Sunday 29 December 2013

እኔ ኣላውቅም ፈራሁ ጁሃር (ሄኖክ የሺጥላ )

የበደሌ ቢራ ፋብሪካ ከ ኣዲስ ኣበባ 483 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ኢሉ-ኣባ-ቦራ ( Eloo The father of Holstein Friesian) ኢልባቡር ከተማ በሁለት መቶ ሃምሳ ሺ ስኩውር ሜትር ይዞታ ላይ ስራውን እንደ ኣውሮጳውያን ኣቆጣጠር በ 1993 ማከናወን የጀመረ ትልቅ የቢራ ማምረቻ ድርጅት ነው።
ኢሊባቡር መልካም ምድራዊ ኣቀማመጡም ሆነ ምድራዊ ልምላሜው፥ እንደ በቆሎ ፤ ገብስ፤ ጤፍ፤ የቅባት እሎች፤ ማር፤ ከነ ቦራ ደሞ ወተት፤ ቅቤ እና ወዘተ የሚዘራባት፤ የሚታጨድባት፤ የሚቆረጥባት፤ የሚታለብባት ሃገር እንድትሆን ኣድርጉዋታል።
ኢሊባቡርን የጽሁፌ መንደርደሪያ ኣደረኩ እንጂ ዋናው ነጥቤ እሱ ኣይደለም። ዛሬ መናገ ወይም መጻፍ የፈለኩት ቴዲ ኣፍሮ በቅርቡ በመላው ኢትዮጵያ የሙዚቃ ዝግጅቱን እንዲያሳይ ወኪል የሆነውን የበደሌ ቢራን ያለመጠጣት ኣድማ ( boycotting) በመላው ኢትዮጵያ ይደረግ ዘንድ ኣንዳንድ ግለሰቦች የጀመሩትን ነገር ሰምቼ፤ ለምን በደሌን፤ ለምን ቴድን የሚል ጥያቄ ለሚጠይቁ፤ መልስ የሚመስለኝን ለመተየብ፤ ከተቻለም ለማሳየት መመኮር በመሻቴ ነው ።
ቴዲ ኣፍሮ በቅርቡ በ ጋዜጣ ላይ ስለ ኣድዋ ድል በሰጠው ኣስተያየት የተቆጡ፤ የተቀየሙ ግለሰቦች፤ ቴዲ ኣፍሮ ጥቁር ሰው ብሎ ንጉስ ሚኒሊክን፤ ከዛም በላይ የኣድዋ ድልን በመዘከሩ የተበሳጩ የህብረተሰብ ኣካሎች፤ ቴዲ ኣፍሮ ከዚህ ቀደም ጃ ያስተሰርያል ብሎ በመዝፈኑ ቂም የቁዋጠሩ ሰዎች፤ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በሊግ ኦፍ ኔሽን በ 1936 የኢጣልያንን የተለከለ የኬሚካል መሳሪያ መጠቀምን በመቃወማቸው፤ ኢትዮጵያን የ ዩናትድ ኔሽን ኣባል በማድረጋቸው፤ ቅራኔዎችን ኣብርደው ያፍሪካን ህብረት በመመስረታቸው፤ ለነዚህ ጉልህ ኣስተዋጾዎቻቸው በመዝፈኑ፤ ለነዚህ ለተጠቀሱት መልካም ስራቸው መታሰቢያ የጭንቅላቱ ውጤት የሆነውን ምዚቃ በማበርከቱ፤ ቴዲ ኣፍሮ ፤ ኣቀንቃኝ ና ኣዝማሪ ፤ ገጣሚና ሰኣሊ፤ ሃያሲና ደራሲ፤ ጸሃፊ ተውኔቱና ብላታው፤ ኣፉን በለጎመበት ዘመን፤ በብእሩ የታሪክ ጋሻ፤ በግጥሙ ለቆሰለ ታሪክ ማገገሚያ፤ በዘፈኖቹ ( ከ ማሊ ሱፊዎች ባልተናነሰ መልኩ) የነብስን ክር እየተጫነ ያላስለቀሰው፤ ያላስተከዘው፤ ሰው እንደሌለ የገባቸው ሰዎች፤ በይበልጥም የኣድዋ ድል፤ የጥቁር ኣንበሳዎች ድል መሆኑን ያሳየበት በመሆኑ እና ይህም የሚያማቸው ሰዎች፤ ዛሬ በደሌ ቢራ ቴዲ ኣፍሮን ስፖንሰር ስላደረገ፤ በደሌ ቢራን ያለመጠጣት ኣድማ ጠርተዋል። ኣሁን ቴዲ ኣፍሮን ኣብዶ በረንዳ ( የጫት ማከፋፈያ በረንዳ ነው) ቢሆን ስፖንሰር ያረገው ምን ሊሉ ነበር።። ባረገው እና የተከታዮቻቸውን መልስ ባየን። ኣንድ ጊዜ ቆይ ጠብቁኝ ሳቄ መጣብኝ ያለው ተናጋሪ ማን ነበር።
