Monday, 26 May 2014

የሀገራችንን ችግር ከነችግር ፈጣሪዎቹ ልቅምቅም አድርጎ ለማስወገድ by Sebhat Amare (Norway)

በአንድ ሀገር የዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ የዜጎች በሰብዓዊ መብት፣ በዲሞክራሲ፣ በፖለቲካ እንዲሁም በማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ላይ ያላቸው ንቃተ ህሊና የሚጫወተው ሚና እጅግ ከፍተኛ ነው። የሲቪክና የፖለቲካ ማህበራት ፣ የጋዜጠኞችና የነፃ ሚዲያዎች በብዛት መኖር ከሰፊ ተሳትፎ ጋር የማህበረሰብ በዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ያለውን ንቃተ ህሊና ማሳደግያ መሆናቸው ዕሙን ነው። ነገር ግን የዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታን በበጎ መልኩ አይቶ ከማበረታታት ይልቅ ህዝብን ለማስተዳደር የተያዘን ስልጣን ዜጎችን ለመጨቆንና ረግጦ ለመግዛት ማዋል ግን የለየለት ፀረ-ዲሞክራሲያዊ ወንጀል ነው።
ሀገራችን ላለፉት ሃያ ሶስት አመታት ስለልማቷ፣ ስለእድገቷ ብዙ ተብሏል፥ እየተባለም ይገኛል። ሆኖም ግን አደገች፣ በለጸገች እየተባለ ይነገረን እንጂ ሕዝቧ/ዜጎቿ ከጊዜ ወደ ጊዜ ኑሯችን እያሽቆለቆለ፣ ፍትህ እየተዛባ፥ መብት እየተረገጠ አስከፊ ችግር ውስጥ ተዘፍቀን እንገኛለን። የሀገራችን እድገት ምስክሮች እኛውና የኛው ኑሮ መሆኑ ቀርቶ ሌሎች አውሮፓውያኖችና ለጋሽ መንግስታት ‘ለመንግስታችን’ እየመሠከሩለት፣ ወያኔም ምሥክርነታቸውን እንዳረጋገጡለት ለኛ መልሶ በቴሌቪዥንና በሬድዮ ቀንና ማታ ያደነቁረናል። ሃገራችን ችግር ላይ ነች ብለን ስንል የታየንንና የተረዳነውን ገሃድ አውጥቶ መነጋገርና መፍትሄ መፈለግ ለህዝብና ለሃገር በማሰብ እንጂ እንደወያኔ በአግድም ወይንም የተገላቢጦሽ አተረጓጎም በሃገርና በህዝብ ላይ ችግር መፍጠር ወይንም ህዝብን ለአመጽና ለብጥብጥ ማነሳሳት ወይንም መጋበዝ ማለት አይደለም። መንግስት ነኝ ብሎ የተቀመጠው ስብስብ የተሞላው በራስ ወዳዶች፣ ብልጣ ብልጦች፣ አስመሳዮችና የህዝብ ችግርና ሰቆቃ በማይሰማቸው ግለሰቦች ነው። ይህንን የሃገራችንን ችግር ከነችግር ፈጣሪዎቹ ልቅምቅም አድርጎ ማስወገድ የማናችንም ሃገር ወዳድ ዜጋ ሃላፊነትና ግዴታ ነው። ሃገራችን ጭርሱን የማይፈታ አደጋ ውስጥ ከገባች በኋላ ጣት እየተጠቋቆሙ ስህተትን እያነሱ መጨቃጨቅ ከፀፀት ውጪ የሚያመጣው መልካም ነገር ያለ አይመስለኝም። እኛም የምናወራው ስለ አንድ የተባበረች ኢትዮጵያችን ነው። ኢትዮጵያን ከችግር የማውጣት ግዴታ ያለብን ደግሞ እኛው ልጆቿ ኢትዮጵያውያን ነን እላለሁ።
ህወሃት በግድ ለህዝቡ ‘እኔ አውቅልሃለው፣ እኔ የምለውን ብቻ ዝም ብለህ ተቀበል’ የሚል ጊዜው ያለፈበት ያረጀ ያፈጀ የማናለብኝነት አምባገነናዊ ድርጊት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰበት ይገኛል። የኢትዮጲያ ህዝብ የሚበጀውንና የማይበጀውን፥ አንድነቱን የሚጠብቅለትንና የሚከፋፍለውን አይቶና አመዛዝኖ እንዲሁም አጣርቶም አጥርቶም የሚያውቅ የበሰለ፥ ታሪካዊና አንድነቱን ከጥንት ጀምሮ ጠብቆ የኖረ ታላቅ ህዝብ ነው። ህዝባችን