Friday 8 May 2015

መልዕክተ ሎንደን ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን

May 4, 2015
ከለንደን ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን አባላት
የኦርቶዶክስ ሃይማኖትን እና አማራን በጠላትነት በመፈረጅ አከርካሪውን ሰብረነዋል በማለት በእብሪት ሲለፍፉ የነበሩት የሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ (ወያኔ) ባለሥልጣናትና ደጋፊዎች በአሁኑ ወቅት ደግሞ የኦርቶዶክስ እምነት ተቆርቋሪና አሳቢ ነኝ በማለት በለንደን ደብረ ጽዮን ቤተ ክርስቲያን ላይ ከፋፋይ የጥፋት ዘመቻ በማካሄድ ላይ ይገኛሉ።
London Ethiopian Orthodox Church
ለንደን ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያንን
በቤተ ክርስቲያኗ ውስጥ የተፈጠረው ችግር ከመንስዔው በቤተ ክርስቲያኑ መተዳደሪያ ደንብና በሃገሪቱ የቻሪቲ ሕግ መሠረት ሕግና ሥርዓትን ጠብቆ መፈታት ሲችል የቤተ ክርስቲያኗ አባላትም ሆኑ ሕግና ደንብ አይገዛንም ያሉ ጥቂት ካህናት ሕዝብን ከድተው ለወያኔ ሹመኞች በባንዳነት አደሩ።
በለስ ቀናኝ ያለው ወያኔም ሕዝብን የከዱትን ባንዳዎች በመጠቀም ስደተኛው ሕዝብ በሃብቱና በጉልበቱ ገዝቶ ያቆመውን ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን በመውረስ የራሱና የደጋፊዎቹ ለማድረግ በሁሉም ዘርፍ እንቅስቃሴ ጀመረ።
በእነ አባይ ፀሐዬ ትዕዛዝና ቁጥጥር የሚንቀሳቀሱ ጳጳሳትን ወደ ውጪ በመላክ ቤተ ክርስቲያኗን ከነንብረቷ በቁጥጥር ሥር ለማዋል እንዲንቀሳቀሱ አደረገ።
አልበገሬዎቹ የቤተ ክርስቲያኑ አባላት ግን ለሁለት ዓመት በዓላማቸው ጸንተው በመታገል ጉዳዩን ለፍርድ ቤት በማቅረብ የመጀመሪያው ምዕራፍ የሆነውን ቤተ ክርስቲያኗን በእኩል የመጠቀም መብታቸው እንዲጠበቅላቸው አስፈረዱ።
በዚህ የተደናገጡት የወያኔ ሹማምንቶች የእንግሊዝን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሳኔ ባለመቀበል የተቃውሞ ሰልፍ በማድረግ የሚቀለበስ መስሏቸው የወያኔው ጳጳስ ሳይቀሩ ሰላማዊ ሰልፍ በመውጣት መሳቂያና መሳለቂያ ሆኑ።
በዚህም አላበቃም በሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ የሚመራው መንግሥት የሚቆጣጠረው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንም አስነዋሪውን ሰላማዊ ሰልፍ ግንባር ቀደም ዜና በማድረግ አቀረበው።
ይህም ወያኔ በለንደን ደብረ ጽዮን ቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ መግባቱን ለማመን ያዳግታቸው ለነበሩ አንዳንድ ግለሰቦች ተገቢ ማረጋገጫ ነበር።
የኢትዮጵያው ቴሌቪዥን ስለ ለንደን ደብረ ጽዮን ቤተ ክርስቲያን ያሰራጨውን ዜና የሚከተለውን ሊንክ በመጫን ይመልከቱ።
በቅጥፈትና በክህደት የቆሸሸው የሃሰት ቋቱ ወያኔ፤ ሃገር ያወቀውን፤ ፀሐይ የሞቀውን ጉዳይ ዓይኑን በጨው ታጥቦ
• የእንግሊዝ ከፍተኛው ፍርድ ቤት በቀረበለት ከእውነት የራቀ አቤቱታ ላይ ተመርኩዞ ፈረደ ይላል፤
• በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩትን የቤተ ክርስቲያኑን አባላት የተለየ ዓላማ የያዙ ጥቂት አባላት ናቸው ይላል፤
• ቀኖና ቤተ ክርስቲያን ተጣሰ፤ የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ፈረሰ ይላል፤ (እግዚአብሔር ያሳያችሁ ወያኔ የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተቆርቋሪ ሆኖ)
• ቤተ ክርስቲያኗ ከዓላማዋ በእጅጉ ለተለየ ተግባር ልትውል ነው ይላል፤ (ወያኔን የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ጉዳይ በእጅጉ አሳስቦት)
