Monday, 29 February 2016

እርቅ፤ የሚነገር – የማይተገበር (ይገረም አለሙ

ይገረም አለሙ
በአቶ ኦባንግ ሜቶ በሚመራው ድርጅት አዘጋጅነት በተጠራ ጉባኤ ላይ የተገኙ ኢትዮጵያዉያን ስብሰባቸውን ያጠናቀቁት በሀገራችን እርቅ አስፈላጊ መሆኑ ላይ በመተማመንና  ለዚህም ተግባራዊነት እርቅን ከራስ መጀመር እንደሚገባ አጽንኦት በመሰጠት  መሆኑን ሰምተናል፡፡ የእስከዛረሬው ተሞክሮአችን ተግባራዊነቱን አንድንጠራጠር ቢያደርገንም የአሰባሳቢዎቹ ተግባርም ሆነ ተሰብሳቢዎቹ የደረሱበት ድምዳሜ የሚደነቅ ብቻ ሳይሆን ለተግባራዊነቱ ድጋፍ ሊቸረው የሚገባ ነው፡፡
የእርቅ ተቃራኒ ጸብ ነው፡፡ ከሁለቱ ደግሞ የትኛው ቀላል እንደሆነ ለማንም ግልጽ ነው፡፡ እርቅ ብዙ መንገድ መሄድ፣ ብዙ ተግባር መከወንን ያሻል ብዙ መስዋዕትነትም ይጠይቃል፡፡ ለዚህም ነው ሲነገር እንጂ ሲተገበር የማንሰማው፣ ሲወጠን አንጂ ከግብ ሲደርስ የማናየው፡፡ ጸብ ግን  ማሰብና መጨነቅ፣ ማመዛዘንና ረጋ ብሎ መወሰን የማይጠይቅ በደቂቃ ውስጥ  ሊከውኑት የሚችል ነው፡፡Ethiopian Council for Reconciliation and the Restoration of Justice
ቢያንስ ባለፉት ሀያ ዓመታት የእርቅን አጀንዳ  በየግዜው ቢነሳም ከንግግር ማድሚቂያነት አልፎ  ተግባራዊነቱ ሊታይ አልቻለም፡፡ የሚናገሩትን መተግበር  ያልቻሉቱ የፖለቲካው  ተዋናዮች የሚያቀርቡት ምክንያት ደግሞ  አንድና የተለመደ  ከቁም ነገር ሊገባ የማይችል ነው፡፡ ኮ/ል መንግሥቱ ስለ እርቅ ሲጠየቁ የሀገር ጉዳይ ነው የባልና ሚስት ጸብ አይደለም ማለታቸውን የሰሙና መጨረሻ የሆኑትን ያዩ ወያኔዎች ከዚህ ባለመማር እነርሱ ደግሞ በተራቸው እርቅ ሲባሉ ማን ከማ ጋር ተጣላና ነው በማለት ይሳለቃሉ፡፡በአንጻሩ አንዴ ብሔራዊ እርቅ ሌላ ግዜ ሀገራዊ መግባባት ወይንም ብሔራዊ መግባባት ያስፈልጋል እያለ የሚጮኸው ተቃዋሚ ለነገሩ ተግባራዊ አለመሆን የወያኔን እምቢተኝነት በምክንያት እያቀረበ ለአመታት ዘልቋል፡፡
እርቅን የማይፈልጉ ከጸብ የሚያተርፉ መሆናቸው እሙን ነው፡፡ ወያኔ አጣልቶ እንጂ አስማምቶና ተስማምቶ፤ አለያይቶ አንጂ አንድነትን አጠናክሮ  በስልጣኑ ሊቆይ አንደማይችል ስጋት ስላለው እርቅን ቢጠላ መግባባትን በሩቁ ቢል ከዓላማው የመነጨ ነው፡፡ ተቀዋሚዎቹ ግን ሀያ አራት አመታት ስለ እርቅ ሲጠይቁ አንጂ የሚችሉትን ሲያደርጉ አለመታየታቸው ለምን ይሆን  የሚል ጥያቄ ያነሳል፡፡  ለዚህ መልሱ የወያኔ አምቢተኝነት ነው  የሚባል ከሆነ ራስን ማታለል ይሆናል፡፡
