Monday 20 October 2014

ሥልጣን ወይስ ኢቦላ? – ከአባ ኃይለጊዮርጊስ ድንቅነህ

መልካም አስተዳደር የሚመመዘንበት ዋነኛ መለኪያ ሕዝብን የሥልጣን ባለቤት ማድረግ መቻሉ ነው። በአንድ ሃገር የሕግ
የበላይነትን የሚያከብር እና የሚያስከብር ማኅበረሰብን መገንባት የሚቻለው ለድርጊቶቹ ተጠያቂነትን ያነገበ፣ የሕዝቦችን ሰብዓዊ
እና የዜግነት መብት የሚጠብቅ፣ በሕዝቦች መካከል የሚኖሩ ኤኮኖሚያዊና ትውልዳዊ ልዩነቶችን ለሃገር ሁለንተናዊ ልማት ግብዓት
አድርጎ መጠቀም የሚችል መንግሥት መፍጠር ሲቻል እነደሆነ ይታወቃል።
ኢትዮጵያ በኅብረቀለም በተመሰሉ ብሔረሰቦቿ ፣ በኃይማኖት መቻቻል በበለፀጉ ወንድማማች ሕዝቧ፣ ለዓይን በሚስብ መልክዐ
ምድሯ በአለም ትታወቅ ነበረ። ነበረ መባሉ ከላይ የተጠቀሱት መስሕቦቿ በመልካም አስተዳደር እጦት በመክሰም ላይ መሆናቸውን
ለማስገንዘብ ነው። የመልካም አስተዳደር እጦት ዋነኛ ተጠያቂው የኢሕአዴግ /ሕወሓት መንግሥት ኢትዮጵያን ከአንጡራ
የመቻቻል ባሕሏ ውጤቱ አስከፊ የሆነና ለትውልድም ሊተላለፍ ወደሚችል ሕዝባዊ ባላጋራነት እያመራት እንደሆነ መገመት
አያዳግትም:: ፈረንሣዊው ባለቅኔ ቪክቶር ሁጎ “When dictatorship is a fact, revolution becomes a right” –
አምባገነንነት እውነት በሆነበት፣ አብዮታዊነት ይሆናል መብት – እንዲል ኢሕአዴግ/ሕወሓት መንግስትነቱን ካወጀበት ጊዜ አንስቶ
የነጻነት ታጋይ ድርጅቶች ቁጥር በእጅጉ አሻቅቧል::
ኢሕአዴግ ኢትዮጵያን ለመምራት የበቃ መንግሥት ያለመሆኑን ለማስረዳት በቂ ማስረጃዎችን ማቅረበ ይቻላል::
ኢሕአዴግ/ሕወሓት ከአመሰራረቱ (ከስያሜው) ጀምሮ ለአንድነት ሳይሆን ለልዩነት የተፈጠረ ድርጅት መሆኑን “የትግራይ ሕዝቦች
ነጻ አውጪ” በሚለውና ዛሬም ድረስ አገልግሎት በሚሰጠው መጠሪያ ስሙ መገንዘብ ይቻላል:: የልዩነት አስተዳደሩን
ከሚያረጋግጡበት ማስረጃዎች በፌደራሊዝም ሥርዓት ሽፋን በብሔረሰቦች መካክል ያለመቻቻል እንዲፈጠር ማድረጉ ዋነኛው
ነው:: ኢሕአዴግ የአንድን ብሔረሰብ ቋንቋ የማይናገር፣ ትውልዱ ከብሔረሰቡ ወገን ያልሆነ ግለሰብ እንደጠላት እንዲታይና ክልሉን
በግዴታ እንዲለቅ የማስገደድ ፕሮፖጋንዳ መጠቀም ከጀመረ ቆይቷል:: ኑሮዋቸውን በቤንሻንጉል ጉምዝና በኦሮሚያ ክልል ያደረጉ
በርካታ የአማራ ተወላጆች ቀያቸውን ለቅቀው እንዲሰደዱ በተገደዱ ጊዜ በዝምታ መመልከቱን እንደምሳሌ ማንሳት ይቻላል::
በጋምቤላ ክልልም የአካባቢውን ሕዝብ በማፈናቀል ለም መሬቱን ለኢሕአዴግ/ሕወሓት ከፍተኛ አባላት በመስጠት ደኑን
በመመንጠር የእንጨት ከሰል ንግድ እንዲሰማሩ ማድረጉን የጋምቤላ ሰብዓዊ መብት ተከራካሪው አቶ ኦባንግ ሜቶ በማስረጃ
ማቅረባቸው አይዘነጋም::
