Saturday, 25 October 2014

ለቅድስት ቤተ-ክርስቲያን መልካም ሥራ የሚሠሩ ማኅበራትን ለማፍረስ መሞከር ቅድስት ቤተ-ክርስቲያንን ለማፍረስ እንደመሞከር ይቆጠራል


  • 284
     
    Share
መግለጫ ፎቶ
ጥቅምት 10 ቀን 2007 ዓ.ም.
ቁጥር : 10102014/0038
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሃዱ አምላክ አሜን
ለቅድስት ቤተ-ክርስቲያን መልካም ሥራ የሚሠሩ ማኅበራትን ለማፍረስ መሞከር ቅድስት ቤተ-ክርስቲያንን ለማፍረስ እንደመሞከር  ይቆጠራል::
ለቅድስት ቤተ-ክርስቲያናችን ሕልውና ዘወትር በትጋት በማገልገል ላይ የሚገኘውን ማኅበረ-ቅዱሳንን ለማፍረስ እየተካሔደ ያለውን እንቅስቃሴ በመቃወም ከዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን እምነት ተከታዮች አንድነት የወጣ መግለጫ
“ነገር ግን ሐሰተኞች ነቢያት ደግሞ በሕዝቡ መካከል ነበሩ እንዲሁም በመካከላችሁ ደግሞ ሐሰተኞች አስተማሪዎች ይሆናሉ:: እነርሱም የዋጃቸውን ጌታ እንኳ ክደው የሚፈጥንን ጥፋት በራሳቸው ላይ እየሳቡ የሚያጠፋ ኑፋቄን አሹልከው ያገባሉ ብዙዎችም በመዳራታቸው ይከተሏቸዋል:: በእነርሱም ጠንቅ የእውነት መንገድ ይሰደባል:: ገንዘብንም በመመኘት በተፈጠረ ነገር ይረቡባችኋል ፍርዳቸውም ከጥንት ጀምሮ አይዘገይም ጥፋታቸውም አይዘገይም::” ፪ኛ ጴጥሮስ  ፪ ፥ ፩ – ፫