የተፃፈን ሁሉ እያነበበና የተወራን አሉባልታ ሁሉ እየሰማ በስሜት የሚነዳ ህዝብ እንዳልሆነ ሊያውቁት ይገባል። አምባገነኖች ከሚያስቡት በላይ ህዝባችን የሚሆነውንና የሚጠቅመውን በሚገባ ጠንቅቆ ያውቃል። ነገር ግን የወያኔ መንግስት ለብዙ ሃገርና ህዝብ ጠቃሚ ነገሮች ሊውል የሚችል፥ ለተቸገረው ህዝባችን ጠቃሚ መሰረተ ልማትን መገንባት የሚያስችል በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር የሃገር አንጡራ ሃብትና ንብረት የተለያዩ ሚዲያዎችን፣ ለሃገር አንድነትና ለፍትህ የሚቆረቆሩ ዜጎችን ለመሰለልና ለማፈን እንዲሁም በሃሰት ለመወንጀል ሲውል በእጅጉ ይቆጫል። ይህ ድርጊት በውሸትና በተራ ፕሮፓጋንዳ የተሞላውን የመንግስት ሚዲያ በግድ ያለ ህዝብ ፍላጎት በአየር ላይ በማዋል ከህዝብ ጆሮ እንዲደርስ በማድረግ በተቃራኒው ግን ዜጎች ስለሚወዷትና ስለሚኖሩባት ውዲቱ እናት ሃገራቸው በአገዛዝ፣ በኢኮኖሚና በፍትሃዊ ስርዓት በተለያዩ መወያያ መድረኮችና ማህበራዊ ሚዲያዎች እንዳይወያዩ ማድረግና የተወያዪም ካሉ ደግሞ እንደ ሽብር ወንጀል እንዲቆጠር በማድረግ ዜጎችን በገዛ ሃገራቸው ባይተዋር በማድረግ ተሸማቀው እንዲኖሩ ማድረግ የወያኔ ቡድን አንዱና ዋነኛ ስራው ሆኗል።
በዚህ ቴክኖሎጂ በተስፋፋበት በዚህ ዘመን ሰብዓዊ ፍጡር ስለሚኖረው ኑሮና ህይወት፣ ስለሚኖርበትና ያገባኛል ይመለከተኛልም ስለሚለው ሃገሩ ሰብዓዊ ተፈጥሯዊ መብቱን ተጠቅሞ ያለውን አስተያየትና አመለካከት በነጻነት እንዳይገልጽ ማገድ ወይንም መከልከል ፀረ-ዲሞክራሲያዊነት ብቻ ሳይሆን ፀረ-ተፈጥሯዊም የመሆን ያህል ነው። የዜጎችን ድምፅ ያለገደብ ማፈንም የስርዓቱን መጨረሻ ማፋጠን መሆኑን ህወሃቶች ሊረዱት ይገባል። በተጨማሪም ሊረዱት የሚገባው ነገር የጨቆኑት ሰፊው ህዝብ ከሚያስቡትና ከሚገምቱት በላይ አመዛዛኝና አርቆ አሳቢ መሆኑን፥ የሚነዙት ተራ ፕሮፓጋንዳ ከማሰልቸትና የውድቀታቸውን መጨረሻ ከማፋጠን ውጪ ሌላ የሚፈይደው ነገር አለመኖሩን ሊያውቁት ይገባል። አሁንም ደግሜ ደጋግሜ የምናግረው ህዝባችን የሚበጀውንና የሚሆነውን በሚገባ ያውቃል። ኢትዮጵያዊ ስለተፈጠረባት፣ ዕትብቱ ስለተቀበረባት፣ ስለሚወዳትና ስለሚኖርባት ሃገር በነፃነት እንዳይወያይ ማገድ ኢ-ዲሞክራሲያዊ ከመሆንም አልፎ ወንጀልም ነው።
በእድገት ተራምደዋል በሚባሉት ሃገራት የምንኖር ለዲሞክራሲያዊና ፍትሃዊ ስርዓት ግንባታ የጋዜጠኝነት፣ የመፃፍና የሚዲያ ነፃነት ምን ያህል ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚያረግ እንዲሁም በዲሞክራሲ ላይ በተመሰረቱ የሃገራት ውስጥ የመፃፍ፣ የመናገርና የነፃ ሚዲያዎች መኖር ምን ያህል ታላቅና ጉልህ ሚና እንደሚጫወት እያየንና እያስተዋልን ነው። ነገር ግን እንደሃገራችን ኢትዮጵያ አይነት የዲሞክራሲና መልካም አስተዳደር ስርዓት ይቅርና እጅግ መሰረታዊ የሚባሉት ሰብዓዊ መብቶች በእንጭጩ የተቀበሩባት ሃገር መናገርና መፃፍ እንደወንጀል እየተቆጠረ ነው። ከብዙ በጥቂቱ ሰሞኑን በዞን 9 ጦማርያን ላይ፣ ቀደም ብሎም በጋዜጠኞቹ በእስክንድር ነጋና በርዕዮት ዓለሙ ላይ የደረሰውን ማየቱ ብቻ በቂ ይሆናል። ይባስ ብሎም ሰሞኑን የጋዜጣና የመጽሔት አከፋፋዮችን በሕገወጥ ነጋዴነት