ኢሕአዴግ/ሕወሓት በኃይማኖት ተቋማት ውስጥ ቀጥተኛ ተጽዕኖ መፍጠር የጀመረው ከሁለት አስርተ አመታት ጀምሮ ነው::
በሕገ-መንግስቱ አንቀጽ 11 የመንግሥትና የኃይማኖት መለያየትን በሚመለከት የቀረቡትን፣ ማለትም:
1ኛ. መንግሥትና ኃይማኖት የተለያዩ ናቸው
2ኛ. መንግሥታዊ ኃይማኖት አይኖርም
3ኛ. መንግሥት በኃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም፣ ኃይማኖትም በመንግሥት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም
የሚሉትን ሕግጋት በመተላለፍ የኃይማኖት መሪዎችን የሚሽርና የሚሾም፣ ኃይማኖታዊ ትምህርቶች በሳንሱር ተመርጠው እንዲቀሩ
የሚያደርግ ሥርዓትን በመዘርጋት ምዕመኑን ከኃይማኖት መሪዎቹ ጋር እንዲጋጭ፣ በተቋማቱም አስከፊ ልዩነቶች እንዲሰፍን
አድርጓል:: አመራሩ ኢትዮጵያ በቁጥር ከፍተኛ የሕሊና እስረኞች ከሚገኙባቸው ሃገራት ተርታ እንድትመደብ አድርጓታል::
ከ’ሽብርተኛ’ነት ጋር በተያያዘ የታሰሩትን 9 ወጣት ጦማርያን አስመልክቶ መንግሥቱ በሂውማን ራይትስ ዎች (Human Rights
Watch) አገላለጽ በገዛ ራሱ ሕገ-መንግሥትና በፍርድ ሥርዓቱ ላይ የሚሳለቅ እንደሆነ ተዘግቧል::
የግንቦት 7 ንቅናቄ ዋና ጸሐፊ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በቅርቡ በኢህአዴግ የጸጥታ ሃይሎችና በየመን መንግሥት የጋራ ሴራ መያ’ዝና
ለከፍተኛ እንግልት መዳረግ የሥርዓቱ ደባ መረብ ከሃገር ውጪም እንደተዘረጋ ያስገነዝባል:: በተያያዥ ድንበር አዋሳኝ በሆኑት
የሱዳን፣ የጅቡቲና የኬንያ መንግስታት ከገዢው የኢህአዴግ መንግሥት ጋር በመመሳጠር በየሃገራቱ ከግፍ አገዛዝ ሸሽተው የመጡ
ጥገኞችን አሳልፎ በመስጠት የዕኩይ ምግባርን ተስቦ ልክ እንደ ተውሳኩ የኢቦላ በሽታ ሁሉ ተቋዳሽ አድርጓቸዋል::
ስለዚህ ይህ ሥልጣን ነው ወይስ ኢቦላ?
በመጨረሻም የኢትዮጵያዊነትን ጸጋና ክብር ለመመለስ ዜጎችንም ከመልካም አስተዳደር እጦት ለመታደግ ሁላችንም የበኩላችንን
አስተዋጽኦ ማድረግ አለብን ብዬ አምናለሁ:: የቀድሞው የአሜሪካን ፕሬዝዳንት ጆን.ኤፍ.ኬኔዲ “Those who make
peaceful revolution impossible will make violent revolution inevitable” – ሰላማዊ ትግልን የሚከለክሉ
ሁሉ ኃይላዊ አብዮትን አይቀሬ ያደርጋሉ – እንዲል ማንነታችን ለመመለስ የሚያስከፍለውን መስዋዕትነት ሁሉ ለመክፈል ዝግጁ
እንሁን እላለሁ:: –
ከአባ ኃይለጊዮርጊስ ድንቅነህ (Abba Haile Georgis Dinkneh – Wetzlar – Germany) – ኦክቶበር 14 ቀን 2014

No comments:

Post a Comment