ባንዲራ ጨርቅ ነው ፤ የአክሱም
ሐውልት ለወላይታው ምኑ ነው ? ኢትዮጵያ ሀገራዊ ህልውና የመቶ አመት ጉዳይ ነው ፤ ያለ ‘ብሄሮች ፈቃድ’ የኢትዮጲያ ነገር አከተመለት ከተባለ 23 አመታት በሁዋላ ሰሞኑን ጎሰኝነትና የከርሞው ‘ ኢትዮጵያ ለምኔ’ ቱማታ እንደገና ‘በህዳሴ’ ብቅ ማለት የጀመረ ይመስላል። ምስጋና ‘ለወጣቱ ምሁር’ ጃዋር መሀመድ ይድረሰውና ! ጃዋር ብቻውን ስላይደለ እንቅስቃሴውም የተደራጀ እንደመምሰሉ ለዚህ ጽሁፍ ይሆን ዘንድ ‘የሜንጫ ፖለቲካ’’ ስል እሰይመዋለሁ። ይህን ስያሜ የመምረጤ አብይ ምክንያት የዚህ ቡድን አባላት ቢሳካላቸው ተፈጸመብን የሚሉትን የፓለቲካ አድልዎና በደል ሊያርሙ የሚመርጡት መንገድ ግፍን በግፍ የማረም መሆኑን ለማስገንዘብ ነው። አንባቢዎች በዚህ ምትክ ያሻቸውን ስያሜ ሰጥተው ሊጠቀሙ መብታቸው ነው።
ሐውልት ለወላይታው ምኑ ነው ? ኢትዮጵያ ሀገራዊ ህልውና የመቶ አመት ጉዳይ ነው ፤ ያለ ‘ብሄሮች ፈቃድ’ የኢትዮጲያ ነገር አከተመለት ከተባለ 23 አመታት በሁዋላ ሰሞኑን ጎሰኝነትና የከርሞው ‘ ኢትዮጵያ ለምኔ’ ቱማታ እንደገና ‘በህዳሴ’ ብቅ ማለት የጀመረ ይመስላል። ምስጋና ‘ለወጣቱ ምሁር’ ጃዋር መሀመድ ይድረሰውና ! ጃዋር ብቻውን ስላይደለ እንቅስቃሴውም የተደራጀ እንደመምሰሉ ለዚህ ጽሁፍ ይሆን ዘንድ ‘የሜንጫ ፖለቲካ’’ ስል እሰይመዋለሁ። ይህን ስያሜ የመምረጤ አብይ ምክንያት የዚህ ቡድን አባላት ቢሳካላቸው ተፈጸመብን የሚሉትን የፓለቲካ አድልዎና በደል ሊያርሙ የሚመርጡት መንገድ ግፍን በግፍ የማረም መሆኑን ለማስገንዘብ ነው። አንባቢዎች በዚህ ምትክ ያሻቸውን ስያሜ ሰጥተው ሊጠቀሙ መብታቸው ነው።
በዚህ ጽሁፍ በኦሮሞ ማህበረሰብ ኢትዮጵያዊነት ላይ በሀገራችን ነገስታት የስልጣንና ሀብት ቅርምት በይበልጥም የግዛት ማስፋፋት ሂደት ውስጥ የተፈጸሙትን ሁነቶች በተመለከተ የጭብጥ ክርክር ውስጥ ብዙም አልገባም።ለዚህም በርካታ ምክንያቶች አሉኝ፤፡ አንዱና ዋናው ምክንያት አዲሶቹ ጎሰኞች በመረጃና ታሪክ ጠቀስ ክርክር እምብዛም ስለሆኑ ነው፡፡ ለምሳሌ የታሪክ ነክ ክርክሮችን በኢትዮጵያውያን አዋቂዎች ድርሳናት ማመሳከር አይቻልም ፤ በእነርሱ የጨዋታ ሕግ መሰረት ኢትዮጵያውያን የታሪክ አዋቂዎች ሁሉ ‘ደብተራዎች’ ናቸው ፤ ስራቸው ለምስክርነት የማይቀርብ ። የአውሮፓውያኑን ድርሳናት ማመሳከር ደግሞ ፈረንጆቹን ‘በነጭ ነፍጠኝነት’ ያስከስሳል። ሁለተኛው ምክንያቴ ደግሞ የክርክራቸው አሰልቺነት ነው። የተዛባ ማስረጃና ጩሀት ተደጋግሞ ስለተነገረ እውነት የሚሆን ይመስል ውሃ ወቀጣ ይበዛዋል ፡፤ ኢትዮጵያ ከህወሃት መንግስት በፊት ከኦሮሞዎች በቀር ለተቀሩት ብሄረሰቦች በተለይም ለአማራው ‘ምድራዊ ገነት’ እንደነበረች ነው ተደጋጋሚው ስብከቱ። የባሌ ኦሮሞ በቀዳማዊ ሀይለስላሴ ላይ ሲያምጽ የጎጃም ሰው ቤቱ በሰላም ውሎ የገባ ይመስል አልያም የወሎ ሰው በረሃብ ሲጠቃ ንጉሱ ‘ ወገኔን’ ብለው ያደሉለት ይመስል። እሺ ካለፈው የተማረ ስረአት መመስረት ላይ ለምን አይሆንም ውይይቱ ለሚል መልስ የለም ፤ ዘፈኑ ተመልሶ ወደ ሚኒሊክ ፤ ሲያሻው ወደ ሃይለስላሴ ይሄዳል ፤፡ የፊትን የማየት ነገር የሚባል ልማድ እዚያ አካባቢ የለም ፡ እንዲያውም ‘በትምክተኝነትና ሴረኛ አማራነት’ ያስከስሳል። ከሁሉም ከሁሉም ከእንደዚህ አይነት ሰዎች ጋር ረብ ያለው ውይይት ማድረግ የማይቻለው የእልህና ቁጣ ፖለቲካ መልመዳቸው ነው። ለምን ማህበራዊ ድረ ገጽ ላይ አይሆንም የሀሳባቸውን ፋይዳ ቢስነት መተቸት ቁጣና ለከት የሌለው ዘለፋ ያስከትላል። እናም ለጊዜው ይህን ጽሁፍ ሰሞኑን ፈገግ አለያም እንዴ ባሰኙኝ ጉዳዮች እንዲያተኩር አደርጋለሁ።
‘የሜንጫ ፖለቲካ’’ ዋንኛ ባህሪው እንደ አብዛኛው አፍሪካዊ አፋጣኝ ስልጣን ፈላጊ የፓለቲካ ልሂቅ የቆየ ብሶትን መቆስቆስ መሰረት ያደረገ ነው ። ፈረንጆች ግሪቫንስ ፓለቲክስ እንዲሉ። የአፍሪካ ፓለቲካ ልሂቃን በዚህ የተካኑ ናቸው የ እኛዎቹን ጨምሮ : ታሪካዊ ፤ ነባራዊና ማህበራዊ ልዩነቶችን ፣ እነዚህ ውስጥ ያሉ ክፍተቶችን እንዴት ተጠቅመው ተከታዮቻቸውን ማባዛት በተለይም በምሬት ማነሳሳት ያውቁበታል። በሀገራችን ከድህረ ወያኔ መራሄ መንግስትነት በሁዋላ ይሄ ስልት የፓለቲካ ወደጅና ጠላትን ከመፈረጅ ባለፈ የፌዴራል አደረጃጀቱን ፤ የመሬት ስሪቱንን ያልተጻፈውን የኢኮኖሚ ፓሊሲና ከሁሉም ከሁሉም የፓለቲካ ስርአቱን ቅርጽና ይዘት ለማደራጀት ጠቀሜታ ላይ ውሏል። እንደ አብዮታዊ ዲሞክራሲያውያኑ እይታ ትልቁ የፓለቲካ ፋይዳቸው ‘ስልጣን ተመልሶ ነፍጠኞችና ትምክተኞችና ያለፈው ስርአት ናፋቂዎች እጅ እንዳይገባ ማድረግ ነው። ያ እንዲሆን ደግሞ በየጎጡ የተሰለፈው የፓለቲካ ልሂቅና ጀሌው ትናንት ጡትህን ሲቆርጡህ የነበሩትን ፤ ትናንት እንዲህ ሲሉህ የነበሩትን እያሸንልህ ነው አንተም ክንድ አበድረን ይባላል። በፕሮፓጋንዳ ስሜቱ የተንቦገቦገ ቆም ብሎም አያስብም በክንድ ፈንታ የክላሹን ቃታ ነው የሚስበው፡፡