ሰበብ ያለንግድ ፈቃድ በመሥራት እና ታክስ ባለመክፈል ወንጀል ለመክሰስ በማሰላሰል ላይ ያለው ወያኔ በጭላንጭል ይታይ የነበረው የግል ፕሬሶችን እንቅስቃሴያቸውን በመግታት ደብዛቸውን ለማጥፋት ወያኔዎች የቀራቸውን አማራጭ ለመጠቀም ደፋ ቀና እያሉ ይገኛሉ። ሀገርንና ህዝብን አስተዳድራለሁ ብሎ ከዜጎች ይሁንታ ውጪ ስልጣኑን የተቆጣጠረው እንደ ወያኔ ያለ አምባገነናዊ ስብስብ ‘እንዴት የአስተዳደር ችግሮቼ በጋዜጠኛና በብሎገሮች ፅሁፍ ይተቻል፣ እንደፈለገሁ አስራለሁ/ እገድላለሁ’ ብሎ ለሃገርና ለህዝብ ኑሮ መሻሻል በጎ ሃሳብና መፍትሄ የጠቆሙና ያወያዩ፥ ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት መገንባትና ለሃገር ማደግ በጨዋነት እይታቸውንና እውቀታቸውን ለማካፈል ብዕራቸውን ያነሱ ጦማርያንና ጋዜጠኞች ሁሉ እየሰበሰቡ የሌለባቸውን የሽብርተኛነት ስም እየሰጡ በየእስር ቤቱ ማጎር፣ ፍትህን ማጓደልና የፍርድ ሂደቱንም አሰልቺ እና ተስፋ አስቆራጭ እስኪሆን ድረስ በማራዘም ሌሎችንም በማስፈራራት መወያያና የመማማርያ መድረኮችን ማፈን ብሎም እንዲጠፉ ማድረግ ለጊዜው ከሆነ ነው እንጂ በዘላቂነት የትም አንደማያደርስ ወያኔ ከወዲሁ ሊያውቀው ይገባል።
ወያኔን ከሌሎች አምባገነናዊ መንግስታት የሚለየውና የባሰ ያደረገው ደግሞ ስለህዝብና መንግስት መልካም አስተዳደር በጎ ግንዛቤ የሚያስጨብጡ ሚዲያዎችን ማፈኑና መከልከሉ ብቻ ሳይሆን ህወሃት እንደጦር ከሚፈራው የዲሞክራሲን ምንነት አስገንዛቢ ከሆኑ ሶሽያል ሚዲያዎች ባሻገር ዜጎችን እያዝናኑ የተለያዩ የኑሮ ክህሎትንና እውቀትን የሚያስጨብጡ ሚዲያዎችን አለመፍቀዱም ጭምር ነው። አማራጭ የፖለቲካ ስርዓት አመንጪ አካላት ለህዝብና ለሃገር የሚጠቅሙ እቅዶችንና መረጃዎችን ህዝብ ጆሮ አለማድረሳቸው ከሚፈጥረው ጉዳት ባሻገር በተለያዩ ያደጉ ሃገራት ለዜጎች ከፍተኛ ጥቅም በመስጠት የሚታወቁትን የህዝብን ንቃተ ህሊና የሚያዳብሩ እንዲሁም ፍትህንና ዲሞክራሲን የሚሰብኩ አስተማሪና ጠቃሚ ሚዲያዎችን ከህዝብ እይታና እውቅና ውጪ ማድረግ ዓይን ያወጣ ተፈጥሯዊ በሆነው በሰብዓዊ መብት ላይ የመብት ረገጣ ነው። ስለሆነም በአሁኑ ሰዓት የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠላት ህወሓት እና ህወሓት የዘረጋው አምባገበናዊ ጎጠኛ ሥርዓት ነው። የጋራ ትኩረታችን በጋራ ጠላታችን ላይ በማድረግ የወያኔን የርስ በርስ በዘርና በቋንቋ ከፋፍሎ የማጣላት እኩይ ሰይጣናዊ ታክቲኩን ተረድተን በአንድነት እንነሳ፥ ትኩረታችንን ለመበተንና አንድነታችንን ለማፍረስ ብዙ ማሰናከያዎችን ማድረጉ የማይቀር ቢሆንም፤ ግን በእንዲህ ዓይነት ድርጊታቸው ትኩረታችን ፈጽሞ መበተንና መዘናጋት የለበት። እኛ ኅብረታችንን ስናጠናክር የተዳከመው ወያኔ ይበልጥ ይዳከማል። ሊበታትኑን የሚዳክሩትን ዘረኞችን አሳፍረን ኅብረታችን ስናጠናክር የወያኔ ውድቀት ብሎም የእማማ የኢትዮጵያን ትንሣኤና ነጻነትን ይፋጠናልና በርትተን በአንድነት እንደቀድሟችን እጅ ለእጅ በመያያዝ የጀመርነውን ትግል በተጠናከረ መልኩ በማደራጀትና በማንቀሳቀስ ለበለጠ ትግልና ድል እንነሳ።
ኢትዮጵያ በክብር ለዘለዓለም ትኑር !!

No comments:

Post a Comment