Tuesday 5 May 2015

ወላይታ ላይ ሰማያዊ ፓርቲ ቅስቀሳ እንዳያደርግ ተከለከለ

በነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር
• ‹‹ወላይታ ውስጥ መንግስት የለም›› አቶ ስለሽ ፈይሳ
blue partyበወላይታ ዞን ሰማያዊ ፓርቲ ቅስቀሳ እንዳያደርግ እንደተከለከለ የሰማያዊ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበርና የምርጫ ጉዳይ ኃላፊው አቶ ስለሽ ፈይሳ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ ወላይታ ዞን ሶዶ ከተማ በመኪና ላይ ቅስቀሳ እያደረጉ እንደነበር የገለጹት አቶ ስለሽ ሆኖም የገዥው ፓርቲ ካድሬዎች በሞተር ብስክሌት በመከታተል የመኪናውን ጎማ በሚስማር በማስተንፈስ እንዲሁም የምርጫ ዘመቻ አባላቱን በመደብደብ ቅስቀሳውን ማስተጓጎላቸውን ገልጸዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር የሰማያዊ ፓርቲን የቅስቀሳ ወረቀት የሚቀበለውን ህዝብ እየተከታተሉ እንደሚያስፈራሩና እንደሚደባደቡ አቶ ስለሽ ገልጸዋል፡፡ በተመሳሳይ ጌትነት በሱፍቃድ የተባሉ ዕጩና ሌላ የሰማያዊ ፓርቲ አባልን ሞባይሎች በመቀማት ከፍተኛ ድብደባ እንደፈፀሙባቸው ተገልጾአል፡፡
የገዥው ፓርቲ ካድሬዎች ስም፣ የሚጠቀሙበትን መኪና ታርጋና ሌሎችም የፈፀሙትን ድርጊት በዝርዝር በማቅረብ ለፖሊስ ቢያቀርቡም ፖሊስ ‹‹ይህ ማስረጃ ሊሆን አይችልም›› በሚል ለተፈፀመባቸው በደል ምንም አይነት ትኩረት እንዳልሰጠው አቶ ስለሽ ገልጸዋል፡፡ ፖሊስ ለጉዳዩ ትኩረት ባለመስጠቱ ለዞኑ የምርጫ ኃላፊ ቢያመለክቱም፣ የምርጫ ኃላፊው ‹‹ይህንማ ሊያደርጉ አይችሉም፡፡ ከዞኑ የኢህአዴግ የድርጅት ጉዳይ ጋር እንነጋገርበታለን›› እንዳሉ ገልጸው ምርጫ ቦርድም ከኢህአዴግ የድርጅት ጉዳይ ጋር ተነጋግሮ ነው ውሳኔ የሚሰጠው ብለዋል፡፡ ለሚፈፀምባቸው በደል መፍትሄ የሚሰጥ አካል እንደሌለ የገለጹት አቶ ስለሽ ‹‹ወላይታ ውስጥ መንግስት የለም›› ሲሉም በፓርቲው ላይ ስለሚደርሰው በደል ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡

No comments:

Post a Comment