቲክ ኦርቶዶክስ
(ተዋህዶ) ቤተ ክርስቲያን ቄሶች የትምህርት ቤቱ ዋና አስተዳዳሪዎች እንተደረጉ ባህሩ ዘውዴ (ታሪክ ገጽ 108)
ያመለክታል። በኢትዮጵያ በዘመናዊ ትምህርት እና አብሮት በሚመጣው ዘመናዊ ስልጣኔ ላይ ለዘመናት
ተዘግቶ የነበረው በር ለመጀመሪያ ጊዜ በጥቂቱ የተከፈተው በዚህ አይነት ሁኔታ ነበር።
ዐፄ ኃይለ ስላሴ ለዘመናዊነት የኢትዮጵያን በር ከፈቱት። በኃይለ ስላሴ ዘመነ መንግስት በ1942 ዓመተ ምህረት
(እ.ኤ.አ. 1950) የአዲስ አበባ የተፈጥሮና የሶሻል ሳይንስ ኮሌጅ ተከፈተ። ኮሌጁ የተደራጀው በኢትዮጵያ
አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን በመክፈት በንቃት ይሰሩ በነበሩ ካናዳውያን እየሱሳውያን (Jesuits)
ሲሆን የተማሪዎቹ ቁጥር ከ100 በታች ነበር። የመምህራኑና የአስተዳዳሪዎቹ ቁጥር ደግሞ 9 ያህል ነበር።
የአዲስ አበባ ምህንድስና እና የአለመያው እርሻ ኮለጅ በ1944 ዓመተ ምህረት ተከፈቱ። የአለመያው እራሻ
ኮሌጅ የተከፈተው በአሜሪካው ኦክላሆማ ዩንቨርስቲ እርዳታ ነበር። በ1946 የአዲስ አበባ ህንጻ ኮሌጅ
በስዊድሾች ተከፈተ። ከዚያ የጤና ኮሌጅ በጎንደር ስራውን ጀመረ። በ1953 ዓመተ ምህረት እነዚህ ሁሉ
ኮሌጆች በአንድነት ተጠቃለው ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ዩንቨርስቲን ፈጠሩ።
ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ዩንቨርስቲ ሲኬት የተማሪው ቁጥር ከ1 ሺ በላይ እንደነበር ይገመታል። በ1960ዎቹ
ማለቂያና በ1970ዎቹ የዩንቨርስቲው መምህራንና አስተዳደር በአሜሪካኖች መሞላት እንደጀመረ፣ የቢዝነስ
የአስተዳደር፣ የህግና የህክምና ኮሌጆች እንደተጨመሩ፣ የተማሪውም ቁጥር ወደ አራትና አምስት ሺ ከፍ
እንዳለ ክፍሉ ታደሰ (The Generation, p. 15-16) ጨምሮ ይገልጻል። ከዚያ የህዝቡ ቁጥር እየጨመረ ሲሄድ
የተማሪውም ቁጥር ማደጉ የግድ ሲሆን የኮሌጆችና የዩንቨርስቲዎች ግንባታ ግን ባለማደጉ በ12ኛ ክፍል
መልቀቂያ ፈተና አላለፍክም የሚባለው ተማሪ ቁጥር እየጨመረ ሄደ።
ለኢንዱስትሪ አብዮት መጀመር ከሚጠቀሱት ምክንያቶች ውስጥ ዋንኞቹ ዩንቨርስቲዎችና ኮሌጆች ዘመናዊ
እውቀትን በማሰራጨታቸው በህብረተሰብ ውስጥ የተገኘው የአስተሳሰብና የባህል ለውጥ (1) የሰውን ልጅ
የምርምር ችሎታ፣ የስራ ዝንባሌ፣ እምነትና ባህል በማጎልመሱ እና (2) ነጻነታቸው የተጠበቀ ህግ አውጪ፣ ህግ
አስፈጻሚ እና የዳኝነት ዘርፍ ያሉት ዘመናዊ አስተዳደር (መንግስት) መመስረት በማስቻሉ ነው። ኢትዮጵያ
የኢንዱስትሪ አብዮትን ስልጣኔ ወራሽ እና ተጠቃሚ እንዳትሆን ያደረጋትም ዘመናዊ እውቀትን ቸል በማለቷ
ነበር። ያም ተባለ ይህ ኢትዮጵያ የነበራትን ረጅም የነፃነት ዘመን በስልጣኔ ረገድ እንዳልተጠቀመችበት ስናስተውል
መጸጸታችን አይቀርም። ቢያንስ በእነ ዐፄ ቴዎድሮስ እና በእነ ዐፄ ዮሐንስ ዘመን ቢቻልም ትንሽ ቀደም ሲል ጀምሮ
የነበረው ህዝባችን ጥቂቱ እንኳን በኮሌጀ ደረጃ ዘመናዊ ትምህርት የመማር እድል ቢያገኝ ኖሮ ዛሬ በዚህ ስልጠና
