ይገረም ዓለሙ
ወገንን ጨፍጫፊ ቆዳው የነጣ ነው
በአበሻ የሚጨክን ፈረንጅ ብቻ ነው፤
እያለ የሚያስብ የዋህ ፍጡር ማነው
ጨፈጫፊ ከሆነ አበሻም ጣሊያን ነው
እንቶኔም በተግባር ሲኞር እንቶኔ ነው፤
በአበሻ የሚጨክን ፈረንጅ ብቻ ነው፤
እያለ የሚያስብ የዋህ ፍጡር ማነው
ጨፈጫፊ ከሆነ አበሻም ጣሊያን ነው
እንቶኔም በተግባር ሲኞር እንቶኔ ነው፤
በየግዜው እየከፋ የሄደውን የወያኔ አረመኔነትና የሀገራችንን ጉዞ ወዴትነት ሳስብ ትውስ ያለችኝን ይህችን ስንኝ ወደ ማስታወሻየ ገልብጬ ያኖርኳት በ1980ዎቹ መጨረሻ ግድም ለንባብ ይበቁ ከነበሩት መጽሄቶች ከአንዱ ነው፡፡ ወያኔ ዴሞክራት መስሎ ለመታየት በሞከረበትና ትክክለኛ ማንነቱ ገሀድ ወጥቶ ብዕርን ከጠመንጃ አስበልጦ መፍራት ባልጀመረበት በዛ ወቅት እንዲህ የጻፉት ሰው ዛሬ በህይወት ካሉ ምን ሊሉ እንደሚችሉ መገመት ይቸግራል፡፡
ወያኔዎች ደርግን በጨፍጫፊነት በማውገዝ ዛሬም ድረስ ፈሺስት ናዚ ወዘተ በማለት ይገልጹታል፡፡ በዘመነ ደርግ የተፈጸመውን ቀይ ሽብርም ለአንድ ሰሞን የፖለቲካ ፍጆታ ሊጠቀሙበት ሞክረዋል፡፡ ግን ካወገዙት ተግባር ተምረው ከተጸየፉት ድርጊት ርቀው ሊገኙ አልቻሉም፡፡ በርግጥም ከጅምሩ ስለ ቀይ ሽብር የነበራቸው አያያዝ ሊማሩበት ሳይሆን ሊያደናግሩበት፤ ለተበዳዮች ፍትህ ሊያስገኙበት ሳይሆን ጥላቻን ሊያነግሱበት እንደነበረ መለስ ብሎ በማስታወስ ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ ከቀይ ሽብር ቢማሩ ኖሮ ራሳቸው ያቋቋሙት የቀይ ሽብር ኮሚቴ ይዞት የነበረውን “ያለመቻቻል ፖለቲካ ሰማዕታት፣መቼም እንዳይደገም” የሚለውን መርህ ተግባራዊ ባደረጉና እንዲህ የለየላቸው ጨፍጫፊ ባልሆኑ ነበር፡፡
የቀይ ሽብር ነገር ለወያኔ የፖለቲካ ካርድ በነረበት ወቅት የቀይ ሽብር ኮሚቴ ባዘጋጀው አንድ የውይይት መድረክ ላይ የጥናት ወረቀት ያቀረቡት ፕ/ር ባህሩ ዘውዴ “…የፖለቲካ ልዩነቶችንም በተመለከተ አንዱ ወገን ምንግዜም ቢሆን ፍጹማዊ እውነትን ሊታደል እንደማይችል ተገንዝቦ የሌላውን ወገን ሀሳብ እህ ብሎ ማዳመጥ መቻል ይኖርበታል፡፡ የተቀዋሚ ወገን አየለ ብሎ ቃታ ለመሳብ መጣደፍ ዞሮ ዞሮ ሀገርን በብርቱ የሚጎዳ መሆኑን ከ « ቀይ» ሽብር ያተረፍነው ትልቁ ትምህርት ነው” ብለው ነበር፡፡ ነገር ግን ወያኔዎች ቀይ ሽብርን ያራገቡት ፖለቲካ ሊቆምሩበት እንጂ ሊማሩበት ያለመሆኑን ውለው ሳያድሩ በጀመሩት የሁሉም ነገር መፍትሄ ከጠመንጃ ይመነጫል አይነት ተግባራቸው አሳይተውናል፡፡
