Thursday 1 May 2014

አምቦ በረብሻ እና በእሳት ተቃጠለች

(ኢ.ኤም.ኤፍ) በትላልቅ የትምህርት ተቋማት የሚገኙ የኦሮሞ ተማሪዎች የተቃውሞ ሰልፍ ማድረግ ከጀመሩ አንድ ሳምንት አለፋቸው። የተቃውሞው ምክንያት… የአንዲስ አበባ አጎራባች በሆኑት የኦሮሚያ ዞኖች ሊሰራ በታቀደው መሰረተ ልማት ነው። ለነገሩ መሰረተ ልማቱ አዲስ አበባ እና አጎራባች የኦሮሞ ከተሞችን (ለምሳሌ ቡራዩ፣ ሰበታ፣ ኮተቤ) የመሳሰሉት ከተሞችን ከአዲስ አበባ መሰረተ ልማት ጋር በትራንስፖርት እና በንግድ የማገናኘት እቅድ ነድፏል። ይህ እቅድ ግን ገና ከመጀመሪያው በኦሮሚያ ባለስልጣናት ጭምር አንዳንድ ተቃውሞ ሲቀርብበት ነበር። ውስጥ ውስጡን ደግሞ፤ የአዲስ አበባ መስፋት እና ከሌሎች አጎራባቾች ጋር መዋደድ ወደ ውህደት እንዳይሄድ የሰጉ ሰዎች ነበሩ። እነዚህ ሰዎች የአዲስ አበባን መስፋፋት… የአማርኛ ተናጋሪዎች ባህል እና አስተዳደር መስፋፋት በመሆኑ መሰረተ ሃሳቡን ጭምር አጥብቀው ይቃወሙታል።
በድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ
በድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ
ይህ ተቃውሞ አይኑን አፍጥጦ እና አፍ አውጥቶ አሁን ይውጣ እንጂ፤ ከሁለት ሳምንታት በፊት በራሳቸው የኦሮሚያ ባለስልጣናት መካከል መከፋፈልን ፈጥሮ የነበረ ጉዳይ ነው። በዚያኑ ሰሞን ደግሞ በአዲስ አበባ እና በኦሮሚያ ውስጥ የሚገኙ የኦሮሞ ምሁራን እና ታዋቂ ሰዎች እየታደኑ ሲታሰሩ ነበር። የዚህ የእስር እና አፈና   ዜና በይፋ ባይወጣም፤ ህዝቡ ግን ውስጥ ውስጡን ሲያዝን እና ሲያለቅስበት የነበረ ጉዳይ ነው። አሁን በኦሮሚያ ክልሎች ተማሪዎች የሚያሰሙት ተቃውሞ ዋናው ምክንያት “የአዲስ አበባ መስፋፋት…” ይባል እንጂ በውስጡ ብዙ ብሶት እና ጥያቄዎችን ያዘለ ይመስላል። ለዚህም ነው በድሬዳዋ፣ በሃረር፣ በባሌ፣ በጅማ፣ በነቀምት፣ በአምቦ እና ሌሎች ከተሞች የነበረው ተቃውሞ የምኒልክን ስም ጭምር በመጥራት ተቃውሞው ይቀርብ የነበረው። በሃረሩ አለማያ ዩኒቨርስቲ ሲያሰሙ ከነበሩት የተቃውሞ መፈክሮች መካከል ቴዲ አፍሮን ያወገዙበት አጋጣሚም አንዱ ነው።
አምቦ ላይ በተደረገው የተማሪዎች ሰልፍ ደግሞ አጼ ምኒልክ ከሞቱ ከመቶ ምናንም አመታት በኋላ፤ የሳቸውን ስም እየጠሩ አውግዘዋቸዋል። አጼ ምኒልክን መራገም ወይም የቴዲ አፍሮን ኮንሰርት ማውገዝ ውሃ የማይቋጥር ተቃውሞ ቢሆንም፤ የተማሪዎቹ ሰላማዊ ሰልፎች ግን ከአዲስ አበባ መስፋፋት ውጪ የራሳቸው ብሶት… ብሶቱን ለማባባስ ደግሞ አጼ ምኒልክ እና ሌላውን ኢትዮጵያዊ (ቴዲ አፍሮን ጨምሮ) ማውገዙ እና ማግለሉ ትክክል አይመስልም።
አሁን በሀረር፣ በአምቦ እና በሌሎች የኦሮሚያ ከተሞች የሚደረጉት ሰላማዊ ተቃውሞች ወደ ጸብ እና የርስ በርስ ግጭት እንዳይቀየሩም ያሰጋል። ለምሳሌ በአምቦ ዩኒቨርስቲ ተቃውሞ ሲያደርጉ በነበሩ ተማሪዎች ላይ በተከፈተው የተኩስ እሩምታ “ከሰላሳ በላይ ተማሪዎች ተገደሉ”  ከበኋላ፤ መመሪያውን ሲያስፈጽም የነበረው ኦህዴድ ግን “የሟቾቹ ቁጥር 6 ብቻ ነው” በማለት ይከራከራል። አላማው ምንም ይሁን ምን ህዝብ ሃሳቡን በነጻነት በመግለጹ ሊገደል እንደማይገባው ሁሉም የሚስማማበት ጉዳይ ይመስላል። ሆኖም የተቃውሞውን ሰልፍ በሃይል ለመበተን የሚሞክሩት የክልሉ እና የፌዴራሉ ታጣቂዎች አምቦ ላይ ሌላም ስራ ተጨምሮላቸዋል። ከተቀጣጠለው ተቃውሞ በተጨማሪ  የመንግስት መስሪያ ቤቶች ላይ ጥቃት እየተፈጸመ ነው። አሁን ማምሻውን እንደሰማነው ከሆነ፤ በባንክ እና ሌሎች ህንጻዎች ላይ ቃጠሎ ደርሷል – ተቃውሞውም እንደቀጠለ ነው!!
የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ ማስተር ፕላን በመቃወም በባሌ ሮቢ በትናንትናው እለት በተካሄደ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ በፖሊሶች በተከፈተ ተኩስ የደረሰውን ጉዳት የሚያሳይ ምስል (ምንጭ፡ በኢትዮ ትዩብ)
የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ ማስተር ፕላን በመቃወም በባሌ ሮቢ በትናንትናው እለት በተካሄደ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ በፖሊሶች በተከፈተ ተኩስ የደረሰውን ጉዳት የሚያሳይ ምስል (ምንጭ፡ በኢትዮ ትዩብ)

No comments:

Post a Comment