Friday, 19 December 2014

ምርጫ የዴሞክራሲያዊ ስርአት መገለጫ ብቻ ሳይሆን የሰላማዊ ትግል ስልት አካል ጭምር ነው! – Dave Teshome

ምርጫ በአንባገነን መንግስት ውስጥ?
ምርጫ የዴሞክራሲያዊ ስርአት መገለጫ የሚሆነው ነጻ፣ ፍትሃዊና ተወዳዳሪ (free, fair and contested) ባህሪያትን የተላበሰ እንደሆነ ብቻ ነው፡፡ በኢ-ዴሞክራሲዊ መንግስት ውስጥ የሚደረጉ ምርጫዎች በምንም መመዘኛ የዴሞክራሲ ስርዓት መገለጫዎች አይሆኑም፡፡ በሀገራችን በአጼው፣ በደርግ እና በኢህአዴግ ዘመነ-መንግስታት ተደርገው የነበሩ ምርጫዎች የአጼውን፣ የደርጉንና የኢህአዴግን የአገዛዝ ስርዓቶች የስልጣን ዘመን ለማራዛም የተደረጉ (“mechanism of regime maintenance”) ምርጫዎች እንጂ አንዳቸውም የዴሞክራሲዊ ምርጫ ባህሪያትን የተላበሱ አይደሉም፡፡ በእርግጥ በባለፉት ሁለት የመንግስት ስርአቶችም ሆነ በኢህአዴግ ዘመነ-መንግስት የተደረጉ ምርጫዎች በተለያዩ የፖለቲካ አገዛዝ ስርአቶች ውስጥ እንደመደረጋቸውና በወቅቱ ካለው የሀገራችን የፖለቲካ ዕድገት አንጻር የተለያዩ ባህሪያትን የተላበሱ ነበር፡፡ ይህ ሁኔታ ግን በኢትዮጵያ ብቻ የታየ ሳይሆን በማንኛው ኢ-ዴሞክራሲያዊ መንግስት ውስጥ የሚደረጉ ምርጫዎች አጠቃላይ ገጽታ ነው፡፡
ምርጫ እንደ ሰላማዊ ትግል ስልት?
በአንባገነን ስርአት ውስጥ የሚደረጉ የነጻነት፣ የፍትህ እና የዴሞክራሲያዊ ጥያቄዎች የአንባገነን ስርአቱን ጥቅምና ፋላጎት ባስከበረ መልኩ ሊመለሱ አይችሉም፡፡ ይህ የሚወልደው ፖለቲካዊ ግጭቶችም እልባት የሚያገኙት አንድም እጅን አጣጥፎ በመቀመጥ የአምባገነን ስርአት የፍርሃት እስረኛ በመሆን (passive submission)፣ አሌያ በትጥቅ ትግል(violent)፣ ወይም ደግሞ በሰላማዊ ትግል (non-violent) ነው፡፡ ሰላማዊ ትግልን ከትጥቅ ትግል የሚለየው የጭቆና መጠን ጉልህ ወይም ቀላል የመሆን አለመሆን ፣ ወይም ደግሞ የሰብአዊና ፖለቲካዊ መብቶች ጥሰት አናሳ መሆንና ያለመሆን ሳይሆን ልዩነቱ የሚመጣው በምንክተለው የፖለቲካ ትግል ስልት ላይ ነው፡፡ የሰላማዊ የፖለቲካ ትግል አባት የሚባለው ጄን ሻርፕ፣ የሰላማዊ ትግል ትርጓሜ ሲስቀመጥ፡- “the exercise power depends on the consents of the ruled who, by withdrawing that consent, can control and even destroy the power of their opponents” ብሎ ነው፡፡ ከዚህ የምንረዳው፣ ሰላማዊ ትግል አንደኛ፣ መሰረቱ ተገዢውና ተጨቋኙ ህዝብ ነው፡፡ ሁለተኛ፣ የትግል ስልቱ ህዝቡ ለገዢዎቹ የሰጠውን ይሁንታን በማንሳት ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ ሶስተኛ፣ ህዝቡ ገዢው ፓርቲ ስልጣኑን መኪያስጠብቅበት ጉልበት ያልተናነሰ ጉልበት ለገዢዎቹ በማሳየት (by means of wielding power) ገዢዎቹን መቆጣጠር፣ ከዚህም ከላፈ የመሪዎቹን ጉልበት በማፍራረስ ነጻነቱንና ዴሞክራሲያዊ መብቱን የሚያስጠብቅበት ነው፡፡