ጥንታዊት ታሪካዊትና ሐዋርያዊት የሆነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከተመሰረተችበት ጊዜ አንስቶ ፈተና ርቋት አያውቅም:: ለዘመናት በተለያዩ ኃይሎች የተለያዩ ፈተናዎችን ስታስተናግድ የቆየች ሲሆን ሁሉንም በጠባቂዋ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ተቋቁማ ካለንበት ጊዜ ደርሳለች:: አሁንም በውስጥና በውጪ ጠላቶቿ ፈተና እየተፈራረቀባት ትገኛለች:: በተለይም ኢሕአዴግ በትረ ሥልጣኑን ከተቆጣጠረበት ጊዜ ጀምሮ በመንግሥት የሚደርስባት ጫናና ተጽእኖ እጅግ እየበረታ የመጣ ሲሆን በአማኞቿ ላይ የሚፈጸመው ስቃይና እንግልት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው:: ጉዳዩን በጥልቀት ለሚመረምር ሰው የቤተ ክርስቲያኒቱ የውጪና የውስጥ ጠላቶች ከረጅም ጊዜ ጀምሮ የሚደክሙበትን ቤተ ክርስቲያኒቱን የማሽመድመድና ከተቻለም የማፍረስ ሕልም ተግባራዊ ለማድረግ የሚሰራ ይመስላል:: ሆኖም እዚህ ላይ መረዳት የሚያስፈልገው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የተመሰረተችው በክርስቶስ ደም በመሆኑ ማንም ሊያፈርሳት አይችልም:: ይህንንም ለማወቅ የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ ፲፮ ፥ ፲፰ ማንበብ ያስፈልጋል:: ከታሪክም እንደምንረዳው በግራኝ መሐመድና ዮዲት ጉዲትም ብዙ ደክመው ቤተ_ክርስቲያኒቱን ማጥፋት እንዳልቻሉ ወደኋላ ሄዶ ታሪክን መመርመር ይገባል:: ይህንንም በማየት በቤተክርስቲያኒቱ ላይ የጥፋት በትሮቻቸውን ያነሱት ኃይሎች በሙሉ እጆቻቸውን ከቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ ማንሳት ጠቃሚ ነው እንመክራለን፥ ምክንያቱም ትግሉ ሲጥል እንጂ ሲታገል ከማይታየው ኃያል የምድርንና የሰማይ ፈጣሪ አምላክ ጋር ነውና::
በተደጋጋሚ እንደሚታየውና እንደሚሰማው የመንግስት ባለሥልጣናት ከእነርሱ በላይ የሁሉ ፈጣሪ ልዑል እግዚአብሔር መኖሩን ባለማመን ይሁን ባለማወቅ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖታችንና በተከታዮቿ ላይ ብዙ በደልና ግፍ ሲፈጽሙ ቅንጣት ያህል ሃፍረትና ፍርሃት አይሰማቸውም:: በሥልጣን ወንበሩ ላይ ያስቀመጣቸው ሁሉን ማድረግ የሚችል ኤልሻዳይ እግዚአብሔር መሆኑን ባለመገንዘብም ዘወትር በእብሪትና በትዕቢት የተሞሉ በርካታ ነገሮችን ሲናገሩ ይሰማሉ::
ለምሳሌ ያህል “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአማራ ዋሻ ናት”፤ “የአማራንና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን አከርካሪ ሰብረናል” ፤ “አደረጃጀታችንን ስንጨርስ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ አማኞችም ማዕተብ እናስወልቃለን”፤ የሚሉትና የመሳሰሉት ይገኙባቸዋል:: ከሚፈጽሙት በደሎች መካከልም በልማት ሰበብ አብያተ ክርስቲያናትን ማፍረስ፤ ገዳማትን መዳፈር፤ ይዞታዎችን መንጠቅ ፤ በዘርና በጎሣ በማጋጨት ክርስቲያኖችን ማፈናቀል፣ ማስገደል፣ ማሰቃየት፣ ማንገላታት ወዘተ በጉልሕ የሚጠቀሱ ናቸው::
በ፪ኛ ጴጥሮስ  ፫ ፥ ፱ ላይ ለአንዳንዶች የሚዘገይ እንደሚመስላቸው ጌታ ስለተስፋ ቃሉ አይዘገይም፤ ነገር ግን ሁሉ ወደ ንስሐ እንዲደርሱ እንጂ ማንም እንዳይጠፋ ወዶ ስለ እናንተ ይታገሳል:: ተብሎ እንደተጻፈው የሰውን ጥፋት ሳይሆን መመለስ የሚፈልገው አምላክ ለእነዚህ በሕዝብና በሃይማኖታችን ላይ በደል ለሚፈጽሙ ባለሥልጣናት የንስሐ ጊዜ ቢሰጣቸውና ምልክትም ቢያሳያቸው ከክፉ ሥራቸው ከመመለስ ይልቅ ልባቸውን በማደንደንና ማን አለብን በማለት በጥፋት ላይ ጥፋት እየጨመሩ እንደ ፈርዖን ፈጣሪን በመገዳደር ላይ ይገኛሉ::
ሰሞኑንም በጠቅላይ ቤተ ክህነት አዳራሽ በፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ሰብሳቢነት በተካሔደው ጉባዔ ላይ በተቀናጀ ሁኔታ በማኅበረ ቅዱሳን ላይ ሲሰነዘር የነበረው ውንጀላ በገሃድ የመንግሥትን ተልዕኮ ለማስፈጸም ታቅዶ የተጠራ ፖለቲካዊ ስብሰባ መሆኑን በስብሰባው ላይ የተንጸባረቁት ሃሳቦችና አስተያየቶች የሚያሳብቁ ነበሩ:: ለማስረጃም ያህል በስብሰባው ላይ ወቀሳ ሲያቀርቡ የሚሰሙት ካህናት ተብዬ ካድሬዎች በአብዛኛው ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ይልቅ የፖለቲከኞቹን የአቶ መለስ ዜናዊንና የኢንጅነር ኃይሉ ሻውልን ንግግር እየጠቀሱና በዓለማችን ላይ በአሸባሪነታቸው የሚታወቁ ጽንፈኛ ድርጅቶችን ስም እያነሱ መናገራቸው አንዱ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ጉባዔው የተጠራው መዋቅር ሳይጠበቅና ጽሕፈት ቤታቸው ሳያውቀው መሆኑን የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ብጹዕ አቡነ ማቴዎስ መግለጻቸው ተጨማሪ ማስረጃ ነው::
