Tuesday, 21 October 2014

ሬድ ቡል”ን የመሳሰሉ ሃይል ሰጪ መጠጦች የጤና ችግር ያስከትላሉ ተባለ 

“ሬድ ቡል”ን የመሳሰሉ ሃይል ሰጪ መጠጦች በተለይ ከአልኮል መጠጥ ጋር ተደባልቀው ሲጠጡ የጤና ችግር ሊያስከትሉ እንደሚችል የዓለም ጤና ድርጅት ተመራማሪዎች አስጠነቀቁ፡፡
RedBullበአውሮፓ የተደረገ ጥናት እንዳረጋገጠው፣ ከ70 በመቶ በላይ የሚሆኑ እድሜያቸው ከ18-29 ዓመት የሚደርሱ ወጣቶች፣ እንደ “ሬድ ቡል” ያሉ ሃይል ሰጪ መጠጦችን (Energy drinks) ከአልኮል መጠጥ ጋር እየደባለቁ ይጠጣሉ፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት ጥናት እንደሚለው፤ ዋነኛው የስጋት ምንጭ በመጠጦቹ ውስጥ ያለው ከፍተኛ የካፌይን መጠን ሲሆን ይሄም ፈጣን ወይም ያልተመጣጠነ የልብ ምት፣ ከፍተኛ የደም ግፊት፣ ማስመለስ፣ ከፍተኛ የሰውነት መንቀጥቀጥና ባስ ሲልም ለሞት የሚዳርግ የልብ በሽታ… የመሳሰሉ የጤና ችግሮችን ሊያስከትል ይችላል፡፡
ካፌይን በህፃናት ላይ በጥናት የተረጋገጠ አሉታዊ ተፅአኖ እንዳለው ተመራማሪዎቹ በጥናት ሪፖርታቸው ላይ ጠቁመዋል፡፡
“የሃይል ሰጪ መጠጦች ተወዳጅነት መጨመር ያደረሰው ሙሉ ተፅእኖ ገና በቁጥር አልተቀመጠም፤ ነገር ግን ወጣቶችን ዒላማ ያደረገው የሃይል ሰጪ መጠጦች ጠንካራ የገበያ ስልት በምርቶቹ ላይ ከሚደረግ ውስንና ተለዋዋጭ ቁጥጥር ጋር ሲዳመር እነዚህ መጠጦች ለህብረተሰቡ ጉልህ የጤና ስጋት የሚሆኑበትን ድባብ ፈጥሯል” ብለዋል – ተመራማሪዎቹ፡፡
ዩሮሞኒተር ባሰፈረው መረጃ መሰረት፣ የሃይል ሰጪ መጠጦች ዓለም አቀፋዊ ሽያጭ እ.ኤ.አ በ1991 ዓ.ም ከነበረው 2.4 ቢሊዮን ፓውንድ በ2013 ዓ.ም ወደ 17.3 ቢሊዮን ፓውንድ አሻቅቧል፡፡ “ሬድ ቡል” የተባለው ሃይል ሰጪ መጠጥ በእንግሊዝ በከፍተኛ ሽያጫቸው ከሚታወቁ ለስላሳ መጠጦች በሦስተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ተጠቁሟል፡፡
አንዳንድ የቡና ዘሮች ተመሳሳይ የካፌይን መጠን ያላቸው ቢሆንም ሃይል ሰጪ መጠጦች ቀዝቃዛውን የሚጠጡ በመሆናቸው በከፍተኛ ፍጥነት የሚወሰዱ ናቸው ብሏል – ጥናቱ፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት የጥናት ቅኝት እንደሚለው፤ እስካሁን የሚታወቁት ሃይል ሰጪ መጠጦች ካላቸው የካፌይን መጠን በእጅጉ የላቀ ካፌይን የያዙ አዳዲስ ምርቶች እየተበራከቱ መጥተዋል፡፡
ሃይል ሰጪ መጠጦች ከካፌይን በተጨማሪ ጉዋራና፣ ታውሪንና ቢ ቪታሚንስ የተባሉ ንጥረነገሮችን እንደያዙ የሚናገሩት ተመራማሪዎቹ፤ ስለምንነታቸውና ከካፌይን ጋር ስላላቸው መስተጋብር ለማወቅ ተጨማሪ ምርምር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
የዓለም የጤና ድርጅት ፖሊሲን አይወክልም በተባለ የጥናት ፅሁፍ ላይ እንደተጠቆመው፣ ሃይል ሰጪ መጠጦችን ከአልኮል መጠጥ ጋር ደባልቆ በመጠጣት ጉዳት እንደሚደርስ የሚያሳዩ ማስረጃዎች እየጨመሩ መጥተዋል፡፡ የአውሮፓ የምግብ ደህንነት ባለስልጣን ጥናት፤ ከ70 በመቶ በላይ የሚሆኑ እድሜያቸው ከ18-29 የሚደርሱ ወጣቶች ሃይል ሰጪ መጠጦችን ከአልኮል ጋር ደባልቀው እንደሚጠጡ አረጋግጧል፡፡  አጥኚዎቹ እንደሚሉት፤ አልኮል ብቻውን ከመጠጣት የበለጠ ይሄኛው በጣም አደገኛ ነው፤ ምክንያቱም የስካሩ መጠን ባይቀንስም ሰዎች መስከራቸውን ለማወቅ እንዲቸገሩ ያደርጋቸዋል፡፡
ሃይል ሰጪ መጠጦች በአብዛኛው የስፖርት ብቃትን እንደሚጨምሩ እየተነገረ ቢተዋወቁም ከአካል እንቅስቃሴ ጋር ሲጣመሩ ለአደጋ ሊያጋልጡ እንደሚችሉ ጥናቱ አክሎ ገልጿል፡፡
በእነዚህ መጠጦች ውስጥ መካተት ያለበት የካፌይን መጠን ምን ያህል እንደሆነ ተመራማሪዎቹ በቁጥር ባይገልፁም በጥናት ላይ የተመሰረተ መሆን እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡
በእንግሊዝ የምግብ ጥራት መመዘኛ አጀንሲ፣ ከታህሳስ ወር ጀምሮ ከፍተኛ የካፌይን መጠን የያዙ ሃይል ሰጪ መጠጦች፣ ይሄንኑ በምርቶቻቸው ላይ እንዲጠቁሙና “ለህፃናት ወይም ለነፍሰጡር ወይም ጡት ለሚያጠቡ ሴቶች አይመከርም” የሚል ማስጠንቀቂያ እንዲያሰፍሩ ያስገድዳል ተብሏል፡፡ በግንቦር ወር ደግሞ ሉቱዋኒያ እንዲህ ያሉ መጠጦች እድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች ለሆኑ ህፃናት እንዳይሸጥ የሚያግድ ህግ በማውጣት የመጀመሪያዋ የአውሮፓ አገር ትሆናለች ተብሎ ይጠበቃል፡፡

No comments:

Post a Comment