Friday, 2 January 2015

መልዕክት ከቂሊንጦ እስር ቤት! አብርሃ ደስታ

January 2, 2015
በነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር
‹‹እንደ ኢህአዴግ ያለ አሸባሪ የለም›› አብርሃ ደስታ
እዚህ እስር ቤት ውስጥ በሽብር ስም የገባ ሰው በፈጠራ ወንጀል እንደገባ ነው የሚታመነው፡፡ ስለዚህ የሽበር ክስ ተመስርቶባቸው የታሰሩትን ሰዎች ማንም ወንጀለኛ አድርጎ አይመለከታቸውም፡፡ በእርግጥም አሸባሪ የለም፤ የፈጠራ ክስ ነው ያሳሰራቸው፡፡ አሸባሪ አለ ከተባለም እንደ ኢህአዴግ ያለ አሸባሪ የለም፡፡
ነጻ መውጣት ያለበት ቡድን አለ፣ እሱም ኢህአዴግ ራሱ ነው፡፡ እኔ አልታሰርኩም፡፡ የታሰሩት ኢህአዴጎች ናቸው፡፡ እስር የአዕምሮ ነው፡፡ እኔ አዕምሮየ አልታሰረም፡፡ ነጻ ሰው ነኝ፤ ውስጤ በጣም ነጻነት አለው፡፡ የታሰሩት ኢህአዴጎች ናቸው፡፡Ethiopian political activist Abraha Desta
እኔ እስር ቤት እንድገኝ ያደረገኝ ወንጀል አይደለም፡፡ መቃወሜና ይህን ተቃውሞየን በጽፍም በፊት ለፊትም መግለጼ ነው፡፡ ይህን ደግሞ ብዙ ኢትዮጵያውያን ያውቁልኛል፡፡ ሌላው ቢቀር ጥቂት የህወሓት ሰዎችም ያለ መረጃ እንደታሰርኩኝ በማመን እስሩን እየተቃወሙ ይመስለኛል፡፡ አንድ ቀን ወደ ህሊናቸው ከተመለሱ ስህተታቸው በህዝብ ፊት ያዋርዳቸዋል፡፡
‹‹በሐሰት ፕሮፖጋንዳ ሰው ማሳበድ ይፈልጋሉ›› ኦኬሎ አኳይ፣ የቀድሞው የጋምቤላ ክልል ፕሬዚዳንት
የሆነ ያልሆነውን የሚያወራው በዙሪያዬ ቢሰበሰብም እኔ በጣም ሰላም ይሰማኛል፡፡ ካድሬዎች አብረውን እስር ቤት አሉ፡፡ ወሬ ነው የሚለቃቅሙት፡፡ ይህን ወሬ ሲለቃቅሙ ይቆዩና የሆነ ያልሆነውን እያወሩ፣ የሐሰት ፕሮፖጋንዳ እየነዙ ሊያሳብዱህ ይሞክራሉ፡፡ እስር ቤትም ችግር ፈጣሪዎች ራሳቸው ኢህአዴጎች ናቸው፡፡ እኔማ ሰላማዊ ሰው ነኝ፡፡ ጉዳዩንም ፍርድ ቤት ይጨርሰው፡፡ ፍትህ አገኛለሁ ብዬ ባላስብም ፍርድ ቤት የሚወስነውን እጠብቃለሁ፡፡
እየመጡ የሚጠይቁኝ ዘመዶች አሉኝ፡፡ ቤተሰቦቼ ደህና መሆናቸውን መረጃ አገኛለሁ፡፡ ስለዚህ ምንም የምረበሽበት ነገር የለም፡፡ በህግ የምከራከርባቸው ብዙ ነጥቦች አሉ፡፡ ቢሆንም ከውሳኔ በፊት ምንም ባልናገር ጥሩ ነው፡፡ እዚህ ድረስ እየመጡ ለሚጠይቁኝ ሁሉ ክብር አለኝ፡፡

No comments:

Post a Comment