Saturday, 23 January 2016

የወያኔ “የማንቂያ ደወል” ደኩሜንታሪ — ውሸት ሲገነፍል!

ከመሰረታዊ የእምነት ተግባርና ምንጭ ከስግደትና ቁርዓን ጀምሮ መስጊድ መገንባትና መንፈሳዊ ሥራዎችን ማከናወን ወንጀል ነው በሚል የወያኔ መንግስት በሙስሊሞችና እስልምና ላይ የክተት አዋጅ ነጋሪት እያስጐሰመ ነው።UEMSG logo
“የማንቂያ ደወል” በሚል ስያሜ በቅጥፈት የታጀለው ደኩሜንታሪ 1ኛ-በሙስሊሙና በክርስቲያኑ መካከል ለ14 መቶ ክፍለ ዘመን የቆየውን መተማመንና አብሮነትን ለመናድ፣ 2ኛ- በራሱ በሙስሊሙ ሕብረተሰብ መካከል ቅራኔ ለመፍጠር 3ኛ- አብዛሃኛው የኦሮሞው ሕብትረተሰብ የእስልምና ሃይማኖት ተከታይ ስለሆነ፣ ይህ ጀግና ሕዝብ በአሁኑ ጊዜ በሚያካሂደው ሕዝባዊ አመፅ ላይ በጓዳ በር በመግባት ጥቃት ለመክፈት የተደረገ ከጅምሩ የተኮላሸ ሙከራ መሆኑ ለማንም ግልጽ ነው። ከሁሉም በላይ ግን ደኩሜንታሪው የሚያንፀባርቀው ዘረኛው የወያኔ ሥርዓት የጣረሞት ፍርግጫ ላይ መሆኑንና አንድ ሓሙስ የቀረው መሆኑን ነው።
የአገሪቱ ክፋይ ሕዝብ የእምነቱ መመሪያ የሆነን ቅዱስ መፅሐፍ ሲቃጠል በብሔራዊ የህዝብ መገናኛ ብዙሃን ማሳየት ወያኔ ለእስልምናና ለሙስሊሙ ህብረተሰብ ያለው የመጨረሻው የጥላቻና የንቀት መጋለጫው ነው። እስልምናን ለማጠልሸትና ለማጥፋት ጥረትና ተደጋጋሚ ሙከራ ያደረጉ ሃይሎች የእሳት እራት ሆነዋል። የወያኔ መንግስትም ሙስሊሞችን ለማዳከምና እምነቱንም ለመናድ የሚያሰማው ቀረርቶ እጣ ፋንታ ከዚህ የተለየ አይሆንም።
ወያኔ በራሱ አንደበት የደህንነት አባል ነኝ ብሎ የተናገረ ግለሰብና በእሥር ላይ ያለ ወንጀለኛ ግለሰብ ሳይቀር ምንም የሃይማኖት ዕውቀት የሌላቸውን ቦዜነዎች እንደ እስልምና እምነት ምሁራንና ተንታኞች አርጎ በደኩሜንታሪው አቅርቧቸዋል። ሙስሊም ተብዬዎቹ የወያኔ ካድሬዎች ወጣቱ እየሰገደ ነው፣ መስጊድ እንደ እንጉዳይ በዝቷል፣ የእስልምና መፅሀፍትን ማቃጠል ተገቢ ነው ይሉ ነበር። ይህ ቅንብር ኢብኮን ጥላቻና ሁከትን የሚናኝ የሃሰት ቋት ከመሆን አልፎ የሕዝብ መሳቂያ ለመሆን አብቅቶታል።
ይህ ፊልም የወያኔ መንግስት የውሸት ቶፋ ሞልቶ የገነፈለ መሆኑን አረጋግጧል። የአገሪቱን ኢኮኖሚ በሁለት አሃዝ (double digit) አድጓል፤ ዲሞክራሲ ሰፍኖ ሕዝቡ ሃሳቡን በነፃ መግለፅ ችሏል፤ ሰላም በኢትዮጵያ ተንሰራፍቷል ተብሎ ለሁለት አስርት አመታት የተደሰኮረው ሁሉ ኢብኮ ይነፋው የነበረው መለከት ባዶ ውሸት መሆኑ ታይቷል። ኢኮኖሚው 11% አድጎ ከኢትዮጵያ ተርፎ ጐረቤት አገር መመገብ የሚችል ደረጃ ተዳርሷል የተባለው ቀርቶ 15 ሚልዮን ሕዝብ ተርቦ ሃገሪቱ እህል ልመና ላይ ናት። በነፃ ሃሳብን መግለትጽ የተሰኘው ቀልማዳነት ተጋልጦ ዛሬ ከወያኔ የተለየ አመለካከት ያላቸው የፖለቲካ ሰዎች ፣ ሃሳባቸውን በጽሑፍ የገለጹ ጋዜጠኞች በእስር ላይ ናቸው። የቀረው ሕዝብ በአንድ ለአምስት ተጠርንፎ ጆሮ ጠቢነት የአገሪቱ ዋልታና ማገር ሆኗል። እንኳንስ በአደባባይ ቤተሰብ መካከል እንኳ ስለሚፈፅመው በደልና ጭፍጨፋ መተንፈስ አይቻልም። የፍርሃትና ጥርጣሬ ድባብ ከዳር እስከዳር ሰፍኗል። በመንግስት ጦር የዜጐች ደም በገፍ መፍሰስ የሰላም ሰፍኗልን ሐሰትነት ይመሰክራል። እነዚህን የወያኔን መንግሥት የውሸት ክምር ከ20 ዓመታት በላይ ያየና የሰማ ኢትዮጵያዊ የማንቂያ ደወል የተለመደው የኢብኮ መርዛማ የጋዝ ጭስ መሆኑን አይስትም። ስለዚህ ነው ውሸት የሚያቦኩበት ቶፋ ሞልቶ እየገነፈለ ነው የምንለው። እየፈሰሰ ያለውም ውሸት ወያኔን ከመሠረቱ የሚቦረቡረው ይሆናል።
ከአሁን ወዲህ የወያኔ መንግስት ጦሩን የሰበቀው በቀጥታ በሙስሊሞችእና በእስልምና ላይ መሆኑን አምኖ ለመቀበል የሚያመነታ ሰው ይኖራል ብሎ መገመት ያስቸግራል። ከወያኔ ካድሬዎች በስተቀር ድምፃችን ይሰማ የተያያዝነው የሕልውና ትግል መሆኑን ባስገነዘበው መሠረት ወሳኝ ደረጃ ላይ መሆናችንን ማመን ያሻናል። የኢትዮጵያውያን ሙስሊሞችን እምነት አጥፍቶ፣ ከትምህርት ገበታ አግልሎ፣ ከኢኮኖሚው መስክ አፈናቅሎ በማሀይምነትና በድህነት ማጥ ውስጥ ለመዝፈቅ የወያኔ መንግስት መርዝ የጠነሰሰበትን ጋን መፈረካከስና ውጥኑንም ማክሸፍ የእያንዳንዱ ሙስሊም ግዴታ ነው። ዓላማችንንም ለማሳካት የሚጠይቀውን መስዋእትነት ለመክፈል መዘጋጀት አለብን። ሌላ አማራጭ የለንም። ከሰላታችን፣ ከቁርዓናችንና ከመስጊዶቻችን ተለይተን ሕይወት አይኖረንምና።
የታሠሩ የሙስሊም መሪዎች፣ የተለየ አመለካከት ስላላቸው ብቻ ወደ እሥር የተወረወሩ የፖለቲካ ሰዎች፣ ጋዘጦኞች ያለ ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ፣ በኦሮሞ ወገኖቻችን ላይ እየተፈፀመ ያለው ግድያና እሥር በአስቸኳይ እንዲቆም ለዘረኛው ለወያኔ ጥብቅ ማሳሰቢያ እንሰጣለን። ከዚህ ውጭ ሕዝብ ሰላም ባጣበት አገር ሰላም ሊኖር አይችልም።
የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ለወያኔ መንግስት የሚያበስሩት ሰበር ዜና ቢኖር መስገዱም፣ መስጊድ መገንባቱም፣ ቁርዓንን ማፍቀሩ፣ ማንበቡና መከተሉም ተጠናክሮ እንደሚቀጥልና ምንም ምድራዊ ሃይል ሊያስቆማቸው እንደማይችል ነው። አራት ነጥብ።
ትግላችን በአላህ ፈቃድ እስከ ድል ደጃፍ ይደርሳል!
የተባበረ ሕዝብ ያሸንፋል!
አላሁ አክበር!!!
የኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ሰላማዊ ንቅናቄ ደጋፊዎች ሕብረት

No comments:

Post a Comment