Wednesday 4 May 2016

የ25 አመቱ አጋጅ መሪ (ቢንያም ሙሉጌታ – ከኖርዌይ)

ቢንያም ሙሉጌታ ከኖርዌይ
ወያኔ በቆርጦ ቀጥል የቅንብር መርሁ መሰረት የህዝብን ጥያቄና እሮሮ ከሚፈልገው የበሬ ወለደ ዘገባው ጋር በማዛመድ 25 ለሚያህሉ በአምባገነናዊነት በተሞሉ አመታት በብቸኝነት
binyam mulugeta
ቢንያም ሙሉጌታ
በተቆጣጠረው የሀገሪቱ ሚዲያዎች፤ በጋዜጣ፣ በራዲዮ፣ በቴሊቪዥን፣ እና በመሳሰሉት የመገናኛ አውታሮች እውነታውን በመደበቅ ህዝብን በማስመረር ይገኛል ይህ ብቻ አይደለም በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የሚደርሰውን ወከባ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ከመገናኛ ብዙሀን አፈናው ጋር ተደምሮ በተለይም በአሁን ወቅት በተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎች ላይ እየተደረገ ያለው አሰቃቂ ድርጊት ለአለም ሁሉ በገሀድ የሚታይ የአደባባይ ሚስጢር ሆኗል።
ነጻ ፕሬስ አልያም በጥቅሉ የመገናኛ ብዙህን መድረኮች ህዝብን ከመንግስት ጋር እንዲሁም ግልፅነት በተሞላበት አካሔድ የመንግስትን አሰራር ለህዝብ እያቀበለ እያስተዋወቀ መካከለኛ በመሆን  የዜጎችን  አስተያየትና ጥያቄዎች ለሚመራው መንግስትና ለሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ማስተላለፊያ ድልድይ ነው፡፡ መንግስትና ህዝብን አገናኝ፣ አስተያየትና ብሶትን መተንፈሻ፣ መፍትሄን መቀየሻ መሳሪያ ነው ፡፡ ነጻ ሚዲያ መልካም ሀሳቦች እንዲጎለብቱ፣ መታረም ያለባቸው ደግሞ እንዲታረሙ መጠቆሚያ ብርቱ ክንድም ጭምር ነው፡፡
ህዝብ ከገዢው  ወገን ትክክለኛ እና ወቅታዊ የሆኑትን መረጃዎን ለማግኘት እጅጉን ከባድ በሆነበት፤ ሒደቶችን  ከዜጋው በመደበቅ አሊያም በመሰወር በሀገራችን ምን እየተከናወነ እንደሆነ  የመገናኛ ብዙሀን አዋቂዎች ሙያቸውን ተጠቅመው  ለመግለጥ የሚያደርጉት ሁሉ ድምፃቸው ታፍኖ ትክክለኛው  የመረጃ ምንጭ ሆነው እንዳይሰሩ በማስፈራራት፤ይልቁንም ደግሞ ታላቅ ግፍ እና ውንጀላ እየተፈፀመባቸው ጋዜጠኞቻችንን እና ፀሀፍቶች በሙሉ ከአሽባሪ ጎራ ተመድበዋል። የህትመት ውጤቶች በእንዲህ አይነት  ውንጀላ መፈረጅ በራሱ በፍርድ የሚያስጠይቅ ጉዳይ ነው።  በእርግጥም ገዢው ፓርቲ  ለፕሬሱ ሆነ ለሚዲያው እድገት መጫዎት የሚገባው የራሱ ሚና ጎልቶ መውጣት በተገባው ነበር፤ ምክንያቱም የፕሬሱ እድገት የሀገሪቱን  አሰራር ዘመናዊ፣ ግልጽና ተጠያቂነት የሰፈነበት የማድረግ ሚናው የላቀ ስለሆነ ማለት ነው፡፡
የወያኔን ከወረቀቱ የማይከብድ  ህገ-መንግስት ተብዬውን ያየነው እንደሆን   ዜጎች በአመቻቸው መንገድ ሁሉ ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን ሰጥቶ እንደገና በተግባር ግን መብቱን በአደባባይ እየጣሰ ይገኛል፡፡ ወያኔ ሌብነቱ መዝበራው ግድያውና ጭቆናው እንዲሁም በራሱ ላይ የሚቀርቡበትን ማናቸውም አይነት ትችት በመፍራት ጋዜጦችን እና መጽሔቶችን ይዘጋል፤ ያግዳል፤ ድህረ-ገጾችን ‹ብሎክ› ያደርጋል፤ እንዲሁም ጋዜጠኞችን በተደጋጋሚ ለእስርና ለእንግልት፣ አንዳንዴም ለሞት እንዲዳረጉ በማድረግ የህዝብን መረጃ በነጻነት የማግኘትን መብት በከፋ ሁኔታ እያፈነ ይገኛል፡፡
