Sunday 24 November 2013

ጎንደር ዩኒቨርስቲ አንድ ተማሪ ተገደለ

በጎንደር ዩኒቨርስቲ የ3ኛ አመት ማርኬቲንግ ተማሪ የነበረው አንተነህ አስፋው መገደሉን የደረሰን ዘገባ አመልክቷል። ትላንት ምሽት ወደ ዩኒቨርስቲው ከሴት ጓደኛው ጋር ወደዩኒቨርስቲ እየሄደ የነበረው ወጣት፤ ከግቢው ውጭ የዩኒቨርስቲው ጠባቂ ያስቆመዋል። ተማሪውም “ከዩኒቨርስቲ ውጪ ልታስቆመኝ አትችልም” የሚል ክርክር ይገጥማል። በዚህ መሃል ሴት ጓደኛው ተመትታ ራሷን ስታ ትወድቃለች። ከዚሁ ጋር ተያይዞ በተነሳ ግርግር ጥበቃው ተኩስ ይከፍትና ተማሪዎች ይበታተናሉ። በንጋታው ጠዋት ግን ያልተጠበቀ ነገር ገጠማቸው።
ምሽቱን ተማሪዎችን ለመበተን ይሁን ወይም ሆን ተብሎ በተተኮሰው ጥይት አንድ ተማሪ ቆስሎ ኖሮ፤ ጠዋት ወደ ዩኒቨርስቲ ሲመለሱ፤ አንድ ተማሪ ሞቶ ተገኝቷል። ሁኔታው በጣም አሳዛኝ ነው። በጎንደር ዩኒቨርስቲና በከተማው አካባቢ ይህ ጉዳይ ህዝቡን እያነጋገረ ይገኛል። ይበልጥ ነገሩን ያካረረው ደግሞ፤ የጥበቃውን ተግባር ለመሸፈን ሲባል ፖሊስ “እርስ በርስ በጩቤ ተወጋግተው ነው የተገደለው” ማለቱ ነው። ተማሪዎቹ ግን “የለም። ገዳዩ ምሽት ላይ የተኮሰው የጥበቃ ሰራተኛ ነው” በማለት ላይ ናቸው። እንግዲህ የአስከሬን ምርመራ የሚደረግ ቢሆን፤ የአሟሟቱን ምክንያት ለማወቅ ይቻላል። እስከዚያው ግን ነገሩ እንዳወዛገበ ይቆያል – ማለት ነው።
የሟችን ፎቶ እና ተጨማሪ መረጃዎች ካገኘን ቆየት ብለን እናቀርባለን።

No comments:

Post a Comment