Monday 18 November 2013

ለራሱ ነጻ ያልወጣ የባእድ አገልጋይ መንግስት ለዜጎቹ ጥብቅና ለመቆም የሞራል መሰረት የለውም!!! በነጻነት አድማሱ

የወያነ መንግስት የሳውዲ መንግስትን ለማውገዝ ለምን ተቆጠበ? ለመሆኑ በዜጎቻችን ላይ እየደረሰ ያለው
መከራ ወያኔን የሚያስደስት ነው ወይስ የሚያሳዝን? ኢትዮጵያን እያስተዳደረ ያለው ማን ነው? እውነት
የወያነ መንግስት ህዝብንና ሀገርን ወክሎ የሳውዲ መንግስትን የማውገዝ ባህርይና የሞራል ዓቅም አለውን?
ለጥያቄው ቀጥተኛ መልስ ከመስጠቴ በፊት የወያነ ባህርይ ምንድን ነው? የሚለውን መነሻ እንዲሆነን አለፍ
አለፍ ብዬ እንደሚከተለው በጥቂቱ ለመጥቀስ እሞክራለሁ። የወያነ ታሪክ የደላላነት፣ የሎሌነትና የክሕደት ታሪክ
መሆኑን ከተግባሩ በላይ ሌላ ምስክር አይኖርም።
1... ወያኔ በዓረቦች ጉርሻና ጡጦ ያደገ የባዕድ ተላላኪ ቡድን ነው።

የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ለመበታተን ብሎም ኢትዮጵያውያንን ነፃነታቸውንና ክብራቸውን የመከላከል
ዓቕም ለማዳከም ተብሎ ወያነ በሻዕቢያ ተወልዶ በዓረቦች ጡጦና ጉርሻ ያደገ የባዕዳን አገልጋይ መሪሲነሪና የማፊያ
ቡድን መሆኑን ከተግባሩ ሌላ ምስክር አይኖርም። ሌላውን ትተን በትጥቅ ትግሉ ዘመን ወያነ የገንዘብና የሎጂስቲክስ
ምንጭ የሚያገኝበት ከሱዳን ቀጥሎ ትልቁ ፅሕፈት ቤቱ በሳውዲ ነበር። አሁንም በኢትዮጵያ ስም ያለው ኤምባሲ
ካለፈው የቀጠለ የወያነ የገንዘብና የስለላ መሳሪያነት የሚያገልግል ያለው በዚያ በሳውዲ ነው።

2... ወያኔ በኤርትራና በኢትዮጵያ መካከል በደላላነት ሲሰራ የቆየ የሻዕቢያ ዲቃላ ነው።

ወያኔ በትግራይ ለጋ ወጣቶች ደም እየነገደ በኤርትራና በኢትዮጵያ መካከል ሁለት ወንድማማች ህዝቦችን ለማለያየትና
ለማናከስ የረጅም ጊዜ አላማ ይዞ ከተፈጠረበት ቀን ጀምሮ እስካሁንዋ ደቂቃ ድረስ በደላላነት እየሰራ ያለ የባዕድ ሎሌ
ነው። ኢትዮጵያ ያለ ባሕር በር ሽባ ሀገር ሆና እንድትቀር ከማድረጉም ባሻገር በኤርትራና በኢትዮጵያ ህዝብ መካከል
የእስራኤልና የፍልጤም ዓይነት ግንኙነት እንዲፈጠር ሆን ብሎ ሲሰራ የቆየ ድርጅት ነው። ስለዚሁ ጉዳይ በሰፊው
መዘርዘር ለቀባሪ ማርዳት ስለሚሆንብኝ፤ ወያነን ከመሰረቱትና ኰትኩተው ካሳደጉት አንዱ የሆኑትን አቶ አስገደ
ገብረስላሴ “ከህዲ” በሚል መፅሓፋቸው የወያነ መሪዎች ታሪክ የሎሌነት ታሪክ መሆኑን ከሃድ በማውጣት በዝርዝር
ያስቀመጡት ሓቅ የድርጅቱን ምንነት የሚገልፅ በቂ ማስረጃ ነው።