ኣዲሱ የቴዲ ኣፍሮ ኣልበም ( ጥቁር ሰው) የብዙዎቹን እትዮጵያዊያኖች ድምጽ ያስገኘለትን ያህል፤ ንጉስ ሚኒሊክ በድሎናል፤ ጡታችንን ቆርጦዋል፤ ወዘተ ወዘተርፈ ለሚሉት ደሞ፤ ከሚኒሊክ መፈጠር፤ ከታሪክ ኣንቅጽነቱና ኣኩሪ ገድሉ ጋር የጀመሩትን እጹብ ጸብ ውሃ የሚደፋበት በመሆኑ፤ ጠላት ሊያፈራበት እንደሚችል መገመት ብዙም ኣይዳግትም። እናም ‘ነዚህ ሰዎች ቀደም ብዬ እንደ ጠቀስኩት፤ በደሌ ቢራን ያለመጠጣት ኣድማ እናድርግ እያሉ ነው። ልክ ናቸው፤ ህዝብ በጥላቻም በቢራም ሰክሮ እንዴት ይሆናል፤ ባንዱ ብቻ ይበቃልና።
በነገራችን ላይ ይህንን ኣድማ ለማስመታት ከሚራወጡት እና ከሚሯሯጡት ሰዎች መሃከል ኣንዱ ጁሃር መሀመድ መሆኑን ሰምቼ ኣፍሬ ጥፍሬ ውስጥ ልገባ ነበር። ባንድ ወቅት ይሄ ወጣት ፖለቲከኛ ስለ ራሱ ሲናገር “እኔ እናቴ መንዜና የኦርቶዶክስ ክርስቲያን ነች ኣባቴ ደሞ ኦሮሞና ሙስሊም ነው ፤ ታዲያ ከኔ በላይ ኢትፖጵያዊነትን የሚወክል ምንነት ኣለ ወይ” ብሎ ነበር። መልሱ ሊሆን ይሚችለው ጁሃርዬ በውነትም የለም፤ እንዳንተው ኣቶ መለስም እኮ የተላቀቀ ነገርን ማጣበቅ የሚችል (ኡሁ የሆነ) (UHU…glue) ደም ነበራቸው፤ ግን ደሙ ሳይሆን የደሙ ባህሪ ነው ወሳኙ ነገር። የተሸከምነው ደም ሳይሆን በውስጣችን ያፋፋነው ስብዕና ነው ማንነት ፤ ማንነት ስራ ነው እንጂ ኣንተ እንዳልከው የ-ኢ-ተጎራባች ዘር ደም ውህደት (ኬሚስትሪ ውጤት ኣይደለም)፤ ክርስቶስ ( ኤሳው… ኣለይሁ ሰላም) በ-በረት ተወለደ ብለን እናምናለን፤ ግን እንደ ሰብኣዊ ፍጡር በ-በረት መወለዱ ሳይሆን ሰው ሆኖ ሲኖር ያደረገውን ነገር ነው የምናስበው፤ ስለ ነብዩ ሙሃመድ (ሰ.አ.ወ) ኣንድ ሙስሊም ሲያስብ ስለ ዘራቸው ሳይሆን ስለ ስራቸው ነው የሚያስበው ብዬ ኣስባለሁ ። ባንድ ወቅት ይሄው ሰው፤ ፹ ከ ፻ የሚሆነው የሃገሬ እስላም ኦሮሞ ነው፤ እናም የእሮሞ ህዝብን ኢምፓወር ማድረግ፤ እስልምናን ኢምፓወር እንደማረግ ነው ኣለን፤ ለመስማት ኣይደል የተፈጠርነው እናም ሰማነው፤ ባሜጃ ኣለን ዝም ብለን ሰማነው፤ ቀጥሎም ኢትዮጵያ ኣውቶ ኦፍ ኦሮሚያ ኣለን እሱንም ሰማነው። በነገራችን ላይ ኢትዮጵያ ኣውት ኣፍ ኦሮሚያን ወደ ፈርንጅኛ ስቀዳው ( the child give birth of her mother) ኣይመስላችሁም ? ለመተርጎም የተገደድኩት የመጀመሪያው ራሱ እንግሊዘኛ መሆኑን ስለ- ተጠራጠርኩ ነው። ለነገሩ ስታንፈርድና ኮሎምቢያ ዩንቨርስቲ እኮ መፈክር ኣያስተምሩም።