ከሰላማዊ ትግል ዘዴዎች አንዱ የፖለቲካ ትብብርን መንፈግ (the method of political noncooperation) ነው፡፡ ከዚህ ዘዴ ውስጥም፣ ተቋዋሚ ፓርቲዎች በአምባገነኑ ስርአት ውስጥ የሚደረጉ ምርጫዎች ውስጥ እራሳቸውን ማግልለ አንዱ ስልት ነው፡፡ ሆኖም ግን፣ በተደጋጋሚ እንደታየው ከምርጫ እራስን ማግለል ውጤታማ የሆነ የሰላማዊ ትግል ስልት አይደለም፡፡ ከ1990 እስከ 2009 እ.ኤ.አ ከተደረጉ 171 ከምርጫ እራስን የማግለል ማስፈራራት እና ከምርጫው እራስን በማግለል የተገኙ ውጤቶች ሲታዩ ከምርጫ እራስን ማግልለ ሳይሆን ከምርጫ እራስን አገላለው የሚል የማስፈራራት ስልት ውጤታማ እንደሆነ መረጃዎች ያመላክታከሉ፡፡ ከምርጫ እራስን የማግለል ስልት ደካማ ጎኑ በራሱ ቁሞ ውጤት የሚስገኝ ስልት አለመሆኑ ነው፡፡ በሀገራችንም በ1985 ዓ.ም እና በ2005ዓ.ም ተሞክሮ ውጤት አልባ መሆኑን አይተንዋል፡፡
በሌላ በኩል፣ ይህን ክፍተት የተረዱ የፖለቲካ ሳይንቲስቶች ምርጫን እንደ ሰላማዊ ትግል ስልት መጠቀም የሚቻልበትን ዘዴ ቀይሰዋል፡፡ ይህን ዘዴ Democratization by Elections በሚል የሰየሙት ሲሆን፣ ዋና ዋና ሃሳቡም፡-
• ምርጫዎ ለአንባገነኑ መንግስት መጨቆንን በጣም ከባድ እና መዘዘ-ብዙ እንዲሆን ያደርጋሉ፣
• ምርጫን ማካሄድ ለአንባገነኑ መንግስት ከውጭ መንግስታት ጋር ለሚያካሂደው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ዲፕሎማሲያዊ ጥቅም መስጠቱ፣
• ዜጎች አንባገነናዊ መንግስትን ከሚታገሉበት ስልት አንዱ መብቶቻቸውን ለማስከበር የሚያደርጉት ትግል አንዱ ነው፡፡ በምርጫ መሳተፍ (እንደ መራጭም ተመራጭም) ደግሞ የዜጎች ፖለቲካዊ መብት ነው፡፡ ይህን መብት መጠይቅ፣ ለመብታቸውም መታገል፣ ድምጻቸውን በምርጫ መስጠት፣ ድምጻቸውን እንዳይሰረቅ ማስጠበቅ አንዱና ወነኛው ስልት መሆኑ፣
• በሌላ ጊዜ አምባገነኑ መንግስት የሚዘጋቸውን በሮች ለምርጫ ሲባል ብቻ የሚከፍታቸው በሮች መኖራቸው፣
• ምርጫዎች ተቋዋሚ ፓርቲዎችን በጋራ በትብብር እንዲሰሩና ወደህዝቡ እንዲቀርቡ እንድል ስለሚፈጥሩ፣ እና
• ምርጫዎች ሰብአዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ፖለቲካዊ መብቱን የሚጠይቅ ዜጋን ለመፍጠርር መነቃቂያ መድኮች በመሆናቸው (bargaining power) ነው፡፡
በመጪው ምርጫ በመሳተፍ ይህን ዘዴ ከሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር በመቃኘት ተግባራዊ ማድረግ ይቻል ይሆን?
መነሻ ሃሳብ
1. በመጪው ምርጫ መሳተፍ ማለት ምርጫው ዴሞክራሲያዊ ነው፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲያዊ ሂደት አለ ማለት አይደለም፡፡ ኢ-ዴሞክራሲያዊ ምርጫ መሆኑን ማንም የሚገነዘበው ነው፡፡ አለምአቀፉ ማህበረሰብም የሚረዳው ነው፡፡
2. ኢህአዴግ የኢትዮጵያ መንግስት ነው፡፡ ምን አይነት መንግስት ነው? ኢ-ዴሞክራሲያዊ፣ አምባገነናዊ መንግስት ነው፡፡
3. በምርጫው እራስን በማግለል ተቋዋሚ ፓርቲዎች ሊያገኟቸው የሚችሉ ውጤቶች አናሳ (እሱም ካለ) ናቸው፡፡
4. ገዢው ፓርቲ የሚከፍታቸውን በሮችና የተገኙ እድሎችን በአግባቡ መጠቀም ተገቢ ነው፡፡
5. ባለፉት 23 ዓመታት ስለገዢው መንግስት ጨቋኝነት፣ አምባገነንነት ተወርቷል፡፡ ይሄ ምንም ውጤት አላመጣም፡፡ አሁን ደግሞ የዕይታ ለውጥ ያስፈልጋል፡፡ የተቋዋሚ ፓርቲዎች ላይ ማተኮር ተገቢ ነው፡፡ ሰላማዊ ትግል መሰረቱ የአምባገነን የጨቋኝነት አቅም ላይ የተመሰረተ ሳይሆን የተጨቋኙ አቅም ላይ የተመሰረተ ነውና፡፡
6. ማንም ተቋዋሚ ፓርቲ ብቻውን በመሮጡ ሊያሳካው የሚችለው ውጤት አናሳ ነው፣ በጋራ ሊገኝ ከሚችለው ውጤት አንጻር፡፡
7. በዚህ ምርጫ ሊገኝ የሚችለው ውጤት መንግስትን መቀየር የሚያስችል ውጤት ሳይሆን፣ ሊገኝ የሚችለው ውጤት መመዘን ያለበት ዴሞክራሲያዊ ስርአት የተገነባባት፣ ፍትህ የነገሰባት፣ እኩልነት የሰፈነባት ሃገር ለመፍጠር ምን ያህል ወደፊት ያራምደናል ከሚል መሆን አለበት፡፡
ይህን ዘዴ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችሉ ዘዴዎች
ገዢው ፓርቲ በሚከፍተው በር ሁሉ ለመጠቀም ውስጣዊ አቅም መገንባትና ዝግጁ፡- የሬዲዮ ክርክር፣ የቴሌቭዥን ክርክር፣ በህትመት ሚዲያዎች የሚሠጡ ዕድሎችን በአግባቡ በመጠቀም በግል ሚዲያ አለመኖር የሚፈጥረውን ክፈተት ማጥበብ እንዲሁም ገዢው ፓርቲ ላይ ስራ ማብዛት፣
ተቋዋሚ ፓርቲዎች ተናቦ የመስራት ዘዴ መከተል፡- ተቋማዊ ፓርቲዎቻችን በአንድነት መስራት ከብዷቸዋል፡፡ እርስ በእርስ የሚያረጉትን ትርጉም የለሽ የፖለቲካ ሽኩቻ በማስወገድ፣ ከተቻለም በምርጫው ጊዜ የእርስ በእርስ ውድድር እንዳይኖር የዕጩዎቻቸውን የመወዳደሪያ ክልል አወሳሰን ላይ በጋራ በመስራት ከገዢው ፓርቲ ጋር በአብዛኛው የምርጫ ክልሎች ላይ መወዳደር፡፡ እንዲህ በማድረግ የገዢውን ፓርቲ ጉልበት መሳሳትና መበተን ይቻላል፣ የጭቆና ወጪውም ከፍተኛ ይሆናል፣