3... ወያኔ በዜጎችና በሰብኣዊ ፍጡር ደም የሚነግድ ጨካኝ፣ አረሜኔና ፀረ ዲሞክራሲ ቡድን ነው።

ወያነ ደርግን ማሸነፍ ማለት የኢትዮጵያ ህዝብ ማሸነፍ ማለት አድርጎ ስለሚቆጥረው የህዝቡን ጥያቄ፣ ችግር፣ ክብርና
ማንነት የዶሮን ያህል ክብር አይሰጠውም። ይንቃል። ያንቋሽሻል። የገዛ ወንድሙን እየገደለ፣ እየማረከና እየዘረፈ አዲስ
አበባ ምኒሊክ ቤተ መንግስት ገብቶ ስልጣን ስለያዘ ብቻ እንደ ትልቅ ጀብድ ተቆጥሮ ያለ ነሱ ጀግና ሌላው ግን የሀገር
ተስፈኛና ፈሪ አድርገው ያስባሉ። ከዚህ በመነሳት የቆየ ቂማቸውን መወጣጫ በማድረግ ዜጎችን በተለያየ ሰብብ አስባብ
እየፈለጉና የተለያየ ስም እየለጠፉ ይገድላሉ፣ ያስራሉ፣ ይሰውራሉ፣ ያጠፋሉ። ከወያነ የዘር ማኒፌስቶ የተገለበጠውን
ሕገ መንግስት ሕጋዊ በማስመሰል በዲሞክራሲ ስም እየማሉ ህዝቡን ለማታለል ይሞክራሉ። ከነሱ የተለየ አመለካከት
ያለው ዜጋ እንደ ጠላት በማየት በገዛ ሀገሩ እንደ አውሬ ያሳዱዱታል፣ ሰብኣዊና ዜግነታዊ መብቱ በመንጠቅ እንዲኮላሽ
ወይም ከሀገር እንዲሰደድ ያደርጉታል። በዚህ ምክንያት ወደ ባዕድ ሀገር የሚሰደደው ወጣት ቁጥሩ ብዙ ነው።


 4... የወያኔ የፓለቲካ ምሰሶ ዘር፣ ጥላቻና ምንቀኝነት ነው።

ወያኔ ኢትዮጵያን ለመበታተን፣ ህዝቧን ለያይቶ፣ አናክሶና ሆድና ጀርባ አድርጎ ለመግዛት እንዲመቸው ከሚጠቀምበት
ስትራተጂ አንዱ ኢትዮጵያዊነትን በረቀቀ መንገድ ቀስ በቀስ ማዳከምና ማኰላሸት ነው። በአንድ በኩል የብሄር
ብሄረሰቦችን ጠበቃ ለመመስል በሌላ በኩል ደግሞ ለኢትዮጵያ አሳቢ በመመስል የተለያዩ ቀለሞችን እየቀያየረ
ያደናግራል፣ ያናክሳል፣ ያራርቃል፣ ጥርጣሬ እንዲፈጠር በማድረግ አንዱን ብሄረሰብ ለሌላው ብሄረሰብ ስጋትና ጥፋት
በማስመሰል በህዝቦች መካክል የጥላቻ ፕሮፓጋንዳ መርዝ ያሰራጫል። ለምሳሌ ወያኔ የትግራይን ህዝብ ነፃ አውጪ፣
ጋሻና መከታ አድርጎ በመቁጠር የትግራይ ህዝብ ታሪክ ከደደቢት የሚጀምር፣ የትግራይ ህዝብ ህልውና ከወያኔ ጋር
የተቆራኘ መሆኑን ይገልፃል። ይህ ማለት የትግራይ ህዝብ ወያነን በስልጣን ላይ እስካለ ድረስ የሚኖር፣ ወያነ ስልጣን
ላይ ከሌለ ደግሞ የአማራና የኦሮሞ ሰለባ በመሆን ከወያነ ጋር አብሮ የሚጠፋ አድርጎ በመቁጠር ህዝቡን በተለይም
ወጣቱን ትውልድ ለማታልልና ለማደናገር የማይፈነቅለው ድንጋይ፣ የማይጭረው እሳትና የማይሰብከው የጥላቻ
ፓለቲካ የለም። በኢትዮጵያና በኤርትራ ህዝብ ላይ ያለው አመለካከትም ተመሳሳይ ነው። ወያኔዎች የኤርትራ ነፃነት
ባለውለታና መከታ ሌላው ኢትዮጵያዊ ግን የኤርትራ ህዝብን በጥላቻ የሚመለከት በማስመሰል ርካሽ ተወዳጅነት
ለማግኘት በጓሮ ይመፃደቃሉ፣ በኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅምና የደም ዋጋ ይደራደራሉ።

