ጌታቸው ሺፈራው
በአገራችን ከ‹‹ልማታዊ መንግስት›› እስከ ‹‹አብዮታዊ ዴሞክራሲ››፣ ከ‹‹ኪራይ ሰብሳቢነት›› እስከ ‹‹ሽብርተኝነት››፣ ከ‹‹መሃል መንገድ›› እስከ የ‹‹ጽንፍ ፖለቲካ››፣ ከ‹‹ዘረኝነት›› እስከ ‹‹ወያኔነት››፣ ከ‹‹ብሄር›› እስከ ‹‹ጎሳ›› ያልተተረጎሙ ነገር ግን ማንም እያነሳ የሚጥላቸው፣ ሊተነትናቸው የሚሞክራቸው የፖለቲካ ቃላት አሉ፡፡ እነዚህ አብዛኛዎቹ ማንም አንስቶ የሚለውሳቸው የፖለቲካ ቃላት በአብዛኛው በገዥው በኩል የተለመዱ ሲሆኑ በተቃዋሚው ጎራም ሳይቀር የሚዘወተሩ ነገር ግን ያልተተረጎሙ፣ ረጋ ብለን የማናያቸውም ናቸው፡፡
ከእነዚህ መካከል በተደጋጋሚ የሚሰማው የ‹‹ዜሮ ድምር ፖለቲካ›› የሚባለው ነው፡፡ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ተሳታፊ አሊያም ተመልካች ነን የሚሉ አካላት በተለይም ‹‹ተቀናቃኞች›› የሚሄዱበት መንገድ ትክክል አለመሆኑን ለመግለጽ ‹‹በዜሮ ድምር ፖለቲካ›› ባህላቸው ይወቅሷቸዋል፡፡ በግልጽነት ተናገርን የሚሉ ራሳቸውን አሊያም አጠቃላይ የአገራቸውን ሁኔታ ‹‹የዜሮ ድምር ፖለቲካ ባህል›› እንደተጠናወተው ይተቻሉ፣ ይተነትናሉ፣ ያማርራሉ….፡፡
እኔ እስከ ማውቀው የኢትዮጵያ ፖለቲካ የዜሮ ድምር ፖለቲካ በሚባሉበት አጋጣሚ ‹‹አይደለም›› ያለ አካል አላጋጠመኝም፡፡ ይልቁን ልዩነቱ የሚመጣው ለዚህ ‹‹ባህል›› ተጠያቂው ላይ ነው፡፡ ተቃዋሚዎቹ ገዥውን ፓርቲ አሊያም ሌሎች ተቀናቃኞቹን፣ ገዥው ደግሞ ተቃዋሚዎችን ይወቅሳሉ የፖለቲካ ባህላችን የ‹‹ዜሮ ድምር›› እንደሆነ በማይተማመኑትም መካከል ስምምነት የተደረሰበት ይመስላል፡፡ እኔ ደግሞ ለዚህ ብልሹ የፖለቲካ ባህልም አልደረስንም ባይ ነኝ፡፡
የዜሮ ድምር ፖለቲካ ተብሎ የሚጠራው ‹‹የፖለቲካ ሁኔታ›› ከእንግሊዝኛ የመጣ እንደመሆኑ ከአማርኛው ይልቅ ‹‹zero sume game›› የሚለው የእንግሊዝኛው ሀረግ ይበልጡን ይገልጸዋል፡፡ ይህ የፖለቲካ ሁኔታ የፖለቲካ ጨዋታ ነው፡፡ ጨዋታ ደግሞ ህግ፣ የመጫወቻ ሜዳ፣ ሁለትና ከዚያ በላይ ተጫዋቾች፣ ተመልካች፣ ዳኛ፣ ቢቻል ታዛቢ ያስፈልገዋል፡፡ በተጫዋቾች መካከል የተግባቡበት ግንኙነት ሊኖር የግድ ነው፡፡ ፈረንጆቹ ‹‹political game›› ወይንም