Friday 8 May 2015

ግብጾች ለኢትዮጵያዉይን ሲቆሙ ሕወሃቶችስ ? – ናኦሚን በጋሻው

የዙሉ አክራሪዎች በኢትዮጵያዉያን እና ሌሎች የአፍሪካ ዜጎችን ላይ ኢሰብዓዊ ጥቃት በሚፈጽሙበት ጊዜ፣ እንደ ናይጄሪያ ያሉ አገሮች በዙማ መንግስት ላይ ጠንካራ አቋም ወሰዱ። ዙማ ተጽኖ ሲበረታባቸው፣ አስቸኳይ እርምጃዎች ለመዉሰድና ነገሮችን ለማረጋጋት ተገደዱ። ከነናይጄሪያ በደረሰው ግፊትና ጫና በደቡብ አፍሪካ ያለው ሁኔታ ለጊዜውም ቢሆን መረጋጋት ታየበት። በዚሁ ሁሉ ግን ሕወሃት/ኢሕአዴጎች የተከሰተዉን ቀውስ አሳንሰው በማቅረብ፣ ለኢትዮጵያዉያን ጥብቅና የቆሙ ሳይሆን፣ የዙማ ቃላ አቀባይ ነበር የመሰሉት።
ብዙም አልቆየም፣ እሁድ ሚያዚያ 11 ቀን በሊቢያ ወገኖቻችን አንገታቸው ተቀላ። ኢትዮጵያ በትልቅ ሐዘን ተመታች። የዚያኑ ቀን ቢቢስ፣ አል ጃዚራ፣ ሲ.ኤን.ኤን የመሳሰሉ ታላላቅ ሜዲያዎች ኢትዮጵያዉያን ክርስቲያኖች እንደተገደሉ መዘገብ ጀመሩ። ሰኞ ሚያዚያ 12 ቀን የአሜሪካ መንግስት በይፋ ለኢትዮጵያ ህዝብ እና ለሕወሃት/ኢሕአዴግ የሐዘን መግለጫ አቀረበ። ሆኖም ሕወሃት/ኢሕአዴግ ዜናውን አሳንሶ በማቅረብ፣ እንደ ሶስተኛ ተራ ዜና «በሊቢያ ስደተኞች በአይሰስ ተገደሉ። አንዳንድ ሜዲያዎች ኢትዮጵያዉይን ናቸው ይላሉ። ግን ኢትዮጵያዊ ስለመሆናቸው ምንም አይነት ማረጋገጫ የለም» ሲል ኢትዮጱያዉያን መሆናቸውን በኢቢሲ/ኢቲቪ ካደ። የሚያስብና የሚጨነቅ መንግስት እንደሌለ በመገለጽ ሕዝቡ በራሱ አነሳሽነት ተቃዉሞዉን እና ሐዘኑን፣ ሀሙስ ሚያዚያ 15 ቀን እንዲገልጽ የሐዘን እና የተቃዉሞ ቀን በሚል፣ በሶሻል ሜዲያ ዘመቻዎች ተከፈቱ።ሰልፎችና የሥራ ማቆም አድማዎች ተጠሩ።
በነጋታው ማክሰኞ ሚያዚያ 13 ቀን ከሶሻል ሜዲያ ፎቶዎችን በማየት ልጆቻቸው እንደሞቱ ያረጋገጡ ወላጆች፣ በጨርቆስ አካባቢ ድንኳን ጣሉ። ያኔ በጨርቆስ ያሉ ሰላዮች መረጃዎች ለጌቶቻቸው አቀረቡ። ብዙም አልቆየም ሰበር ዜና ብሎ፣ ኢቢሲ/ኢቲቪ የተገደሉት ኢትዮጵያዉይን መሆናቸውን ፣ ፓርላማው በነጋታው ተሰብስቦ የሶስት ቀን የሐዘን ቀን እንደሚያወጅ ገለጸ። የዚያኑ ቀን በጨርቆስና ሌሎች በርካታ ቦታዎች፣ ሐሙስን ሳይጠበቁ፣ የተለያዩ የተቃዉሞና የሐዘን ሰልፎች ተደረጉ።
ሕወሃት/ኢሕአዴግ የሐሙስን ሰልፍ ለማጨናገፍ ሲል፣ ቀድሞ፣ ረእቡ ሚያዚያ 14 ቀን ሰልፍ ጠራ። በሰልፉ ህዝቡ ሐዘኑን ገለጸ። ተቃዉሞዉን አሰማ። ሆኖም ዜጎች በአደባባይ በግፍና በጭካኔ ተደበደቡ። ከአንድ ሺህ በላይ ታሰሩ። በሰልፉ ወቅት «እኛን ከምትደበድብ፣ አይሰስን ደብድቡ» ነበር ያላቸው። ሆኖ ሕወአት/ኢሕአዴጎቭ አይሰስ ላይ ሳይሆን ጡንቻዉን ሰላማዊ ዜጎች ላይ አሳዩ። ሴቶች ሁሉ ሳይቀሩ ተደበደቡ።
ሕወሃት/ኢሕአደግ አገር ቤት ያሉትን በማሰርና በመደብደብ ተጠምዶ ባለበት ሁኔታ፣ በሊቢያ ቁጥራቸው እጅግ በጣም በርካታ የሆኑ ኢትዮጵያዉያን ችግር ላይ እንዳሉ በኢሳትና በአሜሪካን ድምጽ ራዲዮ መስማት ጀመርን። ሕወሃት/ኢሕአዴግ፣ ግብጽ ባሉት አምባሳደሩ በኩል «በሊቢያ በአይሰስ እጅ ዉስጥ የገቡ ኢትዮጵያዉይስን የሉም። በሊቢያ ያለውም ሁኔታ በአንጻራዊነት ሰላም ነው» በሚል ለጉዳዩ ክብደት ሳይሰጡበት ቀረ። ሕወሃት/ኢሕአዴግ ፣ ከወዲሁ የዉሸት የሆነው ምርጫ ላይ እና አገር ቤት ያሉ ሰላማዊ ዜጎችን ማሳደዱ ላይ ጊዜና ጉልበት ማጥፋቱን ቀጠለ።
