Saturday 7 June 2014

ሪፖርተር – ግንቦትና የማያቆመው የባህር በር ጥያቄ በኢትዮጵያ – በመንግሥቱ መስፍን

ወርኃ ግንቦት የቀድሞ ወታደራዊ አገዛዝ ከሥልጣን የወረደበትና አሁን አገሪቱን በመምራት ላይ የሚገኘው መንግሥት ወደ ሥልጣን የመጣበት በመሆኑ በየዓመቱ መታወስ ከጀመረ 23 ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡
በእግርጥ በግንቦት ወር 1981 ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያምን ከሥልጣን ለማወረድ ያሴሩ ከፍተኛ መኰንኖች የመፈንቅለ መንግሥት ያደረጉበት ጊዜም ነው፡፡ በዚሁ ወር በዓመቱ በጦር ፍርድ ቤት ሲታይ የከረመው የጄኔራሎቹ የመንግሥት ግልበጣ ወንጀል ‹‹መቋጫ›› አግኝቶ ሞት ተፈርዶባቸው በጭካኔ የተፈጸመበት ጊዜ መሆኑም አይዘነጋም፡፡ ለነገሩ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ቢሆኑም ሲፎክሩና ‹‹አይዞህ ግፋ›› ሲሉ ከርመው የኮበለሉት በዚሁ ወር በዕለተ 13 አይደል?
የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ግን የግንቦትን ገድል መዘከር ወይም አገሪቱ ከግንቦት 1983 ዓ.ም. የሥርዓት ለውጥ ወዲህ ያስገኘችውን ውጤት መዘከር አይደለም፡፡ ይልቁንም በዚሁ ወቅት ኢትዮጵያ የባህር በር አልባ መሆኗን ደጋግመው የሚሞግቱ ወገኖችን ድምፅ ለማስተጋባት ይሞክራል፡፡ ጉዳዩ የኤርትራና የኢትዮጵያ መንግሥታት የተሟላ ሕዝበ ውሳኔ ባይባልም የፖለቲካ ውሳኔ የፈጠረው ክስተት ቢሆንም፣ ፋይሉን እንደተዘጋ መቁጠር እንደማይገባም ለማሳሰብ ነው፡፡
ለዘመናት የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥታት የድንበራቸውን ጫፍ ቀይ ባህር አድርገው፣ በወደቡ ሲጠቀሙ በኖሩበት ሀብት ይቅርና ግብፅና ሱዳን ለሺሕ ዓመታት ሲገለገሉበት የኖሩትን ታላቁ ወንዝ እንኳን ዛሬ ለሌላ አዲስ ጥቅም እያዘጋጀነው አይደል?! ስለዚህ የኢትዮጵያን የባህር በር ጥያቄ ማንሳትም ሆነ ጮክ ብለው የሚናገሩ ዜጐችን ማዳመጥ የቀጣዩ ትውልድ የቤት ሥራ መሆኑ የሚቀር አይመስልም፡፡
የዓለም ሁለት ሦስተኛው ክፍል ውኃ (ውቅያኖስ) ከመሆኑ አንፃር በምድር ላይ የሚካሄዱ ብዙዎች ጉዞዎች የሚካሄዱት በባህር ላይ ነው፡፡ በተለይ ግዙፍ ምርቶችና ጥሬ ዕቃዎች፣ የግዙፍ ፕሮጀክት ግብዓቶች፣ የቴክኖሎጂ ዘመን አመጣሽና የጦር መሣሪያን የመሰሉ ከፍተኛ ጭነቶች ካለባህር ትራንስፖርት የአገሮችን ፍላጐት ለማሟላት አያስችሉም፡፡ የባህር ትራንስፖርት ሲታሰብ ደግሞ የወደብ ጉዳይ በቀዳሚነት የሚመጣና ወሳኙ ከፍታ ነጥብ ነው፡፡