ውድ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታዮችና ወዳጆች። ለሃይማኖታቸው፤ ለቤተ ክርስቲያናቸውና ለመብታቸው ጸንተው የታገሉት የለንደን ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን አባላት ሃሰት የተጠናወተው ወያኔ እንደሚለው ሳይሆን እውነቱ ሌላ ስለሆነ አባላቱ በፍርድ ቤት ፍትሕ ካገኙ በኋላ ቤተ ክርስቲያናቸው ውስጥ በመግባት የሆሳዕና በዓልን ሲያከብሩ የሚያሳየውን ቪድዮ የሚከተለውን ሊንክ በመጫን ተመልከቱና ወያኔ የአጸያፊ ውሸትና ቅጥፈቱ ማሰራጫ ካደረገው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ካስተላለፈው ነጭ ፕሮፓጋንዳ ጋር በማነጻጸር እውነታውን ተረዱ። http://londondebretsion.org/
ከዚህም በማስከተል የሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ (TPLF) ሹማምንቶችና ወኪሎች የለንደን ደብረ ጽዮን ቤተ ክርስቲያን አባላትን ከድተው ለወያኔ በባንዳነት ያደሩ ጥቂት ካህናትን በመያዝ የሚነዙት የሃሰት ፕሮፓጋንዳ ፋይዳ ቢስ ስለሆነባቸው በአሁኑ ወቅት ደግሞ በወያኔ ወኪሎች የሚመሩ አብያተ ክርስቲያናትን በማስተባበር በለንደን ደብረ ጽዮን ቤተ ክርስቲያን አባላት ላይ እንዲዘምቱ ለማድረግ አስተባባሪ ግብረ ኃይል አቋቁመው በመንቀሳቀስ ላይ መሆናቸውን በየ አብያተ ክርስቲያኑ በሚያሰሙት አዋጅ ለማረጋገጥ ተችሏል።
ቀጥሎ የተመለከተውን ሊንክ በመጫን የወያኔውን ሹመኛ ሙሉ ቃል ያድምጡ።
ከዚህ በማስከተልም ሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ መራሹ መንግሥት የዲያስፖራውን ኢትዮጵያዊ ትግል ለማዳከም ወደ ውጪ ሀገራት የሚልካቸው ካድሬዎቹና ባለሥልጣናቱ ምንም ሳይፈይዱ ተዋርደው እየተመለሱ ስለተቸገረ በአሁኑ ወቅት የተያያዘው ደግሞ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ጳጳሳትንና የቤተ ክርስቲያን ሹማምንትን በማሰማራት በሃይማኖት ሽፋን እነሱ ያቃታቸውን ተግባር እንዲያከናውኑለት ማድረግ በመሆኑ በዚህ መሠረት በአሁኑ ወቅት አቡነ ገብረኤልና አቡነ ቀውጦዎስ የተባሉ ሁለት ጳጳሳት የወያኔ ባለሥልጣናትና ካድሬዎችን ሥራ ለማከናወን ለንደን ዩናትድ ኪንደም ገብተው ይገኛሉ።
St, Mary of London Deber Tsion latest
እንደ እግዚአብሔር ትዕዛዝና እንደ ክርስትና ሃይማኖት ቢሆን ኖሮ “የሚያስታርቁ ብፁአን ናቸው፤ የእግዚአብሔርም ልጅ ይባላሉና” (ማቴ፡ 5:9) ተብሎ እንደተገለፀው በክርስቲያኖች መካከል ችግር ሲፈጠር እነዚህ ሁለት ጳጳሳት ሰላምና እርቅን ለማምጣት በጸሎትና በልመና በአማላጅነትና በአስታራቂነት በደከሙና በጣሩ ነበር።
እነሱ ግን በፁእ የሚለውን ማዕረግ ከመያዝ ባለፈ ተግባር የለባቸውምና ለንደን ከገቡበት ጊዜ ጀምሮ ከዘረኛው የወያኔ አገዛዝ የተሰጣቸውን ተልዕኮ ለማሳካት ወደሚያመቿቸው የገብሬኤል እና የሥላሴ ቤተ ክርስቲያናት በመሄድ ከወያኔ ሹማምንቶች ጋር እጅና ጓንት በመሆን ሃይማኖትንና መንፈሳዊ አገልግሎትን በሽፋንነት በመጠቀም የሁለቱን ቤተ ክርስቲያናት አባላት በማስተባበር ላለፉት 24 ዓመታት ከማንኛቸውም የወያኔ ሥርዓት ተጽዕኖ ነጻ ሆና በኖረችው የለንደን ደብረ ጽዮን ቤተ ክርስቲያን እላይ የጥቃት ዘመቻ ከፍተው ይገኛሉ።
አቡነ ገብረኤልና አቡነ ቀውጦዎስ ለንደን ከሚኖሩ የወያኔ ካድሬዎችና የኤምባሲ ባለሥልጣናት ጋር በመሆን ካከናወኗቸው ወያኔያዊ ተግባራት ውስጥ፡
1ኛ) የእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን ህንጻ ተከራይተው ጳጳሳቱ በተገኙበት በሊቢያ በረሃ መስዋዕት ለሆኑት ኢትዮጵያኖች ጸሎተ ፍትሐት ይካሄዳልና ሃዘኑ የተሰማው ኢትዮጵያዊ ሁሉ ይገኝ በማለት የማታለያ ጥሪ አሰራጩ።