ላይ የመንግስት ሽግግር የፖለቲካ ትግላችን በትጥቅ ትግል ሳይሆን በምርጫ እና በሰላማዊ ትግል ቢፈጸም ይሻላል
የሚል ውይይት ባላደርግን ነበር። እንደ አውሮፓ የምርጫ ፖለቲካ ባህላችን አድጎ በተገኘ ነበር።
በስልጠና ክፍል አንድ ዐፄ ቴዎድሮስ ኢትዮጵያ በዘመናዊ ስልጣኔ ከአውሮፓ እጅግ ብዙ ወደ ኋላ መቅረቷን
አስተውለውት እንደነበር እና በዘመነ መንግስታቸው ፍፃሜ ግድም ዘመናዊ ትምህርት ወደ ኢትዮጵያ ለማስገባት
ያደረጉትን ጥረት አጭር ታሪክ በመተረክ ነበር ስለ ዘመናዊ ስልጣኔ የጀመርነውን ጥናት ያጠናቀቅነው። ታሪኩ
እንደሚከተለው ተጨምቆ ሊቀርብ ይችላል።
በ1858 ዓመተ ምህረት በክፍያ ዘመናዊ ትምህርት የሚያስተምሩ አውሮፓውያን ኢትዮጵያ መጥተው የኢትዮጵያን
ወጣት እንዲያስተምሩ ለመቅጠር ደብዳቤ ላኩ። ከአውሮፓ የቴክንክ ትምህርት መምህራን ቀጥረው የኢትዮጵያን ወጣቶች ለማስተማር ክፍት የስራ ቦታ እንዳላቸው የሚገልጸውን ደብዳቤ አስይዘው ጓደኛቸውን ሚሲዮናዊውን
ማርቲን ፍሌድን (Martin Flad) ወደ አውሮፓ ላኩ። ማርቲን የፕሮቴስታንት ሃይማኖት ሚስዮናዊ ጓደኛቸው
ወደ አውሮፓ ይዞት የሄደው የመምህራን መመልመያ የስራ ማስታወቂያ መልዕክት የሚከተለውን ይል ነበር።
“ አቶ ፍሌድን ወደ አውሮፓ ልኬዋለሁ። የእጅ ጠበብቶች እፈልጋለሁ። የመጠቻሁትን በሙሉ ለመቀበልና
ለማስተናገድ ደስተኛ ነኝ። እዚህ መኖር ከፈለጋችሁም በደስታና በምቾት እንደምትኖሩ ላረጋገጥ እውዳለሁ።
አስተምራችሁ ወደ አገራቸው መመለስ ከፈለጋችሁም ደሞዛቸሁን ከፍዬ ወደ አገራችሁ በደስታ እንደምሸኛቸው
ላረጋግጥ እውዳለሁ” ማለቱን ባህሩ ዘውዴ (ታሪክ ገጽ 37) ያመለክታል።
ኢትዮጵያ የዚህ ዘመናዊ እውቀት ወራሽ እና ተጠቃሚ ከመሆን ፈንታ ቸል በማለቷ በ19ኛው እና በ20ኛው መቶ
አመቶች ውስጥ የፈጠረቻቸው ምሁራን እና ነገስታት እነ ዳግማዊ ዐፄ ቴዎድሮስ (1847-1860)፣ እነ ዐፄ ዮሐንስ
አራተኛው (1864-1881) እና እነ ዳግማዊ ዐፄ ምንሊክ (1882-1906) ሳይቀሩ ትምህርታቸው የገዳም መንፈሳዊ
ትምህርት ነበር። የሩቆቹን የምዕራብ አውሮፓውያንን መሪዎች ስልጣኔ ደረጃ ትተን የጎረቤታችንን የግብፅን
ሙስሊም መሪዎች ሁኔታ ብንመለከት እንኳን ባፄ ዮሐንስ ዘመን አቻቸው የግብጹ ገዢ ከዲቭ ኢስማኢል (1855-
1871) በካይሮ ኮሌጆች የሚሰጠውን ትምህርት ካጠናቀቀ በኋላ የፈረንሳይ አገር ኮሌጅ ተጨማሪ ዘመናዊ
ትምህርት ነበረው። ከዲቭ ኢስማኢል በኢትዮጵያ ላይ ሁለት ጊዜ ወታደራዊ ወረራዎች ፈጽሞ በሃፍረት
የተመለሰው የግብጽ መሪ ነው። በከዲቭ ኢስማኢል መንግስት ውስጥ የነበሩት ሹማምንት ሳይቀሩ ከፍተኛ ዘመናዊ
ትምህርት እንደነበራቸው እና ፈረንሳይኛም ሆነ እንግሊዘኛ ቋንቋዎችን አስተርጓሚ ሳያስፈልጋቸው እንደልባቸው
ይናገሩ እንደነበር ዐፄ ዮሐን እና የኢትዮጵያ አንድነት በሚለው መጽሐፉ ተክለ ፃዲቅ መኩሪያ በዚያን ዘመን ባፄ
ዮሐንስ እና በከዲቭ ኢስማኢልን መንግስቶች መካከል የነበረውን የስልጣኔ ደረጃ ልዩነት ዘርዘር አድርጎ አቅርቧል።
