Wednesday 2 April 2014

የአዲስ አበባ ህዝብ እሪታውን እንዲቀላቀል በድጋሚ ተጠየቀ!! ህግን ተላልፈን ከህገወጦች ጋር አንተባበርም! ከአንድነት የአዲስ አበባ ም/ቤት የተሰጠ መግለጫ

የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ የአዲስ አበባ ስራ አስፈጻሚ በዛሬው ዕለት በፓርቲው ዋና ጽ/ቤት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ‹‹በህገ ወጥ መንገድ የሚቀለበስ ሰላማዊ የትግል ስልት ባለመኖሩ የአዲስ አበባ ህዝብ ለቀረበለት የሰላማዊ ሰልፍ ጥሪ ምላሹን እንዲሰጥ በአክብሮት እንጠይቃለን››ብሏል፡፡
የሰላማዊ ሰልፍ ማሳወቂያ ክፍል ህገ ወጥ ደብዳቤ በመጻፍ ሰልፉን ማከናወን አትችሉም ማለቱ ከህግ በላይ ነኝ የሚል መንፈስ እንዳለው እንደሚያሳይ የገለጸው ፓርቲው በአገሪቱ ህገ መንግስቱንና ሌሎች አዋጆችን የማስከበር ስራ የሚሰሩ ተቋማትም ለህግ መከበር ያላቸውን ቁርጠኝነት እንዲያሳዩ ጠይቋል፡፡
‹‹የእሪታ ቀን›› በሚል መሪ ቃል መጋቢት 28 ቀን 2006 ዓ.ም በአዲስ አበባ እንዲደረግ ቀጠሮ የተያዘለት ሰላማዊ ሰልፍ በተያዘለት ቀጠሮ መሰረት እንደሚደረግም ፓርቲው በመግለጫው አስታውቋል፡፡
ህግን ተላልፈን ከህገወጦች ጋር አንተባበርም!
ከአንድነት የአዲስ አበባ ም/ቤት የተሰጠ መግለጫ
የእሪታ ቀን በሚል መሪቃል በመዲናችን አዲስ አበባ ያሉ ማህበራዊና ኢኮ ኖሚያዉ ቀውሶችን አስመልክቶ በተለይም ከተማዋን ወደ ማህበራዊ ቀውስ እየመሯት የሆኑትን የውሃ፣ መብራት፣ ስልክ፣ የትራንስፖርት ችግር እንዲቀረፍ ህዝቡ የተቃውሞ ድምፁን እንዲያሰማ መጋቢት 28 ቀን 2ዐዐ6 ዓም ለማካሄድ ያቀደውን ሕዝባዊ ሠላማዊ ሠልፍ አስመልክቶ በህዝብ መገናኛ ብዙሃን ይፋ ካደረግንበት ቀን ጀምሮ የሚጠበቅብንን ህጋዊ የማሣወቅ ሥራዎችን ስንሠራ የቆየን መሆኑና መድረስ ለሚገባው አካል ሁሉ አካል ሁሉ በተገቢው ሁኔታ ማሳወቃችን ይታወቃል፡፡ ነገር ግን ጥሪው ለሕዝብ ይፋ ከተደረገበት ጊዜ ጀምሮ የሚመለከተው የሠላማዊ ሠልፍና ስብሰባ ማሳወቂያ ክፍል በህግ የተቋቋመበትን ኃላፊነት በመዘንጋት ለጠየቅነው ጥያቄ ቀጥተኛ መልስ ከመስጠት ይልቅ ህግ በመተላለፍ ክልከላ አዘል ደብዳበ ልኳል፡፡ ሆኖም የአንድነት የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት በትላንትናው እለት ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ ለሠላማዊ ሠልፍ ማሳወቂያ ክፍል የላከው ደብዳቤ በአዋጅ ከተደነገገ ህግ ጋር የሚጣረስና የዜጎችን መብት የሚያፍን መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ የአንድነት ምክር ቤት ግንዛቤ በመያዝ ከዚህ የሚከተለውን የአቋም መግለጫ በማውጣት ለመገናኛ ብዙሃን እንዲተላለፍ ወስኗል፡፡
