Friday 1 August 2014

ትግሉን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ጠንካራ መሪ ማውጣት የወቅቱ አንገንጋቢ ጥያቄ ነው!!! የአንድነት ቦስተን ድጋፍ ድርጅት

የአንድነት ቦስተን ድጋፍ ድርጅት፣ ለአመታት አገር ቤት የሚደረገዉን ሰላማዊ ትግል የሚደግፍ ድርጅት እንደ መሆኑ፣ በቅርቡ በአንድነትና በመኢአድ የሚደረገዉን የዉህደት እንቅስቃሴ በደስታና በጉጉት እየተከታተለው ነው። የአመራር አባላትን ለመምረጥ የሚደረገዉ አስደሳች ዴሞክራሲያዊ ዉይይትና ቅስቀሳ ፣ አንድነት ምን ያህል የዲሞክራሲ ባህል እያዳበረ እንዳለ አመላካች ከመሆኑም በተጨማሪም ያኮራን ነገር ነው።
የእጩ ፕሬዘዳንት ምርጫ ላይ ድምጽ የሚሰጡትና የሚወስኑት፣ አገር ቤት ያሉ፣ ትልቅ ዋጋ እየከፈሉ ያሉ ጀግኖች ወገኖቻችን ናቸው። እንደዚያም ሆኖ ግን ፣ አንድነት የሕዝብ እንደመሆኑ ፣ የአንድነት ቦስተን የድጋፍ ድርጅት የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት፣ ረቡዕ ጁላይ 30፣ 2014 ዓ. ም በተጠራ ስብሰባ፣ ሰፊ እና ጥልቅ ውይይት ካደረጉ በኋላ፣ ድጋፍ ማህበሩ እንደ አንድነት ደጋፊ፣ ያለውን ሐሳብ በማጋራት፣ የዲሞክራሲያዊ ሂደቱ አካል መሆኑ ጠቃሚ እንደሆነ በመገንዘብ፣ ከዚህ የሚቀጥለውን መግለጫ አውጥቷል።
1ኛ. የአንድነት እና መኢአድ ውህደትን አስመልክቶ የአንድነት ፓርቲ ፤ ፓርቲውን ወክሎ የሚወዳደር እጩ ተወዳዳሪዎችን በመመዝገብ እና ለሕዝብ ይፋ በማድረጉ ፓርቲው ምን ያህል ዲሞክራሲያዊ እና ግልጽ ምርጫ እያደረገ ያለ መሆኑን የሚያሳይ ፤ ሊበረታታ የሚገባው በመሆኑ አሁንም በተለይ በውጭም ሆነ በአገር ውስጥ ያሉ ደጋፊዎች እና በምርጫው የሚሳተፉ የፓርቲው ተወካዮች የበለጠ ሰለ እጩዎች ግንዛቤ እንዲኖራቸው መድረክ በማዘጋጀት የበለጠ እንዲተዋወቁ ቢደረግ የተሻለ እንደሚሆን ከመጠቆም አናልፍም።
2ኛ. በአንድነት በኩል እጩ ፕሬዘዳንቶችን አስመልክቶ በፓርቲው ክርክር ተደርጎ፤ እጩ ፕሬዘዳንቶቹ ወደ ጠቅላላ ጉባዔ ሄደው ከሦስቱ አንዱ እንዲመረጥ በዴሞክራሲያዊ መንገድ በድምፅ የተወሰነ ሲሆን ፤ በፓርቲው እጩ ሆነው ለውድድር የቀረቡት እጩ ፕሬዘዳንቶች
1. ኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራው
2. አቶ በላይ ፍቃዱ
3. አቶ ትዕግስቱ አወሉ መሆናቸውን ፓርቲው ይፋ አድርጓል፤ ይህም ዲሞክራሲያዊ አሰራር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ሙሉ እምነታችን ነው፤