እንደ አጠቃላይ ‹‹game theory›› በሚሉት የፖለቲካ ሁኔታም ተጫዋች፣ ህግ፣ ተመልካች፣ ዳኛ ከተቻለም ታዛቢ እንዳለው እናያለን፡፡ በአብዛኛው የዜሮ ድምር ፖለቲካ የሚባለው በየትኛውም የፖለቲካ ‹‹ጨዋታ›› አሸናፊና ተሸናፊ አለ ከሚል አስተሳሰብ በመነሳት ነው፡፡ አሸናፊና ተሸናፊነት በፖለቲካ መድረክ አንዳንዴ አጨቃጫቂ ቢሆንም በግልጽ የሚታዩባቸው እንደ ምርጫ አይነት መድረኮችን መግለጽ ይቻላል፡፡
ፈረንጆቹ ‹‹ጌም ቲዮሪ›› የሚባለውን ‹‹the study of mathematical models of conflict and cooperation between intelligent rational decision-makers›› ብለው ይተረጉሙታል፡፡ ‹‹የዜሮ ድምር ፖለቲካ›› የሚባለው የአማርኛው ፍችም ከመሰል የእንግሊዝኛው ትርጉም የመጣ ነው፡፡ በዚህ ትርጉም ደግሞ ‹‹የዜሮ ድምር ፖለቲካም›› በሂሳብ ስሌት፣ በታሰበበት ውሳኔ እንጂ በማንቦጫረቅና በዘፈቀደ ላይ የተመሰረተ እንዳልሆነ ነው፡፡
በ‹‹ፈረንጆቹ ትርጉም›› መሰረት የዜሮ ድምር ፖለቲካ አብላጫውን ያገኘው አካልና ያጣው አካል ተደምሮ ዜሮ የሚመጣ ከሆነ ብቻ ነው፡፡ አንዱ ያገኘውና ሌላኛው ያጣው ተደምሮ ዜሮ ይመጣል እንደማለት ነው፡፡ ይህ በሂሳብ ስሌት አንዱ 2 ሲያገኝ ሌላኛው ሁለትን ያጣል አሊያም ነጋቲቭ ሁለት ያገኛል እንደማለት ነው፡፡ በአገኘውና ያጣው ሲደመር ውጤቱ ዜሮ ይመጣል ማለት ነው፡፡
በ‹‹ፈረንጆቹ ትርጉም›› መሰረት የዜሮ ድምር ፖለቲካ አብላጫውን ያገኘው አካልና ያጣው አካል ተደምሮ ዜሮ የሚመጣ ከሆነ ብቻ ነው፡፡ አንዱ ያገኘውና ሌላኛው ያጣው ተደምሮ ዜሮ ይመጣል እንደማለት ነው፡፡ ይህ በሂሳብ ስሌት አንዱ 2 ሲያገኝ ሌላኛው ሁለትን ያጣል አሊያም ነጋቲቭ ሁለት ያገኛል እንደማለት ነው፡፡ በአገኘውና ያጣው ሲደመር ውጤቱ ዜሮ ይመጣል ማለት ነው፡፡
በአገራችን ‹‹የዜሮ ድምር ፖለቲካ›› ስንል አንዱ ሁሉንም ጠቅልሎ የሚወስድበት አሊያም ሌላኛው ሁሉንም የሚያጣበት የሚለው ትርጉም ይሰጠዋል፡፡ አንዳንዴ ደግሞ ተወያይቶ ችግርን አለመፍታት፣ ተደራድሮ አለመታረቅ፣ ተነጋግሮ አለመደማመጥ ሁሉ ‹‹ዜሮ ድምር ፖለቲካ›› እየተባለ ይጠራል፡፡ ሁሉም የሚያጣበት ፖለቲካ ተብሎ ተተረጎመ ማለት ነው፡፡ ዜሮ ሲደመር ዜሮ ያው ዜሮ እንደማለት ነው፡፡
