Wednesday, 19 March 2014

ሰማያዊ ፓርቲ የምርጫ ስነምግባር ደንብ እንደማይፈርም አስታወቀ

በ2002ቱ ጠቅላላ ምርጫ መቃረቢያ ላይ ከ60 ያላነሱ ሀገር አቀፍና ክልል አቀፍ ፓርቲዎችም እንገዛበታለን ብለው ከፈረሙበት በኋላም ሕግ ሆኖ የወጣው የስነ-ምግባር ደንብ ላይ ሰማያዊ ፓርቲ እንደማይፈርም አስታወቀ። የፓርቲው ፕሬዚዳንት ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት ለሰንደቅ እንደተናገሩት፤ የምርጫ ስነ-ምግባር ደንብ በሀገሪቱ ፓርላማ ሕግ ሆኖ እስከወጣ ድረስ ፓርቲው እንደገና የሚፈርምበት ምክንያት የለም ብለዋል።
Yilkal Getnet
ኢህአዴግን ጨምሮ ዘጠኝ ሀገር አቀፍ ፓርቲዎች በሚሳተፉበት የፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ለመግባት እንደ ቅድመ ሁኔታ እየቀረበ ያለው የምርጫ የስነ-ምግባር ደንብ በቅድሚያ ፈረሙ የሚባለውን “እኛ እንደቁምነገር አንቆጥረውም” ሲሉ የመለሱት ኢንጂነሩ ከኢህአዴግም ጋር የሚደረግ ማናቸውም ውይይት በቅድመ ሁኔታ ላይ መመስረት እንደሌለበት ገልፀዋል። በቅድመ ሁኔታ ላይ የተመሠረተ ውይይትም ሆነ የጋራ ምክር ቤት የምክር ቤቱን ነፃነት ጥያቄ ላይ የሚጥል ስለሆነ ለመነጋገርና ለመወያየት የምርጫ ስነ-ምግባር ደንብ ፊርማ እንደቅድመ ሁኔታ መቅረብ የለበትም ብለዋል።
“አሁን ተቋቁሟል የሚባለው የፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት በራሱ ብዙ ችግር ያለበት፣ ኢህአዴግና ደጋፊዎቹ ተሰብስበው የሚቀልዱበት እንጂ ሐቀኛ ሆኖ በነፃነት ውይይት የሚደረግበት ም/ቤት አይደለም” ሲሉ ኢንጂነር ይልቃል ተናግረዋል። ስለሆነም ፓርቲያቸው ለጊዜው በፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት የመሳተፍ ፍላጎት የለውም ብለዋል።
ከኢህአዴግ ጋር ለመነጋገርም ሆነ ተቀራርቦ ለመወያየት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መሆን እንዳለበት የጠቀሱት ኢንጂነሩ ሕጋዊ ፓርቲዎች ሆነን በምርጫውም እንደምንሳተፍ ሰለሚታወቅ ሌላ የተለየ ቅድመ ሁኔታ አያስፈልግም፣ ወደፊርማ የሚያስገባ ሕጋዊ መሠረት የለም ብለዋል።
ኢንጂነር ይልቃል ወደፊርማ የሚያስገባ ሕጋዊ መሠረት የለም ቢሉም፤ የፖለቲካ ፓርቲዎችን የምርጫ ስነ-ምግባር ለመደንገግ በወጣው አዋጅ 662/2002 ዓ.ም አንቀጽ 21(6) እና (7) ላይ አዋጁ እንዲወጣ ተስማምተው በፈረሙ ፓርቲዎች እንደሚቋቋምና የስነ ምግባር ደንቡ ሲቀርፅ በልዩ ልዩ ምክንያት ያልተሳተፉ ሌሎች ፓርቲዎች የጋራ ም/ቤቱ የሚያወጣውን የስምምነት ሰነድ መፈረም እንዳለባቸው ያስገድዳል።
ይሁን እንጂ፤ “የምንፈርመው ነገር የለም” ያሉት ኢንጂነር ይልቃል ፓርቲያቸው በዚህ ውስጥ የመሳተፍ ፍላጎት እንደሌለው አረጋግጠዋል። በምርጫውም የሚኖራቸው ተሳትፎም ደንቡን በመፈረምና አለመፈረም ላይ የተመሠረተ ሳይሆን በአጠቃላይ ገዢው ፓርቲ የፖለቲካውን መድረክ ጨምድዶ በያዘበት ሁኔታ ነው ብለዋል። አሁን ባለው ሁኔታም ምርጫው ፍትሐዊ ይሆናል ብለው እንደማያስቡ ነገር ግን መብቱን የማስከበር የሕዝቡ እንጂ የኢህአዴግ መልካም ፈቃድ አይደለም ሲሉ አስረድተዋል።
blue party
በቅርቡ ኢህአዴግ በመወከል ወደ ፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት አባልነት የተዛወሩት የቀድሞ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ደስታ አስፋው በበኩላቸው ማንኛውም ፓርቲ የፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት ለመግባት በማመልከቻ መጠየቅ እንዳለበት ሀገር አቀፍ ፓርቲ መሆንና በጥር ወር 2002 ዓ.ም የወጣውን የፖለቲካ ፓርቲዎችን የምርጫ ስነ-ምግባር ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 662/2002 ዓ.ም መፈረም አለበት ብለዋል። ፓርቲዎቹ ወደ ፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት ሲመጡ የስነ-ምግባር ደንቡን እንዲፈርሙ የሚያስገድደው በፓርቲዎች ስምምነት ሕግ ሆኖ የወጣው አዋጅ እንጂ ኢህአዴግ አለመሆኑንም አያይዘው ጠቅሰዋል።

No comments:

Post a Comment