Wednesday 4 May 2016

የላብ አደሮች ቀን ለኛ በተለይ ለሴቶች ምናችን ነው? (አርሴማ መድህኑ – ኦስሎ ኖርዌ)

አርሴማ መድህኑ – ኦስሎ ኖርዌ
ካፒታሊስት አገሮች አንድ የቆየና ጊዜ ያነኩዋኮተው አባባል አላቸው። ይህንን አባባል ያስታወሰኝ ዛሬ እዚህ ያሰባሰበን ” የላብ አደሮች ቀን” ነው። ይቅርታ ይደረግልኝ ” ወይንም የዓለም የወዛደሮች ቀን” ኢትዮጵያችንን ጨምሮ መሆኑ ነው። ያው እንግዲህ የዚሁ ዓለም አካል በመሆናችን !!
አባባሉ እንዲህ ነው። “በካፒታሊስት ስርዓት ውስጥ ሰራተኛ የስርዓቱ ባሪያ ነው። ሴት ደግሞ የባሪያ ባርያ ናት” ይህን አባባል ኢህአዴግ ወደ ሚገዛት አገራችን ህወሃታዊ ቁዋንቁዋ ስንመልሰው ” በጥቅሉ የ ላብ አደሮች የህወሃት ባሪያዎች ናቸው። ሴቶች ደግሞ የባሪያ ባሪያዎች ናቸው” እንግዲህ ኢህአዴግ በጥቅሉ የህወሃት ባሪያ ድርጅት ከሆነ አባባሉ መሻሻያ ሊደረግበት ግድ ነው። ሲሻሻል ” ኢህአዴግ የህወሃት ባሪያ ከሆን ሁሉም “ላብ አደሮች የህወሃት ባሮች ናቸው። ሴቶቹ ደግሞ ይበልጥ ባሮች ናቸው”
በአገራችን ላብ አደሮች አሉ።ላብ አደሮቹ በሙሉ አምነውም ይሁን ሳያምኑ ኢህአዴግና አፍቃሪ ህወሃት ናቸው። በድንገት በተስፈነጠሩት የህወሃት የነገር አባት አባባል ” በመርህ ደረጃ” ሁሉም ሰራተኛ የ “ተጠረነፈ” ካልሆነ በስተቀር ” ላብ አደር ” የሚለውን ክብር አያገኝም። ስለዚህ ላብ አደር ለመሆን ቅድሚያ ህወሃትን የግል አምልኮ አድርጎ መቀበል ግድ ነው። አለያ ስራ አይታሰብም። ኑሮም ገደል ነው። ካብራክ የወጡ ልጆችን አቃምሶ ማሳደርና ማስተማር ህልም ይሆናል።
ባገራችን ነጻ ማህበር በሎ ነገር የለም። ነጻ ሆኖ የመደራጀት ጭላንጭል አይታይም። ህወሃት ባርኮና መርቆ፣ መሪ ሰይሞና መተዳደሪያ ደንብ አርቅቆ ያላቁዋቁዋመው ድርጅት ይፈረሳል። ተለጣፊ ተስይሞለት በፍርድ ቢት ሙዋምቶ እንዲከስም ይደረጋል። በዚህ ሃቅ መሰረት ላብ አደሮች ኢትዮጵያ ውስጥ ማህበር የላቸውም። እና በዛሬው ቀን አገራቸው ውስጥ በነጻነት መደራጀትና ጥቅማቸውን ማስከበር ያልቻሉ ላብ አደሮች የዓለም የወዛደሮች ቀን ምናቸው ነው? እስኪ ከሴቶች ጋር ላገናኘው።
ሴቶች በፐሮቶኮል ስምምነት ወደ አረብ አገራት እየተሻገሩ ሲደፈሩ፣ ሲንገላቱ፣ ከፎቅ ላይ ሲወረወሩ፣ በየጎዳናው ሲጎተቱ …….. መስማትና ማየት የተለመደ ነው። በረሃና ባህር የበላቸውን ቤት ይቁጠራቸው። ራስን መግቦ ለማሳደር አለመቻል በሚፈጥረው የስነልቦና ህመም፣ ህወሃትን አምለኮ አድርገው ያለመቀበል ጣጣ፣ ድህነት፣ ቅጥ ያጣው ብሔርን መሰረት ያደረገ አድልዎና የፖለቲካው ውል አልባ መሆን አንድ ላይ ተዳምሮ በተለይም ሴቶችን ክፉኛ ተጎጂ አድርጉዋቸዋል።
ለዚህ ነው ይህ ታላቅ ቀን በውስጡ በያዛቸው ፈሬዎች ሲለካ ” ሚያዝያ 23 ለኔ ምኔ ነው ?” ያልኩት!! አዎ መሳሪያ በያዙበት ወቅት ሲሞካሹ የነበሩትን የራሱን ሴት የበረሃ አባላት የበላ ህወሃት ለሌሎች ሴቶች ዜጎች ይራራል ማለት ህልም ነው። እናም በፕሮቶኮል ስምምነት ለአረብ አገራት ባርነት የሸጣቸውን ሴት ዜጎችን እያሰብን፣ ተሽጠውም የት ደረሱ ሳይባሉ፣ ከዓለም የስራተኛ ህግ ውጪ የሚበዘበዙ ሴቶች ጥሪ ወደ ጎን በሚባልበት ስርዓት ውስጥ ሆኖ ” የዓለም የወዛደሮች ቀን” ን ማክበር ፋይዳው አይታየኝም። እንደውም ስላቅ ነው። ፍሬዎቹ የደረቁበት ክብረ በአል እንደ ” ጣኦት አምልኮ ” ድንጋይ ስር እንደመርመጥመጥ ነው።
በኦሮሚያ ሴት እህቶችና እናቶች እስረኛ የጥፋባትን በማፈላለግ ላይ ናቸው። የተቀሩትም ስንቅ አመላላሽ ናቸው። እርም ያወጡም አምጦ መውለድን እየረገሙ ነው። በሰሜን የማንነት ጥያቄ ሃጢያት ሆኖ እናትና እህቶችን ሃዘን ደረት እያስደቃቸው ነው። በሶማሌ፣ በአፋር፣ በደቡብ ኢትዮጰያ እንዲሁ የሴቶች ችግር አሳሳቢና ህሊናን የሚወጋ ነው። በጋምቤላ የችግሩ ገፈት ቀማሾች ሴቶች ናቸው። ራሱ ህወሃት ይህን ሲነግረን አላፈረም። በዚህ ሁሉ ላይ ችጋር እየጠበሰን ነው። ችግሩ ተደምሮ የት እንደሚያደርሰን ሲታሰብ ቀውስ እንጂ መፍትሔ አይታይም። ግና ኢትዮጵያ የወላድ መካን አይደለችምና ተስፋ አለን።

No comments:

Post a Comment