ሌላው ተናጋሪ የነበሩት ዶ/ር የራስ ወርቅ አድማሴ ባቀረቡት ጽሁፍ ደግሞ “ከኛ ትውልድ ስህተት በመማር የልጆቻችንን ትውልድ ከፖለቲካ ግድያ፣ከዘር ማጥፋት ፍጅትና ከስጋትም ጭምር ነጻ በሆነችና ፍትህ በነገሰባት ኢትዮጵያ እንዲኖሩ እንመኛለን፡፡ ይህን ምኞታችንን እውን ካደረግን ደግሞ እሱ ጊዜ የማይሽረውና የማያደበዝዘው ዕውነተኛው የሰማዕታት መታሰቢያ ይሆንልናል፡፡”» በማለት ዋናው ቁም ነገር የድንጋይ ሀውልት ማቆሙ ሳይሆን ካለፈው ተምሮ መሰል ጥፋት እንዳይደገም ማድረጉ እንደሆነ ነበር የገለጹት ፡፡ግና አንደ አለመታደልም ሆነና ወያኔን ሀይ የሚለውም ጠፋና ይሄው ዛሬ ድረስ ስጋቱም ፍጅቱም እንዳለ አለ፡፡
ባለፉት ሀያ አራት ዓመታት ወያኔ ከምንይልህ ቤተ መንግሥት ሆኖ የፈጸማቸው ኢ- ሰብአዊ ተግባሮቹን ለታሪክና ለትውልድ ፍርድ ትተን ዛሬም በእብሪትና በማን አለብኝነት የሚፈጽማቸውን ተግባራት ስናስተውል ጨፍጫፊ ከሆነ ሀበሻም ጣሊያን ነው የሚያሰኙ ናቸው፡፡ታዲያ እኒህን ከእለት እለት እየባሱ የመጡ አረመኔያዊ ድርጊቶቹን ምን ስም አንስጣቸው፡፡ ይመጥ አይመጥነው ባይታወቅም አንድ ሰሞን አንዳንድ ሰዎች ጥቁር ሽብር ማለት ጀምረው ነበር፡፡
ባለፉት ሀያ አራት ዓመታት ወያኔ ከምንይልህ ቤተ መንግሥት ሆኖ የፈጸማቸው ኢ- ሰብአዊ ተግባሮቹን ለታሪክና ለትውልድ ፍርድ ትተን ዛሬም በእብሪትና በማን አለብኝነት የሚፈጽማቸውን ተግባራት ስናስተውል ጨፍጫፊ ከሆነ ሀበሻም ጣሊያን ነው የሚያሰኙ ናቸው፡፡ታዲያ እኒህን ከእለት እለት እየባሱ የመጡ አረመኔያዊ ድርጊቶቹን ምን ስም አንስጣቸው፡፡ ይመጥ አይመጥነው ባይታወቅም አንድ ሰሞን አንዳንድ ሰዎች ጥቁር ሽብር ማለት ጀምረው ነበር፡፡
ከወራት በፊት አቶ ኤፍሬም ማዴቦ “አይኔ እያየስ እዚህ ውስጥ አልገባም, መሠረት ሙሴ” በሚል ርዕስ ባስነበቡን ጽሁፍ ስሙ የተጠቀሰው ወጣት ከሌሎች ሁለት ወጣቶች ጋር ጎነደር መተማ ላይ ተያዘ፡፡ ሁመራ ተወስደው ጫካ ውስጥ ሊረሸኑ ጉድጓድ አፍ ላይ ቆመው ገዳዮቹ አንደኛውን ወጣት በጥይት መትተው ወደ ጉድጓድ ሲከቱት አይኔ እያየስ እዚህ ውስጥ አልገባም ያለው መሰረት እግሬ አውጪኝ ብሎ ሮጦ አካሉ በጥይት ቢነዳደልም አምልጦ በሻዕቢያ ወታደሮች እጅ መውደቁንና ታክሞ ድኖ ግንቦት ሰባትን መቀላቀሉን ነግረውናል፡፡( ይህን አንብበን ዝም ማለታችን ራሱ አስገራሚ ነው)
