Monday 29 February 2016

ዶ/ር ማይገነት ሽፈራው ታላቅ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ

ኢትዮጵያ ሀገራችን የሰብአዊ መብት ተሟጋች ልጇን አጣች።
በሰብአዊ መብት ተሟጋችነታቸው፣ ለሰላምና ለዲሞክራሲ መስፈን ታጋይነታቸው የሚታወቁት ዶር ማይገነት ሽፈራው ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።
Dr. Maigenet shiferaw passed away
ዶር ማይገነት ሽፈራው ስለ ሰላም የሰበኩ ያስተማሩና የጻፉ ቀንዲል ኢትዮጵያዊ ነበሩ። ድህነትና በሽታ፣ ርሐብና ስደት፣ አምባገነንትና ጦርነት እያለ የኢትዮጵያ ሴቶች መብት መከበር፣ የሰብአዊ መብት መረጋገጥ፣ ዲሞክራሲና ሰላምን ማስፈን አይቻልም በሚል እምነታቸው በጽናት ታግለው ያታገሉ የዘመናችን ጣይቱ ነበሩ። የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ፣ የመናገር የመጻፍ የመሰብሰብ የመደራጀትና በሰላማዊ መንገድ ተቃውሞን የማሰማት መሠረታዊ መብቶች እውን እንዲሆኑ እንዲሁም ለኢትዮጵያ ሕዝብ ሰብአዊ መብት መከበር፣ ለሃገራችን ሰላም፣የሃገራችን የፖለቲካ ችግር በዲሞክራሲ፣ በመቻቻልና በሰከነ ውይይት እንዲፈታ፣ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ እድሜያቸውን ሙሉ ታግለው ያታገሉ እናት፣ እህትና ወገን ነበሩ።
ዶር ማይገነት ሽፈራው (Ethiopian Women for peace and development (EWPD) ) እ.ኤ.አ. በ 1991 ዓም ከመሥራቾቹ አንዷ በመሆን ለ21 ዓመታት ያገለገሉ ሲሆን በ2012 ዓለምአቀፍ የኢትዮጵያ ሴቶች ጉባኤ ባደረገውም ተከታታይ ስብሰባ የኢትዮጵያ ሴቶች የመብት ማዕከልን (Center for Rights of Ethiopian Women (CREW) ) ሲመሠረት ሀሳቡን ከመጠንሰስ ጀምሮ በምሥረታው ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ካደረጉትና ከመሥራቾቹ አንዷ ናቸው። ከተመሠረተም በኋላ በተደጋጋሚ በመመረጥ ድርጅቱን በብቃት የመሩ የመሪነት ችሎታቸውን በተግባር ያስመሰከሩ ናቸው።
ይህ አዲስ የተወለደው የሴቶች ማዕከል የተነሳበት ዓላማና የሚታገልላቸው ጥያቄዎች የኢትዮጵያ ሴቶች የሰላምና የልማት ድርጅት (EWPD) ለ21 ዓመታት ሲታገሉላቸው ከነበሩት ዓላማዎች ጋር አንድ በመሆናቸው ተመሳሳይ ድርጅት ለየብቻ ሆኖ ኃይልና ጉልበትን ከመከፋፈል በአንድ ላይ ሆኖ ያለውን ጉልበትን አሰባስቦ ጠንክሮ ለውጤት በመሥራት የተሻለና ጠንካራ የሴቶች ድርጅት በመሆን ለኢትዮጵያ ሴቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማህበራዊ ፍትህ፣ ለሰብአዊ መብት መከበር፣ ለዲሞክራሲ መብት መስፈን እየታገሉ የሴቶችን በራስ የመተማመን አቅም ለማጎልበት እጅ ለእጅ ተያይዞ መሥራት የወቅቱ ቁልፍ መፍትሔ መሆኑን በማመን ለ21 ዓመት በጽናት የቆዬውን