(ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው)
በእርግጠኝነት ኢትዮጵያዊ ልብ ላለው ሰው ሁሉ ስለ አድዋ ድል ሲሰማና ሲያወራ ልቡ በኩራት ይሞላል መንፈሱ ይነቃቃል፡፡ ኢትዮጵያዊ ብቻም አይደለም በየትኛውም ዓለም ያለ በቅኝ ግዛት ቀንበር ፍዳ ያየ የትኛውም የሰው ዘር ጭምርም እንጅ፡፡ ይህን አንጸባራቂ ድል መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በአንድነት ተሰልፎ ካስመዘገበ እነሆ ነገ የካቲት 23 ቀን 2006ዓ.ም 118 ዓመቱን ይይዛል፡፡ ይህንን ድል ለመቀዳጀት ፈተና የነበሩት ነገሮች ምን ምን ናቸው? ለመሆኑ ይህ ድል እንዴት ተገኘ ? የዚህ ታላቅ ድል ትሩፋቶችስ ምን ምን ናቸው? የዚህ ድል ጠላቶች እነማን ናቸው? ይህ ድል እንዴት ይጠበቃል? ብዙ ቢባልለት ከማይበቃው ከአድዋ ድል እነዚህን ነጥቦች ብቻ ነጥለን ለማየት እንሞክራለን፡፡
ዐፄ ምኒልክ ምታ ነጋሪት ክተት ሠራዊት ብለው ፋሽስት ጣሊያን በዘመነ ዐፄ ዮሐንስ 4ኛ ከነበረበት አልፎ የትግሬ ገዥ የነበሩትን ዐፄ ዮሐንስ 4ኛ ከእሳቸው ቀጥለው እንዲነግሡ በማሰብ ሊሞቱ በሚያቃትቱበት ወቅት ወራሸ ነው ለእኔ ያደረጋችሁትን ሁሉ ለእሱም አድርጉ በማለት ተናዘውላቸው የነበሩትን ራስ መንገሻን ድል አድርጎ ሠራዊታቸውን ከበተነ በኋላ አልፎ መላዋን ሀገራችንን ቅኝ ለመግዛት ወደ መሸገባቸው ቦታዎች ወደ አንባ አላጌ፣ መቀሌ እንዳሥላሴና አድዋ ከመዝመታቸው እነዚያን አኩሪ ድሎች ከማስመዝገባቸውና ታሪክ ከመሥራታቸው በፊት እነኝህን ድሎች እንዳንቀዳጃቸው የሚያደርጉ እጅግ ከባባድ ፈተናዎች ተጋርጠውብን ነበር፡፡ የአድዋን ድል በሌሎች ሀገራት ከተገኙት ድሎች ልዩ የሚያደርገውም ይሔው ነው፡፡ እነዚህ ፈጽሞ ሊታለፉ የማይቻሉ መሰናክሎችን ታልፎ የተገኘ ድል በመሆኑ፡፡
የአድዋን ድል ለመቀዳጀት አያስችሉ የነበሩት ፈተናዎች ምን ምን ናቸው፡-
- የከብት እልቂት፡- ፋሺስት ጣሊያኖች ኢትዮጵያን ቅኝ ለመያዝ ሲያስቡ ቅኝ ገዥዎች በአፍሪካና እስያ በቀላል ግጭት ቅኝ ሀገር መያዝ እንደቻሉ ሁሉ በኢትዮጵያ ይህ መልካም እድል እንደማያጋጥማቸው ጠንቅቀው ዐውቀውት ነበር፡፡ በመሆኑም ጦርነት መግጠማቸው የማይቀር ከሆነ የኢትዮጵያንና የመንግሥቷን አቅም ለማዳከም የሚያስችል ስልት ነደፈ ከስልቶቹ አንዱም የሀገሪቱ ሀብት መሠረት የሆነውን ግብርናዋን ማሽመድመድ መጉዳት ነበር፡፡ ይህንን ሲያስቡ ግብርናዋን ለመጉዳት ማድረግ የሚችሉት ነገር ሆኖ ያገኙት የከብት ሀብቷን መጨረስ ነበር፡፡ ይህንን ለመፈጸም ሲባል ከህንድ ሀገር ሶስት የታመሙ ከብቶችን በምጽዋ በኩል አስገብተው ከደማቸው እየወጉ የኞቹን ደኅናዎቹን ከብቶች በመውጋት አጋቡባቸው በሽታውም በአጭር ጊዜ ተዛምቶ ከኢትዮጵያም አልፎ አጠቃላይ የቀጠናውን ከብት ፈጀው፡፡ ውጤቱም ፋሽስቶቹ ከጠበቁት እጅግ የበዛ ሆኖ በሀገራችን ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ‹‹ክፉ ቀን›› በመባል የሚታወቀውን ረሀብና ችጋር አመጣ፡፡ የሚበላ ነገር ጠፍቶ ዋልካ አፈርና ሳር ቅጠሉ ሁሉ የተበላበት ዘመን ነበር፡፡ ሕዝቡ ደቀቀ አለቀ ሀገሪቱ ተሽመደመደች፡፡
- የስንቅና ትጥቅ (logistics) ዝግጅት እጅግ ውስንነት፡- ፋሽስት ጣሊያን በወቅቱ ኃያላን ከሚባሉ የአውሮፓ ሀገራት አንዱ ነበረ፡፡ እንደ ኃያልነቱም ከ20 ሺ በላይ ለሆነው ላሰለፈው ጦሩ ዘመናዊ መሣሪያ በነፍስ ወከፍ ከማስታጠቁም ባሻገር ሠራዊቱ በወጉ የተደራጀ ዘመናዊ የውትድርና ሥልጠና የወሰደ ባጠቃላይ ከበቂ በላይ የስንቅና ትጥቅ ዝግጅት የነበረው ነበር፡፡ በእኛ በኩል የነበረው ደግሞ ባጋጠመው የረሀብና አስከፊ ችጋር የደከመ ሠራዊት ከመሆኑም በላይ ከፍተኛ የሆነ የስንቅና ትጥቅ አቅርቦች ችግር ነበረበት፡፡ በወቅቱም ሠራዊቱ ነፍሱን ለማቆየት በቀን እጅግ መጥኖ ከሚቀምሳት በየ አገልግሉ ቋጥሮ ከያዛት ጥቂት ዳቦቆሎ፣ የደረቀና የሻገተ ቂጣ፣ ቆሎና በሶ የመድኃኒት ያህል ጥቂት ጥቂት የሚቀምስ ሠራዊት ነበረ እንጅ የስንቅ አቅርቦቱን አስቦ በየ ዕለቱ አብስሎ የሚያቀርብለት አካል አልነበረም፡፡ ሰራዊትም ሲባል ሐበሻ እንዲያው በተፈጥሮው ተዋጊ በመሆኑ እንጅ ሊገጥመው እንደተዘጋጀው ጠላቱ ሠራዊት በወጉ የወሰደው የውትድርና ትምህርት ጨርሶ አልነበረም፡፡ የታጠቀው መሣሪያም ቆመህ ጠብቀኝ በሚባል የሚታወቁ ኋላ ቀር መሣሪያ ሆኖ ይሄንንም ቢሆን የያዙት ከሠራዊቱ እጅግ ጥቂቶቹ ነበሩ የተቀረው ግን የያዘው ጦርና ጋሻ ጎራዴ ነበር፡፡ ይሔም አይጠቅምም ማለት ሳይሆን በጦር በጎራዴና በጋሻ ውጊያ የሚደረግበት ዘመን አልፎ ከሩቁ ጠላትን መልቀም ማስቀረት የሚቻልባቸው ከመድፍ እስከ መትረየስ ያሉ ዘመናዊ መሣሪያዎች የወጡበት ዘመን በመሆኑ ለሚደረገው ጦርነት የጦር የጎራዴ እና የጋሻ ጥቅምና አገልግሎት እጅግ በጣም ውስን ሆኖ ነበር፡፡ ጦርነት በጦር በጎራዴ ይደረግ የነበረበት ዘመን ለእኛ እጅግ የቀና የበጀና የሰለጠም ነበር፡፡