ወጣቱ በፈጣሪ ቸርነት በማምለጡና አቶ ኤፍሬምንም በማግኘቱ የአይን ምስክርነቱን ሊሰጥ ቻለ፡፡ ባይሆን ኖሮ ይኑሩ ይሙቱ ሳይታወቅ ቤተሰብም እርሙን ሳያወጣ ጫካ እንደተጣሉ ይቀሩ ነበር፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ በየደረጃው ባሉ ዘመንኞች እየተረሸኑ በጅምላ የተቀበሩና በየጫካው የተጣሉ ዜጎችን ቤት ይቁጠራቸው ማለት ይቻላል፡፡ አንድ ቀን ግን መጋለጡ አይቀርም፡፡
እዛው ጎንደር ውስጥ የወንድሞቹ በረሀ መግባት በሰላም ለሚኖረው ክብሩ አሰፋ ወንጀል ሆኖ 18 ዓመታት አስፈርዶበት በጎንደር ወህኒ ቤት ስድስት ኣመታትን ካሳለፈ በኋላ ከእስር ቤት ተወስዶ መረሸኑን ከአርበኞች ግንቦት ሰባት መግለጫ አንብበናል፡፡ይህም ወያኔዎች ጠላታችን የሚሉትን ሰው አስረው እንኳን እንቅልፍ የማይወስዳቸውና ካልገደሉ የማይረኩ መሆናቸውን የሳየ ነው፡፡ በዚህ መልክ የተረሸኑ ወገኖቻችንስ ምን ያህል ይሆኑ?
ከሁለት ዓመት በፊት አዲስ አበባ ውስጥ ከስድስት ኪሎ ወደ ፈረንሳይ የሚሄደው መንገድ ሲሰራ ሶስተኛ ሻለቃ በመባል ይታወቅ የነበረውና ወያኔ ስሙን እየቀያየረ የሚጠቀምበት የጦር ሰፈር ጫፉ ላይ አጥሩ ፈርሶ ሲቆፈር የቅርብ ግዜ አስክሬን ከነተጠቀለለበት ብርድ ልብስ መገኘቱ ይታወሳል፡፡ በማህበራዊ ድረ ገጽም ምስሉ ተለቆ ለአንድ ሳምንት መነጋገሪያም ሆኖ ነበር፡፡ (ንዴት ቁጣችን፣ ተቃውሞ ፉከራችን ከአንድ ሳምንት አይዘል አይደል!) ሳይታሰብ በመንገድ ስራ ቁፋሮ ምክንያት ለእይታ የበቃው ያ የወገን አጽም የወያኔ የጦር ካምፖች ለወታደራዊ ተግባር ብቻ ሳይሆን ታፍነው ለሚሰወሩ ዜጎች ማሰቃያ መግደያና መቀበሪያነትም የሚያገለግሉ መሆናቸውን ያጋለጠ ነው፡፡ በዚህ መልክስ ስንት ወገኖቻችን በአረመኔዎች እየተገደሉ በየቦታው ተቀብረው ይሆን; ጠያቂ ጠፍቶ ጯሂ አልተገኝቶ ሆኖ እንጂ ቁፈራው ሰፋ ተደርጎ ቢቀጥል ብዙ ጉድ በተጋለጠ ነበር፡፡
የፖለቲካ ትርፍ አገኛለሁ ብሎ በደርግ እየተገደሉ በየቦታው የተቀበሩ ወገኖቻችንን አጽም እያወጣና በቴሌቭዥን እያሳየ ሲያስለቅሰንና ሲያላቅሰን የነበረው ወያኔ እሱ በተራው ሀያ አራት ዓመት ሙሉ አስሮ አሳቃይቶና ገድሎ ሊረካ አልቻለም፡፡ መታሰር መሰቃየትና መገደል በቃን ብለን ካላመረርንና ካልተባበርን አለበለዚያም ለወያኔ ሰጥ ለጥ ብለን ካላደርን በስተቀር ወያኔ ከዚህ አድራጎቱ መቼም የሚገታ አይመስልም፡፡ ግና ዘላለማዊ ምድራዊ ኃይል የለምና አንድ ቀን የጨለመው ሲበራ ህሊናቸው ፋታ ነስቶአቸው ወይንም ህግ አስገድዷቸው ወያኔ በዘመነ ሥልጣኑ እየገደለ በየቦታው ስለቀበራቸው ኢትዮጵያውያን የአይን እማኝነታቸውን የሚሰጡ ሰዎች መኖራቸው አይቀርም፡፡