ዛሬ ኢትዮጵያን በመሰለች ሰፊ አምራችና ሸማች ኃይል (በአጭር ጊዜ 100 ሚሊዮን የሚደርስ) ያላት አገር፣ ሰፊ መሬትና የመልማት አቅም ያላት ምድር ያለወደብ መኖር እንደሌለባት የሚከራከሩ አሉ፡፡ ይኼ ከኢኮኖሚ ፋይዳው አንፃር ሲታይ ብቻ ሳይሆን ለአገር ደኅንነት ዋስትናም ቢሆን እንደ ምሥራቅ አፍሪካ ላለ ቀጣና ወደብ ያለውን ወሳኝ አቅም ይጠቅሳሉ፡፡
‹‹አሰብ የማን ናት?›› በሚል የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄን የዳሰሱት ዶ/ር ያዕቆብ ኃይለ ማርያም፣ ‹‹የኢትዮጵያ የወጪና የገቢ ንግድ የሚካሄደው አብዛኛው በባህር ላይ ሲሆን ኢትዮጵያ የኬንያ፣ የሱዳን፣ የጂቡቲ አንዳንዴም የሶማሊያ ወደቦችን ትጠቀማለች፡፡ ሆኖም የኢትዮጵያ ወደ ውጭ የምትልከውና ከውጭ የምታስገባው ጠቅላላ ንግድ 90 በመቶ በጂቡቲ ወደብ ነው፤›› ብለው አስቀምጠዋል፡፡ በእርግጥም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ፣ በመጠጥ ውኃ አቅርቦትና ጫትና ቡናን በመሳሰሉ የግብርና ምርቶች ግብይት ከጂቡቲ ጋር የገበያ ትስስሩ የተሻሻለ ቢመስልም፣ በየዓመቱ ከሦስት ቢሊዮን ዶላር በላይ ካፒታል ለጂቡቲ ወደብ ኪራይ የምትከፍል ብቸኛ አገር ኢትዮጵያ ነች፡፡
አሁን ጥያቄው ለምን ለወደብ 60 ቢሊዮን ብር በዓመት ከፈልን ወይም ለምን በጂቡቲ ወደብ ተጠቀምን አይደለም፡፡ ለምን የአሰብን ወደብ የባለቤትነት ጥያቄ ወደ ጐን ገፍተን እንዳላየና እንዳልሰማ በክርክር ነጥቡ ላይ አፈር እንደፋበታለን የሚለው ተጠየቅ ነው፡፡ የታሪክ ድርሳናት እንደሚያስረዱት ከ100 እስከ 150 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ የኢትዮጵያ የባህር በር አዱሊስ መሆኑ ተገልጿል፡፡ እንዲያውም የወቅቱ ንጉሥ አፄ ካሌብ ባህር ተሻግሮ የመንና ደቡብ ዓረቢያን ይቆጣጠር እንደነበር “Christian Photography” የተሰኘ መጽሐፍ ላይ ተጠቅሷል፡፡
ከአፄ ዘርዓ ያዕቆብ (1434 እስከ 1468) ጀምሮ በተለያዩ ጊዜያት አገሪቱ የባህር በር እንደነበራት፣ በዘመነ መሳፍንት የማዕከላዊ መንግሥት መዳከም ምክንያት የውጭ ወራሪ ኃይል የባህር በር ይዞታዋ መዳከሙንም ከታሪክ እናነባለን፡፡ ያም ሆኖ በአፄ ባካፋ፣ በአፄ ኢያሱ፣ በአፄ ኢዮአስ (1720 እስከ 1770) ኢትዮጵያ በቀይ ባህር የተጠናከረ ይዞታ እንደነበራት ዶ/ር ተወልደ ትኩዕ ‹‹የኢትዮጵያ አንድነትና ኢጣሊያ›› በሚለው መጽሐፍ ዘርዝረውታል፡፡