የሚገርመው እነ ጃዋር ይሄንን ለ23 አመታት ስንሰማው የነበረውን ዜማ ከልሰው ፤ አራዶች እንደሚሉት ‘ሪሚክስ’ አድርገው በአዲስ መልኩ ሊያቀርቡት መፈለጋቸው ነው። ይህ ሕዝብን ከሕዝብ የማባላትና በሂደቱም ስልጣንን የማቆየት ዘዴ የዛሬን አያርገውና ‘ እኒያን ሽርጣም ሲሉዋችሁ የነበሩትን ነፍጠኞች በሉዋቸው ሲባል ተቀኝቶለታል በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ታምራት ላይኔ ። ይህንን ተከትሎ ዘርና ደም እየተቆጠረ ከስራ ማባረር ፤ እስርና ግድያ በብዙዎች ላይ ተፈጽሞአል። እንዲህ አይነቱ ግፍ በቀደሙት ስርአት ግፉአን ነበሩ የተባሉትን ብሄረሰቦችና የማህበረሰብ ክፍሎች ቁስሎች ያሽሩ ይሆን ? የለም ! ወያኔ ስልጣኑን ለማደላደል በተጠቀመበት በዚህ አይነቱ የመስዋእት በግ አሰሳ ዋና ተሳታፊ የነበሩ እንደ ኦነግ ያሉ ድርጅቶች ፤ ነፍጠኛው ነው የሚፈጀው እኛ ምን ከዳችን ሲሉ ከዳር ቆመው የነበሩ ኦሮሞዎችም በሁዋላ ላይ የስርአቱ አዶ ከበሬ ደምና የእስር ቤት ግብር ሲሻ ገፈቱን ቀምሰውታል ፤ ዛሬም ድረስ በሺዎች የሚቆጠሩ ንጹሃን የዝዋይና ሸዋ ሮቢትን እስር ቤቶች ታጉረውም ይገኛሉ። የሽግግር ( እናታችን የችግር ትለዋለች) ስርአቱ ሲመሰረት ነጻ አውጪ ነን ሲሉ የተሰባሰቡት ፓለቲከኞች ከብሶትና በቀል ፓለቲካ አርቀው አይተው ብሄራዊ መግባባትን ፈጥረው ቢሆን ኖሮ ይሀው ዛሬም እቀድሞ ሲዜም የነበረው ቢሊሱማና ወልቂጡማ የሚኒያፓሊስን ተራሮች አያንቀጠቅጣቸውም ነበር።
ከአስገራሚዎቹ ‘የሜንጫ ፖለቲካ’’ ባህሪያት መሀከል ዋናው ደግሞ ተጋፊነቱና ኢፍትሀዊ አመለካከቱ ነው። ሰሞኑን እንደምናነበውና እንደምንሰማው ከሆን የእነ ጃዋር ‘ኦሮሚያ’ እውን ትሆን ዘንድ የሌሎቻችን መብቶች ሁሉ መታቀብ አለባቸው። አዲሶቹ ነጻ አውጪዎች ወገኖቻችን ለሚሉዋቸው የህብረተሰብ ክፍሎችና ብሄረሰቦች ወደፊት ሊቸሩዋቸው ከሚያሰቡአቸው መብቶች ውስጥ የተወሰኑትን ለእኛ ለወደፊቱ ጎረቤቶቻቸው ባይነፍጉን ምናለ? እነ ጃዋር የኢትዮጵያ ሙስሊሞች (ሰሞኑን ወደ ኦሮሞ ሙስሊሞች ወረድ ብሎ ይሆናል ) በሀገሪቱ እኩል የእምነት ነጻነትን በሰበኩበት አንደበታቸው እነርሱ ሰፈር ቤተስኪያን ሊሰራ ላሰበ አማኝ ለምን ሜንጫ ይመኙለታል ? እነርሱ የራሳቸውን የታሪክ ድርሳናት አማክረው በአደባባይ የሚዘልፉትን ፤ የተቀረው አለም ቢያንስ ቢያንስ ‘’በማያዳግም መልኩ የነጭን ሰራዊት ለመጀመሪያ ጊዜ ድባቅ የመታ ሕዝብን የመራ ንጉስ’’ ሲል የመሰከረለትን መሪ የለም ስሙን በደግ አታንሱ ይላሉ። የእነርሱ ህልም እውን ይሆን ዘንድ ያለፈ ታሪክን መልካም ገጽ ማንቆላጰስና በሂደቱም ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት መታቀብ አለባቸው ። ለምሳሌ እነርሱ ሚኒሊክ ፈጸሙት የሚሉትን ግፍ ለማስታወስ ሙዙየም ማሰራታቸውን ፤ ሃውልት ማቆማቸውን ሌላው ማህበረሰብ በዝምታ ሲያልፈው ታሪክን በሌላ ገጽ የሚመለከተው ማህበረሰብ ለምን የእነርሱን ያህል መብት እንዲያጣ ይፈለጋል? ከዚሁ በተጓዳኝ ከሁሉም የሚያሳፍረው ተግባር ደግሞ የእነርሱን ጽንፍ የነካ ዘረኝነት የማይጋሩ ኦሮሞዎች ላይ የሚያደርሱት ጫና ነው። ትናንት ከመገንጠል ውጭ አማራጭ የለም ሲሉ ይታገሉ የነበሩ ፤ ዛሬ ደግሞ የለም ከብሄራዊው ዳቦ የድርሻችንን ነው ለማግኘት መታገል ያለብን የሚሉ ጎምቱ የኦሮሞ ፖለቲከኞች አይደለም ሀሳባቸው ሊሰማ በመጀመሪያ ከሜንጫ ፓለቲከኞች የኦሮሞነት መታወቂያ ማግኘት አለባቸው። እንዲያ በማሰባቸው ብቻ ‘ጎበናዎች’ ይሆናሉ በአንድ ሌሊት ። ይሄ ተዋልጄያለሁ ተዛምጄያለሁ የሚለውን ኦሮሞማ ለጊዜው መተው ነው ፤ ሲጀመርም እንደ ‘አርያን ሜንጪስት’ አይቆጠርም።
ሌላው ‘ የሜንጫ’ ፖለቲከኞች መለያ ፤ የተከታይን ቀልብ ይስባል ተብሎ የሚታሰበውን ሁሉ ፍለጋ ከዛፍ ዛፍ መዝለል። ባለፈው የስኮትላንዱ ፈረስት ሚኒስትር አሌክስ ሳልመንድ የስኮትላንድን የሪፈረንደም ማኒፌስቶ ባወጀ ሰሞን እነ ኦቦ ጃዋርም የወንድም ሀገር ስኮትላንድ አርአያነት ለተከታዮቻቸው ይሰብኩ ገቡ። እነርሱ ዘንድ ዩናይትድ ኪንግደም የአራት ሀገራት ህብረት እንደሆነች ፤ ስኮትላንድ ከሕብረቱ ወጣች አልወጣች የራሳ ብሄራዊ አስተዳደር እንዳላት አይታወቅም። የትም ይሁን የት ብቻ (ቲቤት ይሁን ፑንትላንድ፤ ኪውቤክ ይሁን ሞኖሶታላንድ ) የብሄራዊ ማንነት ጥያቄ ይነሳ ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁናቴ ጋር ይዛመድ አይዛመድ እነ ሜንጫ በፍጥነት ‘ ላይክ’ ያደርጋሉ። ይሄው ፈገግ አድርጎን ብዙም ሳንቆይ ደግሞ በማንዴላ እልፈተ ሞት ምክንያት የእነ ጀነራል ታደሰ ብሩና ኮሎኔል ፍቃዱ ዋከኔ ገድል መነሳት ጀመረ። እንደ ልማዳቸው የእኛዎቹ ‘ የነጻነት ታጋዮች ’ አጋጣማውን ለግልብ የፓለቲካ ገበያ ሊጠቀሙበት ተንጠለጠሉበት፡፤ ማንዴላ እንደ ሁለተኛ ሐገሬ ነው የማያት ያሏት ኢትዮጵያ ፤ እነ ጀነራል ታደሰ ብሩና ኮሎኔል ፍቃዱ ዋከኔ የተዋደቁላት ኢትዮጵያ ‘በፎቶ ሾፕ’ ከምስሉ ወጣችና የመኮንኖቹ ጎሳና ደም ተቆጥሮ በአንድ ሌሊት ታሪክ ተቀይሮ ማንዴላ ‘ከኦሮሚያ’ የጦር ልምምድ ስልጠና አግኝተው ነበር ተባለ። የእነ ማንዴላ ቁስል አድራቂነት ፤ አስታራቂነት ፤ ዘርና ማህበራዊ ክፍፍል ያላሸነፈው የፓለቲካ ርእዮትማ ማን ያስተውለው ? ለስሜትና ብሶት ፖለቲካ አይመችማ !