በአብዛኛው የእኛ አገር ፖለቲካ ማንም የማያተርፍበት ፖለቲካ ነው፡፡ በተለይ ተወያይቶ ችግርን አለመፍታት፣ ተደራድሮ አለመታረቅ፣ ተነጋግሮ አለመደማመጥ፣ ተባብሮ አለመስራት፣ ተነጣጥሎም መውደቅ፣ ተባብሮም አለመተባበር ሁሉንም ሲያከስሩ ይታያል፡፡ ይህ ግን ከዋነኛው ትርጉም አንጻር የ‹‹ዜሮ ድምር ፖለቲካ›› ሊሆን አይችልም፡፡ አንዱ ያጣውና ሌላኛው ያገኘው ተደምሮ ሳይሆን ሁለቱም ምንም ያገኙ አይደሉም፡፡ ምን አልባት ‹‹አንችም ዜሮ ዜሮ፣ እኔም ዜሮ ዜሮ›› ለሆነው ለዚህ የፖለቲካ ሁኔታ ሌላ ትርጉም ያስፈልገው ይሆናል፡፡
የእንግሊዝኛው ትርጉም ‹‹አሸናፊው ያገኘው ተሸናፊው ካጣው ከበለጠ (ድምሮ ከዜሮ ይበልጣል) ወይንም አሸናፊው ያገኘው መጠን ተሸናፊው ካገኘው ካነሰ (ሁለቱ ሲደመር ከዜሮ በታች ነው የሚሆነው) ዜሮ ድምር ፖለቲካ አይደለም›› ይላል፡፡ የሁለቱ አካላት ያገኙትና ያጡት ተደምሮ ከዜሮ የሚያንስ ወይንም የሚበልጥ ከሆነ የዜሮ ድምር አይደለም ማለት ነው፡፡ አንዳንዶቹ ይበልጡን አትራፊ ሲሆኑ ሌሎቹ ደግሞ ይበልጡን ከሳሪዎች ይሆናሉ፡፡
በእርግጥ የእኛው አገር የ‹‹ፖለቲካ ጨዋታ›› ከቁጥር ስሌት፣ ከድምር ፖለቲካም የሚገባ አይደለም፡፡ የዜሮ ድምር ፖለቲካ ህግ፣ የመጫወቻ ሜዳ፣ ተጫዋቾች፣ ተመልካቾች፣ ዳኞች፣ ቢቻል ታዛቢዎች ይኖሩታል፡፡ የእኛ አገር የ‹‹ፖለቲካ ጨዋታ›› ህግ፣ ተጫዋች፣ ተመልካች፣ ዳኛ፣ ታዛቢን የሚያሟላ አይደለም፡፡ በእኛ አገር ፖለቲካ በአንድ ‹‹ጨዋታ›› የተለያየ ማሊያ ለብሶ ተጫዋች፣ ዳኛ፣ ተመልካችም፣ ታዛቢም፣ ዳኛም የሚሆነው ራሱ ገዥው ፓርቲ ነው፡፡
በአንድ አካል የበላይ ተዋናይነት የሚመራው የ‹‹ፖለቲካ ጨዋታው›› በቋሚ ህግ የሚመራ ሳይሆን ይህ ሁሉ በእጁ ሁሉ በደጁ የሆነ አካል ሲፈልግ ‹‹ጨዋታ ፈረሰ›› የሚልበት፣ ህግ ብሎ ካስቀመጠው ውጭ ጨዋታውን የሚዘውርበት፣ ተቀናቃኝ ተጫዋች ወይንም ቡድን የሚወስንበት፣ የሚያሰለጥንበት፣ የሚቀጣና የሚሸልምበት መድረክ ነው፡፡ በመሆኑም በእኛ አገር የ‹‹ዜሮ ድምር ፖለቲካ›› በሂሳብ ስሌት ማን አገኘ፣ ማን ምን ያህል አጣ፣ ተደምሮስ ስንት ይሆናል ከማለታችን በፊት ‹‹ጨዋታ››ነትን አላሟላም ማለት ነው፡፡