5... ወያኔ ትውልድ ገዳይ ነው።

የሰው ልጅ ምግብ፣ ወሃ፣ ልብስና መጠሊያ እንደሚያስፈልገው ሁሉ ያለ ነፃነትም ህልውና የለውም። ነፃነት ማለት
ደግሞ አንድ ዜጋ በራሱ፣ በሀገሩና በህዝቡ ጉዳይ ላይ ለመወሰን ነፃ የሓሳብ አማራጭ እንዲኖረው ያለ ገደብ መፍቀድ
ማለት ነው። ዛሬ በኢትዮጵያ በወያኔ ስርዓት እየታየ ያለው ግን በተቀራኒው ነው። ዜጎች ከመዋእለ ህፃናት ጀምሮ
በየደረጃው እስከ ዩኒቨርሲቲ ድረስ በወያኔ ሰይጣናዊ አመለካከትና ርእዩተ ዓለም ተጠምቀውና ተኰትኩተው
እንዲያድጉ ከመደረጉም በላይ በሀገሪትዋ ያለው ረሃብ፣ የንሮ ውድነትና ስራ አጥነት እንደ የፓለቲካ መሳሪያ በመጠቀም
በተለይም ለጋ ወጣቶች ለዕለት ጉርስና ለጥቅማ ጥቅም ሲሉ ሳይወዱ በግድ የወያነ/ኢሕአዴግ አባላት እንዲሆኑ
በማድረግ የአንድ ፓለቲካዊ ድርጅት አገልጋይና የአመለካከት ባርነት እንዲቀበሉ እየተደረገ ይገኛል። ይህ ደግሞ ሆን
ተብሎ በሀገሩ፣ በህዝቡና በራሱ መተማመን የሌለው የደነዘዘና የተኰላሸ ትውልድ እንዲፈጠር የተጠነሰሰ ሴራ ነው።
አባል ለመሆን ወይም የወያነ የተዳቀለ አመለካከት አንቀበልም በማለት ፍቃደኛ ያልሆኑ ወይም የተለየ ነፃ አመለካከት
አላቸው ተብለው የሚጠረጠሩ ዜጎች ደግሞ እንደጠላት እየታዩ ነፃነታቸው ተገድቦ ሁለተኛ ዜጋ ሆነው እየተሸማቀቁና
በፍርሃት ተሸብበው እንዲኖሩ ይደረጋል። ለምሳሌ በተቃዋሚ ድርጅቶች እየተካሄደ ያለው የመንጥር፣ የማሳደድና
የማንገላታት ዘመቻ የስርዓቱ ምንነት ጉልህ ማሳያ ነው። በዚህ ምክንያት ሀገሩንና የሞቀ ቤቱን ትቶ ሳይወድ በግድ ወደ
ባዕድ ሀገር ተሰዶ ለሞትና ለእንግልት የሚዳረገው ዜጋ ቁጥሩ ቀላል አይደለም።

