Sunday, 30 November 2014

የሆድ ድርቀት * ምልክቶች * የሚያጋልጡ ነገሮች * ህክምና

አንድ ሰው ለተከታታይ ሳምንታትና ከዚያ በላይ በቂ ጊዜ ሰገራ መዉጣት የሚያስቸግረዉ ከሆነ ወይም በሳምንት ከሶስት ጊዜ በታች ሰገራ የሚወጣ ከሆነ ለረጅም ጊዜ የቆየ የሆድ ድርቀት( Chronic constipation) አለዉ ተብሎ በህክምናው ላይ ይገለፃል፡፡
Chronic constipation
ጊዜያዊ የሆነ የሆድ ድርቀት ብዙ ጊዜ የሚከሰት ነገር ነዉ፡፡ ነገር ግን ለረጅም ጊዜ የቆየ የሆድ ድርቀት በሚከሰትበት ወቅት የታማሚዉን የዕለት ተዕለት የስራ እንቅስቃሴ ከማወኩም በላይ ታማሚዉ ሰገራ በሚወጣበት ወቅት ረዘም ላለ ጊዜ የማስማጥና ሌሎች ምልክቶችም አሉት፡፡
የሆድ ድርቀት ምልክቶች
• በሳምንት ከሶስት ጊዜ በታች ሰገራ መዉጣት • የደረቀ ሰገራ መዉጣት
• ሰገራ በሚቀመጡበት ወቅት ማስማጥ
• ሰገራ በሚቀመጡበት ወቅት አንዳች ነገር ደንዳኔዎትን የዘጋዉ ነገር ያለ ስሜት መሰማት
• ሰገራ ለመዉጣት እርዳታ መፈለግ(በእጅዎ ሆድዎትን መግፋት፣በጣትዎ ሰገራን ለማዉጣት መሞከር)
ለሆድ ድርቀት የሚያጋልጡ ነገሮች
• በእድሜ መግፋት
• ፆታ /በአብዛኛው ሴቶች ላይ ይስተዋላል/
• በቂ ፈሳሽ ያለመዉሰድ
• በፋይበር( fiber) የበለፀጉ ምግቦችን ያለመጠቀም(አነስተኛ የፋይበር መጠን ያላቸዉን ምግቦች ማዘዉተር)
• አነስተኛ ወይም ምንም አይነት የአካል እንቅስቃሴ ያለማድረግ
• ለድርቀት ሊያጋልጡ የሚችሉ መድሃኒቶችን መጠቀም፡-ለምሳሌ የደም ግፊት ለመቀነስ የሚረዱ፣ለስነዓዕምሮ ችግሮች የሚሰጡ (ሴዳቲቭስና ናርኮቲክስ) የመሳሰሉት ናቸዉ፡፡ የሆድ ድርቀት መንስዔዎች
የሆድ ድርቀት አብዛኛዉን ጊዜ የሚከሰተዉ ከምግብ መፈጨት በኋላ የሚቀረዉ ቆሻሻ ወይም ሰገራ በአንጀት ዉስጥ የሚያደርገዉ እንቅስቃሴ(ጉዞ) በጣም ዘገምተኛ በሚሆንበት ወቅት ሲሆን የሚከተሉት መንስዔዎች አሉት፡-
• በትልቁ አንጀት ወይም በደንዳኔ ዉስጥ መዘጋት በሚኖርበት ወቅት
• የፊንጢጣ መቀደድ( Anal fissure)
• የአንጀት መታጠፍ
• የትልቁ አንጀት ካንሰር
• የትልቁ አንጀት ጥበት
• አንጀት ላይ ጭነት ሊፈጥሩ የሚችሉ ሌሎች የሆድ ዉስጥ ካንሰሮች
• የደንዳኔ ካንሰር
በደንዳኔ ግድግዳ ላይ አድገዉ የሰገራን መተላለፊያ ሊዘጉ የምችሉ ነገሮች(ሬክቶ ሲል)
• በትልቁ አንጀትና በደንዳኔ አካባቢ ባሉ ነርቮች ላይ ችግር በሚከሰትበት ወቅት
የነርቭ ችግር መኖር በደንዳኔና ትልቁ አንጀት ጡንቻዎች ላይ መኮማተርን ስለሚያስከስት የሰገራን እንቅስቃሴ ይገድባል፡፡ ይህን ችግር ሊያስከስቱ ከሚችሉ ነገሮች ዉስጥ፡