- የባንዶች ሚናና የጠላት የመከፋፈል ስልት፡- ፋሽስት ጣሊያን የኢትዮጵያን ሠራዊት ለማዳከም ከተጠቀመበት ስልት ሌላኛው ባላባቶችንና መሳፍንቱን እስከ ራሶች ድረስ እንዲከዱ በማድረግ ከጎኑ ማሰለፍ ነበር፡፡ ጥቂት የማይባሉትንም ማስካድ ችሎ ነበር ነገር ግን እነዚህ የከዱና ከነሠራዊታቸው በባንድነት የተሰለፉ መኳንንት የጠበቁትንና የፈለጉትን አቀባበልና መስተንግዶ እንዳላገኙና እንደማያገኙም ሲገባቸው የዐፄ ምኒልክ ይቅር ባይነት ዋስትና ሆኗቸው ብዙዎቹ ተመልሰዋል፡፡ ይሁን እንጂ እነኝህ ከድተው የነበሩ ሹማምንት መመለሳቸው የእውነት ከልብ ነው ወይስ ለተልዕኮ? የሚለው ጉዳይ ለወገን ሠራዊት በወቅቱ እጅግ አንገብጋቢ ጥያቄና እውነቱን ለመረዳት ከመቸውም አጋጣሚ በበለጠ አምላክነትን የሚያስመኝ፤ ሥጋት ጥርጣሬውም እረፍትና እንቅልፍ የሚነሳ አምኖ ለማሰለፍም ለመተውም ያስቸገረበት ጉዳይ ሆኖ ነበር፡፡
- የፋሽስት ጣሊያን ጦር መሽጎ ያለ መሆኑ፡- ጦርነት በሚደረግበት ወቅት ጦርነት ከሚያደርጉት ባላንጣ አካላት አንደኛው ምሽግ ይዞ የሚጠብቅ ከሆነ ጦርነቱ ለአጥቂው ወይም ምሽግ ላልያዘው ክፍል እጅግ ከባድና አስቸጋሪ የሚያስከፍለው ዋጋም ከመሽገው አካል ጋር ሲነጻጸር በጣም የሚበዛ መሆኑ የማይቀር ነው፡፡ እኛንም ያጋጠመን ይሄው ነበር በሶስቱም ቦታዎች የጠላት ጦር ምሽጉን በሚገባ ገንብቶ ከምሽግ ማዶም በባዶ እግሩ የሚጓዘውን አርበኛ ሠራዊት እንዲቆራርጥ በጠርሙስ ስብርባሪና በጦር ችካሎች ከዚያም በፈንጂ የታጠረ ምሽግ ውስጥ ሆኖ አድፍጦና መሽጎ ይጠብቅ የነበረ ጦር ከመሆኑ የተነሣ የጠላትን ጦር ከዚህ ምሽጉ ለማስወጣት ምን ያህል መሥዋዕትነት ሊጠይቅና ሊያስከፍል እንደሚችል መገመት ይቻላል፡፡ እንኳንና ተመጣጣኝ ትጥቅ ሳይያዝ ቢያዝም እንኳ ሁኔታው እጅግ ከባድ ነው በዚህ ላይ የእኛ ጦር ዘመናዊ የውጊያ ስልት ካለመማሩ ጋር ተያይዞ ተኝቶ መሬት ላይ በመሳብ መተኮስን እንደ ነውርና ፈሪነት አድርጎ የሚቆትር በመሆኑ ደረቱን ሰጥቶ በከፍተኛ ድፍረትና ወኔ ይዋጋ የነበረ ጦር ከመሆኑ ጋር ተያይዞ መሥዋዕትነቱን እጅግ የከበደ አድርጎት ነበር፡፡ የሚገርመው ነገር ግን ከነዚህ ነባራዊ ሁኔታዎች አኳያ ከጦርነቱ በኋላ የደረሰብን የሟችና ቁስለኛ መጠን በጠላት ሠራዊት ከደረሰው እምብዛም የሚበልጥ አልነበረም፡፡
- የህክምና አገልግሎት ችግር፡- እንዲህ ዓይነት የሕዝብ እንቅስቃሴ በሚደረግበት ወቅት ወረርሽኝ ይከሰታል፡፡ ወረርሽኝ ሲከሰትም ለዚህ ጉዳይ ቀድሞ የተዘጋጀ ህክምና ከሌለ ከባድ ጥፋት አስከትሎ ያልፋል፡፡ የወገን ጦር ይሔንን አደጋ መከላከል የሚችልበት አቅምና ዝግጅት አልነበረም ሌላው ቀርቶ ቁስለኛን እንኳን ማከም የምንችልበት መድኃኒትና ባለሙያ አልነበረንም ሁሉም ለየራሱ ሐኪም ነበረ፡፡ አስተናግር ቅጠሉን ጨምቆ አዘጋጅቶ ይዞት የመጣውን ቁስሉ ላይ እያፈሰሰ እርስ በራሱ ለመተካከም ይሞክራል እንጅ ይሔንን ጉዳይ የሚከውን የህክምና ቡድን አልነበረም፡፡