ኢትዮጵያ ነፃነቷን ለረጅም ዘመን ማስከበሯ ሲያኮራ ከዘመናዊ ትምህርት የሚገኘውን ስልጣኔ ፍጹም ቸል ማለቷ
ግን ይጸጽታል። ስለዚህ እስከ 20ኛው መቶ አመቶች ድረስ በኢትዮጵያ የሰጥ የነበረው ትምህርት የ20ኛው መቶ
ክፍለ ዘመን ከሚጠይቀው የስልጣኔ ደረጃ እጅግ ወደኋላ የቀረ ነበር። ዘመናዊ ትምህርት በኢትዮጵያ መሰጠት
የተጀመረው በ21ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ግድም በመሆኑ ቀደም ብሎ ኢትዮጵያ በጣም ጠቃሚ የሆኑት ዘመናዊ
የሳይንስ፣ የህክምና፣ የኢኮኖሚክስ፣ የምህንድስና፣ የህግ፣ ዘመናዊ የጦር መሳሪያ የመስራት፣ የፖለቲካ ሳይንስ እና
የመሳሰሉት ዘመናዊ እውቀት የነበረው ሰው ኢትዮጵያ አልነበራትም።
እርግጥ ነው ዛሬ ይኽ ችግር ከኋላችን ነው። በርካታ ዩንቨርስቲዎች አሉ። ቁጥራቸው እና የሚሰጡት ትምህርት
ጥራት ሳያቁርጥ መሻሻል አለበት። በዘመናዊ እውቀት ላይ በር ዘግታ የቆየች ኢትዮጵያ ስታከማቸው የነበረው
ኋላቀርነት እንዲ ባጭር ጊዜ የሚወገድ አይደለም። ዛሬም ኋላቀርነት አብሮን ቆሞ ሲሄድ የሚታይ ነው ልብ
ለሚል። ወደ ስልጣኔ የሚወስዱ ብዙ ስራዎች ይጠብቁናል። የርስ በርስ ጦርነት ግን አንዱ አይደለም።
ስለዚህ ዘመናዊ (Secular) ትምህርት በምዕራብ አውሮፓ ቀደም ብሎ ከቤተ ክህነት ትምህርት ጋር እየታገለ
የማደግ እድል ሲያጋጥመው በኢትዮጵያ ግን የቤተ ክህነት ትምህርት በዘመናዊ (Secular) ትምህርት ላይ በር
ዘግቶ ኢትዮጵያን በጨለማ ውስጥ አቆይቷል። ዘመናዊ (Secular) ትምህርት በምዕራብ አውሮፓ መሰራጨት እና
የህብረተሰቡን ባህል መቀየር ከጀመረ 900 አመቶች ያህል ጊዜ ዘግይቶ ኢትዮጵያ በመግባቱ ነው ኢትዮጵያ
በስልጣኔ ወደኋላ የቀረችው። ይህ አንደኛው ምክንያት ነው። ሁለተኛውን ምክንያት ለጥቀን እንመልከት።
(2ኛ) የኢትዮጵያ የመንግስት ስልጣን ሽግግር ባህሏ

ለዘጠኝ መቶ አመቶች ላላነሰ ጊዜ ኢትዮጵያ በዘመናዊ (Secular) ትምህርት እና ትምህርቱን ተከትሎ ለሚመጣ
ዘመናዊነት እና ስልጣኔ ጀርባዋን መስጠቷ ለኋላ መቅረቷ አንዱ አውራ ምክንያት እንደነበር ከፍ ብለን አንብበናል።
በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ደግሞ ቢያንስ ቢያንስ ከአክሱም ስልጣኔ መውደቅ ወዲህ ጀምሮ አምባገነኑ
ህውሃት/ኢህአዴግ በ1983 ዓ.ም. ስልጣን እስከጨበጠበት ጊዜ ድረስ በእርስ በርስ ጦርነት ይፈጸም የነበረው
የመንግስት ሽግግር ባህሏ ኢትዮጵያን እጅ እና እግሯን ተብትቦ ስለስልጣኔ የምታስብበት መተንፈሻ ጊዜ እንኳን
እንዳይኖራት አድርጓት ነበር። ስለዚህ ኢትዮጵያ ከውጭ ወረራ ረጅም የነፃነት ዘመን ቢኖራትም በስልጣኔ
እንዳትገፋ ያደረጋት ሁለተኛው አውራ ምክንያት በእርስ በርስ ጦርነት የሚፈጸመው የመንግስት ሽግግር ባህሏ ነበር
ማለት ይቻላል። በዚህ ጉዳይ ላይ ተክለ ፃዲክ መኩሪያ፣ ባህሩ ዘውዴ፣ ሃሮልድ ማርኪውስ እና ፓንክረስት
የመሳሰሉ የታሪክ ምሑራን ብዙ ጽፈውታል።
 የመንግስት ሽግግር ባህሏም በበኩሉ ከስልጣኔ እንድትርቅ አድርጓል። ለምን ያህል ጊዜ (ስንት አመቶች)? ግምት
መስጠት እንችላለን? እንሞክር!

