ኢንጂነር ግዛቸው ሺፈራው ከሁለት ዓመታት የፖለቲካ እረፍት በኋላ የአንድነት ፓርቲ አመራር ሆነው እንዲሰየሙ ጥሪ ሲደረግላቸው ጥሪውን የተቀበሉት
‹‹ወጣቶችን ለአመራርነት ለማብቃት››
ከሚል ውስጣዊ ቅንነት ጋር እንደነበር መናገራቸው አይዘነጋም፡፡ ኢንጂነሩ ከዶክተር ነጋሶ የተረከቡት ፓርቲ ከመኢአድ ጋር የጀመረውን የውህደት ድርድር በማስቀጠልና ተቃዋሚዎች እየተዋሃዱ አንድ አቢይ ተቃዋሚ ፓርቲ እንዲመሰርቱ በመርህ ደረጃ ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡
በእኔ እምነት ኢንጂነሩ ፓርቲውን ለመምራት የቀረበላቸውን ጥያቄ የተቀበሉበት ተገቢነት የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ የደረሰበት ወቅት ከፊታቸው ተደቅኗል፡፡ኢንጂነሩን ለመረከብ አዲስ ፊት የሆነውና በብዙ የአንድነት እንቅስቃሴዎች የጀርባ አጥንትና ሞተር ሆኖ የቆየው በላይ ፈቃዱ ራሱን ዕጩ በማድረግ አቅርቧል፡፡
አንድነትን የአዛውንቶች ክበብ አድርገው ለሚመለከቱ የበላይ ለፕሬዘዳንትነት ራሱን በዕጩነት ማቅረብ አንድነትን የአዛውንቶች ክበብ በማድረግ ይተቹት ለነበሩ ሁሉ ፓርቲው አዲስ ጉልበት እንዳለውና መካን አለመሆኑን ያሳይበታል፡፡ከበላይ በወጣትነት የዕድሜ ክልል ከመገኘት በተጨማሪ አንድነት ወጣት ሲል ዕድሜ ላይ ብቻ የተሰፋ አለመሆኑን ወጣትነት ለአንድነት ከአዲስ የትግል መንፈስ፣ከአዲስ አስተሳሰብና ፖለቲካው ከሚፈልገው ዘመናዊነት ጋር የተቆራኘ መሆኑን ለማሳየት በላይ ፈቃዱ ትክክለኛው ማሳያ ይሆንለታል፡፡
ከቀጣዩ ዓመት ምርጫ አንጻር ቀጣዩ ዓመት አገር አቀፍ ምርጫ የሚከናወንበት መሆኑም ለሚፈጠረው ውህድ ፓርቲ ትልቅ የፈተና እና የትግል ጊዜ ይሆናል፡፡በዚህ ወቅት አባላት ከምርጫው ጋር የተያያዘ አጠራጣሪ ተሞክሮ የሌለው መሪ ማግኘት ይኖርባቸዋል፡፡በዚህ ረገድ አንድነት ላወጣው የስትራቴጂክ እቅድ ዝግጅት ከፍተኛ አስተዋእጾ ያበረከተው በላይ ውህዱ ፓርቲ ሊከተለው በሚገባው የትግል ስትራቴጂ ዙሪያ በተመሳሳይ መልኩ እምቅ የፖለቲካ አቅሙን በማውጣት አገልግሎቱን ሊያበረክት ይችላል፡፡
በላይ ለመኢአድ አባላት አዲስ መሆኑ ኢንጂነር ግዛቸው ከመኢአድ የወጡ በመሆናቸውም በእርሳቸው አመራርነት ዙሪያ በመኢአድ ውስጥ ጥያቄና ተቃውሞ የሚኖራቸው ሰዎች አይኖሩም በማለት መገመት የዋህነት ብቻ ሊሆን ይችላል፡፡በላይ ፈቃዱን የመኢአድ አባላትና አመራሮች የሚያውቁት ከውህደት ኮሚቴው ጋር በቅርበት ሲሰራ በመሆኑ ለእርሱ ድምጽ የሚሰጡበት ዕድል እንደሚኖር መገመት አያዳግትም፡፡
ከሌሎች ፓርቲዎች አንጻርሰማያዊ ፓርቲ እንዲመሰረት ገፊ ምክንያት የሆኑ ሰበዞች የሚመዘዙትና ማጠንጠኛ የሆኑት ኢንጂነር ግዛቸው ናቸው፡፡ሰማያዊ ሲመሰረት የእኛ ጥያቄ የመርህ ይከበር እንጂ ፓርቲ የመመስረት አይደለም በማለትም ከሰማያዊ መስራቾች ተርታ ራሳቸውን ያወጡ አባላትም ግዛቸው ተመልሰው መንበሩን በመረከባቸው ደስተኞች አይመስሉም፡፡እነዚህን ሀይሎች በውህደትና በእርቅ ወደ ፓርቲው ለመመለስ አልያም በአብሮነት ለመስራት ከበላይ የተሻለ ስለመገኘቱ ጥርጣሬ አለኝ፡፡
No comments:
Post a Comment