በዚህ መሐል ከሁለት ሳምንታት በኋላ ፣ የግብጽ ወታደሮች ወደ ሰላሳ የሚሆኑ ኢትዮጵያዉይንን ከአይሰስ እጅ ነጻ እንዳወጡ ተዘገበ። ኢትዮጵያዉያኑ ከሊቢያ ወደ ግብጽ ሲመጡም ፕሬዘዳንት አሲሲን ጨምሮ በርካታ የግብጽ ባለስልጣናት አቀባበል አደረጉላቸው። ኢትዮጵያውያኑ፣ መንግስታቸው ረስቷቸው፣ በግብጽ መንግስት እርዳታ ከሞት አመለጡ።
የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶር ቴድሮስ አዳኖም ኢትዮጵያዉይን ከሊቢያ ወደ ኢትዮጵያ እየመጡ እንደሆነ በመናገር መንግስታቸው ጥረቱን እንደሚቀጥል በፌስ ቡካቸው ገልጸዋል። ሆኖም ሮይተርስ ፣ ኢትዮጵያዊያንን የማስወጣቱ ሥራ 100% በግብጽ እንደተሰራ ነው ያሳወቀው። በዘገባው ምንም አይነት የኢትዮጱያ መንግስት አስተዋጾ እንዳለ የገለጸበት ሁኔታ የለም። ኢትዮጵያዊያንን ይዞ የመጣውም አይሮፕላን የኢትዮጵያ አየር መንገድ አይሮፕላን ሲሆን፣ ኢትዮጵያዉያኑንም ለመቀበል ዶር ቴዶርስም ሆነ ሌሎች የኢትዮጵያ ከፍተኛ ባልስልጣን አልተገኙም።
እዉነቱ እንደዚያ ሆኖ፣ ሕወሃት/ኢሕአዴግ ፣ በማጭበርበር ፖለቲካ የተካነ እንደመሆኑ፣ ጅብ ከሄደ ዉሻ ጮኸ እንደሚባለው፣ «ዜጎቼን ከሊቢያ አወጣሁ» የሚል የፕሮፖጋንዳ ዘመቻ ሊያደርግ እንደሚችልም ይገመታል።
ኢትዮጵያዉያኑ ከቤንጋዚ አካባቢ መምጣታቸው ለኢትዮጵያዉያን ሁሉ ትልቅ አስደሳች ዜናና የጸሎታችን መልስ ቢሆንም፣ አሁን በተለይም በትሪፖሊና በሚስራታ አካባቢ እጅግ በጣም በርካታ ኢትዮጵያዉያን አሉ።ትሪፖሊና ቤንጋዚን የሚቆጣጠረው ኃይል፣ ቤንጋዚን እንደሚቆጣጠረው ኃይል ከግብጽ ጋር ወዳጅነት ያለው ኃይል አይደለም። ይህ ዜና አስደሳች ቢሆንም ከፊታችን ገና ብዙ ይጠብቀናል። ላመለጡ ወገኖቻችን ጌታን እያመሰገንን፣ ገና አደጋ ላይ ላሉት ጸሎታችንን አናቋርጥ። እግዚአብሄር ጸሎትን ይሰማል። ግብጾች በዚህ መልኩ ይረዱናል ብሎ ማን ጠበቀ ?
ኢትዮጵያዉይን ግብጾችና ናይጄሪያኖች ሁልግዜ ይቆሙልናል ብለን መጠበቅ የለበንም። አሁን ስልጣን ላይ ያለው አገዛዝ ህዝብን የሚያሸብር ሳይሆን፣ ሕዝብን የሚያገለግልና ለሕዝብ የቆመ እንዲሆን ለማድረግ ግፊታችንን ከመቼዉም ጊዘ እየበለጠ ፣ማጠናከር አለብን። በተቃዋሚ ጎራ ያለነውም ከስልጣን እና መርዛማ ከሆነው የድርጅት ፍቅር ተላቀን፣ በአገራችን ለዉጥ እንዲመጣ መሰባሰብ አለብን። አሁን ካልተነሳን መቼ ? እኛ ካልተነሳን ማን ?
(በነገራችን ላይ ህወሃት/ኢሕአዴግ የተወሰኑትን ከግብጽ ወደ አዲስ አበባ እንዲመጡ አድርጓል። ለዚህ ምስጋና ካስፈለጋቸው መስጠት ይቻላል)11193405_818245314927071_2869514135485100463_n

No comments:

Post a Comment