በኢትዮጵያ ሲደረግ የነበረው የመንግስት ሽግግር ታሪካችን ሁለት አኪያሄዶች ነበሩት። አንደኛው አኪያሄድ ከአንድ
ዝርያ ወደ ሌላ ዝርያ የሚደረግ የመንግስት ሽግግር ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በአንድ ዝርያ ውስጥ ከአባት ወደ ልጅ
የሚፈጸም የመንግስት ስልጣን ሽግግር ነበር። ሁለቱም አይነት የመንግስት ሽግግሮች ከጦርነት ነፃ አልነበሩም።
በጦርነቶቹ መካከል ልዩነት ካለም የጦርነቱ አስከፊነት መጠነ እና የጦርነቱ እድሜ ብቻ ነበር።

ለጥናት እንዲያመቸን ካፄ ኢዛና (321 ዓ.ም.) በፊት ለመንግስት ሽግግር (ለስልጣን) የተደረጉትን የእርስ በርስ
ጦርነቶች በሙሉ ከግምት አናስገባም። ጥናታችንን ይበልጥ ቀላል ለማድረግ ስንል ካፄ ኢዛና ወዲህ ተሞክረው
ያልተሳኩትን ቁጥር ስፍር የሌላቸው ለመንግስት ሽግግር የተደረጉ የእርስ በርስ ጦርነቶች በሙሉ ወደጎን
እንተዋለን። ጥናታችን ካፄ ኢዛና ወዲህ በተደረጉት የተሳኩ የመንግስት ሽግግሮች ላይ ያተኩራል። ስለዚህ በ321
ዓ.ም. በስልጣን ላይ ከነበረው ካፄ ኢዛና ዘመነ መንግስት ጀምረን እስከ በ1983 ዓ.ም. በእርስ በርስ ጦርነት ስልጣን
የጨበጠው አምባገነኑ የህውሃት/ኢህአዴግ መንግስት ድረስ ከነበሩት 1662 አመቶች ውስጥ የመንግስት ሽግግር
ባህሏ ስንት አመቶች እጅ እና እግሯን ተብትቦ በማሰር ስልጣኔ ከውስጥም እንዳታበቅል እንዳደረጋት አጠቃላይ
ግምት ለመስጠት እንሞክራለን። እያንዳንዱ የመንግስት ሽግግር ባህላችን ጦርነት የፈጀው ጊዜ በዝርዝር ተጽፎ
የተላለፈልን መረጃ የለንም። ለግዜው ማድረግ የምንችለው እነ ተክለ ፃዲቅ ጽፈው ካወረሱን ትረካ ግምት
ለመውሰድ መሞከር ነው። እያንዳንዱ የተሳካውም ያልተሳካውም የመንግስት ሽግግር የፈጀውን ጊዜ አመት
በአመት የማስላቱን ስራ ለመጪው ትውልድ ታሪክ ተመራማሪዎች እንተዋለን።

ካፄ ኢዛና (321 ዓ.ም.) ወዲህ የተደረጉትን ዋናዎቹን የመንግስት ሽግግሮች እንደሚከተለው መከፋፈል እንችላለን፥
(1) ከኢዛና ዝርያዎች ወደ ንግስት ዮዲት (ቤተ እስራኤሎች) ዝርያዎች፣ (2) ከቤተ እስራኤሎች ወደ ላስታው መራ
ተክለ ሃይማኖት (ዛጉዌ ስረወ መንግስት) ዝርያዎች፣ (3) በ1262 ከላስታ አገዎች ወደ ሸዋው ይኩኖ አምላክ
ዝርያዎች፣ (4) በ1523 ዓ.ም. ያፄ ይኩኖ አምላክ ዝርያ ከነበረው ልብነ ድንግል ወደ ይማም አህመድ (ግራኝ በሚል
የሚታወቁት እና በአባታቸው የኦጋዴ በእናታቸው ደግሞ የሐረር ተወላጅ የሆኑት)፣ (4) በጎንደር ካፄ ገላውዲዎስ
1533-1552) እስከ ዐፄ እዮዋስ (1747-1761) (በአባት የቋራ አማራ በእናት ደግሞ የየጁ ኦሮሞ)፣ (5) ከራስ ስሑል
እስከ የየጁው ትንሹ ራስ ዐሊ (ዘመነ መሳፍንት)፣ (5) ካፄ ቴዎድሮስ (1847-1860) እስከ ሰቆጣው ዐፄ ተክለ