በመሆኑም ዜሮ ድምር ፖለቲካ ሊኖር የሚችለው (በአወንታዊም ሆነ በአሉታዊ መልኩ) ስርዓት ላበጁ፣ ስርዓቱ ምንም ይሁን ምን በዛ ስርዓት ወይንም ህግ ለሚገዙ አካላት ነው፡፡ በእርግጥ ይህ ነው የሚባል ስርዓት የሌላቸው ወይንም ብልሹ የፖለቲካ ስርዓት ላይ የመጫወቻ ሜዳቸውን የመሰረቱ አገራት ላይ በገዥነት ላይ የተቀመጡ ስርዓቶችም ከእኛዎቹ ገዥዎች የተሻሉ ወደ ‹‹ፖለቲካ ጨዋታው›› ይጠጋሉ፡፡
ለአብነት ያህል የምርጫ ቦርድ የሚባል ዳኛ፣ የምርጫ ስነ-ምግባር፣ የምርጫ ቦርድ አዋጅ፣ ህገ መንግስትና ሌሎችንም ህጎች አውጥቶ፣ ፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲኖሩ ‹‹ፈቅዶ››፣ ምርጫ የሚባል መወዳደሪያ ሜዳ እንዳለ አሳውቆ፣ ህዝብ (ተመልካች) በነጻነት እንደሚመርጥ ቃል ገብቶና በህግ አጽድቆ ይህን ሁሉ ተግባር በራሱ ከሚወጣው ኢህአዴግ ይልቅ እነዚህን ቀልዳቀልዶች ሁሉ እንደሌሉ ህዝቡ እንዲያውቅ ቁርጡን ተናግሮ ብቸኛ ‹‹ሀቀኛ›› ተጫዋች ነኝ ያለው የኢሳያስ አፈወርቂ መንግስት ‹‹ለፖለቲካ ተጫዋችነት›› የቀረበ ነው ማለት ይቻላል፡፡
የኢሳያስ መንግስት ራሱ የሚያዘው ምርጫ ቦርድን ‹‹ነጻ ነው!››፣ ራሱ ያሰማራቸውን ካድሬዎች ታዛቢዎች ናቸው፣ መንቀሰቀቀስ የማይችሉትን ተቃዋሚዎች ተቀናቃኞች ናቸው፣ ስርዓቱ የመሰረተውንና በሱ ሳንባ የሚተነፍስ ሚዲያ ነጻ ሚዲያ ነው ብሎ የሌለ ‹‹ጨዋታን›› እንጫወት ብሎ ባለማሞኘቱ ከኢህአዴግን በአንጻራዊነት የተሻለ ያደርገዋል ባይ ነኝ፡፡
እንደ ሙጋቤ ያሉት አምባገነኖች ህግን በቀጥታ ከመጣስ ይልቅ ለእነሱ የሚመች የመጫወቻ ሜዳ ያበጃሉ፡፡ ለዚህም ሲባል የዚምባብዌ ህገ መንግስት በርከት ላለ ጊዜ ተሻሽሏል፡፡ ይህም በቀጥታ የጨዋታውን ህግ ከመጣስ ይልቅ የጨዋታውን ህግ የማስቀየር ጨዋታን ነው የሚጫወተው፡፡ ከዛ በኋላ ግን ላወጣው ህግ ሲገዛ ይታያል፡፡ ይህም ቢሆን ከኢህአዴግ የተሻለ ነው ባይ ነኝ፡፡
እነዚህ አምባገነኖች የገነኑባቸው አገራት ከኢትዮጵያው ሁኔታ ይሻላል በሚል እንጂ ትርጉሙን ያሟላሉ በማለት አይደለም፡፡ የዘሮ ድምር ፖለቲካ በአብዛኛው በተጫዋቾቹ ብቃትና ውሳኔ የሚወሰን ነው፡፡ በእርግጥ ዳኛ፣ ተመልካች፣ ታዛቢም በዜሮ ድምሩ ይቅርና በሌሎች የመዝናኛ ጨዋታዎችም አሸናፊና ተሸናፊን ይወስናሉ፡፡ ሆኖም ግን ተጫዋቾቹ ሚና በመጀመሪያ ደረጃ የሚቀመጥ ይሆናል፡፡ በፖለቲካው ዓለምም ተፎካካሪ በአንድም ሆነ በሌላው ተሳታፊ ተጽዕኖ አግባብ ያልሆነ ውጤት ሊያገኝ ይችላል፡፡