የምርጫ ስትራተጂ፡- የተቋማዊ ፓርቲዎች የምርጫ ስትራተጂ ህዝባዊ መሰረት ለመፍጠር፣ ከዚህ ምርጫ ባሻገር የፖለቲካ መሰረት በመጣል ለቀጣይ ስራዎች ግብዓት የሚሆኑ አደረጃጀቶች መፍጠርንም ማካተት ይሆናል፡፡ የሚፈጠሩት አደረጃጀቶች ለቀጣይ ሰላማዊ ትግል መሰረት ይሆናሉ፡፡
በምርጫው ሂደት ንቁ ተሳታፊ መሆን፡- የምርጫ ታዛቢዎች ምርጫ ላይ፣ የምረጡኝ ቅስቀሳ ላይ እና በሁሉም የምርጫው ሂደት ውስጥ ንቁ ተሳታፎ ማድረግ፡፡ እንዲህ በማድረግም በተቻለ አቅም ለገዢው ፓርቲ ምርጫ ለማጭበርበር የማያመች ሁኔታ መፍጠር
ሰነዶችን የመያዝ አካሄድ፡- በምርጫው ወቅት የሚፈጸሙ የመብት ጥሰቶችን፣ የምርጫ ማጭበርበርን፣ ህገወጥ የሆነ የገዢውን ፓርቲ እንቅስቃሴ የሚያሳዩ ሰነዶችና መረጃዎች በአግባቡ በማሰናዳት የምርጫዉን ኢ-ዴሞክራሲያዊነት ማሳየት ይቻላል፡፡
ሊጠበቁ የሚችሉ ውጤቶች
የአጭር ጊዜ ውጤቶች
ተቋማዊ ፓርቲዎች ያላቸውን አነስተኛ የፋይናንስ፣ የሰው ኃይል እና ድርጅታዊ አቅም በአግባቡ መጠቅም ያስችላቸዋል፡፡
በህግ ማውጫው ምክር ቤት ውስጥ በመሳተፍ አማራጭ ፖሊሲዎቻቸውንና የመፍትሄ ሃሳቦቻቸውን ለማቅረብ የሚችሉ ይሆናል፡፡ የህዝቡን ብሶት፣ የመብት ጥሰት የሚያሰሙበት መድረክ ይኖራቸዋል፡፡
የረጅም ጊዜ ውጤቶች
በጋራ አምባገነኑን መንግስት መገዳደር ይችላሉ፡፡ ከአምባገነኑ ስርአት መውደቅ በኃላ ለሚፈጠረው ስርአት ግብዓት የሚሆን በመተባበር ላይ የተመሰረተ ተቋዋሚ ፓርቲዎች ግንኙነት ይፈጠራል፡፡
ሊደርስባቸው ከሚችልው የገዢው ጭቆና በጋራ የመከላከልና የመደጋገፍ ባህል ያጎለብታሉ፡፡
ትግሉን ከዲያስፖራ ወደ ሀገር-ቤት ወዳለው ህዝብ ይመለሳል፡፡ ይህም ለተቋዋሚዎች የበለጠ የመንቀሳቀሻ እድልና የስራ ነጻነት ይሰጣቸዋል፡፡ ይህም የድል ቀኑን ያቀርበዋል፡፡ “ድል ሁል ጊዜም የህዝብ ነው” እንዲሉ አበው፡:10846237_352811124921249_4560187603685275681_n
10253855_881406218556844_7018080946558430689_n
905888_388429767988047_2591897697800020709_o
10153833_587630041337455_4078181881316786241_n

No comments:

Post a Comment