ጊዮርጊስ (1860-1864) ከዚያ ወደ ተምቤኑ ዐፄ ዮሐንስ (1864-1881) ከዚያ ወደ ሸዋው ምኒልክ (1882-1906)፣
(6) ከምንሊክ ወደ ልጅ ልጃቸው ልጅ እያሱ ከዚያ ወደ ምኒልክ ሴት ልጅ ዘውዲቱ ከዚያ ወደ ኃይለስላሴ ከዚያ
ወደ ደርግ ከዚያ ወደ ህውሃት/ኢህአዴግ። እነዚህ የመንግስት ሽግግሮች በሙሉ የተጠናቀቁት በእርስ በርስ ጦርነት
እና ሽብር ነበር።

ከአባት ወደ ልጅ የተደረጉ የመንግስት ሽግግሮችም ከሁከት እና ከእርስ በርስ ጦርነቶች የጸዱ ስላልነበሩ ሁከቱን
እና ጦርነቱን ለመቀነስ ነገስታቱ ልጆቻቸውን በጠባቂ በሚከተሉት እስርቤቶች ሆነው የንጉስነት ተራቸውን
(እድላቸውን) እንዲጠብቁ አድርገዋል። (1) ደብረ ዳሞ አምባ እስር ቤት፥ በአክሱም ዘመነ መንግስት በዙፋን ላይ
የሚገኘው ንጉሱ ታመመ በተባለ ቁጥር በቤተ ዘመድ ውስጥ “ዙፋን ይገባኛል” “ተረኛው እኔ ነኝ” የሚሉ ሁከቶች
እና ጦርነቶች ይነሱ ነበር። ስለዚህ ይኽን ሁከት እና የርስ በርስ ጦርነት ለማስወገድ ነገስታቱ ልጆቻቸውን እና
በቅርብ ከሚዛመዱዋቸው የሚወለዱትን ጨምረው በትግራይ ከአዲግራት በስተ ምዕራብ በሚገኘው ደብረ ዳሞ
አምባ ጠባቂ ተደርጎላቸው የንግስና ተራቸውን እንዲጠብቁ ይደረግ እንደነበር ተክለ ፃዲቅ መኩሪያ ይገልጻል። (2)
ግሸን አምባ እስር ቤት፥ የአክሱም ነገስታትን ልማድ በመከተል የላስታዎቹ ነገስታትም ተመሳሳይ ችግር ለማስወገድ
ከደሴ በስተምዕራብ ግሸን አምባ ይባል የነበረውን ተራራማ ቦታ ለእስር ቤት ተጠቅመውበታል። (3) ግሸን አምባ
እስር ቤት (እንደገና)፥ የአክሱምን እና የላስታን ነገስታት ልማድ በመከተል እስከ ልብነ ድንግል ድረስ የነበሩት
የሸዋ ነገስታትም ይህንኑ ግሸን አምባን እንደ እስር ቤት ተጠቅመዋል። በግሸን አምባ የነበሩት የነገስታት ዝርያዎች
በሙሉ በእስር ላይ ሳሉ በልብነ ድንግል እና በይማም አህመድ መካከል የተካሄደው እንደፈጃቸው ተክለ ፃዲቅ
መኩሪያ እና የውጭ ታሪክ ጸሐፊዎች ጽፈዋል። (4) ወህኒ ተራራ እስር ቤት፥ በጎንደር ዘመነ መንግስት ደግሞ ካፄ
ፋሲል ጀምሮ ከጎንደር በስተ ምዕራብ የሚገኘውን ወህኒ ተራራን ለተመሳሳይ ተግባር ነገስታቱ ተጠቅመዋል።

ለጥቀን ከኢዛና ዘመነ መንግስት (321 ዓ.ም.) እስከ ህውሃት/ኢህአዴግ ስልጣን እስከጨበጠበት 1883 ዓ.ም. ድረስ
ከተደረጉት የመንግስት ሽግግሮች ውስጥ አለፍ አለፍ እያልን ጥቂት ምሳሌዎች እንመለከታለን፥
 (1) ወደኋላ መለስ ብለን የንግስት ዮዲትን ዘመን ብናይ ከመንግስት ስልጣን በፊት 50 አመቶች ግድም እና
በስልጣን ዘመኗ ደግሞ 40 አመቶች በድምሩ 90 አመቶች የጦርነት ዘመን እንደነበሩ ተጽፎ እናያለን። (90)
(2) በቱርክ እና ግብጽ የታገዙት የይማም አህመድ ዘመንንም ብንወስድ በቱርክ ወታደራዊ የበላይነትን