የአቋም መግለጫው የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር የሠላማዊ ሠልፍና የፖለቲካ ስብሰባ ማሳወቂያ ክፍል ፓርቲያችን መጋቢት 15 ቀን 2ዐዐ6 ዓም ላስገባለት የሠላማዊ ሠልፍ እውቅና መጠየቂያ ደብዳቤ መጋቢት 17 ቀን 2ዐዐ6 ዓም በሠጠው ምላሽ የሠላማዊ ሠልፍ ጥያቄውን አለመቀበሉን ማሳታወቁንና ለዚህ ደብዳቤ የላክንለትን መልስ አልቀበልም በማለት የወጣ ነው፡፡
1. የሠላማዊ ሠልፍ ማሳወቂያ ክፍሉ ለሚቀርብለት የሠላማዊ ሠልፍ የእውቅና ጥያቄ ህገ መንገሥቱንና አዋጅን በሚቃረን መልኩ ምላሽ መስጠት የማይችል ቢሆንም በማን አለብኝነት አዋጁን በጣሰ መልኩ ምላሽ መስጠቱን አልተቀበልነውም፡፡
2. ህዝብን በተለይም ህገ መንግሥታዊ ድንጋጌዎች እንዲያገለግል ኃላፊነት የተሰጠው አካል ህጋዊ እውቅና ካገኘ ተፎካካሪ ፓርቲ የሚቀርብለትን ደብዳቤ አልቀበልም ማለቱም ህገ ወጥ ተግባር በመሆኑ ግለሰቡ በመደበኛ ፍርድ ቤት ክስ እንዲመሰረትባቸው ወስነናል፡፡
3. ለህግና ህገ መንግሥታዊነት ጥብቅና ለመቆም ቃል የገቡት የፌዴራልና የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊሶች ህግን አክብሮ እየተንቀሳቀሰ ከሚገኘው ፓርቲያችን ጎን እንዲቆሙ እንጠይቃለን፡፡
4. አዋጁን ያፀደቀው ፖርላማ ለሠላማዊ ሠልፍ ጥያቄያችን የተሰጠን ምላሽ ህገ ወጥ መሆኑን እንዲመለከት አባሪ በማድረግ ለላክንለት ደበዳቤ አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጠን እንጠይቃለን፡፡
5. ለመጋቢት 28 ቀን 2ዐዐ6 ዓም የጠራነው ‹‹የእሪታ ቀን›› ሠላማዊ ሠልፍ ህጋዊ መስመሩን ተከትሎ የቀረበ በመሆኑና በህገ ወጥ አሰራር ሊታጠፍ ስለማይችል ምክር ቤታችን ሙሉ እውቅና ሰጥቶታል፡፡
6. በሠላማዊ ሠልፍ ለሚደርስ ማናቸውም አይነት ኪሳራዎች፣ ጉዳቶችና መጉላላቶች ተጠያቂው ህጋዊ ቢሮ ይዞ ህገ ወጥ አሰራር የሚከተለው አካል መሆኑን ለማሳወቅ እንወዳለን፡፡
7. አሁን የገጠመን የመሠረታዊ አገልግሎቶች ችግር የውሃ፣ የመብራት፣ የስልክ ችግር የመኖርና ያለመኖር ጥያቄ ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ህዝብ የገጠመውን ስቃይ እሪ በማለት እንዲያሰማ አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) መድረኩን ያዘጋጀ ስለሆነ ጥያቄያችሁን ለመንግሥት እንድታስተላልፉ የአዲስ አበባ አንድነት ም/ቤት ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡
ስለሆነም በአዲስ አበባ ከተማ የሚደረገው የቅስቀሳ ስራ ከዛሬ መጋቢት 24 ቀን 2ዐዐ6 ዓም ጀምሮ በይፋ የሚጀመር መሆኑን እየገለጽን፤ በዚህ የዘመቻ ስራ ላይ መንግሥት አስፈላጊውን ትብብር እንዱያደርግ ከወዲሁ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡ ከዚህ ውጭ በቅስቀሳው ስራላይ ለሚገጥመን ህገወጥ ችግር መንግሥት እንደሚወስድ እንገልፃለን፡፡
ድል የህዝብ ነው!
መጋቢት 24 ቀን 2ዐዐ6 ዓም
አዲስ አበባ10157340_613396448745293_925372809_n

No comments:

Post a Comment