3ኛ. አንድነት ካቀረባቸው ሦስት ጠንካራ እጩዎች መካከል የጠቅላላ ጉባዔ ተሳታፊው አንዱን እጩ ፕሬዝዳንት አድርጎ በዴሞክራሲያዊ መንገድ ይመርጣል፤ በዚሁ መስረት ኢንጅነር ግዛቸው ሽፈራው፤ ፓርቲውን ለረጅም ጊዜ በምክትል ፕሬዘዳንት እና ተጠባባቂ ፕሬዘዳንት፤ እንዲሁም አሁን በድጋሚ ፕሬዘዳንት በመሆን ለፓርቲው እዚህ ደረጃ መድረስ ትልቅ አስተዋጻኦ ማድርጋቸው ግልጽ ነው፤ በተጨማሪም ‹‹ወጣቶችን ለአመራርነት ለማብቃት›› ለመስራት እንደሚጥሩ መናገራቸው የሚታወስ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት በርካታ ወጣቶች በፓርቲው ከፍተኛ አመራር ላይ ይገኛሉ፤ ከነዚህም ወጣቶች አንዱ አቶ በላይ ፈቃዱ፣ የአንድነት ምክትል ፕሬዘዳንት፤ የፍኖተ ነጻነት ኤዲቶሪያል ቦርድ ስብሳቢ ሲሆኑ፣ ለአመታት ፓርቲው እዚህ ደረጃ እንዲደርስ ከፍተኛ ድርሻ ይወጡ የነበሩ እጩ ተወዳዳሪ ናቸው። አቶ በላይ ካላቸው የስራ ልምድ እና አገልግሎት፣ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር ባሉ የአንድነት ደጋፊዎች ዘንድ፣ በተለይ በወጣቱ አካባቢ፣ ያላቸው ተቀባይነት፣ ትግሉን ወደ ሕዝቡ ለማውርድ የተጀመረውን እንቅስቃሴ ፣ ትርጉም ወዳለው ደረጃ ከፍ ያደርጉታል የሚል እምነት አለን። በአሁኑ ሰዓት ተበታትነው የሚገኙትን የተቃዋሚ ፓርቲዎችን በማሰባሰብ፣ ወደ ውህደት ወይም በቅርብ ተባብሮ በመስራት ደረጃ ትልቅ ለውጥ ሊያመጡ ይችላሉ ተብለው የሚገመቱ፣ በሌሎች የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችም ዘንድ ከበሬታ ያላቸው መሪ ናቸው። አቶ በላይ በተለያየ ጊዜያት ለውጭው ማህበረስብ የሚያደርጓቸውን ውይይቶች በአንክሮት ስንከታትለው የነበረ ሲሆን ፣ በሚሊዮኖች ድምጽ ለነጻነት እንቅስቃሴ፣ ሐሳቡን ከማመንጨት ጀመሮ፣ በግንባር ቀደምትነት እንቅስቃሴዉን እየመሩ ያሉ፣ ብሩህ ራእይ ያላቸው፣ ለፓርቲው ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያም መሪነት ተስፋ የሚጣልባቸው ወጣት አመራር ናቸው። በተለይ በአሁኑ ወቅት፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጠረውን ውስብስብ ችግሮችን በሚገባ የሚረዱ እና መፍትሄ በመፈለግ አገሪቷ ከገባችበት ማጥ፣ በቀላሉ ለማውጣት ይችላሉ ከሚባሉ መሪዎች መካከል አንዱ ናቸው ብለን እናምናለን፡፡

በመሆኑም፣ የቦስተን አንድነት ድጋፍ ድርጅት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ተወያይቶ፣ በሙሉ ድምጽ፣ አቶ በላይ ፍቃዱ ቢመረጡ ደስተኛ እንደሚሆን በአክብሮት እየገለጸ ኢንዶርስመንቱን ለአቶ በላይ በፍቃዱ ይሰጣል።
ሙሉ ባለስልጣን እና ወሳኙ አካል የሆነው የዉህዱ ፓርቲ ጠቅላላ ጉባኤ፣ ዲሞክራሲያዊና ግልጽ በሆነ መንገድ ፣ ከአቶ በላይ ዉጭ ሌላ ፕሬዘዳንት ከመረጠ፣ ድርጅታችን፣ የጉባኤውን ዉሳኔ ሙሉ ለሙሉ እንደምንቀበልና ከአዲሱ አመራር ጋር እጅ ለእጅ ተያይዘን ትግሉን እንደምንቀጥል ለማረጋገጥ እንወድለን።
አንድነት ቦስተን ድጋፍ ድርጅት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ
ቦስተን
ረቡዕ, ጁላይ 30, 2014 ዓ. ም.10523227_758965607495524_448766099872658266_n

No comments:

Post a Comment