በወገኖቹ ላይ የተፈጸመው አረመናዊ ድርጊት ያሳዘነውና ያስቆጨው ኢትዮጵያዊ ሃዘኑን ለመግለጽ በቦታው ላይ ሲገኝ እነሱ ግን የሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ አምባሳደር እና ሌሎች የወያኔ ባለሥልጣናትን የክብር እንግዳ በማድረግ በግፍ የፈሰሰውን የወገኖቻችንን ደም ስደትን በኢትዮጵያ አንግሶ ወገኖቻችንን የአረመኔዎችና የባህር ሰለባ በማድረግ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን የአለም መዛበቻ ያደረገው የወያኔ አገዛዝ የፖለቲካ መጠቀሚያ መድረክ ሊያደርጉት ችለዋል።
በግፍ የፈሰሰው የኢትዮጵያውያንን ደም ጳጳሳቱ ከወያኔ ካድሬዎች ጋር በመሆን ለፖለቲካ ፍጆታ ካዋሉበት ሂደት የተወሰድ ምስል።
St, Mary of London Deber Tsion latest issueበዚህ ምስል ውስጥም ወያኔ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰዎችን በግፍ ሲገድልና ሲጨፈጭፍ፤ ሰብዓዊ መብታቸውን ገፎ በአረመኔነት ሲያስርና ሲገርፍ፤ ከዚህም አልፎ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በሳዑዲ አረቢያ ሲገደሉ፤ ሴቶች ሲደፈሩና እንደውሻ ሲሳደዱ አንድም ነገር እንዳልተደረገ በማስተባበልና በኢትዮጵያም ውስጥ ነጻነትና ዲሞክራሲ ሞልቶ ተትረፍርፏል እያለ ለንደን ላይ ተቀምጦ የሚወሸክተው ሆድ አደሩ አምባሳደር ብርሃኑ ከበደ ለኢትዮጵያውያን ያዘነ መስሎ ከጳጳሳቱ ጎን በክብር ተቀምጦ ታዩታላችሁ።
2ኛ) አቡነ ገብረኤልና አቡነ ቀውጦዎስ በለንደን የሚገኙ በሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ወኪሎችና ካድሬዎችች የሚመሩ አብያተ ክርስቲያናትን በማስተባበር በስደት ሃገር የመሠረትናትን ቤተ ከርስቲያናችንን ለወያኔ አሳልፈን አንሰጥም በማለት በመታገል ላይ የሚገኙትን የለንደን ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያንን አባላት ለማጥቃት የሚያስችል ገንዘብ ለማሰባሰብ ከ02/05/15-እስከ 05/05/15 የሚዘልቅ የፈንድ ሬዚን መርሃ ግብር በማካሄድ ላይ ይገኛሉ።
3ኛ) እነዚሁ ሁለት ጳጳሳት ከዚህ ሁሉ በማለፍ የክርስቶስን መስቀል ተሸክመው የክርስቶስ መንገድ ከሆነው የሃይማኖቱ ሕግ የሰላም፤ የፍቅር፤ የእርቅና የይቅር ባይነት መንገድ ጨርሰው በመውጣት ውግዘትን ለፖለቲካ መሣሪያነት ለመጠቀም በመጣር ላይ ይገኛሉ።
ስለ ውግዘት ከተነሳ እነሱ ራሳቸው በስደት ላይ በሚገኘው ሕጋዊው ሲኖዶስና ቀደምት አባቶች እጅግ በጠነከረና በከረረ ውግዘት መወገዛቸውን ሁሉ ክርስቲያን የሚያውቀው ጉዳይ ነው። አሁን ላይ ግን ራሳቸው እንዳልተወገዙና እነሱም መልሰው እንዳላወገዙ ሁሉ የቀጥታም ሆነ የተዘዋዋሪ የሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ አገዛዝ ተጽዕኖን አንቀበልም ያሉ የለንደን ደብረ ጽዮን ቅድስ ማርያም ቤተ ክርስቲያን አባላትን እኛ የምንለውን ካልተከተላችሁና በወያኔ ጫና ሥር ካልዋላችሁ እናወግዛችኋለን በማለት ውግዘትን የጎሰኝነት ፖለቲካ መጠቀሚያ ለማድረግ በመጣር ላይ ይገኛሉ። ይህ እግዚኦ የሚያሰኝ ነገር አይደለም?
ይህ ሁሉ ግርግር እውነትን ከቦታዋ ባያነቃንቃትም ሆኖም ግን ጳጳሳቱ በዚህ ክርስቲያናዊ ያልሆነ ድርጊታቸው ተዋርደውና ተንቋሸው ሃይማኖታችንም ሆነ ቤተ ክርስቲያናችን መሣለቂያ ከምትሆን የማይሳነው እግዚአብሔር ልቦና ሰጥቶአቸው ከዚህ ተግባራቸው ይታቀቡ ዘንድ ልንጸልይላቸው ይገባል።
ወስብሓት ለእግዚአብሔር!!
ከለንደን ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን አባላት።

No comments:

Post a Comment