እንግዲህ እነዚህና ሌሎች ሊታለፉ የማይችሉ እንደተራራ የገዛዘፉ ከባባድ ደንቀራዎችን ፈተናዎችን በእግዚአብሔር ቸርነት በሐበሻነት ጽናት እናት አባቶቻችን አልፈው ነው የአንባላጌውን፣ የመቀሌውን፣ በመጨረሻም የአድዋን ድል ለመቀዳጀት የቻሉት፡፡ የአድዋ ድል በሌሎች ዜጎች ዘንድም በከፍተኛ አድናቆት የሚደነቀው የሚከበረውም ከዚህ የተነሣ ነው፡፡
ለመሆኑ ይህ ድል እንዴት ሊገኝ ቻለ?፡- ለድሉ መገኘት ትልቁ ድርሻ የእግዚአብሔር ረድኤት ቢሆንም እግዚአብሔር ሲሠራ በምክንያት ወይም መሣሪያ የሚያደርገው ነገር መኖሩ አይቀርምና ለእናት አባቶቻችን ቁርጠኝነትን፣ ጽናትን፣ መጨከንን ሰጥቶ ከቶውንም የማይታለፉትን ፈተናና መከራን አስተናግዶም በእነሱም ደክሞ ደቆ የነበረ ሕዝብ ተሰባብሮ ተነሥቶ እንዲህ ዓይነት አስደናቂ ድል ለማስመዝገብ በቃ፡፡ እንዲህ ዓይነቱን ድል ለማስመዝገብ ሐበሻ ሆኖ መገኘትን የግድ ይጠይቅ ነበር አደረግነውም፡፡ በመሆኑም “ነፃነት ወይም ሞት” “ባሪያ ሆኖ ከመኖር ነፃ ሆኖ መሞት” የሚለው የጨከነ መርሑ ከፊቱ የተደቀኑ ግዛዙፍ ፈተናዎችን መሰናክሎችን ከነ አካቴው ከግምት ውስጥ እንዳያስገባ አድርጎት በከፍተኛ ቁርጠኝነትና ጽናት በመዋጋቱ ድሉን ሊያገኝ ቻለ፡፡
የዚህ ታላቅና አንጸባራቂ ድል ትሩፋቶች ምን ምን ናቸው? ይህ ታላቅ ድል ከእኛም አልፎ ለመላው ዓለም ጭቁኖች በርካታ ትሩፋቶችን አበርክቷል ከእነዚህ በርካታ ትሩፋቶቹ ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህል፡-
1. የቀለም ልዩነትን መሠረት ያደረገው የብቃት ደረጃ ልዩነት አስተሳሰብን ፉርሽ መሆኑን ማረጋገጥ ችሏል፡፡ ከዚህ ድል አስቀድሞ ጥቁር ሲባል ሰብአዊ እሴት አልባ፣ ለባርነት የተፈጠረ፣ ሥልጣኔ የማይገባው አድርገው ያስቡት ነበር፡፡ ከዚህም አልፈው ተናጋሪ እንስሳ እያሉ ይገልጹት ነበር፡፡ ጥቁሮቹ እናት አባቶቻችን ግን ፈጽሞ ሊታለፉ የማይቻሉ ፈተናዎችን አልፈው ለክብራቸው ለነፃነታቸው፣ ለሉዓላዊነታቸው የማይችሉት ነገርም እንኳን ቢሆን አንችለውምና ምን እናድርግ ብለው ክብራቸውን፣ ነፃነታቸውን፣ ሉዓላዊነታቸውን ለድርድር ሳያቀርቡ ለሰብአዊ ክብራቸውና ለማንነታቸው ታይቶ በማይታወቅ ቀናኢነት በየትኛውም የዓለም ክፍል ያለ ማንኛውም ዓይነት የሰው ዘር አደርገዋለሁ ብሎ ሊሞክረው ቀርቶ ሊያስበው በማይችለው ሁኔታ በግሩም ችሎታና የአጨራረስ ብቃት ከውኖ በማሳየቱ ጥቁር እንዲህ እንዲህ ነው እየተባለ ዝቅ ተደርጎ ይቆጠርና ይታይ የነበረው አስተሳሰብ የተሳሳተ መሆኑን የግዳቸውን እንዲያምኑ አድርጓል፡፡