ዘግየት ብሎ ደግሞ ‘የሜንጫ ፓለቲካ’ የተመልካቾችን ቀልብ ይገዛልኛል ፣ ተከታዮቼንም ያበዛል በሚል ስልት ታዋቂው አቀንቃኝ ‘ቴዲ አፍሮ’ ላይ እመር ብሎ ሰፍሯል። እነ ጃዋር ቀድሞውንም ቢራ በአፋቸው አይዞርም የሚባልላቸውንና ከአማርኛ ሙዚቃ ከተፋቱ 23 አመት የሞላቸውን ‘ወገኖቻቸውን’ ፤ ቢራ አትጠጡ ሙዚቃም አታድምጡ እያሏቸው ነው። ለዚህ ዘመቻቸው ሰበቡ ያው የፈረደባቸው ምኒሊክ ለምን ተወደሱ ነው። ይሄ እንግዲህ የፓለቲካ ‘ ስትራቴጂስቱ’ ኦቦ ጃዋር እንደ አስማተኛ ሊያጃጅለን እፊታችን ያቀረበው ‘ቀይዋን ያየ’ መሆኑ ነው። በእርሱ ቤት እኛ ‘የታላቂቷን ኦሮሚያ’ የመመስረት ቅዠት አናውቅም ፣ ይህ ሕልም እውን ይሆን ዘንድ ገና አንድ ሺ አንድ ሰበቦች እንደሚደረደሩም እሚገባን አይደለንም። ከዚሁ ጋር በተያያዘ አስቂኙ የሜንጫ ፓለቲከኞች ሰሞናዊ ተግባር ደግሞ ይህቺን ጊዜያዊ ትርኢታቸውን ለማሳመር በአርባና አምሳ ሺ እስር ቤት አጎረን ያሉት ወያኔን ‘አስኮቱ’ ማለታቸው ነው። ቴዲ አፍሮ ‘ በአስራ ሰባት መርፌ’ ሲል የተዘባበተብህ እኛንም አጥንታችን ድረስ ዘልቆ ይሰማናል አሉታ ክንዱን ሊዋሱት። ህወሃት ምላጭ መሆኑን ከአጎቶቻቸው ‘የሽግግር’ ጊዜው ታሪክ የተማሩም አይመስሉም ። ወያኔ ዛሬ ቴዲን ቢበላ በአንድ ጎጆ ሁለት አባወራ እንደማይኖር ስለሚያምን ነገ የእነ ጃዋርን ጆሮ እንደሞቆረጥም ልብ ያሉ አይመስልም። ለማንኛውም እነ ሜንጫ ፓለቲከኞች እደጃችን የቆመውን አስቀያሚ ሁነት እንድናውቀው ስለወተወቱን እናመሰግናቸዋለን። ሲሆን በአንድነት ቆመን ‘እምቢ ለዘረኝነት’ ብለን እናቆማቸዋለን ፣ አይሆንም እንደለመድነው እርስ በራሳችን እየተጯጯህን በሩን የምንከፍትም ከሆነ ሜንጫው የት እንደሚያርፍ ማሰቢያ ጊዜ አለንና ተመስገን ነው።
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር
ሳምሶን. ብ. ለንደን
No comments:
Post a Comment