የኢትዮጵያ ሴቶች የሰላምና የልማት ድርጅት የሠራቸውን ሕዝባዊ ሥራዎችንና ያካበተውን የትግል ልምድ ይዞ ኢትዮጵያ ሀገራችን የሰብአዊ መብት የሚከበርባት፣ የሕግ የበላይነት የሚያብባት፣ ሰላም የሰፈነባትና የሴቶች ስብእናቸው የሚከበርባት አገር እንድትሆን በጋራ ቆሞ ለመሥራት ከኢትዮጵያ ሴቶች የመብት ማዕከል ጋር አንድ በመሆን ሲዋሃድ ዶር ማይገነት ሽፈራው ውህደቱን እውን እንዲሆን ወሳኝ ሚና ተጫውታዋል::
ዶር ማይገነት ሽፈራው የኢትዮጵያ ሴቶች ጠንካራ ተቋም እንዲኖራቸውና በሃገራቸው የፖለቲካ፣የኤኮኖሚና የማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ እንዲኖራቸው በነበራቸው ከፍተኛ አላማና ምኞት ንቃተ ህሊናቸውን ለማሳደግ የመጀመሪያው እርምጃ ሴቶች ወደ ትምህርት ቤት እንዲሄዱ እንዲማሩ የሚያበረታቱና የሚያስተምሩ ኃላፊነት የሚሰማቸው አብነታቸው ብዙዎችን የሚያነሳሳ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ሴቶችን ለመሪነት ማብቃት ለነገ የማይባል ግዴታችንና ኃላፊነታችን ነው ብለው የሚያምኑ ለዚህም ሳያሰልሱ ያስተማሩ ምርጥ መምህር ነበሩ።
የኢትዮጵያ ሴቶች የመብት ማእዕከል (CREW) መሪውን በማጣቱ የተሰማውን ከፍተኛ ኃዘን እየገለጸ ዶር ማይገነት በተውሉንን መልካም ሥራዎቻቸውንና በጎ ሀሳባቸው እየተጽናናን  የደከሙበትንና የታገሉለትን አላማና አርማ ቀጣዩ ትውልድ በማንሳት የነገይቱ ኢትዮጵያ  የሃገራችን የፖለቲካ ችግር በዲሞክራሲና በሰከን ውይይት ተፈትቶ የሴቶች መብት የሚሰፍንባት፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰብአዊ መብት የሚከበርበት፣ የመልካም አስተዳደር መሠረት የሚጥልበት እንደሚሆን ጥርጥር  አይኖረንም።
“ዞሮ ዞሮ ከቤት ኖሮ ኖሮ ከመሬት” የማይቀርበት የህይወት ጉዞ ነውና ለዶር ማይገነት የሰላም እረፍትን እንዲሆንላቸው እየጸለይን፤ እንዲሁም ለባለቤታቸው፣ ለልጆቻቸው፣ ለቤተሰቦቻቸውና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ብርታትና መጽናናትን እንመኛለን።
የኢትዮጵያ ሴቶች የመብት ማእዕከል (CREW)
የዶ/ር ማይገነት ሽፈራው  የቀብር ስነስርአት ፕሮግራም የሚካሄደው ሰኞ ፌብሩዋሪ 29 2016 ነው፡፡
የቤተክርስትያን ስነስርአት የሚፈዐመው ፡ ከ 10፡00 ኤ.ም -1፡00 ፒ.ኤም
ቦታው፡ ቅዱስ ገብርኤል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን
አድራሻ፡ 2601 Evarts St. N.E Washington DC 20018
የቀብር አገልግሎት የሚከናወነው፡ 2፡00ፒ.ኤም
የቀብር ቦታ አድራሻ፡ 9500 Riggs RD Adelphi, MD, 20783

ከቀብር ስነስርአቱ ፍፃሜ በኋላ የምሳ ፕሮግራም በቅዱስ ገብርኤል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን ተዘጋጅቷል፡፡

No comments:

Post a Comment