ከማግኘታቸው በፊት እና ወታደራዊ የበላይነትን የያዙበት አመቶች እንዲሁም ፖርቱጋሎች ክርስቲያኖችን
አግዘው የተዋጉበት አመቶች በድምሩ ከ30 አመቶች በላይ ይሆናል። (30)
(3) ከሠርፀ ዘድንግል ወደ ፋሲል አባት (ዐፄ ሱስነየስ) የተደረገው የመንግስት ሽግግር በቀጣይነት የርስ በርስ
ጦርነት ዘመን ነበር። ሠርፀ ሲሞት ለትንሽ ልጁ አቆብ (1590-1595) አወረሰ። የአጎቱ ልጆች ዙፋን ለኛ
ይገባል የሚል ጦርነት ከፍተው ዙፋኑ ከአቆብ ወደ ዘድንግል (1595-1596) ከዚያ ከዘድንግል እንደገና ወደ
ያእቆብ (1596-1598) ከዚያ በመጨረሻ ወደ ፋሲል አባት ሱስነየስ (1598-1625) የተሸጋገረው በድምሩ 10
አመቶች የርስ በርስ ጦርነት ከተደረገ ቧላ ነበር። ምናልባትም ለዚህ ነበር ፋሲል ዮሐንስ ከተባለው ልጁ
በስተቀር የቀሩትን ልጆቹን እና ሌሎች ዘመዶቹን ወደ ተራራ ወህኒን የላከው። (20)
(4) ታላቁ እያሱ ከተገደለበት (1698) ጊዜ ጀምሮ ባባቱ ቋራ በእናቱ የጁ የሆነው ዐፄ እዮአስ እስከተገደለበት
1761 ዓ.ም. ድረስ የነበሩት 63 አመቶች የማያቋርጥ የእርስ በርስ ጦርነት አመቶች ነበሩ። (63)
(5) በ1761 ዓ.ም. ዘመነ መሳፍንት ከተነሳ ወዲህ እስከ ወደቀበት 1847 ዓ.ም. ድረስ 86 አመቶች ሲኖሩ ከዚያ
ውስጥ የየጁው ራስ ጉግሳ በገዙበት ዘመን ከነበረው ትንሽ መረጋጋት በስተቀር ሰላም አልነበረም። (86)
(6) ከዚያም ያፄ ቴዎድሮስ ዘመን (1847-1860) ማለቂያ ባልነበረው የማስገበር ዘመቻ ተጠምዶ ስለነበር እስከ
ፍጻሜያቸው ድረስ የነበሩት 13 አመቶች የመንግስት ሽግግር የእርስ በርስ ጦርነት አመቶች ነበሩ። (13)
(7) ያፄ ተክለ ጊዮርጊስ 4 አመቶችም የጦርነት ዘመን ነበሩ። (4)
(8) ያፄ ዮሐንስ ዘመን (1864-1881) በግብጾች እና በቅኝ ገዢዋ ኢጣሊያ ጦርነቶች ከመጠመዱ ባሻገር ለስልጣን
ከውስጥ የሚያፈነግጠው ጥቂጥት አልነበረም። በዚህ የተነሳ ዮሐንስ መጨረሻ መተማ ላይ እስከሞቱበት ጊዜ
ድረስ በቤተ መንግስታቸው ያደሩባቸው ቀኖች በጣም ጥቂት ነበሩ። (17)
(9) ከምኒሊክ ዘመነ መንግስት (1882/9-1906/13) እስከ ምኒልክ ፍጻሜ (1906/13) ድረስ የተወሰነ የሰላም ጊዜ
ቢኖርም ከዚያ እስከ ኃይለስላሴ ንጉሰ ነገስት (1922/30-1967/75) ያልተቋረጠ የመንግስት ሽግግር ጦርነቶች
ተካሂደዋል። የምኒልክን ዙፋን ወራሽ የልጅ እያሱ ዘመን (1906/13-1919/27) ከመንግስት የተፈነቀለው
በብዙ የርስ በርስ ደም መፋሰስ ነበር። ከዚያም ወደ ኃይለስላሴ ንግስና በተደረገው የመንግስት ሽግግር ሂደት
የልጅ እያሱን ደጋፊዎች፣ የንግስት ዘውዲቱን (1919/27-1922/30) ደጋፊዎች፣ የምኒልክን ባለቤት የእቴጌ
ጣይቱን ደጋፊዎች የማጽዳት በርካታ የርስ በርስ ጦርነት ተፈጽሟል። የኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ ከርካሳ