ይሄው ሰሞኑን ደግሞ በየመድረኩ ስለፍትህ ስለ መልካም አስተዳደር ተቃውሞን በሰላማዊ መንገድ መግለጽ ስለመቻል ወዘተ እየደሰኮሩ በተግባር ግን በሰላማዊ መንገድ ጥያቄ ባቀረቡና ተቃውሞ ባሰሙ ወጣቶች ላይ ነብሰ ገዳይ ወታደሮቻቸውን አሰማርተው እያስደበደቡ እያሳሰሩና እያስገደሉ ነው፡፡ ለሀያ አራት አመታት በስልጣን ለመቆየት የቻሉት በማናቸውም ወገን የሚነሳን ማናቸውንም ጥያቄና ተቃውሞ በእስር በድብደባና በግድያ ጸጥ በማሰኘት በመሆኑ ሌላ ለጥያቄ መልስ መስጫ ዘዴም ሆነ ተቃውሞን ማስተናገጃ መንገድ አያውቁም፡፡
የአረመኔነታቸው ክፋት ጎንደር እስር ቤት ተቃጥሎ እስረኞች ህይወታቸውን ለማትረፍ ሲሮጡ እየተኮሱ ገድለዋል፡፡ ያለህበት ቤት ሲቃጠል አይንህ እያየ ዝም ብለህ ተቃጠል የሚሉ ነው የሚመስለው፡፡ እንደው እነዚህ ከእሳት የሚያመልጥን ዜጋ ተኩሰው የሚገድሉ ነብሰ በላዎች ከምን አይነት ማህጸን የተፈጠሩ ይሆኑ! ወይስ ወያኔዎች ሲያሰለጥኑዋቸው ከምግብ ወይንም ከሚጠጣ ነገር ጋር ቀላቅለው የሚሰጡዋቸው ከሰውነት ወደ አንስሳነት የሚቀይር፣ ሰዋዊ አስተሳሰብን አደድቦ ህሊና ቢስ የሚያደርግ ነገር ይኖር ይሆን፡፡
ወያኔዎች የአረመኔነታው ክፋትና የንቀታቸው ብዛት አንድም ገደሉ መቶ ለአፋቸው ይህል እንኳን በተፈጠረው ነገር እናዝናለን አይሉም፡፡ እነርሱ የሚያውቁት በሟች ቁጥር ላይ መሟገት ነው፡፡ ሰሞኑን የምንሰማውም ይህንኑ ነው፡፡
በሰላም ተቃውሞ በሚያሰሙ ( ቢቢስ ድንጋይ ይወረውሩ ይሆናል) ወጣቶች ላይ እንዲህ በየግዜው ግድያ የሚፈጽሙት ወያኔዎች ደርጎች ላይ እንደሆነው በአዲስ አበባ ከተማ በትላልቆቹ ባለሥልጣኖች ላይ ቢተኮስባቸው፣ ከመካከላቸው ቢቆስልና ቢሞትባቸው ምን ሊያደርጉ እንደሚችሉ መገመት አይከብድም፡፡ አብርሀ ደቦጭና ሞገስ አስግዶም የጣሊያኑን ጀነራል በቦምብ ካቆሰሉ በኋላ ጣሊያኖች በአዲስ አበባ የፈጸሙት ጅምላ ፍጅት መቼም የሚረሳ አይደለም፡፡ ወያኔዎች ከእስከዛሬ ተግባራቸው እንዳወቅናቸው ከመካከላቸው አንድ ሰው ቢገደል ወይንም ቢቆስል ተመሳሳይ ተግባር ከመፈጸም ወደ ኋላ እንደማይሉ ፡፡ ታዲያ ይህን በቀይ ሽብር ለተጨፈጨፉ ወገኖች ሀውልት አቁሞ ጭፍጨፋ የሚፈጽም አረመኔ ቡድን ለእሱም ሆነ ለድርጊቱ ምን ስም እናውጣለት፡፡
No comments:
Post a Comment