እነዚህን የታሪክ እውነቶችን የዘነጉ ወይም ያልፈለጉ አንዳንድ ጥራዝ ነጠቆች ግን የኢትዮጵያ ታሪክ (በተለይም የሰሜን ኢትዮጵያን) እውነተኛ ዕድሜ ሊያሳጥሩት ይሻሉ፡፡ ‹‹ኤርትራ›› የሚለው ስም በኢጣሊያ ወራሪ ኃይል በ1890 ገደማ መውጣቱ እየተዘነጋም፣ የሁለት ዓለም ሰዎች ያህል ተለጥጦ ይነገራል፡፡ ምንም ተባለ ምን የምፅዋ (ሰሜን ኤርትራ) ቢቀር የአሰብ ወደብ የኢትዮጵያ ንብረት መሆን እስከ ደርግ መውደቂያ ባለው 40 ዓመት ባለቤትነት ብቻ ሳይሆን በታሪክ፣ በጂኦግራፊና በሕግ የኢትዮጵያ ሀብት መሆኑ ነው በብዙዎች የሚነገረው፡፡
እዚህ ላይ አንድ የማይካደው እውነት ኢሕአዴግ መራሹ የአገሪቱ መንግሥት ከኤርትራ መንግሥት (ሻዕቢያ) ጋር በነበረው የበረሃ ስምምነት ወደ ወደብ ጥያቄም ሆነ በአንድ ላይ እነኑር ውዝግብ ላለመግባት የወሰነ መሆኑ ነው፡፡ በእርግጥም በሥርዓቱ ውስጥ በነባር ታጋይነት የሚጠቀሱት እነአብርሃም ያየህና አረጋዊ በርሄ የመሰሉ ታጋዮች አንዱ ልዩነታቸው ከኤርትራ በተለይም ከአሰብ ወደብ ጋር በተያያዘ ኢሕአዴግ በያዘው ለዘብተኛ አቋም ነው፡፡ በ1993 ዓ.ም. በሕወሓት ውስጥ በተፈጠረው ልዩነት ምክንያት ከአየር ኃይል አዛዥነት ኃላፊነታቸው የተነሱት ሜጀር ጄኔራል አበበ ተክለ ሃይማኖት “Ethiopia’s Sovereign Right of Access to the Sea under International Law” የሚለው ጥናታቸው፣ ኢሕአዴግ በአሰብ ጉዳይ ላይ የያዘውን አቋም ክፉኛ መተቸታቸው ፋይሉ ገና ያልተዘጋና የቀጣዩ ትውልድ የቤት ሥራ መሆኑን ያመለክታል፡፡
ቀደም ሲል የተጠቀሱት ዶ/ር ያዕቆብን ጨምሮ በርካታ የታሪክ ምሁራን በአሰብ ወደብ የኢትዮጵያን ንብረትነት ጉዳይ ዛሬም ድረስ በርካታ መጻሕፍትና ጥናቶችን ለንባብ አብቅተዋል፡፡ ብዙዎቹ ሰነዶች የሚመዟቸው የሕግ፣ የታሪክና የጂኦግራፊ እውነታዎች ታዲያ እጅግ በብዛት ስለጉዳዩ መናገር ከማይወደው የኢትዮጵያ መንግሥት ሐሳብ በላይ ሚዛን የሚደፉ ናቸው፡፡ ምናልባት ያልተዘጋውና ለጊዜው የተጋረደው የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ዝምታ ውስጥ ያለው በሽግግር መንግሥቱ ምሥረታ ወቅት ፕሮፌሰር አሥራት ወልደየስ ላቀረቡት አሰብ የኢትዮጵያ ይዞታ ነች ጥያቄ፣ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቄ የሰጡት መልስ ሊሆን ይችላል፡፡ ‹‹ታሪክና ሕግ የሚሉትን ዝባዝንኬ ለትምህርት ቤት ክፍል ይተውት፡፡ ይህ ፖለቲካዊ ጉዳይ በጦር ሜዳ ተፈትቷል፤›› ነበር ያሉት፡፡