2. የነፃነት ትግልን አነቃቅቷል ቀስቅሷል፡- ጥቁር አፍሪካዊያን ለአምስት ምእተ ዓመታት ያህል በግፈኛ ነጮች ሲሰበክላቸው የኖረውን የጥቁርን ተገዥነት ወይም ለአገልጋይነት መፈጠር አምኖ ተቀብሎ ሰጥ ለበጥ ብሎ የመገዛትን አስተሳሰብ አዳብሮ ወደ አውሮፓና አሜሪካ እየተጋዘ እየተሸጠ እየተለወጠ ይገዛ ያገለግል ነበር፡፡ ሐበሾቹ ጥቁሮች አድዋ ላይ ያበሩላቸው ፀሐይ ግን ይሄንን የጨለመ አስተሳሰብ ጠራርጎ በማጥፋቱ የነጻነት ትግልንና የነፃነት ታጋዮችን በየስፍራው በየአቅጣጫው እንዲቀጣጠል አድርጎ እነሆ ዛሬ ላይ ያን ሁሉ ግፍ በጥቁርነቱ ብቻ ይጋት የነበረው የሰው ዘር ነጻነቱን አረጋግጦ ቢያንስ በገዛ ሀገሩ እንኳን እንደ ሰው መኖር የሚችልበትን ሁኔታ መፍጠር እንዲችል አብቅቷል፡፡
3. የተረሳውን ታሪካችንን አስታውሷል፡- ሐበሻ እንደሕዝብና እንደ ሀገር ከማንም የቀደመ የሥልጣኔና የመንግሥት ታሪክ ያለውና የነበረው ሕዝብ ነው ይህ ግን በወቅቱ በነበረው አስገዳጅ ችግር ሳቢያ ከዐፄ ፋሲል ጀምሮ ለረጅም ጊዜ ቆይቶ በነበረው ዝግ መመሪያ (closed policy) ምክንያት ዓለም እኛን እኛም ዓለምን ረስተን ተረሳስተን ስለነበረ ዓለም በየጊዜው መረጃውን እያደሰ እንዳወቀን እዲቀጥል ማድረግ ሳንችል ቀርተን ነበር፡፡ የአድዋ ድል ግን ዓለም ስለኛ ያለውን መረጃ ካጎረበት እያወጣ እንዲያወራ እንዲህ እኮናቸው እንዲህእኮ ነበሩ እያለ እንዲያወራ አድርጎታል፡፡ ያወሩልን ይፅፉልን ከነበረው ታሪኮቻችን የሚበዛው እኛም እንኳን እራሳችን የማናውቃቸው ናቸው፡፡
4. የሕዝባችንን አንድነት አጽንቷል፡- የጠላት ወረራ ለመኳንንቶቻችንና ለመሳፍንቶቻችን ትልቅ ትምህርትን ሰጥቷል፡፡ በአንድነት የመቆምን አስፈላጊነት የአንድነትን ጥቅም በሚገባ አስገንዝቧቸዋል፡፡ ከዚያ አስቀድሞ ከዘመነ መሳፍንት ጀምሮ በመሳፍንቱና በባላባቶች ዘንድ የየራሳቸውን ጎጥ እንደ ሀገር በመቁጠር የየራሳቸውን ‹‹ሀገር›› የመመሥረት የማይጠቅምና ኋላ ቀር አስተሳሰብ ያስቡ ነበር፡፡ ይህን የትም የማያደርስ አስተሳሰብ ለማጥፋት ዐፄ ቴዎድሮስን እጅግ አድክሟል፡፡ በዐፄ ቴዎድሮስ እጅ ያደጉት ዐፄ ምኒልክ 2ኛም የዐፄ ቴዎድሮስ 2ኛ ሕልም ገብቷቸው ስለነበር ጥረታቸውና ሁኔታዎች ፈቅደውላቸው የዐፄ ቴዎድሮስን ሕልም ለማሳካት ችለዋል፡፡ የአድዋ ድልም ለመሳፍንቱ የማይረሳ ትምህርትን ስለጣለላቸው ከዚያ በኋላ አስቀድሞ የነበረው ዓይነት የመሳፍንት አስተሳሰብ እንዳይኖር አድርጓል፡፡
