Wednesday, 1 October 2014

የኢትዮጵያ ኢምባሲ ሰራተኛው እጣ ፋንታ አልታወቀም

መስከረም ፳(ሃያ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ትናንት ሰኞ በኦጋዴንና በጋምቤላ በተጨፈጨፉ ኢትዮጵያውያን ዙሪያ በአሜሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ተወካዮችን ለማነጋገር በኢምባሲው አካባቢ በተገኙት  ኢትዮጵያውያን ላይ አንድ የስልጣን ደረጃው ያልታወቀ ሰለሞን
ወይም በበረሃ ስሙ ወዲ ወይኒ የተባለ ግለሰብ ጥይቶችን በመተኮሱ የኢትዮጵያውያንንና አለማቀፍ የመገናኛ ብዙሃንን ትኩረት ስቧል።
አለማቀፍ እውቅና ያላቸው ሮይተርስ እና  ዋሽንግተን ፖስት የመሳሰሉ የዜና አውታሮች ዜናውን በድረገጾቻቸው ይዘው የወጡ ሲሆን፣ የከተማዋ ፖሊስ ተኳሹን ግለሰብ በቁጥጥር ስር ማዋሉን የፖሊስን ምንጮች ዋቢ በማድረግ ዘግበዋል። ይሁን እንጅ ግለሰቡ ይታሰር
አይታሰር እስካሁን የታወቀ ነገር የለም። አንድ ስሙ ያልተጠቀሰ በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ውስጥ የሚሰራ ባለስልጣን፣ ተኳሹ ግለሰብ የዲፕሎማቲክ ከለላ ያለው በመሆኑ እንዳልታሰረ ገልጸዋል። የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት እስካሁን ያወጣው
መግለጫ የለም። የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤትም በጉዳዩ ዙሪያ ያወጣው ይፋዊ የሆነ መግለጫ የለም።
የኢምባሲው ሰራተኛ ያሳየው ድርጊት በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የጸጥታ ሃይሎች ባህሪ እንደሚያንጸባርቅ የተለያዩ አስተያየቶች በመገናኛ ብዙሃን እየቀረቡ ነው። ኢትዮጵያውያን  ተቃዋሚዎች የጦር መሳሪያ ሳይዙ ሰላማዊ በሆነ መንገድ እየተቃወሙ መታየታቸው
በስርአቱ ውስጥ የሚያገለግሉ የጸጥታ ሃይሎች ባህሪ በውጭ አገራትም በተመሳሳይ መንገድ እየተንጸባረ መሆኑን እንደሚያሳይ አስተያየት ሰጪዎች በማህበራዊ ድረገጾች ጽፈዋል።

No comments:

Post a Comment