‹‹ኢትዮጵያ በራሷ የሚተዳደርና የራሷ የሆነ ወደብ ያስፈልጋታል፤›› የሚሉ ተከራካሪዎች፣ የአሰብን ጉዳይ ደጋግመው ቢያነሱም መንግሥት እምብዛም ትኩረት የሰጠው አይመስልም፡፡ ይልቁንም በቀጣናው ከጐረቤት አገሮች ጋር የተጀመረው የኢኮኖሚ ትስስር በሁሉም አቅጣጫ ወደቦችን ለመጠቀም እንደሚያስችል ያስረዳል፡፡ ምን ጊዜም ‹‹ሰጥቶ መቀበል›› ላይ የተመሠረተውና በጋራ ዕድገት ላይ የሚገነባው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ እስከተከተልን ድረስ ምንም አንሆንም የሚል መስሏል፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የድኅረ ምረቃ ዕጩ ተመራቂው ፍሰሐ (የአባታቸው ስም አልተጠቀሰም) ግን ከዚህ የተለየ ሐሳብ ያንፀባርቃሉ፡፡ ‹‹ኢሕአዴግ በበረሃ ስምምነቱ ለተከታታይ ዓመታት የቀጠለውን የእርስ በርስ ጦርነትና ስደትን ባለመፈለግም ሆነ በተለየ ምክንያት የባህር በር ጥያቄውን ከፊት ለፊት ማምጣት አልፈለገም፡፡ በመሠረቱ በወቅቱ የተዳከመውንና ብዝኃነት ያለውን ሕዝብ ማስተዳደርና ኢትዮጵያ እንደ አገር እንድትቀጥል ቅድሚያ መስጠቱ ተገቢ ይሆናል፤›› ይላሉ፡፡ አስገራሚው ነገር ግን ከኤርትራ ግጭት በኋላ በድንበር ማካለሉ ዓለም አቀፍ ድርድር ላይ እንኳን የአሰብን ጉዳይ ‹‹ውሾን ያነሳ ውሾ!›› እንዲሉ በቸልታ መታለፉ እንደሆነም ምሁሩ ያስረዳሉ፡፡
ለአንድ አገር ዕድገትም ሆነ ድህነት የወደብ ባለቤትነት አስፈላጊነት በሳይንስም የተረጋገጠ ነው፡፡ ዶ/ር ያዕቆብ በመጽሐፋቸው፣ ‹‹በ2008 ዓ.ም. በዓለም 44 ወደብ አልባ አገሮች ሲኖሩ ከእነዚህ ውስጥ 31 ያህሉ ደሃ ሲሆኑ፣ አሥራ ሦስቱ ደግሞ የደሃ ደሃ የሚባሉ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ እነዚህ ደሃ አገሮችም ሁሉም በአፍሪካ ውስጥ የሚገኙ ናቸው፡፡ እነዚህ ወደብ አልባ ደሃ አገሮች ወደ ውጭ የሚልኳቸው ምርቶቻቸው በአብዛኛው በአንድና በሁለት ሰብሎች ወይም በአንድና በሁለት የኢንዱስትሪ ውጤቶች ወይም ጥሬ ዕቃ የተወሰኑ ናቸው፡፡ ስለሆነም ከድህነተ የመላቀቅ ዕድላቸው በጣም የመነመነ መሆኑን ሊቃውንት ይናገራሉ፤›› በማለት የመጨረሻዎቹ ደሃ ቢሊዮኖች (The Bottom Billions) በሚለው መጽሐፋቸው ፖል ኮልየር የጻፉትን ጠቅሰዋል፡፡