በአንድ ያደገ ሀገር ብቃት ያለው ህዝብን የሚያገለግል ሚዲያ አለ፤ ህዝብም የመረጃ ነፃነት እንዳለው ያውቃል ይህንንም የሚያስፈጽም መንግሥት አለ። በመሆኑም መንግሥት ህዝብና ሚዲያ በመቀናጀት ብቃት ያለው መረጃ ለህዝብ ያደርሳሉ። እኛ ግን ለዚህ ፈፅሞ አልታደልም!!!
ወያኔ ከሚጠቀምባቸው የማገጃ ስልቶች የመጀመሪያው “አዳዲስ ሕጎችን በማውጣት በነጻነት ሐሳብን መግለጽን መከልከል እና እንዲህ የሚያደርጉትንም ማሰር”  ነው። ሌላው ደግሞ ሰዎችን በገንዘብ በመደለል ስለ መንግሥታቱ በጎ ነገር (እንዲጽፉ፣ እንዲናገሩ፣ እንዲያሰራጩ) ማድረግ እንዲሁም አሉታዊ ሐሳብ የሚያስፋፉትን ሰዎች ድረ ገጾች በዘዴ በመስረቅ (hijacking and hacking) በስማቸው ተገቢ ያልሆነ ነገር መለጠፍ የሚለው ነው። ይህንንም ዓለም በስፋት እየተጠቀመች ያለውን  ፌስ ብክ አንድ ሰው ከአንድ በላይ አካውንት በመክፈት ብሔርን ከብሔር ጎሳን ከጎሳ በማባላት እና በማጋጨት ደርጃ ወያኔ በዚህ ተልካሻ ስራ ተጠምዶ እንዳለ ግልፅ ነው። ይህም ድርጊት ተግባራዊ የሚሆንበት ወጪ የሚገኝውም ከደሀው  ሕዝቡ  በተነጠቀ ገንዘብ ነው። ማንነታቸው የማይታወቁ ሰዎችን በኢንተርኔት ላይ በማሰማራት የተለያዩ ደጋፊ ሐሳቦችን ማሰራጨት፣ የኢንተርኔት የውይይት አቅጣጫዎችን ማስቀየር፣ ተቃዋሚዎችን በተለያየ መንገድ ማዋረድ እና ክብራቸውን መንካት፣ ስለ ተቃዋሚዎች መሠረት የለሽ አሉባልታዎችን በመንዛት በአደባባይ ስለ ኢትዮጵያቸው እየታገሉ ያሉትን ስም ማበላሸት የወያኔ ዋነኛ እንቅስቃሴ ነው። ይህም ከፍርሀት የሚመጣ መሆኑን ሁሉም ይስማማበትል።
ወያኔ ከ20 ሚሊዩን ህዝብ በላይ  ተርቦ እህል እና ሌሎችም የልብስ የመጠለያ እንዲሁም የመድሀኒት እርዳታ ለማድረግ መረባረብ ሲገባው ከሀዲዎችን ቀጥሮ ለዚህ ሀገር በታኝ ተልዕኮው ማሰማራቱ ምን ያህል ስግብግብ እና ከፋፋይ መሆኑን በግልፅ የሚያሳይ ነው። በኢትዮጵያ ህዝብ ገንዘብ  ከሚሠሩት አፈና ባሻገር የማይደግፏቸውን ጦማርያን፣ የሚዲያ ተቋማት እና የፖለቲካ ፓርቲዎች የኢንተርኔት አድራሻዎች ማለትም ፌስቡክና ትዊተሮችን፣ ድረ ገጾችንና ብሎጎችን በመመዝበርም ይታወቃሉ። ወደ ተቃዋሚዎቻቸው የኢንተርኔት አድራሻዎች ሰብረው በመግባት የማይፈልጉትን ዘገባ፣ ዜና፣ ሐተታ ይለውጣሉ፤ የድረ ገጾቹን ባለቤቶች ሙያዊ ክብር ለማዋረድ እና ተቀባይነት ለማሳጣት የማይሆን ነገር ይለጥፋሉ፤ የሚለዋወጧቸውን ኢ-ሜይሎች ያነብባሉ፤ በክስ ወቅትም ለፍርድ ቤት በማስረጃነት የሚቀርቡት በተፈበረኩ የሀሰት ሰነዶች ምክንያት ደብዛቸው የጠፉ ምሁራን እጅግ ብዙ ናቸው። ይህንንም በመፍራት እና በመሸሽ በተገኘው አጋጣሚ ከሀገር ተሰደው በየበረሀውና በባህርም ሰጥመው የቀሩ ዜጎቻችንን ስናስብ በእጅጉ እናዝናለን። ከወያኔ አጋችነት እና አፋኝነት የተነሳ በዓለም ሁሉ የኢትዮጵያውያን አንገት እንዲደፋም ተደርጓል። ይህም የሚያሳየው ኢትዮጵያ ለዜጋ መብት ብሎም  እድገት የቆመ እና የሚታገል መሪ እንደሌላት ያስረዳል።
አጋጁ ማገድ ማንነቱ ነውና ሁሉን ያስራል ሲያሻው ለፖለቲካው መሰሪነት ሲል ይፈታል። በኢትዩጵያ ያልታገደ የለም። ለወያኔ እንቅፋት የሆነ ሁሉ ይያዛል፤ ብዙ የወንበዴ ብዕሮች ለሆዳቸው ያደሩቱ የፈራረሰውን ስርዐት ለመጠጋገን ቢሞክሩም እውነት ሁልጊዜም ትረታለችና ኢትዮጵያን ለ25 ዓመታት የሚመራው አጋጁ መሪ በኢትዮጵያውያን የተባበረ ክንድ ይገረሰሳል።
ኢትዩጵያ ለዘላለም ትኑር!!!

No comments:

Post a Comment