ነገር ግን መጀመሪያ አንደኛው ተጫዋች ሌላኛውን በህጋዊ ሰውነት የሚያይበት፣ እኩልና ተወዳዳሪው መሆኑን የሚያምንበት፣ ህግ ለመጠቀሚያ ሳይሆን ሁለቱን ለመዳኘት የሚውልበት፣ ተመልካቹ በተጫዋቾቹ ብቃት የሚደግፍና የሚመርጥበት፣ ዳኛውና ታዛቢው በገለልተኝነት የሚሰሩበት መድረክ መዘጋጀት አለበት፡፡ በዚህ ሁኔታ በሰዋዊ ስህተትም ሆነ በሌላ መንገድ ማጭበርበር ቢኖርም አንደኛው ተጫዋች ተነስቶ ዳኛ የሚሆንበት፣ ተቃናቃኙን የሚታዘብበት፣ ተመልካቹን አስገድዶ የራሱ የሚያደርግበት መሆን የለበትም፡፡ አሊያም ይህ ስህተት የሚዳኝበት ህጋዊ መሰረት ይኖራል፡፡
ይህ ካልሆነ ግን ልክ እነ ኢሳያስ እንኳን ‹‹እንደ ኢትዮጵያ ከሆነ በአመትም 10 ምርጫ ማድረግ እንችላለን›› እንደሚሉት የኢትዮጵያ አይነት የማሞኛ ምርጫ መሆኑ ነው፡፡ እንዲህ አይነት ‹‹ተጨፈኑ ላሞኛችሁ›› ደግሞ ‹‹ዜሮም ሆነ የሚሊዮን ድምር›› የሚያበቃ የ‹‹ጨዋታ›› ለዛ የለውም፡፡ በዚህ ረገድ ፖለቲካችን ከ‹‹ጨዋታ›› ይልቅ ‹‹መጫወቻ፣ መቀለጃ›› የሆነ ብልሹ ፖለቲካ ነው፡፡
የፖለቲካ ጨዋታ ዜሮም ይሁን ምን ተጫዋች፣ ተመልካች፣ ህግ፣ ተመልካች፣ ታዛቢና ሜዳ የሚኖረው በመሆኑ በእኛ አገር ራሳቸው ህግ አውጥተው፣ ራሳቸው ከሚጥሱት፣ እየተጫወቱ ተመልካችም፣ ዳኛም ታዛቢም ከመሆኑት ብቸኛ ተጫዋችነትን በገሃድ ባወጁት ‹‹ቅን አምባገነኖች›› አለ ቢባል ይቀላል፡፡ በትርጉሙ መሰረት ደግሞ ወጠምሻዎች ከሚመሩት ‹‹ስርዓት›› ይልቅ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በገነቡት አገራት ሊኖር የሚችል የ‹‹ፖለቲካ ጨዋታ›› ነው፡፡
ይህን ሁሉ ስናይ የኢትዮጵያ ፖለቲካ በብልሹነቱ ከምናነሳው የ‹‹ዜሮ ድምር›› ፖለቲካም ደረጃም አልደረሰም ማለት ነው፡፡ የሂዳን ስሌቱ እንዳለ ሆኖ ቢያንስ በዛ ‹‹ብልሹ ፖለቲካ››ም ውስጥ ተጫዋቾች፣ የሚከበር ህግ፣ ተመልካቾች፣ ዳኞች፣ ታዛቢዎች መኖር ይጠበቅባቸዋልና ነው፡፡
No comments:
Post a Comment