ማኅበረ ቅዱሳን በእኛ ተቋምም ሆነ በሕዝበ ክርስቲያኑ ዘንድ የሚታወቀው፦
፩/ ገጠሪቱ ኢትዮጵያ ድረስ ዘልቆ በመግባት በችግር ምክንያት የተዘጉ አብያተ ክርስቲያናትን ችግራቸውን አስወግዶ በማስከፈት፤
፪/ የቤተ ክርስቲያኒቱ የዕውቀት ምንጭ የሆኑትን የአብነት ት/ቤቶችን በመርዳት፤
፫/ የቤተ-ክርስቲያኒቱ ዕንቊ የሆኑ የአብነት መምህራንንና የአብነት ተማሪዎችን የሚያስፈልጋቸውን በማሟላት፤
፬/ በቤተ-ክርስቲያኒቱ ላይ የቅሰጣ ሥራ የሚሰሩ የመናፍቃን ተላላኪዎችንና የቤተ-ክርስቲያኒቱን ሀብት የሚመዘብሩ አማሳኞችን በማጋለጥ፤
፭/ ለሀገርና ለወገን በተለይም ለቤተ-ክርስቲያን ተቆርቋሪ የሆነ መንፈሳዊነትን የተላበሰ ትውልድ በማፍራት፤
፮/ በሀገራችን የሚገኙ ጥንታዊና ታሪካዊ ገዳማትን በመንከባከብና ምዕመናን የማያውቋቸውን እንዲያውቋቸው በማድረግ፤
፯/ በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃንና በሕትመት ሥርጭቶች ስብከተ ወንጌልን በማስፋፋት ሲሆን እነዚህን ዋና ዋናዎቹን ለአብነት ጠቀስን እንጂ ማኅበሩ ቀን ከሌሊት የሚተጋባቸው ብዙ በጎ ሥራዎች እንዳሉት ለማንም የተሰወረ አይደለም::
ታዲያ ይህ ሁሉ በጎ ሥራው እየታወቀ ፍጹም ፖለቲካዊ በሆነና ማመዛዘን በጎደለው መልኩ በእውነት ላይ ያልተመረኮዘ ትችት በማቅረብ ማህበሩን ለማፍረስ መሞከሩ ብዙ ምዕመናንን ያሳዘነና ያስቆጣ ከመሆኑም በላይ ከፓትርያርኩ ጀምሮ እስከ ካህናቱ ድረስ ለያዙት ሰማያዊ ሥልጣንና ኃላፊነት የማይታመኑ አድርጓቸዋል:: ከዚህ በተጨማሪ ፓትርያሪኩም ሆኑ ካህናቱ ሊረዱት የሚገባው ዋነኛው ነገር፣ ማኅበረ ቅዱሳንን እናፈርሳለን ሲሉ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጋውን አባላቱን እና የማኅበሩ ደጋፊ የሆኑትን ምዕመናን ከቅድስት ቤተ-ቤተክርስቲያናችን እንደመግፋት እና እንደማባረር እንደሚቆጠር ሊገነዘቡት ይገባል። መንግሥትም በተደጋጋሚ እንደሚያደርገው እራሱ ያዘጋጀውን ሕገ-መንግሥት በመጣስ በሃይማኖታችን ውስጥ ገብቶ ለማተራመስ እየዳከረ በመሆኑ ሕዝበ ክርስቲያኑን ወደ አልተፈለገ አመፅ እና እንቅስቃሴ ውስጥ እንዲገባ እየገፋው እንደሆነ ሊረዱት ይገባል::
ስለዚህ የኢሕአዴግ መንግሥት ይህንን ተገንዝቦ ለቤተ-ክርስቲያኒቱ በጎ ሥራ የሚሰራውንና ከፖለቲካ ነጻ የሆነውን ማኅበር በቤተ-ክርስቲያኒቱ ውስጥ በሰገሰጋቸው ካድሬዎቹ ተጠቅሞ በእጅ አዙር ለማፍረስ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ በአስቸኳይ እንዲያቆም እያሳሰብን፤ በማንኛውም መንገድ ማኅበሩን ለማፍረስ የሚካሔደው ስውር ደባ ቤተ-ክርስቲያኒቱን ለማፍረስ የሚካሔድ ተግባር አድርገን ስለምንቆጥረው በጽኑ የምናወግዘውና የምንቃወመው መሆኑን እንገልጻለን::
በመጨረሻም የቤተ-ክርስቲያኒቱ የበላይ ጠባቂ ቅዱስ ሲኖዶስም ሆነ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ክፍሎች ሁሉ ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት በማኅበሩ ላይ የሚካሔደውን ሤራ እንዲያስቆሙ ስንጠይቅ ሕዝበ ክርስቲያንም በሙሉ በኃይማኖታችን ላይ የሚሸረበውን ስውር ደባ በአጽንዖት እንዲቃወሙና ሁላችንም አንድ ሆነን ቅድስት ቤተ-ክርስቲያናችንን እንድንጠብቅ ጥሪያችንን እናቀርባለን::
ዓለም አቀፍ የኢ/ኦ/ተ/ቤተ- ክርስቲያን እምነት ተከታዮች አንድነት
ግልባጭ
  • ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት
  • ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ
  • ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ
  • ለብፁዕ አቡነ ማቴዎስ
  • ለብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ
  • ለብፁዓን አባቶች በሙሉ

No comments:

Post a Comment