Thursday 10 December 2015

ፓትርያርኩ ለሕክምና ወደ አሜሪካ አመሩ | ከባድ የሰውነት መዛል ታይቶባቸዋል

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ ለከፍተኛ ሕክምና ወደ አሜሪካ ሀገር ማምራታቸውን የመንበረ ፓትርያርኩ ምንጮች ገለጹ። ከትላንት በስቲያ ማምሻውን ከአንድ ሊቀ ጳጳስ እና ሌላ ረዳታቸው ጋር የተጓዙት ፓትርያርኩ፣ ከሁለት ሳምንት ላላነሰ ጊዜ በሕክምና እንደሚሰነብቱ ተገልጧል። የ73 ዓመት የዕድሜ ባለፀረ የሆኑት ፓትርያርኩ በሀገር ውስጥ በሚገኝ አንድ ሆስፒታል የጤና ክትትል ሲያደርጉ መቆየታቸውን የጠቀሱት የዜናው ምንጮች፤ የሕመማቸው መንሥኤ ከከፍተኛ የደም ግፊት ጋር የተያያዘ መሆኑን ጠቁመዋል። ባለፈው ሳምንት በርእሰ አድባራት ወገዳማት አኲስም ጽዮን ማርያም ተገኝተው የክብረ በዓሉን ጸሎተ ቅዳሴ በመሩበት ወቅት ከባድ የሰውነት መዛል እንደታየባቸው የዜናው ምንጮች ተናግረዋል፤ ከዚያም በኋላ የሚሰማቸው ከፍተኛ አካላዊ ድካም የዕለት ተግባራቸውን እንዳያከናውኑ እክል እንደፈጠረባቸውና የተሻለ ሕክምና በማስፈለጉ ወደ ውጭ ሀገር መጓዛቸውን አስረድተዋል። የፓትርያርኩ የጤንነት ሁኔታቸው አሳሳቢ የሚባል እንዳልሆነ የገለጹት ሌሎች ምንጮች በበኩላቸው፤ አቡነ ማትያስ አጠቃላይ የጤና ምርመራቸውንና መደበኛ ክትትላቸውን እስከ ታኅሣሥ 13 ቀን 2008 ዓ.ም ድረስ አጠናቀው እንደሚመለሱ አስታውቀዋል። - See more at: http://www.zehabesha.com/amharic/archives/48900#sthash.3J4YG69t.dpuf

No comments:

Post a Comment