ምሁሩ፣ ‹‹በዓለም በሕዝብ ቁጥር ትልቋ ወደብ አልባ አገር ሆነች፡፡ በተጨማሪም በኢትዮጵያ ድንበርና በባህሩ መካከል ያለው 60 ኪሎ ሜትር በዓለም በአንድ አገርና በባህሩ ያለው ርቀት በጣም አጭሩ ለመሆን በቃ፤›› ሲሉ በገጽ 46 ላይ ፀፀታቸውን መግለጻቸውም ይታያል፡፡
ዕጩ ተመራቂ ፍሰሐም የመጽሐፉን ሐሳብ ተጋርተው፣ ‹‹ወደብ አልባ አገሮች ከድህነት ሊወጡ ይችላሉ፡፡ በምንም ተዓምር ግን ብልፅግናን ለማረጋገጥ መቸገራቸው አይቀርም፤›› ይላሉ፡፡ በተለይ የነብር ኢኮኖሚ ዕድገት (Tiger Economic Development) እንዳስመዘገቡ የሚነገርላቸው እነኮሪያ፣ ታይዋን፣ ቻይና፣ ጃፓን ያሉት ከአንድም አራትና አምስት ግዙፍ ወደቦችና በርካታ የባህር በር ባለቤቶች ናቸው፡፡ እየገነኑ የመጡት የዓለም ኢኮኖሚ ፈጣን የሚባሉት ብራዚል፣ ቻይና፣ ህንድ፣ ሩሲያና ደቡብ አፍሪካ ዋነኛ የዓለም የወደብ ባለቤቶች መሆናቸው ሲታይ የኢትዮጵያን የመጪው ጊዜ ፈተና ያመለክታል፡፡
ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት ኢትዮጵያን ለዘመናት ሊያስተዳድርና ሊመራ አይችልም፡፡ በተለያዩ ትውልዶች ውስጥ በዲሞክራሲያዊ ምርጫ ሕዝቡ ዕውቅና እየሰጠው ይምራ ቢባል እንኳን፣ በአዳዲሶች ትውልድ የተዋቀረ ድርጅት መሆኑ ተፈጥሯዊ ነው፡፡ ኢሕአዴግ በዲሞክራሲያዊና በሰላማዊ ምርጫ ሥልጣኑን ቢያስረክብም፣ በአሁኑ ወቅት በተቃዋሚነት የተሠለፉ ብዙዎቹ ኃይሎች የባህር በር ጥያቄን እንደ ኢሕአዴግ ከጠረጴዛ ሥር እንደማያስቀምጡት እየገለጹ ነው፡፡ እዚህ ላይ ሁሌም መረሳት የሌለበት የባህር በር ጥያቄ ሲነሳ ሕጋዊ መንገዶች ከምንም ነገር በላይ ቀዳሚ መሆን አለባቸው፡፡ ኢትዮጵያዊ ታሪካዊ፣ ጂኦግራፊያዊና ሕጋዊ መብት አላት ሲባል የጦረኝነት አባዜ ሊወገድ ይገባል፡፡ ሕጋዊውን መብት በሕጋዊ መንገድ ለማስከበር መነሳት ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል፡፡
ሲጠቃለል ግንቦትን ስናስብ የኢትዮጵያ ሕዝብና የአገሪቱ መልካም ገጽታዎች በበጐ የሚጠቀሱበት አዲስ ጊዜ ተፈጥሯል፡፡ ነገር ግን የባህር በር ጥያቄን የመሰሉ የብሔራዊ አጀንዳ ቀዳሚ ጉዳዮች ሊዘነጉ የሚገባቸው አይደሉም፡፡ ይህ ሲባል ግን በወረራና የሌሎችን ሕጋዊ ጥቅም በመግፈፍ ሳይሆን፣ ሕጋዊና ታሪካዊ እንዲሁም ጂኦግራፊያዊ መብቶችን በመጠቀም ሊሆን ይገባል፡፡ ይህ ደግሞ የትውልዱ አደራ ነው፡፡ መሆንም አለበት፡፡

No comments:

Post a Comment