እና ዛሬ በደሌ መጣ እና ወንድሜ ጁሃር ሰማኒያ ከመቶ ካለው ሃሳብ ጋ ግንባር ለግንባር ተጋጨ ( head on collusion) እናም ሁለት የሚጋጩ ነገሮችን እንግዲህ እናስተውላልን።
፩) መቼም ፹ ከመቶው እስላም ኦሮሞ ነው ብለኽን፤ ኣንተም በዘር ብቻ ሳይሆን በእምነትም ጭምር ጠበኽ፤ ኣልገባኝም ታዲያ እንዴት ነው፤ እነማን ቦይ ኮት እንዲያረጉልኽ ነው ጥሪውን ያቀረብከው፤ ፳ ፐርሰንቱ እስላም ያልሆነው ኦሮሞ ? ደሞ ከ ፹ ከመቶ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ውስጥም ቢሆን ኣዲስ የበደሌ ኣድመናኛ ማግኘት ይቸግራል ብዬ ኣስባለሁ፤ ምክኒያቱም እነሱ ላንተ ሲሉ ሳይሆኑ ለዲናቸው ሲሉ ድሮም እንዲህ ኣይነቱን ነገር ይነኩት ነበር ብዬ ኣላስብም፤ በፍጽም ኣያደርጉትም፤ ታዲያ የማይጠጡ ሰዎችን ነው ኣድማ የጠራነው፤ ወይስ ሙሉ የኢትዮጵያዊነት ማሳያ ምሳሌ እንድትሆን ያደረገችህ የመንዜዋ እናትህን ዘመዶች፤ እኔ ኣላውቅም ፈራሁ ሄኖክ ነው ያለኝ የልጅነት ጉዋደኛዬ፤ ባንድ ትልቅ የውሃ ጉድጉዋድ ውስጥ እንሹለክ ስለው። እኔ ኣላውቅም ፈራሁ ጁሃር።
ዛሬ ጀርመን ያላትን ቅርጽ እንድትጠብቅ ወይም እንዲኖራት ያደረገው ኦቶ ቮን ቢስ ማርክ፤ የደም ትግል ውጤት ነው። ታዲያ ጀርመኖች በ ቢስ ማርክ ተናደው ፒሊሲነርን ( የጀርመን ታዋቂ ቢራ ነው) ቦይ ኮት እናርግ ኣላሉሉም። በፈረንሳይ እንዲህ የሚባል ታሪክ ኣለ፤ በኣሜሪካም፤ ኣረ ሆመር በጥንታዊያኖቹ የግሪክ ዘመን ስለነበረው ጦርነትም ጽፎዋል፤ ስለ ስርኣቱ፤ ስለ ኣገማምኖን እና የወንድሙ መንግስት፤ ስለ ሄለናዊው ስርኣት፤ ከዚያም በሁዋላ እነ ዳንቴ ስለ ጻፉት ስለ ዲቫይን ኮሜዲ፤ ፍሬድሪክ ዊልሃልም ኒቺ ስለተራቀቀበት የማህበረሰብ ስነ ልቦና፤ እነ ኣልበርት ካሙ ስለጻፉለት የፈረንሳይ ማህበረስብ እና በየስራቶቹ ውስጥ ስለ ነበርው ፍዳ፤ እነ ልዮ ቶሎስቶይ በሰላ ብእራቸው ስለዘገቡት የሩሲያ የጭቆና ቦለቲካ፤ እነ ፓብሎ ፒካሶ ጉሬንሽያ ብለው ስለገለጹት የስፔን ከተማ ስለ ስንቱ ለዚህ ለወጣቱ ፖለቲከኛ እንንገረው እስኪ ባክህ ጁሃርዬ ገረፍ ገረፍ ኣርጋቸው (በቃ እንደውም ለዚህ ክረምት ለፐርሰናል ዲቨሎፕመንት…ትመለከታቸው ዘንድ እጠይቅ፤ሃለሁ (ማሳሰቢያ በኣብዛኛው በኣማራ ጻሀፊ ኣይደልም የተጻፉት ቢሆኑም ደሞ ኣነተ ኣምሳ ፐርሰንት ኣማራ ኣይደለህ እንዴ፤ የምሬን እኮ ነው)
በታሪክ ላይ ጥላሸት መቀባት በፍጹም ለማንም ኣይሳካም፤ ወደድንም ጠላንም፤ ጠቅልለን የምንጎርሰውን እንጀራ የፈጠሩት ኣባቶቻችን ናቸው፤ ለሆዳችን ያለን ቅርበት ለታሪካችንም ይኑረን። ቴዲ እንዳለው ክፉውን በክፉ ለመመለስ ማሰብ ሌላ ክፉነት ነው። ሁለቱ ደሞች እንደ ደም ይሰሩ፤ ያስቡ ዘንድ ሰው እንሁን።

No comments:

Post a Comment