Monday, 10 March 2014

በሴቶች የነጻነት ቀን በሴት አባላቶቻችን ላይ የተወሰደውን ህገ ወጥ እርምጃ እናወግዛለን!

March 11, 2014
ከሰማያዊ ፓርቲ የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ
መጋቢት 1 ቀን 2006 ዓ.ም
አዲስ አበባ
‹‹ማርች-8›› የሴቶችን ነጻነትና እኩልት እንዲሁም ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ የሚከበር የሴቶች ቀን እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ይህን በዓል አስመልክቶ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ባለፈው ዕሁድ የካቲት 30/2006 ዓ.ም ሴቶች ብቻ የሚሳተፉበት የጎዳና ላይ ሩጫ ማዘጋጀቱ ይታወቃል፡፡ በዚህ የሐገራችንም ሆነ የዓለም ሴቶች የነጻነት ቀናቸውን በሚያከብሩበት ዕለት እንደሌሎች ሴቶች ሁሉ የሰማያዊ ፓርቲ አባላትም አላማውን ደግፈው በዕለቱ ቀኑን አስመልክቶ በተዘጋጀው ሩጫ ላይ ተሳትፈዋል፡፡Semayawi party statement on arrested female activists
እንደሚታወቀው ታላቁ ሩጫ በተለያየ ጊዜ በሚካሄድበት ወቅት ተሳታፊዎች በሐገራቸው የሰፈነውን ጭቆና በመቃወም ሀሳብን የመግለጽ ህገ መንግስታዊ መብታቸውን በመጠቀም ድምጻቸውን የሚያሰሙበት በመሆኑ ‹‹የብሶት መግለጫ›› መድረክ እስከመባል ደርሷል፡፡ ልክ እንዳለፉት ጊዜያት ሁሉ በእሁዱ የጎዳና ሩጫም በርካታ የሩጫው ተሳታፊዎች ይህን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ የመጣውን ጭቆና በመቃወም ድምጻቸውን ሊያሰሙበት ችለዋል፡፡
በዚህ በሴቶች የነጻነት ቀን በስርዓቱ ላይ የሚነሱ ብሶቶችን ካሰሙት ተሳታፊዎች ውስጥ የሰማያዊ ፓርቲ አባላት የሚገኙበት ሲሆን፣ በተለየ መልኩ በእነዚህ አባላቶቻችን ላይ ያነጣጠረ የአፈሳ እርምጃ ተወስዶባቸዋል፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ እንደዚህ አይነት ህዝባዊ መድረኮችን ላይ ብቻ ሳይሆን ሁሌም ህዝብ ላይ የሚደርሰውን በደል በማጋለጥ ለህዝብ መብት እና ለአገራችን ብሄራዊ ጥቅም በመቆሙ በገዥው ፓርቲ ተደጋጋሚ ህገ ወጥ እርምጃ ሲወሰድበት ቆይቷል፡፡ በትናንትናው ዕለት የተደረገውም ከዚሁ ፓርቲው ለህዝብና ለአገር መቆሙን ተከትሎ እየደረሰበት ያለው የከፋ የጭቆና አካል ነው፡፡
ምንም እንኳ ይህ የህወሓት/ኢህአዴግ ህገ ወጥ እርምጃ አዲስ ባይሆንም በሴቶች ነጻነት ቀን በአባላቶቻችን ላይ የተወሰደው ህገ ወጥ እርምጃ አገዛዙ በህገ መንግስቱም ሆነ በሌሎች ህጎች ለሴቶች መብት መከበር የደነገጋቸው አንቀጾች ከወረቀት ያለፉ እንዳልሆኑ በተጨባጭ ያሳየ ምሳሌ ነው፡፡ ከምንም በላይ አባላቶቻችን የታሰሩበት ምክንያት ‹‹የጣይቱ ልጅ ነን፣ የምኒልክ ልጅ ነን›› ማለታቸው እንደሆነ በመርማሪ ፖሊስ የተገለጸላቸው መሆኑ ነው፡፡
ይህም ህወሓት/ኢህአዴግ ምን ያህል ከታሪክ ጋር የተጣላ መሆኑን ከማሳየቱም በተጨማሪ አባላቶቻችን ለማሰር አሳፋሪ የሆኑ ምክንያቶች እየፈለገ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ ይህኛውን እርምጃ የተለየ የሚያደርገው ሰማያዊ ፓርቲ በመላው አገሪቱ መዋቅሩን እያደራጀና ህዝብን ከጎኑ እያሰለፈ ባለበት ወቅት መሆኑ፤ የህዝብ ድጋፍ የሌለው ገዥው ፓርቲ በሰበብ አስባቡ ሰማያዊ ፓርቲን ከወዲሁ ለማዳከም የወሰደው ነው፡፡
በተለይ የምርጫ ወቅት እየቀረበ መሆኑን ተከትሎ ይህን ህገ ወጥ እርምጃ መውሰዱ አሁንም ቢሆን የአገራችን የፖለቲካ ምህዳር ምን ያህል እየጠበበ እንደሄደ ያሳያል፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ መቼም ቢሆን ይህንና መሰል የአገዛዙን አፈናዎች አጥብቆ የሚያወግዛቸውና የሚታገላቸው መሆኑን እየገለጸ በሴቶች የነጻነት ቀን ያላአግባብ የታሰሩ አባላቶቻችን በአስቸኳይ እንዲፈቱ ይጠይቃል፡፡ ኢትዮጵያውያንና መላው የዓለም ማህበረሰብ ይህን ህገ ወጥ እርምጃ ተመልክቶ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጎን እንዲቆም ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!!!
መጋቢት 1 ቀን 2006 ዓ.ም
አዲስ አበባ

No comments:

Post a Comment