6... ወያኔ ዘራፊና የኢኮኖሚ ልማት ነቀዝ ነው።

ወያነ የኢትዮጵያ ህዝብ አንጡራ ሀብት መዝረፍ የጀመረው የሀገራችን ብሄራዊ ጥቅም ለባዕዳን አሳልፎ በመስጠት ብቻ
የተወሰነ አይደለም። እንደነ “ትእምት”(ኤ.ፈ.ር.ት) የመሳሰሉ ሕጋዊ ልባስ ይዘው፣ ጨለማ ለብሰው የሚሰሩና እንደ
ምስጥ የሚቦረቡሩ የመዝረፊያ መሳሪያዎች በማቋቋምና በማደራጀት ነው። ድርጅቱም በማዕድን፣ በንግድ፣ በፋይናንስ፣
በእርሻ ምርት፣ በኮንትራክሽን፣ በትራንስፓትተሽን፣ በኢንጅነሪንግ፣ በተለያዩ የአገልግሎት ዘርፎችና ኢንዲስትሪዎች
በመሰማራት የሀገሪትዋን ቁልፍ የኢኮኖሚ ደም ስር ተቆጣጥረውታል። አቶ ስብሓት ነጋ በቅርቡ ከአሜሪካ ድምፅ
ራዲዮ የአማራኛ ክፍል ባደረገው ቃለ ምልልስ እንደገለፀው “ኤ.ፈ.ር.ት.” በአሁኑ ጊዜ በቀንድ አፍሪቃ ተወዳዳሪ
የሌለው ግዙፍ የኢኮኖሚ ሀይል ነው” ብሎ መግለፁ የሚታወስ ነው። የዚሁ ተቋም አላማም ከተለያዩ ሰዎች የተለያዩ
ሀሳቦች ይንፀባረቃሉ። 1. በወያነ ፕሮግራምና ሕገ መንግስት ላይ እንደሰፈረው ሁሉ ለወደፊት የመገንጠል አማራጭ
ቢመጣ በኢኮኖሚ የዓቅም መደላድልና መሰረት ጥሎ መቆየት የሚል ነው። 2. ልማታዊ መንግስት በሚለው የወያነ
ድርጅታዊ ሞኖፓላዊ መርሕ መሰረት አልፋ ወ ኦሜጋ የስልጣን ሄጆሞኒን ለማረጋገጥ እንደ መሳሪያ ሆኖ እንዲያገለግል
የተፈጠረ ነው። 3. የወያነ ባለ ስልጣናት የህዝብ ሀብት ለመዝረፍ እንደጓሮ አትክልታቸው አድርገው የሚጠቀሙበት ተቋም ነው። የትግራይ ህዝብ ግን “ኤ.ፈ.ር.ት” ልማት ሳይሆን ከጭቁኖች አፍ የተነጠቀና የተዘረፈ ጊዜው ጠብቆ
የሚፈነዳ እንደ ተቀበረ ፈንጅ አድርጎ ነው የሚያየው።

ሌላው የዝርፊያ መስካቸው የመንግስትን ስልጣን ተጠቅሞ የሚቦረቦር ሀብት ነው። የሀገራችን ገበሬ ሲተርት “የአህያ
በሬ፣ የጅብ ገበሬ፣ የዝንጀሮ ጎልጓይ፣ የጦጣ ዘር አቀባይ፣ አንድም የሌላቸው ሁሉም እንብላ!! እንብላ ባይ” እንዳለው
ሁሉ የወያነ/ኢሕአዴግ ባለስልጣናት በልማት ስም በተለያየ ስምና መልክ ወደ ውጭ ሸልኮ የሚወጣውን ሀብት ትተን
በዋና ዋና ከተሞች ቆመው የሚታዩ ሰማይ ጠቀስ ህንፃዎችና ቪላ ቤቶች የማን እንደሆኑና በማን ሀብትና ገንዘብ
እንደተሰሩ ለኢትዮጵያ ህዝብ ነጋሪና ዋቢ የሚያስፈልገው አይደለም። ኢትዮጵያ ለጥቂት ባለስልጣናትና ካድሬዎቻቸው
እንደ ኬክ የምትበላ ገነት ለብዙሃኑ ደግሞ ስደት፣ ውርደት፣ ረሃብና እልቂት በሆነበት ዘመን በሀገሪቱ ላይ ልማት አለ
ብሎ መናገር የሕልም እንጀራ ከመሆን አያልፍም። ነፃነት፣ ሰላም፣ መልካም አስተዳደር፣ የዜጎች ልዕልና መከበር፣ የሕግ
የበላይነትና ዲሞክራሲ ጠፍቶ ህዝባችን በገዛ ሀገሩ ባይተዋርና የበይ ተመልካች ሆኖ እስር፣ ሽብር፣ አፈናና ግደዲያ
በገነነበት ሀገር ሽሕ ወንዞች ቢገደቡ ያንድ ሰው ነፃነትና መብት አይተኩም።