እርቅ የሚጠይቁት ፖለቲከኞች ርስ በርሳቸው አይደለም መጀመሪያ ከራሳቸው መች ታረቁ፤ብሄራዊ መግባባት ሲሉ የሚደመጡት እነርሱ በተቃዋሚነት ደረጃ ፓርቲ ከፓርቲ አይደለም በአንድ ፓርቲ ውስጥ ግለሰቦች አንኳን መች መግባባት አላቸው፡፡ ብዙ ተባዙ የተባሉ ይመስል የተግባር ሳይሆን የቁጥር ፓርቲ በውጪም በውስጥም የሞላው በዚሁ ምክንያት አይደለምን፡ ከወያኔ ጋር ውይይት እንሻለን የሚሉት እነርሱ መች ለውይይት አንድ ላይ መቀመጥ የሚችሉ ናቸው፡፡ በአንድ ብሄር ስም አራት አምስት ድርጅት የመሰረቱ ስለ አንድነት እያወሩ መለያየየትን የሚተገብሩ፣ ሀገራዊ መግባባት እየጠየቁ ድርጅታዊ መናቆር የሚያካሂዱ አይደሉምን፡፡
ወያኔ ተቀዋሚዎቹ እርቅ ብለው የሚጮሆት በምርጫ ያጡትን ሥልጣን በአቋራጭ እናገኛለን ብለው በማለም ነው ብሎ እያሰጋ የሥልጣን ነገር ደግሞ ለርሱ የነበር ጅራ ሆኖበት ማስተዋል ነስቶት እንጂ እኔ ከዚህ ሁሉ ድርጅት ተብየ ጋር ውይይት መቀመጥ አልችልም መጀመሪያ ራሳችሁ ታረቁና፣ አለያም  በመካከላችሁ መግባባት ፍጠሩና ከዛ በኋላ ጠበብ ባለ ቁጥርና በተወሰነ አጀንዳ መነጋገር አንችላለን ቢል ተቀዋሚዎቹ ይህን ፈተና ማለፍ ይችላሉ ብሎ  በርግጠኝነትመናገር አይቻልም፡፡
መጀመሪያ ከራሳችን አንታረቅ የሚለው የእነ አቶ ኦባንግ ስብሰባ ውጤት ተግባራዊ ቢሆን ይህን ችግር ይቀርፍ ነበር፤ መጀመሪያ ግለሰቦች ከራሳቸው ጋር፣ ቀጥሎ በአንድ ፓርቲ ወስጥ ያሉት ርስ በርሳቸው  ከዛም በመቀጠል  ፓርቲ ከፓርቲ እየተባለ እርቁም ይን መግባባቱ ቢፈጠር ፓርቲዎቹ ቁጥራቸው የተወሰነ ከወያኔ ጋር አንነጋገርበታለን የሚሉት አጀንዳ የተመጠነ ሀይላቸው የጠነከረ ይሆናል፡ ያኔ ወያኔ በእምቢተኝነቱ ቢጸና የማስገደድ አቅም ይኖራቸዋል፡፡አሁን ባሉበት ደረጃ ሆኖ ስለ እርቅ አስፈላጊነትና ስለ ወያኔ አምቢተኝት ማውራት  ከምር እርቅ ፈላጊነትን አያሳይም፡፡ የዓለም አቀፉ ማህበረስብ አካላትና የሀያላኑ መንግሥታት ተወካዮች በአንዲት ሀገር ኢትዮጵያ ጉዳይ ከስንቱ ጋር እንደሚነጋገሩ እየቸገራቸው እባካችሁ አንድ ሆናችሁ ኑ ማለታቸውን በተደጋጋሚ ራሳቸው ፖለቲከኞቹ አንደነገሩን አንዘነጋውም፡፡
የእርቅ አስፈላጊነትንና ጠቀሜታን የማይረዳ ሰው ይኖራል ተብሎ አይታሰብም፡፡ ችግሩ ሁሉም የሚያሰበው እርቅ ለሀገሪቱ ስለሚያስገኘው ጠቀሜታና ለትውልድ ስለሚያቆየው በረከት ሳይሆን እሱ ስለሚያጣውና ስለሚያገኘው ግለሰባዊ ጥቅም ( ፕ/ር መስፍን በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ጭንቅላት ላይ አለ የሚሉት ዘውድ ሊሆን ይችላል) በመሆኑ  እርቅ የሚናገሩት አንጂ የማይተገብሩት አጀንዳ  ሆኖ አመታት ያስቆጠረው፡፡
ዛሬ የተነሳው እርቅን ከራስ የመጀመር ጉዳይ በተለያየ ግዜ በግለሰቦችም በድርጅቶችም የተባለና ከመባል ያላለፈ ነው፡፡ ከፖለቲካው መድረክ ውጪም ያሉ በጽሁፍም በንግግርም ሀሳብ የሰጡበት ነው፡፡ ምንግዜም በኢትጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ በቀዳሚነት የሚወሳው  ቅንጅት በምርጫ 97 ማንፌስቶው ውስጥ  “በሐገሪቱ ታሪክ ውስጥ እንደ መጥፎ ገጽታ የሚታዩ የእርስ በእርስ ግጭቶችም ደም ያፋሰሱ ጦርነቶችና እልቂቶችም በተለያዩ ምክንያቶች ተከስተዋል፡፡በሀገራችን የሚመሰረተው ዴሞክራሲያዊ ሥርዐት በማይናወጥ ዴሞክራሲያዊ መሰረት ላይ መገንባት  ካለበት የእስካሁኑ የጥላቻ የበቀልና ያለመተማመን ምዕራፍ ተዘግቶ ለተከታይ ትውልድ የሚዘልቅ አዲስ ምዕራፍ መከፈት ይኖርበታል፡፡ በመሆኑም እያንዳንዳችን ከራሳችን ፤ሕዝብ ከሕዝብ መንግሥት ከሕዝብ የፖለቲካ ፓርቲ ከፖለቲካ ፓርቲ ለመግባባት የሚችሉበት ብሔራዊ ዕርቀ ሰላም ከሁሉ በፊት መቅድም አለበት ብሎ ቅንጅት ይምናል፡ በማት ነበር የገለጸው፡፡
ይህን የጻፉት ሰዎች ግን ራሳቸውም አብረው መዝለቅ ሳይችሉ ቀርተው የማይሆን ሆነ፡፡  እርቅ አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን በወያኔ አባባል ለመጠቀም የህልውና ጉዳይ ነው፡፡ ስለሆነም ሀያ አራት አመት የተነገረው ይብቃና አሁን ከምር ወደ ተግባር ይገባ፡፡ ለዚህ ደግሞ ሁሉም ከራሱ ከቤቱ ከጎረቤቱ የሚጀምርበት ሁኔታ ይፈጠር፡፡ በተመሳሳይ ስም ( በአንድ ብሄር)  እየተጠሩ አንድ አይነት አላማ እየተናገሩ አራት አምስት ሆነው የቆሙ ውደ አንድ ይምጡ፤የሚችሉ የታረቁ፣የማይችሉ የአንድ ሀገር ልጅነት መግባባት ይፍጠሩ፤ ይህም የማይሆንላቸው ወያኔ ከኢትዮጵያ ህዝብ ላይ መነሳት ያለበት በመሆኑና በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ይግባቡ፡፡ ይህን ማድረግ ከተቻለ የወያኔ ምርጫ  ተገዶ ወደ እርቅ መምጣት አለያም በተባበረ ሀይል ተገፍቶ ሥልጣኑን ማጣት ይሆናል፡፡ ከወያኔ በኋላ ስልጣን በሚይዝ ሀይል ፖለቲካዊ የበቀል ርምጃ የማይጠበቅ ቢሆንም ተገዶ ከስልጣን መውረድ ብዙ ነገር ስለሚያከትል ሁለተኛውን መንገድ  ወያኔዎች ባይመርጡት ይመከራል፡፡
እኔም ለማለት ያህል አልኩት አንጂ  ተቀዋሚው ወገን ካለፈው ተምሮ ፣በወያኔ እብሪትና እኩይ ድርጊት ተማሮ ስለ እርቅ ከማውራት አለፍ ብሎ  እርቅን ከየራሱ በመጀመር  በተቀዋሞው ጎራ ሀገራዊ መግባባት ሊፈጠር ይችላል ብሎ ማሰቡ ራሱ ይከብዳል፡፡ በተቃውሞው ጎራ ይህ አንደ ተአምር የሚፈጠር ነገር ተግባራዊ ሆኖ ጠንካራ የተባበረ ሀይል መፍጠር ቢቻል ወያኔን ለእርቅ ማስገደድ ካላሆነም ከሥልጣን ለማስወገድ የሚገድ አይሆን ነበር፡፡
ወያኔ ንቀቱ የበረታው ጥፋቱ የከፋውና የሚፎክር የሚደነፋው የተቃውሞው ጎራ ምንነትና ማንነት አንደማያሰጋው ስላረጋገጠ ነው፡፡ አንባገነን ያሉትን ሀይል ያስገድዱታል አንጂ እንታረቅ እያሉ አይለምኑትም፡፡ ወያኔ ልመና አይሰማ ተቀዋሚው ለማስገደድ አይበቃ፣በዚህ መሀል ህዝብ አሻፈረኝ ብሎ ተነስቶ በየቀኑ የጥይት ሰለባ እየሆነ ነው፡፡የሚያሳዝነው ይህ የዜጎች እልቂት ለወያኔ ከቁብ ያልተቆጠረ ለተቀዋሚው ያላስመረረ መሆኑ ነው፡፡

No comments:

Post a Comment