• የህብለ ሰረሰር (Spinal cord) ጉዳት መኖር • ስትሮክ( Stroke)
• የፓርኪንሰን ህመም
• አዉቶኖሚክ ንይሮፓቲይ የሚባል የነርቭ
ህመም
• መልቲፕል ስክሌሮሲስ የመሳሰሉት ናቸዉ፡፡ • ሰገራን ከሰዉነት ለማስወገድ በሚረዱ ጡንቻዎች ላይ ችግር መከሰት
• ሰገራን ለማስወገድ የዳሌ ጡንቻዎች መለጠጥ ያለመቻል(Inability to relax the pelvic muscles)
• የዳሌ ጡንቻዎች በደንብ በተቀናጀ መልኩ ያለመለጠጥና ያለመኮማተር (ዲሲነርጂ)
• የዳሌ ጡንቻዎች መልፈስፈስ
• በሰዉነት ዉስጥ ባሉ ሆርሞኖች ላይ ችግር መከሰት
ሆርሞኖች በሰዉነታችን ዉስጥ ያለዉ ፈሳሽ ተመጣጥኖ እንዲገኝ የሚያደርጉ ሲሆን ይህንን ስርዓት የሚያዛቡ ህመሞች ካሉ ለሆድ ድርቀት ሊያጋልጡ ይችላሉ፡፡ ከነዚህም ዉስጥ፡-
• የስኳር ህመም
• የፓራታይሮይድ ዕጢ ችግር(ሃይፐርፓራታይሮይድዝም)
• እርግዝና
• የታይሮይድ ዕጢ ሆርሞኖች ማነስ(ሃይፓታይሮይድዝም)
የሆድ ድርቀት ህክምና
ለረጅም ጊዜ የቆየ የሆድ ድርቀት በሚኖርበት ወቅት ከሚመከሩ ነገሮች ዉስጥ የአመጋገብና የአኗኗር ዘይቤ ለዉጥ ማድረግ ሲሆን ይህም ሰገራ በአንጀት ዉስጥ የሚቆይበትን ጊዜ ይቀንሳል፡፡ይህን ማድረግዎ ለዉጥ ካላመጣ የህክምና ባለሙያ ማማከር ይጠበቅብዎታል፡ ፡ የህክምና ባለሙያዎች የሚከተሉትን ነገሮች ሊመክሮት ይችላል፡፡
• የፋይበር አወሳሰዶችን መጨመር እና በቂ ፈሳሽ መዉሰድ፡- ቀስ በቀስ አትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም የጥራጥሬ ዘሮች በብዛት መመገብ
• የአካል እንቅስቃሴ ማዘዉተር፡- ይህ የአንጀትን የጡንቻዎችን እንቅስቃሴ ስለሚጨምር ድርቀትን ይከላከላል
• የሰገራ መምጣት ስሜት ባለዎት ጊዜ ሳያሳልፉ መዉጣት
• የሰገራ ማለስለሻ መጠቀም፡- ፋይበሮች፣ሰገራ ማለስለሻ መድሃኒቶች፣ሰገራን ሊያላሉ የሚችሉ ነገሮችን መጠቀም( Stool softeners)
• የዳሌ ጡንቻዎች ስልጠና፡- በዚህ ረገድ በሰለጠኑ ባለሙያዎች በመታገዝ ሰገራን ከሰዉነት ለማስወገድ የሚረዱትን ጡንቻዎችን በማላላትና በማጠንከር ማሰልጠን ሰገራን በቀላሉ ለመዉጣት ይረዳል፡፡
• የቀዶ ጥገና፡-በቀዶ ጥገና ሊስተካከሉ የሚችሉ የጤና ችግሮችን ለምሳሌ የፊንጢጣ መቀደድ፣ሬክቶሴሌና የአንጀት ጥበት የመሳሰሉት ሲሆኑ እነዚህ ሁኔታዎች ሲኖሩ የቀዶ ጥገና ባለሙያን ማማከር ይመከራል፡ ፡ጤናዎ ይሰመርሎት ዘንድ እየተመኘን ቸር እንሰንብት እንላለን፡፡

No comments:

Post a Comment