 ወደ ዋናው የተነሳሁበት ጉዳይ ልመለስና “““የወያነ “ መንግስት የሳውዲ መንግስትን ከማውዝ ለምን ተቆጠበ?””””
የሚለውን ጥያቄ ብዙ ሰዎች በተለያየ መልኩ እየገለፁበት ያለ ጉዳይ ቢሆንም እኔም የተሰማኝን ያህል ጥቂት ልበል።

 አዎ!! ከላይ በጥቂቱ የተጠቀሱትን የዓመታት ፍዳ ድምር ውጤት ለኢትዮጵያ ህዝብ ያስገኘው ትርፋት ጭቆናና
ውርደት መሆኑን በተግባር በግልፅ እየታየ ነው። ሰሞኑን በሳውዲ ዓረቢያ በወገኖቻችን ላይ የደረሰው አሰቃቂ ክስተት
ምንጩ የወያነ አረሜናዊና አምባ ገነናዊ ስርዓት የፈጠረው ውጤት መሆኑን አሉ የማይባል ያዳባባይ ሚስጢር ነው።
ወያነ ““““ራሱ ገድሎ ልቅሶ ይደርሳል! ራሲ ገርፎ ራሱ ይጮዃል”””” እንደተባለው ራሱ በፈጠረው ችግር አዛኝ መስሎ
በስተጀርባ ከሱዕዲ መንግስት ጋር በመመሳጠር በዜጎች ላይ ችግሩን እያወሳሰበ ይገኛል። ወያነ እውነት ለህዝቡ ክብርና
ጥብቅና ቢኖረው ኖሮ የተፈጠረውን ችግር ለዓለም ማሕበረሰብና ለሳውዲ መንግስት ብሎም ለኢትዮጵያ ህዝብ
ድርጊቱን በመንግስት ደረጃ ማውገዝና ተመጣጣኝ የሆነ እርምጃ መውሰድ ይችል ነበር። ነገር ግን አላደረገም። ለምን?

ሀ) ወያነ ከአፈጣጠሩም ሆነ ባህርዩ ከኢትዮጵያ ህዝብ ፍላጎትና ብሄራዊ ጥቅም ጋር የሚቃረን ስለሆነ የባዕድ
አገልጋይና መሳሪያ ከመሆን አልፎ የህዝብ ጠበቃ መሆን አይችልም። አብዛኞቹ በስልጣን ላይ ያሉት የወያነ
ባለስልጣኖች በሳውዲና በሌሎች ዓረብ ሀገሮች የገንዝብና የማተሪያል ድጋፍ አዲስ አበባ የገቡ ናቸው። ስለዚ ሳውዲ
ለወያነ ባለውለታው እንጂ ጠላቱ አይደለም።

ለ) የሳውዲ መንግስት በኢትዮጵያ የነገስታቱ ሸሪክ በመሆን የወያነ መንግስትና የኢኮኖሚ አውታሮች የሚቆጣጠሩ
እንደነ ሸክ አላሙዲንን የመሳሰሉት የሳውዲ ቱጃሮች ወኪሎች አሉዋቸው። በአሁኑ ጊዜ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ
የሳውዲ ዶላርና የሸኩ ገንዘብ ያልቀመሰ የወያነ/ኢሕአዴግ ባለስልጣን አለ ቢባል ውሸት ነው። ስለዚህ በፔትሮ ዶላር
የተሸበበ የባለስልጣን አፍ ደፍሮ የሳውዲ መንግስትን ያወግዛል ብሎ ማሰብ የማይሆን ነው።

ሐ) የወያነ ንብረት የሆነውን “ኤ.ፈ.ር.ት” እንደ ቁም እንስሳት የመሳሰሉ የምርት ውጤቶች ወደ ሳውዲ መላክ ከጀመረ
ቆይቷል። ይህንን የንግድ ግኑኝነት እንዲጠነክር የሚያደርጉ ደግሞ በኢትዮጵያ ኤምባሲ ስም በሳውዲ የሚሰሩ የወያነ
ወኪሎች ናቸው። ስለዚ ወያኔዎች በግርግሩ እንዲጠቀሙ እንጂ እንዲጎዱ አይፈልጉም።

