Monday, 24 November 2014

ሱዳን 2 ሺ ኢትዮጵያውያንን በጉበትና በኤድስ ተጠቅተዋል በሚል ልታባርር ነው

ኀዳር ፲፭(አስራ አምስትቀን ፳፻፯ / ኢሳት ዜና :-በሱዳን የሰሜን ግዛት በምትገኘዋ ኤል ዳባ የሚኖሩ ከ2 ሺ በላይ ኢትዮጵያውያን ተጠርንፈው ወደ ካርቱም የተላኩ ሲሆን፣ የከተማዋ ባላስልጣናት ኢትዮጵያውያኑ ሄፒታይተስ ሲ የተባለው የጉበት በሽታና የኤድስ ቫይረስ ስላለባቸው መላካቸውን ገልጸዋል።
የኤል ዳባ ፖሊስ ኮሚሽነር  ኢስላም አብደል ራህማን ለሱዳን ትሪቢዩን እንደተናገሩት የግዛቱ ባለስልጣናት በውጭ አገር ዜጎች  ላይ በድንገት ባደረጉት የህክምና ምርምራ ከ15 ኢትዮጵያውያን መካከል 6ቱ ሄፒታይተስ ሲ የሚባለው የጉበት በሽታ እንደተገኘባቸው፣ እንዲሁም በድጋሜ ከተመረመሩ 54 ኢትዮጵያውያን መካከል በ5 ቱ ላይ በሽታው መገኘቱን ተናግረዋል። በምርምራው ሁለት ኢትዮጵያኖች በኤች አይ ቪ ቫይረስ መያዛቸው በዘገባው ተገልጿል።
ይህን ተከትሎ ፖሊስ በግዛቱ የሚኖሩ 2 ሺ ኢትዮጵያውያንን በአንድ ላይ በመጠረዝ ካርቱም ለሚገኘው ለፓስፖርትና ኢምግሬሽን መስሪያ ቤት አስረክበዋል። በአሁኑ ሰአት በግዛቱ ውስጥ 10 የውጭ አገር ዜጎች ብቻ እንደሚገኙ ጋዜጣው አክሎ ዘግቧል።
ድርጊቱ ፍጹም ዘረኝነት የተሞላበትና ኢትዮጵያውያን ከመቼውም ጊዜ በላይ የተዋረዱ ዜጎች መሆናቸውን እንደሚያሳይ ሱዳን የሚገኙ ስደተኞች ገልጸዋል። በሌሎች አገር ዜጎች ላይ የማይፈጸም ድርጊት በኢትዮጵያውያን ላይ ይፈጸማል የሚሉት ነዋሪዎች፣ ኤች አይ ቪ ኤድስም ሆነ የጉበት በሽታ በየትኛውም አገር ተሰዶ መኖርን እንደማይከለክል ይገልጻሉ። በሽታው ሰበብ መሆኑን የሚገለጹት ስደተኞች፣ የኢትዮጵያ መንግስት ሱዳን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከታዋሚዎች ጋር ያብራሉ በሚል ስጋት ከሱዳን መንግስት ጋር ያቀነባበረው ድርጊት መሆኑን ይገልጻሉ።
ሱዳን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢትዮጵያውያንን በሰበብ አስባቡ ከአገሯ እያስወጣች ነው።

No comments:

Post a Comment