5. ለቀጣይ ትውልድ ታሪክ እንዴት እንደሚሠራና እንደሚጠበቅ ምሳሌነቱን ትቶ አልፏል፡- ሀገራችን ከ4500ዓመታት በላይ የመንግሥት ታሪክ አላት እንደ ሀገር ከቆመችበት ጊዜ ጀምሮ ነጻነቷን ለመንጠቅ ተደጋጋሚና አደገኛ ፈተናዎችን አሳልፋለች፡፡ እነዚሁ ጣሊያኖች በቀደመው ስማቸው ሮማዊያን ከቄሳሮች ዘመን ከሁለት ሽህ ዓመታት በፊት ጀምረው ሲፈታተኑን ኖረዋል፡፡ የአድዋ ድል እናት አባቶቻችን የዚህችን ሀገር ነጻነት እንደምን ባለ መሥዋዕትነት አስጠብቀው እንደቆዩና ይህ ረጅም ታሪኳ እንዴት እንደተሠራ የቅርብ ጊዜ ምሳሌነት የተወ ድል ነው፡፡ በደካማ ጎን መግባት የሚችሉበት ጠላቶቻችን ግን የትግል ስልታቸውን በቀጥታ ከሚተኮሰው አፈሙዝ ወደ ተለየ ዓይነት በመለወጥና ባንዶችን በማሠማራት የአድዋ ድል ከተወልን ምሳሌነት ልንማርና እኛም የድርሻችንን ታሪክ ልንሠራ የምንችልበትን ዕድል አጥበውት ሀገርን፣ አንድነትን፣ታሪክን፣ ነጻነትን፣ ሉዓላዊነትን፣ ክብርን መሠረቱ ያላደረገ የየግል ዓላማና አስተሳሰብ አራጋቢዎች አድርገውን አንድነታችንን አደጋ ላይ ጥለውታል፡፡በዚህ ረገድ እየተሳካላቸው ይገኛል፡፡ ፈጣሪ ይቅደምልን እንጂ የዚህ ውጤት ደስ የሚያሰኝ አይሆንም፡፡
6. የታሪክ ሀብትን ትቶልናል፡- አንዲት ሀገር ዜጎቿ ጠንካሮች ከሆኑ ሁለቱም ሀብቶች ይኖሯታል ቁሳዊና መንፈሳዊ ሀብቶች ታሪክ መንፈሳዊ ሀብት ነው፡፡ ታሪክ መነቃቃትን የሚፈጥር ታላቅ ኃይል ነው፡፡ ቁሳዊ ሀብትም የመፍጠር ዐቅም አለው፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያ ሁለቱም ሀብቶች ነበሯት፡፡ ነበሯት ማለቱ ግድ ሆኗል አሁን ላይ ቁሳዊው እንደሌለ ግልጽ ቢሆንም መንፈሳዊው ሀብታችንም ራሱ ድራሹ እንዲጠፋ በከፍተኛ ትጋት እየተሠራበት ነውና ነበረን ማለቱ ይቀላል፡፡ ሊገባኝ ያልቻለው ነገር ግን ከዚህ ማን ምን ዓይነት ትርፍ አንዴት ሆኖ እንደሚያገኝ፤ ጥቅሙ ምን እንደሆነ ነው፡፡ ለሕዝቡ ልጠይቅ የምሻው አንድ ጥያቄ አለኝ የእናት አባቶቻችን ሀገር ኢትዮጵያ በዓለም ውስጥ ከነበሩት አራት ኃያላን መንግሥታት አንደኛዋ ነበረች፡፡ ይህች ሀገር ዛሬ የዓለም ጭራ ደሀዋ ሀገር ሆናለች ለምን? ይህ እንዴት ሲሆን ቻለ? እነሱ ጋር የነበረው ጠንካራ ጎን ይህችን ደሀና ደካማዋን ኢትዮጵያ ከፈጠርነው ከእኛ ጋር ያለው ደካማ ጎን ምንድን ነው?