መ) ሳውዲ ዓረቢያ በአፍሪቃ ቀንድ በተለይም በቀይ ባሕር ቀጠና ያላትን ጂኦ ፓለቲካዊ ንክክ የወያነ መንግስት
ሊያሰጋው የሚችል ነው። በተለይም ከዓባይ ግድብና ከኤርትራ ጋር በተያያዘ ጉዳይ ከግብፅ ጋር በመወገን ልታበጣብጥ
እንደምትችል ችላ የሚባል አይደለም። በቅርቡ አንድ የሳውዲ ሚኒስትር ስለ ዓባይ ግድብ አሉታ ተናገረ ተብሎ የወያነ
መንግስት ምን ያህል እንደተርበደበደ ይታወሳል። ስለዚህ ወያነ ለግድቡና የስልጣኑን ዕድሜው ለማራዘም ሲል
ሳውዲን በይፋ ከማውገዝ ዝምታ ቢመርጥ የሚያስገርመን አይደለም።
 ሰ) ወያነ በዲያስፓራ ያለው የኢትዮጵያውያን ተቃውሞ ስለሚያስጋውና ለመቆጣጠር ስለማይችል የትም ይሁን የትም
በኢትዮጵያውያን ላይ የሚደርሰው ጥቃት፣ መፈናቀልና ክብር መድፈር የሚያሳዝነው ሳይሆን የሚያስደስተው ነው።
በሳውዲ ዓረቢያ በወገኖቻችን ላይ የተፈጠረው ችግርም አዛኝ መስሎ ለመታየት ቢሞክርም በአካባቢው ከሚገኙ
የወያነ ወኪሎች ጋር በተባበር ለፓለቲካ ፍጆታ ሲባል እየተጠቀመበት ይገኛል። በተለይም የስርዓቱ ደጋፊ አይደሉም
በሚባሉ ወገኖች እንዲባረሩና ተገደው ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ በማድረግ በስተጀርባ ብዙ ጉድ እየተሰራ መሆኑን
የሚጠቁሙ ብዙ መረጃዎች እየወጡ ናቸው። ስለዚ ወያነ በስደተኞች ወገኖቻችን ላይ የሚደርሰው ሶቆቃ በሀገር ቤት
ላሉ ወገኖቻችን “እኔን ብትቃወሙ መውጫ መግቢያና መሰደጃም የላችሁም” በማለት ተስፋ ቆርጠው የስርዓቱን
ባርነት ተቀብለው እንዲኖሩ የሚጠቀምበት እንጂ ከህዝብ ጋር ለመወገን የሚያስችል ሞራል የለውም።

በማጠቃለል፡- ለራሱ ነፃ ያልወጣና በራሱንና በህዝቡን የማይተማመን የዉጭ አገልጋይ የሆነ መንግስት ለዜጎች
ርህራሄና ጥብቅና በመቆም ከጥቃት ይከላከላል ወይም ያወግዛል ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው። በዓረቦች ጉርሻና ጡጦ
ተወልዶ ያደገውን የወያነ ቡድን ለህዝብና ለሀገር ክብር በቁርጠኝነት ይቆማል ብሎ ማሰብም የባሰ የዋህነት ነው።

ይባስ ብሎ ወያነ የሳውዲ ሰው በላ መንግስትን በማውገዝ ሳይሆን የተጠመደው በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ነው
የዘመተው። ትናንት በኢትዮጵያ በሰላማዊ መንገንድ ቁጣቸውና ተቃውሞቻቸው ለመግለፅ አደባባይ የወጡትን ንፁኃን
ዜጎቻችን ፍቃድ በመከልከል ብቻ ሳይሆን በማሰርና በመደብደብ እስር ቤት እያጎራቸው ይገኛል። ይህንን እርምጃ
ለመውሰድ የተገደዱበት ምክንያት ደግሞ ለሳውዲ ነገስታት ለማስደሰትና ታማኝነታቸውን ለመግለፅ ሲሆን በአንፃሩ
የህዝባችን ሞራል እንዲደቆስና አንገቱን እንዲደፋ ለማድረግ ነው። ከሳውዲ ተመለሱ የተባሉትም ከጥቂቶቹ በስተቀር
ብዙዎቹ የት እንደገቡና ወዴት እንደተወሰዱም የሚታወቅ ነገር እንደሌለ ታዛቢዎች እየገለፁ ነው።

በቸር ይግጠመን

No comments:

Post a Comment