አውሮፕላን የመጀመሪያ ስራ ለመንግስት ሽግግር በጎንደር ተቃዋሚዎች ላይ ቦንብ መጣል እንደነበር እና
የኢትዮጵያ የመጀመሪያው ታንክም በአዲስ አበባ ለተመሳሳይ ጉዳይ ስራ ላይ ውለው እንደነበር ባህሩ ዘውዴ
ያመለክታል። የኃይለስላሴን የመጨረሻዎቹ አመቶች የእርስ በርስ ጦርነቶች ብንጨምር ከምኒልክ ዘመነ
መንግስት ጅማሬ እስከ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግስት ፍጻሜ ድረስ በግምት 16+4=20 አመቶች የጦርነት
አመቶች ብሎ መውሰድ ይቻላል)
(10) የደርግ 17 አመቶች ከዘመነ መሳፍንት በባሰ ደረጃ ከ7 በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵያዊ ድርጅቶች እርስ በርስ
ተዋግተዋል። (17)

ስለዚህ ካፄ ኢዛና ከነገሰበት ከ321 ዓ.ም. እስከ በ1983 ዓ.ም. ድረስ ከነበሩት 1662 አመቶች ውስጥ የተሳኩት
የመንግስት ሽግግሮች በግምት ከ360 እስከ 400 አመቶች ያህል ጊዜው ወስደዋል ብንል ስህተት አይመስለኝም።

በ400 አመቶች ላይ ያልተሳኩት የመንግስት ሽግግሮች የወሰዱት ጊዜ ቢጨመርስ? በዚያ ላይ ኢትዮጵያ ከቱርኮች
እና ከኢጣሊያ ጋር ያደረገቻቸው ጦርነቶች የወሰዱት ጊዜ ቢጨመርስ?

እንደ እኔ ከሆነ በአጠቃላይ በትንሹ ከ500 አመቶች ላላነሰ ጊዜ ኢትዮጵያ እጅ እና እግሯ በጦርነት ተተብትቦ
ከአገር ውስጥ ስልጣኔ እንዳይበቅል ተደርጓል። ትንሽ የሰላም ጊዜ እና ጥሩ መሪ ሲገኝ የሚደረገው እድገትም
ለጥቀው በሚካሄዱ ጦርነቶች ይወድማሉ። አገሪቱ ወደ ኋላ ትሄዳለች። ይህን የእርስ በርስ ጦርነት አውዳሚነት
እና ጎታችነት ጸባይ አስመልክቶ ተክለ ፃዲቅ መኩሪያ ካፄ ልብነ ድንግል እስከ ዐፄ ቴዎድሮስ በሚለው መጽሐፉ
የታላቁ እያሱን ዘመን እንደ ምሳሌ በመውሰድ በታላቁ እያሱ በዘመን የገነባው በሙሉ ከታላቁ እያሱ በኋላ
በመጡት የርስ በርስ ጦርነቶች መውደማቸውን ይተርካል።

የመንግስት ሽግግር እርስ በርስ ጦርነት ታሪካችን ኢትዮጵያችንን ወደ ኋላ የማስቀረት እንጂ ወደ ስልጣኔ
የማራመድ ሚና ተጫውቶ እንደማያውቅ ግልጽ ይመስለኛል። የመንግስት ሽግግር ባህላችን ብዙ ጊዜ አቃጥሏል
ኢትዮጵያ ወደፊት እንዳትራመድ በማድረግ። ከዚህ በኋላ ኢትዮጵያ በስልጣኔ ብዙ እርቀዋት የሄዱትን አገሮች ለመድረስ የርቀት ቅነሳ ስራ ላይ በትጋት መሰማራት አለባት። ወደ ስልጣኔ መንደር የሚያደርሱ ብዙ ስራዎች
በትጋት መስራት ይጠበቅባታል። ለመንግስት ሽግግር የሚደረግ የ’እርስ በርስ ጦርነት ግን አንዱ አይደለም።

በቅርቡ ደግሞ ትጥቅ ትግል ለማጣፈጥ ሲባል አዲስ ሰበካ ተጀምሯል። እኛ የምናካሂደው ትጥቅ ትግል የማንዴላ
አይነት ትጥቅ ትግል ነው የሚል ማጭበርበሪያ። ጦርነት ጦርነት ነው። ይህን አባባል የሚያስተጋባው ቡድን
በአንድ በኩል ተከታዮቹ መከተላቸውን እንዲቀጥሉ ለማድረግ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ሰላማዊ ትግል
ካደረሰበት ትኩሳት ለጊዜው እረፍት ለማግኘት በሰላማዊ ትግል ንድፈ አሳብ ተማሪዎች እና ደጋፋዊዎች ላይ
የከፈተው የማሸማቀቅ የስነ ልቦና ጦርነት ነው። መለስ ዜናዊ በምርጫ 97 የተቃሚው አሳብ የህዝብ ድጋፍ እያገኘ
መሄዱን ሲያስተውል ደጋፊዎቹን ለማረጋጋት እና ተቃዋሚውን ለማሸማቀቅ ኢንተርሃምዌይ እስከማለት ደረሶ
እንደነበር አስታውሳለሁ። አምባገነኖች ብዙ ይላሉ። የሚሉት ሁሉ ግን ከአጭር ጊዜ መፍትሄነት ባሻገር
አይረዳቸውም። ይሄም ያን አይነት የስነ ልቦና ጦርነት ነው። የአለም ህዝብ ለማንዴላ ክብር የለገሰው ጠበንጃ
በማንሳቱ አይደለም። በሃውልቱም ላይ የሚጻፈው ጦረኛ መሆኑ አይደለም። ቤተሰቡም እስከ ልጅ ልጆቹ ድረስ
በአደባባይ ስለማንዴላ የሚሰብኩት ሰላማዊነቱን እና በሰላማዊ መንገድ አፓርታይድን እንዳፈረሰ ነው።
አፓርታይድ የፈረሰው በትጥቅ ትግል አይደለም። የደቡብ አፍሪካ የመጀመሪያው ጥቁር ፕሬዘዳንት ሊሆን
የቻለው በትጥቅ ትግል አይደለም። ጥቁር እና ነጭ ደቡብ አፍሪካውያን በህብረት ያደረጉት ሰላማዊ ትግል
መዘንጋት የለበትም። ታዋቂ ጥቁር እና ነጭ ደቡብ አፍሪካውያን አርቲስቶች የአለምን ህዝብ በአፓርታይድ ላይ
ለማስተባበር ያደረጉት ቀጣይነት ያለው አለም አቀፍ ሰላማዊ ዘመቻቸው መዘንጋት የለበትም። ማንዴላን
ለማስፈታት እና አፓርታይድን ለማስፈታት የአለም ህዝብ ያደረገው ሰላማዊ ትግል መዘንጋት የለበትም።
በማንዴላ ሃውልት ላይ የሚጻፈው የጦር አበጋዝነቱ እና የገደለው ሰው ቁጥር ሳይሆን ማንዴላ ከእስር ቤት ከወጣ
በኋላ የፈጸመው ነው።


በመጨረሻ ወደ ኢትዮጵያ ልመለስ እና ውይይቴን ልደምድም። ሰላማዊ ትግል ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ ብቻ
አይደለም። ሰላማዊ ትግል በምርጫ መሳተፍ ብቻ አይደለም። ሰላማዊ ትግል በአደባባይ ወጥቶ መቃወም ብቻ
አይደለም። ሰላማዊ ትግል እነዚህን ሁሉ ማድረግ ነው። በተጨማሪ ሰላማዊ ትግል ህዝብን የራሱ ነፃ አውጭ
በማድረግ (1) በስልጣን ላይ የሚገኝን አምባገነን መንግስት አስወግዶ ህዝብን የመንግስት ስልጣን ባለቤት
ማድረግን፣ (2) መፈንቅለ መንግስት ቢነሳ ትብብር መንፈግ፣ (3) እንደ ህውሃት/ኢህአዴግ ከጫካ ወይንም
ከጎርቤት አገር (ኤርትራን ጨምሮ) ተነስቶ ልውረርህ የሚል ቡድን ቢመጣ ህዝባዊ መከላከል (Civil Resistance)
ማድረግን ያካትታል። ሰላማዊ ትግልን በሚመለከት ግንዝቤያችን ሰፋ ያለ መሆን አለበት። የቀድሞው የመንግስት
ሽግግር ባህላችን ደደብ ነው። ብልህ ሰዎች አይከተሉትም። 

No comments:

Post a Comment