7. ዕውቅናና መከበርን አትርፎልናል፡- ይህ ድል የማያውቁን አንዲያውቁንና ሀገር ለሀገር ለሚደረግ ግንኙነት ተመራጭ እንድንሆን አድርጓል፡፡ የሚያውቁንም እንዲያከብሩን አድርጓል፡፡ ባጠቃላይ ወዳጅ ብቻ ሳይሆን ጠላትም እንዲሁ በተመሳሳይ ሳይወድ በግድ ዕውቅናና ክብር እንዲሰጥ አድርጎታል፡፡ የዛሬን አያርገውና ከዚያ በኋላ ለመጣችው ኢትዮጵያም ሞገስን አጎናጽፎ በዲንሎማሲው (በአቅንዖተ ግንኙነቱ) ተደማጭ ተከባሪ እንድንሆን አድርጓል፡፡
8. ለመሪነት ሚና ተመራጭ እንድንሆን አድርጓል፡- ይህ ድል በሰጠን ዕውቅና ሳቢያ በተለያየ አቅጣጫ የፈጠራቸው በቅጭ ግዛት ይማቅቁ የነበሩ ሀገራት የፀረ ቅኝ ግዛት እንቅስቃሴ በሚያደርጉበት ወቅት ይህንን እንቅስቃሴያቸውንና ትግላቸውን እንድንደግፍ እንድናስተባብር ለመጠየቅ አስገድዷቸዋል፡፡ ሀገራችንም ይህንን ትግል የመምራቱን ታሪካዊ ኃላፊነት ሙሉ ለሙሉ በማመን ሀገራቱ ነጻ እስኪወጡ ድረስ የራሷን የጦር መሪዎችንና ተዋጊዎችን በማሰለፍ ጭምር ትግሉን ስታግዝ ስታስተባብር የተጣለባትንም አደራ በሚገባ ተወጥታለች፡፡ ለቀድሞው የአ.አ.ድ ለአሁኑ አ.ህ እና ለሌሎች አህጉራዊና ዓለም ዓቀፋዊ ድርጅቶች መቀመጫነት እንድትመረጥ ያበቃትም የዚሁ ድል ትሩፋት ነው፡፡
9. ሰንደቅ ዓላማችንን እንድንወስን አብቅቷል፡- በእርግጥ ከአድዋ ድል አስቀድሞም የሀገራችን ነገሥታት ቀይ ቢጫ አረንጓዴ ወይም አረንጓዴ ቢጫ ቀዩን ሰንደቅ ይጠቀሙ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ነገር ግን በአዋጅና በይፍ ዕውቅና ተሰጥቶት ሀገራችንንና ሕዝባችንን እንድትወክል የተደረገው ዐፄ ሚኒልክ አድዋ ላይ ይህንን አንጸባራቂ ድል ከገኙ በኋላ እዚያው አድዋ ላይ አዋጅ አስነግረው ከእንግዲህ ወዲህ ይህ ቀይ ቢጫ አረንጓዴ ሰንደቅ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ሆኗልና ከክብር በላይ ክብርን፣ ከፍቅር በላይ ፍቅርን፣ ከአለኝታነት በላይ አለኝታነትን ስጧት ብለው በማስነገራቸው ይፋዊ ሰንደቃችን ሆና ለመቀጠል ቻለች፡፡
እንግዲህ በአጭር እንቋጨው እንጅ የአድዋን ትሩፋት እንዲህ በቀላሉ ዘርዝሮ የሚጨረስ ጉዳይ አይደለም፡፡ በመቀጠል የአድዋ ድል ጠላቶች እነማን ናቸው? የሚለውንና ይህንን ቅርስ እንዴት ልንጠብቀው እንችላለን? የሚለውን በአጭር በአጭሩ ዐይተን እንቋጭ ፡፡
የአድዋ ድል ጠላቶች እነማን ናቸው?
የእድለቢስነት ጉዳይ ሆኖ ሀገራችን ኢትዮጵያ ለጠላት የታደለች ሀገር ነች፡፡ በዚህች ሀገር በየትኛውም ሀገር ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ለቁጥር የሚያታክቱ ጦርነቶች ከውጭና ከውስጥ በሚፈጠር ቀውስ ሰበብ አስተናግዳለች፡፡ ይህች ሀገር ካስተናገደችው የጦርነቶች ብዛት አንጻር በታሪኳ በአማካኝ ከ10 ዓመታት ያለፈ የሰላምና የእፎይታ ቆይታ ዓይታ አታውቅም፡፡ ተአምር የሚሆንብኝ ነገር ቢኖር ይህንን ያህል የአውዳሚ ጦርነት ዓይነት ያስተናገደች ሀገር ደብዛዋ አለመጥፋቱ የሥልጣኔና የታሪክ አሻራዎቿም ጥቂቱንም ያህል ቢሆን መቆየት መቻላቸው ነው፡፡ አሁን ላይ አስቀድሞ የነበሩን ጠላቶቻችንም ሆኑ ሌሎች አዳዲስ ቢኖሩ ጥቃታቸውን እየፈጸሙብን ያለው እንደቀድሞው በወረራ ሳይሆን በመሀከላችን ልዩነቶች እንዲፈጠሩ በማድረግና እርስ በእርስ በማናቆር በማፋጀት ሆኗል፡፡ ይሄም ይዞላቸዋል፡፡ አርቀውና አስፍተው ማሰብ የማይችሉ ወገኖቻችን የሀገራችን የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ምንም እንኳን እንከን የለሽ ነበር ማለት ባይቻልም በየትኛውም የዓለም ክፍል ከነበረው እጅግ የተሻለው እንጅ ተመሳሳይ እንኳን እነዳልነበረ፤ በበቂ ምክንያትና አማራጭም በመታጣቱ ለሀገር አንድነትና ህልውና ሲባል አንዳንድ የማያስደስቱን ነገሮች መደረጋቸውን መገንዘብ ማስተዋል የተሳናቸው ደናቁርት ለእነኝህ ጠላቶቻችን መሣሪያ በመሆን የሀገራችንንና የሕዝባችንን ህልውና ገደል አፋፍ ላይ አድርሰውታል፡፡ ዛሬ ላይ በየትኛውም የዓለም ክፍል ላይ ያሉ የባርነትና ጭቆና ቀማሽ የነጻነት ደጋፊና አቀንቃኞች የሚኮሩበትን የሚያከብሩትን የሚያደንቁትን የአድዋን ድልና ያንን ድል ያስገኙልንን አርበኞች እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ ሆነው በጥላቻ የሚመለከቱ መጥፋት መረሳቱን የሚፈልጉ ለዚህም የሚሠሩ ዜጐች ለማየትና ለመስማት ደርሰናል፡፡ መፍትሔው ምንድን ነው ትላላቹ?
ይሄንን ቅርስ እንዴት ልንጠብቀው እንችላለን?
ይሄንንና ሌሎች ቅርሶቻችንን ሀብቶቻችንን ታሪኮቻችንን ልንጠብቃቸው የምንችለው ለነዚህ ሀብቶቻችን አንድ ዓይነት መግባባት ሲኖረን ሀብቶቹ በሚገባ የመጠበቅ እድል ይኖራቸዋል፡፡ አእምሮ ካለን እዚህ አንድ ዓይነት መግባባት ላይ ላንደርስ የምንችልበት እንድም ምክንያት አይኖርም፡፡ ወደራሳችን ወደ ውስጣችን እንመልከት፡፡ እያደረግነው ያለውን ነገር ከመፈጸሙ በፊት የሚገኘውን ትርፍና ኪሳራ እንመዝን፡፡ እንዲህ እንድናደርግ እንድንናቆር እንድንባላ የሚመክሩን የሚገፋፉን የሚደግፍን ሀገራት በታሪካቸው ከእኛ የከፋ የእርስ በእርስ ሰብአዊ መብት ገፈፋ ዝጋብ (record) ያለባቸው ሀገራት ናቸው፡፡ ነገሥታቶቻቸው ሲያርፉ ጠባቂ እያሉ ሰዎችን ከነነፍሳቸው ግራና ቀኝ ይቀብሩ የነበሩ ናቸው፡፡ የሰው ልጆችን ከአራዊት ጋራ እያታገሉና እያስበሉ ለመዝናኛነት ይጠቀሙ የነበሩ ሀገራት ናቸው፡፡ ይህ ተሞክሮ በሀራችን ፈጽሞ ኖሮ አያውቅም፡፡ ዛሬ ላይ እነሱ እንኳን አንድ ዓይነት መግባባት ደርሰው በአንድነት ቆመው ለሀገራችው ጥቅሞች በአንድ የተሰለፉ ሆነዋል፡፡ እነሱ ለዚህ የበቁ እንደነዚህ ያሉ ዘግናኝና ኢሰብአዊ ድርጊቶችንና አስተሳሰቦችን ዓይተን የማናውቀው እኛ ኢትዮጵያዊያን እንዴት አንድ ዓይነት መግባባት ላይ ለመድረስ ያቅተናል? ለሀገርና ለሕዝብ እስካሰብን ጊዜ ድረስ ፈጽሞ አያቅተንም፡፡ ሀገርንና ሕዝብን ጠልተንና ንቀን ባንዳነትን ከመረጥን ግን መቸም ጊዜ ቢሆን ልንግባባና የሰላም አየር ልንተነፍስ አንችልም፡፡
ዘለዓለማዊ ክብር ለአርበኞቻችን!!
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!
amsalugkidan@gmail.com
No comments:
Post a Comment